ሰሚ ያጣው የሕፃናት ጩኸት

በዲ/ን ታደለ ሲሳይ

ቀኑ ወረፋውን ለጨለማው ለመልቀቅ በማመናታት ላይ ያለ ይመስላል፡፡ የአዲስ አበባ ምድርም የፀሐይን ብርሃን በሰው ሠራሽ ብርሃን ለመተካት ፓውዛዎቿን ስልም ቁልጭ እያደረገች ነው፡፡ ሁሉም በየፊናው እየተሯሯጠ ነው፡፡ ጠዋት ሥራ የገባው ወደ ቤቱ ለመመለስ፣ ማታ የሚሠራው ደግሞ በአዲስ መንፈስ ለመሥራት ጥድፊያ ላይ ነው፡፡

ከዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ተነሥቼ በድካም የዛለ ሰውነቴን ለማሳረፍ ወደ ቤቴ እያመራሁ ነው፡፡ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ዋናውን አስፓልት አቋርጬ ቀጥታ በድባብ መናፈሻ አድርጌ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ግቢን ትቼ ወደ ታች ስታጠፍ በርቀት የሚስረቀረቅ የሕፃናት ኅብረ ድምፅ ሰማሁ፡፡ ምን እንደሚሉ አይሰማም፤ የድምፃቸው ጣዕመ ዜማ ግን ልብን ሰርስሮ ይገባል፡፡

የራቀኝን ድምፅ ቀርቤ ልሰማው፣ የአንደበታቸውን ፍሬ ቀርቤ ልለየው ወደ ፊት ገሰገስኩ፡፡ የተበጣጠሰ ልብስ የለበሱና ተያይዘው የተወለዱ የሚመስሉ ሕፃናት ብርዱን በኅብረት ለማሸነፍ ተቆላልፈው ያንን አንጀት የሚበላ ድምፅ አሁንም ያስተጋባሉ፡፡ ፊት ለፊታቸው ከለበሱት ልብስ የማይተናነስ ብጥስጣሽ ዘርግተዋል፡፡ ከፊት ለፊታቸው የተዘረጋውን ልብስ ሳይ ምን ፈልገው እንደሚያዜሙ ለመረዳት አላቃተኝም፡፡ እንደ ዜማቸው ሁሉ በዜማው መሃል ያለውን ግጥም ለመስማት ጓጉቻለሁ፡፡ ከጀርባቸው ካለው ድንጋይ ላይ ቀስ ብየ ተቀመጥኩና የሕፃናቱን መልእክት መስማት ጀመርኩ፡፡

ባይሆንልኝ እንጂ ከሞቀ ቤት መኖር

ከወላጆቼ ጋር እውል አድር ነበር፡፡

ጎዳና ነው ቤቴ ጎዳና ነው ቤቴ

የተወለድኩበት ኑሮዬና እድገቴ፡፡

ጎዳና ጎዳና ርስቴ ጎዳና

ልብሴ ነፋስ ሲሆን ቀለቤ ልመና፡፡

ግጥሙና ዜማው ከሕፃናቱ አንደበት የሚወጣ አይመስልም፤ ግን ከባድ ሮሮ ነው፡፡ ሰው ሁሉ እያየ ነው የሚያልፋቸው፡፡ አልፎ አልፎ አንዳንድ ሰዎች ዐሥርም አምስትም ኪል እያደረጉ ይጥሉላቸዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ዐይቶ ከንፈር መምጠጥ ብቻ ነው፡፡

አንድ ወጣት በድንገት ሲያልፍ አያቸውና፣

«አቤት ይህቺ ሀገር!» አለ በመቆጨት ስሜት፡፡

«ይህቺ ሀገር ምን አደረገች?» አለ እንደኔ በርቀት የሕፃናቱን ድምፅ ሲሰማ የነበረው ሰው ተናዶ፡፡

ወጣቱ ድንገት ዘወር አለና፣ «እንደነዚህ ያሉትን ሕፃናት መርዳት የሀገሪቱ ድርሻ ነዋ፡፡»

«አትሳሳት ወንድሜ፤ ሀገር ማለት እያንዳንዳችን ጭምር ነን፡፡ አንተ አይተህ እያለፍክ ሀገር አትውቀስ፡፡ ምክንያቱም የሀገሪቱ አንድ አካል ነህና፡፡»

«እኔማ ምንም የለኝም»

«ያለህን ስላልሰጠህ ነው እንጂ አለህ»

«ምን?»

