“በሃይማኖት ጽኑ” (፩.ቆሮ. ፲፮፡፲፫)

መ/ር ቢትወደድ ወርቁ

“ሃይማኖት” የሚለው ቃል ሃይመነ፣ አሳመነ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም፦ ማመን መታመን፣ አመኔታ ማለት ነው። ይኸውም ቅድመ ዓለም ከሁሉ በፊት የነበረ ፍጥረታትን የፈጠረ፤ ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ፤ ዓለምንም አሳልፎ የሚኖር፤ ለእርሱ ግን አስገኝ አሳላፊ የሌለው፤ በአንድነት በሦስትነት ያለ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳለ ማመን ነው። (ሮሜ ፲፥፱)

አንዳንድ ሰዎች “ሃይማኖት አያድንም”፣ “ጌታን በግልህ አምልከው”፣ “መጽሐፍ ቅዱስን እንደፈለግህ በገባህ መንገድ አንብበህ ተረዳ” እያሉ መጮህን ልማድ አድርገውታል፡፡ በዚህም ስብከታቸው ግላዊነትን፤ በነጻነት ስም ልቅነትንና ዋልጌነትን ተቋም አልባ እምነት አስፋፍተው ትውልዱን ከሃይማኖት ለማስወጣት ጥረት ሲያደርጉ ይታያል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ግላዊነትንና ገደብ የለሽነትን አያስተምረንም፡፡ ይህን በሚገባ ለመረዳት ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ በመልእክቱ የጻፈልንን በጥቂቱ አፍታተን እንመልከተው፡፡ ከዚህ ከሐዋርያው መልእክት የሚከተሉትን መንፈሳዊ መልእክቶችን እንረዳለን፡-

ሃይማኖት የተሰጠው ለድኅነት መሆኑን

ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነው የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ በመልዕክቱ “ወንድሞች ሆይ ስለ ሁላችን መዳን እጽፍላችሁ ዘንድ በሁሉ ተፋጠንሁ፤ እጅግ ተግቼ እጽፍላችኋላሁና ለቅዱሳን የተሰጠችውንም ሃይማኖት ትጋደሉላት ዘንድ እማልድላችኋለሁ፡፡” በማለት ይናገራል፡፡ (ይሁ. ፩፡፫) ይላልና በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሃይማኖት፡ የእግዚአብሔር የአካል ሦስትነት፣ የባሕርይ፣ የሕልውና፣ የመፍጠር፣ የመስጠት፣ የመንሣት፣ መለኮታዊ አንድነት፣ የክርስቶስን በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆኖ መገለጥ፣ መከራ መቀበል፣ መሞት፣ መነሣት፣ ማረግና ዳግም መምጣትን ማመን፤ ያለ ጥምቀት፣ ያለ እርሱ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ሕይወት እንደሌለ መቀበልና በፍጻሜም ሰው ከሞተ ከፈረሰ ከበሰበሰ በኋላ ይነሣል ብሎ ጽኑዕ ተስፋን መያዝ ማለት ነው፡፡ (ዘፍ. ፩፥፳፮፤ ፫፥፳፪፣ ኢሳ. ፯፥፲፬፤ ፱፥፮፤ ሚክ. ፭፤፩፣ መዝ፣ ፵፱፥፪፤ ኢሳ. ፵፥፲፤ ራእ. ፳፪፥፲፪፤ ዮሐ. ፫፥፭፤ ማር. ፲፮፥፲፮፤ ዮሐ. ፮፥፶–፶፱፤ ማቴ. ፳፮፥፳፮፤ ኢሳ. ፳፮፥፲፭-፲፮፤ ዳን. ፲፪፭፪)

ይህ ባይሆን ቅዱሳን ሐዋርያት ደጋግመው “በሃይማኖት ጽኑ”፤ “በሃይማኖት ቁሙ” ፤ “ሃይማኖታችሁን ጠብቁ” በማለት ባላስተማሩን ነበር፡፡(ቆላ. ፩፳፮-፳፯፤ ፩ቆሮ. ፲፮፥፲፫፤ ቆላ. ፪፥፯፤ ይሁ. ፩፥፳፤ ሐዋ. ፮፥፯፤ ፲፬፥፲፯)፡፡

