መንፈሳዊ ሰው እና ሳይንሳዊ ምርምር (ክፍል ሁለት)

ጥያቄ ፫፡-  ሳይንሳዊ የምርምር ዘዴ ብዙ ጊዜ መነሻው ጥርጥር ነው፡፡ ማለት በአንድ ጉዳይ ላይ፣ በአንድ ነገር ላይ እርግጠኛ የሆነ የታወቀ ነገር ስለሌለ ከዛ ጥርጥር በመነሳት ነው ያን ነገር ወደ ማጥናት፣ አዲስ ግኝት ወደማግኘት የሚኬደው፤ ለአንድ መንፈሳዊ ሰው ዶግማዊ በሆኑ ነገሮች ተምሮ የአባቶቹን ትውፊት ተቀብሎ ከሚኖር መንፈሳዊ ሰው በነገሮች ላይ ከጥርጥር መነሣት አይከብደውምን? አያስቸግረውምን?

ዲ/ን ያረጋል፡- በመጀመሪያ የሳይንሳዊ ምርምር መነሻው ጥርጥር ነው የሚለው ከፊል እውነታ ነው ልንል  እንችላለን፤ የተወሰነ እውነታ አለው፡፡ ሙሉ ገጽታውና እውነታው ግን ይኼ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ምርምር ሳይንሳዊም ብንለው የሚነሣው ከእምነት ነው፡፡ የሆነ ነገርን ተቀብሎ ነው የሚነሣው እንጂ መቶ በመቶ ሁሉን ነገር አረጋግጦ የሚራመድ ምንም ሳይንሳዊ ዕውቀት የለም፡፡ የሚነሣው ምንም ከማይጠየቁ ነገሮች ነው፡፡ እነዚህ “አግዚየምስ” ይባላሉ፤ “ፖስቹሌት”ም ይባላሉ፤ እንደ ማኅበራዊ ሳይንስ ባሉት “ቲዎሪዎች” ደግሞ “አሳምፕሽን” ይባላሉ፡፡ እነዚህ ተቀምጠው በዛ መሠረት ነው “ቲዎሪ” የሚዳብረው፡፡ ያለ ምንም “አሳምፕሽን” “ቲዎሪ” ሊኖር አይችልም፡፡ እነዛ “አሳምፕሽኖች” የተረጋገጡ አይደሉም፤ እውነት መሆናቸው አይታወቅም፡፡ ምክንያቱም ማንም እውነታን “እንዲህ ብለን እናስብ” ብሎ መውሰድ አያስፈልገውም፡፡ ፀሐይ በምሥራቅ ትወጣለች ብሎ “አስዩም” ማድረግ ማንም አያስፈልገውም፡፡ ነገር ግን ያለነዚያ “አሳምፕሽኖች” ምንም ነገር ማውራት፣ ምንም ማድረግ ስለማይቻል የሆኑ ነገሮችን እንቀበል ብሎ ይነሣና ከዚያ በኋላ ነው ወደ ቀጣይ የሚሄደው፡፡ ስለዚህ ምንም ነገር መሠረቱ እምነት ነው፡፡ በየትኛውም መንገድ ቢሆን የሆነ ነገርን ከመቀበል ነው የሚነሣው፡፡

ለምሳሌ ቀጥ ያለ መስመር (Straight line ) 1800 ነው ከሚለው ካልተነሣ፣  ቋሚ አንግል (Right Angle) 900 ነው፣ ወዘተርፈ ከሚሉ መሠረታዊ ነገሮች ካልተነሣ እንዴት ብሎ ነው ሌላ “ጂኦሜትሪ” የሚኖረው?  “‘Right Angle’ ለምን 900  ይሆናል? ለምን 950 አይሆንም?” ብዬ ብከራከር እንዴት ነው ይኼን ማስረዳት የሚቻለው? 90“የዲፍኒሽን” ጉዳይ ነው፡፡ ለምን 100 አይሆንም? “Straight line” ለምን 90 አይሆንም? ለምን 180 ይሆናል? የግድ የሆነ ነገርን ከመቀበል ነው የሚነሣው፡፡ “እንዴት ብሎ ይሄንን አለ?” ካልኩ ምንም መራድ አይቻልም፤ በቃ እዚያው ነው የሚቆመው፡፡

 

የማንኛውም ነገር መሠረቱ እምነት ነው፡፡ ገበሬም ቢሆን የሚዘራው በእምነት ነው፡፡ ቀድሞ ዐይቶ አይደለም የሚያምነው፤ አምኖ ነው ወደ ድርጊቱ የሚሄደው፡፡ በፍልስፍናውም ቢሆን እንደዚያ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው “ማቴሪያሊስት” ነኝ የሚለው “ማቴሪያሊዝምን” አረጋግጦ አይደለም፡፡ በምን መንገድ ያለው ነገር መቶ በመቶ ቁሳዊ ብቻ መሆኑ ተረጋገጠ? ግን “ማቴሪያሊስት” ነኝ ብሎ ያምንና ያን ለማረጋገጥ ይሄዳል፡፡ ብዙ ነገሮች በእምነት ነው የሚጀመሩት፡፡ ስለዚህ ሁሉ ነገር ተረጋግጦ አማን በአማን በቃ ከዚህ በላይ የሚወጣ የሚወርድ የለም ተብሎ አይደለም የሚጀምረው፡፡ አንዱ ይሄ ነው፡፡

 

ሁለተኛው ጥርጥር ስንል ተገቢ የሆነ ጥርጥር አለ፤ ተገቢ ያልሆነ ጥርጥር አለ፡፡ ጥርጥር ጥንቃቄ ወይንም እውነትን ፍለጋ ብለን ብንወስደው ይኼ አግባብነት አለው፡፡ ጥርጥርም ብንለው ተገቢ የሆነ አለ፤ ያልሆነ አለ፡፡ ተገቢ የሆነ ጥርጥር ወይም ጥንቃቄ የምንለው ከፍጡራን የተገኘውን ዕውቀት በሙሉ በጥንቃቄ ማየትን ነው፡፡ እንደወረደ መቀበል መንፈሳዊነት አይደለም፡፡ ከሰው የተገኘን ዕውቀት፣ ከፍጡራን በምርምር በሂደት የተገኘን ዕውቀት በሙሉ “ይኼ በቃ፣ አይወጣም አይወርድም፣ መቀበል አለብን” የሚባል ነገር የለም፡፡ በሰው የተገኘ ነው፤ በሂደት ይዳብራል፤ ይለወጣል፤ ወዘተርፈ… በአንፃሩ ከእግዚአብሔር የተገኘውን ዕውቀት ግን መጠራጠር አንችልም፡፡ ከእግዚአብሔር በላይ የለማ፡፡ እንግዲህ ይኼ የእምነት ጉዳይ ነው፡፡ የእምነት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ይኽንን እውነት በተለያየ መንገድ አረጋግጧል፡፡ አሁን ወደ ዝርዝር አንገባም እንጂ በሥነ ፍጥረትም እየተቆፈረ የሚወጣው እውነት ሁሉ እግዚአብሔር የተናገረውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉትን እውነቶች፣ የተነገሩትን ታሪኮች የሚጠራጠሩ ብዙዎች ሳይቀሩ ዛሬ በ“አርኪዎሎጂ” የሚገኙ ነገሮች እነዚያን እያረጋገጡ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር በላይ ማንም እውነቱን ሊናገር አይችልም፡፡ እግዚአብሔር የተናገረውን ሰው ካላመነ ይኼ ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ በሰው አስተሳሰብ፣ ምርምር፣ ሀተታ፣ ዳበሳ የሚገኙ ነገሮችን ግን ልክ ነው ወይም አይደለም ብሎ ቢጠራጠር፥ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ቀጣይ እርምጃ ቢሄድ ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ ጥርጥር ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ አለ የማይሆንበት ጊዜ አለ ማለት ነው፡፡

 

ጥያቄ ፬፡- ሳይንሳዊ ምርምር ገደብ (Scope) ሊኖረው ይገባል? መመርመር የሌለባቸው ነገሮች የሉም?  ገደብ ካስፈለገው እስከ ምን ድረስ ነው መመርመር ያለበት? ገደቡን (Scope) ማስቀመጥ ይቻላል? 

ዲ/ን ያረጋል፡- አዎ ሳይንሳዊ ምርምር ገደብ አለው፤ ሊኖረውም ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሳይንሳዊ ምርምር ወይም ሳይንስ አሁንም መስተዋል ያለበት ነገር የሆነ የሚፈልጥ፣ የሚቆርጥ፣ አዋጅ የሚያወጣ አካል አይደለም፡፡ ሰዎች “ዕውቀት የሚገኘው በዚህ መንገድ ነው” ብለው ያዘጋጁት አንድ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ የሰዎች አስተሳሰብ እስከሆነ ድረስ የሰው አስተሳሰብ፣ ዕውቀት፣ አቅም፣ መጠን ምንጊዜም ውስን ነው፡፡ ሰው በጊዜና በቦታ የተወሰነ እስከሆነ ድረስ በዚህ በአእምሮአዊ ምርምር የሚደርስበት ዕውቀትም የተወሰነ፣ የተገደበ ነው፡፡

 

“ከቦታና ጊዜ ውጪ የሆነውን ነገር ሁሉ እኔ እደርስበታለሁ፤ አለዚያ ደግሞ እኔ ካልደረስኩበት የለም” የሚል ከአቅሙ በላይ የሆነ ሕግ ማውጣት የለበትም፡፡ ገደቡ በጊዜና በቦታ የተወሰነውንና ሊታይና ሊመረመር የሚችለውን ነገር ነው ሳይንስ ማወቅ የሚችለው፡፡ ለምሳሌ ወደ ኋላ ሄዶ “ይኼ ዓለም ሲፈጠር ምን ነበር?”  የሚለውን ሳይንስ ማረጋገጥ አይችልም፤ ምክንያቱም ሳይንሳዊው መንገድ እያዩ ማረጋገጥ ነው፤ ከሆነ ዘመን በፊት ዓለም ሲፈጠር ያልነበረ ሰው ዛሬ እንዴት አድርጎ ነው ስለዛ እውነተኛ እንደሆነ ስለ “ቢግ ባንግ” ስለ ሌሎች “ቲዎሪዎች” ማውራት የሚችለው? አልነበረማ፡፡ ይኼ ራሱ ከሳይንሱ መንገድ ውጪ ነው ፡፡ በሳይንስ ስም ግን እንዲህ ያሉ ፕሮፓጋንዳዎች ይነዛሉ፡፡ እምነቶች ናቸው እንጂ እነዚህ ሳይንስ አይደሉም፡፡

 

ስለዚህ ሳይንስ ገደቡ ማየት፣ ማረጋገጥ የሚቻለውን ነገር በጊዜና በቦታ የተወሰነውን ነገር ማጥናት ነው፡፡ ከዚህ ያለፈ ሳይንስ ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ አቅሙም መጠኑም አይደለም፡፡ ለምሳሌ ተአምራትን በሳይንሳዊ መንገድ ማጥናት አይቻልም፡፡ ጌታችን በቃና ዘገሊላ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ቀይሯል፤ ለውጦታል፡፡ ታዛዦቹ ውኃውን እስኪያመጡና በጋኑ እስኪሞሉ ያውቃሉ፤ ሂደቱ ግን፣ እንዴት ተለወጠ  ለማንም አይታወቅም፡፡ ተለውጦ ብቻ ነው የታየው፡፡ ይኼን በሳይንሳዊ መንገድ ማጥናት አይቻልም፡፡ ተአምር ነው፤ የእግዚአብሔር ሥራ ነው፡፡ “እኔ ይኼ ይኼን ስላላጠናሁት ወይም አሁን አንድ ሳይንቲስት ውኃ በጋን ሞልቶ ወደ ወይን ጠጅ መቀየር ስላልቻለ ያ አልሆነም ነበር፤ ወይም ያንን መቀበለ አልችልም” ካለ ራሱ በራሱ የተሳሳተ ሕግ እያወጣ ነው፡፡ ሲጀመር “ሁሉን ነገር እኔ የደረስኩበት ብቻ መሆን አለበት” ከሚል የተሳሳተ መነሻ የሚደርስ የተሳሳተ ድምዳሜ ነው፡፡

ስለዚህ በአጠቃላይ ሳይንሳዊ የምርምር መንገድ የሚባለው ሊሠራ የሚችለው በሚጨበጥ፣ በሚዳሰስ፣ በሚታይ በዚህ መንገድ ሊሰበሰብ የሚችል መረጃን እና ሊጠና የሚችልን ነገር ብቻ ነው፡፡ ከጊዜ ከቦታ ውጪ ያሉን ነገሮች ሳይንስ ማጥናት አይችልም፡፡ አቅሙም መጠኑም አይደለም፡፡ አቅሙን አውቆ ዳርቻውን አውቆ መቀመጥ ነው ያለበት፡፡

 

ጥያቄ ፭፡- ጊዜያዊ የሆኑ እና ሊለወጡ፣ሊሻሻሉ የሚችሉ ሳይንሳዊ ግኝቶች ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር በቀጥታ የሚቃረኑ ቢሆን አንድ መንፈሳዊ ተመራማሪ ምን ማድረግ አለበት?

 

ዲ/ን ያረጋል፡- በመጀመሪያ በምርምር የሚገኝ ዕውቀት ሁሉ የማይለወጥና ዘላለማዊ እውነት አይደለም፡፡ ለጊዜው የተደረሰበት ድምዳሜ ወይም ግኝት ነው፤ ጊዜያዊ ነው፡፡ በ20ኛው መ/ክ/ዘ ወደ በኋላው ላይ ሳይንቲፊክ ሜተድን በደንብ ድክመቱን የሚያሳዩ ጠንካራ ሳይንቲስቶች ተነሥተው አልፈዋል፡፡ ካርል ፖፐር አንዱ ጠንካራ ሰው ነው፤ ቅድም ያነሳሁላችሁ ፓውል ፋየራባንድ አንዱ ሌላው ሰው ነው፡፡ እኔ በዚህ በ “ሳይንቲፊክ ሜተድ” ዙሪያ በደንብ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ለማግኘት እንደ ሃይማኖት የሚያራግቡትን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ከሌላም አቅጣጫ ያለውን ለማወቅ የእነዚህን ሰዎች ሥራዎች ማንበብ በጣም ጥሩ ነው ብዬ እመክራለሁ፡፡ ካርል ፖፐር “Scientific knowledge is provisional-ሳይንሳዊ ዕውቀት ለጊዜው የተደረሰበት ነው ” ይላል፡፡ ዛሬ የሆነ ነገር ሊደርስበት ይችላል፤ ነገ ደግሞ ሊለወጥ ይችላል፡፡

 

ለምሳሌ፡- ሉሲ የሰው ዘር፣ ቅድመ ምናምን፣ ዘራችን ናት ሲባል ሲዘመርላት ኖረ፤ አሁን ደግሞ ሉሲ ቀርታለች፡፡ ያው ለኘሮፓጋንዳ ስለሚመች ተብሎ ካልሆነ በስተቀር ሉሲ ቀርታ አሁን አርዲ ነው፡፡ ሉሲ የሰው ዘር ሳትሆን “አውስትራሎፒቲከስ” የተባለ የጦጣ ዝርያ ናት፤ ቆማ የምትሄድም፣ የሰው ዘርም አልነበረችም፡፡ አንዴ ሉሲ ይላሉ አንዴ አርዲ ይላሉ የሰው ዕውቀት እንደዚህ ነው፡፡ አንድን አባት ሁለት ሰዎች እስከ ስንት ሰዓት ነው የምንጾመው አሏቸው ይባላል፤ እስከ 6 አሉ፡፡ ከዛ ሁለቱም የኔታ ስድስት ሰዓት እኮ ሆኗል አሏቸው፡፡ አይ ሰዓቱ ያለው እናንተ እጅ ነው አሏቸው፡፡ ስለዚህ አሁን “ካርቦን ዴቲንግ” ይባል ሌላ እነዚህ ሰዎች እጅ ነው ያለው፡፡ በሆነ መንገድ እንዲህ ነው ይላሉ፡፡

 

በሳይንስ በንጹሕና በጥሩ መንገድ እንኳን የተደረሰበት ዕውቀት ነው፥ ሌላ ነገር  ከጀርባው የለም ብንል ለጊዜው ሰው የደረሰበት ዕውቀት ነው፡፡ የሰው ዕውቀት ጊዜያዊ ነው፡፡ አሁን ድሮ ያልነበሩ ዛሬ የተቀየሩ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ወይም ድሮ እንዲህ ነው ሲባሉ ኖረው በኋላ ግን እንደዛ ያልሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሥነ ፍጥረት ያልተፈጠረ ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር፡፡ አሁን ግን ሳይንሱ ሥነ ፍጥረት ወይም “cosmos” ወይም ዓለም፣ “ዩኒቨርስ” መጀመሪያ እንደነበረው ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡ ቢዘገይም አሁንም ጥሩ ነው፡፡ ድሮውንም በሃይማኖት ሥነ ፍጥረት መገኛ እንዳለው ይነገር ነበር፡፡ ስለዚህ ሰዎች ወደዚህ እውነት ስላልመጡ እኛ የሰዎችን አስተሳሰብ ይዘን አንሄድም፡፡ ምክንያቱም የሰው አስተሳሰብ ጊዜያዊና ተለዋዋጭ ነው፡፡

 

እንግዲህ የእውነት ሰው እያወቀ ከመጣ እግዚአብሔር ወደገለጠው እውነት ነው የሚመጣው፡፡ ብዙ ነገሮች በየዘመኑ እየተናፈሱ አንድ ሰሞን እንደ አይነኬ ተደርገው የተወሰዱ ተቀይረዋል፡፡ ስለዚህ ሰው የሚደርስበተ ዕውቀት የሚባለው ሁሉ ጊዜያዊ ነው፡፡ ነገ ምን እንደሚባል አናውቅም፡፡ እግዚአብሔር ለጊዜው እንጠቀምበት ዘንድ ያዘጋጀዋል፡፡ ለምሳሌ የኒውተን ሕጎች ሁሉ እንደ ዘላለማዊ እውነታ ነበር የሚወሰዱት፤ በኋላ ግን “ሪሌቲቪቲ ቲዎሪ” መጣ፡፡ ወደ ፊት ምን እንደሚመጣ አናውቅም፡፡ ስለዚህ የሰውን ዕውቀት እንደ ፍጹም እውነት ወስዶ ከዛ አንፃር የእግዚአብጠርን እውነታ ማነፃፀር ፈጽሞ ስሕተት ነው፡፡

 

ሁለተኛ እውነተኛ ዕውቀት ከሆነ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር ሊጋጭ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሥነ ፍጥረት እኮ እግዚአብሔር የገለጠው መጽሐፍ ነው፡፡ አዎ በምንም ሒሳብ እውነት ከእውነት ጋር ሊጋጭ አይችልም፡፡ ከዚህ በፊት ለማንሣት እንደሞከርኩት መጽሐፍ ቅዱስን ለመተቸት ይቸኩሉና ይፈልጉ የነበሩ ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ነገር እያነሱ ይኼ በታሪክ ያልተረጋገጠ ነው፤ ውሸት ነው፣ እንደውም ይቃረናል እያሉ ብዙ ነገሮችን አንሥተው ነበር፡፡ አሁን ብዙ “አርኪዮሎጂያዊ” ነገሮች ሲቆፈሩ ያለፍላጎታቸው የቀደሙ ሰዎች ስሕተት ነው ያሉትን፥ የተቹትን ነገር እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡ “አርኪዮሎጂ” በዚህ ረገድ በእውነት ባለ ውለታ ነው፡፡ እንደውም ብዙዎቹ መረጃውን ለማበላሸት እየሞከሩ ነው እንጂ ብዙ ነገሮችን እያረጋገጠ ነው፡፡ የሚጋጭ ነገር ካለ ያ ሰው የደረሰበት ዕውቀት፥ ወይ የተገኘው መረጃ ስሕተት ነው ማለት ነው፤ ወይ አተረጓጎሙና ትንተናው ስሕተት ነው ማለት ነው፡፡

 

ለምሳሌ ሰው የሚያገኘው አንድ አጥንት ነው፡፡ ያ አጥንት እንዲህ ነኝ አይልም፡፡ ሰው ነበርኩ አይልም፤ ጦጣ ነበርኩም አይልም፤ ምንም አይልም፡፡ እንግዲህ ግንባታውን፣ ማዋቀሩን የሚሠራው ሰው ነው፤ እንደገና ያዋቅሩታል፡፡ እንደገና ሲያዋቅሩ ከሆነ “ቲዎሪ” ተነስተው ነው፡፡ ካርል ፖፐር “All observation is selective and theory laden. There are no pure or theory free observations” ይላል፡፡ አንድ መረጃ የሚተነተንበት መንገድ በሆነ “ቲዎሪ” ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለምሳሌ “input” ወደ “output” የሚለወጠው በሆነ “ሶፍትዌር”፣ “ፕሮግራም” ወይም “ሀርድዌር”፣  ነው፡፡ ያን “ፕሮግራም” ማን ሠራው? “ፕሮግራሙ” ምንድነው?  “output”ን የሚወስነው ዳታው ብቻ ሳይሆን “ፕሮግራሙም” ነው፡፡ “ፕሮግራሙ” ሰዎች የተቀበሉት “ቲዎሪ” ነው፡፡ ስለዚህ በተበላሸ “ቲዎሪ” ከተተነተነ የተበላሸ ድምዳሜ የማይሰጥበት ምክንያት የለም፡፡ እግዚአብጤር የገለጠው እውነት በምንም መንገድ ከሚገኝ እውነት ጋር አይጋጭም፡፡

 

ሌላው ሦስተኛው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የምንለውስ የትኛውን ነው? የሚለውንም በደንብ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን እምነት የመንለው ምኑን ነው? ንጹሕ ዶክትሪኑን ነው? ምርመራውን (speculation)? በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አለ፡፡ ከዛ ደግሞ በሊቃውንት የተብራራ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አለ፡፡ ከዛ ውጪ ደግሞ ምርምራዊ ነገሮች (speculation) አሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን መለየት ያስፈለጋል፡፡ ምርምር የሰው ምርምር ስለሆነ ምንም መንፈሳዊ ምርምር እንኳን ቢሆን እንደ መገለጥ አይወሰድም፡፡ የሰዎች ምርምር ነው፤ ሰው በደረሰበት መጠን ነው የሚመራመረው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንኳን “ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ አሰብኩ” ብሏል፡፡ “አሁን ደግሞ እንደ አዋቂ አስባለሁ፡፡” ምን ጊዜም ሰው ሂደት ነው እንጂ የረጋ (static) አይደለም:: ስለዚህ ሰው በልጅነት ጊዜው ተመራምሮ፣ በተመስጦ (meditation) የደረሰበትን ነገር እንደ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትና አቋም አድርጎ መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ ተጋጨ ስንል ከየትኛው አንፃር ነው? የሚለውን ማየቱ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እግዚአብሔር የገለጠው እውነት አለ፡፡ ሰዎች ያን እውነታ ሲተረጉሙና ሲያብራሩ የገለጡትንና እግዚአብሔር የገለጠውን ማምታታት የለብንም፡፡

 

 

 

ጥያቄ ፡- በስተመጨረሻ ለግቢ ጉባአያት ተማሪዎች የሚመክሯቸው ነገር ካለ?

 

ዲ/ን ያረጋል፡- የምመክራቸው ነገር ቢኖር ራሴንም ጨምሮ ማለት ነው የምመክረው፡-

 

፩ኛ፡- ሰው እውነትን ከፈለገ ምንጊዜም ቢሆን እውነት እሩቅ አይደለም፡፡ ችግሩ ግን ሰው የተሳሳተ ነገር አስቀድሞ አእምሮው ላይ ይቀመጥና በዛ በተሳሳተ ነገር አእምሮው ይታጠብና ይዘጋል፡፡ እውነትን ላለማየት፣ ከዛ ውጪ ሌላ ነገር ላለመስማት ያንኑ እያረጋገጠ የሚሄድለትን ነገር ብቻ እየመረጠ የሚሄድ አለ፡፡ ከእውነት ጋር ተጣልተው የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እንደዚህ በሆነ መንገድ ስለሚሄዱ ነው፡፡ “ጅል መምህር አስቀድሞ አይልከፍ” እንደተባለው የሆነ ጅል ፍልስፍና ወይም አስተሳሰብ አስቀድሞ ይለክፋቸውና በዛው ተበክለው፣ የዛ ጅል አስተሳሰብ ተሸካሚ ሆነው ይኖራሉ፤ ይዘልቃሉ፡፡ ሰው ግን አእምሮውን ንጹሕ ልቡናውን ንቁ አድርጎ እውነትን ከፈለገ እግዚአብሔር ቅርብ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሆሴ. 6፡3 “እግዚአብሔርን እንፈልገው እንደ ማለዳ ብርሃን ወገግ ብሎ እናገኘዋለን፡፡” የሚለው፡፡ እግዚአብሔርን ፈልጎ ያላገኘ ማንም የለም፡፡ ነቢዩ ዳዊትም “ ለይትፈሳህ ልብ ዘየሐሶ ለእግዚአብጤር” ያለው “እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው”  እውነትን የሚፈልግ ሰው የትም ቢሆን እግዚአብሔር ይጠራዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለዚህ ምስክር ነው፡፡ አይሁዳዊ ሆኖ የክርስትና አሳዳጅ ነበር፡፡ ግን እውነትን ይፈልግ ነበር እንጂ ዝም ብሎ ፈሪሳዊነትን በጭፍን ለመደገፍ ብሎ ብቻ አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር ጠራው፡፡ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን ይፈልጋል፤ እውነትን ይፈልጋል ግን ሮማዊ ነው፤ አሕዛብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ወደ መዳን መንገድ ጠራው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ሐዋ. 17 ላይ ከአቴና ፈላስፎች ጋራ ሲነጋገር ያነሳው ይኼንን ነው፡፡ ስለዚህ ሰው እውነትን ከፈለገ እግዚአብሔር እንደ ወገግታ፣ እንደ ማለዳ ብርሃን የተዘጋጀ ሆኖ ያገኘዋል፡፡

 

፪ኛ. ሰው አቅሙን ሳያውቅ ወይም ለዛ ደረጃ ሳይደርስ ሁሉን ነገር እኔ መመዘን፣ መለካት እችላለሁ እያለ ያላቅሙ ያበዱ ሰዎችን አስተሳሰብ እያነበበ ባይጎዳ መልካም ነው፡፡ አሁን ዝም ብለው አዲስ አስተሳሰብ የሌላቸው  ጥንት ከነበሩ ከተለያዩ ፈላስፎች በግዴለሽነት እየቀያየጡ፥ ቅየጣ የሆነ አስተሳሰብን የሚያመጣ መጽሐፍ የሚጽፉ እንደ ኦሾ ዓይነት ሰዎች አሉ፡፡ ማስካድ ቀላል ነው፡፡ እግዚአብጠር የለም ማለት በጣም ቀላል ነው ሕሊናው ለሌላው ሰው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ያበዱ፣ በመጨረሻ ራሳቸውን እያጠፉ፣ መላቅጥ ጠፍቷቸው የሞቱ የተጃጃሉ ሰዎች በጅልነትና በእብደት የጻፉትን ሁሉ እንደ ቋሚ እውነት እያደረጉ ሰዎች ራሳቸውን ባይጎዱ ጥሩ ነው፡፡ ሰው መጀመሪያ ሕፃን ሆኖ የትልቅ ሰው ምግብ ካልበላሁ ካለ ያለጊዜው ጥርሱን ወይም ሰውነቱን ይጎዳል እንጂ አይጠቅመውም፡፡ ሲደርስበት ነው፡፡ ለቁሳዊው እንደዚህ ከሆነ ለመንፈሳዊ ነገር ደግሞ ይኼንን ማሰቡ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ያን ደረጃ፣ መጽሐፍ ወይም ያን አስተሳሰብ ለመረዳትም፣  ለማንበብም፣ ለመተቸትም፣ ለመመዘንም አቅም ሳይኖረው ወደዛ ዓይነት ነገር በመግባት ራሱን ለችግር አሳልፎ ባይሰጥ ጥሩ ነው፡፡

በመጨረሻ፡- በዚህ እድሜያቸው ቅዱሳት መጻሕፍትን ቢያነቡ፣ የቀደሙ የአበው ሊቃውንት ትምህርቶችን ቢያነቡ፣ በተለያየ ሳይንሳዊ በሚባለው ዕውቀትም በነገረ ሃይማኖትም በጣም ጥልቅ ምናልባት ብዙዎችን እንዲህ ያለ ነገር ያን ዘመን ነበር ወይ ብለን የሚያስደንቁ ነገሮችን ያገኛሉ፡፡ ከአባቶቻችን ትምህርቶች ጋር ብንተዋወቅ በጣም ብዙ ጥያቄዎች ይመለሳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡

እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