“በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ፤ ጉባኤውንም ዐውጁ” (ኢዩ.  ፪ ÷፲፭)

ክፍል አንድ

በኃይለ ኢየሱስ ዘጼዴንያ

ጾም የሥጋን ምኞት እስከ መሻቱ ቆርጦ የሚጥል፣ ለመንፈስ ልዕልና የሚያበቃውን መሣሪያ የሚያስታጥቅ ነው፡፡ ክርስቲያን ይህን መሰል መንፈሳዊ የጦር ዕቃ እንዳይለየው አጥብቆ ይለምናል፡፡ የጦር ልምድ እንደሌለው ወታደር ጠላቱን የሚቋቋምበት የጦር ትጥቅ ሳይዝ አውላላ ሜዳ ላይ ባዶውን አይቆምም፡፡ መንፈሳዊ ውጊያን በሥጋዊ ጥበብ ማሸነፍ ስለማንችል ነው አበው አጽዋማትን በአስተምህሮአቸውና በሕይወታቸው የሰበኩልን፡፡

አጽዋማት ሲደርሱ ክርስቲያኖች የሚደሰቱት ጾም የሥጋ ፈቃድ እንዳይሰለጥንባቸው፣ ቁስለ ሥጋን በማከም፣ ቁስለ ነፍስን ስለሚፈውስላቸው ነው፡፡ ጾም የቁስል መፈወሻ ኃይለ መዊዕም (ድል ማድረጊያ) ይሆናል፡፡ ከሥጋም ከመንፈስም ተቆራኝቶ ሰውን ወደ ጥፋት የሚወስድን ክፉ መንፈስ ለማራቅም ይጠቅማል፡፡

ጾም እነዚህንና መሰል መንፈሳዊ በረከትን ስለሚያስገኝ ክርስቲያኖች ይመጣላቸው ዘንድ ይናፍቁታል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ በዓመት ውስጥ የሚጾሙ አጽዋማትን ደንግጋ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ከዲያብሎስ ፈተናና ወጥመድ ያመልጡ ዘንድ አበርክታለች፡፡ እነዚህም ሰባቱ አጽዋማት በመባል ይታወቃሉ፡፡ ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)፣ ጾመ ገሀድ(ጋድ)፣ ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዐርብ) እና ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡

በዚህ ዝግጅታችን ከእነዚህ የዐዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ የሆነውን ጾመ ነቢያትን በተከታታይ በሁለት ክፍል እናቀርብላችኋለን፡፡

ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)  

ጾመ ነቢያት ለአዳም የተነገረው ትንቢት ማለትም፡- አዳም ስለ በደሉ በማልቀሱና ንስሓ በመግባቱ ምሕረቱ ወሰን የሌለው አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር “አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” ተብሎ የተናገረውን የተስፋ ቃል በማሰብ ነቢያት የጾሙት ጾም ነው፡፡ በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት የእግዚአብሔር ወልድ መውረድ፣ መወለድ በትንቢት መነጽርነት እየተመለከቱ፣ እንዲሁም እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበው ምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ፣ የረቀቀው ገዝፎ እየተመለከቱ፤ ምሥጢረ ሥጋዌ እውን ሊሆን መቃረቡን በማሰብ ነቢያት ጾመውታል፡፡

ይህንንም ቅዱሳን ነቢያት የተስፋው ቃል በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር “የማያደርገውን አይናገር፣ የተናገረውንም አያስቀርም” ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ (ኢሳ. ፶፰÷፫-፲፬)

ቅዱሳን ነቢያት ስለ እግዚአብሔር ወልድ መወለድ፣ ወደ ግብፅ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ መጠመቅ፣ በትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለ መቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢትም ፍፃሜ ይደርስላቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን ተማጽነዋል፡፡

 ነቢያት “ይወርዳል ይወለዳል” ብለው ከጾሙ እኛ እርሱ ወርዶ፣ ተወልዶ ተሰቅሎ ካዳነን በኋላ ያለን የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ስለምን የነቢያትን ጾም እንጾማለን? ቢሉ እንደቀደሙት ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያልን ሳይሆን እነርሱ የጾሙትን ጾም በማሰብ መጾማችን ድኅነተ ሥጋ፣ ድኅነተ ነፍስ፣ በረከተ ሥጋ፣ በረከተ ነፍስ እንድናገኝበት ነው፡፡

ጾመ ነቢያት ከኅዳር ፲፭ ጀምሮ እስከ ታኅሳስ ፳፱ ቀን ድረስ ለ፵፬ ቀናት ይጾማል፡፡ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ እስከ ታኅሳስ ፳፰ ቀን ለ፵፫ ቀናት ይጾማል፡፡ ከእነዚህም መካከል ፵ ቀናት ጾመ ነቢያት፣ ፫ ቀናት ጾመ አብርሃም ሶርያዊ፣ እንዲሁም አርድእተ ፊልጶስ የጾሙት ጾም ሲሆን የቀረው ፩ ቀን ደግሞ የገሃድ ጾም ነው፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፭፣ ፭፻፷፯)፡፡

የጾመ ነቢያት ስያሜዎች

ጾመ ነቢያት በተለያዩ ስሞች ይጠራል፡፡ እነዚህም።-

ጾመ አዳም፡-  ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ ስለ ተፈጸመበት ጾመ አዳም ይባላል፡፡ አዳም በገነት ያለውን ሁሉ ይገዛ ይነዳ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቃድ ሲሰጠው አንድ ነገር ግን ከልክሎታል፡፡ በገነት ካሉት ዛፎች ዕፀ በለስን እንዳይበላ አዘዘው፡፡ ይህንንም ተላልፎ ቢገኝ የሞት ሞትን እንደሚሞት ነገርሮታል፡፡ ነገር ግን አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቆ መኖር የቻለው ለሰባት ዓመታት ከሁለት ወር ከአሥራ ሰባት ቀናት ብቻ ነው፡፡ አትብላ የተባለውንም ዕፀ በለስ በላ፤ ራቁቱንም መሆኑን ተረዳ፣ ጸጋውም ተገፈፈ፡፡ በተድላ በደስታ ከሚኖርበት ገነትም ወደ ምድረ ፋይድ ተባረረ፡፡ (ኩፋ. ፫፥፲፯-፳፬)

አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፉን የሞት ሞትም እንደሚሞት በተረዳ ጊዜ ከእግዚአብሔር የተነገረውን ቃል አሰበ፤ የፀፀት ዕንባን እያነባ ይቅርታን ከአምላኩ ዘንድ ለመነ፡፡ እግዚአብሔር ቸርነቱ ወሰን የለውምና ለአዳም “አምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን) ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ (ቀሌ. ፫፥፲፯-፲፱) አዳምም ቃል ኪዳኑ ይፈጸምለት ዘንድ ጾመ ጸለየ፡፡

ይህንንም ጾም ከአዳም ጀምሮ እስከ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ድረስ የነበሩት ነቢያት ጾመውታል፡፡ ነቢያት ለምን ጾሙት ብንል፤- ለአዳም የተገባውን ቃል ኪዳን ይፈጸም ዘንድ እየናፈቁ ከድንግል ማርያም ይወለዳል፣ በሞቱም ሞት የተፈረደበትን የሰው ልጅ ነፃ ያወጣዋል ሲሉ ነው፡፡ ለመጥቀስ ያህል ሊቀ ነቢያት ሙሴ ፵ ቀን ጾሟል (ዘፀ ፴፬÷፳፯)፤  በተጨማሪም ነቢዩ ዕዝራ፣ ሌሎችም ነቢያት ጾመውታል፡፡

ጾመ ማርያም፡- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወልደ አብን ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ በማለት ጾማዋለችና ጾመ ማርያም ይባላል፡፡ ይህን ያለችው በመደነቅ፣ በትሕትና እና ቀደምት አባቶቿ ነቢያት ሲጾሙት አይታ ጾማዋለች፡፡ እንዴት ፀንሼ እወልደዋለሁ ማለት ጥርጥር ሳይሆን ተደምሞ፣ መደነቅ የነገረ ልደቱን አይመረመሬነት ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትሕትና ነው፡፡

እግዚእሔር ወልድ በነቢያት ምሳሌ እየተመሰለ፣ ትንቢት እያናገረ አምስት ሺህ አምስት መቶው ዘመን ሲፈጸም ንጽሕት ቅድስት ከምትሆን ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ተወልዷል፡፡ የነቢያትም ትንቢት ተፈጽሟልና የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑም የልደት ጾም ተብሏል፡፡

ዘመነ አስተምሕሮ(አስተምህሮ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመን አከፋፈል ሥርዓት መሠረት ከኅዳር ፮ ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፯ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምህሮ ይባላል፡፡

 አስተምህሮ፡- ቃሉ በሀሌታው “ሀ” ሲጻፍ የቃለ እግዚአብሔር ማስተማሪያ (የትምህርተ ወንጌል) ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም “መሀረ – አስተማረ፤ ለመምህር ሰጠ፤ መራ፤ አሳየ፤ መከረ፤ አለመደ” ወይም “ተምህረ – ተማረ፤ ለመደ” የሚለው የግእዝ ግስ ሲሆን፣ ይኸውም የእግዚአብሔር ቸርነቱ፣ ርኅራኄው፣ ትዕግሥቱና የማዳን ሥራው በቤተ ክርስቲያን በስፋት የሚሰበክበት ጊዜ ነው፡፡

አስተምሕሮ፡- ስንል ደግሞ ቃሉ በሐመሩ “ሐ” ሲጻፍ ደግሞ የምሕረት፣ የይቅርታ ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም “መሐረ – ይቅር አለ፣ ዕዳ በደልን ተወ” ወይም “አምሐረ – አስማረ፤ ይቅር አሰኘ፤ አራራ፤ አሳዘነ” የሚለው የግእዝ ግስ ነው፡፡ ዘመነ አስተምሕሮ ስለ እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ፤ እርሱ በደላችንን ሁሉ ይቅር እንደሚለን እኛ ምእመናንም እርስ በእርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡

ይህ ዘመነ አስተምሕሮ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምእመናንንም በጾም በጸሎት ተወስነው ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፣ እግዚአብሔርንም   የሚማጸኑበት ጊዜ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረትና ይቅር ባይነትም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡

በዘመነ አስተምሕሮ የሚገኙ ሰንበታት፡- በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት እንደተቀመጠው በዘመነ አስተምሕሮ ውስጥ የሚገኙ ሰንበታት (ዕሑዶች) አስተምሕሮ፣ ቅድስት፣ ምኵራብ፣ መጻጉዕ እና ደብረ ዘይት ተብለው ይጠራሉ፡፡ ሳምንታቱን በዚህ መልክ የከፋፈለውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ (ድጓ ዘአስተምህሮ)፡፡ ከመጀመሪያው ሳምንት (ከአስተምሕሮ) በቀር የአራቱ እሑዶቹ ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡

የዘመነ አስተምህሮ ሰንበታት (እሑዶች) ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ስያሜ ጋር ተመሳሳይ ይሁን እንጂ በእነዚህ ሳምንታት ሌሊት የሚዘመሩ መዝሙራት፣ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትና የሚቀርቡ ትምህርቶች ግን በይዘትና በምሥጢር ይለያያሉ፡፡ ትምህርቶቹ በምስጢር ይለያያሉ ስንልም በዚህ ወቅት የሚነገረው ምስጢርና ይዘት በወቅቱ ላይ የሚያተኩር መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡

ይቆየን

ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚያስገባ ቁልፍ

በመ/ር ተመስገን ዘገዬ

እግዚአብሔር ሰውን ሕያው ሁኖ እንዲኖር በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮታል፡፡ ይህ ማለት ግን ሰው:- ኃጢአት የማይሠራ፣ ሞትም የማይስማማው፣ ባሕርይው ድካም የሌለበት እንደሆነ መናገር አይደለም፡፡

እግዚአብሔር ሰውን አእምሮ ሰጥቶ እንደ መላእክት ሕያው ሆኖ እንዲኖር ከፈጠረውና የጸጋ አምላክነትን ደርቦ ከአከበረው ኃጢአት ላለመሥራትና ትእዛዘ እግዚአብሔርን ባለመተላለፍ መጽናት ነበረበት፡፡ ነገር ግን አዳም ሕግን ተላለፈ፣ ቅጣትንም አስተናገደ፡፡ በዐዋቂ አእምሮው የፈጠረውን የአምላኩን ትእዛዝ መተላለፉን፣ መበደሉንና የሞት ሞትም እንደሚሞት በተረዳ ጊዜ ተፀፀተ፣ የንስሓ ዕንባም አነባ፡፡ እግዚአብሔርም በምሕረት ዐይኑ ተመልክቶትና ንስሓውን ተቀብሎ ከልጅ ልጁ ተወልዶ ወደ ቀደመ ክብሩ እንደሚመልሰው ቃል ኪዳን ገባለት፡፡

ለመሆኑ ንስሓ ምንድነው?

ንስሓ የቃሉ ፍቺን በተመለከተ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት “ሐዘን፣ ፀፀፀት፣ ቁጭት፣ ምላሽ፣ መቀጮ፣ ቅጣት፣ ቀኖና፣ የኃጢአት ካሣ” በማለት ይተረጉመዋል፡፡

ንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ ንስሓ የሚገባ ሰው ከሠራው ኃጢአት በሙሉ ልቡ ይመለስ ዘንድ ይገባዋል፡፡ እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ ነውና ወደ እርሱ ለሚመለሱት ሁሉ ይቅር ባይ ነው፡፡ አይሁድን “ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፣ እርሷንም አልጠበቃችሁም፡፡ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፡፡” (ሚል. ፫፥፯) በማለት ከበደላቸው ይነጹ፣ በይቅርታውም ይጎበኙ ዘንድ ይጠራቸዋል፡፡

ቅዱስ ያዕቆብም “ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ” በማለት ኃጢአት የነፍስ ሞት፣ ንስሓ ደግሞ ሕይወት    መሆኑን አስተምሯል፡፡ (ያዕ. ፭፥፳) ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም “እኛ … ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃለን” በማለት ምስክርነቱን ገልጧል፡፡ (ዮሐ. ፫፥፲፬)

ንስሓ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ባስተማረው በሁለተኛው መልእክቱ ከበደላቸው ርቀው፣ ንስሓ ገብተው ከእግዚአብሔር ጋር ይታረቁ ዘንድ ሲያመለክታቸው ” … ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን  እንለምናችኋለን”  በማለት ተናግሯቸዋል፡፡  (፪ኛ ቆሮ.፭፥፳)

ንስሓ ከኃጢአት ባርነት ነፃ መውጣት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው፡፡ ባሪያም ለዘላለም በቤት አይኖርም … እንግዲህ ልጁ (ወልደ እግዚአብሔር) አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ” (ዮሐ. ፰፥፴፬—፴፮) በማለት ከኃጢአት ባርነት መውጣት የሚቻለው ከእግዚአብሔር   በተሰጠች ንስሓ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ሰው በፍጹም ልቡ ካልተመለሰ ስለ ኃጢአቱ እያዘነ ሊያለቅስ አይችልም፡፡ንስሓ ስለ አለፈው ስህተት(ኃጢአት) አብዝቶ ማልቀስያለፈውንም የኃጢአት ኑሮ ማውገዝና መኰነን መሆኑን መረዳት ይገባል። ነቢዩ ኢዩኤል “አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” በማለት የሚመክረን ለዚህ ነው፡፡ (ኢዩ. ፪፥፲፪)

ንስሓ ፍጹም የሆነ የሕይወት ለውጥ እንጂ ጊዜያዊ ስሜት አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” ሲል ንስሓ ፍጹም ወደሆነ የሕይወት ለውጥ (ከኃጢአት ወደ ጽድቅ) የምንመለስበት እንጂ በጊዜያዊ ስሜት ላይ ተመሠርተን የምንፈጽመው አለመሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ (ሮሜ ፲፪፥፪)

ንስሓ ኃጢአት ሲሠሩ ከመኖር ይልቅ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን (መምረጥ) ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚወደውንና የሚደስበትን፣ ጽድቅ የሚገኝበትን፣ መልካም ምግባርና ትሩፋት በመሥራት እርሱን በማምለክና በማገልገል መኖርን መምረጥ ነው፡። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ለእኔስ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” በማለት ምርጫውን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጓል፡፡ (መዝ. ፸፫፥፳፰)

ንስሓ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የሚያስችል ወደ መንግሥተ እግዚአብሔርም የሚያስገባ ቁልፍ ነው፡። ስለዚህ ንስሓ ከሚመጣው መከራና ሐዘን መዳኛ ወይም ማምለጫ መንገድ ነው፡። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን የነነዌ ሰዎች ከኃጢአታቸው የተነሣ የእግዚአብሔር ቍጣ እንደመጣባቸው በነቢዩ ዮናስ አማካኝነት በተሰበከላቸው ጊዜ ሊወርድ ከነበረው የእሳት ዝናብ ለመዳን የቻሉት በንስሓ እና በልቅሶ ነው፡፡ (ዮና. ፫፥፲) በነቢዩ ኤርምያስም “አሁንም መንገዳችሁን፣ ሥራችሁን አሳምሩ፣ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፣ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተወዋል፡፡” (ኤር. ፳፮፥፲፫) በማለት የገለጸው ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡

ንስሓ ለዕርቅ የተዘረጋ የእግዚአብሔር እጅ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰውን የቀደመ ኃጢአት ይቅር የሚልበትና የሚያጥብበት መንፈሳዊ ምሥጢር ነው፡፡ ሰው በንስሓ የታጠበ እንደሆነ ከበረዶ ይልቅ ይነጻል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፤ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ … በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ” እንዲል (መዝ. ፶፥፪-፯)

ንስሓ የሰማያዊም የምድራዊም ደስታ ምንጭ ነው። አንድ ኃጢአተኛ ንስሓ ቢገባ በሰማይ ደስታ እንደሚደረግ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ “ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኃጢአተኛ በሰማያት ፍጹም ደስታ ይሆናል፡፡ … ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት በሰማያት ደስታ ይሆናል” በማለት እንደተገለጸው፡፡ (ሉቃ. ፲፭፥፯-፲)

ንስሓ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ የሚሰጥበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ የሚታየው አገልግሎት የተነሣሒው ፀፀትና ኑዛዜ፣ የቄሱ የንስሓ ጸሎት ሲሆን፤ የማይታየው ጸጋ ደግሞ ተነሳሒው የሚያገኘው ስርየተ ኃጢአት ነው፡፡ በአጠቃላይ ንስሓ ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚያስገባ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ የድኅነት ቁልፍ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል

ሚካኤል የሚለው ስም አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘው መዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ሲገልጹ ቃሉ የዕብራይስጥ ሲሆን፤ ሚ ማለት “መኑ” ፥ ካ ማለት “ከመ” ማለት ሲሆን፥ ኤል ማለት ደግሞ “አምላክ” ማለት ነው። በዚህም መሠረት ቅዱስ ሚካኤል የስሙ ትርጓሜ “መኑ ከመ አምላክ፥ ማን እንደ እግዚአብሔር” ማለት ነው።

በሥነ ፍጥረት ትምህርት እግዚአብሔር ሳጥናኤልን ቅሩበ እግዚአብሔር፣ ለእግዚአብሔር የቀረበ አድርጎ እንደ ሾመው ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ነገር ግን ሳጥናኤል ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ክብር ትቶ አምላክነትን በመሻቱ በትዕቢቱ ምክንያት ሥልጣኑ ተገፍፎ ወደ ምድር ጥሎታል፡፡ በቦታውም ቅዱስ ሚካኤልን ሾሞታል፡፡ የቅዱስ ሚካልን ሲመት ምክንያት በማድረግም ዕለቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር ፲፪ ቀን በየዓመቱ በድምቀት ታከብረዋለች፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ)

ይህም ብቻ አይደለም፤ እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት ቀንበር ተይዘው ለ፪፲፭ በስቃይ ሲኖሩ ያለቀሱት ዕንባ መንበረ ጸባዖት ደርሶ ከግብፅ ወደ ምድረ ርስት ይገቡ ዘንድ እግዚአብሔር ሊቀ ነቢያት ሙሴን አሥነስቶ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ አሻግሮ፣ ለዐርባ ዘመናት ሲጓዙ ቀን በደመና ሌሊቱን በብርሃን እየመራ ያደረሳቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ቀን መታሰቢያ አድርጋ የምታከብርበት ዕለት ነው፡፡

ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ ወልደ ነዌ በሰው አምሳል ተገልጦ “የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ አየ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ ‘ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ?’ አለው፡፡ እርሱም ‘እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ፤ አሁንም ወደ አንተ መጥቻለሁ’ አለ፡፡ ኢያሱም ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ” በማለት እግዚአብሔር የቅዱስ ሚካኤልን ክብር ገልጧል፡፡ (ኢያ. ፭፥፲፫-፲፬)

የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይ ጭምር ነው፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል፣ ለእኛ ለሰዎች አማላጅ ሲሆን ለቅዱሳን፣ ፃድቃን ሰማዕታት ደግሞ አጋዣቸው ነው፤ በሕይወታቸውና በተጋድሏቸውም እስከ መጨረሻው ይረዳቸዋል፡፡

ይህንንም በቤተ ክርስቲያናችን በመጽሐፈ ስንክሳር እና ድርሳነ ሚካኤል ኅዳር ፲፪ ቀን እንደተጻፈው መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱ ቴዎብስታን ከዲያብሎስ ፈተና የታደገበት ዕለት ነው፡፡

ዱራታዎስና ቴዎብስታ ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር፡፡ ነገር ግን በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ ለቅዱስ ሚካኤልም ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን እስኪያጡ ድረስ ቸገራቸው፡፡ ዱራታዎስም የእርሱንና የሚስቱን ልብስ ሸጦ ለመልአኩ በዓል መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኮንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለትና ወደ ባለ ጸጎች ሄዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ፣ ሁለተኛም ወደ ባለ ስንዴ ዘንድ ሄዶ በእርሱ ዋስትና ስንዴን እንዲወስድ፣ ዳግመኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ዘንድ ሄዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ፣ ነገር ግን ወደ ቤቱ ሳይርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አዘዘው፡፡ ዱራታዎስም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ቤቱ ሁሉ በበረከት ተመልቶ አገኘው፡፡ እርሱም እጅግ ተደስቶ የዚህን የክቡር መልአክ የመታሰቢያውን በዓል አደረገ፡፡ ጦም አዳሪዎችንና ድኆችንም ጠርቶ አጠገባቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቴዎብስታ ቅዱስ ሚካኤል ለሁለተኛ ጊዜ ተገለጠላቸው፡፡ ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንዲሰነጥቅ አዘዘው፡፡ በሰነጠቀውም ጊዜ ፫፻ (ሦስት መቶ) የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ውስጥ ተገኘ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱን ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው፡- “ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ፣ ለባለ ዓሣውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ፡፡ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፣ በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አዘጋጅቶላችኋል” አላቸው፡፡

እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ደነገጡ፤ የከበረ ገናናው መልአክም “ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ፤ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም” አላቸው፡፡ ይህንንም ከነገራቸው በኋላ ወደ ሰማያት ወጣ፤ እነርሱም በፍርሃትና በክብር ሰገዱለት፡፡”

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከበዓሉ በረከት ረድኤት ይክፈለን፤ ጥበቃውና አማላጅነቱ አይለየን፡፡ አሜን፡፡

ምንጭ፡ድርሳነ ቅዱስ ሚካኤል፣ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር፣ መጽሐፈ አክሲማሮስ፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ

“ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት አርአያ የሚሆን ትውልድን በመቅረጽ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል”

አቶ አበበ በዳዳ

 (በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ)

ክፍል ሁለት

በእንዳለ ደምስስ

የማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ድረ ገጽ አዘጋጅ ከአቶ አበበ በዳዳ የማስተባበሪያው ኃላፊ ጋር ያደረገውን ክፍል አንድ ቆይታ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በነበራቸው ቆይታም የግቢ ጉባኤት አገልግሎት ማስተባበሪያ ዋና ዋና ተግባራት፣ ከማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ከማእከላት እና ከግቢጉባኤያት ጋር በቅንጅት የሚከናወኑ ተግባራት፣ እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸውን በተመለከተ የሰጡትን ምላሽ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በክፍል ሁለት ያደረግነውን ቆይታ ደግሞ ቀጥለን እናቀርባለን፡-

አሁን ጎልቶ ከሚታየው የዓለም አቀፋዊነትና የዘመናዊነት አስተሳሰብ አንጻር ግቢ ጉባኤያት   ተማሪዎች ሕይወት ከመታደግ አንጻር ምን እየተሠራ ነው?

አቶ አበበ፡- ወጣትነትን በአግባቡ ካልመሩት የሚጎዳንና የሚጠቅመንን ሳንለይ አዲስ ነገር ለመሞከር የምንፈጥንበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ በተለይም በዚህ ዘመን ወጣቶችን እየፈተነ ያለው የዓለም አቀፋዊነትና የዘመናዊነት አስተሳሰብ ለበርካታ ችግሮች ተጋላጭ ሲያደርጋቸው እንመለከታለን፡፡ የግቢ ጉባኤት አገልግሎት ማስተባበሪያም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  የሚገቡ ተማሪዎችን በማሰባሰብ ይህንን የወጣትነትና ሁሉን ልሞክር ባይነት ዘመናቸውን በመግራት እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲኖሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ወጣቶች ከቤተሰብ የመራቅ ዕድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ ጥንቃቄን ይሻልና በአንድ ላይ ለማግኘት አመቺ ከመሆኑ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ኃላፊነት ወስዶ ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ፣ የመማሪያ መጻሕፍትን አዘጋጅቶ ተከታታይ ትምህርት ይሰጣል፡፡ መንፈሳዊነትን የሕይወታቸው አካል አድርገውም ከክፉ ሁሉ ርቀው እጇን ዘርግታ ለጥፋት ከምትቀበላቸው ዓለም ተለይተው ያገለግሉ ዘንድ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል፡፡

በሙያቸውም ዕውቀትንና ክህሎትን ይዘው በተሠማሩበት ሁሉ በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግሉ አቅጣጫ ማሳየት ነው የእኛ ሥራ፡፡ በዚህም መሠረት የዓለም አቀፋዊነትንና የዘመናዊነትን አስተሳሰብ በመንፈሳዊ ሚዛን መዝነው ሕይወታቸውን እንዲመሩ መንፈሳዊውን ትጥቅ በማስታጠቅ ለአገልግሎት እናሠማራለን፡፡

በተጨማሪም ሥልጠናዎች ይሰጣሉ፣ የምክክር መርሐ ግብራት ይደረጋሉ። እነዚህ ደግሞ በጣም ብዙ ልምድ እና ዕውቀት እንዲገበዩ ይረዷቸዋል፡፡ ሌላው የአንድነት ጉባኤያት፣ የጽዋ ማኅበር፣ የጉዞ እና የንስሓ አባት መርሐ ግብራት ይዘጋጃሉ፤ ይህም ተማሪዎቻችን ራሳቸውን እንዲገዙ፣ ዓለምን የመረዳት ግንዛቤአቸው ከፍ እንዲል ያደርጋቸዋል፡፡ በድረ ገጽ፣ በመጽሔት፣ … በመሳሰሉት የሚዲያ አማራጮችም መረጃዎችን የመሥጠቱ ሥራ ይሠራል፡፡

በምረቃ ሰሞን ግን ብዙ ጊዜ ተመራቂ ተማሪዎች ፶፣ ፻ ቀናት እያሉ ሥጋዊ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለመዝናናት ትኩረት ስለሚሰጡ ለኃጢአት ራሳቸውን አሳልፈው ሲሰጡ እንመለከታለን፡፡ ይህንን ለመከላከል በየጉባኤያቱ የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መንፈሳዊ መርሐ ግብራትን በማዘጋጀት ከግቢ ሲወጡ በሕይወታቸው ሊገጥማቸው ከሚችሉ ነገሮች እንዲጠበቁ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ተማሪዎችን የመታደግ ሥራዎች ይከናወናሉ።

ማኅበረ ቅዱሳን ላለፉት ፩ ዓመታት በርካታ የግቢ ጉባኤት ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ ነገር ግን ከምረቃ በኋላ አገልግሎት ላይ  ሲሳተፉ አይታይምና ይህንን ችግር ለመፍታት ምን እየተደረገ ነው?

አቶ አበበ፡- ይህንን ጥያቄ ብዙዎች ሲጠይቁ እንሠማለን፡፡ ነገር ግን የአገልግሎት ብያኔያችንን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ አገልግሎት ማለት የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ብቻ አይደለም፡፡   ያስመረቅናቸውን ተማሪዎች ሁሉም ቢመጡ እዚህ መያዝ እንችላለን ወይ? የሚለው ነገር ግልጽ መሆን አለበት፡፡ የምናስተምራቸው ተማሪዎች ለሀገር፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለማኅበረሰብና ለራሳቸው የሚጠቅሙ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በአገልግሎትም በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ  በዋናው ማእከል፣ በማእከል፣ በወረዳ ማእከል፣ በግንኙነት ጣቢያ፣ በሰ/ት/ቤት፣ በሰበካ ጉባኤ ታቅፈው ያገለግላሉ፡፡

አገልግሎትን ስናስብ ማኅበረ ቅዱሳን  ሕንጻ ላይ ብቻ የምናየው ከሆነ ልክ አይደለም፡፡ በግቢ ጉባኤ ያስተማርናቸው በሰ/ት/ቤት የሚያስተምሩ፣ የአብነት ትምህርት የሚያስተምሩ እና ሥልጠና የሚሰጡ ናቸው። አገልግሎትን ጠቅለል አድርገን ካላየነው በስተቀር ሰው ራሱንና ቤተሰቡን  በትክክል መምራት ከቻለ መጨረሻ ላይ እንዲሆኑ የሚፈለገው የጽድቅ ሥራ እንዲሠሩ እና እንዲጸድቁ ነው ፡፡

የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ገብተው በታማኝነት እያገለገሉ ያሉ የግቢ ጉባኤ ፍሬዎች ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት ያስተማራቸው ተማሪዎች የት ናቸው? ብሎ መጠየቅ አይገባም፤ ፊት ለፊት የምናየው ተጨባጭ እውነት አበረታች ነውና፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የበለጠ አንድነታችንን ለማጠናከር እየተሠሩ ያሉ አበረታች ሥራዎችም አሉ፡፡ አንዱ “ዓለም አቀፍ የግቢ ጉባኤያት ምሩቃን ሕብረት” በሁለት ወር አንድ ጊዜ ጉባኤ እየተሠራ ሁሉም ማእከላት በቀኑ እያሰቡ እንዲያገለግሉ ይደረጋል፤ በ ኢኮኖሚ ለማስተሳሰር ሙከራ እና ጥረት ይደረጋል፣ ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የጋራ ማኅበራዊ ትስስር እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ለሥራ በተሠማሩበት ቦታ ቅድስት ቤት ክርስቲያንን እና ሀገርን በታማኘት በቅንነት እንዲያገለግሉ ምን ይመክራሉ?

አቶ አበበ፡- እግዚአብሔር ወደ ምድር ሲያመጣን በዓላማ ነው እና ዓላማን ማወቅ ተቀዳሚው ነገር ነው፡፡ ተማሪዎች በግቢ ጉባኤ ቆይታቸው መንፈሳዊውን ትምህርት እንዲማሩ ዕድሉን የሰጣቸው እግዚአብሔር መሆኑን ማሰብ አለባቸው፡፡ ወደ  ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገቡ መንፈሳዊው ማዕድ ተዘጋጅቶ ነው የሚጠብቃቸውና ይህንን ዕድል ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

የመጡት መንግሥት በመደባቸው ትምህርት ዘርፍ ተመረቀው እንዲወጡ ቢሆንም እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖም መንፈሳዊ ትምህርት ጎን ለጎን አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ስለዚህ የተሰጣቸውን መክሊት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። አንድ ተመራቂ ከራሱ ሕይወት ነው መጀመር ያለበት፤  ኦርቶዶሳዊ ሲሆን ለሰው ሁሉ ክብር ይኖረዋል፣ እኩል ለሰው ሁሉ ይራራል ፣ ክፉ ነገር ሁሉ ያንገበግበዋል፡፡ ስለዚህ ዋናው ኦርቶዶሳዊ ሆኖ ለራሱ፣ ለቤተሰቡ፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር መኖር ይገባዋል።

ሁለተኛ በእያንዳንዱ በሚሠማራበት ቦታና የሥራ መስክ የቤተ ክርስቲያን አምባሳደር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አምባሳደር ደግሞ የክርስቶስን መስቀል ተሸክሞ ነው የሚኖረው፡፡ ያንን የተሸከመው መስቀል የክርስቶስን መከራና ሥቃይ፣ ለሰው ልጆች ሁሉ የከፈለውን ዋጋ በማሰብ በአባቶች ቡራኬ በአደራ መስቀል እናስመርቃቸዋለን፡፡ ምንድነው ማድረግ ያለብኝ፣ እውነት የተሰጠኝን አደራ በአግባቡ እየተወጣሁ ነው? በምሠራበት፣ በምኖርበት አካባቢ እንደ ኦርቶዶክሳዊ የሚጠበቅብኝን ነገር እየተገበርኩ ነው ወይ? እያለ ማሰብ መቻል አለበት እንጂ በሌሎች ተጸእኖ ውስጥ መውደቅ የለበትም፡፡

ሌሎች እርሱ ያደረገውን መልካምነት እንዲከተሉ እንጂ ሌሎች የሚያደርጉትን ጥፋት በመከተል መጓዝ የለበትም፡፡ ለሁሉም የሰው ልጆች እኩል የሚያገልግል፣ እኩል በፍትህ የሚመራ ከሆነና በሙያው ያለ አድልዎ መስጠት የሚችለውን አገልግሎት መስጠት ከቻለ ለሌላው አርአያነቱ የጎላ ነው፡፡ ይህንንም መሠረት አድረጎ ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት አርአያ የሚሆን ትውልድን በመቅረጽ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡

ለሰጡን ማብራሪያ እያመሰገን የመጨረሻ መልእክትዎን ቢያስተላልፉ?

አቶ አበበ፡- የግቢ ጉባኤ አገልግሎት የታወቀ አገልግሎት ነው፡፡ ታሪክን ወደ ኋላ ስንመለከት እግዚአብሔር ባወቀ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተመሠረተ ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ ተቋማት ውስጥ ያለው ወጣት የሰው ኃይል እንዳይባክን በአግባቡ ቁም ነገር ላይ እንዲወል እግዚአብሔር ያዘጋጀልን አንዱ መድረክ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን መድረክ በአግባቡ ለሚቀጥለው ጊዜ ማሻገር ያሰፈልጋል፡፡ ይህን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ደግሞ የተለያዩ አካላት ድርሻ አላቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል በዋነኛነት የተማሪ ቤተሰቦች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡

ልጆቻቸው ወደ ከፍተኛ ተቋማት  ሲገቡ ጎን ለጎን በግቢ ጉባኤ አገልግሎት ውስጥ መሳተፍ እንዳለባቸው በደንብ ትኩረት ሰጥተው በማስገንዘብ ሊልኳቸው ይገባል፡፡ መንፈሳዊውን ትምህርት ቢማሩ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ጠንካራ ይሆናል፣ ከአልባሌ ቦታ ይርቃሉ፣ ዓላማም ይኖራቸዋል፡፡ አሁን አሁን እየተቸገርንበት ያለውን የዘረኝነትና የብሔር አመለካከትን በማራቅ የሰው ልጅ አንድ የእግዚአብሔር ፍጡር መሆኑን የሚረዳ አስተሳሰብ እንዲኖረው ያግዘዋል፡፡

ቤተሰብ ልጆቻቸውን በሰ/ት/ቤት እንዲሳተፉ እንደሚያደርጉ ሁሉ ወደ ከፍተኛ ተቋማት ሲመጡ ደግሞ ግቢ ጉባኤ እንዲሳተፉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስ/ት/ትቤት የሚማሩት እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንንም እየተማሩ በአገልግሎት ክፍሎች እየተሳተፉ የድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል፡፡

ሌላው ማን ነው የሚያስተምረን? የሚለውን ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡  ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ስኖዶስ ፈቃድ ዕውቅና ያለውና በመላው ዓለም በመንፈሳዊ አገልግሎት የሚሳተፍ ማኅበር መሆኑን መረዳት፣ እንርሱንም ኃላፊነትም ወስዶ በግቢ ጉባኤያት መንፈሳዊ ትምህርቱን እያስተማራቸው እንደሆነ ሊረዱ ይገባልል፡፡

ሌላው ሰ/ት/ቤቶች፣ ማኅበራት፣ የአካባቢ ምእመናን፣  የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ይህ ኃላፊነት በጋራ የተሰጠን ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን መምሀር መድቦ ካስተባበረ አጥቢያው የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ቦታ በማመቻችት በጋራ አገልግሎታችንን በተቀናጀ ሁኔታ እንድናገለግል ጥሪ አስተላፋፍለሁ፡፡ ምክንያቱም እንደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው የመማር መብት አላቸውና ይህንን ትብብር እንዲያደርጉ፣ በመንግሥት መዋቅር ሥር ያሉ አካላትም የግቢ ጉባኤ አገልግሎት ማለት ለሀገር ሰላም፣ ለመቻቻል፣ አብሮ ለመኖር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነውና የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት የዘረኝነት እና የጎሰኝነት አስተሳሰብን ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ ሀገር አንድ ሆኖ ለመኖር የሚያግዝ አገልግሎት ስለሆነ ይህን መረዳትም ያስፈልጋል፡፡

ግቢ ጉባኤ ማለት በሥነ ምግባር የታነጹ፣ በሥራቸው ደግሞ አንቱ የሚባሉ ሰዎች የሚወጡበት ነው። መልካም ትዳር፣ መልካም ቤተሰብ መመሥረት የሚቻለው በሃይማኖት በምግባር የቀና ትውልድ መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከጋብቻ ይልቅ ፍቺ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ስለመምጣቱ በቅርቡ የአዲስ አባባ ከተማ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል፡፡  እንደዚህ ዓይነቱን ማኅበራዊ ቀውስ ከማስወገድ አንጻር ወጣቶችን ከመጀመሪያው ጀምሮ በሥነ ምግባር የታነጹ ሆነው ለትዳራቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለልጆቻቸው ክብር እንዲሰጡ አደርጎ ማብቃት አሰፈላጊ ነው፡፡  እንዲህ የሚያደርጉ ተቋማትን ደግሞ መንከባከብ ያስፈልጋል። ለዚህ የተለየ ድጋፍ ባይደረግ እንኳን በአገልግሎቱ ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥሩ መልእከቴን አስተላልፋለሁ፡

በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡

አቶ አበበ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

የግቢ ጉባኤያት ሥርዓተ ትምህርት ክለሳ የግብአት ማሰባሰቢያ የውይይት መርሐ ግብር ተካሄደ

በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ነባሩን ሥርዓተ ትምህርት ለመከለስ የግብአት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብርን አስመልክቶ ቅዳሜ ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም በማኅበሩ ሥራ አመራር መሰብሰቢያ አዳራሽ ከባለ ድርሻ አካላት ውይይት ተካሄደ፡፡

በዚህ ውይይት ላይ ከፍተኛ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ባለሙያዎችና ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራን የተገኙ ሲሆን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አበበ በዳዳ የነባሩን ሥርዓተ ትምህርት መከለስ ያስፈለገበትን መሠረታዊ ምክንያት በመተንተን ጉባኤውን አስጀምረዋል፡፡

አቶ አበበ የነባሩን ሥርዓተ ትምህርት ጉድለቶች በመተንተን የክለሳውን አስፈላጊነት ሲገልጹ፡- ነባሩ ሥርዓተ ትምህርት ዲጂታል ቴክኖሎጂን አለማካተቱ፣ ከተመደበው ጊዜና ቅደም ተከተል ጋር የተያያዙ ጉድለቶች መኖራቸው፣ ከማኅበረ ቅዱሳን ተቋማዊ ለውጥ አስተሳሰቦች አንጻር፣ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርትና ሥልጠና የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉና ትግበራ መጀመሩ፣ የሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ትግበራ መጀመር፣ ከሌሎችም ምክንያቶች አንጻር ተመዝኖ ነባሩን ሥርዓተ ትምህርት መከለስ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት ያስችል ዘንድ መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በክፍል ሁለት ዝግጅት ሥርዓተ ትምህርቱን በመከለስ ረገድ ኃላፊነት ከተሰጣቸው የዘርፉ ምሁራን መካከል ዲ/ን አንዱአምላክ ይበልጣል “ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት ላይ ተግባራዊ የሚደረገው የሥርዓተ ትምህርት ፍልስፍና” በሚል ዐቢይ ርእስ በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ያቀረቡ ሲሆን፡፡ እነዚህም፡- የሥርዓተ ትምህርት ትኩረት፣ የመምህሩ ሚና፣ የትምህርት አሰጣጥ መንገዶችና የማስተማሪያ ዘዴዎች፣ እንዲሁም የምዘናና የግምገማ ሥርዓት እንዴት መሆን እንዳለበት አብራርተዋል፡፡

ዲ/ን አንዱአምላክ በክፍል ሦስት ገለጻቸውም በሥርዓተ ትምህርት ሊታሰቡ የሚገባቸው የግቢ ጉባኤያት ነባራዊ ሁኔታዎች /Theoritical Approach/ ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡ በዚህም ማብራሪያቸው የሀገራችንን አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ታሳቢ ስለማድረግ፣ የተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚቆዩበት ጊዜ መለወጥ፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት አሰጣጥ ላይ የተለየ አቀራረብ መኖሩ፣ የመደበኛ ትምህርት ነባራዊ ሁኔታዎች፣ የተማሪዎች አስተዳደርና ሃይማኖታዊ ግንዛቤ፣ የሀገሪቱ  ውጥረትና ፖለቲካዊ የሥልጠና ፖሊሲዎች አለመረጋጋት፣ … እንዲሁም ሌሎች ነጥቦችን አንሥተው ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የክፍል አራት ገለጻው ደግሞን ከፍተኛ የትምህርት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ ሀብቴ “የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጭብጦች /Thematic Areas/” በሚል ርእስ ላይ ያቀረቡ ሲሆን ከሥርዓተ ትምህርቱ ይዘት፣ ከመምህራን ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን፣ የሥርዓተ ትምህርቱ አቀራረብ፣ ምዘናና ሠርቲፊኬሽን ሂደት፣ የተማሪዎች ዳራ፣ ተቋማዊ ለውጥ እንዲሁም የነባሩ ሥርዓተ ትምህርት ግምገማና ሊሻሻሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድረገው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር ቴዎድሮስ አክለውም በክፍል አምስት ላይ “የሥርዓተ ትምህርቱ የመማር ብቃቶች” በሚል ርእስ ባቀረቡት ማብራሪያ፡- ዶግማዊ የመማር ብቃት፣ ፖለቲካዊ የመማር ብቃት፣ ኢኮኖሚያዊ የመማር ብቃት፣ ማኅበራዊ የመማር ብቃትን ሌሎችንም ጉዳዮች አንሥተዋል፡፡

ቀጥሎም በሁለቱ የትምህርት ባለሙያዎች የቀረቡትን ዝርዝር ነጥቦች መነሻ በማድረግ በአራት መሠረታዊ የመወያያ ርእሰ ጉዳዮች ማለትም፡- ለተማሪዎች ምን ምን ይዘት ያላቸውን ትምህርቶች እናስተምራቸው? የትምህርት አቀራረቡ በምን መልኩ ይሁን? የማኅበረ ቅዱሳን የመምህራን ትምህርት ሥልጠና በተሻለ ሁኔታ እንዴት ይቅረብ? የምዘናና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ አስመልክቶ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም ከታዳሚው የቀረቡትን አስተያየቶች በመቀበል ጠቃሚ ግብአቶችን እንዳገኙና በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸው ነጥቦችን በመለየት እንደሚሠሩ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ባለሙያዎቹ በመግለጽ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ለመጀመሪያ ጊዜ ለግቢ ጉባኤት ተማሪዎች የሚሆን ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ ተግባራዊ ያደረገው በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ሲሆን ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ሥርዓተ ትምህርቱን የበለጠ ውጤታማና ዘመኑን የዋጀ አድርጎ ለማቅረብ አሁን እየተሠራበት ያለውን ሥርዓተ ትምህርት በ፳፻፪ ዓ.ም ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ለግቢ ጉባኤያት ተተኪ መምህራን እና አመራሮች ሥልጠና ተሰጠ

በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ከማእከላትና ግቢ ጉባኤያት ጋር በመተባበር ከሐምሌ ፩ – ፴ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ድረስ  ለተተኪ መምህራን የደረጃ ሁለት  እና ለአመራሮች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና መሰጠቱን በማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት ማደራጃና የአቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል አስታወቀ፡፡

ሥልጠናው በሀገር ውስጥ በሚገኙ ስድስት ማስተባበሪያዎች በ፲ ሥልጠና ማእከላት የተሰጠ ሲሆን ፫፻፸፩ የደረጃ ሁለት ተተኪ መምህራንና ፫፻፴፬ አመራሮች መሳተፋቸው የተጠቀሰ ሲሆን   በደረጃ ሁለት የመምህራን ሥልጠና ከወሰዱት መካከል ፷፩ መምህራን በአፋን ኦሮሞ የሠለጠኑ መሆናቸውን ዋና ክፍሉ ገልጿል፡፡

ተተኪ መምህራኑ ዐሥራ አንድ የትምህርት ዓይነቶችን ማለትም ትምህርተ ሃይማኖት፣ ነገረ ማርያም፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ክርስቲያናዊ ሕይወት እና ሥነ ምግባር፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ እና የስብከት ዘዴ፣ ትምህርተ አበው፣ ኦርቶዶክሳዊ የጾታ ትምህርት እና የማማከር አገልግሎት፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ነባራዊ ሁኔታዎች እና የሰባክያነ ወንጌል ድርሻ በሚሉ ትምህርቶች ለአንድ ወር ሲሠለጥኑ ቆይተው ተመርቀዋል፡፡

የግቢ ጉባኤያት አመራሮች ሥልጠናም ለአንድ ሳምንት የተሰጠ ሲሆን የመሪነት ክህሎት፣ ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? ኦርቶዶክሳዊ ሕይወትና ክህሎቱ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአመራርነት ሚና ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ፣ ግቢ ጉባኤያትና መገለጫ ጠባዮቻቸው፣ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ፣ ማኅበረ ቅዱሳን እና አገልግሎቱ በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ሥልጠናው እንደተሰጣቸው በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ማደራጃና የአቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል፡፡

ለተተኪ መምህራኑና ለአመራሮቹ ከተሰጡት ሥልጠናዎች በተጨማሪ ሠልጣኞቹ ለሚያነሷቸው ጥያቆዎች ምላሽ፣ የምክክር እና የውይይት መርሐ ግብሮች ተካሂደዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥ በሚገኙ ፬፻፴፩ እና በውጭ ሀገራት በ፳፫ ግቢ ጉባኤያት፣ በአጠቃላይ በ፬፻፶፬ ግቢ ጉባኤያት መንፈሳዊ ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በክረምት ምን ይጠበቅባቸዋል?

አሸናፊ ሰውነት

ግቢ ጉባኤያት ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በዓለማዊና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ሆነው ሀገርንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በታማኝነት ያገለግሉ ዘንድ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበትና ክርስትናን በተግባር የሚገልጹበት ቦታ ነው።

ወጣትነት የምንለው ደግሞ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ከሃያ እስከ ዐርባ ዓመት ያለው ዕድሜ ነው፡፡ይህ የዕድሜ ክልል የእሳትነት ባሕርይ ጎልቶ የሚታይበት ጊዜ ሲሆን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ከራስ አልፎ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናውን መልካም ፍሬን ማፍራት የሚቻልበት ወርቃማ ጊዜ ነው። ነገር ግን በተቃራኒው የወጣትነት ዕድሜን በመልካም መንገድ መምራት ካልተቻለ ከራስ አልፎ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን መጉዳትን ያስከትላል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ግን የመንፈሳዊ ሕይወትን ጉዞ ጀምረዋልና ከራሳቸው አልፈው ለሌላው በመኖር እነርሱ የጀመሩትን መንፈሳዊ ሕይወት ጓደኞቻቸውም እንዲጀምሩና የክርስቶስ የፍቅሩን ጣዕም እንዲቀምሱ በማድረግ ኦርቶዶክሳዊና ማኅበራዊ ግዴታቸውን መወጣት ይገባቸዋል። እነዚህ የሩቅ መንገደኞች በክረምት ወቅት መደበኛ ትምህርታቸው ለዕረፍት በመዘጋቱ በዚህ ወቅት ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? ስንል ከሚጠበቅባቸው ተግባራት ውስጥ ሁለቱን እንመለከታለን።

. መማር፡- እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ዐዋቂ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ ዕለት ዕለት በሚያደርገው እንቅስቃሴም አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ፣ ክፉውንና ደጉን የመለየት ነፃነት ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን ይህንን ስጦታ የሚጠቀሙበት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በጎውን በመተው ክፋትንም በማድረግ ኃጢአትን በራስ ላይ በማንገሥ እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል” እንዲል እስራኤላውያን ለተለያዩ የኃጢአት ሥራዎች ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠታቸው እግዚአብሔር በነቢዩ ሆሴዕ ላይ አድሮ ገሥጿቸዋል፡፡ (ሆሴ.፬፥፮) አባቶቻችንም “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” በማለት እንደሚናገሩት በዘመናችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከሚፈትናት ነገር አንዱ የምእመናን ስለ ሃይማኖታቸው ለመማር የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ መሆን ነው፡፡

ለመማር ጥረት የሚያደርግ ትውልድ ያውቃል፣ የሚያውቅ ደግሞ በቀላሉ ለክፉ ሥራ አይጋለጥም፤ ዘወትር ለመልካም ሥራ ይተጋል እንጂ፡፡ ስለዚህ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በዚህ ዘመን በፍጥነት እየተለዋወጠች ባለች ዓለም ላይ እንደ አንድ ኦርቶዶክሳዊ የድርሻን ለመወጣት በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መንገዱን ማሳየትና ማሳወቅ  እንደ ግዴታ ሊቆጥሩት ይገባል። የማወቂያ አንዱ መንገድ ደግሞ መማር ሲሆን ዕውቀት ደግሞ ስለ አንድ ነገር ያለን መረዳት ወይም ግንዛቤ ነው፤ ዕውቀት ሥጋዊና መንፈሳዊ ተብሎ በሁለት ይከፈላል።

መንፈሳዊ ዕውቀትን ስንመለከት ለማገልገልም ሆነ ለመገልገል አስፈላጊ ነው። ከሐዋርያትም ታሪክ የምንማረው ይህንኑ ነው። በቅድሚያ ከጌታችን እግር ሥር ተማሩ፤ የተማሩትን ደግሞ   በቃልና በተግባር ፈጸሙት። የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችም በግቢ ቆይታቸው የተማሩትን መንፈሳዊ   ትምህርት ለማጠናከር በደረጃቸውና እንደ አካባቢያቸው ምቹ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚሰጡ ትምህርቶችን ጊዜ ሰጥቶ መማር ይጠበቅባቸዋል። ይህ ከሆነ በመነሻችን ላይ እንደ ጠቀስነው በግቢ ጉባኤ ቆይታቸው በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ሆነው ለመውጣት የሚያደርጉትን ሩጫ ያቀልላቸዋል።

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ወጣቶች እንደመሆናቸው መጠን ከስሜታዊነት ርቀው ዕውቀትን ፍለጋ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ከሐሰተኛ ትርክቶችና የምዕራባውያን አእምሮ በራዥ ትምህርቶች በመራቅ በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ላይ ሊገነቡ ይገባል፡፡ የቀደምት ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ታሪክ የሚነግረን ዕውቀትና ጥበብን አጥብቆ ፈላጊዎች መሆናቸውን ስለሆነ እነርሱን አርአያ በማድረግ የወደፊት የሕይወት አቅጣጫቸውን በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ላይ መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከላይ የተነሡት መሠረታዊ ጉዳዮችን ወደ ተግባር ለመቀየር በሚደረግ ጥረት ውስጥ ችግሮች አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡- ስሜታዊነት፣ የዓላማ አለመኖር፣ የሚያስፈልጋቸውን   አለማወቅ፣ ቁርጥ ውሳኔ አለመወሰን፣ ነገሮችን በሥጋዊ ዓይን ብቻ ማየት፣ የአብነት ትምህርትን ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ብቻ ነው ብሎ ማሰብና ሌላ ጊዜ እደርስበታለሁ ብሎ መዘናጋት፣ …  ተጠቃሾች ናቸው። የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በዚህ ክረምት እነዚህንና ሌሎችም ከመንፈሳዊ ጉዟቸው ሊያደናቅፉ ከሚችሉ ነገሮች በመራቅ ለዕውቀት ልዩ ትኩረት በመስጠት መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ሊያንጹ ይገባል፡፡

. ማገልገል፡- አገልግሎት እግዚአብሔርን የመውደዳችን አንዱ መገለጫ ነው። ማገልገል ስንል የግድ ሰንበት ትምህርት ቤት ገብተን አልያም ዐውደ ምሕረት ላይ አትሮንስ ተዘርግቶ ብቻ ላይሆን ይችላል። ቅዱስ ጳውሎስ አገልግሎትን “ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን፤ በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት መልካምን ነገር እናስባለንና” በማለት ገልጦታል፡፡ (፪ኛቆሮ. ፰፥፳-፳፩) ስለዚህ ጊዜና ቦታ መርጠን ሳይሆን የትም ቢሆን መቼም የምናደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ በሥርዓትና በአግባቡ ማድረግ ተገቢ ነው።

ይህም ማለት መንፈሳዊ አገልጋይ በመንፈሳዊና በማኅበራዊ ሕይወቱ ራሱን በመጠበቅ ለሰዎች እንቅፋት ሊሆኑ ከሚችሉ ድርጊቶችም በመራቅ ሊኖር ይገባል፡፡ ምክንያቱም ክርስትና በቃልም፣ በተግባርም የሚገልጥ ነውና፡፡ አገልጋይ ልቡናው በፍቅረ እግዚአብሔር የተሞላ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር መልካም እንደሆነ ቀምሶ ያየና ሌሎችንም ወደዚህ ሕይወት እንዲመጡ የሚጋብዝ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ቀጠሮ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም የመዳን ቀን አሁን ነውና።

በአገልግሎት ውስጥ ያለ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዳይመላለስና አገልግሎቱንም በትጋት እንዳይፈጽም ከራሱ፣ ከሰይጣንና ከአካባቢ በሚመነጭ ፈተና ሊፈተን ይችላል፡፡ አንድ ክርስቲያን እነዚህ ሁሉ የግድ ሊጠብቃቸው የሚገቡ ናቸው እንጂ አገልግሎት አልጋ በአልጋ ሊሆን እንደማይችል መረዳት ያስፈልጋል። ያ ቢሆን ኖሮ ቅዱሳን ሐዋርያት በመቀጠልም ሰማዕታት ብሎም ሐዋርያነ አበው ያ ሁሉ መከራና ሥቃይ ባለደረሰባቸውም ነበር።

ስለዚህ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ለአገልግሎት ያላቸውን አመለካከት በማስተካከልና ነገ አገለግላለሁ ከማለት ወጥተው በቅንነት ሊያገለግሉ ይገባል። ስለሚበሉት፣ ስለሚጠጡት፣ ስለሚለብሱት፣ ነገ ስለሚኖራቸው መኖሪያ ቤት፣ ስለሚይዙት መኪና፣ ስለ ሥልጣንና መሰል ነገሮች በማሰብ ቁሳዊ ብቻ መሆን ሳይሆን ለራሳቸውና ለሌሎች ድኅነት ሊተጉ ይገባል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አገልግሎት ስላለን አንታክትም” በማለት እንዳስተማረው (፪ኛቆሮ.፬፥፩) እንደ አባቶቻችን ዕለት ዕለት መጨነቅ የሚገባው ስለ የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ መሆን አለበት። ለአንድም ሰው ቢሆን የድኅነትን መንገድ ማሳየትና መምራት ዋጋ ስላለው መድከም፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይም መሠማራት፤ የእግዚአብሔርን ቃል መናገር ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ አካሄዳችሁንም አይተው የማን ፍሬ እንደሆናችሁ ያውቃሉና እንደተባለው።

በመጨረሻ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በክረምት ወቅት ማድረግ ስላለባቸው ጉዳዮች በተመለከተ መማርና ማገልገልን የሚሉትን ነጥቦች አነሣን እንጂ በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ይጠብቋቸዋል፡፡ እነዚህንም በማከናወን ሂደት ውስጥ ዓላማና ግብ ያላቸውን ዕቅዶች በማውጣት ለተግባራዊነቱም ቁርጥ ውሳኔና ጥረት በማድረግ፣ እግዚአብሔርን በጸሎት በመጠየቅና አገልግሎቱም ፍሬ ያፈራ ዘንድ በመትጋት ክረምቱን በመንፈሳዊ አገልግሎት ማሳለፍ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጾመ ፍልሰታ

በሳሙኤል ደመቀ

ጠቢቡ ሰሎሞን አስቀድሞ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት በትንቢት ተናግሯል፡- “ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ” በማለት (መኃ. ፪÷፲)፡፡ ፍልሰት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሔድ መወሰድ፣ መሰደድ፣ መፍለስ የሚል ፍቺ ይኖረዋል፡፡ ፍልሰታ ቃሉ የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴ ሴማኒ ዕፀ ሕይወት ወደአለበት ወደ ገነት፤ ኋላም ከዕፀ   ሕይወት ሥር መነሣቱን የሚያመለክት ነው፡፡

የፍልሰታ ለማርያም ጾም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ከሰባቱ የዐዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ድረስ የምንጾመው ጾም ሲሆን ጀማሪዎቹም ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው፡፡ የጌታችን እናት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤና ዕርገት ያዩ ዘንድ ጾመውታልና፡፡ የእመቤታችን ፍቅር እንዲበዛልን ልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከበረከቷ እንዲከፍለን፣ በዓለም ካለ መከራና ችግር በአማላጅነቷ ጥላ ከልሎ እንዲያሳልፈን ስለምንማጸንበት መምጣቱን በፍቅር የምንጠባበቀው የጾም ጊዜ ነው የፍልሰታ ለማርያም ጾም፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአፅብ ለኵሉ፤ ሞትስ ለሚሞት ይገባዋል፤ የማርያም ሞት ግን ከሁሉ ያስደንቃል” በማለት እንዳመሰገነው እመቤታችን ከፍጥረት ሁሉ የምትከብር ከሁሉ ከፍ ያለች ብትሆንም በተፈጥሮ ከሰው ወገን ናትና እንደ ሰው ትሞትን ትቀምስ ዘንድ ስለሚገባ ቅዱሳን እያመሰገኗት በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋለች።

ቅዱሳን ሐዋርያትም አስቀድሞ ሞቷ በመንፈስ ቅዱስ ስለተገለጸላቸው ከያሉበት ተሰባስበው  የተቀደሰ ሥጋዋን ገንዘው ለመቅበር ወደ ጌቴሴማኒ ሲሄዱ አይሁድ “ቀድሞ ልጇ ሞተ፣ ሞትንም ድል አድርጎ ተነሣ ይላሉ፤ አሁን ደግሞ እናቱ ሞታ ተነሣች እያሉ እንዳያስቸግሩን   አስከሬኗን በእሳት እናቃጥለው” በማለት በክፋት ተነሡ፡፡ ምክንያቱም የጌታችን ከሞት መነሣትና ማረግ በዓለም ሁሉ እየታመነበት ስለመጣ እርሷም እንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ያስተምራሉ በሚል ፍርሃት ነበር፡፡ ከአይሁድ ወገን የሆነ ታውፋንያ የተባለ ብርቱ ሰው የእመቤታችን የተቀደሰ ሥጋዋ ያረፈበትን ቃሬዛ ከቅዱሳን ሐዋርያት ለመንጠቅ ሲሞክር መልአከ እግዚአብሔር ተገልጾ በእሳት ሰይፍ እጆቹን ቆረጣቸው። ቅዱስ ጴጥሮስም ወደ  እመቤታችን ቢለምን በእመቤታችን አማላጅነት የታውፋንያ እጆቹ እንደነበሩ ተመልሰውለታል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችን በመላእክት ዝማሬ ታጅባ በደመና ነጥቆ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡  ይህንንም ከወንጌላዊው ከቅዱስ ዮሐንስ በቀር ለሌሎች ቅዱሳን ሐዋርያት ለጊዜው አልተገለጠላቸውም ነበር። ቅዱሳን ሐዋርያትም ለእመቤታችን ካላቸው ፍቅር የተነሣ ለምን አልቀበርናትም? ለምንስ የሥጋዋ ምሥጢር ለቅዱስ ዮሐንስ ተገልጾ ለእኛ ይሰወረናል? በማለት መንፈሳዊ ቅናት እየቀኑና እያዘኑ ቆይተው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ በጾምና በጸሎት ቆይተው ነሐሴ ፲፬ ቀን ሥጋዋ ተሰጥቷቸው በታላቅ ክብርና ምስጋና በጌቴሴማኒ ቀበሯት። በ፫ኛውም ቀን ነሐሴ ፲፮ በልጇ ሥልጣን ከተቀበረችበት ተነሥታ በታላቅ ክብር ዐርጋለች።

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አርጋኖን በተባለ ድርሰቱ እመቤታችንን በከበሩ ደንጊያዎች እየመሰለ የሚያመሰግንበት ክፍል አለው፡፡ በዚህ ምስጋናው በምሳሌ እመቤታችንን ካመሰገነበት የደንጊያ ዓይነቶች አንደኛው የደወል ደንጊያ ነው፡፡ ለምን የደወል ደንጊያ እንዳላት ሲያብራራ እንዲህ ይላል፡- “አንዲት በምጥ የተያዘች ሴት የደወል ደንጊያ ሲመታ ብትሰማ ልቡናዋ በድምጹ ውበት ስለሚመሰጥ ምጧን እንደምትረሳና እስከምትወልድ ድረስ ሕመሙ አይሰማትም” በማለት ጠቅሶ ሰማዕታትም ከእመቤታችን ፍቅር በመነጨ የሚደርስባቸውን መከራና ሕማም እንደሚዘነጉት ይገልጻል፡፡ በፍልሰታም እንደዚሁ ነው፡፡ ከሕፃናት እስከ አረጋውያን ያሉ ወንዶችም ሴቶችም ለእመቤታችን ካላቸው ፍቅር በመነጨ ረኀቡና ጥሙ ሳይታወቃቸው ሳይመረሩ በደስታ ይጾሙታል፡፡

የጾሙ ጣዕም የመብልን አምሮት የሚያስንቅ ነው፡፡ መንፈሳዊነት በሰውነታችን እንዲሰለጥን ያደርጋል፡፡ ይኸውም የእመቤታችን በረከት ውጤት ነው፡፡ ጾሞ ለመጠቀም ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቆይታ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተመራቂዎች ጋር

ክፍል ሦስት

በእንዳለ ደምስስ

“ትምህርቴን በስኬት እንዳጠናቅቅ የረዳኝ ግቢ ጉባኤ ነው” (ዲ/ን አሰፋ አያሌው)

የክፍል ሦስት እንግዳችን ምሥራቀ ግዮን ኮሌጅ (የግል ኮሌጅ) በነርሲንግ ትምህርት ክፍል ተመራቂ የሆነው ዲ/ን አሰፋ አያሌው ነው፡፡ ዲ/ን አሰፋ ደሴ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው ምሥራቀ ግዮን ኮሌጅ (የግል ኮሌጅ) በነርሲንግ ትምህርት ክፍል ከኮሌጁ ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሰባት (3.97) በማምጣትና ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡

ዲ/ን አሰፋ የምሥራቀ ግዮን ጉባኤ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን ከትምህርቱ በተጨማሪ የአብነት ትምህርቱን ተከታትሎ ዲቁና ተቀብሏል፤ ዐራተኛ ዓመት ላይ ደግሞ የተመራቂዎች ኮሚቴ (Graduation Committee) ሰብሳቢ ሆኖም አገልግሏል፡፡

ኮሌጅ ከገባ በኋላ የገጠመውን ሲገልጽ፡- “ኮሌጅ እንደገባሁ ግቢ ጉባኤ ውስጥ ለመሳተፍ አልሞከርኩም፡፡ ነገር ግን ከሁለተኛ ዓመት ጀምሮ ያለማቋረጥ ነው በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሰጠውን ተከታታይ ትምህርት ለመማር የቻልኩት፡፡ ጊዜዬን በእቅድ እንድጠቀምና ከመደበኛ ትምህርቴ ጋር አጣጥሜ እንድጓዝ፣ በስኬታማነት እንዳጠናቅቅም የረዳኝ ግቢ ጉባኤ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ግቢ ጉባኤ ውስጥ መሳተፍ እንደጀመርኩ የአብነት ትምህርቱንም ጎን ለጎን መከታተል ጀመርኩ፡፡ በዚህም መሠረት የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ተሳክቶልኝ ዲቁና ለመቀበል በቅቻለሁ፡፡ አሁንም ከግቢ ከወጣሁ በኋላ የአብነት ትምህርትን ለመማር እንደ እቅድ ይዣለሁ፡፡ “ በማለት ግቢ ጉባኤ በሕይወቱ ውስጥ ያሳረፈውን በጎ ተጽእኖ ይገልጻል፡፡

የጊዜ አጠቃቀምን በተመለከተም፡- “የመጀመሪያ ዓመት ላይ ጊዜዬን በአግባቡ ለመጠቀም አልሞከርኩም በተቃራኒው ሌሎች ጓደኞቼን ለመምሰልና በዙሪያዬም የነበሩ ሊያዘናጉ ከሚችሉ ነገሮች ለመራቅ እንኳን ሙከራ አላደርግም ነበር፡፡ ነገር ግን ግቢ ጉባኤ መሳተፍ ከጀመርኩ በኋላ በጊዜ አጠቃቀም ዙሪያ ምክርና ትምህርትም ይሰጠን ስለነበር በትክክል ተጠቅሜበታለሁ፡፡ ዐራተኛ ዓመት ላይ ግን የተመራቂ ተማሪዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ (Graduation Committee) ሆኜ ማስተባበር ተጨምሮብኝ ስለነበር ትንሽ ሁሉንም አጣጥሞ ለመጓዝ ከብዶኝ ነበር፡፡ መደበኛ ትምህርቴ፣ ግቢ ጉባኤ፣ የአብነት ትምህርቴ፣ ጥናት እና የተመራቂ ተማሪዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ መሆኑ አጨናንቆኝ የነበረ ቢሆንም እግዚአብሔር ረድቶኝ ከዩኒቨርሲቲው ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሰባት አጠቃላይ ውጤት በማምጣት የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚ ለመሆን በቅቻለሁ፡፡ ግቢ ጉባኤ በመንፈሳዊ ሕይወቴ ጠንክሬ መጓዝ እንድችልና ውቴታማ ሆኜ ከግቢው እንደወጣ አስችሎኛል”ሲል ተሞክሮውን ገልጾልናል፡፡

ዲ/ን አሰፋ ያጋጠሙትን ችግሮች በተመለከተ ሲገልጽም “ዐራተኛ ዓመት ላይ የመመረቂያ ዓመት ስለነበር የጊዜ እጥረት እየገጠመኝ እየተጨናነቅሁ በአግባቡ መጓዝ አቅቶኝ ነበር፡፡ በተለይም ከምረቃ ጋር ተያይዞ በርካታ ሥራዎችን እንሠራ ስለነበር በከፍተኛ ሁኔታ የጥናት ጊዜዬን ይሻማብኝ ነበር፡፡ በተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲው መውጫ ፈተና (Exit Exam) ዝግጅት ጋር ተያይዞ ማጥናትን ይጠይቅ ስለነበር ከባድ ጊዜ ለማሳለፍ ተገድጄ ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አግዞኛልና ጎዶሎነቴን እየሞላ በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ ችያለሁ፡፡”

ዲ/ን አሰፋ እርሱ ያለፈበትን ሕይወት መነሻ በማድረግ ባስተላለፈው መልእክትም “ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገቡ ተማሪዎች የምመክረው ከመጀመሪያው ጀምሮ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ለመሳተፍ ወስነው መምጣትና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ነው፡፡ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ማሳለፋቸው ጠንካሮችና የዓላማ ሰው እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ እኔ በመጀመሪያ ዓመት ላይ በግቢ ጉባኤ አለመሳተፌ ውጤቴ ላይ ዋጋ አስከፍሎኛል፡፡” ሲል መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

ልዩ ማስታወሻ ከአዘጋጁ፡-

ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ሠላሳ አንድ ዓመታት ግቢ ጉባኤ ላይ በመሥራት የተጣለበትን አደራና ኃላፊነት ለመወጣት ክፍተኛ ጥረት አድርጓል፣ በማድረግም ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ጥረቱ በርካቶችን በየከተኛ ትምህርት ተቋማት መሠረታዊ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በማስተማር በአባቶች ቡራኬና በአደራ መስቀል እያስመረቀ ይገኛል፡፡ ብዙዎችም ለውጤታማነታቸው ማኅበሩ በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሰጠውን መንፈሳዊ ትምህርት በመከታተላቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያውቁ፣ እምነታቸውን ጠንክረው እንዲይዙ፣ በሥነ ምግባር ታንጸው በየተሠማሩበት ቦታና ሙያ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን በማገልግል የድርሻቸውን መወጣት እንዲችሉ እንደረዳቸው ይመሠክራሉ፡፡

የተከበራችሁ የድረ ገጻችን ታዳሚዎች በተከታታይ በሦስት ክፍል የወንድሞችና የእኅቶች ይግቢ ጉባኤ ተሞክሮ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነውና ወደፊት የሚገቡ ተማሪዎች አርአያነታቸውን ተከትለው እንዲጓዙ ያደርጋቸዋል በሚል ከብዙ በጥቂቱ ያቀረብንበትን ዝግጅት በዚሁ እንቋጫለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት እንዲሁም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፡- እግዚአብሔር አምላካችን በይቅርታውና በምሕረቱ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ አምስት ዓመተ ምሕረት የድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ።

ወእምኵሉሰ ዘይቀድም ተፋቀሩ በበይናቲክሙ በምልአ ልብክሙ እስመ ተፋቅሮ ይደፍኖን ወይደመስሶን ለኵሎን ኃጣውእ፤ ከሁሉ አስቀድሞ በሙሉ ልባችሁ እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ፣ መፋቀር ሁሉንም ዓይነተ ኃጢአት ይሸፍናልና ይደመስሳልምና” (፩ጴጥ. )

ሁላችንም እንደምናውቀው የቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ መሠረትና ጣርያ ወለልና ግድግዳ በፍቅርና በፍቅር ብቻ የተገነባ ነው፤ ፍቅር እግዚአብሔር ዓለምን ያዳነበት መድኃኒት ነው፣ ፍቅር የጥላቻና የመለያየት ግንብን ንዶ ይቅርታንና አንድነትን የሚገነባ ጠንካራ ዓለት ነው፤ ፍቅር መጽናናትንና ደስታን የሚያፈራ ጣፋጭ ተክል ነው፤ በፍቅር ለፍቅር የሚደረግ ሁሉ ፍሥሐን እንጂ ጸጸትን አያስከትልም፤ በመሆኑም በሰብኣዊ ድክመት ምክንያት ሰዎች ፍቅርን ሙሉ በሙሉ በሚፈለገው ደረጃ ባንጠብቀውም በዓለማዊም ሆነ በመፈንሳዊ ሕይወት ከፍቅር የበለጠ ጠቃሚ ነገር የለም፤ ፍቅር የማይሻርና ለዘላለሙ ጸንቶ የሚኖር እንደሆነ በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቦአል፤ ምክንያቱም ፍቅር ከሞት ቡኋላም ቢሆን በእግዚአብሔር መንግሥት ይቀጥላልና ነው፤ ዛሬ የሚጀመረው የድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታም በፍቅር ለፍቅር የተፈጸመ ነው፣ ይኸውም ቅዱሳን ሐዋርያት የድንግል ማርያምን የማረፊያ ቦታ ለማየት ሲሉ የጾሙት ጾም ነው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት የገለፁት ፍቅረ ድንግል ማርያምን ብቻ ሳይሆን ያረፈችበትንም ቦታ ጭምር ያመለከተ ነበረ፥ ይህ ሊሆን የቻለው ከልብ የሆነ እውነተኛ ፍቅር በሐዋርያት ዘንድ ስለነበረ ነው፡፡

እኛም ዛሬ የምንጾመው ይህንን የማርያም ጾም እንደ አበው ሐዋርያት ፍቅረ ድንግል ማርያም በልባችን ውስጥ ተተክሎ ስላለ ነው፤ እግዚአብሔር በፍቅርና በሃይማኖት የሚቀርብለትን ሁሉ ይቀበላልና የሐዋርያትን ጾምና ጸሎት ተቀብሎ ጥያቄአቸውን መልሶአል፡፡ ዛሬም ይህንን ጾም የምንጾመው እግዚአብሔር ጾማችንን ተቀብሎ የልባችንን መሻት ይፈጽምልናል ብለን ነው፣ በፍቅርና በሃይማኖት እስከ ጾምን ደግሞ እግዚአብሔር ይቀበለናል። 

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

እንደ እግዚአብሔር ቃልም እንደ አባቶቻችን ትውፊትም የጾመ ፍልሰታ ጾም ሲጾም የበደለ ይቅርታ ጠይቆ፤ ተገቢውንም ካሣ ከፍሎ፣ ቂም በቀሉን አሰርዞ፣ ፍቅርን መሥርቶ ነበረ፤ የተበደለም በበኩሉ ዕርቅን አውርዶ፣ ይቅርታን ሰጥቶ የአእምሮ ማለስለሻና ማስረሻ የሆነውን ካሣውን ተቀብሎ ቂሙንና በቀሉን ከአእምሮው አውጥቶና አጽድቶ፣ ለእግዚአብሔር ስል ከልቤ ይቅር ብያለሁ ብሎ፤ ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ በፍቅር ይታረቃል፡፡

በዚህ ሁኔታ ፍጹምና ልባዊ ፍቅር ተይዞ ሲጾም ሁሉም ዓይነት ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ይደመሰስለታል። እግዚአብሔርም ይቅርታ ጠያቂውንም፣ ይቅርታ ሰጪውንም አሸማጋዩንም ይባርካል ።ማኅበረ ሰቡም በዚህ ቅዱስና ሃይማኖታዊ ባህልና ትውፊት ተጠብቆ ለብዙ ዘመናት አንድነቱንና ሃይማኖቱን ወንድማማችነቱንና ነጻነቱን አስጠብቆ እስከ ዛሬ ደርሶአል፤ ይህ ለሀገራችን ታላቅ የሆነ የእግዚአብሔር በረከት ነበረ፤ ይህ እውነተኛ በረከት በአሁኑ ጊዜ ቸል በመባሉ ፈተናችን በዝቶአል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ሰው በኃጢአት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ ጥልና መገዳደል በየትኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ሀገር በየትኛውም ማኅበረ ሰብ ይከሠታል፣ ዛሬም በሀገራችን በተፈጠረው አለመግባባት ከባድ ችግር ተፈጥሮአል፣ የሚያስገርመው ነገር ቢኖር እንዴት እንደ ባህላችንና እምነታችን በቀላሉ በዕርቅና በይቅርታ ማስተካከል አቃተን የሚለው ነው፤ የዘመናችን ልዩ ነገር ይህ ነው፤ ለዚህም ብዙ የተለያየ ምክንያት ሊኖረው ይችላል፤ በሃይማኖት ዓይን ሲታይ ግን ለእግዚአብሔር ቃል የምንሰጠው ክብር በእጅጉ ስለተቀነሰ ነው የሚል ሆኖ ይገኛል፤ ይህ ዝንባሌ አሁን ላለውም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ አደገኛ ስለሆነ የኦርቶዶክስ ሕዝበ ክርስቲያንም ሆነ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን በጥልቀት ሊያጤኑትና ሊያርሙት ይገባል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናንት!

ሽማግሌ የሀገር በረከት ነው፤ አስታራቂ ሽማግሌ የችግር ሐኪምና ፈዋሽ ነው፤ የፍቅርና የተግባቦት መሐንዲስም ነው፤ በእግዚአብሔርም “የሚያስታርቁ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው” ተብሎ ውዳሴ ተችሮአቸዋል፣ እነዚህን ሽማግሌዎች ተጠቅመን ችግሮቻችንን መፍታት ጊዜው የሚጠይቀው አስገዳጅ ጉዳይ ሆኖአል፤ ሁሉም ታየ፤ ሁሉም ተሞከረ፤ ዘላቂ መፍትሔ ሲያመጣ ግን አልታየም፤ እንዲያውም ችግሩ ወደ ሃይማኖት ተዛምቶ ቤተ ክርስቲያንም የገፈቱ ቀማሽ ለመሆን ተገዳለች፡፡

በተጨባጭ እንደሚታወቀው ሕዝብንና ሃይማኖትን ነጣጥሎ ሰላምን ማረጋጋጥ ከቶውኑ ሊታሰብ አይችልም፤ ምክንያቱም ሕዝብ የሃይማኖቱ ቤተሰብ ነው፣ ሃይማኖቱም በሕዝቡ መንፈስ ውስጥ ነግሦ የሚኖር መለኮታዊ ኃይል ነውና፣ ከዚህ አንጻር “ወልድ ሲነካ አብ ይነካ እንደሚባለው ሕዝቡ ሲነካ ሃይማኖቱ ይነካል፤ ሃይማኖቱ ሲነካ ደግሞ ሕዝቡ ይነካል፤ በመሆኑም በተካሄደው ግጭት ብዙ ነገሮች መመሳቀላቸው የማይካድ ቢሆንም ችግሩ በዕርቅና በካሣ በይቅርታና በመተው ካልተዘጋ ለማንም ስለማይበጅ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለዕርቅ ዝግጁ እንዲሆኑ፣ የበደሉም እንዲክሱ የሀገር ሽማግሌዎችም የማስታረቅ ሥራን በሐቅ በገለልተኝነትና ዕንባን በሚያደርቅ ስልት እንዲሸመግሉ መንግሥትም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም

የገጠመንን ፈተና ሁሉ ሊያቀልልንና ሊያስወግድልን የሚችል እግዚአብሔር ስለሆነ በዚህ የጾመ ማርያም ወቅት ምእመናን በተመሥጦና በንሥሐ ሕይወት ለእግዚአብሔር በመንበርከክ ስለ ሰላምና ፍቅር እንዲማፀኑ፣ ካላቸውም በረከት ለተራቡትና ለተፈናቀሉት እንዲለግሱ ሁሉም ወገኖች በሆነው ነገር ይብቃን ብለው ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲቀርቡ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የጾመ ማርያም ሱባዔ ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም

 ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ነሐሴ 2015 ..