ድልዋኒክሙ ንበሩ [ተዘጋጅታችሁ ኑሩ]! ማቴ ፳፬፥፵፬
እንኳን ለዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት ደብረ ዘይት በሰላም አደረሳችሁ/አደረሰን።
የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ዓላማ፡
- የደብረ ዘይትን ምንነት ማስረዳት (ስያሜ፣ የት፣ መቼ፣ ለምን)? ፤
- ጌታችን በደብረ ዘይት ቅዱሳን ሐዋርያትን ምን እንዳስተማራቸው መማር፤
- አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ያስተማራቸውን የዳግም ምጽአት ምልክቶች ማሳወቅ ፤
- ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም በግርማ መለኮት፣ በክበበ ትስብእት፣ በይባቤ መላእክት ኅብረት እንዲኖረን ተዘጋጅተን መጠበቅ እንዳለብን መጠቆም ፤
- ማጠቃለያ፣ ጸሎት
ደብረ ዘይት ከሁለት ቃላት የተገኘ ሐረግ ነው። “ደብር” ማለት “ተራራ፣ ጋራ” ማለት ሲሆን «ዘይት» ማለት ደግሞ «ወይራ፣የተክል ዕንጨት» ማለት ነው። ስለዚህ “ደብረ ዘይት” ማለት የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ የወይራ ተራራ ማለት ነው። በመኾኑም ደብረ ዘይት የወይራ መብቀያ፣ በወይራ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገፅ ፫፻፴፮ና ፬፻፲፱)፣ ኢንሳይኮሎፒዲያ)
የደብረ ዘይት ተራራ በእስራኤል ሀገር ከኢየሩሳሌም ከተማ በስተምሥራቅ ፸፭ ሜትር ርቀት የሚገኝ ሲኾን፣ ባለ ብዙ የኖራ ድንጋይ ሸንተረር ያለበትና በቄድሮን ሸለቆ/ወንዝ ተሻግሮ ፰፻፰ ሜትር ከባሕር ጠለል በላይ ከፍታ ያለው ተራራ ነው። ከግርጌው ጌቴሴማኒ የተባለው የአትክልት ስፍራ ይገኛል። ይህም ተራራ ለመጀመሪያ ጊዜ ከብሉይ ኪዳን የታሪክ መጽሐፍት አንዱ በኾነው በመጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ ላይ ተጠቅሷል ። “ዳዊትም ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጣ” (፪ኛ ሳሙ ፲፭፥፴) ። በተጨማሪም ነቢዩ ዘካርያስ ስለመጨረሻው ዘመን በተናገረበት ምዕራፍ ላይ ስለዚህ ተራራ ጽፎ እናገኘዋለን ፤ “በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ” (ዘካ ፲፬፥፬ )
ይህም ተራራ (Mount of Olives) ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ሥራን ከሠራባቸው ቅዱሳት መካናት አንዱ ነው።ታላላቅ ምሥጢራት የተከናወኑበት፣ ለደቀመዛሙርቱ ትምህርት የሰጠበት፣ ስለ ምሥጢረ ምጽአቱ ያስተማረበት፣ ወደ ሰማይ ያረገበትና ዳግመኛ ለፍርድ የሚመጣበት ተራራ ነው። በዚሁ ተራራ ላይ ቀን በከተማና በገጠር ሲያስተምር ውሎ ሌሊት የሚያድርበት የኤሌዎን ዋሻ ይገኛል። (ሐዋ ፩፥፲፪ ፤ ሉቃ ፳፬፥፶)
ማኅቶተ ቤተክርስቲያን ማኅሌታይ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የዐቢይ ጾም እኩሌታ ያለውን ሰንበት በዚህ ተራራ ስም ሰይሞታል። በዚህም ዕለት ስለ ጌታችን ዳግም ምጽአት በስፋት ይሰባካል። “እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይምጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም፤ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ [እግዚአብሐር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፤አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይነድዳል]” መዝ ፵፱፥፫ እግዚአብሔር በግርማ መለኮት፣ በክበብ ትስብእት፣ በይባቤ መላእክት ለጻድቃን ሊፈርድላቸው፣ በኃጥአን ሊፈርድባቸው ይመጣል፣ መጥቶም ዝም አይልም ጻድቃንን ንዑ ኀቤየ ብሎ ይጠራል ፣ ኃጥአንን ሑሩ እምኔየ ብሎ ያሰናብታል፤ በፊቱም እሳት ይነድዳል፣ በዙሪያውም ጥልቅ ነፋስ አለ ማለት ጻድቃን የሚድኑበት ሕይወት ኃጥአን የሚጠፉበት መቅሰፍት በባሕርዩ አለ። ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል (፪ኛ ጴጥ ፫፥፲)። በዚያን ጊዜ ከመጀመሪያዉ ሰው ከአዳም ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሰው ድረስ ሁላችንም በሕይወተ ሥጋ በነበርንበት ጊዜያችን የሠራነዉን ሥራ ይዘን በፊቱ እንቀርባለን (፪ቆሮ.፭፥፲)። ጌታችንም በጎ የሠሩትን ቅዱሳን በቀኙ፤ ክፉ የሠሩትን ኃጥአንን በግራው ያቆማቸውና ፍርዱን ያስተላልፋል (ማቴ. ፳፭፥፴፩ እስከ ፍጻሜ)። የወጉትም ያዩታል እንደተባለ (ራዕ ፩፥፯)፣ በዚያን ጊዜ በእርሱ ላይ የፈረዱበት፣ በቅዱሳንም ላይ መከራን ያጸኑ ሞትንም የፈረዱ ሁሉ ለፍርድ ይቀርባሉ ሁሉን ትተው የተከተሉት፣ ስለ እርሱ መከራን የተቀበሉ፣ ሞትም የተፈረደባቸው ደግሞ በፍርድ ወንበር ተቀምጠው ይፈርዳሉ (ማቴ ፲፱፥፳፷)። በዚህ ሳምንት ስለ ዳግም ምጽአትና ስለዓለም ፍጻሜ ምልክቶች በስፋትና በምልአት ትምህርት ይሰጣል፥ ይሰበካል ። በዕለቱ የሚነበበው የወንጌል ክፍልም ማቴ ፳፬፥፩-፴፮ ነው።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት በሄደበት ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ አጠገቡ ቀርበው ዘሩባቤል ያሳነፀውን የመቅደስ ግንቦች እያሳዩት ቀረቡ። የጥዋት ፀሐይ አርፎበት ያሸበረቀውን ቤተመቅደስ ምን ዓይነት ጥበበኛ ሠራው እያሉ እያደነቁ ነበር። አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን የንጉሣቸው ምልክት አድርገው ይመለከቱት ነበር። እግዚአብሔር ክብሩን የሚገልጽበት እና ከምእመናን እጅ መሥዋዕቱን እና መባውን የሚቀበልበት ብቸኛ ቦታ ነው። አይሁዳውያን በየትኛውም ቦታ ቢሆን፣ ፈተና ሲያጋጥመቸው፣ ወደ ቤተመቅደስ ይሄዳሉ፣ ከእግዚአብሔርም ምሕርት ይቅርታን ይለምናሉ፣ እግዚአብሔርም ይባርካቸው ነበር። ለዚህም ነው ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደስን ሕንፃ ለጌታ ለኢየሱስ ሊያሳዩት የፈለጉት።(የማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜ በቀሲስ ታድሮስ ማላቲ : Matthew – Fr. Tadros Yacoub Malaty)። ሐዋርያቱ ጌታችንንም አብሮ እንዲያደንቅ ሲጠብቁ አስደንጋጭ ነገር ነገራቸው። ጌታችን ኢየሱስም “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” አላቸው። (ማቴ ፳፬፥፪)። ያ የሚያደንቁት ቤተ መቅደስ እንደሚፈርስ ነገራቸው። ወደ ደብረ ዘይት በደረሱ ጊዜ “ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? ምልክቱስ ምንድን ነው ብለው ጠየቁት። ጌታችንም ይህ መቼ ይሆናል ላሉት ጥያቄ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ማቴ. ፳፬፥፴፮ ብሏል። ይህን ማለቱም ሩቅ ቢሆን በየዘመኑ የሚነሡ ክርስቲያኖች ሩቅ ነው ብለው እንዳይዘናጉ ጊዜው ሲቀርብ የሚነሡት ደግሞ ደረሰብን ብለውም እንዳይሸበሩ/እንዳይታወኩ ለመጠበቅም ጭምር ነው። ወልድም አያውቃትም ማለትም ልማደ መጽሐፍ ስለሆነ ነው። አዳም ወዴት ነህ? ከእርሱ እንዳትበላ ብየ ካዘዝኩህ ዛፍ በላህን? (ዘፍ. ፫፥፱፤ ፫፥፲፩)፤ ሰዎች የሰውን ልጅ ምን ይሉታል? እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ? ( ማቴ. ፲፮፥፲፫-፲፭)፤ አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት? ዮሐ ፲፩፥፴፬ እና ሌሎችንም እያወቀ ያላወቀ አስመስሎ ሲጠይቅ እንመለከታለን። ይህም አላዋቂ ሥጋን እንደተዋሐደ ለማጠየቅ ነው። አንድም በሥራ አላወቃትም ማለት ነው። ይህም ማለት በአብ ልብነት ታስባ በወልድ ቃልነት አልተነገረችም ማለት ነው።
አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ምልክቶቹ ከመንገሩ በፊት ማንም እንዳያስታችሁ ተጠበቁ ነበር ያላቸው፣ ቀጥሎም የዳግም ምጽአት ምልክቶች ምን ምን እንደኾኑ፣ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው በስፋትና በምልአት አስተምሯቸዋል። የዳግም ምጽአት ምልክቶቹም የቤተመቅደስ መፍረስ፣ የሐሰተኛ ነቢያት መገለጥ፣ የጦርነት እና የተለያዩ አደጋዎች መነሣት ፣ የሰው ልጅ የሚገጥሙት የተለያዩ ችግሮች፣ በቤተመቅደስ ውስጥ ያለው የጥፋት ርኩሰት፣ ታላቁ መከራ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ለሰው ልጅ የምልክቱ መገለጥ፣ የበለሲቱ ዛፍ ምሳሌ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣቱ ማረጋገጫዎች፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት ተዘጋጅተው ስለመጠበቅ ዝግጅት፣ የባሪያውና የአለቃ ምሳሌ ናቸው ( ማቴ ፳፬፥፩-፶፩)። የክርስቲያኖች ቁጥር እያነሰ መምጣት፣ የአብያተ ክርስቲያናት መዘጋት፣ ሰውን ሰው የሚያሰኘዉን ክብርና ሞገስ ትቶ በግብሩ እንስሳትን ሲመስል፣ የቅድስና ሕይወት ሲጠላና ሲናቅ፤ በአንጻሩ ደግሞ የሰው ልጅ ለረከሰው ለዚህ ዓለም ምኞትና ፈቃድ ሲገዛ ስናይ የዚህ ዓለም ፍጻሜ ጊዜው እየደረሰ መሆኑን ዐውቀን፤ ኖኅ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ቢኖርም ራሱን በቅድስና ጠብቆ እንደኖረ (ዘፍ.፮-፰)፤ ሎጥም እንዲሁ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ሲኖር በእነርሱ ኃጢአት እንዳልተባበረ (ዘፍ. ፲፱) ከዚህ ዓለም ክፉ ሥራ ተለይተን ራሳችንን በቅድስና በመጠበቅ መጋደል አለብን። ዓለሙ ስለ እምነታችን ቢጠላንም እኛም ስለ ክፉ ሥራዉ ንቀነው መኖር የግድ መሆኑን እንወቅ እንጂ ስለ እምነት፣ ስለ ቅድስናም ከዓለም በጎ ነገር መጠበቅ የለብንም። በተለያዩ ሁኔታዎች የሚደርሱብንን ፈተናዎች ሁሉ በትዕግሥት እንቀበላቸዉ እንጂ በማማረር አንዘን፤ ምክንያቱም ስለ ስሜ በዓለም ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ ተብለናልና። በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ቦታዎች፣ ሁኔታዎች ልንሆን እንችላለን። ግን ምን ማድረግ ይገባናል ? ተዘጋጅተን መጠበቅ!
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ወቅቶችና ሀገራት ብዙ ሐሰተኛ ክርስቶሶች እንደሚነሡ ተናግሯል። የጌታችን ቃል ሳይፈጸም አይቀርምና ከዚህ ቀደም ብዙ ሰዎች «እኔ ክርስቶስ ነኝ» በማለት ተነሥተው ነበር። በዮሐንስ ራእይ ላይ ዋናው አውሬ ተብሎ የተጠቀሰውና በቅዱስ ጳውሎስ «የዐመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ» የተባለው ብዙ ጥፋትና መከራ የሚያደርሰው ባለ 666 ዓ.ም (ስድስት ስድሳ ስድስት) መለያ ምልክቱ ሐሰተኛ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ብዙ ሐሰተኞች ክርስቶሶች ተነሥተዋል። በእውነተኛው ንጉሥ ክርስቶስ ዳግም መምጣት የሚደመሰሰው ሐሳዊ መሲሕ የመጨረሻውና ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚወጋ የታላቁ መከራ ፈጻሚና አስፈጻሚ ይሆናል (ራእ ፲፫፥፭)። ጌታችን እስኪመጣ ድረስ እንዳንሰናከል አስቀድሞ «ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ … በዚያን ጊዜ ማንም እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ» ሲል ያስጠነቀቀን ለዚህ ነው።
በሀገራችንም ኢትዮጵያም በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንገሥት «እኔ ክርስቶስ ነኝ» የሚል ሐሳዊ (ሐሰተኛ) ክርስቶስ ተነሥቶ እንደነበር በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቧል። ይህ ሐሳዊ ልክ እንደ እውነተኛው ክርስቶስ ፲፪ ሐዋርያት፣ ፸፪ አርድእትና ፴፮ ቅዱሳት አንስትን አስከትሎ ክርስቶስ እንደሆነ በመናገር በየሥፍራው ሲንቀሳቀስ ንጉሡ አስቀርበው «አንተ ማን ነህ?» ቢሉት በድፍረት «እኔ ክርስቶስ ነኝ» አላቸው። ንጉሡም «ክርስቶስማ ከድንግል ማርያም ተወልዶ አስተምሮ፣ ተሰቅሎ፣ ዓለምን አድኖ ከሞት ተንሥቶ ዐርጓል፤ ዳግም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል፤ አንተ ግን ማነህ?» አሉት፤ እርሱ ግን «አዎ ትክክል ነው። ከዚህ ቀደም ከቤተ እሥራኤል ከምትሆን ከድንግል ማርያም ተወልጄ፣ አስተምሬ፣ ተሰቅየ፣ ሙቼ፣ ተነሥቼ ዐርጌ ነበር፤ አሁን ድግሞ ጥቁሮች አፍሪካውያን ባይታወር አደረገን እንዳይሉኝ ከእናቴ ከድንግል መርዐተ ወንጌል ለጥቁሮቹ ዳግም ተወልጄ ነው» አላቸው። ንጉሡም «ሰይጣን በሰው እያደረ እንዴት ይጫወታል» ብለው በሰይፍ አስቀጡት፤ ተካታዮቹም ተበተኑ ይባላል።
ጌታችን ለሐዋርያቱ ስለ ዳግም ምጽአቱ ብዙ ምልክቶች ነግሯቸዋል። ከምልክቶቹ መካካል አንዱ ጦርነት ነው። ጦርነት ቀደምት የነበረ፣ በአሁኑ ዘመን በብዛት የተከሰተ ነገር ግን በተለይ በዚህ ጊዜ በብዙ ሀገራት፣ በኛ ሀገረ ጭምር እየተካሄድ ነው፡፡ ጦርነት በቀደምት ዘመናት ሴቶችን፣ አቅመ ደካማ ሽማግሌዎችንና ሕፃናትን ለእልቂትና ለጥፋት የማያጋልጥ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ጦርነት ማንንም የማይለይ፣ ለማንም የማይራራ፣ የሁሉን ደም የሚያፈስና እጅግ አስከፊ ሆኗል። ይህንንም ጌታችን የዳግም ምጽአቱን ምልክት ለጠየቁት ለደቀ መዛሙርቱ ሁለተኛ ምልክት አድርጎ «ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና» ሲል ተናግሯል። (ማቴ.፳፬፥፮)
ሌላውና አሳዛኙ ጉዳይ የፍቅር መቀዝቀዝ ነው፤ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነውና የሰው ልጅ ፍቅርን ማጣት የለበትም። አሁንም «ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች» የሚለው ትንቢት እንዳይፈጸምብን ፍቅርን መንከባከብ፣ ማልማትና ማስፋት ይገባል። (ማቴ.፳፬፥፲፪)። ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው፤ ፍቅር የመልካምና በጎ ነገር ሁሉ መገኛና ምንጭ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ቤተመቅደስ አድርጎ ሲያከብረን ጠላት ዲያብሎስ ደግሞ ይህንን ቤተመቅደስ ለማፍረስ ሁሌም ሩጫ ላይ ነው፤ ስለዚህም ሁልጊዜም በፍቅር መኖር ይገባናል።
የወንጌል ለዓለም መዳረስ ለደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽአቱ ምልክቶች ሁነው ከተሰጡት አንዱ ነው። በፍርድ ቀን በክርስቶስ አምኖ እና እምነቱን በሥራ ገልጾ ስለመኖር ሲጠየቅ «አልሰማሁም፤ አላየሁም፤ አላወኩም» የሚል ከኃጥአን ጋር ይፈረድበታል፤ «ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል» ተብሎ እንደተነገረው በሁሉም ቤት ወንጌል ይሰበካል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፲፪)። በመሆኑም በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዕለት «ንዑ ኀቤየ ቡሩካኑ ለአቡየ ትረሱ መንግሥተ ሰማያት ዘድልው ለክሙ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም [እናንተ የአባቴ ቡሩካን ኑ፥ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ]» እንድንባል ቅዱስ ቃሉን ሰምተን፣ አምነንና ታምነን እስከ መጨረሻው በሕገ እግዚአብሔር መመራትና በበጎ ምግባር በቅድስና ሕይወት ልንኖር ይገባል፡፡ (ማቴ.፳፭፥፴፬)
የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም እና ለአርዓያነት በተገለጠ ጊዜ አመጣጡ በአጭር ቁመት እና በጠባብ ደረት ተወስኖ በትሕትና ነበር። ዳግመኛ የሚመጣው ግን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ነው። ስለዚህ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ብሎ አስተማረን። ያቺን ቀን ከእርሱ በቀር የሚያውቃት የለም። በኖኅ ዘመን እንደነበረው የእርሱም መምጣት እንደዚያ ይሆናል። ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃና ቤቱን በጠበቀ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወው ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። ይህ ቀን ስለማይታወቅ ሁል ጊዜ በንስሐ እና በሥጋ ወደሙ ተዘጋጅተን ልንኖር ይገባናል። ቅዱስ ጴጥሮስ የጌታችን ምጽአት የሚዘገይ እንዳልሆነ ሲያስረዳ «ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል (፪ኛ ጴጥ ፫፥፱)» ብሏል። እስከመጨረሻው የጸና ይድናልና እስከመጨረሻው ጽኑ። ለመከራ አሳልፈው ሲሰጧችሁ፣ ሲገድሏችሁ፣ ስለ ስሜም የተጠላችሁ ስትሆኑ በእምነታችሁ ጽኑ። ብዙዎች ሲሰናከሉ፣ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ሲሰጣጡ፣ ከአመጻም ብዛት የተነሳ ፍቅር ስትቀዘቅዝ በእምነታችሁ ጽኑ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «በጊዜውም ያለጊዜውም ጽና» ያለው ለዚህ ነው (፪ኛ ጢሞ ፬፥፪)። በዚህ ወቅት መከራን መታገስ፣ አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ መሥዋዕትነትን በመክፈል ጽናትን ማረጋገጥ ይገባል። እስከ መጨረሻው በጽድቅ አገልግሎት የሚጸና በጌታ ምጽዓት የክብር ትንሣኤ ይነሣልና።
ከበለስ ምሳሌነት ወስደን እንድንማር ሌላ አስደናቂ ሥነ ፍጥረታዊ ምሳሌ ጌታችን ሰጥቶናል። «ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ» ማቴ. ፳፬፥፴፪። በመጀመርያ የበለስን ነገር መናገር ይገባል። በለስ በክረምት የምትደርቅ በበጋ የምትለመልም ወይም ክረምት ከማይስማማቸው ዕፅዋት አንዷ በመሆኗ ስትለመልም የክረምቱ ጊዜ ማለፉን የበጋ ጊዜ መተካቱን ሰው እሷን ተመልክቶ መረዳት ይችላል። እንደዚህም ሁሉ እናንተም ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች ሁሉ ሲከሠቱ የመጨረሻው የፍርድ ቀን፣ የዓለም ፍጻሜና የጌታ ዳግም መምጣት ጊዘው እንደቀረበ ዕወቁ። ቅርበቱም የደጃችሁን ያህል እንደሆነ ዕወቁ ብሎ የጊዜ ማወቂያ ምሳሌ አደርጎ ነው የጠቃሳት።
የደብረ ዘይት ዕለት ጻድቃን የሚናፍቋት የተስፋ መንግሥተ ሰማያት ዕለት ናት። ተስፋ ብርሃናዊ መገስገሻ መንገድ ናት። ተስፋ የማይታየውን አጉልታ፣ ሩቁን አቅርባ የምታሳይ መነጽር፣ መከራውን ደስታ የምታደርግ ሐሴት፣ ደካማውን የምታበረታ ኃይል ናት። የሰው ልጅ የተስፋ መንግሥት ሰማያትን ፍጹም ደስታ፣ የቀቢጸ ተስፋ ገሀነመ እሳትን ፍጹም ሥቃይ ቢያውቅ፣ ቢረዳው ኖሮ በዚህ ዓለም ይድላኝ ሳይል ኑሮው በመንኖ ጥሪት ይሆን ነበር። «ወምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኲሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ሃጉለ። ወምንተ እምወሀበ ሰብእ ቤዛሀ ለነፍሱ [ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?]» (ማቴ ፲፮፥፳፮ ) እንዲል። ተስፋ የምናደርጋት መንግሥተ ሰማያት የእግዚአብሔር መንግሥት ናት። እርሷም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያዘጋጃት፣ የእግዚአብሔር ምሕረቱና ጥበቡ የሚገለጽባት፣ በትንሣኤ ዘጉባኤ ፍርድ ቀን በእርሱ ያመኑ የሚገቡባት የእግዚአብሔር ቤት ናት። «በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ … እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።» እንዳል ጌታ ማቴ ፲፬፥፩።
በአጠቃላይ ደብረ ዘይት ሁለት ተቃራኒ ነገሮች የሚፈጽሙበትን የነገረ ዳግም ምጽአት ሁኔታን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምንማርበት የዐቢይ ጾም ሳምንት ነው። ይኸውም ትንሣኤ ዘለክብር እና ትንሳኤ ዘለሀሳር ነው። አንዱ ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆንበት ሌላው ከሰይጣን ጋር ኑሮው የሚወሰንበት፣ አንዱ መንግሥተ ሰማያትን የሚወርስበት ሌላው ገሀነመ እሳት የሚገባበት፣ አንዱ የሚደሰትበት ፣ ሌላው ዋይታ የሚያሰማበት፣ የበረከትና የመርገም ቀን፣ የተስፋና ተስፋ የመቁረጥ ቀን፣ የደስታና የጭንቅ ቀን፣ የእልልታና የዋይታ ቀን፣ አንዱ ሌላውን የማያድንበት፣ እናት ልጄን የማትልበት፣ ልጅ እናቴን የማይልበት፣ ባልና ሚስት የሚለያዩበት፣ጓደኞች ዳግም የማይገናኙበት፣ ኃጥእ ከጻድቅ መተያየት የሚያበቁበት የመጨረሻ እለት ዳግም ምጽአት ናት።
ማጠቃለያ
የእግዚአብሔር ጥሪ ሁሉም የአዳም ዘር መንግሥቱን እንዲወርሱ ቢሆንም የሰይጣንን ወጥመድና አሸከላ ሁሉ አልፈው፤ በሐሰተኞች ምትሐታዊ ተአምራት ሳይሳቡና ሳይሰናከሉ እስከ መጨረሻው ጽንተው በዚያ በዳግመኛ ልደት እና የመጨረሻ የዋጋ ቀን በጌታቸው ቀኝ የሚቁሙ የታደሉ ናቸው። በመንፈሳዊ ሕይወትም ተዘጋጅቶ መኖር ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ጉዳይ ሲሆን የሚከተሉትን ነጥቦችም በውስጡ ይይዛል፦ ድልዋኒክሙ ንበሩ [ተዘጋጅታችሁ ኑሩ] ( ማቴ፳፬፥፵፬)
ሀ. በጽኑ እምነት መኖር፦
ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣበት ዋና ዓላማ እኛ በእርሱ ቤዛነት በፍጹም ልባችን አምነን ከኩነኔ እንድን ዘንድ ነው። ለዚህም ነው “እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም” (ሮሜ ፰፥፩) የሚለው። በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ማለት በእርሱ አምኖ በትክክለኛው መንፈሳዊ ሕይወት መኖር ማለት ነው። እግዚአብሔርን የምናስደስተው በእምነት ስንኖር ነው። እምነት ከሌለን እርሱን ደስ ማሰኘት አንችልም፤ ለዚህም ነው “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም” (ዕብ ፲፩፥፮) ተብሎ በቅዱሱ መጽሐፍ የተጻፈው። ስለሆነም በጽኑ እምነት መኖር ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው።
ለ. በንስሐ ሕይወት መመላለስ፦
ሁላችንም በዚች ፈታኝ ዓለም ላይ ስንኖር በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ ኃጢአትን እንሠራለን። እግዚአብሔር ደግሞ በባሕርይው ቅዱስ ስለሆነ ኃጢአትን ይጸየፋል። ስለሆነም ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ ዘወትር በንስሐ ሕይወት በመመላለስ በቅድስና ሕይወት መኖር ያስፈልጋል። “ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” (፩ኛዮሐ ፩፥፯) ስለሚል ቃሉ እርሱ መድኃኔዓለም በዕለተ አርብ ባፈሰሰው ደሙ እንዲያነጻን “ዘወትር ጠዋት ማታ ያለማቋረጥ ባፈሰስከው ደምህ ይቅር በለን፤ አንጻን ልንለው” ይገባል።
ሐ. ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን መቀበል፦
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን እንድንቀበል አዞናል። ስለሆነም ሥርዓተ ቅዳሴውን እየተከታተልን ብቻ ወደ ቤታችን መሄድ ሳይሆን ንስሐ በመግባት ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን መቀበል ይኖርብናል። “ዘበልዐ ሥጋየ ወሰትየ ደምየ ቦ ሕይወት ዘለዓለም ወአነ አነሥኦ በደኃሪት ዕለት [ሥጋየን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ህይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው እለት አስነሣዋለሁ]” ዮሐ ፮፥፶፬
መ. በፍቅር ሕይወት መመላለስ፦
ፍቅር የእግዚአብሔር ባሕርይ ነው፤ እኛም በፍቅር እንድንኖር አዞናል። ፍቅር በብዙ ሰዎች ዘንድ እየቀዘቀዘች ባለችበት ወቅት በፍቅር መኖር ታላቅ መታደል መሆኑን ተረድተን በፍቅር ልንኖር ይገባል። እግዚአብሔር አምላካችንን በፍጹም ልባችን በመውደድ እንዲሁም አጠገባችን ያለውን ወንድማችንን በመውደድ ፍቅርን በሕይወት ልንኖረው ይገባል። “በፍቅሬ ኑሩ” (ዮሐ ፲፭፥፱) የሚለውን ትእዛዝ ፈጽመን ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ በሀገራችንም ሆነ በዓለም ላይ የንጹሐን ደም አይፈስም ነበር። ዘወትር በፍቅር ሕይወት በመመላለስ ጥላቻ እንዲወገድ የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ያስፈልጋል።
ሠ. በተስፋ መኖር፦
በመንፈሳዊው ዓለም በተስፋ መኖር ማለት በተረጋገጠና እውነተኛ በሆነ ተስፋ መኖር ማለት ነው። መንፈሳዊው ተስፋ እንደ ምድራዊው ተስፋ ይሆናል ወይም አይሆንም በሚሉ ሁለት ሃሳቦች የተከፈለ አይደለም። ፈተናዎችና መከራዎች እንኳን አብዝተው ሊያስጨንቁን ቢሞክሩ ” እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ ፲፩፥፳፰) ብሎ ጌታችን የተናገረውን በማሰብና በመረዳት በእርሱ እርፍ እያልን በተስፋ መኖር ይገባናል። በተስፋ መኖር በምድራዊውና በሚጠፋው ነገር እንዳንወስድ ያደረግናል። በቀኙ ለመቆም እንዲያበቃን የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን የርኅርኂተ ኅሊና የድንግል ማርያም አማላጅነት፣የቅዱሳን ሁሉ ረድኤት አይለየን፤ አሜን።
ጸሎት
አቤቱ አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፣ ዳግም በግርማ መለኮት ፣ በክበበ ትስብእት ፣ በይባቤ መላእክት በምትመጣበት ጊዜ የእግዚአብሔር በግ የሆንህ አንተ በመስቀል ላይ መሥዋዕት ስትሆን በኀዘን ዕንባ ስለቆሰለች እናትህ ብለህ ማረን ፣ በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ ፣ ክርስቶስ ሆይ ስለ ድንግል ማርያም ብለህ ይቅር በለን ፣ አስበን ። በመጨረሻም እንዲህ እያልን እንዘምር “ደምረነ ምስለ ኵሎሙ ቅዱሳን ምስለ እለ ገብሩ ፈቃደከ እለ እምዓለም አሥመሩከ/፪/፣ እለ ዐቀቡ በንጽሕ ሥርዓተ ቤትከ ፣ ወእለሰበኩ በሠናይ/፪/ በሠናይ ዜናከ”። አሜን!
ማጣቀሻዎች/References/
- ወንጌል ቅዱስ አንድምታ
- መዝሙረ ዳዊት አንድምታ
- ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
- የማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜ በቀሲስ ታድሮስ ማላቲ
- የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገፅ
- መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ 1972 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ 215
- https://www.britannica.com/place/Mount-of-Olives
- ዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ፤ 12ኛ ዓመት ቁጥር 5፤ መጋቢት 30 ቀን 1949 ዓ.ም፤ ገጽ 1፡
- https://nohamin.blogspot.com/2016/04/blog-post.html
- https://www.ethiopianorthodox.org
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/በሰ/ት/ቤቶች/ ማ/መ/ማ/ቅ ሩቅ ምሥራቅ ማእከል ሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ክፍል
መጋቢት ፲፬ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
ቻይና