ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? (ክፍል ሁለት)
በመ/ር ኃ/ሚካኤል ብርሃኑ
ቤተ ክርስቲያን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እግዚአብሔርን በማመን የጸኑ በሥራቸው የተመሠከረላቸው የእውነተኛ አማኞች ማኅበር ናት፡፡ በምድር ላይ ከተመሠረቱ ማኅበራት ሁሉ ይልቅ አምሳያ የሌላት በእግዚአብሔር ፈቃድ ለእግዚአብሔር ዓላማ በእግዚአብሔር የተመረጡና የተጠሩ ሰዎች ጉባኤ በመሆኗ ከሁሉ የተለየች ተብላለች፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እንደጻፈው ”እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህንም ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው” (ሮሜ 8÷30) ይላልና፡፡
በእግዚአብሔር የተጠራ ሕዝብ ማለት የተጠራበት ዓላማ ከእርሱ ጋር አንድነት እንዲኖረው ነው፡፡ እግዚአብሔር አብሯት ስላለና አንድነቷ ከእግዚአብሔር ጋር ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም የሰዎች ስብሰባ የተለየች ክብርትና ቅድስት ናት፡፡
ቤተ ክርስቲያንን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ በሐዲስ ኪዳን የሚገኙ ምእመናን በምድር ላይ የተሰበሰቡባት ማኅበር (ቤተ ክርስቲያን) ሕዝበ እግዚአብሔር እንደ ደመና የከበቧት ሩጫቸውን በድል ያጠናቀቁ ምስክሮች እንዳሏት ያስገነዝባል (ዕብ 12÷1) ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምርጥ እቃ ብሎ የጠራው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በበሉይ ኪዳን የነበሩ ከሩቅ ሆነው በእምነት መነጽርነት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልክተውና ተስፋ አድርገው ተጋድሏቸውን በድል አጠናቀው ዐረፍተ ዘመን ገቷአቸው የሞቱት አባቶች ናቸው፡፡
ከቀደሙት አባቶች መካከል አንዱ ስለሆነው ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገለጸበት በዕብራውያን መልእክቱ “ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ (ዕብ 11 ፥ 25) በማለት ቤተ ክርስቲያንን የብዙ አባቶች ምስክርነት እንደከበባት ያስረዳል፡፡
በሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ስንል ከነገድና ከቋንቋ፣ ከአሕዛብና ከአይሁድ፣ በክርስቶስ ደም የተዋጁትንና በመካከላቸው የነበረው የጠብ ግድግዳ በመስቀሉ ደም ፈርሶ አንድ ሕዝብ የሆኑትን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ በዚህ መሠረት ዳግም ከመንፈስ ቅዱስ የተወለዱ፣ ለእግዚአብሔር አምልኮ የተለዩ የሐዲስ ኪዳን ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ተብለው እንደሚጠሩ፤እግዚአብሔርን ለማምለክና ለማመስገን የተጠሩ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደሆኑ እንረዳለን፡፡
በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ማለት በሥጋዊ ሕይወት ማለትም በአካለ ሥጋ ሰውነታቸውን የክርስቶስ ማደሪያ ያደረጉና በምድር ያሉትን፣ በሥጋቸው እግዚአብሔርን አክብረው በሥጋዊ ሞት ከምድር የተለዩትንና በአካለ ነፍስ ከክርስቶስ ጋር ያሉትን፣ ከመልካም ሥራቸው የተነሣ ሞትን እንዳያዩ ወደ ብሔረ ሕያዋን በሥጋ ያረጉትን ቅዱሳን በሙሉ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሲባል ክርስቲያን ምእመናንን፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርንና ሕንጻ ቤተ መቅደስን ያጠቃልላል፡፡
ቤተ ክርስቲያን የምትታወቅባቸው አራት ባሕርያት አሏት፡፡ እነሱም፦ አንዲት፣ (ሮሜ.12፡4) ቅድስት፣ (ኤፌ5፡25) ኩላዊት፣(ማር 16፡15) ሐዋርያዊት (ማቴ28፡19) ናት፡፡ አነዋወሯንም በሁለት መልኩ ማየት ያስፈልጋል፡፡ እሷም በዚህ ዓለም በገድል ላይ ያለችና ዓለሙንና ፈቃዱን ድል አድርጋ የድል አክሊል ተቀዳጅታ በዕረፍት ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህም የቅዱሳን ጻድቃን ሰማእታት እና የምድራውያን ደናግል መነኮሳት፣ ካህናት ዲያቆናት፣ መሃይምናንና መሃይምናት አንድነት ማለት ነው፡፡
በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ገና በዚህ ዓለም በተጋድሎ ላይ ያሉት የምእመናንና ዓለሙንና ፈቃዱን ድል አድርገው በክብር ላይ ክብር ተጨምሮላቸው በሰማይ ያሉት የቅዱሳን አንድነት ናት፡፡ ለዚህም ጌታችን በወንጌል “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ“ (ዮሐ16 ፥ 33) በማለት በዓለም ያሉ ምእመናን በመከራ ውስጥ እንደሚያልፉ ተናግሯል፡፡
ምእመናን በዓለም እየኖሩ ሰማያዊ ዜግነት ያላቸው ናቸውና ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ነገሮች ኃላፊ ጠፊ መሆናቸውን ስለሚያምኑ ናፍቆታቸው ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌም ነው፡፡ ዓለም ደግሞ የራሷ ባልሆኑት ለእግዚአብሔር በተለዩት ምእመናን ላይ መከራ ታደርስባቸዋለች፡፡ ምክንያቱም ዓለም የራሱ የሆኑትን በምድራዊ አሳብና በሥጋዊ ፈቃድ ብቻ የሚኖሩትን ትወዳለች፣ ትሾማቸዋለች፣ ትሸልማቸዋለች የራሷ ያልሆኑትን ማለትም ዓለምንና ፈቃዷን ንቀው በመንፈሳዊ ሕይወት የሚመላለሱትን ስለምትጠላቸው መከራ ታደርስባቸዋለች፡፡
ጌታችን እንዳስተማረን “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደጠላኝ ዕወቁ ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል፤ ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ እኔን አሳደውኝ እንደሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዷችኋል፤ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ፤ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ስለ ስሜ ያደርጉባችኋል” (ዮሐ 15 ፥ 20) ብሎናል፡፡
ስለዚህ ዓለም በተደጋጋሚ ቀስቷን በቤተክርስቲያን ላይ ብትወረውርም ጌታችን ቀድሞ ስላስተማረን ምንም አይደንቀንም፡፡ ይልቁንም ከዓለም የሚሰነዘሩባትን ሰይፎችና መከራዎች ሁሉ በድል አጠናቃ፣ የድል አክሊል ለመቀበል ሁል ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በተጋድሎ ላይ ናት፡፡ በውስጧም ሐሰተኞችና ክፉዎች ተደባልቀው ይኖሩባታል፡፡ ይህም ማለት ይሁዳ ከጌታ ደቀ መዛሙርት ከሐዋርያት ጋር እንደነበረ፣ ከሐዋርያት ጋርም ቢጽ ሐሳውያን እንደነበሩ፣ በየዘመናቱ ቤተ ክርስቲያን ከምታፈራቸው ከሊቃውንቱ ጋር መናፍቃን እንደ ነበሩ ማለት ነው፡፡ ይህም ይሆን ዘንድ ግድ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጸው ‹‹ በእናንተ ዘንድ የተፈተኑት እንዲገለጡ በመካከላችሁ ደግሞ ኑፋቄ ሊኖር ግድ ነውና›› (1ኛ ቆሮ 11፥19) ይላልና፡፡
ወደዚህች አንድነት የሚገቡትም ምእመናን በዚህ ዓለም እያሉ ሃይማኖታቸውን በመጠበቅና መልካም ሥራን በመሥራት የኖሩ ብቻ ናቸው፡፡ “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፤ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም” (2ኛ ጢሞ 4፥7) እንዲል፡፡
ባለ ራእዩ ቅዱስ ዮሐንስም በፍጥሞ ደሴት ተግዞ ሳለ በራእይ ቅዱስ ጳውሎስ የመሰከረላትን ሰማያዊቷን ጉባኤ ተመልክቷታል፡፡ ይህንንም ሲገልጥ ‹‹አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ባሕርም ወደፊት የለም ቅድስቲቱም ከተማ አዲስቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ›› (ራዕ 21፥1) በማለት የዚህን ዓለም ፈተና በድል አጠናቅቃ በክብር የምትኖር መሆኗን መስክሯል፡፡
በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ስንል በዓለመ መላእክት ያሉ የሰማያውያን ቅዱሳን መላእክት፣ ጻድቃን ሰማእታት፣ በብሔረ ሕያዋን የሚኖሩ ቅዱሳን፣ በዚህ ዓለም ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት ኤጲስ ቆጶሳት መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ መሃይምናትና መሃይምናን አንድነት ስትሆን እነዚህም የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ሰውና መላእክት በአንድነት የሚዘምሩባት፣ሰውና እግዚአብሔርን የምታገናኝ በምድር ያለች ሕንጻ ቤተ መቅደስ በሰማይም ያለች የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡(ራእ.11÷19)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!