ሃይማኖት የተሰጠው ለቅዱሳን እና አምነው በስሙ ለተጠሩት መሆኑን፡-

ሃይማኖት ለቅዱሳን የተሰጠ ስለሆነ ሐዋርያው “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠ” አለን፡፡ የክርስትና ሃይማኖት የተሰጠ መሆኑን ሲያጠይቅ፡፡ ቅዱሳን ስንል መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን:-

  • ቅዱሳን መላእክትን (ማቴ. ፳፭፥፴፩፤ ዳን. ፬፥፵፪)
  • ቅዱሳን ነቢያትን(፪ጴጥ. ፩፥፳፩፤ ፫፥፴፪)
  • ቅዱሳን ሐዋርያትን(፪ጴጥ. ፫፥፪)
  • ቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታትን ነው (ሉቃ ፩፥፮፤ ፪ጴጥ. ፪፥፯-፰፤ ዕብ. ፲፥፩-፴፬)
  • እንዲሁም አምነው በስሙ ለተጠሩት እና በስሙ ለሚጋደሉ ሁሉ የተሰጠ ነው፡፡ (፩ቆሮ. ፩፥፪-፫፤ ሮሜ. ፰፳፰-፴)

ስለዚህ ሃይማኖት ለቅዱሳን የተሰጠ ነው ስንል ለቅዱሳን መላእክት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማዕታት፣ እንዲሁም በስሙ ልጅነትን አግኝተው ጸንተው ለተጋደሉ ሁሉ የተሰጠ ነው ማለታችን ነው፡፡ እኛ የክርስትና ሃይማኖት ተቀባዮች እንጂ ጀማሪዎች አይደለንምና ሌላ እንመሥርት፤ ይህን እንጨምር፣ ያን እንቀንስ የማለት መብቱም ዕውቀቱም ፈቃዱም የለንም፡፡ “በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፡፡” እንዲል፡፡ (ኤፌ. ፪፥፲፱-፳) ሃይማኖት የምንጨምርበት የምንቀንስበት የምንቀጥልበት የላብራቶሪ ውስጥ ቁስ፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም፣ የአስተዳደር ሥርዓት ወይም የፋሽን አይደለምና፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘላለምም ያው ነው፡፡” እንዲል፡፡ (ዕብ. ፲፫፥፯)

የክርስትና ሃይማኖት በባሕርይው ማኅበራዊ እንጂ ግላዊ አይደለም፡፡ “በግልህ አምልክ”፤ “በግልህ ብቻ ጸልይ” ወዘተ የሚሉ መራዥ ንግግሮች በሐዋርያት ትምህርት ቦታ የላቸውም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ጽኑ፣ ጹሙ፣ ጸልዩ፣ ተሰብሰቡ ብለው የክርስትና ሃይማኖትን ትክክለኛ ጠባይ እኛ እንጂ እኔ እንደማይባልበት ነግረውናል፡፡ አንድነታችንን እንድናጸናና ግለኝነትንም እንድናርቅ ሰብከውናል፡፡ (፩ቆሮ. ፩፥፲፪፤ ዕብ. ፲፥፳፭፤ ሐዋ. ፬፥፵፪፤ ሐዋ. ፪፥፵፯)

ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለምን፣ ዓለም በዝና ከፍ አድርጋ የሰቀለቻቸውን ሰዎች ንግግር ወይም አቋም፣ እንዲሁ ሳንመረምር የተቀበልነውን ነገር በመያዝ የማንም መንጋ ወይም ተከታይ ሳንሆን ነቢያት ሐዋርያት ያስተማሩንን ትምህርት በመቀበል የክርስቶስ መንጋዎች ልንሆን ይገባል፡፡ (ሐዋ. ፵፥፵፰፤ ዮሐ. ፲፥፳፯)

የክርስትና ሃይማኖት ፍጹም መሆኑን

ቤተ ክርስቲያን ስለ እግዚአብሔር በአካል ሦስት፣ ባሕርይ አንድ ስለ መሆኑ፣ ስለ ጥምቀት፣ ስለ ቁርባን፣ ስለ ሙታን ትንሣኤ፣ ስለ ቅዱሳን ክብር የምታስተምረው ትምህርት ፍጹም ነው፡፡    “ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት” መባሉን ልብ በሉ፡፡ ስለዚህም በቤተ ክርስቲያን ሆኖ በኃጢአት፣ በዝሙት፣ በስካር፣ በገንዘብ ፍቅር፣ ሆድንና ሥልጣንን በመውደድ ከእግዚአብሔር አንድነትና ፈቃድ የራቀን ሰውነት በንስሓ በማደስ ወደ ፍጹምነት ለማድረስ መጋደል እንጂ ፍጽምት የሆነች የክርስትና ሃይማኖትን ላድስ ማለት ወደ ከፋ የክሕደት፣ የጥፋትና የሞት መንገድ ይወስዳል፡፡(ማቴ. ፭፥፭፰፤ ዘፍ. ፮፥፱፤ ፩ጴጥ. ፭፥፲፩) የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጉድለትንም የክርስትና ሃይማኖት ጉድለት ከማድረግ እንቆጠብ፡፡

ሃይማኖት የተሰጠው አንድ ጊዜ መሆኑን

ወደ ሕይወት የሚወስድ አንድ መንገድ እንጂ ብዙ ወይም አቋራጭ መንገዶች አይደሉም፡፡ (ኤር. ፮፥፲፮፤ ማቴ. ፯፥፲፫-፲፬) ወደ ሥልጣን፣ ወደ ባለጠግነት፣ ወደ ዕውቀት የሚያደርሱ ብዙ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ወደ እግዚአብሔር የሚወስደው መንገድ (ሃይማኖት) ግን አንድ ብቻ መሆኑን ከላይ የተጠቀሱትን ኃይለ ቃላት በማስተዋል ማንበብ እና በቅንነት መረዳት ይቻላል፡፡ “አንድ ጌታ፤ አንድ ሃይማኖት፤ አንዲት ጥምቀት” እንዲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ (ኤፌ. ፬፥፬)

በአንጻሩም እጅግ በሰፋ የምግባር ብልሹነትና ልክ በሌለው የሥጋ ፈቃድ የተሞሉ የጥፋት መንገዶች እንዳሉ እነርሱም ለሰው ቅን እንደሚመስሉ ተነግሮናል፤ የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ አይደለምና፡፡ (ምሳ. ፲፬፥፲፪፤ ማቴ. ፯፥፲፫-፲፬) ከአዳም ጀምሮ የተነሡ ቅዱሳን በሙሉ ወደ እግዚአብሔር የደረሱት በአንድ እምነት ተጉዘው እንጂ በተለያየ መንገድ ሄደው አይደለም፡፡ ሰው በፈለገው መንገድ ለመጓዝ ነጻ ፈቃድ ከተጠያቂነት ጋር እንደተሰጠውም አንዘንጋ፡፡ በሃይማኖት እየኖሩ መጋደል እንደሚገባ ሐዋርያው በዚህ መልእክቱ በክርስትና ሃይማኖት አምነን ከእርሱ   ጋር ስንኖር ፈተና እንዳለና ፈተናውንም ሁሉ በመቋቋም መጋደል እንደሚገባ አስተምሮናል፡፡ ተጋድሎውም ከሥጋውያን ከደማውያን ሰዎች ጋር ሳይሆን በሰዎች ላይ አድረው ከሚመጡ ክፉዎች መናፍስትና ርኩሳን አጋንንት ጋር ነው፡፡ “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፡፡” እንደተባለ፡፡ (ኤፌ. ፮፥፲፩-፲፮)

የቤተ ክርስቲያን ውጊያ ከሰዎች ጋር አይደለም፤ ድሉም የትግል ስልቱም ማሸነፊያ መሣሪያውም ሥጋዊ አይደለም፡፡ ማሸነፊያው ቃለ እግዚአብሔርን መማር፣ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መጮህ፣ የየራሳችንንም መንፈሳዊ ድርሻ በመንፈሳዊ መንገድ መወጣት፣ እያንዳንዳችንም ራሳችንን መመርመርና ንስሓ መግባት ቅድስናን በመለማመድና ገንዘብ በማድረግ ነው፡፡ (ማቴ ፲፯፥፳፩፤ ኤፌ. ፮፥፲፯፤ ፪ቆሮ. ፲፫፥፭) ስለዚህም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እስከ ምጽአተ ክርስቶስ ፈተና እንደማይለያት ጠንቅቀን እንወቅ፡፡ በሃይማኖትም ጸንተን እንኑር፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን በረከት   አይለየን!!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *