“በማርያም ልደት ዛሬ ደስታ ሆነ” (ቅዱስ ያሬድ)

በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግንቦት አንድ ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት የሚከበርበት ዕለት ነው፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት እግዚአብሔር አስቀድሞ በትንቢት፣ በምሳሌና በራዕይ የሰውን ልጅ ድኅነት በጉጉት ሲጠባበቁ ለነበሩ ነቢያት ገልጿል፡፡ በልዩ ልዩ ምሳሌዎችም መስለው ከፊታቸው ያለውን ዘመን አሻግረው በመመልከት ተናግረዋል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ይወጣል፡፡” ብሎ ትንቢት የተናገረላት፤ ልበ አምላክ ዳዊት “የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ፤ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ “ፀሐይን የተጎናጸፈች፣ ጨረቃን የተጫማች፣ አሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል በራሷ ላይ ያላት” በማለት ተባብረው የመሰከሩላት ቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደችባት ቀን ናት፡፡ (ኢሳ. ፲፩፥፩ ፤ መዝ. ፵፬፥፱፤ ራዕ. ፲፪፥፩)

ነቢየ እግዚአብሔር ሰሎሞን በመኃልየ መኃልየ ድርሰቱም “ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ፤ ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ” እያለ ተናግሮላታል፡፡ ይህም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት በሊባኖስ ሀገር ስለመሆኑ ያመለክታል፡፡ (መኃ. ፬፥፰) በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት መሠረት የእመቤታችን የትውልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለው ተራራማ ሀገር ነው፡፡

የእመቤታችንን የዘር ሐረግ ወደ ኋላ ሰባት ትውልድ ስንቆጥር ቴክታና ጴጥርቃ የተባሉ ባልና ሚስት ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስትወጣ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስትደርስ፤ ስድስተኛዪቱ ጨረቃን ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ በሕልም በማየታቸው በሀገራቸው ለሚገኝ መፈክረ ሕልም (ሕልም ፈች ሊቅ) ሄደው ነገሩት፡፡ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም” አላቸው፡፡ እነርሱም ጊዜ ይተርጉመው ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ልጅ ወለዱ፡፡ ስሟንም “የተሳልኩትን አገኘሁ፤ የተመኘሁትን አገኘሁ” ሲሉ “ሄኤሜን” አሏት፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ለአካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡

ኢያቄምና ሐና መካን ስለነበሩ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ጸልየው፤ ሲሰጣቸውም መልሰው ለእርሱ እንደሚሰጡ ስዕለትን ተስለው ነበር፡፡ ጸሎታቸው ሲደርስ ለሐና በሕልም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጸላት፡፡ ፀዓዳ ርግብ ሰባቱ ሰማያትን ሰንጥቃ መጥታ በራሷ ላይ ተቀምጣ በጆሮዋም ገብታ በማሕፀኗ ስትተኛ አየች፡፡ ኢያቄምም በተመሳሳይ ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ዖፍ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ ሁለቱም በሕልም ያዩትን በመግለጥ ተነጋገሩ፡፡

ሐናም ፀነሰች፤ ሐና መጽነሷ በታወቀ ጊዜም የአርሳባንን ልጅ ዓይን በማብራቷና ሳሚናስ የሚባለውን የጦሊቅን ልጅ ከሞት በማስነሣቷ አይሁድ በቅናት ተነሳስተውባቸው ሊገድሏቸው እንደሚሹ ለሐናና ኢያቄም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ ስለነገራቸው ወደ ሊባኖስ ተራራ እንደሄዱ እና በጨረቃ የተመሰለች ድንግል ማርያም በሊባኖስ ተራራ እንደ ተወለደች የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን፤ ፀዓዳ (ነጭ) መሆኗ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፡፡ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መሆኗን ሲያጠይቅ ነው፡፡

በሐዲስ ኪዳን ሊቃውንትም ትንቢተ ነቢያትንና ወንጌልን በማጣጣም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት አመስጥረው አስተምረዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ጥቂቶቹን ብንመለከት፡-  ቅዱስ ያሬድ “ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች” ሲል ተናግሯል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደፈረሰው ዓለም በንጽሕና፣ በቅድስናና በድንግልና ስታበራ መኖሯንና ኋላም የዓለም ብርሃን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መውለዷን አመስጥሮ ተናግሯል፡፡

አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ” በማለት የድንግል ማርያምን በንጽሕና፣ በቅድስና መወለድ ተናግሯል፡፡

ሐና እና ኢያቄም ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደው በአድባረ ሊባኖስ ሥር እመቤታችንን ወለዱ፡፡ በወቅቱ ከቤት የወጡት ለሽሽት ነበርና ስንቅ ስላልያዙ ምግባቸው ንፍሮና ጥራጥሬ ነበር፡፡ ይህንን ትውፊት በመያዝ ምእመናን ንፍሮ አዘጋጅተው በዝማሬና በእልልታ እንደሚያከብሩት ሁሉ አንዳንዶች ባልተገባና ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ባፈነገጠ ሁኔታ ሲያከብሩትም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ አካሄድ ፍጹም ተገቢ ባለመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡

በእውነት የእርሷ ልደት የልዑል እግዚአብሔር ማደሪያው መቅደስ የተሠራባት፣ የነቢያት ትንቢት የተፈፀመባት፣ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰው ልጆች ሁሉ (ለሕያዋን ሁሉ) ታላቅ የደስታ ቀን በመሆኑ ሁላችንም “ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ እነሆ ዛሬ በእመቤታችን ልደት ደስታ ሆነ” እያልን በዝማሬ እናመስግናት።

የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *