“ግቢ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን በወጣትነት ዘመናቸው ልጆቿን አቅፋ የያዘችበት ትልቁ ተቋም ነው” (ዐወቀ አበብሽ ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ)
ክፍል ሁለት
በእንዳለ ደምስስ
የተከበራችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች በክፍል አንድ ዝግጅታችን በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ በ፳፻፲፮ ዓ.ም ካስመረቃቸው ተማሪዎች ፫.፱ አጠቃላይ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫና ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነውን የዐወቀ አበብሽን ተሞክሮ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ክፍል ሁለትን እንዲህ አዘጋጅተነዋል- መልካም ቆይታ፡፡
- ካለህ ውጤት አንጻር የጊዜ አጠቃቀምህን ብታብራራልን?
የጊዜ አጠቃቀምን በተመለከተ እንደ ተማሪው ሥነ ልቡና እና አስተሳሰብ የሚወሰን ነው፡፡ በግቢ ውስጥ ብዙ ዓይነት የተማሪዎችን ባሕርይ ነው የምትመለከተው፡፡ ለጊዜ ግድ የሌለውና በመዝናናት ጊዜውን የሚያባክን፣ ራሱን በጥናት ብቻ የሚጠምድና እወድቃለሁ ብሎ የሚጨነቅ፣ ብቻውን መሆን የሚፈልግ፣ … ብዙ ዓይነት ተማሪ ነው ያለው፡፡
እኔ ግን ከመደበኛ ትምህርቴ ውጪ ጊዜዬን አብቃቅቼ ለቤት ሥራ፣ ለጥናት፣ ለአገልግሎት፣ ለቤተ ክርስቲያን እያልኩ ከፋፍዬ ሳልጨናነቅ ነው ሕይወቴን በዕቅድ የመራሁት፡፡ አንዳንድ ጊዜ የማጥናት ፍላጎት ከሌለኝ ከመተኛት ቀጥታ ወደ ቤተ ክርስቲያን ነው የምሄደው፡፡ ጸሎት አድርጌ፣ ራሴን አረጋግቼና ጥሩ ስሜት ይዤ እመለሳለሁ፡፡ ያኔ ሙሉ ዐቅም ስለሚኖረኝ ለማጥናት አልቸገርም፡፡ በጣም የሚገርምህ ክፍል ውስጥ በደንብ ስለምከታተል፣ እንዲሁም የተማርኩትን ቶሎ ስለምይዝ ለረጅም ሰዓት የማጥናት ልምዱ የለኝም፡፡ ለአላስፈላጊ ሳቅና ጨዋታም ብዙም ትኩረት አልሰጥም፡፡ ይህንን ስል ጓደኞች የሉኝም አልልም፡፡
ለሌሎች የምመክረው ነገር ቢኖር ለጊዜ ያላቸው ትርጉምና አፈጻጸም ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸው ነው፡፡ “በኋላ እደርሳለሁ” የሚለው አስተሳሰብ ከዓላማ የሚያዘናጋ በመሆኑ ሁሉንም ነገር በጊዜው ማከናወን ተገቢ ነው፡፡ በርካታ ተማሪዎች ስልቹዎች ናቸው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቤተ ክርስቲያን ቢሄዱና ጸሎት አድርሰው የጥሞና ጊዜ ወስደው መመለስ ቢችሉ መልካም ነው፡፡ በተለይ ሌሊት ኪዳን አድርሶ መመለስና ማጥናት፣ እንዲሁም ማታ ከራት በኋላ ተመራጭ የጥናት ጊዜያት ስለሆኑ ቢጠቀሙበት እላለሁ፡፡
- የጓደኛ ተጽእኖን እንዴት ተቋቋምከው?
ጊዜን በአግባቡ እንዳንጠቀም ከሚያደርጉን ነገሮች ውስጥ ጓደኛ ማብዛት ነው፡፡ የጓደኛ ተጽእኖ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ጓደኛ የራሱ የሆኑ ባሕርያት ስለሚኖሩት ወደአልተፈለገ ድርጊት ሊመራን ስለሚችል ጓደኛን ማወቅ፣ ቁጥራቸውንም መቀነስ ይገባል፡፡
በቅድሚያ የጓደኛ አመራረጥ የሚወሰነው በአንተ አስተሳሰብና ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ መምረጥ ሲባል እገሌ ይሆነኛል አይሆነኝም ተብሎ ሳይሆን በሂደት ነው፡፡ ጓደኛን ለመምረጥ ሂደትን ይጠይቃልና፤ በቅጽበት በአንድ ጊዜ የሚከናወን ስለማይሆን እዚህ ላይ ጥንቃቄ ይሻል፡፡ ጓደኛን የምታገኘው አንተ በምትውልበት፣ በምታድርበትና በምትሄድበት ስለሆነ በሂደት በአስተሳሰብ፣ ፍላጎትና ዓላማ ላይ ተመሥርቶ ነው መመረጥ ያለበት፡፡
በምትጓዝበት የሕይወት መስመር ላይ በባሕርይ አንተን የሚመስል ሰው ልታገኝ ትችላለህ፡፡ መግባባትና መጠናናት፣ ከዚያም ውሳኔ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ በጓደኛ አመራረጥ ደረጃ ከታች ክፍል ጀምሮ አብሮኝ የተማረ ጓደኛዬ አንድ ላይ ደርሶን ስለነበር አልተቸገርኩም፡፡ በተረፈ የምቀርባቸው ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ወንድሞችና እኅቶች ስለሆኑ ክፉ ጓደኛ አልገጠመኝም፡፡
- ትምህርትህ ላይ ብቻ ትኩረት አድርግ፤ ወደ ግቢ ጉባኤ እንዳትሄድ የሚል ቤተሰብ ወይም ጓደኛ አልገጠመህም?
ያደግሁት ገጠር ውስጥ ነው፡፡ ቤተሰቦቼም ገበሬዎች ስለሆኑ ስለ ግቢ ጉባኤ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ የእነርሱ ፍላጎትና ምኞት እኔ ተምሬ ጥሩ ደረጃ እንድደርስ የሚችሉትን መርዳት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ግቢ ጉባኤ እንዳልሄድ ያገደኝ ነገር አልነበረም፡፡ በርግጥ አንዳንድ ተማሪዎች ከቤተሰብ ወይም ከጓደኛ በሚደርስባቸው ተጽእኖ ምክንያት “ወደ ግቢ ጉባኤ አትሂዱ” ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ካለመረዳትና ጥቅሙን ካለመገንዘብ የመነጨ ነው፡፡ እኔ ውጤቴ ያማረ እንዲሆን የግቢ ጉባኤ ሚና ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡
- ግቢ ጉባኤ በመሳተፍህ ምን ጥቅም አገኘህ?
ግቢ ጉባኤ ውስጥ መሳተፍ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ተማሪ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ሲያጠና አይቆይም፡፡ ከትምህርት በኋላ ያለው ጊዜ በጣም ብዙ ስለሆነ ካልተጠነቀቅህ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጥ አይቀርም፡፡ በግቢም ሆነ በውጪ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ከተማሪዎች የማይጠበቁ ድርጊቶች ስለሚከናወኑ ተጋላጭ ትሆናለህ፡፡ ግቢ ጉባኤ ውስጥ ስትሳተፍ ዓላማ ያለው ሰው ሆነህ ትቀረጻለህ፡፡ ግቢ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን በወጣትነት ዘመናቸው ልጆቿን አቅፋ የያዘችበት ትልቁ ተቋም ነው፡፡ በመንፈሳዊ ትምህርት ታድጋለህ፣ በወንድሞችና እኅቶች ምክር ትታነጻለህ፡፡ ስለዚህ ግቢ ጉባኤ ውስጥ መሳተፍ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው፤ ከክፉ ነገር ትጠበቃለህ፣ በባሕርይ፣ በአስተሳሰብ፣ … አድገህና ተቀርጸህ እንድትወጣ ያደርግሃል፡፡
- ቤተ ክርስቲያን በእያንዳንዱ የግቢ ጉባኤ ተማሪ ውስጥ ያላት ድርሻ ምንድነው ትላለህ?
ቤተ ክርስቲያንን ማወቅ፣ በቃሏም መመራት፣ ወደ ቅድስናው ስፍራም ዘወትር መገስገስ እንደ አማራጭ የሚቀርብ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትሄድና ስትጸልይ የተበታተነው አእምሮህ ይሰበሰባል፤ በመንፈሳዊ ዕወቀትም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወት እያደግህ ትሄዳለህ፤ ውጤታማም ሆነህ ትወጣለህ፡፡ ስለዚህ ከራስ ጀምሮ ሀገርን ለማገልገል ቤተ ክርስቲያን ያላት ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡
በቀን ውስጥ ትምህርት ላይ የምንሆነው ከስምንት ሰዓት በላይ አይሆንም ስለዚህ ባለን ትርፍ ሰዓት ቤተ ክርስቲያን ሄደን ብንገለገል፣ እንደ ጸጋችንም ብናገለግል በረከት እናገኛለን፡፡
- በግቢ ጉባኤ አገልግሎት ውስጥ እንደ ችግር የምታነሣው ሐሳብ ካለህ?
እንደ ጅግጅጋ ግቢ ጉባኤ እንደ ችግር የማነሣው ቢኖር ዩኒቨርሲቲው ካለው ርቀት አንጻር ክትትል ያስፈልገዋል፡፡ ማእከሉንም ሆነ ግቢ ጉባኤያቱን መቃኘት፣ የጎደሉ ነገሮችን ማሟላት ላይ የዋናው ማእከል ግቢ ጉባኤት ማስተባበሪያ እገዛ ይፈልጋል፡፡ በተለይ ሦስተኛ እና አራተኛ ዓመት ላይ ለተማሪዎች የሚደረገው ክትትል ዝቅ ያለ ስለሆነ ቢታሰብበት እላለሁ፡፡
ሌላው አንዳንድ ጊዜ የመርሐ ግብር መደራረብ ይታያል፡፡ ግቢዎቹ የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የፈተና የጊዜ ሰሌዳው ሊለያይ ስለሚችል አንዱ ግቢ ፈተና ሲሆን ሌላው ትምህርት ላይ ወይም ፈተና ጨርሶ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ቢሆን፣ የመምህራን እጥረትና አቅምም ከግምት ውስጥ በማስገባት በሥልጠና ዕውቀታቸውን ማሳደግ ቢቻል ጥሩ ነው እላለሁ፡፡
- ከምረቃ በኋላ በርካታ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች መንፈሳዊነትን እዚያው የጨረሱ ስለሚመስላቸው ወደ አገልግሎት ሲመጡ አይታይም፡፡ አንተስ ምን አስበሃል? ለሌሎችስ ምን ትመክራለህ?
የዩኒቨርሲቲው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ወዲያው ነው የተፈጸመው፡፡ የግቢ ጉባኤው መርሐ ግብር ግን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በጥሩ ሁኔታ በመንፈሳዊ ምክር፣ በወንጌል ትምህርት፣ በዝማሬና በአባቶች ቡራኬ ነው ያስመረቀንና በጣም ደስተኞች ነን፡፡ እኔ ወዲያው ነው ከግቢ ከወጣሁ በኋላ ማገልግል እንዳለብኝ ራሴን ያሳመንኩት፡፡ እስከ አሁን ከነበረኝ አገልግሎት በይበልጥ አገለግላለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልዩ ክብር ሰጥታ ነው “ልጆቼ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብላ አክብራ በቡራኬ ያስመረቀችን፡፡ ስለዚህ እኛ ደግሞ ውለታዋን ልንመልስ ያስፈልጋል፡፡ ሰፊ አገልግሎት ውስጥ መሳተፍ ባንችል እንኳን ራሳችንን ጥሩ አርቶዶክሳዊ አድርገን ማነጽ በራሱ አገልግሎት ነው፡፡
አገልግሎት ከሥራ ጋር አይመችም የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከሥራ በኋላ ልናገለግል የምንችልባቸው መንገዶች በርካታ ናቸው፡፡ በሰንበት ት/ቤት፣ በሰበካ ጉባኤ፣ በማኅበራት፣ በማኅበረ ቅዱሳን መዋቅር በማእከላት፣ በወረዳ ማእከላት፣ … መሳተፍ እንችላለን፡፡ ራሳችንን ለስንፍና ከማጋለጥ ልንቆጠብ ያስፈልጋል፡፡
የእያንዳንዳችን ፀጋና የአገልግሎት መንፈስ ስለሚለያይ የሚያስተምረው ቢያስተምር፣ ይበልጥ መማር ያለበት ቢማር፣ የሚያስተባብረውም እንደተሰጠው ኃላፊነት ማገልገል ያስፈልጋል፡፡
- ተሞክሮህን ስላካፈልከን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡
እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር