መናፍቃን የሚስቱባቸውና የሚያስቱባቸው መንገዶች (የመጨረሻ ክፍል)

…በዳዊት አብርሃም…

የግል ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንዲያገኝ መጣር

ትክክለኛ የክርስቲያን ነገረ መለኮት ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ አንዳንዶች ግን የሚፈልጉትን ነገረ መለኮት በራሳቸው ፈልስፈው ሲያበቁ የግል አሳባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋፊ እንዲሆን ጥቅሶችን ማፈላለግ ይጀምራሉ፡፡ የእነርሱን ሐሳብ  የሚደግም ወይም የሚደግፍ የሚመስል ቃል ሲያገኙ ደስ ተሰኝተው ያንን ያገኙትን አንድ ጥቅስ ደጋግመው ይጠቅሳሉ፡፡ የነርሱን ሐሳብ የሚቃወም ጥቅስ ሲያጋጥማቸው ደግሞ ጥቅሱን እነርሱ ወደሚፈ ልጉት ሐሳብ  ለማምጣት ይጥራሉ፡፡ ማርቲን ሉተር አሳቡን የተቃወመበትን የያዕቆብ መልእክት ‹‹ገለባ›› ብሎ በግልጽ ከማጣጣል ውጪ ብዙ አልተቸገረም፡፡ የእርሱ ተከታዮች የሆኑት ግን እንደ መምህራቸው ቅዱስ ቃሉን ሰድቦ ማለፍ እንደማያዋጣ ገብቷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሐሳባቸውን ለመቀየርና ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘውን ነገረ መለኮት ለመቀበልም አልፈለጉም፡፡ ለዚህ አጣብቂኝ እንደ መፍትሔ የተጠቀሙት የሐዋርያው ያዕቆብን መልእክት እንዴት ቢተረጐም የነርሱን ሐሳብ ሊደግፍ እንደሚችል በማሰብ ቃሉን ወደራሳቸው ግላዊ ሐሳብ  ማምጣት ነው፡፡ ይህንንም ስልት ተጠቅመው እንደሚከተለው ደመደሙ፡፡

 … “መዳን በእምነት ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ያዕቆብ በመልእክቱ መዳን በማመን ብቻ ሳይሆን በሥራም ጭምር ነው ሲል ጽፏል፡፡ ይህ የሐዋርያው ቃል መዳን በማመን ብቻ ነው ከሚለው አስተምህሮ ጋር ባለመስማማቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንን ሲያከራክር ኖሯል፡፡ በመጨረሻ ግን ምሁራኑ ነገሩ ገብቷቸዋል፡፡ አንድ ሰው ማመኑ የሚታወቀው በሥራው ነው፡፡ መልካም ሥራ የማይሠራ ከሆነ ያመነ ቢመስልም እምነቱ ግን እውነተኛ አይደለም ማለት ነው ብለው ምሁራኑ ተርጕመውታል፡፡ …” (ይህንን ሐሳባቸውን በልዩ ልዩ መንገድ ማረጋገጥ የሚቻል ሲሆን ለአብነት ያህል ፕሮቴስታንታዊ ትምህርቶች ከሚለቀቁበት ድረ ገጽ መካከል በአንዱ በሚከተለው አድራሻ መመልከት ይቻላል፡፡ https://www.gotquestions.org/Amharic/Amharic-faith-alone.html) ይህ ጥረት እንግዲህ የተሳሳተን ግላዊ አሳባቸውን ሳይለውጡ ትክክለኛውን የሐዋርያውን ቃል ጎትተው ወደራሳቸው ለማምጣት ያደረጉት ሙከራ ነው፡፡

እውነታው ግን ያ እነርሱ የተናገሩት አይደለም፡፡ የሐዋርያው መልእክት በግልጥ እንደሚነግረን ለመዳን እምነት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ያመነ ሰው ማመኑ ጥሩ ቢሆንም መልካም ሥራን ደግሞ ጨምሮ ሊሠራ ይገባዋል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ አምነው መልካም ሥራ ስለሌላቸው ወገኖች ሲያስተምር አጋንንትን በምሳሌነት ይጠቅሳል፡፡ እንዲሁም እምነት ኖሯቸው መልካም ሥራ ግን የሌላቸው ሰዎች በብዛት ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ጀምረው በሥጋ በመጨረሳቸው የወቀሳቸው የገላትያ ሰዎች አማኞች ነበሩ፡፡ ዓለምን ወዶ ከእምነቱ የወጣው ዴማስ አስቀድሞ በትክክለኛ እምነት ውስጥ የነበረ ነው፡፡ በዮሐንስ ራእይ ጌታ መልእክት የላከላቸው የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ከማመንም አልፈው ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩ አባቶች ነበሩ፡፡ ቢሆንም መልካም ሥራ ባለመሥራታቸውና ስለ ክፉ ሥራቸው ተነቅፈው ንስሐ እንዲገቡ ተነግሯቸዋል፡፡

ይህ ሁሉ የሚያመለክተው አንድ ሰው እምነት ኖሮት መልካም ሥራ ግን ላይኖረው እንደሚችል ነው፡፡ በርግጥ መልካም ሥራ የእምነት ፍሬ ነው፡፡ ያለ እምነት የሚሠራ መልካም ሥራ ጥቅም የለውም፡፡ ነገር ግን ለመዳን ከእምነት ቀጥሎ መልካም ሥራ የግድ አስፈላጊ ነው እንጂ የእምነት መኖር ብቻውን በቂ ሆኖ የመልካም ሥራን መኖር ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም ሆነ ሌሎቹ ሐዋርያት ያስተማሩት ይህን ግልጽ እውነታ ስለሆነ ቃሉን መለወጥ ሳያስፈልግ እንዳለ ልንቀበለው ይገባናል፡፡ አለበለዚያ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያፈነገጠ ነገረ መለኮት ይኖረናል፡፡ “መዳን በእምነት ብቻ” የሚለው ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ የሆነበት ምክንያትም እንደዚህ ዓይነቱን የግል ሐሳብን ፈልስፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ለማስደገፍ በሚደረገው የተገላቢጦሽ አካሔድ ነው፡፡

በአጠቃላይ አንድን ጥቅስ አንሥተን ስንናገር ያን ማድረጋችን ለጥቅማችን እንኳ ቢሆን በዚያ በአንዱ ጥቅስ ላይ ብቻ ልንመሠረት አይገባንም፡፡ ለምሳሌ “ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።” (1ኛዮሐ.2፡29) ከሚለው ተነሥተን በዚህ ጥቅስ ውስጥ ጽድቅን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጧልና ለመዳን ጽድቅ ማድረግ በቂ ስለሆነ እምነት፣ ጥምቀትና ሌሎች ምስጢራት አያስፈልጉም ወደሚል ጽንፈኛ አቋም ልንወድቅ አይገባም፡፡

ሐዋርያው በሌላ ቦታ ደግሞ ፍቅር ከሞት ወደ ሕይወት የሚመልሰን መሆኑን ያስተምራል፡፡ “እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል።” (1ዮሐ.3:14) በዚህ ጥቅስ ላይ ተመሥርተን ደግሞ ለመዳን ወንድሞችን መውደድ በቂ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ብንደርስ አሁንም ልክ አይደለንም፡፡ ሐዋርያው ስለፍቅር ታላቅነት ደጋግሞ ሲያስተምር “እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል” ብሏል፡፡ (1ዮሐ.4፡16)

ስለፍቅር ለማስተማር ብለን እንኳን ቢሆን በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ልንመሠረትና ሌላውን ችላ ልንል አይገባንም፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለፍቅር ሲያስተምር ፍቅር ከእምነት እንደሚበልጥ ገልጧል፡፡ “ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።” (1ኛቆሮ.13፡2) “እንዲህም ከሆነ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” (1ኛቆሮ.13፡13) ስለዚህ መዳን በእምነት ብቻ የሚል ሰው እነዚህን ጥቅሶች ምን ሊያደርጋቸው ይችላል? በአንጻሩም በአንድ ጥቅስ ተወስኖ መደምደም የለመደ ሰው የፍቅርን ታላቅነት የሚያወሳውን ጥቅስ በመምዘዝ ‹መዳን በፍቅር ብቻ ነው› ብሎ ሊሳሳት እኮ ነው፡፡

በተመሳሳይም ጌታችን ለወጣቱ ባለጸጋ “ወደ ሕይወት ልትገባ ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” (ማቴ19:17) ባለው ላይ ብቻ ተመሥርተን ለመዳን መንገዱ ይህ ብቻ ነው ብለን ብንደመድም ስሕተት ላይ እንወድቃለን፡፡ ያለ እምነት የሆነ መልካም ሥራ ብቻውን እንደማያድን ካወቅንና የወንጌልን ቃል በዚህ ብቻ ተመሥርተን ለመዳን ሕግጋትን መጠበቅ ይበቃል የማንል ከሆንን እንዲሁም ስለእምነትና በጸጋው ስለመዳን የሚናገሩ ጥቅሶችንም ስናነብ በእነርሱ ብቻ ሳንወሰን አጠቃላዩን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለመረዳት በትዕግሥት ማጥናት ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡ ከዚህም ጋር የሐዋርያውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ “እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።” (2ኛቆሮ.3:6)

የመዳንን ነገር ለመረዳት በንባቡ ብቻ ሳንወሰን የንባቡን ትክክለኛ መንፈስ ማለትምም ትርጓሜ በመያዝ፣ በአንድ ጥቅስ ላይ ብቻ ሳንወሰን ወይም ጉዳዩን ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳንመለከት በስፋትና በጥልቀት የሆነውን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት በማወቅ መጽናት፣ ለሚጠይቁንም ምላሽ መስጠት ያስፈልገናል፡፡ በአንድ ጥቅስ ላይ ተመሥርቶ ነገረ ድኅነትን ለማወቅ መሞከር ምን ያህል አደገኛ መሆኑን አንድ ምሳሌ እንመልከት፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” (ሮሜ.10፡13) ይላል፡፡ ይህን ጥቅስ መሠረት አድርገን የጌታን ስም ስለጠራን ብቻ እንድናለን ብለን ብናስብ ከሚከተለው ጥቅስ ጋር እንጋጫለን፡፡ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” (ማቴ7፡21)

እነዚህ ከብዙ የስሕተት መንሥኤዎች መካከል ተመርጠው የቀረቡ ብዙ መናፍቃን ላይ ተደጋግመው የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ ያልተጠቀሱ ሌሎች ምክንያቶችም ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ዘዴዎች መከተል ወደስሕተት ማድረሱ አይቀሬ ስለሆነ ከነዚህ የተለመዱ የስሕተት አካሔዶች ታርሞ በትክክለኛው መንገድ እውነታውን ለማወቅና በእውነታው ለመጽናት መጣር ያስፈልጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *