ሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ “መኑ ከመ አምላክ፤ ማን እንደ እግዚአብሔር” ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ወንጌላዊው ቅደስ ዮሐንስ በራእዩ “በእግዚአብሔር ፊት የቆሙ ሰባት መላእክትን አየሁ” ብሎ ከተናገረላቸው መላእክት ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ የሰባቱም ሊቃነ መላእክት አለቃ እንዲሆን እግዚአብሔር መርጦ ሹሞታል፡፡
እስራኤላውያን ለ፪፻፲፭ ዓመታት በግብፃውያን ከደረሰባቸው የባርነትና የሥቃይ ዘመናት በኋላ በሊቀ ነቢያት ሙሴ አማካይነት ወደ ምድረ ርስት ሲወጡ ቀን በደመና፣ ሌሊቱን በብርሃን እየመራ ማድረሱን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይነግረናል፡- “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁልህም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ፥ እኔ መልአኬን በፊትህ እልካለሁ። ራስህን ጠብቅ፣ ስማው፣ እምቢም አትበለው፤ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ይቅር አይልምና፡፡” (ዘጸ. ፳፫፥፳-፳፩) እንዲል፡፡
ቅዱስ ሚካኤል ከግብሩ በመነሣት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ በልዩ ልዩ ቅጽል ስያሜዎች ይጠራል፡፡ ከእነዚህም መካከል “መጋቤ ብሉይ፣ መልአከ ኃይል፣ እንዲሁም መልአከ ምክር” ይባላል፡፡ መጋቤ ብሉይ መባሉ በብሉይ ኪዳን ከእግዚአብሔር እየተላከ እስራኤላያንን ቀን በደመና፣ ሌሊቱን በብርሃን እየመራ መና ከሰማይ እያወረደ በመመገቡ፣ መልአከ ኃይል መባሉም እግዚአብሔር በእርሱ አማካይነት ታላላቅ ሥራዎችን በመሥራት ኃይሉን የገለጸ፣ ዲያብሎስን ከነሠራዊቱ ድል ያደረገ በመሆኑ ሲሆን፣ መልአከ ምክር ወይም የእግዚአብሔር የምክሩ አበጋዝ የተባለበት ምክንያት እግዚአብሔርን በምክሩ ይረዳዋል ለማለት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ ለወዳጁ ለቅዱስ ሚካኤል ይገልጽለታል፤ በእርሱም አማካኝነት ይሠራል ለማለት ነው፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በስሙ ለሚማጸኑ ሁሉ ታላላቅ ተአምራትን በማድረግ ከሚደርስባቸው ችግር ሁሉ የሚታደግ መልአከ ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ቅዱስ ሚካኤል ያደረጋቸውን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ተአምራት ቢኖሩም በተለይም በሰኔ ፲፪ ቀን ያደረገውን ተአምራት ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
በእስክንድርያ ሀገር አክላወባጥራ የተባለች ንግሥት የንጉሥ በጥሊሞስ ልጅ ዙሐል በሚባል ኮከብ ስም ያሠራችው ታላቅ ምኵራብ ነበረና በየዓመቱ ሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን በዚያ ምኵራብ ሕዝቡ ተሰብስቦ ታላቅ በዓል ያደርጉ ነበር፡፡ በዚያም ምኵራብ ውስጥ ዙሐል የሚሉት ታላቅ የነሐስ ጣዖት ነበረና በዓሉ በሚከበርበት ዕለት ብዙ ፍሪዳዎችን ያርዱለት ነበር፡፡ ሊቀ ጳጳሱ እለእስክንድሮስ እስከተሾመበት ዘመን ድረስ ለዚያ ጣዖት እንዲህ ሲያደርጉ ኖሩ፡፡
እለእስክንድሮስ በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ እና ቆስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት ስለ ተስፋፋች ያን ጣዖት አባ እለእስክንድሮስ ሊሠብረው ወደደ፡፡ ነገር ግን የሀገሩ ሰዎች “እኛ በዚህ ቦታ ይህን በዓል ማክበርን ለምደናል፡፡ እነሆ ከአንተ በፊት ዐሥራ ስምንት ሊቃነ ጳጳሳት አልፈዋል፤ ይህን ልማዳችንንም አልለወጡብንም” በማለት ተከራከሩት፡፡ አባ እለእስክንድሮስ ግን ገሠፃቸው፤ አስተማራቸውም፡፡
“ይህ ጣዖት የማይጎዳና የማይጠቅም ነው፡፡ እርሱንም የሚያመልክ ሰይጣናትን ያመልካቸዋል፡፡ምክሬንስ ብትሰሙ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ ይህን በዓል እሠራላችኋለሁ፤ ይኸውም ጣዖቱን እንድንሰብረው፣ ምኵራቡንም እንድንባርከውና በከበረ መልአክ በመላእክት አለቃ በሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አድርገን እንድንሰይመው ነው፡፡ እኛም ይህን ታላቅ በዓል እንሠራለን፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነት ያለው ስለ ኾነ ስለ እኛ ይማልዳልና፡፡” ይህንንም ብሎ በዚህ በጎ ምክር አስወደዳቸው፤ እነርሱም ታዘዙለት፡፡
ከዚህም በኋላ ያንን ምኵራብ አድሰው በዚህ የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አደረጉት፡፡ በዚችም ዕለት አከበሩዋት፡፡
እግዚአብሔርን የሚፈራ የከበረ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ይልቁንም በሰኔ እና በኅዳር ወር አብልጦ የሚያከብር አንድ ሰው ነበር፡፡ በጐረቤቱም ርኅራኄ የሌለው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፡፡ ይህን እግዚአብሔርን የሚፈራውን ሰው የከበረ መልአክ የሚካኤልን በዓል በሚያደርግበት ጊዜ ይጠላውና ያቃልለው ነበር፡፡ ከኃላፊው ዓለም ድካምም የሚያርፍበት ጊዜ በደረሰ ጊዜ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ታደርግ ዘንድ ሚስቱን አዘዛት፡፡ ከዚህም በኋላ ዐረፈ፡፡
ሚስቱም ፀንሳ ነበር፡፡ የመውለጃዋ ደርሶ ምጥ በያዛት ጊዜም በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ሆና ጸለየች፡-የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን በአማለጅነቱ ይደርስላት ዘንድ ተማጸነቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በቤቷ ውስጥ ብርሃን በራ፡፡ መልኩ ውብ የኾነ ወንድ ልጅንም ወለደች፡፡ የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን እንዲህ ብሎ ባረከው፡- “ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለጠጋ ገንዘብና ሀብት፣ ጥሪቱንም ዅሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ እግዚአብሔር አዝዟል” አለ፡፡
ባለ ጠጋውም በቤቱ፣ በዐልጋው ላይ ሳለ ጌታ ጆሮውን ከፍቶለት ይህን ነገር ከመልአኩ ሰማ፡፡ ይህንን በሰማ ጊዜ ታላቅ ኀዘን ደረሰበት፡፡ ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመረ፡፡ ምክንያትም አዘጋጅቶ “የሚያገለግለኝ ልጅ ይኾነኝ ዘንድ ልጅሽን ስጪኝ፡፡ እኔም እየመገብኹና እያለበስኹ አሳድገዋለሁ፡፡ ለአንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ” አላት፡፡ ይህንንም ነገር ከባለጠጋው በሰማች ጊዜ ስለ ችግሯ እጅግ ደስ አላት፡፡ ልጅዋንም ሰጠችው፡፡
ባለጠጋውም በልጁ ቁመት ልክ ሣጥን አሠርቶ ሕፃኑን በሣጥኑ ውስጥ አስገብቶ ከዘጋበት በኋላ ወስደው በባሕር ጣሉት፡፡ ለሃያ አንድ ቀናትም ሳጥኑ በባሕሩ ላይ እየተንሳፈፈ ወደ አንድ ወደብ ደረሰ፡፡ በዚያም በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቅ አንድ ሰው ነበርና ሣጥኑን በውኃ ላይ ተንሳፎ አየው፡፡ እርሱም ከባሕሩ አውጥቶ ወደ ቤቱ ወሰደው፡፡ ሳጥኑ በቁልፍ የተቆለፈ ስለነበር ለመክፈት ተቸገረ፡፡ ነገር ግን አንድ አሣ የሚያጠምድ ሰው በማግኘቱ “መረብህን በኔ ስም ጣል፡፡ ለሚያዘው ዓሣ ዋጋውን እሰጥሃለሁ” አለው፡፡
አጥማጁም እንዳለው አደረገ፡፡ ያን ጊዜም ታላቅ ዓሣ ተያዘ፡፡ ይዞም ወደ ቤቱ ሔደ፡፡ ለራትም ይጠብሰው ዘንድ አረደው፡፡ በሆዱም ውስጥ መክፈቻ አገኘ፡፡ በሣጥኑ ቀዳዳም በአስገባው ጊዜ ፈጥኖ ተከፈተ፡፡ በውስጡም ታናሽ ብላቴና አገኘ፡፡ ልጅ የለውም ነበርና ታላቅ ደስታ ደስ አለው፡፡ ጌታችንንም አመሰገነው፡፡ ሕፃኑንም በመልካም አስተዳደግ አሳደገው፡፡ ሕፃኑም አድጎ ጐልማሳ ኾነ፡፡
ከብዙ ዘመናትም በኋላ ያ ባለ ጠጋ ተነሥቶ ወደዚያ አገር ሔደ፡፡ በመሸም ጊዜ ወደ በግ ጠባቂው ደጅ ደረሰ፡፡ በግ ጠባቂውን “እስከ ነገ የምናድርበት ማደሪያ በአንተ ዘንድ እናገኛለን? ኪራዩንም እሰጥሃለሁ” አለው፡፡ ባለ ጠጋውም በዚያ አደረ፡፡ ራት በሚቀርብም ጊዜ ከባሕር ላገኘው ልጅ “ባሕራን” ብሎ ሲጠራው ባለ ጠጋውም ሰምቶ “ልጅህ ነውን?” ብሎ ጠየቀው፡፡ በግ ጠባቂውም “አዎ፤ ታናሽ ሕፃን ኾኖ ሳለ ከሃያ ዓመት በፊት ከባሕር ላይ አግኝቼዋለሁና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጄ ነው” አለው፡፡
ባለጠጋውም እርሱ ወደ ባሕር የጣለው ሕፃን መኾኑን ዐውቆ እጅግ አዘነ፡፡ በማግሥቱም ጎዳናውን ሊጓዝ በተነሣ ጊዜ ሰይጣናዊ ምክንያት አመካኝቶ በግ ጠባቂውን እንዲህ አለው፡- “ከአገር ስወጣ በቤቴ የረሳሁት ጉዳይ ስላለ እንድልከው ልጅህን ትሰጠኝ ዘንድ እሻለሁ፡፡ እኔም የድካም ዋጋውን ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሃለሁ” አለው፡፡
የብላቴናውም አባት ስለ ገንዘቡ ደስ ብሎት ልጁ ባሕራንን ሰጠው፡፡ ባለ ጠጋው ወደ መጋቢው ደብዳቤ ጻፈ፤ “ይቺን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ልጅ ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው፤ ማንም ዐይወቅ፡፡” በማለት በመካከላቸውም የሚተዋወቁበትን ምልክት ጽፎ አሸጋት፤ ለባሕራንም ሰጠው፡፡
ባሕራንም ሲጓዝም ሰንብቶ የአንዲት ቀን ጉዞ ሲቀረው እነሆ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ “አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው?” አለው፡፡ “ከአንድ ባለጠጋ የተጻፈች መልእክት ናት” አለው፡፡ “ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ” አለው፡፡ እርሱም ስለ ፈራ ሰጠው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ያቺን የሞት መልእክት ደመሰሳት፡፡ በእርሷ ፈንታም በንፍሐት ለውጦ እንደህ ብሎ ጻፈ፤ “ይቺን ደብዳቤ ይዞ ለመጣ ባሕራን ለሚባል ሰው ልጄን አጋቡት፡፡ በውስጥና በውጭ ያለ ንብረቴንና ጥሪቴን፣ ወንዶችና ሴቶች ባሮቼን፣ ጠቅላላ ንብረቴንም አውርሼዋለሁና የፈለገውንም ሊያደርግ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና እኔን አትጠብቁኝ፡፡ እኔ ብዙ እዘገያለሁ ለዚህም በእኔና በአንተ መካከል ይቺ ምልክት እነኋት፡፡” በማለት ደብዳቤውን አሽጐ ለባሕራን ሰጠው፡፡ “ወደ ባለጠጋው ቤት ሒደህ ይቺን ደብዳቤ ለሹሙ ስጠው፡፡በጎዳናም እኔ እንደ ተገናኘሁህ አትንገረው፡፡ እንዳይገድልህም ይህን የሞት ደብዳቤ ለውጬልሃለሁ” አለው፡፡ ባሕራንም “እሺ ጌታዬ ያዘዝኸኝን ዅሉ አደርጋለሁ” አለ፡፡
ባሕራንም ወደ ባለ ጠጋው ቤት በደረሰ ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው፡፡ በአነበባት ጊዜ በመካከላቸው ያለውን ምልክት አገኘ፡፡ አስተውሎም እርግጠኛ እንደ ኾነ ዐወቀ፡፡ ከዚህም በኋላ ለባሕራን ሠርግ አዘጋጅቶ እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል የባለ ጠጋውን ልጅ አጋቡት፡፡ ዐርባ ቀን ያህልም ደስታና ሐሴት እያደረጉ ኖሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ባለ ጠጋው ከሔደበት መመለሻው ጊዜ ኾኖ በደስታ የኾነውን የመሰንቆና የእንዚራ ድምፅ ሰምቶ “ይህ የምሰማው ምንድነው” ብሎ ጠየቀ፡፡ እነርሱም “ስሙ ባሕራን ለተባለ የአንተን ደብዳቤ ላመጣ ጐልማሳ ሰው ልጅህ ዕገሊትን አጋቡት፡፡ እነሆ ለዐርባ ቀናት በሠርግ ላይ ነው፡፡ገንዘብህንና ጥሪትህን ዅሉ ወንዶችና ሴቶች ባሮችህን አንተ እንዳዘዝኽ ሰጥተውታል” አሉት፡፡ ይህንም በሰማ ጊዜ ደንግጦ ከፈረሱ ላይ ወደቀ በድንገትም ሞተ፡፡
ባሕራንም በጎ ሥራዎችን የሚሠራ ኾነ፡፡ የተገለጠለትና ከመገደል ያዳነው የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል እንደ ኾነ፤ ሊገድለው የሚሻውን የባለ ጠጋውን ጥሪቱን ዅሉ ያወረሰውም እርሱ እንደ ኾነ ተረዳ፡፡ የዚህንም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን መታሰቢያ በየወሩ ያደርግ ጀመረ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሠራለት፡፡ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕሉን አሥሎ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ አደረገው፡፡ ከእርሱም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡
ዳግመኛም በዚህች ቀን እግዚአብሔርን የሚፈራ አስተራኒቆስ የሚስቱ የቅድስት አፎምያ የዕረፍቷ መታሰቢያ ኾነ፡፡ ይህም ሰው በየወሩ ሦስት በዓላቶችን እያከበረ ኖረ፡፡ እሊህም ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ በየወሩ በሃያ ዘጠኝ፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓል መታሰቢያ በየወሩ በሃያ አንድ፤ የከበረ የመላእክት አለቃ የኾነ የቅዱስ ሚካኤል በዓል መታሰቢያም በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን ናቸው፡፡ የሚሞትበትም ጊዜው ሲቀርብ እርሱ ሲሠራው የነበረውን ምጽዋት ይልቁንም እሊህን ሦስቱን በዓላት እንዳታስታጉል ሚስቱን ቅድስት አፎምያን አዘዛት፡፡
እርሷም የከበረ የመልአኩ የሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባሏን ለመነችው፡፡ እርሱም አሠርቶ ሰጣትና በቤቷ ውስጥ በክብር አኖረችው፡፡ ባሏም ከዐረፈ በኋላ ባሏ ያዘዛትን መሥራት ጀመረ፡፡ ሰይጣን ግን ቀናባት፡፡ በመበለት ሴት መነኵሲት ተመስሎ ከእርሷ ጋር ተነጋገረ፡፡ እንዲህም አላት፤ “እኔ አዝንልሻለሁ፤ እራራልሻለሁም፡፡ ገንዘብሽ ሳያልቅ፣ የልጅነትሽም ወራት ሳያልፍ አግብተሽ ልጅ ትወልጂ ዘንድ እመክርሻለሁ፡፡ባልሽም መንግሥተ ሰማያትን ወርሷል፡፡ ምጽዋትም አይሻም፡፡” አፎምያም እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ “እኔ ከሌላ ሰው ጋራ ላልገናኝ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አድርጌያለሁ፡፡ ርግቦችና መንጢጦች እንኳ ሌላ ባል አያውቁም፡፡ በእግዚአብሔር አርአያ ከተፈጠሩ ሰዎች ይህሊኾን እንዴት ይገባል?”
ምክሩንም ባልሰማች ጊዜ አርአያውን ለውጦ በላይዋ ጮኸባት፡፡ እንዲህም አላት፤ “እኔ በሌላ ጊዜ እመጣለሁ፡፡” እርሷም የከበረ የመልአኩ የሚካኤልን ሥዕል ይዛ አሳደደችው፡፡ ከዚህም በኋላ ሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን የከበረ የመልአኩ የሚካኤል በዓል በሚከብርበት ዕለት እርሷም የበዓሉን ዝግጅት ስታዘጋጅ ሳለች ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ “አፎምያ ሆይ! ሰላም ላንቺ ይኹን! እኔ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነኝ፡፡ ጌታ ወደ አንቺ ልኮኛልና እርሱም ይህን መመጽወትሽን ትተሽ ለአንድ ምእመን ሚስት ትኾኚ ዘንድ አዞሻል፡፡” ባል የሌላት ሴት መልሕቅ የሌለውን መርከብ እንደምትመስል ዕወቂ፤ እንደ አብርሃምና ያዕቆብ እንደ ዳዊትም እንደነርሱ ያሉ ብዙ ሴቶችን እንዳገባ፤ እግዚአብሔርንም ደስ እንዳሰኙት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥቅሶችን ያመጣላት ጀመረ፡፡
ቅድስትአፎምያም መልሳ “አንተ የእግዚአብሔር መልአክ ከኾንኽ የመስቀል ምልክት ከአንተ ጋር ወዴት አለ? የንጉሥ ጭፍራ የኾነ ዅሉ የንጉሡን ማኅተም ሳይዝ ወደ ሌላ ቦታ አይሔድምና” አለችው፡፡ ሰይጣኑም ይህንን በሰማ ጊዜ መልኩ ተለወጠና አነቃት፡፡ እርሷም ወደ ከበረው መልአክ ወደ ሚካኤል ጮኸች፡፡ ወዲያውኑም ደርሶ አዳናት፡፡ ያንም ሰይጣን ይዞ ይቀጣው ጀመረ፡፡ ሰይጣኑም ጮኸ፡፡ “ማረኝ፤ ያለ ጊዜዬ አታጥፋኝ፤ እግዚአብሔር እስከ ዓለም ፍጻሜ ታግሦናልና” እያለ ለመነው፡፡ ከዚያም ተወውና አባረረው፡፡
የከበረ መልአክ ሚካኤልም እንዲህ አላት፤ “ብፅዕት አፎምያ ሆይ! ሒደሽ የቤትሽን ሥራ አዘጋጂ፡፡አንቺ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ትለዪአለሸና፡፡ እነሆ እግዚአብሔርም ዐይን ያላየውን፣ ጆሮም ያልሰማውን፣ በሰው ልብም ያልታሰበውን አዘጋጅቶልሻል፡፡” ይህንንም ብሎ ሰላምታ ሰጣት፡፡ ወደ ሰማያትም ዐረገ፡፡ የበዓሉንም ዝግጅት እንደሚገባ ከፈጸመች በኋለ ወደ ኤጲስቆጶሱና ወደ ካህናቱ ዅሉ ላከች፡፡ ወደ እርሷም በመጡ ጊዜ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ይሰጧቸው ዘንድ ገንዘቧን ዅሉ አስረከበቻቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ተነሥታ ጸለየች፡፡ የከበረ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤልንም ሥዕል አንሥታ ታቅፋ ሳመችው፡፡ ያን ጊዜም በሰላም ዐረፈች፡፡
ስለዚህም የዚህን ታላቅ የከበረ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ለማድረግመታገል ይገባናል፡፡ “እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካአል ሊረዳኝ መጣ” (ዳን. ፲፥፲፫) እንዲል ቅዱስ ሚካኤል በምልጃው ይራዳን ዘንድ ልንማጸነው ይገባል፡፡ እርሱ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን ዘንድ በዘመናችን ዅሉም ይጠብቀን ዘንድ፤ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይ ዘንድ፤ መከራችንንም ያርቅ ዘንድ፤ የምድራችንንም ፍሬ ይባርክ ዘንድ፤ ፈቃዱንም ለመሥራት ይረዳን ዘንድ፤ ከእኛ ወገን የሞቱትን ዕረፍተ ነፍስ ይሰጥ ዘንድ፤ ወደ መንገድ የሔዱ አባቶቻችንና ወንድሞቻተንን ወደ ቤቶቻቸው በሰላም፣ በጤና ይመልሳቸው ዘንድ፤ በመካከላችንም ፍቅር ያደርግልን ዘንድ፤ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ፤ የክርስቶስ ወገኖች የኾኑ መኳንንቶቻችንንም ጠብቆ በወንበሮቻቸው ላይ ያጸናቸው ዘንድ፤ የሳቱትንም ወደ ቀናች ሃይማኖቱ ይመልሳቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ ይለምናልና፡፡
የቅዱስ ሚካኤል አማላጅነትና ጥበቃው አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ምንጭ፡– መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፲፪ ቀን፡፡