ሆሣዕና
ሆሣዕና የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ሆሼዕናህ የሚል ሲሆን ትርጉሙም እባክህ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል በዘመነ ብሉይ በቀደምት ነቢያት ዘንድ የተለመደ ቃል ነው። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ኦ እግዚኦ አድኅንሶ፤ ኦ እግዚኦ ሠርሕሶ፤ ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር [አቤቱ እባክህ አድነን፤ አቤቱ ጎዳናችንን(መንገዳችንን) አቅና፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው]” እንዳለ። መዝ. ፻፲፯፥፳፭-፳፮። ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም ሰንበታት አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራውና ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ እና ከጌታችን ዘጠኙ በዓላት ውስጥ አንዱ ነው። የሆሣዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሣዕና በአርያም በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው። በዓሉም ሆሣዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው መዝሙር ነው። በአራቱም ወንጌላውያን በቅዱስ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሐንስ ይህንኑ የፍጹም ትሕትና እና የፍቅር ጉዞ አስመልክቶ የተጻፉ የወንጌል ክፍሎች (ማቴ ፳፩፥፩~፲፯ ፣ ማር ፲፩፥፩~፲ ፣ ሉቃ ፲፱፥፳፰~፵፬፣ ዮሐ ፲፪፥፱~፲፱) በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዑደት እየተደረገ በአራቱም አቅጣጫዎች ይነበባሉ።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ባደረገው ጉዞ ቢታንያና ቤተ ፋጌ አካባቢ ሲደርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ አላቸው “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ ማንም አንዳች ቢላችሁ ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዱአችኋል” (ማቴ ፳፩፥፪~፫)። ቤተ ፋጌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጌትነቱን ሥራ ከሠራባቸው መካነ ምሥጢራት አንዷ ናት። ይቺን ቦታ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቢታንያ ናት ይላል። በእኛ ሊቃውንት ትርጓሜ ቤተ ፋጌ ማለት የተመሳቀለ ጎዳና ማለት ነው። ለዚያም ነው የተመሳቀለ ሕይወት ለነበራት ቤተ አይሁድ ወልድ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ መጥቶ የእግዚአብሔር ማደርያ ትሆን ዘንድ ሰውነቷን እንድታስተካክል ማስተማሩን ይገልጻል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ ማለት የማያስፈልግ መሆኑን ሲገልጽ ደቀ መዛሙርቱን በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ ብሏቸዋል። አንድም ሐዋርያት ተመልሰው ወደ ቀደመ ግብራቸው (ዓሣ ማጥመድ፣ ቀረጥ መሰብሰብ፣ ሸክላ ሥራ…) እንዳይመለሱ ለማስተማር ወደፊት ሂዱ ብሏቸዋል። ጌታ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ ካለ በኋላ መንደሯን አለመጥቀሱ ለምን ነው ቢባል መፈታት የነበረባቸው ስመ ገናና የነበሩ ሀገራት ብቻ አልነበሩምና ነው። አንድም ሐዋርያቱ በስም ወደ ማያውቁት ሀገር ሂደው ማስተማር እንዳለባቸው ለመግለጽ ነው። ወደማያውቋት መንደር ከሄዱ በኋላ የታሰረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር እንደሚያገኙ ነገራቸው። አህያዋ የታሰረች መሆኗ ዓለም ኃጢአት በተባለ ገመድ የታሰረ መሆኑን ለመግለጽ ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን፥ ለታሰሩትም መፈታትን፣ ለዕውራንም ማየትን እናገር ዘንድ ልኮኛል” እንዳለ ኢሳ ፷፩፥፩። አህያ ተፈታ ማለት ሰው ተፈታ ነውን? የሚል ጥያቄ ቢነሣ መረሳት የሌለበት ነገር አህያ እና ሰው በደመ ነፍስ አንድ ናቸው። ዋናው ነገር ግን እግዚአብሔር ሰውን ሲያስተምር በምሳሌ ስለሆነ ነው። ምሳሌው ለጊዜው ለቤተ አይሁድ የተነገረ ሲሆን ቤተ አይሁድ በዘመኑ እንስሳዊ ግብር ስለነበረባት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎ ሲያስተምር “የዮሴፍ ልጅ ነህ እንጂ ለእግዚአብሔር ልጅ ለሰማይ ደጅ የለውም” እያሉ ሲቃወሙ ነበር። በዚህ ሥራቸው ከአህያ አንሰው ተገኝተው ነበር። በአህያዋ የተመሰሉ አይሁድ ናቸው ። ይኸውም ክርስቶስ በተገለጠበት ዘመን እግዚአብሔርን የማወቅ ሕጸጽ ነበረባቸውና ነው። “ሰማይ ስማ፤ ምድርም አድምጪ፤ ልጆችን ወለድሁ፤ አሳደግሁም፤ እነርሱም ዐመፁብኝ። በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጥ ዐወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቁኝም፤ ሕዝቤም አላስተዋሉኝም።” ኢሳ ፩፥፪~፬።
ከዚህም በኋላ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ፈትታችሁ አምጡልኝ ማንም አንዳች ቢላችሁ ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዱአችኋል አላቸው። እነርሱም ለምን እና እንዴት ሳይሉ ያለ አንዳች ጥያቄ በፊታቸው ወዳለው መንደር ተጉዘዋል። እርሱ ቀድሞ የነበረውን፣ አሁንም ያለውን፣ ወደፊትም የሚኖረውን የሚያውቅ አምላክ መሆኑን ተረድተዋልና። የታዘዙት ደቀመዛሙርት ጌታ እንደነገራቸው በመንደሩ የታሰረች አህያ ከነውርንጫዋ አግኝተው እንደታዘዙት ማሰሪያዋን ሲፈቱ ባለንበረቶቹ ወጥተው ለምንድን ነው? ብለዋቸዋል። “እነርሱም እንደታዘዙት ለጌታ ያስፈልጉታል አሉ”። እውነት ነው እርሱ እግዚአብሔር ነውና የፈለገውን ለመከልከል የሚቻለው ማንም የለም። ባለቤቶቹ ያለማጉረምረም ለጌታ የሚያስፈልገውን ሰጡ። ደቀ መዛሙርቱ ከእስር የፈቷቸውን አህያና ውርንጫ ወደ ጌታ አመጡ እርሱም በአህያ ጀርባ ተቀመጠ። ሐዋርያት የታዘዙትን ትእዛዝ ፈጽመዋል፤ ክርስቶስ ያዘዘውን መሥራት በረከት ያስገኛል፤ እንደ ትእዛዙ አለመኖር ደቀ መዛሙርት አለመሆን ነው። ጌታ ራሱ “የምትወዱኝ ብትሆኑ ትእዛዜን ጠብቁ፤ እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ፥ በፍቅሩም እንደምኖር እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” እንዳለ። ዮሐ ፲፭፥፲
የጌቶች ጌታ የነገሥታት ንጉሥ የሆነ አምላካችን፥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ራሱን ዝቅ አድርጎ በቤተልሔም በከብቶች በረት እንደተገኘ ሁሉ በሆሣዕና ዕለት በአህያ ጀርባ ተቀመጠ። ይህ በአጋጣሚ የተደረገ ሳይሆን ቀደም ብሎ በብሉይ ኪዳን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በነቢዩ ዘካርያስ ትንቢት የተናገረለት አምላካዊ ምሥጢር ነው። “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” (ዘካ ፱፥፱)። እንኳን ፈሪሳውያኑና ሕዝቡ፥ አብረውት የነበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት እንኳን ይህ ስለ እርሱ እንደተነገረ የተረዱት እርሱ በመስቀል ላይ ከከበረ በኋላ ነው። “ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ነገር ግን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያን ጊዜ ይህ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይህንም እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው” እንዲል (ዮሐ ፲፪፥፲፮)። በትርጓሜ ወንጌል እንደተገለጸው አህያዋና ውርንጫይቱ ምሳሌነትም አላቸው:- ቀድሞ አባቶች ነቢያት ዘመነ ጸብ የሆነ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠው፣ ዘገር ነጥቀው ይታያሉ። ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉ። አምላካችንም እንደ ከበሩ ነገሥታት ሥርዓት በተንቆጠቆጠ ሰረገላና በፈረስ ሳይሆን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ መንግሥቱ የሰላምና የፍጹም ትሕትና መሆኗንና ሁሉም ሰው ተገዶ እና ፈርቶ ሳይሆን በፈቃዱ የሚገባባት መሆኗንም ለማሳየት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ የኅሊና ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲለን በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ሕይወታችን ተጉዟል።
በሉቃ.፪፥፲፫ ላይ እንደተገለጸ መላእክት በዕለተ ልደቱ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል በምድር ሰላም ለሰው ሁሉ ይሁን እያሉ የዘመሩለት የሰላም ባለቤት ነው፡፡ በዮሐ.፲፬፥፳፯ ላይ እንደተገለጸው በመዋዕለ ሥጋዌ ትምህርቱም ሰላሜን እሰጣችኋለሁ ብሎ እንዳስተማረ ያን ሰላም የሚሰጥበትን ዕለት መቅረቡን ለማመልከት ነው በአህያ ላይ ተቀመጠ። አንድም:- ውርንጫይቱ ቀድሞ ምንም ጭነት የማያውቃቸው ሕግን ያልተቀበሉ በሕግ ያልኖሩ አሕዛብ ምሳሌ ስትሆን፣ ጭነት የለመደች አህያይቱ ደግሞ ሕግና ሥርዓት ተሠርቶላቸው የነበሩ የእስራአል ዘሥጋ ምሳሌ ናት። ውርንጫይቱ ገና ግልገል በመሆኗ መጫን አለመደችም፤ አሕዛብም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ምንም ሕግ ያልተሠራላቸው፤ በአምልኮ ጣዖት፣ በገቢረ ኃጢአት የኖሩ ለመሆኑ ምሳሌ ነው። ውርንጫዋ ጌታችን ለመሸከም እንደተመረጠች ከአሕዛብ ወገን የነበሩ ለክህነት እንደተመረጡ ለማጠየቅ አንድም በሲዖል የነበሩ ወደ ገነት በገሃነመ እሳት የነበሩ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመሸጋገራቸው ምሳሌ ነው።አንድም ውርንጫዋ የእመቤታችን ምሳሌ ናት። ውርንጫዋ የዓለም ሸክም አቅልላለችና በእመቤታችን ትመሰለላለች። እመቤታችን ምክንያተ ድኅነት ጌታን የተሸከመች ንጽሕት እንከን የሌላት እናት ናትና።
በአጠቃላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላከ ሕዝብ ወአሕዛብ ሆኖ በምድር ለክህነት በሰማይ ለገነት እንደመረጠን ለማጠየቅ ነው። የፍጥረቱ ሁሉ ጌታ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ እስትንፋሷን የገበረችለትን አህያ አሁን በፈቃዱ ስለ ሰው ሁሉ ሊሞት ሲል ንጉሥነቱን ሊመሰክርባት ወደደ። ኪሩቤል ዙፋኑን የሚሸከሙለት እርሱ ራሱን ዝቅ አድርጎ በተናቀች እንሰሳ ላይ መቀመጡ ዕጹብ ድንቅ ነው። በሌላ በኩልም በአህያ ጀርባ መቀመጡ ኅቡዕ ምሥጢር አለው። በአህያ ጀርባ የተቀመጠ ሰው ሌላውን አሳድዶ አይዝም፣ እርሱም ሮጦ አያመልጥም። በዚህም ጌታችን በእምነት ለሚፈልጉት የሚገኝ ቅርብ ሲሆን በእምነት ለማይፈልጉት ግን የማይገኝ መሆኑን አስተምሯል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ፀሐይ ዕድሜያችን ሳትጠልቅ በእምነት እንፈልገው። የተናቀችው አህያ ጌታ ሲቀመጥባት ሁሉም አክብሮ ልብስ አነጠፈላት። ይህም ጌታ ሲያድርብን የሚንቁን እንደሚያከብሩን ማሳያ ነው። የአህያን ጀርባ ያልናቀ ጌታችን ትሑት ሰብእና እና የተሰበረ ልቡና ወዳለው ሰው ዘወትር ይጓዛል፤ የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ አይንቅም። ኢሳ. ፷፮፥፪፤ መዝ.፶፥፲፯።
በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሐት፣ ጸሎተ አስተስርዮ ስለማይፈጸም ጸሎተ ፍትሐትና አስተስርዮ የሚደረገው በዚሁ በሆሣዕና ዕለት ነው።
በሆሣዕና ዕለት በእጃችን እደ ቀለበት ማሰራችን የምን ምሳሌ ነው?
- ጌታ ለአዳም የሰጠውን ቃል ኪዳን ለማስታወስ፡-ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁ ያለውን የተስፋ ቃል ለማስታወስ፡፡
- ጌታ ለእመቤታችን የገባላት ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው
- ጌታ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው
- ጌታ አዳምን ከሰይጣን ግዛት ነጻ እንዳወጣው ሁሉ እኛም ከሰይጣን ግዛት ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ከክፋት ከኃጢአት አውጣን ማረን ለንስሓ ሞት አብቃን ከቤትህ አትለየን እንደ ቸርነትህ ይቅር በለን ስንል ለጌታ ዳግም ላናጠፋ ቃል የምንገባበት ነው፡፡
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ዘንባባ የመነጠፉ ምሥጢር የምን ምሳሌ ነው?
- ዘንባባ
➥ አብርሃም ይሐስቅ በተወለደ ጊዜ ደስ ብሎት ዘንባባ ይዞ እግዚአብሔርን አመስግነዋል።
➥ደርቆ እንደገና ሕይወት ይዘራል፡- የደረቀ የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
➥የሰላም ምልክት ነው፡- የሰላም አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
➥ የደስታ መግለጫ ነው፡- አንተ ደስ የምታሰኝ ኃዘናችንንም የምታርቅልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
➥ እሾሃማ ነው፡- አንተ ሕያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
➥ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል እንጂ። ጌታም አንተ ባሕርይህ የማይመረመር ነው ሲሉ ነው።
ሕዝቡ ጌታችንን ልብሳቸውን እያነጠፉ ተቀብለውታል። ልብሳቸውን ማንጠፋቸው ለክብሩ መግለጫ ነው። ልብስ አይቆረቁርም ጌታ የማትቆረቁር ሕግ ሠራሁላችሁ ሲል ነው። ሌሎችም ሦስት አይነት ቅጠሎች ማለትም የዘንባባ ዛፍ፣ የቴምር ዛፍ እና የወይራ ዛፍ አንጥፈውለታል። የዘንባባ ዛፍ እሾሀማ ነው፤ ትእምርተ ኃይል ትእምርተ መዊዕ አለህ ሲሉ ነው። ቴምር ልዑል ነው ልዑለ ባሕርይ ነህ ሲሉ ፍሬው አንድ ነው ዋሕደ ባሕርይ ነህ ሲሉ ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው ባሕርይ አይመረመርም ሲሉ ነው። የወይራ ዛፍ ጽኑዕ ነው ጽኑዓ ባሕርይ ነህ ሲሉ፤ ብሩህ ነው ብሩሃ ባሕርይ ነህ ሲሉ ነው። አንድም ዘይት መሥዋዕት ይሆናል አንተም መሥዋዕት ትሆናለህ ሲሉ ነው።
ከዕለቱ ምን እንማራለን?
፩. ፍጹም ትሕትናን
ነቢዩ ኢሳይያስ ”እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር”(ኢሳ ፮፥፩) ብሎ የተናገረለት የጌቶች ጌታ የንጉሦች ንጉሥ የሆነ አምላክ ራሱን ዝቅ አድርጎ በአህያ ጀርባ መቀመጡ ፍጹም ትሕትናን ያስተምረናል። በከበረ ቃሉ ”ከእኔ ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴ ፲፩፥፳፱) እንዳለን የከበረች ትሕትናን ከባለቤቱ መማር ይገባናል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለጌታ ትሕትና የተናገረውንም ማስተዋል ይገባል “እርሱ አምላካችን የሁሉ ፈጣሪና የማይመረመረ ክብር ያለው ንጉሥ ሆኖ ሳለ ለክብሩ በሚገባ ባማረና በተንቆጠቆጠ ቤት አልተወለደም ራሱን ዝቅ አድርጎ በበረት ተገኘ እንጂ። በዚህ ዓለም ባለጠግነትና ብዕል ከተትረፈረፈች እናት አልተወለደም ከደሀይቱ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ተወለደ እንጂ። የትሕትና አባት ነውና ደቀ መዛሙርቱን ሲመርጥ እንኳ እንደ ዓለም ምርጫ ተናጋሪዎችና ጥበበኞች አዋቂዎች የተባሉትን ልምረጥ አላለም ከድሀ ቤተሰብ የተገኙ ድሆችን መረጠ እንጂ። ሊያስተምር በተጓዘበት ሁሉ ከፍ ያለ ዙፋን ዘርጉልኝ መደገፊያ ትራስ አምጡልኝ አላለም ዝቅ ብሎ በምድር ተቀመጠ እንጂ። በሰው ሁሉ ፊት ሲቆም በዕንቁ የተሠራ ልብስ ልልበስ አላለም ከሰዎች እንደ አንዱ ለብሶ ተገኘ እንጂ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝም ፈረስ ጫኑልኝ፣ ልጓም ሳቡልኝ፣ ሰረገላ አዘጋጁልኝ፣ ሠራዊት አቁሙልኝ አላለም ዝቅ ብሎ በአህያ ጀርባ ተቀመጦ ተጓዘ እንጂ” ይህ ግሩም ነገር ነው! ቅዱስ አባ መቃርስም እንዲህ ብሏል “ጌታ እኛን ስለማዳን እንዲህ ራሱን ዝቅ ካደረገ እኛ ስለራሳችን መዳን ምን ያህል ትሕትና ያስፈልገን ይሆን?” የትሑታን አምላክ በቃልም በግብርም ያሰተማረንን የትሕትና ግብር ዕለት ዕለት ልናስበው ልንኖረውም ይገባል። ትሕትና የተለየው ሕይወት ከእግዚአብሔር መንግሥት ለራቀ ሰው ምልክቱ ነወና።
፪. ክብር እና ምስጋናን
የጌታችን የኢየሩሳሌም ጉዞ በምስጋና እና በክብር የተሞላ ነበር። ደቀ መዘሙርቱ፣ ሕፃናቱ እና እጅግ ብዙ ሕዝብ ደግሞ የለበሱትን አውልቀው መንገድ ላይ እያነጠፉ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ እየጎዘጎዙና እያወዛወዙ፣ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ዘምረውለታል። ይህ ክብር የካህናት አለቆችን፣ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ደሰ አላሰኘም። እኛስ ዛሬ እንደ ሕፃናቱ በፊቱ የሚቀርብ እርሱም የሚቀበለው የጸሎትና የምስጋና ሕይወት ይዘናልን? ደቀ መዛሙርቱ ልብሳቸውን እንዳነጠፉለት በንስሓ የነጻ ሕይወታችንን ልናቀርብ ተዘጋጅተናልን? ለምለም የዘንባባ ዝንጣፊን የመሰለ ደምቆ የሚታይ ምግባር በእጃችን አለን?
፫. የእግዚአብሔርን ፍቅርና ርኅራኄ
ጌታችን በኢየሩሳሌም ደጅ ሲቀርብ ከተማይቱን አይቶ ማልቀሱ ለሰው ያለውን ፍጹም ፍቅርና ርህራሄ ያሳየናል። ለሰላም የመጣ አምላክ ነውና ሰላሙን ባለመቀበል ልባቸውን የሚያጸኑ ብዙዎች በኢየሩሳሌም እንዳሉ አይቶአልና ከኀዘኑ የተነሳ የከበረ ዕንባውን አፍስሷል። የካህናት አለቆችና ጻፎች የሚያመሰግኑ ሕፃናትን ድምፅ ላለመስማት ጆሮአቸውን በመድፈን፥ ኋላም ዝም አሰኝልን በማለት በገሃድ ጥላቻቸውን ገልጠዋል። እርሱ የፍቅርና የርህራሄ አምላክ ነውና ልባቸውን አይቶ ስለእነርሱ እንባውን አፈሰሰ። የርሕራሄው ጥልቅነት የሚደንቀው ከዕንባው በላይ የከበረ ደሙን በፍጹም ፍቅር ስለ ሁሉ ሊያፈስ በታላቅ ትሕትና በመካከላቸው መገኘቱ ነው።
ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የሆነ ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ እንደተቀመጠ ሁሉ ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት ዛሬም ያድራል፤ የኅሊና ሰላምን ይሰጣል። ስለዚህ ንስሓ ገብተን ጌታችንን ሆሣዕና በአርያም እያልን ልናመሰግነው ይገባል።
እግዚአብሔር አምላካችን ፍጹም ትሕትና፣ ፍቅርና ርኅራኄ የተሞላ የምስጋና ሕይወት ያድለን ዘንድ፤ መጪውንም ሳምንት በሰላም አሳልፎ ለብርሃነ ትንሣኤው እንዲያደርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።
ምንጭ፦
፩. ወንጌል ቅዱስ በአንድምታ ትርጉም
፪. ፍኖተ ስብከት (በመምህር አዲሱ ላቀው)
፫. ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ
፬. ከሣቴ ምሥጢር (በመምህር አባ ኃይለ መለኮት ይኄይስ)