ሰቆቃወ ድንግል፣ የድንግል ልቅሶ
በእንዳለ ደምስስ
ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ዐርባውን ቀናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ጌታችን መድኃኒታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ታቅፋ፣ ይረዷት ዘንድ ሰሎሜንና አረጋዊው ዮሴፍን አስከትላ ወደ ግብፅ የተሰደደችበትን፣ የተመለሰችበትን የመከራ ወቅት የምታስብበት ጊዜ ነው፡፡
እመቤታችን ልጇን ይዛ ለምን ተሰደደች ስንል፡- በሄሮድስ ዘመን በይሁዳ ክፍል በቤተልሔም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል ይሰግዱለት ዘንድ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡ ጊዜ ንጉሡ ሄሮድስ አግኝቷቸዋል፡፡ “ኮከቡን በምሥራቅ ዐይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናልና የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” ሲሉ ጠየቁ፡፡ ሄሮድስ ይህንን በሰማ ጊዜም እጅግ ደነገጠ፡፡ ሄሮድስ ብቻ አይደለም መላዋ ኢየሩሳሌም መደንገጧን ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ይነግረናል፡፡ ሄሮድስ የካህናት አለቆችንና ጻፎችን ሰብስቦም “ክርስቶስ በየት ይወለዳል?” ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ እነርሱም በይሁዳ ክፍል በቤተልሔም እንደሚወለድ በነቢይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና አሉት፡- “የይሁዳ ምድር አንቺ ቤተልሔም ከይሁዳ አለቆች ከቶ አታንሺም፣ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ ከአንቺ ይወጣልና” የሚለውን በኢሳይያስ የተነገረውን የትንቢት ቃል ነገሩት፡፡ በዞህም ምክንያት ይገድለው ዘንድ ፈለገ፡፡ ዓመት፣ ዓመት ከመንፈቅ፣ ሁለት ዓመት የሞላቸው ሕፃናትንም አስገደለ፡፡
በዚህ ወቅት ነበር የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አረጋዊው ዮሴፍ በሕልም መጥቶ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ፣ እናቱንና ሕፃኑን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፣ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ኑር” ያለው፡፡ ወደ ምድረ ግብጽም ተሰደዱ፡፡ በዚያም ለሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ያህል ረኀብ፣ ጥሙንና እንግልቱን ሁሉ ታግሰው አልፈዋል፡፡ (ማቴ.2.፩-፲፭)፡፡
በዚህም ምክንያት የእመቤታችንን ስደት፣ የደረሰባትን እንግልትና መከራ በማሰብ በረከት ለማግኘት በርካቶች በፍቅር ይጾሙታል፡፡ በቤተ ክርስቲያንም ሊቃውንትና ምእመናን በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሡት ኢትዮጵያዊው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ አባ ጽጌ ድንግል በደረሱት “ማኅሌተ ጽጌ” በተባለው የምስጋና ክፍል እመቤታችንን ያመሰግኑዋታል፡፡
በዘመነ ጽጌ እመቤታችን የምትመሰገንበት ምስጋና የመጀመሪያው ማኅሌተ ጽጌ ሲሆን ሁለተኛው ሰቆቃወ ድንግል ይባላል፡፡ ሰቆቃወ ድንግል የተጻፈው በግጥም ሲሆን ብዛቱ $፮ ነው፡፡ የእመቤታችንን ሰቆቃና ዋይታ በስፋት ይናገራል፡፡
ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል እመቤታችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ መሰደዷን፣ በስደቷም ያጋጠማት መከራ እጅግ ለመራራ ሐዘን ስለዳረገው ድርሰቱን በቀለም ሳይሆን ዕንባውን እያፈሰሰ መጻፉን “የድንግልን ልቅሶ ታሪክ የምጽፈው በዕንባ ቀለም ነው፣ የሚያነበውም ዕንባና ዕዥ ነው ይበል” ይላል/ሰቆቃወ ድንግል/፡፡
ሰዎች መሪር የሆነ ሐዘን ሲገጥማቸው ከዐይናቸው ውኃ መሳይ ዕንባ ብቻ ሳይሆን ደም የተቀላቀለበት ዕንባ የሚያፈሱበት ወቅት አለ፡፡ ውኃ ከደም ጋር ሲቀላቀል ዕዥ ይሆናል፡፡ እስራኤላዊቷ ራሔል ሁለቱን ልጆቿ ከጭቃው ጋር እርገጫቸው ስትባል ሳትወድ በግድ የማሕፀኗን ክፋዮች ከረገጠቻቸው በኋላ ከዐይኖቿ ዕንባና ደም ተቀላቅለው ፈሰዋል፡፡ ደም የተቀላቀለበት ዕንባዋን ወደ ሰማይ ብትረጨው ከመንበረ ጸባኦት ደርሳል፡፡ “በግብፅ ያለውን ሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፡- ከአሠሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፣ ሥቃያቸውንም ዐውቄያለሁ” (ዘፀ.፫.7) እንዲል፡፡
ድንግል ማርያም ሕፃናት እንዲገደሉ የሚለውን አዋጅ ስትሰማ ከልጇ ሞት ይልቅ የእርሷ ሞት እንዲቀድም መመኘቷን ሊቁ እንዲህ ሲል ያስረዳል፡፡ “የልጄ ደሙ ሲፈስ ከምመለከት እኔን አስቀድመው ይግደሉኝ አለች” እያለ የሐዘኗን ጥልቀት ይገልጸዋል፡፡ የሄሮድስ ጭካኔ የተሞላበት አዋጅ ድንግል ማርያምን ከልጇ ሞት ይልቅ የራሷን ሞት እንድትመርጥ አድርጓታል፡፡/ማኅሌተ ጽጌ/
አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ ድንግል ማርያም የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን ስለተሰማው እንደ ልብ ወዳጅ በሐዘን ስሜት በድርሰቱ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፡፡ “ድንግል ማርያም ወዴት ሄደች? በቤተልሔም ፈልግኋት ግን አላገኘኋትም፣ እናንተ የገሊላ ሰዎች ዐይታችኋት እንደሆነ እጠይቃችኋለሁ ወሬዋን ንገሩኝ፣ ወደሄደችበትም በልቅሶ እከተላት ዘንድ መንገዱን አሳዩኝ” እያለ ድንግል ማርያምን በእግረ ሕሊናው ሊከተላት ይፈልጋል፡፡
ስለ ግብፅ ስደቷና የደረሰባት መከራ ሲገልጽም “ልጅሽን አንድ ጊዜ በጀርባሽ፣ አንድ ጊዜ በጎንሽ ስትይዢ ብዙ ደከምሽ፡፡ በእግሩ ድክድክ እያለ ይሄድና እንድታዝይው ደግሞ ያለቅሳል፣ ከሰሎሜ በቀር የሚያግዝሽ፣ ከዮሴፍ በቀር ስንቅሽን የሚሸከም ረዳት አልነበረሽም” ይላል የግብፁ በረሃ ክብደት፣ የአሸዋው ግለት፣ የፀሐዩ ሙቀትበዓነ ኅሊና እየታየው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በግብፅ በረሃ ያልደረሰባት ጸዋትወ መከራ የለም፡፡ የውቅያኖስ ውኃ በመዳፉ የያዘውን አምላክ አዝላ ተጠምታለች፡፡ ገበሬ በማያርስበት ምድረ በዳ ከሰማይ መና አውርዶ የመገበውን አምላክ ይዛ ተርባለች፡፡
ጌታችን በዚያን ክፉ ጊዜ እንደ ሰውነቱ በግእዘ ሕፃናት ይጠማ ይራብ እንጂ እንደ አምላክነቱ ደግሞ ድንቅ ተአምራቱንም አድርጓል፡፡ ሊቁም በዘመድ እጦት ምክንያት በሐዘን ትንገላታ የነበረችውን የድንግል ማርያምን መሪር ሐዘን ከገለጠ በኋላ በልጇ ሁሉን ቻይነት ለሐዘኗ መጽናናትን ለጥሟ ቀዝቃዛ ውኃ እንዳዘጋጀላት ይነግረናል፡፡
አባ ጽጌ ድንግል በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የተከናወነውን ታላቅ መሥዋዕትነት የተከፈለበትን የድንግል ማርያምን ሐዘን፣ ስደትና መከራ ቀጥተኛ ተካፋይ ባይሆንም በመንፈሰ ኅሊና ግን ሰቆቃወ ድንግል ብሎ በደረሰው ድርሰት ሐዘኑን ገልጿል፣ አብሯት እንደነበረ ሁኖ አልቅሷል፣ አብሯት እንደነበረ ሁኖም ተሰዷል፣ በዚህም የመከራዋ ተካፋይ ሆኗል፡፡
ምእመናንም የእመቤታችንን ስደት ለማስታወስ የፈቃድ ጾም በመጾም፣ በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ማሕሌተ ጸጌን ከሊቃውንቱ ጋር በመሆን እየዘመሩ የደረሰባትን መከራና እንግልት ያስባሉ፡፡ በማኅበር በመሆንም ዝክር እየዘከሩ፣ በንስሓ አባቶቻቸው አማካይነት ሌሊቱን ያለ ዕረፍት በያሬዳዊ ዝማሬ ሲያመሰግኑ ያደሩትን ሊቃውንቱንና ካህናቱን በማብላት በማጠጣት የትሩፋት ሥራ ይሠራሉ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጽንሰቱ እስከ ዳግም ምጽአቱ ስለሚሠራው ሥራ አስቀድሞ በነቢያቱ አድሮ ትንቢት አናግሯል፡፡ ስለምን ወደ ግብፅ ተሰደደ ስንል በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት እንችላለን፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡- ለፍቅሩ ይሳሱለት ስለነበር፣ ኪዳነ መልከ ጼዴቅን ለመፈጸም፣ አጋንንትን ከግብጽና ከሰው ልቡና አስወጥቶ ለመስደድ፣ አዳም ከዚህ ዓለም አፍኣ በምትሆን ከገነት ተሰዶ ነበርና ለመካስ፣ ለሰማዕታት ስደትን ለመባረክ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያብራራሉ፡፡ በተጨማሪም ግንቦት ፳፬ ቀን በሚነበበው ስንክሳር “ሔሮድስ ቢያገኘው ሊገድለው እንዳይችል፣ ሌሎች ሰዎች ትስብእቱ ምትሐት ነው ብለው እንዳያስቡ፣ የግብፅ ሰዎች በመካከላቸው በመመላለሱ ጸጋውን እንዲያገኙ፣ ጣዖትንም ቀጥቅጦ ለማጥፋት፡፡ ‘እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብፅ ይወርዳል፣ ጣዖታትም በፊቱ ይወድቃሉ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ” የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
አባ ጽጌ ድንግል በዘመኑ ቢኖር ኖሮ የስደቷና የመከራዋ ተፋካይ ይሆን እንደነበረ በገለጸበት አንቀጹም “እመቤቴ ሆይ በመንገድ ያገኘሽን የቀኑን የፀሐይ ቃጠሎና የሌሊቱን የዱር ቅዝቃዜ ሁሉ ስንቱን እናገራለሁ፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር ሽፍቶች አስቸገሩሽ፣ እኔ ባሪያሽ በእነዚያ ዓመታት ብኖር ከአንቺ ጋር እንድሰደድ በፈለግሁ ነበር፡፡ ሲድህም በድንጋይ የተፈገፈገውን የእጁን አሠር በአፌ በሳምኩት ነበር፣ በማርያም ልጅ ፍቅር ልቤ ቆሰለ” በማለት ፍቅሩን ይገልጻል፡፡/ማኅሌተ ጽጌ/፡፡
በመሆኑም በዚህ በወርኃ ጽጌ የድንግል ማርያምን የስደትና የመከራ ወራት ስናስታውስ ስደተኞችን፣ የሚበሉት፣ የሚጠጡት አጥተው የሚሰቃዩትን፣ ዘመድ ጠያቂ የሌላቸውን በየጸበል ቦታ የወደቁትን በመደገፍ፣ በማብላትና በማጠጣት ሊሆን ይገባል፡፡ ከእመቤታችን ስደት በረከት ይከፍለን ዘንድ የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ምንጭ፡- መጽሐፍ ቅዱስ፣፳፻
ስንክሳር፣ ግንቦት ፳፬፣ ገጽ ፫፻፳፯
ሐመር መጽሔት ጥቅምት ፳፻፲፩ ዓ.ም
ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከጥቅምት ፩-፲፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!