“እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን” (ዮሐ. ፳፥፳፮-፳፱)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ሞትን ሽሮ በትንሣኤው ትንሣኤአችንን ካወጀልን በኋላ በሳምንቱ ሐዋርያት በዝግ ቤት ውስጥ ሆነው ሳሉ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል እንደ ተነሣ እንዲሁ በር ክፍቱልኝ ሳይል በዝግ ቤት ውስጥ ሳሉ በመካከላቸው ተገኝቷል፡፡ ይህንንም ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያችን “ዳግም ትንሣኤ” በማለት በድምቀት ታከብረዋለች፡፡ ዳግም ትንሣኤ የተባለበት ምክንያትም በአከባበር፥ በሥርዓት የመጀመሪያውን ትንሣኤ ስለሚመስል ነው፡፡ የትንሣኤ ዕለት የሚባለው ቃለ እግዚአብሔር ሳይለወጥ፤ በሙሉ በዚህ ቀን ይደገማል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ዕለት ማታ በዝግ በር ገብቶ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ተገኝቶ “ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!” በማለት ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት “ጌታችን አየነው” በማለት በደስታ ሲነግሩት እርሱ ግን “የችካሩን ምልክት ካላየሁ፣ ጣቴንም ወደ ተቸነከረበት ካልጨመርሁ፣ እጄንም ወደ ጎኑ ካላስገባሁ አላምንም” አላቸው፡፡ ቶማስ ትንሣኤ ሙታንን ከማያምኑ ከሰዱቃውያን ወገን በመሆኑ ለጥርጥር እንደዳረገው ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡  “በኋላ እናንተ ‘አየን’ ብላችሁ ልትመሰክሩ፤ ልታስተምሩ፤ እኔ ግን ‘ሰምቼአለሁ’ ብዬ  

ልመሰክር፤ ላስተምር? አይሆንም፡፡ እኔም ካላየሁ አላምንም” አለ፡፡ (ዮሐ. ፳፥፳፬-፳፮)

ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የሐዋርያው ቶማስን ጥርጥር ለማስወገድ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት (ሐዋርያው ቶማስ ባለበት) በተዘጋ ቤት በአንድነት ተሰባስበው እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ “ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!”

በማለት በመካከላቸው ቆመ፡፡ ቶማስንም “ጣትህን ወዲህ አምጣ እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣ ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን” ብሎ አሳየው፡፡ ቶማስም ጣቱን ወደ ተቸነከሩት እጆቹ፣ እጁንም ወደ ተወጋው ጎኑ ሲጨምር እርር ኩምትር አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ምልክቱን በማየቱ፣ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደ ፍላጎቱ በመረዳቱ “ጌታዬ አምላኬም” ብሎ አመነ፡፡ በዚህም ምክንያት የሳምንቱ ዕለተ ሰንበት የትንሣኤው ምሥጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመሆኑ “ዳግም ትንሣኤ” ተብሎ ይጠራል፡፡ (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡  

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *