መንፈሳዊ ኅብረት

ዲ/ን ግርማ ተከተለው

መንፈሳዊ ኅብረት (የክርስቲያኖች የኅብረት ኑሮ) በክርስቶስ ያመኑ ምእመናን የሚኖራቸው አንድነት ማለት ነው። ይህ አንድነት በክርስቶስ ያመኑ ክርስቲያኖች በዕለት፣ ዕለት  እንቅስቃሴያቸው ሁሉ አብሮ በመሆን መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ሕይወታቸውን የሚያሳድጉበት፣ ለጽድቅ የሚያበቃቸውን በጎ ተግባራት የሚያከናውኑበት የኑሮአቸው አካል ነው።

በብሉይ ኪዳን ወንድም/ባልንጀራ በሥጋ ከአንድ አባት እና እናት የተወለደ፣ በጉርብትና የሚኖር እስራኤላዊን የሚያመለከት ሲሆን  እግዚአብሔር በሙሴ በኩል በሰጠው ፲ቱ ትእዛዛት ውስጥ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ሲል በጎረቤታሞች መካከል ንጹሕ ፍቅር እንዲኖር የተሰጠ ትእዛዝ ነው፡፡ (ዘሌ ፲፱፥፲፰)  በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሰፊ ትርጉም ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ወንድም/ባልንጀራ በክርስቶስ አንድ አካል የሆኑትን የሚያጠቃልል ነው። ለዚህም ነው መንፈሳዊ/ክርስቲያናዊ ኅብረት ማለት በክርስቶስ ያመኑ ምእመናን የሚኖራቸው አንድነት ነው የተባለው።

የክርስቲያኖች የመንፈሳዊ ኅብረት ኑሮ የተጀመረውና ጎልቶ የተንጸባረቀው በአባቶቻችን ሐዋርያት ዘመን ነው። ይህ ዘመን ፲፪ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት፣   ፸፪ቱ ቅዱሳን አርድእት፣ እንዲሁም በእነርሱ ትምህርት ተስበው በክርስቶስ ያመኑ ምእመናን ሁሉ በአንድነት ይኖሩበት የነበረ ዘመን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሁኔታ ሲገልጽ “ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ፣ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው” እንዲል፡፡ (ሐዋ. ፬፥፴፪)

በዚያ ዘመን የነበረው ኅብረት በነፍስም በሥጋም አንድ እስከ መሆን የደረሰና ሁሉም ያለውን ሀብት አንድ ላይ ከማድረጉ የተነሣ ችግራቸውን በጋራ ይወጡ የነበረበት ዘመን ነው፡፡ የመንፈሳዊ ኅብረት ኑሮ ዋና ጥቅሙም ይህ ነው፤ በሥጋም በነፍስም መረዳዳት ስለሚንጸባረቅበት።

ከዘመነ ሐዋርያት በኋላ የነበረው ኅብረት (ክርስትና) እየተስፋፋ በመምጣቱ በክርስቲያኖች ላይ የተለያዩ ፈተናዎች ይደርሱባቸው ነበር፡፡ እንደ ዘመነ ሐዋርያት ባይሆንም በመከራ ውስጥ ሆነውም መንፈሳዊ የአብሮነት ሕይወቱን አስቀጥለዋል፡፡ ይህም በየሀገራቱ አንድ ዓይነት መልክ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ገጽታዎች የሚከናወን ሲሆን በሀገራችንም በተለያዩ መንገዶች ሲሠራበት ቆይቷል።

ቀደምት አባቶቻችን ያንን ኅብረት በሰንበቴና በጽዋ ማኅበራት ለማስቀጠል ችለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።” (መዝ. ፩፻፴፫፥፩) በማለት እንደገለጸው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ እነዚህ እየተረሱና እየተተዉ በመምጣታቸው በኅብረት ከመሆን ይልቅ በተለያዩ ምክንያቶች ግላዊ ሕይወት ላይ ትኩረት ማድረግ እየተለመደ መጥቷል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍላቸው “ሌሎች ልማድ አድርገው እንደ ያዙት ማኅበራችንን አንተው፤ እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ” ባለው መሠረት በኅብረት ለመኖርና ቀጣይነት ላለው ሕይወት ትኩረት ልንሰጠው ይገባል። (ዕብ. ፲፥፳፭)

በዚህ ዘመን አንድነታችንን መጠበቅ ከመንፈሳዊ ፋይዳው በተጨማሪ ለህልውናችንም በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ከበፊቱ ይልቅ አጥብቀን ልንይዘው ይገባል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *