ማኅበረ ቅዱሳን እና ግቢ ጉባኤያት

ክፍል አንድ

ኢትዮጵያ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ጠበቃ የሆኑ ዘመን ተሻጋሪ አሻራዎችንና ታሪኮችን በማኖር ዛሬ ድረስ ወደፊትም ስማቸው ሲወሳ የሚኖር ነገሥታትና ሊቃውንት ያፈራች ሀገር ናት፡፡ ሀገርን በመገንባት ረገድም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ድርሻዋ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያበረከተችውን ሁሉ በመዘንጋት እንደ ኋላ ቀር በመቁጠር ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ጀምሮ ወታደራዊው መንግሥት “እግዚአብሔር የለም” አስተሳሰብን በማራመድ በተለይም ኦርቶዶክስ ጠል ርእዮተ ዓለም የሆነውን ማርክሳዊ እና ሌኒናዊ አስተሳሰብን አሰፈነ፡፡ ኦርቶዶክሳውያንም እምነታቸውን በግልጽ እንዳያራምዱ ክልከላን እስከ ማድረግ አደረሰው፡፡ በወጣቱ ትውልድ ላይም የሶሻሊዝም ርእዮተ ዓለም ጽንሰ ሐሳብን በማሥረጽ ከቤተ ክርስቲያን እንዲርቅና የሶሻሊዝም አቀንቃኝ እንዲሆን ከፍተኛ ቅስቀሳ አደረገ፡፡

ቢሆንም ኦርቶዶክሳውያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ኦርቶዶክሳዊነት እንደ ኋላ ቀርነት መቆጠሩ ሳይበግራቸው ያለውን ተጽእኖ በመቋቋም በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ሕንፃ ቁጥር ፭፻፭ ዶርም ፳፰ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፲፱፻፸፯ ዓ.ም በቅዱስ ገብርኤል ስም በ፭ ወንድሞች የጽዋ ማኅበር ጀመሩ፡፡ የጽዋ ማኅበሩ መጀመር ቀስ በቀስ አዲስ አበባ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች እና ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በፍጥነት ለመስፋፋት ቻለ፡፡

ወቅቱ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት መንግሥት የሰፈራ ጣቢያዎችን በማቋቋም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ወደ አካባቢዎቹ ሲያሰማራ ጋምቤላ እና መተከል የደረሳቸው ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በአንድነት በመሰባበሰብ የጸሎት እና የትምህርት መርሐ ግብራትን ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከ፲፱፻፹ ዓ.ም ጀምሮም በዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ጥቂት የቤተ ክርስቲያን ልጆች በክረምት ወቅት በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው በአቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ አማካይነት ሥልጠና የመውሰድ ዕድል ገጠማቸው፡፡

ወቅቱ ጦርነት እየተጠናከረ የመጣበት ጊዜ ስለነበር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ ወደ ተለያዩ ማሠልጠኛዎች እንዲገቡ ተደረገ፡፡ በተለይም በብላቴ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ቦታም ሳሉ ማታ ማታ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ተገናኝተው ጸሎት ማድረግ፣ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት መማራቸውን ቀጠሉ፡፡

ከመንግሥት ለውጥ በኋላም እነዚህ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በመሰባበሰብ ቤተ ክርስቲያንን በዕውቀታቸው፣ በሙያቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ባላቸው ነገር ሁሉ የሚያገለግሉ ወጣቶችን ለማፍራትና ለማሠማራት፣ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጥናትና ምርምሮቻቸውን የሚያደርጉ ወጣቶችን ለማፍራት፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው፣ ሀገሩን እና ቤተ ክርስቲያንን የሚወድ፣ ለእውነት እና ለፍትሕ የሚቆም፣ በሚሠራው ሥራ ኃላፊነቱን የሚወጣ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ እና ከሙስና የጸዳ መልካም ዜጋ ለማፍራት በዋናነት ግቢ ጉባኤያት ላይ እንዲሠራ በማሰብ ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት ፩ ቀን ፲፱፹፬ ዓ.ም በይፋ የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ በማጽደቅ ተመሠረተ፡፡

ይቆየን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *