በእንተ ጾም፣ ጌታችን የጾመበት ምክንያት

በገብረ እግዚአብሔር ዘይኵኖ

 ለቸርነቱ ወሰን የሌለው፣ በኃይለ ረድኤቱ  ያልተለየን ምስጉንና ክቡር የኾነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቸር አባቱ ከእግዚአብሔር አብ እና ከባሕርይ ሕይወቱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋራ ምስጋና ይግባው፡፡ መዋዕለ ጾማችንም ባርኮ ቀድሶ  እንዳስጀመረን በሰላም እንዲያስፈጽመን፤ ጾሙንም የኃጢአት መደምሰሻ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ አድርጐ በቸርነቱ ይቀበልልን፤ ለአገራችን ሰላምን ለሕዝቧም ፍቅር፣ አንድነትን ያድልልን አሜን፡፡

በዚህ ጽሑፍ የጾምን ምንነትና አስፈላጊነት፣ የጌታችንን ጾም እና የመጾሙን ምክንያት በአጭሩ እንመለከታለን፤ ልዑል አምላካችን በቅዱስ ቃሉ የሚገባንን ይግለጥልን አሜን፡፡

የጾም ምንነት

ጾም መተውን፣ መከልከልን የሚያጠይቅ መንፈሳዊ ተግባር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የሕግና የሥርዓት መመሪያ የኾነው ፍትሐ ነገሥት ስለ ጾም ሲገልጽ “ጾምስ የሥጋ ግብር ነው፤  ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ፡ ነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ ነው” ብሏል፡፡ (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15)፡፡ ጾም የጸሎት እናት፣ የአርምሞ እኅት፣ የእንባ መሠረት ናት፡፡ በተጨማሪም የመልካም ተጋድሎ ኹሉ መነሻ ጾም መኾኗ በቅዱሳት መጻሕፍት የተረዳ፣ የታወቀ፣ ጉዳይ ነው ፡፡

በሌላ በኩል ጾም ወደ ፈጣሪአችን የምንመለስባት (የምንቀርብባት) መንፈሳዊት መንገድ መሆኗ በመጽሐፍ ቅዱስ  ተገልጧል፡፡ ይህም ሊታወቅ ልዑል እግዚአብሔር በነብዩ አድሮ “በፍጹም ልባችሁ በጾምም በለቅሶ እና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” ብሏል (ኢዩ. 2፥12) ፡፡ “ወደ እኔ ተመለሱ ’’ በሚለው ቃል ውስጥ ወደ ፈጣሪአችን  የምንመለስባቸው መንገዶች ጾም እና ንሰሐ መኾናቸው ታውቋል፡፡ የንሰሐ  ሕይወት ያለ ጾም፣ ጸሎት  ያለ ንሰሐ አይፈጸሙምና ፡፡

የጾም አስፈጊነት

ከመንፈሳውያን  ሀብቶቻችን  አንዷ ጾም ለነፍስ ብቻ  ሳይሆን ለሥጋም  የምትሰጠው ጥቅም  አላት፡፡ ጾም ወደ ፈጣሪአችን የምንመለስባት መንፈሳዊት መንገድ ናት፡፡  እንዲህም ከኾነ  በበደል፣ በኃጢአት እና በአመጻ ምክንያት ከፈጣሪው የተለየ የሰው ልጅ በጾም፣ በጸሎት እና በንሰሐ ሕይወት ዳግም ወደ አምላኩ ይመለስበታል፡፡ ጾም ወደ ፈጣሪአችን ፈቃድና አሳብ የምንደርስበት መንፈሳዊ መንገድ መኾኗ ቀደም ብለን አይተናል፡፡ ከዚህ አንጻር ቸር እና መሐሪ ወደ ኾነው አምላካችን እንድንቀርብ የምታስችል ናትና ጾም የሰው ልጅ ወደ ፈጣሪው የሚሳብባትና የሚቀርብባት መልካም ጎዳና ኾና  ታገለግላለች፡፡

ጾም ኃይል መንፈሳዊን ታቀዳጃለች

ፈቃደ ሥጋን፣ እኩያን ፍትወታት፣ እኩያት ኀጢውዕን ድል ለመንሣትና መንፈሳዊ ኃይልን ለመቀዳጀት የጾም እርዳታ ከፍተኛ ነው፡፡ ሐዋርያው “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ ደግሞ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛለሁ” (1ኛ ቆሮ. 9፥27) እንዳለ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት የጾም አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መኾኑ ታውቋል፡፡ ፈቃደ ሥጋው በጾም፣ በጸሎት እና በሰጊድ እንዲሁም በመሳሰሉት መንፈሳዊ ተግባራት ታግዞ መግራት ያልቻለ እንዴት መንፈሳዊ ኃይልን መቀዳጀት ይቻለዋል? እንኳን  ለሌሎች ሊተርፍ ለራሱም መሆን አይቻለው ፍትሕ መፈሳዊ በጾም ከሚገኙ ረቦች (ጥቅሞች) አንዱ መንፈሳዊያንን  መላእክትን መምሰል መኾኑን አስረድቷል፡፡

መንፈሳዊያን የምንላቸው ቅዱሳን መላእክት እና ቅዱሳን ሰዎች ነው፡፡ ከቅዱሳን  አባቶቻችን እንዱ ቅዱስ ጰውሎስ  ለቆሮንቶስ ምእመናን ካሳሰባቸው ጉዳዮች  አንዱ እርሱን እንዲመስሉ  ነው፡፡ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ“ በማለት (1ቆሮ፡ 11፡1)፡፡  እንግዲህ ቅዱሳንን  ከምንመስልባቸው ጉዳዮች አንዱ ጾም መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ “ጾም  ይረባናል›› ብለን ከመጾማችን የተነሳ መንፈሳዊያንን እንመስላለን፡፡ እነርሱን ከመሰልናቸውም ደግሞ  እነርሱ የሚመስሉትን ክርስቶስን ለመምሰል ይቻላል፡፡ ዳግመኛም  ጿሚው  የረሃብን ችግር ያውቅ ዘንድ፣  ለተራቡት እና ለሚለምኑት ሁሉ ይራራላቸው  ዘንድ ነው ፡፡ (ፍትሕ መንፈሳዊ 574)

ጌታችን ዐርባ መዓልት እና ዐርባ ሌሊት ለምን ጾመ?

የጾም ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል “ራስን ለመግራት’’ (ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት) መንፈሳዊ ኃይልን ለመቀዳጀት መኾኑ ከዚህ በላይ ተገልጿል፡፡ ይኹንና ጌታችን በገዳመ ቆሮንቶስ  ዐርባ መዓልት፣ ዐርባ  ሌሊት የመጾሙ ምክንያት ግን ከዚህ በላይ ለሰው ልጆች ጾም የተጠቀሱትን ምክንቶች ለማሟላት አይደለም፤ እርሱ ጌታችን ኃይል መንፈሳዊውን የሚሰጥ እንጂ የሚቀበል አይደለምና፡፡  ታዲያ ጌታ ለምን ጾመ?

፩. በጾሙ ጾማችንን ሊባርክ ጾመ፡፡

አስቀድሞ በቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሲፈጸም የቆየውን ጾም ኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አጽንቶታል፡፡ ጌታችን የመጾሙ ምክንያት ኃይል  መንፈሳዊ ለማግኘት አስቦ ወይም ያልከፈለው እዳ ኖሮበት ለማስደምሰስ ሳይሆን በጾሙ ጾማችንን ሊባርክልን ነው፡፡ በባህረ ዮርዳኖስ፣ በዕደ ዮሐንስ ተጠምቆ የእኛን ጥምቀት እንደባረከልን፤ በገዳም ጾሞ ጾማችንን ባርኮልናል፡፡ ሥርዓቱን ኹሉ የሠራው በተግባር ጭምር እንጂ በቃሉ ትእዛዝ ብቻ አይደለምና፡፡

. በጾም ጸሎት አርዕስተ ኅጣውእን ድል ማድረግ እንደሚቻል ሊያስገነዝበን ነው፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐርባ መዓልት ከዐርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ፈታኝ ይዞአቸው የመጣውን ፈተናዎች ሁሉ ድል ነሥቷል፤ ጠላት ዲያቢሎስንም አሳፍሮ መልሶታል፡፡ የሰው ልጆችን ሕይወት የሚፈታተኑ የኃጢአት ራሶች የተባሉትም ሦስቱ  ስስት፣ ትዕቢት እና ፍቅረ ንዋይ ናቸው፡፡ በስስት የመጣውን በትዕግሥት፣ በትዕቢት የመጣውን በትህትና እንዲሁም በፍቅረ ንዋይ ለመጣው ፈተና በጸሊአ ንዋይ ድል አድርጓል፡፡

፫. አብነት ሊሆነን

በቅዱስ ወንጌል ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል፡፡ ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ፣ ጠብቁትም፡፡ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ፡፡ ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፤ እነሱር ግን በጣታቸው ሊነኩት አይወዱም›› ብሏል፡፡ (ማቴ. 23፥2-4)

ከዚህ የጌታችን ትዕዛዝ ቢያንስ ሦስት ጉዳዮችን መረዳት ይገባል፡- እነርሱም ጸሐፍት ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር እስከተቀመጡ የሚናገሩትን መስማት እንደሚገባ፣ የጸሐፍት ፈሪሳውያን ተግባር ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ በመኾኑ በተግባር እነርሱን መምሰል እንደማይገባ  እና በሦስተኛ ደረጃ የጸሐፍት  ፈሪሳውያን ጠባይ መታወቁ ነው፡፡

ከሚናገሩት የእግዚአብሔር ቃል አንዱንም እንኳ አይፈጽሙምና የእነርሱን አብነት ከመከተል ይልቅ ከእርሱ መማር እንዲገባን “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እነ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና” (ማቴ. 11፥28) ሲል ጌታችን ነግሮናል፡፡

እንደ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሳይሆን በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ የአገልጋዮቹን እግር እያጠበ ጭምር ተግባራዊ ትምህርትን ያሳየንን ጌታችንን በጾሙም ጭምር እንመስለው ዘንድ ሥርዓተ ጾምን በተግባር ሠርቶልናል፡፡

፬. ጾምን የሥራችሁ መጀመሪያ አድርጓት ሲል ነው፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ነው ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ የገባው፡፡ ይኸውም አብነት ነው፡፡ ጌታችን ከጥምቀት በኋላ ወንጌልን ወደ መስበክ፣ ተአምራትን ወደ ማድረግ አልተሰማራም፡፡ እንግዲህ እኛም ከኹሉ ተግባራችን አስቀድመን መጾም መጸለይ እንዳለብን በዚሁ የጌታቸን ተግባር እንረዳለን፡፡

 ማጠቃለያ ፡-

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ አድሮ “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም” ብሏል (ኤር.29፥11)፡፡ በዚሁ መሠረት በቀደሙት ወላጆቻችን (በአዳም በሔዋን) ዘመን ጀምሮ የምትረባንን ሥርዓተ ጾም ሠርቶልናል፡፡ ይህም ሊታወቅ አዳምና ሔዋን  በገነት ሲኖሩ እፀ በለስ እንዳይበሉ  መታዘዛቸው አንድም  ሥርዓተ ጾምን ሲያስተምራቸው ነው፡፡

ከዚያም በኋላ  በዘመነ አበው፣ በዘመነ ነቢያት በልዩ ልዩ መልክ ሥርዓተ ጾምና ጸሎት ሲፈጸም ቆይቷል፡፡ ከኹሉ በላይ በደገኛው የምሕረት ዘመን (በሐዲስ ኪዳን) ራሱ ጌታችን በዓት አጽንቶ በፍጹም ትዕግስት ጾሟል፡፡ እንግዲህ እነዚህን ኹሉ አብነት አድርገን ጌታችና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድም በትምህርት፣ አንድም በተግባር ስለ ጾም ያስተማረንን አብነት ወስደን በፍጹም ፍቅርና አንድነት ልንጾም ያስፈልገናል፡፡ ስለኹሉ የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ጸሎት አይለየን አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *