በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ዘለዓለም ሥላሴ።

እንኳን ለዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት (መጻጒዕ) በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በቅዱስ ያሬድ ሥያሜ መሠረት አራተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት መፃጕዕ ብላ ታከብራለች። ይህንንም ሥያሜ እንዴት እንደመጣ ለማየት በዕለቱ የሚነበበውን የወንጌል ክፍል ብንመለከት እንዲህ ይላል። “ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ ‘ልትድን ትወዳለህን’ አለው። ድውዩም ጌታ ሆይ አዎን! ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም እንጂ፤ ነገር ግን እኔ በመጣሁ ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል አለ። ጌታ ኢየሱስም ‘ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ’ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፤ ያም ቀን ሰንበት ነበረ” ይላል። (ዮሐ.፭፥፭-፲) ቅዱስ ያሬድ ከዚህ የወንጌል ክፍል በመነሣት “ዕውራነ መርሐ፥ አጋንንተ አውጽአ፥ እለ ለምጽ አንጽሐ፥ ወሙታነ አንሥአ በዕለተ ሰንበት፤ ወይቤሎሙ አቡየ ኩሎ አብሐኒ” እንዲሁም “አሕየዎ ኢየሱስ ለመፃጕዕ ወፈወሶ በዕለተ ሰንበት አሕየዎ ኢየሱስ ለመፃጕዕ፤ ኢየሱስ መፃጉዕን በዕለተ ሰንበት አዳነው” በማለት ይዘምራል። በዚህ ሳምንትም ጌታችን ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን በትምህርት ስለፈወሰበት፣ ለጊዜው በእግር በኋላ በግብር ስለተከተሉት ሐዋርያት የማዳን ሥራ፣ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ስለሚደረገው ድኅነት የምንማርበት ሳምንት ነው። ለሐዋርያት ለካህናት ስለተሰጠው ታላቅ ሥልጣንም መቅድመ ወንጌል “ወዘክሡትሰ ላዕለ ገብሩ ትእዛዞ አስተርአየት ላዕለ እደዊሆሙ ተአምራት ወመንክራት ወኀይላት ዐቢያት እስመ ውእቶሙ ከሠቱ አዕይንተ ዕውራን ወአንጽሑ እለ ለምጽ ወሞዕዎ ለሞት ወከብረት ነፍሶሙ በውስተ ዓለማት ክልኤቲ ዘዝየ ወዘከሐ” ይላል።

 

ከደዌው ጽናት የተነሣ ስሙ እንኳን የተረሳ፣ ረጅም ዓመታት በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ በመያዙ መፃጕዕ፣ በሽተኛው፣ በደዌ የተያዘው እየተባለ ስለሚጠራው በቤተ ሳይዳ በጠበል ሥፍራ የተኛውን በሽተኛ በዓይነ ኅሊናችን እንመልከተው፤ በእግረ ኅሊናችን ወደ ቤተ ሳይዳ እንገሥግሥ፤ በዚህች የይቅርታ በር ለሠላሳ ስምንት ዓመት ከአልጋው ተጣብቆ የኖረውን ወደ ጠበሉ የሚያስገባው ሰው ያጣውን መፃጕዕን ለትንሽ ደቂቃ አብረነው እንቆይ። መፃጕዕ የእግዚአብሔርን ምሕረት እየተጠባበቀ ለረጅም ዘመን ኖሯልና ከውኃ ዳር ሁኖ ብርድና ሙቀት፣ ውርጭና ፀሐይ፣ ቀንና ሌሊት እየተፈራረቀበት ከአልጋው ውጭ የሚረዳው ዘመድ የሌለውን የእምነቱን ጽናት አስተውሉ። ሊቁ ኤስድሮስ የተኛበትን አልጋ “የብረት አልጋ ነው” በማለት ተርጕመውታል። (ትርጓሜ ወንጌል ዘዮሐንስ ምዕራፍ ፭) ለሠላሳ ስምንት ዓመት የሚቆይ ጠንካራ አልጋ ቢሆን ነውና። ነገር ግን ብረት ውርጭ ይስባል፤ ቀዝቃዛ ነው፤ ይህን ታግሦ ምሕረት እየተጠባበቁ መኖር ምን ይደንቅ! ውሉደ ቤተ ክርስቲያን! ዛሬም የይቅርታ የምሕረት በር በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ብዙ መጻጒዓን የእኛን ርዳታ ሽተው እጃቸውን ዘርግተው እየተጠባበቁን ነውና ሰው እንሁንላቸው። “ተርቤ አላበላችሁኝም፣ ታምሜ አልጎበኛችሁኝም”… የሚለን አምላካችን በድውያን ላይ አድሮ ስለሚኖር ነውና። (ማቴ.፳፭፥፴፩-፵፮) የተቸገረውንና የታመመውን ሰው አልፈን ክርስቶስን ፍለጋ ቤተ መቅደስ ብንገባ አናገኘውምና ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት ሕሙማነ ሥጋን በእንክብካቤ እናግዛቸው። መንፈሳዊነት ማለት ልብሳችንን በዘባነ ዕሩቃን፣ ምግባችንን በከርሠ ርኁባን፣ መጠጣችንን በጉርዔ ጽሙዓን፣ ዓይናችንን በአካለ ድውያን ስናደርግ ነው፤ የሰውነት ልኩም ይሄው ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምጽዋትን ሲተረጉም “ፍቅር” በማለት ይጠራዋል። ምጽዋት መስጠት ፍቅር መስጠት ነውና፤ ታዲያ ክርስቶስን ምን ያህል አፍቅረነዋል? “ዘገበርክሙ ለእሉ ንኡሳን እምአኀውየ ሊተ ገበርክሙ”እንዲል። (ማቴ. ፳፭÷፵) መፃጕዕ በዚያች አልጋ ላይ ተጣብቆ የውኃውን መናወጽ ይጠባበቃል። በሰንበት መልአኩ መጥቶ ሲያናውጸው ሰው ባለመኖሩ ምክንያት ቀድመውት እየገቡ እርሱ አለመዳኑን ስናይ የሰው መድኃኒቱ ሰው መሆኑን እንረዳለን። ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ አልጋ ላይ ተጣብቆ የኖረው ይህ በሽተኛ ወደ ውኃው የሚያስገባው ሰው በማጣቱ ሰው ያለው በሽተኛ ቀድሞት ገብቶ ይፈወሳል። በዚያ ዘመን መንፈሰ ጠንካራ ሳይሆን ጉልበተ ጠንካራ፣ ያመነ ሳይሆን የቀደመ ነበር የሚፈወሰው ማለት ነው። ይህም በሕገ ኦሪት ከመንፈሳዊነት ይልቅ ሥጋዊነት የተስፋፋ መሆኑን ያሳያል። አሁንም በዘመናችን ይህንን የሚመስሉ ነገሮች በተለይ በታላላቅ የጠበል ቦታዎች፣ ገዳማት እንጥፍጣፊውም ቢሆን ይታያል። በረከተ ሥጋም ሆነ ድኅነተ ነፍስ ሌሎቹን ገፍቶ በመቅደም ሳይሆን ስለ እውነት በመገፋት፣ ለሌሎች በመራራትና በማሰብ ነው እንጂ በብልጥነት ሊገኝ አይችልም። ይመስለን ይሆናል እንጂ የእግዚአብሔር ዐይኖቹም አቅም ካጣ፣ ከደከመውና ከተቸገረው፣ ሰው ዐይኑን ካራቀበት ዓለም ጀርባዋን ከሰጠችው ሰው ላይ ናቸው። “ዝንቱ ነዳይ ጸርሐ ወእግዚአብሔር ሰምዖ ወእምኵሉ ምንዳቤሁ አድኃኖ፤ ይህ ችግረኛ ተጣራ እግዚአብሔርም ሰማው ከመከራውም ሁሉ አዳነው”እንዲል ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት (መዝ. ፴፫፥፮)። በመጽሐፈ ኢዮብም “እርሱ የበደለኛዎችን ሕይወት አያድንም ለችግረኛዎች ግን ፍርዱን ይሰጣል” (ኢዮ. ፴፮፥፮) እንዲል። በዘመነ ሐዲስ ወደ መጠመቂያው ቦታ በመውረድ በእግር የቀደመ ሳይሆን በእምነት የቀደመ ነው የሚፈወሰው። አንድ መምህር “በብዙ ምክንያት ሰው ቢያሳምመኝም ከሰው የተሻለ መድኃኒት የለኝም”እንዳለው ክርስቶስ ሰው መሆኑ ደግ ሳምራዊነትን ሊያሳየን ነውና። መፃጕዕ ሰው የለኝም ማለቱ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሚያበላው፣ የሚያጠጣው፣ የሚያለብሰው፣ ሰው አልኖር ብሎ ሳይሆን የደጉ ሳምራዊን የክርስቶስን ሰው መሆን ሲጠባበቅ በነበረው በአዳም ቃል ተገብቶ እየተናገረ ነው። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በበጎች በር በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ በምትባል በመጠመቂያ ቦታ ተገኘ። በበጎች በር ያለውም ክርስቶስ ደግ እረኛ በመሆኑ በበጎች በር መጣ ተባለ፤ መልካም እረኛ በበር ይመጣልና። በዚህ ጊዜ መፃጕዕ አገኘው፤ እርሱም “ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ ትፈቅድኑ ትሕየው፤ ልትድን ትወዳለህን” አለው። መፃጕዕ “እወ እግዚኦ” አዎ፤ አቤቱ አለ። ኢየሱስም የመፃጕዕን መልስ ከሰማ በኋላ “ተንሥእ ወንሣእ ዓራተከ ወሑር፤ ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። (ዮሐ. ፭፥፭-፲) ጌታችን ይህንን ጥያቄ ሳይጠይቅ ፈውሶት ቢሆን ኖሮ ፈውሰኝ ሳልለው ቅዳሜን (ሰንበትን) ሽሮ ፈወሰኝ ብሎ ይከሰው ነበርና የውስጡን ተንኮል ስላወቀ አስፈቅዶ ፈወሰው። ሠላሳ ስምንት ዓመት በአልጋ ቁራኛ ይሠቃይ የነበረው መፃጉዕ በአንድ ጊዜ ዳነ፤ ከሕመሙም ተፈወሰ፤ ያንን የብረት አልጋ ተሸክሞ ወጣ። ማንም ባልነበረበት ሰዓት ያልተለየችውን አልጋ ውለታዋን ሊከፍል ይዞ ወጣ።

ጌታችን ወደ ቤተ ሳይዳ መጥቶ መፃጕዕን “ልትድን ትወዳለህ” ብሎ መጠየቁን ስናይ ይደንቃል! ምሕረትንና ድኅነትን እየተጠባበቀ የኖረው ሰው “አልድንም” የሚል መልስ ሊሰጥ እንደማይችል የታወቀ ነው፤ ታዲያ ስለምን ጠየቀው ቢሉ የነፃነት አምላክ ነውና እኛን ሳያስፈቅድ እንደማይሠራ ለማጠየቅ ነው። የግእዝ በግእዝ ትርጓሜ ላይ “መፃጕዕ ሊድን እንደሚወድ ጌታችን ያውቃል። ሃይማኖቱን ይገልጥ ዘንድ ይጠይቀዋል። ለምን አድንህ ዘንድ አትፈልግም? አላለውም። በትሕትና ‘ልትድን ትወዳለህን?’ አለው እንጂ”በማለት የጌታችንን ትሕትና ያደንቃል። ምሥጢሩ ግን አንድምታ ትርጓሜያችን እንደሚነግረን በዕለተ ዓርብ ጌታን በጥፊ ከመቱት ሰዎች አንዱ ይህ መፃጕዕ ነበርና “ስለምን በጥፊ ትመታዋለህ” ቢሉት ሳልፈልግ አድኖኛል እንጂ አድነኝ ብየው አይደለም እንዳይል ሰበብ እንዳያገኝ ነው።”

በዐቢይ ጾም ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ሰንበታቱን በዚህ መልኩ ሠይማ እንድናከብር የምታዘን እንማርባቸው ዘንድ ነው። ጽድቅን በመሻት ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር እንድናደርግ፣ መንገዱንም እንከተል ዘንድ ነው፡፡ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” (መዝ. ፻፲፱፥፻፭) ተብሎ እንደተጻፈው። ከእያንዳንዱ ሰንበት ሥያሜ የምንወስደውና ገንዘብ ልናደርገው የሚገባን መንፈሳዊ ሕይወት አለ። ኦ ውሉደ ቤተ ክርስቲያን! አንትሙሰኬ ትፈቅዱኑ ተሐይዉ? እናንተስ ልትድኑ ትወዳላችሁን? ወይስ እኛ አልታመምንም ትሉ ይሆን? እኔ ግን እላለሁ ፈውስ የሚያስፈልገን መፃጕዓን ነንና የይቅርታ በር ወደ ሆነችው ቤተ ክርስቲያን እንገሥግሥ። ይህች መፃጕዕ የምንላት ሰሙን (ሳምንት) መታሰቢያነቷ በዚያ ዘመን ለነበረው ለአንዱ ድውይ ወይም ድውያን ብቻ አይምሰላችሁ የሥጋና የነፍስን ደዌ አስተባብረን ለምንገኝ ለኛም ጭምር ነው እንጂ። ሕዋሳቶቻችን ታመው እቤት መዋል (በሥጋ ምኞት ብቻ መመላለስ) ከጀመርን ሰነባብተናልና መዳንን እንሻ። እስኪ ልጠይቃችሁ! ዓይኖቻችን አልታመሙምን? ክርስቶስ በፊታችን እንደተሰቀለ ሆኖ መመልከት ይችላሉን? ዓለም ፊቷን ያዞረችበትን ችግረኛውን ሰው ያያሉን? ጆሮአችንስ ይሰማልን? ቤተ ክርስቲያን ስትጣራ ሰምተናት እናውቃለንን? እንዳኢ! ከዚህ አልፎስ ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ መፃጕዕ የግብር ወንድሟ አልሆነምን? ደዌ ከሠለጠነባት ሕመሙ ከጸናባት ቆይታለች። የታመሙት ሕዋሳቶቻችን ይፈወሱ ዘንድ እንደ መፃጕዕ ከቤተ ሳይዳ ከቤተ ክርስቲያን አንለይ! ከመንፈሳዊነት አንራቅ፤ በዚያ ሆነን የክርስቶስን መምጣት እንጠባበቅ እንጂ። የደዌያችን መንሥኤ ከመፃጕዕ ደዌ ጋር አንድ ነውና ፈዋሹን በንስሓና በእምነት እንጠብቀው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መፃጕዕን ሲፈውሰው “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ብቻ አልነበረም ያለው፡፡“እነሆ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” በማለት አስጠንቅቆታል። (ዮሐ. ፭፤፲፬) ይህም መፃጕዕ ኀጢአተኛ እንደነበርና ፈውሰ ሥጋን ካገኘ በኋላ አምላኩን በማገልገል እንዲኖር ጌታችን አስጠንቅቆታል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ከምድራዊ ስቃይ የባሰ ዘለዓለማዊ እሳት ውስጥ መጣል እንዳለ ሲያመለክተው ነው። የአንድምታ መተርጕማን የዚህ በሽተኛ ደዌ ዘኀጢአት ነው ይላሉ። ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ በበሽታ ሢሰቃይ የኖረው በኀጢአቱ ነው። ወደፊት ኀጢአት አትሥራ የሚለው ቃል ከዚህ በፊት ኀጢአት የሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ጌታ ግን አስቀድሞ እስከአሁን በሥጋ ተቀጥተሃል ወደፊት ኀጢአት ብትሠራ ግን በነፍስህ ለዘለዓለም ትቀጣለህ ብሎት ነበር። ወደኛ ስንመለከት እግዚአብሔር እኛን የፈወሰበት ዘመን ስፍር ቁጥር የለውም። የኛም በደል በዚሁ ልክ ነው። አንድ ባለ ቅኔ “ዕሩያነ ኮኑ በሰመንቱ ምእት ዓመት፤ ሰብዕ በዓመፃ ወእግዚአብሔር በምሕረት”እንዳለ ደጋግመን እግዚአብሔርን የበደልንበት ጊዜ ብዙ ነው። አሁንም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ❝እነሆ ድናችኋል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኛችሁ ዳግመኛ እንዳትበድሉ ተጠንቀቁ❞። ከኀጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሞት ወደ ሕይወት እንሸጋገር ዘንድ የአምላካችንን ቃል መፈጸም እንደሚገባን፣ እስከ ሞትም መታመን እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ በተለይም በንስሓ ሕይወት ውስጥ መኖርና እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችንን እግዚአብሔርን በመፍራት ልንፈጽም ይገባናል፡፡ ሰው ኀጢአት ሠርቶ ንስሓ ከገባ በኋላ ዳግም የሚበድልና ፈጣሪውን የሚያሳዝን ከሆነ የሚያገኘው ጥፋትና ሞት ነው፡፡ ይህን ሁሌም በማሰብ በሕገ እግዚአብሔር በመኖርና እስከ ኅልፈተ ሕይወታችን በእምነት ልንጸና ይገባል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ከወደቅንበት የኀጢያት ባርነት ያድነን ዘንድ መጣ። አምላካችን ተራ የማንጠብቅበት ለሁሉ የሚበቃ፣ ፍጹም የሆነ ድኅነት የምናገኝበትን ዘለዓለማዊ የሆነ መብልንና መጠጥን የምሕረት በር በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ሰጠን። ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ብሎ እንደነገረን “ከፈለነ ንብላዕ እም ዕፀ ሕይወት፤ ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን ይሄውም የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው።” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) የእግዚአብሔርን ፍጹም ስጦታ አውቆ በዚህ አለመኖር ደግሞ ጌታን በጥፊ ከመምታት አይተናነስም። ሰበብ ከፍርድ ባያድንም ጥፊያችን ደግሞ ሰበብ አልባ ነውና ከጥቅም አልባ ሰበብ በቸርነቱ ይጠብቀን።

ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር

ምንጭ፦
፩. ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ትርጓሜ
፪. የዮሐንስ ወንጌል ትርጕም /ማብራሪያ/ በመጋቤ ሐዲስ ስቡሕ አዳምጤ
፫. ጾመ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ
፬. ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/በሰ/ት/ቤቶች/ ማ/መ/ማ/ቅ ሩቅ ምሥራቅ ማእከል ሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ክፍል
መጋቢት ፯ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
ቻይና