መኑ ውእቱ ገብርኄር ?

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ዘለዓለም ሥላሴ!

ገብር ኄር

ስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት “ገብር ኄር” ተብሎ ይጠራል።  ቃሉ “ገብር” እና “ኄር” ከሚሉ ከሁለት የግእዝ ቃላት የተገኘ ሲሆን “ገብር” የሚለው አገልጋይ፣ ሠራተኛ፣ ባሪያ ማለት ሲሆን “ኄር” የሚለው ቃል ደግም መልካም፣ ቸር፣ ጥሩ፣ ደግ የሚል ፍችን ይይዛል። በአንድነት “ገብር ኄር” ማለት “መልካም አገልጋይ ፣ ቸር አገልጋይ፣ ታማኝ አገልጋይ” ተብሎ ይተረጎማል። ይህ ጽንሰ-ሀሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስፋት የሚንጸባረቅ ሲሆን በተለይም በሐዲስ ኪዳን ውስጥ የአገልጋይነትን ትርጉም እና ክርስቲያኖች እንዴት ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ሰዎች ታማኝ አገልጋዮች መሆን እንደሚችሉ ያሳያል። ስድስተኛው ሰንበት “ገብር ኄር” ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት የሚዘመረው የቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ የሚከተሉትን ስለሚጠቅስ ነው።

⇛ “ገብር ኄር ወገብር ምእመን ገብር ዘአሥመሮ ለእግዚኡ ትርጉሙ፦ ጌታውን ያስደሰተው አገልጋይ ታማኝና ቸር አገልጋይ ነው።

⇛ “ገብር ኄር ወገብር ምእመን ዘበውሕድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሰይመከ ትርጉሙም፦ በጥቂቱ የታመንክ ቸር አገልጋይ ሆይ፥ በብዙ እሾምሃለሁ።

⇛ “ዘበምልክናከ ሠናየ ገበርከ ብፁዕ አንተ ገብርኄር ትርጉሙም፦ በሹመትህ በጎ የሠራህ ቸር አገልጋይ ሆይ፥ ብፁዕ ነህ።

⇛“ዘይረክቦ ለእግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሰይሞ ዲበ ኩሉ ንዋዩትርጉሙም፦  በደግ ሥራ ጌታው የሚያገኘውና በገንዘቡ ሁሉ ላይ የሚሾመው ቸር እና የታመነ አገልጋይ ማን ነው

⇛ “ለአግብርት ግዕዛን ለማሃይምናን ሰላም ዛቲ ዕለት ሰንበተ ክርስቲያን ትርጉሙም፦ ይህች ዕለት የክርስቲያን ሰንበት ለአገልጋዮች ነፃነት ለአማኞች ሰላም ናት።

⇛ “ኩኑ እንከ ከመ አግብርት ኄራን ወከመ አግብርተ ክርስቶስ ምእመናን እለ ይጸንሑ ለእግዚኦሙ እስከ የአቱ እምከብካብ ዘበሰማያት ትርጉሙም፦ እንግዲህ በሰማይ ወዳለው መንግሥተ እግዚአብሔር እስክትገቡ ድረስ ጌታችሁን ደጅ እንደሚጠኑ እንደ ቸር አገልጋዮችና እንደ ክርስቶስ ታማኝ አገልጋዮች ሁኑ።

⇛ “ጹሙ ወጸልዩ ከመ አግብርት ተቀነዩ ትርጉሙም፦ እንደ መልካም አገልጋዮች ጹሙ ጸልዩ ለእግዚአብሔር ተገዙ።

በእነዚህ መዝሙራትና ቃላት አማካኝነት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የካህናትንና የምእመናንን የጽድቅ ሥራ ከመልካም አገልጋይ ሥራ ጋር እያነጻጸረ፥ የኃጥአንን የበደል ሥራ ደግሞ በተቃራኒው እያመላለሰ በወንጌል ያስተማረውን ትምህርት ያስታውሳል። በአጠቃላይም ስለ ጻድቃንና ኃጥአን በምሳሌ የተናገረውን ቃለ ወንጌል እየጠቃቀሰና እያነሳሳ ስለሚዘመር፥ ይህ ሰንበት ገብርኄር ተብሎ ይጠራል። ሰለዚህ ይህ ሰንበት የፃድቅ መታሰቢያ ዕለት ነው። በዚህ ዕለተ ሰንበት መታሰቢያነት የተሰጠውን የገብርኄርን የምሳሌ ትምህርት የምናገኘው ቀጥሎ በተጠቀሱት የወንጌል ክፍሎች ነው።  ማቴ ፳፭፥፲፬-፵፮ ፤፲፫፥፲፪ ሉቃ ፲፱፡፲፪-፳፯

 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ እንጂ ያለ ምሳሌ አያስተምርም። አንቀጸ አባግዕን ሲያስተምር የሙሴን በጎች እያሰበ ነበር። አንቀጸ ብፁዓንን ሲያስተምር በብሔረ ብፁዓን ያሉ ይህንን ዓለም የናቁ ከዓለም የራቁ የብፁዓን አበውን ሕይወት ጠቅሶ ነበር። እነዚህ ብፁዓን ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ከኢየሩሳሌም ተውጣጥተው በነቢዩ ዕዝራ መሪነት ብሔር ብፁዓን የገቡ ሲሆኑ እስከዛሬ ድረስ በሕይወት ያሉ መልአከ ሞት የማያስደነግጣቸው ናቸው። እኒህም ኄራን ብፁዓን ይባላሉ። ጌታችን ይህን በምሳሌ አንሥቶ ስለ ደጋግ ባሮች ሲያስተምረን “ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ባለ ጸጋ ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናል። ለእያንዳንዱ እንደ አቅሙ ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ሄደ። አምስት መክሊት የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ። እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቆፍሮ የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመን በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው።” ማቴ ፳፭፥፲፬-፳

ባለጸጋው ማን ነው?

እዚህ ላይ ባለጸጋው እግዚአብሔር አምላካችንን ይመስላል። አገልጋዮቹ ደግሞ እኛ ክርስቲያኖች ነን። ለሰዎች ሁሉ ጸጋን፣ ስጦታን  የሚሰጥ ጌታ ለአገልጋዮቹ እንደ አቅማቸው አምስት፣ ሁለትና አንድ መክሊት ሰጣቸው። መክሊት የተባለው የአገልግሎት ጸጋ ምሳሌ ነው። ጌታችን ለእያንዳንዱ እንደ አቅሙ የአገልግሎት ጸጋ ይሰጣልና። አገልጋዮቹ ደግሞ የአገልግሎት ጸጋ የተቀበሉና ምእመናንን በመንፈሳዊ ሥርዓት የሚያገለግሉ ካህናትና  በልዩ ልዩ ጸጋ የሚያገለግሉ ምእመናን ምሳሌ ናቸው። ጌታ  አምስት ለሰጠው ሁለት፣ ሁለት ለሰጠው አንድ፣ አንድ ለሰጠው አምስት መስጠት ተስኖት ሳይሆን እንደ ችሎታቸው ለመስጠት ነው። ጌታችን ለእኛም እንደ አቅማችን የአገልግሎት ጸጋ ሰጥቶናል። ሁለት የተሰጠው ለምን አምስት አልተሰጠኝም አይበል፣ ይልቁንስ በተሰጠው ይታመን፤ በተሰጠው ታምኖ ሲያገለግል ይጨመርለታልና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው፤ ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ። ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ ለሁሉም ጌታ እየረዳ በየዕድሉ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳንዱ በግልጥ ይሰጠዋል።” (፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፬-፯) እንዳለ ሁላችንም በተሰጠን  ጸጋ መጠን እንድናገለግል መክሊት ተቀብለናል።

“አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን ሰጣቸው” እንደተባለ ሁላችንም በተሰጠን ጸጋ ማትረፍ መቻል አለብን።  ይህም ማለት የተሰጠንን መንፈሳዊ ዕውቀት፣ ጸጋ ለሌሎች ማካፈል፣ በዚያም ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የድኅነት ምክንያት መሆን ማለት ነው። “ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቆጣጠራቸው” እንዲል ጌታችን እግዚአብሔር አገልጋዮችን እንደ አቅማችን የምናገለግል ሁላችንንም በተሰጠን መክሊት ምን እንዳተረፍንበት ሊቆጣጠረን ይመጣል። አምስት መክሊት የተቀበለው ታማኝ አገልጋይ ሄዶ፣ ነግዶ፣ ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ፤ ሁለት የተሰጠውም እንዲሁ በድካም፣ በመታዘዝ ሌላ ሁለት አተረፈ። እነዚህ አገልጋዮች የተሰጣቸውን እንደ ችሎታቸው አትርፈዋልና መንግሥተ ሰማያትን እንደሚወርሱ በሚያስረዳ ምሳሌ “አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” እየተባሉ ተመሰገኑ።

ይህንን ቃል ሊቃውንቱ ሲተረጉሙት፦ አምስት መክሊት በቁሙ ገንዘብ አይደለም። ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ነው ይላሉ። እነዚህ ሀብታት ልዩ ልዩ ሲሆኑ በዚህ ወንጌል  ውስጥ ባለ አምስት መክሊት የተባሉት ነቢያት ናቸው። አምስት የተሰጠው ሌላ አምስት አትርፎ ዐሥር እንዳደረገው ሁሉ ነቢያትም በብሉይ ኪዳን ጌታችንን ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት ተናግረው በሐዲስ ኪዳን ትንቢት የተናገሩለት ጌታችን ተወልዶላቸው አስበ ትንቢታቸውን ተቀብለው ገነት ገብተዋል። ትርፋቸው ገነት መግባት ነውና። ከነቢያቱ መካከል ሊቀ ነቢያት ሙሴን መጥቀስ እንችላለን። ሙሴ ጌታችን ይወርዳል ይወለዳል ከማለቱ በተጨማሪ አምስት መጻሕፍትን ጽፏል። ባለ አምስት መክሊቱ ሌላ አምስት መክሊት አትርፎ ዐሥር ባደረገ ጊዜ፦  “ጌታውም፡ መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።”ማቴ ፳፭፥፳፩። ባለ አምስት መክሊቱ ሌላ አምስት ባተረፈ ጊዜ በብዙ ወገን ይሾማል። ይህ ባለ ብዙ ወገን ሲመት የመንግሥት ሢመት ነው። ከፍጥረተ ዓለም እስከ ሕልቀተ ዓለም ያሉ ምእመናን በሙሉ አምስት ተሰጥተው ሌላ አምስት ካተረፉ መንግሥተ ሰማይ ቤታቸው ናት።

በሁለት መክሊት የተመሰለው ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ሀብቱ ብዙ ነው። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጴጥሮስን ለዚህ እንደ አብነት ይጠቅሱታል። ሁለቱ መክሊት የተባሉት ደግሞ ብሉይ እና ሐዲስ ኪዳን ናቸው። ይህም ማለት የቀለም መምህርነቱ ሲገለጽ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ምሥጢረ ሰማይ ወምድርን ከተረዳ በኋላ ለጊዜው ለቀለሜንጦስ አስተምሯል። ሊቃውንቱ ጨምረውም እኒህን መክሊት በመዓረግ ሲተረጉሙት ደግሞ፦ ባለ አምስት መክሊት የተባሉት ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው። አምስቱ ሀብታት ደግሞ አንብሮተ እድ፣ ቀሳውስትን እና ዲያቆናትን መሾም፣ ጥምቀት እና ቁርባን ናቸው። ሊቀ ጳጳሱ በአንብሮተ እድ ይሾማል። አሐዱ ብሎ አሕዛብን ያጠምቃል። ከዚያ ቀድሶ ያቆርባል። እኒህ አምስቱን መክሊቶች ይፈጽማል። በዚህ ጊዜ ገብር ኄር ተብሎ በጌታችን ቃል ተወድሶ መንግሥተ ሰማይን ይወርሳል። ባለ ሁለት መክሊት የተባሉት ደግሞ ካህናት ናቸው። እኒህ መክሊቶች ደግሞ ጥምቀት እና ቁርባን ናቸው። ባለ ሁለት መክሊቱ ሌላ ሁለት አትርፎ በተገኘ ጊዜ “መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” እንዳለው የተሰጣቸውን መክሊት በአግባቡ ተጠቅመው ያተረፉ ቤታቸው ገነት መንግሥተ ሰማያት ናት።

“አንድ መክሊትም የተቀበለው ቀርቦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ መክሊትህ አለህ አለ። ጌታውም መልሶ አንተ ክፉና ሰነፍ ባሪያ፥ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁበትም እንድሰበስብ ታውቃለህን?” የተሰጠውን የአገልግሎት ጸጋ እንደ አቅሙ ከመጠቀም ይልቅ የመናፍቃንን ክርክርና ሥም ማጥፋት፣ የዓለምን ፈተና፣ የሥጋውን ምኞት መቋቋም አቅቶት መክሊቱን ቀበረው። ጌታው ሲጠይቀው ግን የተገለጠ ድካሙን ከማስተዋል ይልቅ በሐሰት ቃል ጌታውን ወቀሰው። ሰነፍ አገልጋዮች ሁሌም እንዲህ ናቸው፤ ለስንፍናቸው ሌሎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ እንጂ ወደራሳቸው ተመልክተው ስሕተታቸውን አያርሙም። ይህ አሁን በዓለም ያሉ አገልጋዮችን ይመለከታል። ብዙ መክሊትን በመቅበር ይታወቃሉና። ሊቃውንቱ ይህን ሲያብራሩ በባለ አንድ መክሊት ተመስሎ የቀረበው ይሁዳ ነው ብለው ይተረጉሙታል። እንደ እነ ጴጥሮስ ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብሎ ተምሮ ነበር። የተማረውን ማስተማር ስላልቻለ እና በሃይማኖቱ ጸንቶ ስላልኖረ  መንግሥተ ሰማይን አልወረሰም። ለይሁዳ መክሊቱ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብሎ የተማራት ወንጌል ነበረች እርሷኑ ቀብሯት ቀርቷልና። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መክሊቱን በመዓረግ ሲተሩጉሙት ባለ አንድ መክሊት የተባለው ዲያቆን እንደሆነ ይናገራሉ። ይህቺውም ተልእኮ ናት። አንድም ባለ አምስት ጥምቀት፣ ተአምኖ ኃጣውእ፣ ተባሕትዎ፣ ምንኲስና እና ከዊነ ሰማእት ናቸው። ባለ ሁለት ደግሞ ጥምቀት እና ተአምኖ ኃጣውእ ሲሆኑ ባለ አንድ ደግሞ ጥምቀት ናት። አንድም ባለ አምስት አሚን፣ ተስፋ፣ ምሕረት፣ ትዕግሥት፣ ፍሥሐ ናቸው። ባለ ሁለት ደግሞ አሚን እና ተስፋ ሲሆኑ ባለ አንድ ደግሞ አሚን ነው። አንድም ባለ አምስት ፍጹም ባለ ጸጋ፣ ባለ ሁለት በመጠኑ ባለ አንድ ፍጹም ድኃ ነው።

ቸር አገልጋይ ማነው?

ቸር አገልጋይ ማለት ለጌታው የታመነ፣ የተሰጠውን መክሊት ያላስቀረ፣ ነገር ግን ያተረፈና የጨመረ፣ በዚህም ምክንያት ወደ ጌታው ደስታ የገባ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ጌታውን የተሳደበውና በእርሱ ላይ ያመፀው አገልጋይ በባዶ እጁ ወደ ዘላለማዊ ጨለማ ይጣላል።

ጸጋና በረከት

እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ልጁ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ጸጋዎችን ይሰጣል። ይህ ጸጋ በጎ ሥራ እንድንሠራ ይረዳናል፣ ብዙ በረከትንም ያስገኛል። ይህ ጸጋ የምናገኘው ከምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በመሳተፍ፣ ዕለት ዕለት ከቅዱስ ቁርባን በመቀበል እና ከሌሎችም ምሥጢራት ነው። እነዚህ ምሥጢራት የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋዮች እንድንሆን ይረዱናል።

መንግሥተ ሰማያት

በመጨረሻም ታማኝ ሆነን ብንገኝ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን። “ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው” (ዮሐ. ፮፥፶፬) የሚለው የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው። ከመሬት የፈጠረው አምላክ ጌታው የሰነፍ ገንዘብ አዳምን መሬት ነህና ወደ መሬት ተመለስ ይለዋል። “ለመክሊተ ሀካይ አዳም ይቤሎ እንተፈጠሮ መሬተ ውስተምድር ለትባዕ አምጣነ መሬት አንተ [እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከመሬት ፈጥሮ በተሳሳተ ጊዜ ቀድሞም መሬት ነህና ወደ መሬትነትህ ተመለስ]” ያለውን በሰሙ ያስታውሰናል በወርቁ ደግሞ ስንመለከተው ገብር ሐካይ የተባለው የተቀበለውን አንዲት ወርቅ መሬት ውስጥ ቀብሮ ማስቀመጡን የሚገልፅ ነው።

የማያተርፍ አገልጋይ

ከመጀመሪያው ጀምሮ የእግዚአብሔር ልጅነት የሌለው ግን በምድርም በሰማይም ሐዘን ይሆንበታል። መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ቀርቶ ወደ ዘላለማዊ ጨለማ ወደ ጥርስ ማፋጨት ይጣላል።

በመጨረሻም  ቸር አገልጋይ መሆን ታማኝነትን፣ ኃላፊነትን እና የተሰጠንን ጸጋ በአግባቡ መጠቀምን ይጠይቃል። ስለዚህ፥ ወንድሞችና እኅቶች፥ ሁላችንም በሕይወታችን የምንችለውን መልካም ሥራ ሠርተን ወደ ጌታችን ደስታ ለመግባት እንትጋ። አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ ይርዳን!!

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!

ምንጭ፦ 

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ድረ-ገፅ
  • ከሣቴ ምሥጢር (በመምህር አባ ኃይለመለኮት ይኄይስ)
  • ወንጌል ቅዱስ በአንድምታ ትርጉም

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/በሰ/ት/ቤቶች/ ማ/መ/ማ/ቅ ሩቅ ምሥራቅ ማእከል ሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ክፍል

መጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም

ቻይና