ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ዕለታት ስያሜዎች

ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ባለው አንድ ሳምንት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሰባቱን ዕለታት የተለያዩ ምሥጢራዊ ስያሜዎችን ሰጥታ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ታከናውንባቸዋለች፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ቤዛ አድርጎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ተቀብሮ፣ ሙስና መቃብር ሳይወስነው መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሞቱ ሞትን ሽሮ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አውጇልና ኦርቶዶክሳውያን በልዩ ድምቀት የሳምንቱን ዕለታት እናከብራለን፡፡ በዚህም መሠረት የሰባቱ ዕለታት ስያሜዎችን እንደሚከተለው እናቀርባቸዋለን፡፡

ሰኞ

ሰኞ – ማዕዶት ትባላለች፡፡ ማዕዶት ማለት መሻገር፣ ማለፍ ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ፋሲካችን ክርስቶስ  ነፍሳትን ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሐሳር ወደ ክብር፣ ከሲኦል ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ናት፡፡ (ዮሐ. ፲፱፥፲፰፤ ሮሜ. ፭፥፲-፲፯)፡፡

ማክሰኞ 

ይህች ዕለት ለሐዋርያው ለቅዱስ ቶማስ መታሰቢያ ትሆን ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን “ቶማስ” ተብላ ሰይማዋለች፡፡ ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን፤ በቀኖት የተቸነከረው እጁንና እግሩን ካላየሁ አላምንም በማለቱ ክርስቶስም “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን” ብሎታል። ቶማስም ጣቶቹን አስገብቶ በዳሰሰው ጊዜ ስለተቃጠለ “ጌታዬ አምላኬ” ብሎ አመነ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም “ስለ አየኸኝ አመንህን? ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አለው (ዮሐ ፳፥፳፯-፳፱)፤ ቶማስም የጌታን ፍቅር ተገንዝቦ ትንሣኤውን ስላመነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቶማስ ብላ ትታሰባለታች።

ረቡዕ 

አልአዛር ተብላ ትታሰባለች፡፡ የማርታ እና የማርያም ወንድም የሆነው አልአዛር ከሞተና ከተቀበረ ከአራት ቀናት በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቃብር ጠርቶ አስነሥቶታል፡፡ ጌታችን በሥልጣኑ አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱንና በአምላክነቱ ያደረገውን ተአምራት የተመለከቱ ሁሉ በጌታችን አመኑ፡፡ በዚህም መሠረት ረቡዕ “አልዓዛር” ተብላ ትታሰባለች (ዮሐ. ፲፩፥፴፰-፵፮)፡፡ 

ኀሙስ 

ይህቺ ዕለት የአዳም ሐሙስ ተብላ ትጠራለች፡፡ ቃል የተገባለት የአዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ሆና ተሰይማለች፡፡ (ሉቃ. ፳፬፥፳፭-፵፱)፡፡ይህም አዳም እና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፈው በመገኘታቸውና የሞት ሞት ተፈርዶባቸው ከገነት ተባረው ነበር፡፡ ነገር ግን የአምላካቸውን ትእዛዝ ተላልፈዋልና በፍጹም ፀፀት እያነቡ ንስሓ በመግባታቸው ይቅርታን የሚቀበል አምላክ “ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፤ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ተወለደ፤ ለሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከኃጢአት በስተቀር በምድር ላይ ተመላልሶ በስቀል ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ሞትን በሞቱ ሽሮ ተነሥቶ በትንሣኤው ትንሣኤን አውጆ አዳምና ልጆቹን ወደ ቀደመ ክብራቸው መልሷቸዋልና ዕለቲቱ “የአዳም ሐሙስ” ተብላለች፡፡

 ዐርብ

ስድስተኛዋ ቀን ዐርብ “ቤተ ክርስቲያን” ተብላ ተሰይማለች፡፡ በክርስቶስ ደም ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ናት፡፡ ይህም ሁሉም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመባት ዕለት በመሆኗ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ያደረገውን ተአምራት በመስቀሉ ድኅነትን እንዳሳየ፤ በቀራንዮ የሕንፃዋ መሠረት እንደተተከለላትና ሥጋ መለኮት እንደተቆረሰላት፤ ልጆቿን ከማሕፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ ገቦ እንደፈሰሰላት ተገልጾባታል፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት

ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ስያሜ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጕልበታቸው ላገለገሉት፤ በስቅለቱ ጊዜ እስከ ቀራንዮ ድረስ በልቅሶና በዋይታ ለተከተሉት፤ (ሉቃ. ፳፫፥፳፯) በዕለተ ትንሣኤው ደግሞ ሽቱና አበባ ይዘው ወደ መቃብር የገሰገሱትን፤ ከሁሉም ቀድሞ ጌታችን በዕለተ ሰንበት ተነሥቶ ለተገለጸላቸው ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት፣ ሰሎሜንም መታሰቢያ ለማድረግ ነው፡፡”ከሳምንቱ በመጀመሪያይቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ” እንዲል፡፡ ((ማቴ. ፳፭፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፬ ፥ ፩)፡፡

እሑድ

ዳግም ትንሣኤ፡፡ ከዋናው ትንሣኤ ሳምንት በኋላ የምትመጣዋ ዕለተ እሑድ “ዳግም ትንሣኤ” ተብላ ትዘከራለች፡፡ ጌታችን በትንሣኤው ዕለት ማታ በዝግ በር ገብቶ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ተገኝቶ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን! በማለት ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ነገሩት፡፡ እርሱ ግን ከማመን ይልቅ በኋላ እናንተ ‘አየን’ ብላችሁ ልትመሰክሩ፤ ልታስተምሩ፤ እኔ ግን ‘ሰምቼአለሁብዬ ልመሰክር፤ ላስተምር? አይሆንም፡፡ እኔም ካላየሁ አላምንም አለ፡፡

ስለዚህም የሰውን ሁሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው የወዳጆቹን የልብ ዐሳብ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት ሐዋርያት በተዘጋ ቤት በአንድነት ተሰባስበው እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ “ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!” በማለት በመካከላቸው ቆመ፡፡ ቶማስንም “ያመንህ እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን፤ እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ፤” ብሎ አሳየው፡፡ እርሱም ጣቶቹን ወደ ተወጋው ጎኑ አስገባ፤ ጣቶቹም ኩምትር ብለው ተቃጠሉ፡፡ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደ ፍላጎቱ በመረዳቱ “ጌታዬ፣ አምላኬ” ብሎ መስክሮ የክርስቶስን ትንሣኤ አመነ፡፡ በዚህም ምክንያት   የሳምንቱ ዕለተ ሰንበት የትንሣኤው ምሥጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመሆኑ “ዳግም ትንሣኤ” ተብሎ ይጠራል፤ ይከበራል፡፡ (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡

ብርሃነ ትንሣኤውን የገለጸልን አምላካችን ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *