“ሠናይ ውእቱ ለነ ሀልዎ ዝየ” (ማቴ.፲፯፥፬)

በዲ/ን ዐቢይ ሙሉቀን

የቃሉ ተናጋሪ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ነው። ቃሉን የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ሊገልጥላቸው ከነቢያት ሙሴንና ኤልያስን፣ ከሐዋርያት ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ወደ ተራራው ባወጣቸው ጊዜ ነው፡፡ ሙሴና ኤልያስ ከክርስቶስ ጋር ሲነጋገሩ ሰምቶ “በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፣ ብትፈቅድስ ሦስት ሰቀላዎች እንሥራ አንድ ላንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ” በማለት ተናገረ።

በዚህ ጽሑፍ ክርስቶስ ከነቢያት ሙሴንና ኤልያስን፣ ከሐዋርያት ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ ወስዶ ብርሃነ መለኮቱን ለመግለጥ የፈቀደበትን ምክንያት፣ ደብረ ታቦር የምን ምሳሌ እንደሆነ፣ በዚህ እንኑር የሚለው ቃል ምንን እንደሚያመለክት፣ እናያለን።

ሀ. ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ማሳየት ለምን አስፈለገው?

አንደኛ፡-  “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩት ድረስ እዚህ ቆመው ካሉት ሞትን የማይቀምሱ አሉ” (ማቴ.፲፮፥፳፰) ብሏቸው ነበርና ከዚያ ጋር ለማያያዝ።

ሁለተኛ፡- እሞታለሁ ብሎ ቢናገር ቅዱስ ጴጥሮስ አይሁንብህ (ማቴ.፲፮፣፳፩-፳፫) እያለ ተናግሮ ነበርና የሚላችሁን ስሙ ለማለት።

ሦስተኛ፡- በቂሣርያ ሰብስቦ “የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ባላቸው ጊዜ “ከነቢያት አንዱ ነው” (ማቴ.፲፮፣፣፲፫-፲፬) ብለውት ነበርና የነቢያት ጌታ መሆኑን እንዲረዱት ነው።

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ፣ ወልደ አምላክ መሆኑን ሙሴና ኤልያስም መስክረዋል። ሙሴ እኔ ባሕር ብከፍል፣ ጠላት ብገድል፣ መና ባወርድ፣ ደመና ብጋርድ በአንተ ዕርዳታ ነው። ነገር ግን ይህም ሆኖ እስራኤልን ማዳን አልቻልኩም፤ እስራኤልን ማዳን የምትችል አንተን የሙሴ አምላክ የሙሴ ጌታ ነህ ይበሉህ እንጂ ለምን ሙሴ ይሉሃል ብሎ መስክሯል። ኤልያስም ሰማይ ብለጉም፣ እሳት ባዘንም በአንተ ቸርነት እንጂ እኔማ እንዴት ይቻለኛል? ይህም ሆኖ እስራኤልን ከኃጢአታቸው መልሼ ማዳን አልቻልኩም። ይህን ሁሉ ማድረግ የምትችል አንተን የኤልያስ ጌታ ሊሉህ ይገባል እንጂ እንዴት ኤልያስ ነህ ይሉሃል ሲሉ ተሰምተዋል። እንዲሁም በባሕርይ አባቱ ለማስመስከር ነው። ሐዲስ ኪዳን የአምላክ መገለጥ ወይም ዘመነ አስተርእዮ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው። ግራ ሲጋቡ የነበሩ ሐዋርያትም አምላክነቱን ተረድተዋልና።

ለ. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ከነቢያት ሙሴንና ኤልያስን ከሐዋርያት ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ ወሰዳቸው?

ይህን ጉዳይ ስንመለከት ሁሉም የየራሳቸው ምክንያት አላቸው። በመጀመሪያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጣቸው ከብሉይ ኪዳንም፣ ከሐዲስ ኪዳንም፣ ከደናግልም፣ ከሕጋውያንም ነው። ሁሉም መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንደሚችሉ ሲያስረዳ ነው። ይህም በብሉይ ኪዳን ምእመናንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ምእመናን፣ እንዲሁም በድንግልና በኖሩትም ሆነ በጋብቻ ሕይወት በኖሩት ትምክህት እንዳይኖር፣ መንግሥተ ሰማያት በሃይማኖት ጸንቶ፣ መልካም ምግባር ሠርቶ የኖረ ሁሉ የሚወርሳት እንደሆነች ለማስረዳት ነው።

ሌላው ደግሞ ሙሴ በመዋዕለ ዘመኑ ክብርህን አሳየኝ ባለው ጊዜ እኔን አይቶ መቋቋም የሚቻለው የለም (ዘፀ.፴፫፥፲፯-፳፫) ብሎት ነበርና የተመኘውን ሊያሳካለት፣ እንዲሁም በባሕርይው የማይመረመር መሆኑንም ሲገልጽለት ነው። ኤልያስንም ምስክር ትሆነኛለህ ተብሎ ስለነበር። ከዚህም በመነሣት የለመኑትን የማይነሣ፣ የነገሩትን የማይረሳ አምላክ መሆኑን እንድንረዳ፣ እንዲሁም የማያደርገውን የማይናገር የተናገረውንም የማያስቀር እውነተኛ አምላክ መሆኑን እንረዳ ዘንድ መረጣቸው።

ሐዋርያት የተመረጡበትን ምክንያት ሊቃውንቱ በሁለት መንገድ ገልጸውታል። የመጀመሪያው ሦስቱም እንሾማለን ብለው ያስቡ ስለነበር እርሱ ንጉሥነቱ ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳልሆነ፣ ንግሥናው ሰማያዊ መሆኑን አስረድቶ የእነርሱንም ሹመት ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳልሆነ ሊያስረዳቸው። ሌላው ደግሞ እጅግ አብዝተው ይወዱት ስለነበር የፍቅራቸው ዋጋ እንዲሆንላቸው ነው። ሹመት ይመኙ እንደነበር ያዕቆብና ዮሐንስ እናታቸውን ልከው ያስጠየቁ ሲሆን ጴጥሮስ ደግሞ እሞታለሁ ቢለው አትሙትብኝ ብሎ መጠየቁ እርሱ ከሞተ ማን ይሾመኛል ብሎ ነው ብለው መተርጉማኑ ተርጉመውታል። ፍቅራቸውን ግን እኔ የምጠጣውን ጽዋዕ ትጠጣላችሁ ወይ ሲባሉ አዎን ማለታቸው ቢወዱት ነውና፤ ጴጥሮስም አትሙትብኝ ማለቱ ቢወደው ነውና የፍቅራቸው መገለጫ ይሆናቸው ዘንድ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠላቸው። በዚህ ምክንያት ከሌሎች ሐዋርያት ተለይተው ብርሃነ መለኮቱን እንዲያዩ ተመርጠዋል።

ሐ. ቅዱስ ጴጥሮስ የሙሴንና የኤልያስን ምስክርነት ከሰማ በኋላ ለክርስቶስ፣ ለሙሴና ለኤልያስ ቤት እንሥራ  ማለቱ ለምንድነው?

ብንታመም እየፈወስከን፣ ብንሞት እያስነሣኸን፣ ብንራብ ባርከህ እያበላኸን፣ ሙሴም የጥንት ሥራውን እየሠራ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላት እየገደለ፣ መና እያወረደ፣ ደመና እየጋረደ፣ ኤልያስም ሰማይ እየለጎመ፣ ዝናም እያዘነመ በዚህ እንኑር በማለት ተናግሯል። ቅዱስ ጴጥሮስ ለክርስቶስ፣ ለሙሴና ለኤልያስ ቤት እንሥራ ሲል ለራሱና ለሌሎች ሐዋርያት እንሥራ አላለም። ከዚህና ከሌላውም አገላለጹ የምንረዳው መሠረታዊ ነጥብ አለ። እርሱም፡-

የክርስቶስን፣ የሙሴንና የኤልያስን ተግባር መመስከር ሲሆን፤ እውነተኛ ምስክርነትን እንማራለን። በብሉይ ኪዳን ሲተገብሩት የኖሩትን፣ እንዲሁም ክርስቶስ ሁሉን የሚችል አምላክ መሆኑን አስረድቷል። ከዚህ በተጨማሪ ለራሱ አለመጠየቁ አስቀድሞ የነበረውን የዓሣ ማጥመጃ መረብና አንድ አህያ ትተህ ተከተለኝ ተብሏልና፣ እንዲሁም ብር ወይም ወርቅ አትያዙ ተብሏልና ምድራዊ ገንዘብ፣ ቤት ንብረት ማፍራት እንደሌለባቸው የተማሩትን መሠረታዊ ትምህርት ያስታውሰናል። ሌላው ደግሞ ለራስ አለማለትን ሌላውን ማስቀደም እንዳለብን ያስተምረናል።

መ. ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት የሚባለው ለምንድንነው?

በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱ እንደተገለጠባት ቤተ ክርስቲያንም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አዕማደ ምሥጢራት፣ ነገረ እግዚአብሔር ይገለጥባታል። ቅዱስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር እንኑር ማለቱ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን መኖር እንዳለብን ያስረዳናል። ደብረ ታቦር በክርስቶስ ሰብሳቢነት ነቢያትና ሐዋርያት የተገናኙበት የተቀደሰ ተራራ ነው። ቤተ ክርስቲያንም “በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋልና፤ የሕንጻው ማዕዘን ራስ ድንጋይም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (ኤፌ.፪፥፳) በማለት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጸው የብሉይ ኪዳን ምእመናንና የሐዲስ ኪዳን ምእመናን ኅብረት፣ አንድነት ናት።

በደብረ ታቦር በአጸደ ሥጋ ያሉ ሐዋርያትና በአጸደ ነፍስ ያሉት ምእመናን እንደተገናኙ ቤተ ክርስቲያንም በአጸደ ሥጋ ያሉ ምእመናን እና በአጸደ ነፍስ ያሉ ምእመናን አንድነት ናት። በደብረ ታቦት ስውራን እና ሕያዋን እንደተገናኙበት ቤተ ክርስቲያን የእነዚህ ሁሉ ኅብረት አንድነት ናት። በድንግልና የኖሩት ኤልያስና ዮሐንስ በጋብቻ ከኖሩት ሙሴና ጴጥሮስ ጋር አንድ ሆነው ብርሃነ መለኮቱን እንደተመለከቱበት ቤተ ክርስቲያንም በድንግልና ያሉትም፣ በጋብቻ ሕይወት የሚኖሩትም ምእመናን በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነው ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን የሚሳተፉባት እነዚህን ሁሉ አንድ የምታደርግ የአንድነት ቦታ ናት።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ልዩ የሆነ ምሥጢር እንድንረዳው ድክመታችንንም እንኳን ልዩ በሆነው ጥበቡ ሰውሮ ደካማ ነህ ሳይል በልዩ ጥበቡ ሊያስተምረን እንደ ሐዋርያቱ እንደ ነቢያቱ ምሥጢሩን ሊገልጽልን፣ አምላክነቱን ሊያስረዳን፣ ሹመታችን ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳልሆነ ሊያስተምረን ዕለት ዕለት ይጠራናል። ቤተ ክርስቲያን ምድራዊ ሹመት የምንለምንባት ሳትሆን ሰማያዊ ሹመት የምንለምንባት ቅድስት ቦታ ናት። በቅድስና ኑረን ሰማያዊውን ርስት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ የሚያስችል ሥራ የምንሠራባት የቅድስና ሥፍራ ናት።

እኛም ምንም እንኳን ደካማና ለቤቱ የማንመች ብንሆንም፣ በኃጢአት የረከስን፣ ምድራዊ ሹመትና ሀብት በቀላሉ የሚያታልለን ብንሆንም በጥበብ ያስተምረን ዘንድ ዕለት ዕለት ይጠራናልና ጥሪውን አክብረን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው ልንል ይገባል። ይልቁንም ሰላም በጠፋበት ዘመን፣ እርስ በእርስ መስማማት በሌለበት ዘመን፣ ወንድም ወንድሙን በሚያርድበት ዘመን፣ የተበላሸ ርእዮተ ዓለም እንደ ወጀብ እየናጠን ባለንበት ዘመን፣ የተሻለ ብቻ ሳይሆን ምርጫ የሌለው መኖሪያችንን ቤተ ክርስቲያን ልናደርግ ይገባል። ምንም እንኳን በክርስትና ሕይወት እንድንፈጽማቸው የምንታዘዛቸው ሁሉ በፈቃዳችን ልንፈጽማቸው የሚገቡ ቢሆኑም አሁን ካለው ውስብስብ ችግር አንጻር ግን ቢበርደንም፣ ቢርበንም፣ ቢጠማንም፣ ብንቸገርም፣ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ተጠልለን መኖር ግድ ይለናል። ግድ ይለናል ሲባል ግን እግዚአብሔር አምላካችን አስፈቅዶና አስወድዶ የሚገዛ አምላክ እንጂ አስገድዶ የሚገዛ አምላክ እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከክፉ የሚሰውረንን አምላክ ወደንና ፈቅደን ልንገዛለት፣ እንዲሁም ወደንና ፈቅደን ወደ ቤተ ክርስቲያን በመምጣት በቤተ ክርስቲያን ልንኖር ይገባል።

ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ የሕክምና ማእከልና የጤና ጣቢያ ናት። በሽተኛ በዝቷል ተብሎ የሕክምና ማእከላት ይስፋፋሉ እንጂ አይዘጉም። እንዲሁ እኛ ሰዎች ምንም ኃጢአተኞችና ደካሞች ብንሆንም፣ ዘመኑም የከፋ ቢሆንም፣ በሽታውም ቢበረታ የሕክምና ቦታችን ናትና የበለጠ ልናስፋፋት፣ የበለጠ ድጅ ልንጸናት እንጂ ልንሸሻት አይገባምና ሁሌም እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው ልንል ያስፈልጋል። በቤቱ ኖረን ንስሓ ገብተን ሥጋውን ደሙን ተቀብለን የስሙ ቀዳሾች የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን እግዚአብሔር አምላካችን ይፍቀድልን አሜን።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *