የሚከራከርልን መምህር
መምህር ዘየዐሲ፥ መምህር ዘይትቃወም ለነ (የሚሰጥ መምህር፥ የሚከራከርልን መምህር)
ጌታችን ዋጋ የሚሰጥ መምህር ነው። ከዚህ ዓለም መምህር ሲለይ የሚሰጥ መምህር አለ፤ የዚህ ዓለም መምህር ሲያስተምር ውሎ “ይደልዎ አስቦ ለዘይትቀነይ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል”[ሉቃ. ፲÷፯] ይላል ብሎ ዋጋ ይቀበላል እንጂ አይሰጥም። እርሱ ግን ይሰጣል እንጂ አይቀበልምና አንድም ሃይማኖት አስይዞ ምግባር አሠርቶ የዚያን ዋጋ የሚሰጥ መምህር እርሱ ነው።
“እስመ ከመ መኰንን ይሜህሮሙ፤ እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና” እንዲል ንጉሡ እንዲህ አለ እንደሚሉ እንደ መኳንንት ያይደለ፣ እግዚአብሔር እንዲህ አለ እንደሚሉ እንደ ዐበይት ነቢያት ያይደለ፣ ሙሴ እንዲህ አለ ሳሙኤል እንዲህ አለ እንደሚሉ እንደ ደቂቀ ነቢያት ያይደለ፣ ከሚያስተምሩት አንዷን እንኳን እንደማይፈጽሙት እንደ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ያይደለ ከባሕርይው በርኅራኄ በጌትነት በግርማ የሚያስተምር፥ ሲያስተምርም የጎደለበትን እየሞላ (እጅ ለሌለው እጅ፥ እግር ለሌለው እግር፣ ጆሮ ለሌለው ጆሮ፣ ዓይን ለሌለው ዓይን ሰጥቶ፣ ላልተረዳው ገልጦና አብራርቶ፣ ወዲህም በተግባር አሳይቶ) ያስተምራልና።”
የባሕርይ አባቱ አብ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምዕዎ፤ የምወደው የማፈቅረው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” ብሎ የመሰከረለት መምህር [ማቴ. ፫÷፲፯፣ ማቴ. ፲፯÷፭]፣ በሥጋ የወለደችው እናቱ እግዝእትነ ማርያም “ኩሎ ዘይቤለክሙ ግበሩ፤ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” ብላ የምታሳስብለት መምህር [ዮሐ. ፪÷፭]፣ ሥራውን ፈጽሞ ለባሕርይ አባቱ “አባ ሰባሕኩከ ፈጺምየ ግብረ ዘወሀብከኒ፤ አባት ሆይ ላደርገው ዘንድ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ አከበርኩህ። ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው።” [ዮሐ. ፲፯] ብሎ ሥራውን ፈጽሞ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ፣ መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም የተገዙለት፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠ መምህረ ሐዋርያት፣ መምህረ ሰብአ አርድእት፣ መምህረ ቅዱሳት አንስት ወመምህረ ኩሉ ክርስቶስ ነው። [፩ኛ. ጢሞ. ፫÷፲፮፣ ፩ኛ. ጴጥ. ፫÷፳፪]
“ወሰበከ ሎሙ ግዕዛነ ለእለ ሙቅሕታ ትነብር ነፍሶሙ፤ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ሰበከላቸው” እንዲል [፩ኛ ጴጥ. ፫÷፲፱] ኃዳፌ ነፍሳት፥ የነፍሳት መምህር በመስቀል ላይ ሆኖ ነፃነትን የሚሰብክ፣ ተሰቅሎ መከራን ተቀብሎ በመስቀል ትርክዛው እየቀዘፈ ነፍሳትን ከባሕረ ሲኦል ከጭንቅ የሚያወጣ መምህር ክርስቶስ ነው። በዓለም ላይ ሠልጥኖ፣ በሐሰት ትምህርት ገኖ ሕዝብ አሕዛብን ሲያስት የነበረን ሰባኬ ሐሰት፣ ርእሰ ዓመፃ ወአቡሃ ለሐሰት [ዮሐ. ፰÷፵፬] ዲያብሎስን በእውነተኛ ትምህርቱ ድል ያደረገ መምህር ክርስቶስ ነው። ለተጨነቁት መጽናናትን [ኢሳ. ፷፩÷፪]፣ ለደከሙት ዕረፍትን ኃይልና ብርታትን [ዮዲ. ፱÷፲፩፣ ማቴ. ፲፩÷፳፰]፣ ላዘኑት መጽናናትን [ኤር. ፴፩÷፲፫፣ ፪ኛ. ቆሮ. ፯÷፮ ]፣ መንገድ ለጠፋባቸው ብርሃንን [ዮሐ. ፰÷፲፪]፣ ለተራቡት ለተጠሙት የሕይወት ምግብና መጠጥን [ዮሐ. ፮÷፵፰፣ ፯÷፴፰]፣ ለበጎቹ ራሱን ቤዛ አድርጎ [ዮሐ. ፲÷፲፩] የሚሰጥ መምህር ክርስቶስ ነው።
መምህር ዘይትቃወም ለነ አለ የሚከራከርልን መምህር እርሱ ነውና። በ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት አድሮ አርዮስን በ፻፶ው ሊቃውንት አድሮ መቅዶንዮስን በ፪፻ው ሊቃውንት አድሮ ንስጥሮስን እስከ ዕለተ ምጽአት በሚነሡ መምህራን አድሮ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ የሚነሡ መናፍቃንን የሚከራከርልን ተከራክሮም የሚረታልን መምህር እርሱ ነው። “ዖድኩ ምድረ ወኩሎ ዓለመ፥ ኢረከብኩ እግዚኦ ስመ ጥዑመ፥ ዘእንበለ ስመ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ አቤቱ ምድርንና ዓለሙን ሁሉ ዞርሁ ያለ ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በቀር ጣፋጭ ስምን አላገኘሁም፤ እግዚአብሔርን ያገለገሉ የሰው ወገኖች ሁሉ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኩል ነው። …..ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ወገን ሁሉ በአንድነት እግዚአብሔርነትህን ፈጽሞ ያመሰግናል። የጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከማር ወለላና ከሦከር (ሥኳር) ይጥማል። ማርና ወተት በሚበሉበት ጊዜ ይጠገባሉ የጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ግን አይጠገብም። የጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስን ስም በምጠራ ጊዜ ከንፈሮቼ ማርን ያንጠበጥባሉ።…ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከኃጢአት ወገን የሚሆን የክፋት መንፈስን ሁሉ ከእኔ አስወግድ። ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አንተን ደስ የማያሰኝህን ሐሳብ ሁሉ ከኔ ታርቅ ዘንድ ወዳንተ እለምናለሁ ከአንተም እሻለሁ። መዳኛችን በሚሆን በዚህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ክርስቲያኖች ሁላችሁም ፈጽሞ ደስ ይበላችሁ።”
ሰላም ለጉርዔከ በጽምአ ፍቅረ ሰብእ ሐማሚ፥
እስከ ስቴ ሐሞት ጥዕመ ወዘወይነ ትፍሥሕት ከራሚ፥
ኢየሱስ ክርስቶስ መምህረ ጳውሎስ ዘብንያሚ፥
እመ ነሥአ ማኅተመ ጸጋ እንዘ ስመከ ይሰሚ፥
አልቦ አይሁድ ወአልቦ አረሚ።
የሐሞት መጠጥንና የከረመ የደስታ የወይን ጠጅን እስከመቅመስ ደርሶ በሰው ልጅ ፍቅር መጠማት የታመመ ለሆነ ጎሮሮህ ሰላምታ ይገባል። የብንያም ነገድ የሚሆን የጳውሎስ መምህር ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ስምህን ጠርቶ የጸጋ ልጅነት የሚሆን ማኅተመ ጥምቀትን ከተቀበለ አይሁዳዊም አረማዊም የሚባል የለም። [መልክአ ኢየሱስ]
ሃይማኖተ አበው ምዕ. ፫÷፪ አንድምታ ትርጓሜ፣ ማቴ. ፯÷፳፱ አንድምታ ትርጓሜ፣ መጽሐፈ ግብረ ሕማማት ገጽ ፲፩~፲፪