ያለውን ሊያሳየው ተጠጋው፡፡

«ስንት ልብስ እንደለበስክ ታውቃለህ? በውስጥ ስስ፣ ከዚያ ቲሸርት፣ ከዚያ ደግሞ ሸሚዝ፣ ከዚያም ጃኬት፡፡ አየህ? በአንድ ጊዜ አራት ልብስ ደራርበህ ለብሰሃል፡፡ እነዚህን ልጆች ግን ተመልከት፡፡ አንዱ እንኳን በወጉ አልሆን ብሎ ተቀዳዷል፡፡ ያለንን ስለማናስተውል ነው እንጂ ያለንን እያንዳንዳችን ብንሰጥ ጥሩ ነበር፤ ዝም ብሎ ሀገር መውቀስ አይቻልም፡፡» አለው፡፡

ወጣቱ የለበሰውን ልብስ ሊያወላልቅ ሲሞክር «ምን እያደረክ ነው?» አለው፡፡

«አራት ስለለበስኩ አንዱን ልሰጥ ነዋ፡፡» አለው ዐይኑን ከሰውየው ላይ አፍጥጦ፡፡

«ለመስጠት መወሰንህ ጥሩ ነው፡፡ ግን አስበህበትና አምነህበት ነው መስጠት ያለብህ፡፡ እኔ ስለወቀስኩህ በስሜት ማድረግ የለብህም፡፡ አስበህበት ትሰጣለህ» አለው፡፡

ወጣቱ ግራ በመጋባት አይቶት መንገዱን ቀጠለ፡፡

ሰውየው አሁንም ቆሞ እየታዘበ ነው፡፡ አንድ ሌላ ወጣት በልጆቹ ፊት ሲያልፍ አንድ ጠጠር ከጫማው ጋር ተጋጨና ተወርውሮ  ልጆቹ ከሰበሰቡት የሳንቲም ምጽዋት ጋር ተጨመረ፡፡ ከልጆቹ ሳንቲም ላይ ጠጠር መጣሉን አይቶ ካለፈ በኋላ፣ «ሰው ግን ምናለበት ቢተዛዘን!» አለ ለራሱ፡፡

«ምን አልክ?» አለው ያ ቁሞ የሚታዘብ ሰው፡፡

ወጣቱ በመገረም አየውና፣ «ሰው ለምን አይተዛዘንም?» አለው፡፡

«አንተ ራስህ ለምን አታዝንም?»

«ስላዘንኩ አይደል ይህንን የምናገረው»

«ተሳስተሃል፤ ማዘን መናገር አይደለም፡፡ የሚጠበቅብህን ማድረግ ነው»

«የሚጠበቅብኝንማ አደርግ ነበር፤ ግን ድሃ ነኝ፡፡ መርዳት አልችልም፡፡»

«ራስህን አታታል፡፡ ብዙ ነገር አለህ፤ ግን ማድረግ አትችልም፡፡ በእግርህ የገፋሃት ጠጠር ከልጆቹ የምጽዋት ሳንቲም ላይ አርፋለች፡፡ ጠጠሯን አላነሣህም፤ ይቅርታም አልጠየካቸውም፡፡ በጎነት ከይቅርታ ይጀምራል፡፡»

ወጣቱ ምንም ምላሽ አልሰጠም፡፡ ቀንዷን እንደ ተመታች ላም ዘወር ብሎ እንኳን ሳያይ መንገዱን ቀጠለ፡፡

እኔም መታዘቤን ቀጥያለሁ፤ ሰውየውም አንገቱን ደፍቶ መሬት ላይ በእንጨት የማይነበብ ጽሑፍ እየጻፈ የልጆቹን ጣዕመ ዜማ በዕዝነ ልቦናው እያዳመጠ ነው፡፡

አንድ ካህን በርቀት መጡ፡፡ ራሳቸው ላይ ያደረጉት ቆብ ከፊታቸው አወራረድ ጋር ተስማምቷል፡፡  ያጠለቁት ቀሚስ ግርማ ሞገስ አጎናጽፏቸዋል፡፡ በእጃቸው አርዌ ብርት ይዘዋል፡፡ ግርማ ሞገሳቸው አስፈሪ ነው፡፡ እያስፈራ የሚያስደስት ግርማ ሞገስ፡፡

በዚያ ግርማ ሞገሳቸው መሬቱን በተጠንቀቅ እየረገጡ፣ በቁመታቸው አየሩን እየቀዘፉ ደረሱ፡፡ የልጆቹን ልመና ሰሙና ቆም ብለው አዳምጠው «አይ ምእመናን፣ ምናለበት እንደነዚህ ያሉትን ሕፃናት እንኳን ይዛችሁ ብትበሉ» ብለው ሊያልፉ ሲሉ ተችዎችን የሚተቸው ሐያሲ ተናገራቸው፡፡

«ምእመናንን ከመውቀስ ይልቅ ቅድሚያ ራሳችንን እንውቀስ» አላቸው አንገቱን እንደ ደፋ፡፡

አባ የሰሙትን ማመን የከበዳቸው ይመስላሉ፡፡ ቆም ብለው በትካዜ ካዩት በኋላ «ምን መሆንህ ነው ልጄ?» አሉት፡፡

«ምእመናንን ለምን ይወቅሳሉ? ምእመናን ምን አደረጉ?»

«ሕፃናቱን ቢረዱ ብየ ነዋ»

«እርሰዎስ?»

«እኔማ ምን አለኝ? ዓለም ለምኔ ብየ የመነኮስኩ ድሃ እኮ ነኝ?»

«ተሳስተዋል፡፡ ያለዎትን ቢረዱ በቂ ነበር፡፡ ባይኖረዎት እንኳን ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው፡፡»

«እስቲ አሁን እኔ በሰውነቴ ምን ልርዳቸው?»

«ለመሆኑ ምእመናንን ከመውቀስ ይልቅ አምስት ሳንቲም እንኳን ሰጥተዋቸዋል? ሌላው ይቅር፣ እግዚአብሔር በሰጥዎ ሥልጣን የተሸከሙትን የድኅነት መስቀል አሳልመዋቸዋል?»

የአባ ሰውነት ክሽሽ ብሎ በድንጋጤ ተለወጠ፡፡ የሚይዙት የሚጨብጡት ጠፋቸው፡፡ መስቀላቸውን አውጥተው በእጃቸው ያዙት፡፡ ግን አሁንም አላሳለሟቸውም፡፡ በድንጋጤ መስቀሉ ላይ አፈጠጡ፡፡

ወጣቱ ንግግሩን ቀጠለ፡፡

«አባቴ፣ መቼም አንድን ሰው ከማንም ቀድማ ቤተ ክርስቲያን መርዳት የለባትም አንደማይሉኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የተቸገሩት መጠለያ፣ የምስኪናን ዋሻ፣ ያዘኑት መጽናኛ፣ ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡ አሁን መጠጊያነቷ ለማን እንደ ሆነ ለእርስዎ መንገር አይጠበቅብኝም፡፡

ምስኪናን ከቤተ ክርስቲያን እየራቁ መጠጊያው ጠፍቷቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሀብታሞች ስብስብ እስከምትመስል ድረስ አገልግሎታችን ሁሉ ሰው ሰው እየሸተተ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ ሲመሠርታት ለሁሉም እኩል የድኅነት መንገድ እንድትሆን ነው፡፡ ይቅርታ ያድርጉልኝና አባ፣ አንዳንድ አባቶች ከዕለት ጉርሻቸው እንኳን ቀንሰው ለድሆች እንደሚሰጡ አውቃለሁ፡፡ ብዙው ግን አያደርገውም፡፡ አሁን እርስዎ ችግረኞች በቤተ ክርስቲያኗ እንዲረዱ ሐሳብ እንኳን አቅርበው ያውቃሉ?»

አባ ምንም መልስ አልሰጡም፡፡ በአርምሞ እያዳመጡት ነው፡፡

«እግዚአብሔር በሰጠን ሥልጣን አድሎ እንደፈጸምንበት ቅድም ከተናገርኩት መረዳት ይችላሉ፡፡ ሕፃናቱን ሲያዩዋቸው መስቀሉን አላስታወሱትም ነበር፡፡ ሌላ ሰው ቢሆን ቀድመው ያወጡታል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ መረዳዳት ከዚህ ይጀምራል፡፡ መስቀሉ የናፈቃቸው አሉ፡፡ እነዚህ ሕፃናት ወላጆቻቸውን ያላወቁ፣ በመንገድ ተወልደው በመንገድ የሚኖሩ፣ ክርስትና እንኳን ያልተነሱ ይሆናሉ፡፡ የጎበኛቸው የሃይማኖት አባት መኖር ነበረበት፡፡ እንኳን እንደ እርስዎ ላለው የእግዚአብሔር ሹም ለተራ ሰው እንኳን ቢሆን ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው፡፡ ስለጨቀጨኮዎት ይቅርታ ያድርጉልኝ፡፡ አይቶ ማለፍ ስለማይሆንልኝ ነው፡፡» አላቸውና ሒዶ መስቀላቸውን ተሳለመ፡፡ አባም ወደ ልጆቹ ቀርበው ልጆቹን አሳለሟቸው፡፡

መስቀል በመሳለማቸው የተደሰቱት ሕፃናት በጣዕመ ዜማቸው መስቀል ሃይልነ መስቀል ጽንዕነ እያሉ ዘመሩ፡፡ በሃይማኖታቸው የሚንከባከባቸው ሰው እንደሌላቸው ያለማተብ ከሚታየው አንገታቸው ማወቅ ይቻላል፡፡ ያየሁትን ማመን አቃተኝ፡፡ አባ ዕንባ ተናነቃቸው፡፡ በመሐረባቸው ዐይናቸውን እያሻሹ በጸጸት መረብ ወደ ኋላ ተሳቡ፡፡

ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው ያለውን አሰብኩ፡፡ እኔም መርዳት እንደምችል ተገነዘብኩ፡፡ ግን ሰውነቴን አጣሁት፡፡ እውነት ነው፤ ገባኝ፡፡ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው፤ ግን ሰው መሆን ያስፈልጋል፡፡ ሰው ሆኜ ሰው በመሆኔ ብቻ በጎ ነገርን ላደርግ፣ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው ያለውን የብልሁን ንግግር ይዤ ሰውነቴን መፈለግ ጀመርሁ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *