ሆሳዕና 🌿🌿🌿

(በመምህር ኃይለ ማርያም ላቀው)

ሆሳዕና የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ሆሼዕናህ የሚል ሲሆን ትርጉሙም እባክህ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው (መዝ.117፡25-26)። የሆሳዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሳዕና በአርያም በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ በዓሉም ሆሳዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው መዝሙር ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ይህ ዕለት የጸበርት እሑድ/ Palm Sunday/ ይባላል፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫ ሆኖ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ይኸውም ሣራ የወላድነት ዕድሜዋን ጨርሳ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ የጎበኛትን አምላክ አመስግነዋል፡፡ እስራኤል ከአስከፊው የግብፃውያን አገዛዝ ተላቀው ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገሩ የተሰማቸውን እጥፍ ድርብ ደስታ በገለጡ ጊዜ፣ እንዲሁም ዮዲት የተባለች ንግሥተ እስራኤል ሆሎፎርኒስ የተባለ አላዊ ንጉሥን ድል ባደረገች ጊዜ ቤተ እስራኤል እንደ ሰንደቅ ዓለማ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ አደባባይ ወጥተው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በዘመነ ሐዲስም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከሲኦል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወደ ዙፋን መስቀሉ /ሉቃ.22፤18/ በተጓዘ ጊዜ ሕፃናት እና አእሩግ ነጻ የሚወጡበት ቀን መድረሱን እነርሱ ሳያውቁ እግዚአብሔር ባወቀ ዘንባባ በመያዝ ዘምረዋል፡፡ እስራኤል ዘንባባ በመያዝ እንዳመሰገኑት እኛም እስራኤል ዘነፍስ ዕለቱን ዘንባባ በግንባራችን በማሰር በዓሉን በየዓመቱ እያስታወስን እናከብራለን፡፡ በዚህ ዕለት ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝቡ ይታደላል፡፡

ሕፃናትና አእሩግ “ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል” እያሉ ዘምረዋል፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲሆን በሌላ በኩል የነበረው አቀባበል ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ሥርዓተ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ ጌታችንም መልሶ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ ሲል መልሶላቸዋል፡፡ ቅናት አቅላቸውን ያሳታቸው ፈሪሳውያንም የዋህ የሆነው ሕዝብ ምስጋና ወደ ጥላቻ እንዲለወጥ አድርገዋል፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው በዕለተ ሆሳዕና እሑድ ዘንባባ ይዘው የዘመሩለትን ጌታ ዓርብ ይሰቀል ዘንድ ይገባል ብለዋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚህም በነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል (ዘካ.9፡9፤ ማቴ.21፡4፤ ማር.11፡1-10፤ ሉቃ.19፡28-40፤ ዮሐ.12፤15)፡፡ ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲሆንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም እውነተኛ የኅሊና ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲለን በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ሕይወታችን ተጉዟል፡፡

መላእክት በዕለተ ልደቱ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል በምድር ሰላም ለሰው ሁሉ ይሁን/ሉቃ.2፡13/ እያሉ የዘመሩለት የሰላም ባለቤት ነው፡፡ በመዋዕለ ትምህርቱም ሰላሜን እሰጣችኋለሁ/ዮሐ.14፡27/ ብሎ እንዳስተማረ ያን ሰላም የሚሰጥበትን ዕለት መቅረቡን ለማመልከት ነው፡፡ በሌላ በኩልም በአህያ ጀርባ መቀመጡ ኅቡዕ ምሥጢር አለው፡ በአህያ ጀርባ የተቀመጠ ሰው ሌላውን አሳድዶ አይዝም፣ እርሱም ሮጦ አያመልጥም፡፡ በዚህም ጌታችን በእምነት ለሚፈልጉት የሚገኝ ቅርብ ሲሆን በእምነት ለማይፈልጉት ግን የማይገኝ መሆኑን አስተምሯል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ፀሐይ ዕድሜያችን ሳትጠልቅ በእምነት እንፈልገው፡፡ የአህያን ጀርባ ያልናቀ ጌታችን ትሑት ሰብእና እና የተሰበረ ልቡና ወዳለው ሰው ዘወትር ይጓዛል፣ የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ አይንቅም (ኢሳ.66፡2፤ መዝ.50፡17)፡፡ በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሃት ጸሎተ አስተስርዮ ስለማይፈጸም ጸሎተ ፍትሃትና አስተስርዮ የሚደረገው በዚሁ ዕለት ነው።

በሆሣዕና ዕለት ዘንባባ በእጃችን እንደ ቀለበት ማሰራችን የምን ምሳሌ ነው?
✍️ጌታ ለአዳም የሰጠው ቃል ኪዳን ለማስታወስ፦ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድነሃለሁ ያለውን የተስፋ ቃል ለማስታወስ፡፡
✍️ጌታ ለእመቤታችን የገባላትን ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው።
✍️ጌታ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው።
✍️ ጌታ አዳምን ከሰይጣን ግዛት ነጻ እንዳወጣው ሁሉ እኛም ከሰይጣን ግዛት፣ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ፣ ከክፋት፣ ከኃጢአት አውጣን ማረን ለንስኃ ሞት አብቃን ከቤትህ አትለየን እንደ ቸርነትህ ይቅር በለን ስንል ለጌታ ዳግም ላናጠፋ ቃል የምንገባበት ነው፡፡

ጌታችን በዕለተ ሆሳዕና ለምን በፈረስ ወይም በበቅሎ ላይ አልተቀመጠም?
ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል”(ትንቢተ ዘካርያስ 9:9)።

በአህያ መቀመጡ፦ ትሕትናን ለማስተማር፣ የሰላም ዘመን ነው ሲል፣ ለፈለጉኝ ሁሉ የቅርብ አምላክ ነኝ ሲል፣ በንጽሕና በየዋህነት ለሚኖሩ ምዕመናን አድሬባቸው እኖራለሁ ሲል፡፡አህያዎች ትሑታን ናቸው ረጋ ብለው ነው የሚሄዱት፤ በቀላሉ ትወጣበታለህ፤ በቀላሉ ትይዘዋለህ፤ እንደፈለክም ታዝዋለህ፤ ጌታችን እኔም ትሑት ነኝ ሲል ነው።

ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ዘንባባ የመነጠፉ ምሥጢር የምን ምሳሌ ነው?
አብርሃም ይሐስቅ በተወለደ ጊዜ ደስ ብሎት ዘንባባ ይዞ እግዚአብሔርን አመስግኗል፡፡ ዘንባባ ደርቆ እንደገና ሕይወት ይዘራል። የደረቀ የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ ዘንባባ የሰላም ምልክት ነው፡- የሰላም አምላክ ነህ ሲሉ ነው። ዘንባባ የደስታ መግለጫ ነው፡- አንተ ደስ የምታሰኝ ኃዘናችንንም የምታርቅልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ ዘንባባ እሾሃማ ነው፡- አንተ ሕያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ ዘንባባ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል እንጂ፡፡ ጌታም አንተ ባሕርይህ የማይመረመር ነው ሲሉ ነው፡፡

ሕዝቡ ልብሳቸውን ማንጠፋቸው ለክብሩ መግለጫ ነው፡፡ ልብስ አይቆርቁርም ጌታ የማትቆረቁር ሕግ ሠራሁላችሁ ሲል፡፡ ሌሎችም ሦስት አይነት ቅጠል አነጠፉለት፦ የዘንባባ ዛፍ፣ የቴመር ዛፍ እና የወይራ ዛፍ ቅጠል፡፡ የዘንባባ ዛፍ፦ እሾሀማ ነው። ትእምርተ ኃይል፣ ትእምርተ መዊዕ አለህ ሲሉ ነው፡፡ የቴምር ዛፍ፦ ቴምር ልዑል ነው። ልዑለ ባሕርይ ነህ ሲሉ፤ ፍሬው አንድ ነው – ዋህደ ባሕርይ ነህ ሲሉ፤ ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው – ባሕርይህ አይመመረመርም ሲሉ፡፡ የወይራ ዛፍ ጽኑዕ ነው – ጽኑዓ ባሕርይ ነህ ሲሉ፡፡ ብሩህ ነው ብሩሃ ባሕርይ ነህ ሲሉ፡፡ ዘይት መሥዋዕት ይሆናል – አንተም መሥዋዕት ትሆናለህ ሲሉ፡፡

ታላቋ አህያ በምን ትመሳለለች? ውርንጭላዋስ? ታላቋ አህያ የኦሪት ምሳሌ ናት፡፡ ታላቋ አህያ ሸክም የለመደች ናት፤ ሕገ ኦሪትም የተለመደች ሕግ ናትና፡፡ የእስራኤል ምሳሌ ነው፤ ታላቋ አህያ ሸክም እንደለመደች ሁሉ እስራኤልም ሕግ ለመፈጸም በሕግ ለመራመድ የለመዱ ናቸው፡፡ የአዳም ምሳሌ ነው፡- አዳም ሸክም የበዛበት ነበርና፡፡ የፍጹማን ምሳሌ ናት፡፡ ውርጭላዋ በሕገ ወንጌል ትመሰላለች። ምክንያቱም ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰረታት የሠራት አዲሷ ህግ ናትና። በአሕዛብ ትመሰላለች፡- ትንሿ አህያ ሸክም የለመደች አይደለችም እንዲሁም አሕዛብም ሕግን ለመቀበል የለመዱ አይደሉም፡፡ ለሕግ አዲስ ናቸውና፡፡ የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡- የዓለም ሸክም አቅላለችና በእመቤታችን ትመሰለላለች፡፡ እመቤታችን ድኅነተ ምክንያታችን ጌታን የተሸከመች ንጽሕት እንከን የሌላት እናት ናትና፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ያልታሰሩ አህዮች እያሉ ለምን የታሰሩትን መረጠ? አህዮቹ የታሰሩት ሌባ ሰርቆ ነው ያሰራቸው፡፡ ወንበዴ ሰርቆ ነው ያሰራቸው። አህዮቹ ለጌታ ውለታ ሰርተዋል፡፡ ጌታ ሲወለድ አሙቀውታልና ለጌታ ውለታ ልንመልስ ያልቻልንው እኛ ሰዎች ብቻ ነን፡፡ የታሰሩት እዲፈቱ የመረጠበት ምሥጢር፡-እኔ ከኃጢአታችሁ ልፈታችሁ የመጣሁ ነኝ ሲል ነው፡፡ ወንበዴው አህዮቹን ሰርቆ በመንደር እንዳሰራቸው ዲያብሎስም የሰው ልጆችን በኃጢአት ሰንሰለት ከሲኦል መንደር አስሯቸው ነበርና፡፡ ሐዋርያቱ ሲልካቸው ምን ታደርጋላችሁ የሚላችሁ ሰው ቢኖር ጌታቸው ይሻቸዋል በሏቸው አላቸው በተፈጥሮ ጌታቸው ነውና፡፡ ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የሆነ ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ እንደተቀመጠ ሁሉ ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት ዛሬም ያድራል፤ የኅሊና ሰላምን ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ንስሐ ገብተን ጌታችንን ሆሳዕና በአርያም እያልን ልናመሰግነው ይገባል፡፡

ምንጭ፦ ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ መጋቢት/ሚያዝያ 1996 ዓ.ም