ማኅበረ ቅዱሳን እና ግቢ ጉባኤያት

ክፍል ሁለት

ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ በይፋ ዕውቅና ተሰጥቶት በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆኖ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ መሠረት አድርጎ የአገልግሎቱን ትኩረት  በዋናነት ግቢ ጉባኤያት ላይ አደረገ፡፡ በዚህም መሠረት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን ከመደበኛው ትምህርታቸው ውጪ በየአጥቢያቸው የሚገኙ  የስብከተ ወንጌል አዳራሾችን በመጠቀም፣ አዳራሽ የሌላቸም በዛፍ ሥር እየተሰባሰቡ መምህራንን በመመደብ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከሰ/ት/ቤቶች ጋር በመቀናጀት ማስተማሩን ቀጠለ፡፡

ከ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ጀምሮም ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ፳፪ የትምህርት ዓይነቶችን በመለየት ለእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነትም መጻሕፍትን በማዘጋጀት ተማሪዎች ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸውን፣ አስተምህሮዋን እና አገልግሎቷን እንዲረዱ፣ ከተለያዩ ያልተገቡ ጠባያት ምግባራት ርቀው እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲሆኑና በመደበኛ ትምህርታቸውም ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ ከፍተኛ ጥረት ተደረገ፡፡

በየጊዜውም የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችን፣ የተማሪዎችን አቀባበል እና አፈጻጸማቸውን በመገምገም በድጋሚ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት እንዲዘጋጅ በማስፈለጉ በ፳፻፬ ዓ.ም የትምህርት ዓይነቶቹን በመከለስ ወደ ፲፩ ዝቅ እንዲሉ ተደርገዋል፡፡ መምህራንን በየማእከላቱ በመደበኛነት እና በበጎ ፈቃደኝነት እንዲያስተምሩ፤ ከዚያም አልፎ ከተማሪዎች ውስጥ የተተኪ መምህራን እና የአመራር ሥልጠና ወስደው በየግቢያቸው በመመደብ፣ አፈጻጸሙንም በመከታተል ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በዚህም ተማሪዎች ተመርቀው ሲወጡ በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ በመፍጠር የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አደራ ተቀብለው እንዲወጡ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የአንገት ማተብና መስቀል ይደረግላቸዋል፡፡

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ውጤት የሚመረቁ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችም “ለውጤታማነታችን ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ማኅበረ ቅዱሳን ነው” በማለት የተሸለሙትን  ሜዳልያ እና ዋንጫቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም የተሸለሙትን ሜዳልያ ለማኅበረ ቅዱሳን በመስጠት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሒኪም የሆኑት ፕሮፌሰር እንግዳ አበበ ይጠቀሳሉ፡፡ ወደ ሥራ ሲሠማሩም ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ መልሰው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፣ በሚሠማሩበት የሥራ መስክም በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግሉ አስችሏቸዋል፡፡ በቅድስት ቤተ ክርሰቲያን መዋቅር ውስጥ በመግባትም በሰ/ት/ቤቶች እና በሰበካ ጉባኤያት እንዲሁም በአብነት ትምህርት ገፍተው ዲቁና ተቀብለው የሚወጡትም በቤተ ክርስቲያን በውስጥ አገልግሎት እንዲሳተፉ ማድረግ ተችሏል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከተከታታይ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በተጨማሪ በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ አማካይነት “ጉባኤ ቃና” የተሰኘ ተማሪ ተኮር መረጃዎችን የያዘ መጽሔት ከ፳፻ ዓ.ም ጀምሮ በማሳተምና መልሶ ለተማሪዎች በማሠራጨት፣ በምረቃ መጽሔት፣ በድረ ገጽ፣ በፌስቡክ፣ በቴሌግራም ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው እንዲረዱ እገዛ ሲደረግላቸው ቆይቷል፡፡

በበጎ አድራጎት ተግባራትም የመንፈሳዊ ጉዞ መርሐ ግብር፣ ነዳያንን መመገብ፣ አረጋውያንን መንከባከብ፣ ለሕፃናት የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ አብያተ ክርስቲያናት እና የስብከተ ወንጌል አዳራሾችን በማነጽ፣ … ወዘተ ተግባራትን በማከናወን ረገድ ግቢ ጉባኤያት አርአያ የሚሆኑ ሥራዎችን ሠርተዋል ወደፊትም በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላሉ፡፡

ግቢ ጉባኤያትን ለማስተማርና ብቁ ዜጋ አድርጎ ለመቅረጽ የማኅበረ ቅዱሳን ድርሻ ከፍተኛውን ቦታ የሚይዝ ሲሆን እንዚህን ሥራዎች ለመሥራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በርካታ ችግሮችም በእግዚአብሔር ቸርነት ታልፈው ዛሬ ላይ መድረስ ተችሏል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህልም፡-

ውጫዊ ችግሮች ከምንላቸው ውስጥ፡- ዓለማዊነትና ሉላዊነት/Globalization/ አስተሳሰብ መስፋፋት፣ የመገናኛ ብዙኀንና ማኅበራዊ ሚዲያዎች መስፋፋት፣ የምዕራባዊ የባሕል ወረራ፣ የተማሪዎች ከኢትዮጵያዊነት እሴት ማፈንገጥ/ ውርጃ፣ ሱሰኝነት፣ ግብረ ሰዶም፣ ዝሙት፣ ሌሎችም መስፋፋት/፣ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ እና የጎሣ ፖለቲካ አስተሳሰብ መስፋፋት ይጠቀሳሉ፡፡ ውስጣዊ ችግሮችን ስንመለከት ደግሞ፡- የግብረ ገብነት መቀነስ፣ የሙስና መስፋፋት፣ ለሱስ ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች መበራከት፣ ዓለም አቀፋዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ተሳትፎ አናሳ መሆን፣ ለግቢ ጉባኤያት አገልግሎት በብዛትና በጥራት በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያገለግሉ አገልጋዮች እና መምህራን ያለመኖር እንደ ችግር የሚታዩ ናቸው፡፡

ግቢ ጉባኤያት ማኅበረ ቅዱሳን ወደፊት አገልግሎቱን በማጠናከር ተቋማዊ ለውጥን በመተግበር የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ልዩ ትኩረት ሠጥቷቸው ከሚሠራባቸው ዘርፎች አንዱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የጉባኤ ቤት ደቀ መዛሙርትን ለግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማሠልጠን፣ ኢ-መደበኛ መምህራንን በማእከላት ማፍራት፣ መደበኛ መምህራንን እና የአብነት መምህራንን መቅጠር፣ ከአንድ በላይ ተጨማሪ ቋንቋ ለሚያስተምሩ እና ለሚያሠለጥኑ መምህራን የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና መስጠትና ማሠማራት፣ ተተኪ መምህራንን በደረጃ ፫ በልዩ ሁኔታ ማሠልጠን፣ ግቢ ጉባኤያት ተኮር የአንድ ሰዓት የብሮድ ካስት መርሐ ግብር ሥርጭት መጀመር እና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡ ፡ በዚህም የወደፊት ተስፋችን በቅንነትና በታማኝነት ሀገርንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚረከቡ እንዲሁም ሊያገለግሉ የሚችሉ በሁለት ወገን ማለትም በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ዘርፍ የተሣለ ሰይፍ ሆነው የሚወጡ ወጣቶችን ማፍራት ነው፡፡

በዚህም መሠረት የግቢ ጉባኤያትን አገልግሎት ለማጠናከር “ግንቦት ልደታን ለግቢ ጉባኤያት” በሚል መሪ ቃል ከሚያዚያ ፳፰ እስከ ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ልዩ ልዩ መርሐ ግብራትን በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በተለይም በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ውስጥ የሚያጋጥመው የፋናንስ እጥረት ለመቅረፍ ከበጎ አድራጊ ምእመናን፣ ከግቢ ጉባኤያት ተመርቀው በልዩ ልዩ ሥራ ላይ የሚገኙ ወንድሞችና እኅቶች፣ ሌሎችም ተባባሪ አካላት ድጋፍ ለማሰባበሰብ እየሠራ ይገኛል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *