ሆሳዕና በአርያም

ሆሳዕና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕዝቡ በተለይም አእሩግና ሕፃናት “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሳዕና በአርያም” በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡

ሆሳዕና የሚለው ቃል በዕብራይስጥ “ሆሼዕናህ” የሚል ትርጉም ሲኖረው “እባክህ አሁን   አድን” ማለት ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ “ኦ እግዚኦ አድኅንሶ፤ ኦ እግዚኦ ሠርሕሶ፤ ብሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው” እያለም ዘምሯል፡፡ (መዝ.፩፻፲፯፥፳፭-፳፮)፡፡  ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን መነሻ በማድረግ ሆሳዕና የሚለውን ስያሜ ለዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት ሰጥታ ታከብረዋለች፡፡ ስያሜውንም ያገኘው በዕለቱ ከሚዘመረው መዝሙር ነው፡፡

ዕለቱን በተመለከተ የተለያዩ ምሳሌዎች ይመሰላሉ፡-

የጸበርት እሑድ /Palm Sunday/፡-

ይህ ዕለት የጸበርት እሑድ ይባላል፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫም ነው፡፡ እናታችን ሣራ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ በእርግና ዘመኗ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የጎበኛትን አምላክ ለማመስገንና የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ጠይቀዋታል፡፡

የዮዲት አሦራውያንን ድል ማድረግ፡-

የአሦር ንጉስ ናቡከደነፆር እስራኤልን ለመውረር፣ ሀገሪቱንም ለማጥፋትና ለመበርበር ተነሣ፤ የጦር ቢትወደዱን ሆሎፎርኒስን ልኮ ያጠፋቸው ዘንድ ወሰነ፡፡ ሆሎፎርኒስም የጌታውን ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ሀገሪቷንም ይበዘብዛት ዘንድ ሠራዊቱን አስከትሎ በእስራኤል ላይ ዘመተ፡፡

ዮዲትም ወሬውን በሰማች ጊዜ በራሷ ላይ አመድ ነስንሳ፣ ማቅ ለብሳ ጸለየች፡፡ ጸሎቷንም በጨረሰች ጊዜ የመበለትነትዋን ልብስ ለበሰች፤ ጌጣ ጌጦችዋንም አጥልቃ ወደ ሆሎፎርኒስ ቀረበች፡፡ በደም ግባቷም ተማረከ፣ ግብዣም አደረገላት፡፡ ከመጠን በላይ ጠጥቷልና ራሱን በሳተ ጊዜ በራሱ ሰይፍ አንገቱን ቆረጠች፤ በግንብ ጫፍ ላይ እንዲሰቅሉትም አደረገች፤ አሦራውያንም በሽንፈት ተመለሱ፡፡

የእስራኤል ሴቶችም ዝናዋን ሰምተዋልና “ያይዋትና ይመርቋትም ዘንድ ወደ እርሷ ሮጠው ተሰበሰቡ፤ ታላቅ በዓልንም አደረጉላት፤ ዘንባበውንም በእጇ ያዘች፤ ከእርሷ ጋር ላሉት ሴቶች ሰጠች፡፡ በሕዝቡም ፊት ሴቶችን ሁሉ እየመራች በዝማሬ ሄደች፤ የእስራኤልም አርበኞች ሁሉ የጦር መሣሪያቸውን ከዘንባባ ጋር ይዘው እየዘመሩ ተከተሏት” እንዲል፡፡ (ዮዲ. ፲፭፥፲፩-፲፬)፡፡

በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ሆኖ ሕፃናትና አእሩግ “ለዳዊት ልጅ መድኀኒት መባል ይገባዋል” (የማቴ. ወንጌል አንድምታ) እያሉ ዘንባባ ይዘው ሲዘምሩ ኦሪትንና ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ግን “መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” ብለውታል፡፡ ጌታችንም መልሶ “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” ሲል መልሶላቸዋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡ “እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡” እንዲል (ዘካ.፱፡፱)፡፡

ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲሆንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም እውነተኛ የኅሊና ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲል በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ተጉዟል፡፡ (ማቴ.፳፩፥፬፤ ማር.፲፩፥፩-፲፤ሉቃ.፲፱፡፳፷-፵፤ ዮሐ.፲፪፤፲፭)፡፡

፩. አህያዋና ውርንጫዋ፡- 

በዚህ ዓለም አህያ ለሸክም የሚያገለግል፣ የተናቀ፣ ነገር ግን ትሑት የሆነ እንስሳ ነው። ከዚህ በተጨማሪም አህያ እንደ በቅሎ ሰጋር እንደ ፈረስ ፈጣን አይደለም። በአህያ የተቀመጠ ሰውም አሳድዶ አይዝም፤ ጋልቦ ሮጦም አያመልጥም። ተሸክሞ እንኳን በዱላ እየተደበደበ አህያ ጌታውን በቅንነት ያገለግላል። ጌታችን በዚህች ትኁት በሆነችው አህያ መገለጡ በትኁታን ለማደሩ ምሳሌ ነው።

ጌታችን የተቀመጠባቸው አህዮች አንደኛዪቱ ጭነት የለመደች ውርንጫይቱ ደግሞ ገና ያልለመደች ናት። አህያይቱ የኦሪት ምሳሌ ስትሆን ቀንበር መሸከም መቻሏ ሕገ ኦሪትን መጠበቅ የለመዱ የእስራኤል ዘሥጋ፣ ውርንጫዪቱ ደግሞ ቀንበር መሸከም የማትችል ስትሆን የአሕዛብ ምሳሌ ናት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በሁለቱም ተቀምጦባቸዋል። አህያይቱ ቀንበር መሸክም የለመደች እንደሆነች ሁሉ ኦሪትም ሕግ ናትና፤ ውርንጫይቱ ቀንበር መሸክም ያልለመደች እንደሆነች ወንጌልም ያልተለመደች ሕግ ናትና፡፡ (ወንጌል አንድምታ)፡፡

ልብስ:- 

ደቀ መዛሙርቱ አህያዪቱን ከነውርንጫዋ ከታሰረችበት ቦታ ፈትተው እንዳመጡለት በዚያ የነበሩት ሰዎች ልብሳቸውን በአህያዪቱና በውርንጫዪቱ ጀርባ ጎዘጎዙ፤ አህያዪቱ ተራምዳ በምትሄድበት መንገድ ሁሉ ልብሳቸውን አነጠፉ። ይኽም ምሳሌ ነው። ልብስ የውስጥ ገመናን ሸፋኝ ነው። አንተ ገመናችንን ከታች ነህ ሲሉ ልብሳቸውን ጎዘጎዙለት። በሌላ በኩልም ልብስ ክብር ነው፤ ያንን የሚያስከብረውን ልብስ አነጠፉለት። ክብራችን አንተ ነህ ሲሉ ክብራቸውን ዝቅ አደረጉለት። እግዚአብሔር በረድኤት ሲያድርብን ይንቁን ያንገላቱን የነበሩት ሁሉ ያክብሩናል። ቅዱሳን በዚህ ዓለም ሲኖሩ ብዙ መከራ ተፈራርቆባቸዋል። ዓለም ትቢያና ጉድፍ አድርጓቸዋል። ይኹን እንጂ በሃይማኖታቸው ጽናት በምግባራቸው ቅናት እግዚአብሔር አድሮባቸው ሁሉ ያከብራቸዋል። አስጨናቂዎቻቸውን ሳይቀር ይገዙላቸዋል።

ጌታችን በቤተ መቅደስ፡-

 ሕዝቡም በብዙ ምስጋናና እልልታ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ እያነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፎች ጫፍ ጫፉን እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡ ይልቁንም ሽንገላ ከሌለበት ከሕፃናት አፍ የሚፈልቀው ምስጋና እየቀረበለት በልዩ ግርማ ጌታችን በኢየሩሳሌም አደባባይ አቋርጦ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር በሥጋ ተገልጦ እየተመላለሰ ባገለገለባቸው ዓመታት ውስጥ ከተቆጣባቸው ጥቂት ጊዜያት አንዱ በሆሳዕና ዕለት ወደ ቤተ መቅደሱ ሲገባ ነው። የጸሎት ቤት የሆነችውን የእግዚአብሔር ቤት አይሁድ የገበያ ቦታ የቅሚያና የዝርፊያ አደባባይ አደረጓት። በዚህም ትሑቱ ጌታ ተቆጣ። በዚያ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን አስወጣቸው። ወንበራቸውን ገለበጠው። ቤቱን ቀደሰው። “ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል” እንዲል ቅዱስ ዳዊት። አነፃው፤ ለየው፤ አከበረው፤ ወደ ቀድሞ ክብሩ መለሰው። ይኽን ቤት ነገረ ምፅአቱን ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማረበት ወቅት ትቶት ሄዶ ነበር። “ጌታችን ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ” እንዲል ቅዱስ ማቴዎስ። የሆሳዕና ዕለት ግን ለሐዲስ ኪዳን አገልግሎት እንዲሆን ነጋዴዎቹን አጭበርባሪዎቹን አውጥቶ አጽድቶ ሰጠን። በዚያም በተቀደሰው ቤተ መቅደስ “በቤተ መቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡ፤ አዳናቸውም” ተብሎ እንደ ተጻፈው። ማቴ ፳፩፣ ፲፬።

የሊቃነ ካህናትና የጸሐፍት መቆጣት፡-

የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ክቡር በሆነ ምስጋና መመስገን፣ የቤተ መቅደሱ በክርስቶስ መጽዳትና ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ ሊቃነ ካህናትንና ጸሐፍቱን አላስደሰታቸውም። በክፋትና በተንኮል ካባ እንደተጀቦኑ ጻድቃን መስለው ለዘመናት ትሑትና የዋህ የሆነውን ሕዝበ እግዚአብሔር ሲያታልሉ የነበሩት እነዚህ አካላት በጽድቁ ክፋታቸውን የሚገልጥባቸው የክርስቶስ በክብር መገለጥ እንዲሁም መመስገን አስቆጣቸው። የእርሱ መገለጥና መመስገን እነርሱን የሚያሳንስ ክፋታቸውን የሚገልጥ መሆኑን ተረዱት። ጌታችን በወንጌል “ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም (ዮሐ. ፫፣፳)” እንዳለው ሆነባቸው።

ትቶአቸው ሄደ፡-

የታሰሩትን ፈትቶ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ፣ ቤተ መቅደሱንም ባርኮ ፈውስ በረከት አሳድሮበት፣ ተመስግኖበት ለዘላለምም የሚመሰገንበት መሆኑን ለተቃወሙት አስረድቶ ሲያበቃ “ትቶአቸው ከከተማው ወደ ቢታንያ ሄደ። በዚያም አደረ፡፡” ክህነታቸውም አለፈች። ያላቸውን ክብር፣ ሀብት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቅንና ትሑት ልቡና ለነበራቸው ለሐዋርያት ተሰጠች።

በአጠቃላይ በዓለ ሆሳዕና በዚህን ቀን አህዮቹ ከጌታችን የተላኩላቸውን ፈቺዎቻቸውን (ደቀ መዛሙርቱን) አላስቸገሯቸውም። እንደ ልቧ መቦረቅ የምትወድ ውርንጫ እንኳን አደብ ገዝታ ፈቺዎቿን ተከትላ ሄደች። እኛስ? ከታሰርንበት የክፋትና የኃጢአት ሁሉ ማሰርያ መች ይሆን የምንፈታው?  እንግዲህ እንደዚያን ዕለት ሰዎች ልብሳችንን ሳይሆን ልባችንን፣ የዛፍ ቅርንጫፍ ሳይሆን ራሳችንን በጌታችንና የእርሱ እውነተኛ አገልጋዮች በሆኑ በቅዱሳኑ ፊት ዝቅ እናድርግ። ለዚህም የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን። አሜን።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *