ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ (ሰቈቃወ ድንግል)

ቀሲስ ዐቢይ ሙሉቀን

ክፍል ሁለት

. ሥርዐቱ

ሕጉን ጠብቀው፣ እንደ ሥርዓቱ ተጉዘው ሰማያዊውን ርስት ለመውረስ ለሚመኙት እግዚአብሔር ያስቀመጠልን ሕግና ሥርዓት የሚመች፣ የሚጥም ነው። ነገር ግን መሠረታዊ ዓላማቸው ይህ ላልሆነው፣ ጽድቁን ቢያስቡም ያለመከራ ለሥጋዊ ምኞታቸው ቅድሚያ በመስጠት ለመጽደቅ ለሚያስቡት ሕጉና ሥርዓቱ ላይመቻቸው ይችላል። ሕግና ሥርዓት ለእውነተኛ ሰው አይጎራብጥም፤ የሚጎራብጠው እውነትን መከተል ለማይፈልግ፣ ከእውነት ጎዳና አፈንግጦ በራሱ ሐሳብና ምኞት ለሚጓዝ ግን አይመችም። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው” (መዝ.፻፲፰፥፻፭) በማለት የገለጸው ለእውነተኞች የእግዚአብሔር ሕግ የሕይወት መሠረት ስለሆነ ነው። በአንጻሩ በሕግ መኖር ለማይፈልግ ግን ይመረዋል፤ ይጠፋበታልም።

. መንፈሳዊ ተጋድሎ

ሰው በልዩ ልዩ ምክንያቶች አብሮት ከሚኖረውም ሆነ ከማይኖረው ጋር ይጋጫል፣ ይጋደላል። ለምድራዊ ርስት፣ ለምድራዊ ሀብት ንብረት ብሎ የሚጛደል ይኖራል። ለመንፈሳዊው ርስት ብሎ ደግሞ ከሚታየውም ከማይታየውም ጋር ይጋደላል። ምድራዊውን ርስት ፈጽሞ አያስፈልግም ባይባልም ሰማያዊውንነ ርስት አስቦ የሚታየውን ዓለም በማይታየው ዓለም ለውጦ የሚያደርጉት ተጋድሎ መንፈሳዊ ተጋድሎ ተብሎ ይጠራል። ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚጥማቸውም የማይጥማቸውም አካላት አሉ።

. የሚጣፍጣቸው

ቅዱሳን አባቶቻችን እውነተኛውንና መንፈሳዊውን ተጋድሎ በተግባር ፈጽመው አሳይተውናል። እየጣፈጣቸውም ተቀብለውት አልፈዋል። በሃይማኖት ጸንተው የሚቀበሉት መከራ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያስገኝ ክብርን የሚያጎናጽፍ በመሆኑ ይጣፍጣል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ “ስለዚህም ቢሆን በብዙ ራእይ እንዳልታበይ ሰውነቴን የሚወጋ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ። ስለዚህም ከእኔ ያርቀው ዘንድ ጌታዬን ሦስት ጊዜ ማለድሁት። እርሱም ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይልስ በደዌ ያልቃል አለኝ፤ የክርስቶስም ኃይል በእኔ ላይ ያድር ዘንድ በመከራዬ ልመካ ወደድሁ። ስለዚህም ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበልን፣ መሰደብን፣ መጨነቅን፣ መሰደድን፣ መቸገርንም ወደድሁ፤ መከራ በተቀበልሁ ጊዜ ወዲያውኑ እበረታለሁና። (፪ቆሮ ፲፪፥፰) በማለት በእርሱ ላይ ያደረው ደዌ በፈቃደ እግዚአብሔር እንደሆነና ለምንም እንደተሰጠው ሲናገር በመከራው (በደዌው) ምክንያት የሚያገኘው ጸጋ እንዳለ ያስረዳል። ስለዚህ ጸጋ የሚያስገኝ መከራ ይጣፍጣል።

በሃይማኖት ጸንተን ምግባራችንን አቅንተን እየኖርን የሚመጣብን ቅጣት ክብር የሚያሰጥ ነው። ሐዋርያው ያዕቆብ “በመከራ የሚታገሥ ሰው ብፁዕ ነው፤ ተፈትኖ እግዚአብሔር ለሚወዱት ተስፋ ያደረገላቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና።” (ያዕ.፩፥፲፪) በማለት እንዳስተማረን መከራችን፣ ተጋድሏችን ሰማያዊ ክብርን የሚያሰጥ፣ ዘለዓለማዊ ደስታን የሚያጎናጽፍ ነው። ስለዚህ እንደዚህ ያለውን ተጋድሎ ባንጋደል ሰማያዊው ክብር ይቀርብናል። ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ የማያልፈውን፣ የማይጠፋውን፣ ዘለዓለማዊ ክብር የሚያሰጠን ስለሆነ በዚህ መንፈሳዊ ተጋድሎ አለመጽናታችን የምናስበውንና የምንመኘውን ክብር እንዳናገኝ ያደርገናል።

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ሞዕዎ ለእኩይ ኅሊና በእምነቶሙ እስመ ሠናየ ገድለ ተጋደሉ፤ መልካሙን ገድል ተጋድለዋልና በእምነታቸው ክፉውን ሐሳብ ድል አደረጉት” በማለት እንደገለጸው ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ ክፉውን ሐሳብ ጥቅምት/ ፳፻፲፫ ዓ.ም 12 ትምህርተ ሃይማኖት ፲፪ ድል የምናደርግበት ነውና እጅግ ይጥማል። ቅዱሳኑም ሰማያዊውን ዓለም እያሰቡ ተጋድሎውን ሳይሳቀቁት ይልቁንም እየጣፈጣቸውና እየተመቻቸው መከራውን በመቀበላቸውም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ተግባራዊ ክርስትናን አሳይተውናል።

. የሚመራቸው፡

ከላይ የተገለጸው መንፈሳዊ ተጋድሎ ለእነ ቅዱስ ጳውሎስ እንደጣማቸው ለነዴማስ አልጣማቸውም። እነ ቅዱስ ጳውሎስ “አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም ወከዐዉ ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት፤ ሰማዕታት በእውነት የዚችን ዓለም ጣዕም ናቁ ስለ እግዚአብሔር ደማቸውን አፈሰሱ፣ ስለመንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) እንደተባለው በመከራው ሲደሰቱ እነዴማስ ግን እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት ሳይሆን የተሰሎንቄን ከተማ መረጡ። ስለዚህ በመልካም ተጋድሎ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ መቻልን፣ ወይም መንፈሳዊውን ተጋድሎ በጸጋ መቀበልንና በሕይወት መተርጎምን ከሩቅ ለመጡት ጣፋጭ ለቅርብ ሰዎች ግን መራራ አደረገው ማለት በተጋድሎ ሰማያዊውን ዓለም እንደሚወርሱ የተሰበከላቸው የእግዚአብሔር ሕዝቦች የተባሉት እስራኤል ጸንተው መቀበል ሲያቅታቸው ከአሕዛብ ወገን የነበሩት ግን አምነው መልካሙን ተጋድሎ ተጋድለው ይህ ዓይነት ሕይወትም ጣፍጧቸው እንደተጠቀሙበት ለመግለጽ ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና አመንዝሮች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሟችኋል” (ማቴ.፳፩፥፴፩) በማለት የተናገረው ትንቢቱ የተነገረላቸው ሱባኤው የተቈጠረላቸው አምነው መቀበል ሲቸገሩ ትንቢት ያልተነገረላቸው ሱባዔ ያልተቈጠረላቸው አሕዛብ አምነው በመቀበላቸው ለክብር መብቃታቸውን ያስረዳናል።

. ንስሓው

ንስሓ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቅበት፣ ከቅዱሳን ኅብረት አንድ የሚሆንበት ታላቅ ስጦታ ነው። የመልካም አባት ስጦታ፣ የፍቅር ስጦታ እየተባለም በሊቃውንት ዘንድ ይነገራል። ይህን ታላቅ ስጦታ ተረድተውት ለሚጠቀሙበት የሚጣፍጥ ነው። ለማይጠቀሙበት ግን ፍርድን ያስከትላል። ኃጢአታቸውን እያሰቡ ያለቀሱት፣ ዘመናቸውን በአግባቡ የተጠቀሙትን ለምሳሌ ብንጠቅስ አዳም፣ ዳዊት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ በቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ እናገኛለን። ይሁን እንጂ የንስሓ ዕድሜ ተሰጥቷቸው ያልተጠቀሙበት ደግሞ እንደ ይሁዳና ሌሎችም የይሁዳን መንገድ የተከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃሉን አምነው ባለመቀበላቸውና ንስሓም ባለመግባታቸው እንዲህ ይወቅሳቸው ነበር። “ኮራዚ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ ወዮልሽ በእናንተ የተደረገ አምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው አስቀድመው ንስሓ በገቡ ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ጢሮስና ሲዶና ዕረፍትን ያገኛሉ። ቅፍርናሆም አንቺም እስከ ሰማይ ከፍ ከፍ ብትዪ እስከ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺም የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን እስከ ዛሬ በኖረች ነበር። ነገር ግን እልሻለሁ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ የሰዶም ምድር ዕረፍትን ታገኛለች።” (ማቴ.፲፩፥፳፩-፳፬)

ይህ ኀይለ ምንባብ የሚያስረደሳን መድኅነ ዓለም ክርስቶስ በአካል ተገልጦ ቢያስተምራቸው አንመለስም ብለው የንስሓ ሕይወትን ገንዘብ አለማድረጋቸውን ነው። አባ ጽጌ ድንግም “ለሀገሩ ሰዎች መራራ አደረጋት” ብሎ የገለጸው እንዲህ ያለውን በቅርብ የተገኘ ጸጋ በአግባቡ አለመጠቀምን ሲያስረዳን ነው።

. ሥጋ ወደሙ

በሰው ልጅ ሕይወት የሚገድልም የሚያድንም ምግብ አለ። አዳም ከአንዲት ዕፀ በለስ በቀር በገነት ያለው ሁሉ ሲፈቀድለት ዕፀ በለስን ግን ተከልክሏል። የተፈቀደለት ነገር በሕይወት እንዲኖር የሚያስችለው ሲሆን የተከለከለው ግን ሞትን የሚያመጣበት ነበር። የተፈቀደለት ነገርና የተከለከለው ዕፀ በለስ እንዳለ ሆኖ ብላም አትብላም የሚል ትእዛዝ ያልተላለፈበት ዕፀ ሕይወትም ነበረ። አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን ሲበላ ሞት ተፈረደበትና ዕፀ ሕይወትን ተከለከለ። “አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር ስለዚህ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ደስታ ከሚገኝባት ገነት አስወጣው” (ዘፍ.፫፥፳፪-፳፫) እንዲል።

አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን በመብላቱ ዕፀ ሕይወትን ተከለከለው። በአዳም ሕይወት ዕፀ በለስ የሚገድል ዕፀ ሕይወት ደግሞ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያስገኝ ነበር። በሐዲስ ኪዳን ላለን ምእመናን በዕፀ ሕይወት ፈንታ የታደለን ሥጋ ወደሙ ነው። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን ቅድስት ማርያምን ባመሰገነበት በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ ከፈለነ ንብላዕ እም ዕፀ ሕይወት ዘውእቱ ሥጋሁ ለክርስቶስ ወደሙ ክቡር በእንተ ፍቅረ ዚአነ፤ ከሕይወት እንጨት እንበላ ዘንድ አደለን ይኸውም ሰውን ስለመውደዱ ያደለን ሥውና ደሙ ነው” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት እንደገለጸው ሕይወትን የሚሰጠን ዘለዓለማዊ ሕይወትን ገንዘብ አድርገን እንድንኖር የተሰጠን ሥጋውና ደሙ ነው።

የተለያዩ ነገሮች የተለያየ ጠባይና ተፈጥሮ መኖራቸው ላያስደንቅ ይችላል። ዕፀ በለስና ዕፀ ሕይወት የሞትና የሕይወት እንጨት መሆናቸው ብዙ ላይገርመን ይችላል። ነገር ግን አንዱ ዕፀ ሕይወት ለአንዱ ሕይወትን የሚያድል ለሌላው ደግሞ ሞትን የሚያመጣ መሆኑ የረቀቀ ምሥጢር። ሥጋ ወደሙ ሕይወትን የሚያድላቸው እንዳሉ ሁሉ ሞትን የሚያመጣባቸው ወገኖች አሉ። እነርሱ እንማን ናቸው? የሚለውን እንመለከታለን።

. የሚጣፍጣቸው

ፈቅደውና ወደው ንስሓ ገብተው የሚችሉትን ዝግጅት አድርገው ለሚቀበሉት ሕይወት መድኃኒት ነው። ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “እሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ፤ ፈቃዱን ለሚፈጽሙ የሚያድን እሳት ነው” (ቅዳሴ ማርያም) በማለት እንደገለጸው በእግዚአብሔር ፈቃድ ለሚመላለሱት እንድንበታለን ብለው አምነው ለሚቀበሉት ሕይወት መድኃኒት ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን አስፈላጊ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ያለዚያ ሰማያዊ መንግሥትን መውረስ እንደማይቻልም አስተምሮናል። “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በኋለኛይቱ ቀን አነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛመጠጥ ነውና” (ዮሐ.፮፥፶፫-፶፭)

. የሚመራቸው

ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ ብሎ ሲያስተምር በእምነት መቀበል የተቸገሩት አይሁድ “ይህ እንበላ ዘንድ ሥጋውን ሊሰጠን እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በእርሳቸው ተከራከሩ” (ዮሐ.፮፥፶፪) በእርግጥም አምነው ለማይቀበሉት፣ ሳይገባቸው ለሚቀበሉት የማይቻል ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከላቸው መልእክቱ “አሁንም ሳይገባው ይህን ኅብስት የበላ ይህንም ጽዋ የጠጣ የጌታችን ሥጋውና ደሙ ስለሆነ ዕዳ አለበት” (፩ቆሮ.፲፫፥፳፯) በማለት ሳያምኑበትና ያድነኛል ሳይሉ ንስሓም ሳይገቡ ለሚቀበሉት ዕዳ እንደሚሆናቸው፣ እንደማይመቻቸው ያስረዳል። ሊቁ አባ ሕርያቆስም መድኃኒትነቱን ብቻ ሳይሆን የሚያጠፋ መሆኑንም “እሳት በላዒ ለአማጽያን ለእለ ይክህዱ ስሞ” ስሙን ለሚክዱት ለአመጸኞች የሚባላ እሳት ነው። በማለት ከማን አንሼ ብለው፣ እገሌ ሲቈርብ አየን ብለው የሚቀበሉት እንዳልሆነ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ላይ ሆነው ቢቀበሉት ደግሞ መፈራረጃ እንደሚሆን አስረድቷል።

በአጠቃላይ በማይመረመር ጥበቡና በልዩ ፍቅሩ የፈጠረን እግዚአብሔር አምላካችን የሚሰጠን ሁሉ መልካም ነው። ይሁን እንጂ የተሰጠንን ነገር በአግባቡ ባለመጠቀማችን ስንጎዳበት እንስተዋላለን። አንዳንዶቹ በቤቱ እየኖሩ፣ በክህነት አገልግሎት እየተመላለሱ፣ ግን ለቤቱ የሚገባና የሚመች አገልግሎት ባለመፈጸማቸው ሲጠፉበት ይስተዋላሉ። በአንጻሩ ደግሞ ከውጭ ሆነው እግዚአብሔርን በመፍራትና በመንቀጥቀጥ የሚኖሩ ግን ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው መንፈሳዊ ማንነታቸው የማይገለጥ በርካታ ሰዎች አሉ። ለዚህ ነው “ከሩቅ ለመጡት የሚጣፍጥ ለሀገሩ ሰዎች ደግሞ መራራ አደረጋት” በማለት አባ ጽጌ ድንግል የገለጸልን። በቤቱ ኖረን ለቤቱም የሚገባውን ክብር በመስጠት አገልግሎታችንን ፈጽመን ሰማያዊውን ዓለም እንዲያወርሰን እግዚአብሔር ይፍቀድልን አሜን።

ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ (ሰቈቃወ ድንግል)

ክፍል ፩

በቀሲስ ዐቢይ ሙሉቀን

የቃሉ ተናጋሪ አባ ጽጌ ድንግል ነው። ቃሉን የተናገረውም የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደቷን፣ በስደቷ ጊዜም የደረሰባትን መከራና ኃዘን አምልቶና አስፍቶ በገለጸበትና በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና አምላክን የወለደች ድንግል ማርያምንም ባመሰገነበት ክፍሉ ነው። ሙሉ ቃሉን እንደሚከተለው እንመልከተው።

“ሰሚዖ ሕፃን ለእሙ ገአራ፤ ባረከ ኰኵሐ ወአንቅዐ ማየ እምታሕተ እግራ፤ ወእምኔሁ ለጽምዓ ትስተይ አመራ፤ ከመ ኢይስተይዋ ሰብአ ሀገር ለይእቲ ማይ አምረራ፤ ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ፤ ሕፃኑ የእናቱን ጩኸት (ለቅሶ) ሰምቶ፤ ዐለቱን ባርኮ ከቆመችበት ቦታ ውኃ አፈለቀ፤ ከውኃውም ትጠጣ ዘንድ አመለከታት፤ የዚያች ሀገር ሰዎች እንዳይጠጧት ያችን ምንጭ አመረራት፤ ከሩቅ ለመጡት ግን መድኃኒት የጣፈጠችም አደረጋት።” (ሰቈቃወ ድንግል)፡፡

ይህ ኀይለ ቃል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ጋር በተሰደደች ጊዜ የደረሰባትን መከራና ሁሉን የሚችለው አምላክ ወልደ አምላክ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረጋቸው ተአምራት መካከል አንዱን የሚያስታውሰን ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናነበው ሰብአ ሰገል እጅ መንሻ ይዘው “የተወለደው የአይሁድን ንጉሥ የት አለ” እያሉ ሲመጡ በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ በቅንዐት ተነሳሳና ሊገድለው ፈለገ። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ ነገረውና በሌሊት እናቱንና ሕፃኑን ይዞ ወደ ግብፅ ሸሸ። ወንጌላዊው ማቴዎስ ይህን ታሪክ “እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ ገብፅ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ኑር አለው። እርሱም በሌሊት ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ።” (ማቴ.፪፥፲፫-፲፬) በማለት እንደጻፈው ሁሉን የሚችል ፣ ሁሉ የእርሱ የሆነ አምላክ ጠላት ተነሣበትና ስደተኛ ሆነ።

ሰው ከሀገሩ ወጥቶ ስደተኛ ሲሆን ስንቁ ያልቃል፤ ይራባል፤ ይጠማል፤ የሚሰጠው ሊያገኝም ላያገኝም ይችላል። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም በሄሮድስ ላይ አድሮ በጠላትነት እንዲነሣሣ ያደረገ ሰይጣን በሰዎች ላይ እያደረ የሚያዝንላቸው አጥተው ስለነበረ ተራበ፤ ተጠማ፣ ዐለት ሰንጥቆ ውኃ አፍልቆ የሚያጠጣው አምላክ በተዋሐደው ሥጋ ተጠማና አለቀሰ። የልጇን ልቅሶ ስትሰማ እናቱም ምርር ብላ አለቀሰች። ሁሉን የሚችል አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ቢወሰንም አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን ሲያስረዳ፣ ዐለቱን ባርኮ ውኃ አፈለቀ። ማፍለቁ ብቻ ሳይሆን ያፈለቀው ውኃ ለስደተኞች የሚጥምና የሚጣፍጥ በአካባቢው ላሉትና በክፋት ለተሞሉት ሰዎች ደግሞ የሚመር ሁለት ዓይነተ ጣዕም ያለው ውኃ ሆነ።

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይህን ምሥጢር የገለጸለት ደግ አባት አባ ጽጌ ድንግልም ከእግዚአብአብሔር ሁሉን ቻይነት አንጻር የማያስደንቅ ቢሆንም ከፍጡራን ባሕርይና ችሎታ አንጻር ግን እንዲህ እጅግ የሚያስደንቀውን ምሥጢር ገለጸልን። ሰዎች እርሱ የሰጣቸውን ውኃ ሲከለክሉት እርሱ ግን ከአንድ ምንጭ ተገኝቶ ለአንዱ ጣፋጭ ለሌላው መራራ የሆነ ተአምረኛ ውኃ አፈለቀ። ይህ እጀግ የሚያስደንቅና ልዩ የሆነ ምሥጢር ያን ጊዜ እንደ አዲስ የተጀመረ ሳይሆን ጥንትም ሀልወቱን፣ መግቦቱን፣ አምላካዊ ጥበቃውን ሲገልጽበት የኖረ፣ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ የሚኖርም ነው። ለማሳያ የሚሆነን ታሪክ እንመለከታለን።

እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት በከፋ አገዛዝ ሁለት መቶ ዐሥራ አምስት ዓመታት ያህል ኖረዋል። የገዢዎቻቸው ጭካኔ ልኩን ሲያልፍና እነርሱም አብዝተው ሲጮኹ ጩኸታቸውን ሰምቶ በሙሴ አማካኝነት ከግብፅ ምድር አውጥቷቸዋል። በጉዟቸውም ጊዜ መና ከሰማይ እያወረደ ሲመግባቸው፣ ውኃ ከዐለት ላይ እያፈለቀ ሲያጠጣቸው የነበረ መሆኑ የእስራኤልን ታሪክ የጻፈልን ሊቀ ነቢያት ሙሴ መዝግቦት እናገኛለን። በመጽሐፍ ቅዱስም “ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ከኤርትራ ባሕር አውጥቶ ወደ ሱር ምድረ በዳ ወሰዳቸው። በምድረ በዳም ሦስት ቀን ተጓዙ፤ ይጠጡም ዘንድ ውኃ አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ ከማራም ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም፤ ውኃው መራራ ነበርና፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም “መሪር” ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡሙ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አንጎራጎሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፤ በውኃውም ላይ ጣለው፤ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዐትንና ፍርድን አደረገላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። እርሱም “አንተ የአምላክህን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም መልካምን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታደምጥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብፀውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ።” (ዘፀ.፲፭፥፳፪-፳፮) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናነበው በዚህ ጥቅስም እንደተመለከትነው በወቅቱ መራራ የነበረው ውኃ በሙሴ ጸሎትና ልመና አማካኝነት በእግዚአብሔር ቸርነት ጣፍጦላቸው ጠጥተዋል። በጊዜው መጠጣታቸው ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም የሕይወታቸው መመሪያ የሚሆናቸውን አምላካዊ ቃል በሙሴ አማካኝነት አስተላልፏል። እርሱም “አንተ የአምላክህን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም መልካምን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታደምጥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብፀውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ።” እንዲል። እስራኤላውያን ሕጉን ጠብቀው፣ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው፣ እንደ ሥርዓቱ ቢጓዙ በግብፅ ላይ የወረደው መቅሰፍት እንደማይደርስባቸው እንደተነገራቸው ሁሉ ዛሬም በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር እየሠራን የተፈቀደልንን እያደረግን ያልተፈቀደልንን እየተውን ብንኖር አምላካዊ ጥበቃው ሳይለየን እንደምንኖር ያስረዳናል።

በወቅቱ መራራ የነበረውን ውኃ አጣፍጦ እንዳጠጣቸው ሁሉ በሙሴ ጸሎት በእግዚአብሔር ቸርነት ለእስራኤል ከዐለት ላይ ውኃ ፈልቆላቸው ጠጥተዋል። (ዘፀ.፲፯፥፩-፯) እግዚአብሔር ያለውን ማጣፈጥ ብቻ ሳይሆን ከሌለበት ማምጣትና መስጠትም እንደሚችል እንረዳለን። የእግዚአብሔር ቸርነት ካልተከተለን በቀር ከዐለት ላይ ውኃ ማፍለቅ አይቻለንም። እርሱ ግን የማንም ረዳት ሳያስፈልገው ከዐለት ላይ ውኃ ማፍለቅ ይቻለዋል። የኤርትራን ባሕር ከፍሎ እስራኤላውያንን ማሻገር፣ ግብፃውያንን ደግሞ በባሕር ተሰጥመው እንዲቀሩ ማድረግ ችሏል። አሁንም ሁሉን ማድረግ ይችላል።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ዕብን ዘመነንዋ ነደቅት ወይእቲ ኮነት ውስተ ርእሰ ማዕዘንት፤ ግንበኞች የናቋት ድንጋይ እርሷ የማዕዘን ራስ ሆነች።” (መዝ.፻፲፯፥፳፪) በማለት የተናገረውን መተርጉማኑ የተናቀች ደንጊያ የተባለችው ዕብነ ሙሴ እንደሆነች አስረድተዋል። ይቺ ዕብነ ሙሴ ዐሥራ ሁለት ምንጭ ያላት ለዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል እያፈለቀች የምታጠጣ፣ በፊት በኋላ በቀኝ በግራ ሁና ከለላ የምትሆን፣ ጠላት ሲመጣ ረግረግ እየሆነች የምታሰጥም፣ ቀን እንደደመና እየሆነች ከቀን ሐሩር የምትከላከልላቸው፣ ሌሊት የብርሃን ዐምድ እየሆነች የምትመራቸው እንደነበረች በትርጓሜ አስረድተዋል። (መዝ.፻፲፯፥፳፪ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡

ለእስራኤል የተደረገውን ድንቅ ተአምር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉም ያን መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ። ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ።” (፩ቆሮ.፲፥፫-፬) በማለት ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ አስረድቷል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይከተላቸው የነበረ መንፈሳዊ ዐለት በማለት የገለጸውን ይህም ዐለት ክርስቶስ ነበረ በማለት ተርጕሞታል። ሁሉን የሚችለው አምላክ ዐለቱን የውኃ መፍለቂያ ምንጭ አድርጎ የተጠማውን ያጠጣበታል፤ የተራበውን ኅብስተ መና አድርጎ ይመግብበታል፤ ለጠላት መከላከያ መሣሪያም ያደርገዋል። ይሁን እንጂ መለስ ብለን በታሪክ እንደምናስታውሰው ይህ ሁሉ የቸርነት ሥራ ለክፉዎች አይመችም ነበር። አንዱ ሲድንበት ሌላው ሲጠፋበት ኖሯል። በስደቱ ወቅት ያደረገው ተአምርም የሚያስረዳን እንዲህ ያለውን ጉዳይ ነው።

ዛሬም ለአንዱ መራራ ለሌው ጣፋጭ የሚሆን ብዙ ነገር አለ። በእርግጥ መራራም ሆነ ጣፋጭ የሚሆነው ተቀባዩ ለዚያ ነገር ከመብቃትና ካለመብቃት፣ ወዶ ፈቅዶ ከመቀበልና ካለመቀበል፣ ለሚሰጠው ነገር አስፈላጊውን ዝግጅት ከማድረግና ካለማድረግ ወዘተ የሚመጣ ነው እንጂ ስጦታው በተፈጥሮው መራራ ሆኖ አይደለም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ክፉ ነገር አይሰጥም። ሰዎች ግን በአጠቃቀም ስሕተት በመድኃኒቱም ይሞቱበታል። ይህን በተመለከተ የተወሰኑትን እንጥቀስ፡-

. የእግዚአብሔር ቃል

ከላይ እንደተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል የሚመር ሆኖ አይደለም። ከአቀባበል መለያየት የተነሣ ግን የመረራቸው፣ አሁንም የሚመራቸው አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። የጣፈጣቸውም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ ወደፊትም ይኖራሉ። የሚጣፍጣቸውንም ሆነ የሚመራቸውን እንመልከት።

. የሚጣፍጣቸው

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ጥዑም ለጕርዔየ ነቢብከ እምዓር ወሦከር ጥዕመኒ ለአፉየ፤ ቃልህ ለጕረሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ” (መዝ.፻፲፯፥፻፫) በማለት እንደገለጸው የእግዚአብሔር ቃል የሚጣፍጥ ለሕይወትም መሠረት ነው። ለዚህም ነው “ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው” ካለ በኋላ በምድር ላይ ጣፋጭ ከሚባለው “ከማርና ከወለላ ይልቅ ጣፈጠኝ” በማለት እኛ ልንረዳውና ልንገነዘበው በምንችለው አገላለጽ ነገረን። የቃሉን ጣፋጭነትና መድኃኒትነት የተረዳው የመቶ አለቃው “በቃልህ እዘዝ፤ ልጄም ይድናል” (ማቴ.፰፥፰) በማለት ፍጹም የሆነ ሃይማኖቱን ገለጠ።

መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ጊዜም ቃሉ የሚጣፍጣቸው በርካታ ሰዎች ነበሩ። በቅዱስ ወንጌል “በየምኵራቦቻቸውም ሁሉ ያስተምራቸው ነበር፤ ትምህርቱንም ያደንቁ ነበር፤ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።” (ሉቃ.፬፥፲፭) ተብሎ ተጽፎ እናነባለን። እንዲሁም በቅዱስ ወንጌል “ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆምም ወረደ፤ በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር። አነጋገሩም በትእዛዝ ነበርና ትምህርቱን ያደንቁ በር።” (ሉቃ.፬፥፴፩) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ቃሉን በደስታ የተቀበሉት እንዳሉ ነው።

በመሆኑም “ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ” እንደተባለው ቃሉን ለሚሹት፣ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ፈልገው ሲለምኑት ለኖሩት ለአበው ቀደምት፣ ለነቢያት፣ ለቅዱሳን ጣፋጭ አደረጋት። እንዲሁም ከአሕዛብ ወገን ለሆኑት፣ ከሩቅ ለመጡት፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ላልተባሉት ጣፋጭ አደረጋት።

በሌላ አገላለጽ ትንቢት ለተነገረላቸው ሱባኤ ለተቈጠረላቸው ወገኖቹ ለተባሉት እስራኤላውያን መራራ አደረጋት። ማለት እንዳይቀበሉት ዐይነ ልቡናቸው ታወረ። “ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም” (ዮሐ.፩፥፲፩-፲፫) እንዲል የተቀበሉት እንዳሉ ሁሉ ያልተቀበሉትም እንደነበሩ ልንገነዘብ ይገባል።

. የሚመራቸው

በዚህ አገላለጽ አምነው ባለመቀበላቸው አለመጠቀማቸውንና መጎዳታቸውን ለማስረዳት ነው። በመሆኑም ከአብርሃም ዘር በመወለዳቸው የሚመኩትን አይሁድን “እውነት እውነት እላችኋለሁ የአብርሃም ልጆች ብትሆኑስ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ ነበር)” (ዮሐ.፰፥፴፱) በማለት መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የወቀሳቸው እውነተኛውን ቃሉን ሲነግራቸው ማመን ባለመቻላቸው ነበር። ቃሉን አምነው ከመቀበል ይልቅ ሊገድሉት ይሹ ነበር። በእውነት መንገድ ለማይጓዝ፣ እውነትን ገንዘብ የማያደርግ አካል ምንጊዜም ቢሆን እውነት ይመረዋል። እውነቱን ስለነገራቸው ስለኃጢአታቸውም ስለዘለፋቸው ጋኔን አድሮበታል ይሉትም ነበር። “አይሁድም ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም፡፡ አንተ ሳምራዊ እንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ መናገራችን የሚገባ አይደለምን? ብለው ጠየቁት” (ዮሐ.፰፥፵፰) እንዲል።

ቃሉ ሕይወት መድኃኒት ሲሆን በሚገባ ባለመቀበላቸውና የሕይወታቸው መመሪያም ባለማድረጋቸው የተነሣ ተፈርዶባቸዋል። በዕለተ ምጽአትም መፈራረጃ ይሆንባቸዋል። ይህን አስመልክቶ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “አመ ይመጽእ ንጉሥ በግርማ መንግሥት ኵነኔ ድልው ቅድሜሁ ነፍስ ትርእድ ወመጻሕፍት ይትከሠታ ለስምዕ፤ ንጉሡ በግርማ መንግሥት በክበበ ትስብእት በመጣ ጊዜ ፍርዱ በፊቱ ነው፤ ነፍስ ትንቀጠቀጣለች መጻሕፍትም ለምስክርነት ይረቀርባሉ” (ጾመ ድጓ ዘደብረ ዘይት) በማለት ያስረዳናል። ቃሉን ሰምተው አለመጠቀማቸው ለፍርድ ይሆንባቸዋል።

ይቆየን፡፡

 ሱባኤ

ቀሲስ ኃይለሚካኤል ብርሃኑ

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የጽሞና ጊዜያት ከሚፈጸምባቸው መንገዶች አንዱ ሱባኤ  ነው፡፡ ሱባኤ  በሰዋስው ትርጉሙ ሰባት ማለት ነው፡፡ ይኸውም የሚፈጸመውን የጾም ወቅት በቀናት፣ በሳምንታት እና በወራት በመወሰን የአንድ ሱባኤ ልክ ሰባት ቀን ሆኖ የሚፈጸምበት ሥርዓት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ ትውፊት መሠረት ሰባት ቁጥር የፍጹምነት መገለጫ ነው፡፡ በተለይም የኦሪትን ሕግ በሙሴ አማካኝነት በተቀበሉት በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡

በሥነ ፍጥረት ታሪክ ሰባቱ ሰማያት እንዳሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡   እንዲሁም እግዚአብሔር ፍጥረትን በየወገኑ በስድስት ቀን ፈጥሮ በመፈጸም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ፤ ሰባተኛውንም ቀን ቀደሰው፡፡ ለዚህም ነው ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሲጽፍ፡-  “ሰማይና ምድር ዓለማቸውም ሁሉ ተፈጸሙ እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በስድስተኛው ቀን ፈጸመ፡፡ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ፡፡ እግዚአብሔር ሰባተኛዋን ቀን ባረካት ቀደሳትም ሊፈጥረው ከጀመረው ሥራ ሁሉ በእርስዋ ዐርፎአልና”  እንዲል (ዘፍ.፪፥፩)፡፡

እግዚአብሔር ሊፈጥረው ያሰበውን ሁሉ በስድስተኛው ቀን ፈጽሞ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ ማለቱ እግዚአብሔር ሲሠራ የሚደክመው ወይም ያሰበውን ለመሥራት ሲነሣ አቅም የሚያንሰው ሆኖ አይደለም፡፡ በሥራው ሁሉ ጉድለት እና እንከን የሌለበት ፍጹም ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ በዚህ ዓውደ ምንባብ እንደተመለከትነውም “እግዚአብሔር ሰባተኛዋን ቀን ባረካት ቀደሳትም”‘ ማለቱ እነዚህ ፍጥረታት ሁሉ ለክብሩ የተፈጠሩ መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡ ምክንያቱም ፍጥረትን ሲፈጥር ለምስጋና፣ ለተዘክሮ፣ ለምግብ ሥጋ፣ እና ስሙን ቀድሰው መንግሥቱን ይወርሱ ዘንድ፣ ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ በመልኩ ፈጥሮታልና ነው፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ “ስለ እውነት ፍርድህ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ” በማለት ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ሰባት ጊዜ እግዚአብሔርን ማመስገን እንዳለባቸው ይመክራል (መዝ.፻፲፰፥፻፷፬)፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ” ሲል ፍጹም ምስጋና አቀርብልሃለሁ፣ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፣ በንጹሕ ልብ አመሰግንሃለው ማለቱ ነው፡፡ የቅዱስ ዳዊትን ቅኔ (ምስጋና) አብነት አድርጋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የበረቱት በቀን ሰባት ጊዜ ለጸሎት እንዲቆሙ ታስተምራለች፡፡ በተግባርም በገዳም ባሉ አባቶች እና በከተማ የሚኖሩ ጠንካራ ክርስቲያኖችም በየቀኑ ሕይወታቸው ወይም ሱባኤ ይዘው ይኖሩበታል፡፡

ሱባኤን በመንፈሳዊ ትርጒሙ ስንመለከተው አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጾም፣  በጸሎት፣ በስግደት፣ በምሕላ ከፈጣሪዬ እገናኛለሁ ብሎ የሚያስበው መንፈሳዊ የልቡና መሻት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ሳያቋርጥ ቢጾም፣ ቢጸልይ፣ ቢሰግድ  አንድ ሱባዔ ፈጸመ ይባላል፡፡  ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም፣ ቢጸልይ፣ ቢሰግድ ሁለት ሱባኤ ፈጸመ እየተባለ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ሱባኤ ምእመናን ስለ በደላቸው እያሰቡ የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚለምኑበት ሥርዓት ሲሆን የምንሹትንም ነገር ለማግኘት እግዚአብሔርን መማጠኛ (መለመኛ) የልቅሶ፣የዋይታ እና የጥሞና ጊዜ አድርገው የሚሰነብቱበት የቀናት ወይም የሰዓታት ድምር ነው፡፡

የሱባኤን አጀማመር ስንመለከት ምክንያቱ ውድቀት ነው፡፡ይህም የተጀመረው በመጀመሪያው ሰው በአዳም እና በሔዋን ሲሆን ከውድቀት በኋላ  ነው፡፡ አዳም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ አፍርሶ የፈጣሪውን ቃል ጥሶ ከገነት ተባሯል(ተሰድዶአል)፡፡አዳምን ይኖርባት ዘንድ ከተሰጠቸው ከዔደን ገነት  ማን አባረረው ወይም ማን አሳደደው ብለን ስንመለከት ማንም ሳይነካው የሠራው ኃጢአት (ሕገ እግዚአብሔርን መተላለፉ) በክብር አላኖር ብሎት ራሱን ስደተኛ አደረገ፡፡ለዚህም ነው ሙሴ  አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን ከበላ በኋላ ስለ ገጠመው ነገር ሲጽፍ፡- ”እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ አዳም ወዴት አለህ? አለው አዳምም አለ በገነት ስትመላለስ ድምፅህን ሰማሁ ዕራቁቴንም ስለሆንሁ ፈራሁ ተሸሸግሁም‘(ዘፍ.፫፥፱)  በማለት ራቁትነቱ የኃጢአቱ ውጤት እንደሆነ የእግዚአብሔርንም ድምጽ ሰምቶ  በፊቱ ለመቆም የሚያስችል ድፍረት እንዳጣ ከነበረው ክብር እንዳነሰ እንደተጎሳቆለ ራሱ አዳም ተናገረ፡፡ በኃጢአት የወደቀው አዳም ከውድቀት እስኪነሣ ወደ ምድረ ፋይድ ተሰደደ፡፡ ከዚህ በኋላ አዳም በሱባኤ ፈጣሪውን ለመነ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ታህል ስፍራ አጥቶ መኖር እንደማይችል በንስሓ እንባ ፈጣሪውን ጠየቀ፡፡

በመጨረሻም ”በሐሙስ ዕለት ወመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅከ ውሰተ መርህብከ‘ አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁው ብሎ ተስፋውን ሰጥቶታል፡፡ ይህም አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ  ቃል ኪዳን እንደ ገባለት የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ያትታል፡፡ በመሆኑም  ሱባዔ መግባት የሚያስፈልግበትን ዋና ዋና ምክንያቶች በዝርዝር ስንመለከት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

ጸጋ እግዚአብሔርን ለማግኘት

ጸጋ የሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ስጦታ ማለት ነው፡፡  ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ሲገልጽ፡- ”ነገር ግን ስለምትበልጠው ጸጋ ቅኑ ደግሞም የምትሻለውን መንገድ አስተምራችኋለሁ‘(፩ኛቆሮ.፲፪፥፴፩) ይላል፡፡ ከሁሉ የምትበልጠው ጸጋ ከእግዚአብሔር የምትገኝ ስትሆን ብዙዎቻችን በኃጢአታችን ምክንያት እናጣታለን፡፡ ለዚህ ነው ቅዱሳን የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጎድልባቸው ሁሉን ጥለው፣ ሁሉን እያጡ ራሳቸውን በዓለም ድሃ አደረጉ፡፡ የጸጋ ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን ብለው በፍቅሩ ተቃጥለው ስለ መንግሥተ ሰማያት ሲሉ መራራውን ሞት በመታገሣቸው ከሁሉ የሚበልጠውን ሰማያዊውን ጸጋ ወረሱ፡፡ በዓለም እንደምናምንቴ ተቆጠሩ፣ አገር ላገር ስሙን ተሸክመው ተንከራተቱ፣ዳዋ ጥሰው ድንጋይ ተንተርሰው፣ጤዛ ልሰው፣  ግርማ ሌሊቱን፣ ድምጸ አራዊቱን ታግሠው ገድላቸውን በመፈጸማቸው ከሁሉ ይልቅ የሚበልጠውን ዘላለማዊውን ክብር ተጎናጸፉ ፡፡

 ስለዚህ ቅዱሳንን አብነት አድርገን ጸጋ እግዚአብሔርን ለማግኘት መትጋትና አብዝተን መሻት ይኖርብናል፡፡    የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው ሥጋው ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ እግዚአብሔር አዋቂ አድርጎ የሰጠው በጎ ኅሊናው የፈጸመው በደል ትክክል እንዳልሆነ ይወቅሰዋል፤ በዚህም የተነሣ በሠራው ኃጢአት ምክንያት ይደነግጣል፡፡  አምላኩን በማሳዘኑ እና ሕግ በመተላለፉ ከሚመጣበት ቅጣት ለመዳን ንስሓ ገብቶ ሰውነቱን በጾምና በጸሎት በመጥመድ ራሱን በጽድቅ ሥራ ያሳትፋል፤ ይህም የቀድሞ ኃጢአቱ ይቅር ተብሎለት ከሁሉ የምትበልጠውን  ጸጋ እንዲያገኝ  በፍጹም መመለስ  እግዚአብሔርን በሱባኤ  መጠየቅ ያስፈልገዋል፡፡ ድካመ ሥጋ  የሚፈታተነው የሰው ልጅ ያልተወሰነ ጸጋ እግዚአብሔርን  ለማግኘት ሱባዔ መግባት በኃጢአት ሸክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ሰላሙን ለመመለስ መጾምና መጸለይ ግድ ይሆንበታል፡፡

ስለምንሻው በጎ ነገር እግዚአብሔርን ለመማጸን

በየትኛውም መንገድ ቢሆን  ሱባዔ ከምንይዝባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ ይሆንልን ዘንድ ወይም ይፈጸምልን ዘንድ ስለምንሻው መልካም ነገር እግዚአብሔርን ለመማፀን ሲሆን ሱባዔ ለመያዛችን መሠረታዊ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባኤ ከመግባቱ በፊት ሱባኤ የምገባው ለምንድን ነው?  የማገኘውስ ጥቅም ምንድን ነው?  ለሚሉት ጥያቄዎች አስቀድሞ ከመምህራንና ከመጻሕፍት መረዳት አለበት፡፡በመቀጠልም ከራሱና ከንስሓ አባቱ ጋር በግልጽ በመምከር መልስ ማግኘት አለበት፡፡ ያለበለዚያ ምንም የሚጠይቀው ነገር ሳይኖር ሱባዔ ቢገባ የሚያገኘው መልስ ላይኖር ይችላል፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት ሱባኤ የሚገቡ ሰዎች ከሱባኤ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ነገር አይኖርም ሲባል ቢያንስ ኃጢአቱ ይቅር እንዲባልለት አስቦ መሆን አለበት ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ የትኛውም ሰው ሱባኤ ከመግባቱ አስቀድሞ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማፅኖ ሊኖረው ይገባል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ሱባኤ ከመግባታችን በፊት “እግዚአብሔርን መማፀን የምፈልገው ምንድን ነው?” በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ፣ስለ ቤተሰቡ፣ስለ አካባቢው፣ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤናና ላይ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡ በዚህ ጊዜ  ለገባው ሱባኤ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፤ ወይም  መልሱ ሊዘገይ ይችላል ፣ይህ ካልሆነ ደግሞ የማያስፈልግ ጥያቄ ከሆነ ጭራሹኑ መልስ ሳያገኝ ሊቀር ይችላል፣ ከዚህ ባለፈ ግን እምነቱን መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም ጉዳይ ላይ እግዚአብሔርን በጸሎት፣በጾም፣በስግደት(በሱባኤ) ስንለምን እምነት ሊኖረን ይገባልና ነው፡፡

ያም ሆነ ይህ  ከተሐራሚው  ስለ ሁሉም ነገር በማስተዋል፣በትዕግሥት (በመታገሥ) የእግዚአብሔርን ሥራ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ በሱባኤ እግዚአብሔርን ጠይቄው እኔ ባሰብኩት መንገድና ጊዜ ለምን አልሆነም? ለምንስ ላቀረብኩት ጥያቄ ቶሎ መልስ አልተሰጠኝም?» በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማጸነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለውና፡፡

ከቅዱሳን በረከት ለማግኘት

እግዚአብሔር የአባትነቱን በረከት ሲያድለን ቅዱሳን ደግሞ በጸጋ እግዚአብሔር ከብረዋል እና ከእግዚአብሔር  በተገባላቸው ቃል ኪዳን መሠረት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ያድሉናል፡፡ ይህም ቅዱሳን የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር በስማቸው በታነጹ ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ ከቅዱሳኑ በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን የተጋደሉበት ቦታ ቅዱስ ነውና፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ ቅዱሳን ስለተገባላቸው ቃል ኪዳን ሲናገር፡- ”እግዚአብሔር ለጃንደረቦች እንዲህ ይላል ሰንበቴን ቢጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ቢመርጡ በቃል ኪዳኔም ጸንተው ቢኖሩ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም የሚያስጠራ ቦታን  እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስምንም  እሰጣቸዋለሁ‘ በማለት እግዚአብሔር ለቅዱሳን ቃል ኪዳን እንደ ገባላቸው እና በስማቸው የሚጠራ  ቦታ እንደሚሰጣቸው ይናገራል (ኢሳ.፶፮፥፬)፡፡

ለዚህም ነው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በገዳማት እና በአድባራት ለተወሰነ ጊዜ ሱባኤ በመግባት ከእግዚአብሔርን ምሕረት ከቅዱሳን በረከታቸውን መሳተፍ እንደሚገባ የምታስተምረው፡፡ ይህም በጾመ ነቢያት የነቢያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል ከቅዱሳን በረከት ለመቀበልና የቅዱሳን አጽም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ለማግኘት ደጅ የሚጠኑ መናንያንና ምእመናን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡

 የቅዱሳንን ሕይወት  አብነት በማድረግ በትሕርምት የሚኖሩ መናንያን ያገለገሉበትን በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ በርካቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህን ትውፊት ለማጥፋትና ምእመናን ለመናንያን አባቶች ክብር እንዳይሰጡ ያልተገባ ተግባር የሚፈጽሙ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና  የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ መኖራቸውን በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ቀን ቀን  በልብስ ተመሳስለው መናኝ መስለው የሚታዩ መሸት ሲል እንኳንስ ከአንድ አባት ይቅርና ክርስቲያን ተብሎ ከሚጠራ አማኝ የማይጠበቅ ሥራ ሲሠሩ ሊታዩ ይችላሉና፡፡ በተለይ በከተሞች እንዲህ አይነት ማጭበርበሮች በስፋት ይስተዋላሉና   በጥንቃቄ መለየቱ አስፈላጊ ነው፡፡

የተሠወረው ተገልጦ፣ የረቀቀው ጎልቶ  እንዲታየን (ምሥጢር እንዲገለጥልን)

ቅዱሳን አባቶቻችን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢርና ትርምጒም እንዲገለጥላቸው ሱባኤ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ሆነው የገቡትን ሱባኤ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ  በብሉይ ኪዳን ከነበሩት አበው ነቢዩ ዕዝራን ብንመለከት የመጻሕፍትን ምሥጢር  እግዚአብሔር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል (፩ኛ ዕዝ..፲፫፥፵፫)፡፡

በዘመነ ሐዲስም እንዲሁ  ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርም ዕረፍትዋ ሲደንቃቸው ሥጋዋን መላእክት ወስደው በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ማኖራቸውን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ  ሲነግራቸው እነሱም ይህ ምሥጢር እንዲገለጽላቸው  ከነሐሴ ፩-፲፬  የገቡት ሱባኤ  ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ሱባኤ ቅዱሳን ሐዋርያት ተሠውሮባቸው የነበረውን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን የሥጋዋን መገለጥ ብቻ ሳይሆን እያዩ ዳሥሠው የቀበሩትን የሥጋዋን  ዕርገት እና  ትንሣኤዋንም  ተረድተው በረከቷን ለመሳተፍ አብቅቷቸዋል፡፡

በመሆኑም ሱባኤ ከአምላካችን ከልዑል  እግዚአብሔር ጸጋውን በረከቱን እንድናገኝ፣ ምሕረት ቸርነት እንዲሆንልን በፍጹም ልባችን የምንቀርብበት እና ከቅዱሳን ረድዔት በረከት የምናገኝበት ነው፡፡ እንዲሁም በሕይወታችን በጎ መሻታችን እንዲፈጸም ለተማጽኖ ወደ እግዚአብሔር በጾም፣በጸሎት፣በስግደት ተወስነን ለተወሰነ ጊዜ ጽሙና ላይ በመሆን  በተሰበረ ልብ በተዋረደ መንፈስ ሆነን የምንቀርብበት መንገድ ነው፡፡

በዚህ ክፍል የሱባኤን ምንነት እና ለምን ሱባኤ እንደምንገባ ለየሚያስረዳውን ክፍል የተመለከትን ሲሆን በቀጣዩ ክፍል የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የሥጋዋ ፍልሰት(ዕርገትዋን) በማስመልከት አዘጋጅተን ይምናቀርብ ይሆናል፡፡

መልካም ዕውቀት ሞገስን ይሰጣል

ለሰው ልጆች ከተሰጡ ጸጋዎች አንዱ ዕውቀት ነው፡፡ የሰው ልጅ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አዲስ ነገርን የመልመድ፣ አካባቢውን የማጥናትና መገንዘብን  እያዳበረ አካባቢውን ከመልመድ አልፎ በዕውቀት እየጎለመሰ፣ ጥሩውንና መጥፎውን እየለየ ያድጋል፡፡ መልካም የሆነውን መንገድ ለሚከተሉና እንደ እግዚአብሔር ቃል ለሚመላለሱት ዕውቀትና ጥበብን ያሳድርባቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “የምድር ገዢዎች ሆይ ጽድቅን ውደዷት፤ የእግዚአብሔርንም ኃይል በበጎ ዕውቅት አስቡት፣ በቅን ልቡናም ፈልጉት” ይለናል፡፡(ጥበ.፩፥፩)፡፡ መልካም ዕውቀትን በቅንነት መሻትና ፈልጎ ማግኘት ይገባል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ከይሁዳ ነገድ ስለሆነው ባስልኤል ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም፣ በማስተዋልም፣ በዕውቀትም የእግዚአብሔር መንፈስ ሞላበት” ሲል ይነግረናል፡፡(ዘጸ.፴፭፥፴፩)፡፡ አባቶቻችን በዚህ መንገድ አልፈዋልና ከእነርሱ መማር ያስፈልጋል፡፡

ልጆችን በዕውቀትና በጥበብ ተንከባክቦ ለማሳደግ ደግሞ የወላጆች ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ልጆች ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጾና ኮትኩቶ ማሳደግ ከተቻለ ፍሬው ያማረ ይሆናል፡፡ ዛፍ ተጣምሞ ቢያድግ በኋላ ማቃናት እንደማይቻል ሁሉ ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ ቃለ እግዚአብሔርን እየሰሙ ቢያድጉ ለራሳቸው ለቤተሰብ፣ እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ይህንንም በመረዳት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን በሮችዋን ከፍታ ልጆችዋን ለመቀበል ተዘጋጅታ የምትጠብቀው፡፡ በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠርም የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በግቢ ጉባኤያት ላይ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ወጣቱ ትውልድን በማነጽ ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ስንቶቻችን ተጠቅመንበታል?

ዓለም ለሥጋዊ ፍላጎታችን እንድንሮጥ ስታደርገን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ “ጥበብና ዕውቀት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነውና ኑ ልጆቼ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ” ትለናለች፡፡ ዕውቀትና ጥበብ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሰጣሉና ለዚህም በማስተዋል መጓዝ በተለይ ለወጣቶች እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ “ጥበብ ፈጽማ የጎላች ናት፤ ውበቷም አይጠወልግም፡፡ የሚወዷትም ፈጥነው ያዩአታል፤ የሚፈልጓትም ያገኟታል፡፡ ለሚወዷትም ትደርስላቸዋለች፤ አስቀድማም ትገለጥላቸዋለች፡፡” (ጥበ.፮፥፲፪-፲፫) እንዲል፡፡

 በግቢ ጉባኤ ውስጥ መሆን ሕይወታችንን ከክፉ ነገር እንድንታደግ፣ ውጤታማም ሆነን ለመውጣትና የወደፊት ሕይወታችን በእግዚአብሔር ቸርነት የተስተካከለ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ወደ እገዚአብሔር በቀረብን ቁጥር መልካም ሰዎች፣ ለቃሉም የምንታዘዝና እኔ ራሴ ብቻ ልኑር ሳይሆን ስለ ሌሎች መኖርን እንማራለን፡፡ ክርስቲያን እኔ ብቻ ይድላኝ አይልምና፡፡

ግቢ ጉባኤያት ውስጥ መሳተፍ እነዚህን በረከቶች ይዘን እንድንወጣ፣ በአገልግሎትም ጠንካሮች እንድንሆን መንገዱን ያመቻችልናል፡፡ እግዚአብሔርም መንገዱን እንድንከተል ዘወትር ይጠራናል፣ ዓይኖቹም ወደሚፈልጉት ነውና ሕይወታችን ከእግዚአብሔር እንዳይለይ ዕውቀትን፣ ጥበብንና ሞገስን አስተባብረን እንድንይዝ ያደርገናል፡፡ ሕይወታችንም በወንዝ ዳር እንደምትበቅል ዛፍ ለምልማ መልካም ፍሬ እንደምትሰጥ ሁሉ በሕይወታችን እንለመልማለን ለሌላውም አርአያ በመሆን ፍሬ እናፈራለን፡፡ ስለዚህ ለዓለሙ እና ለክፉ ተግባሩ ተባባሪዎች እንዳንሆን መንፈሳዊውን ዕውቀትና ጥበብን ገንዘብ እናደርግለን፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርሷንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ” እንዳለው እኛም እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ሊኖረን፣ በቅጥሩም ልንጠለል ያስፈልጋል፡፡(መዝ.፳፮፥፬)፡፡ ይህንን ብናደርግ እግዚአብሔር ሞገስን ይሰጠናል፡፡

የግቢ ጉባኤ ጥቅሞች በርካታ ናቸውና እግዚአብሔር በዚህ ዘመን የሰጠን በረከታችን ነውና እግዚአብሔርን ለመፈለግ በምናደርገው ጥረት ውስጥ መንገዱን በመምራት ሠላሳ፣ ስልሣ፣ መቶም በማፍራት ለሌሎች አርአያ እንሆናለን፤ እግዚአብሔርም አገልግሎታችንን  ይባርክልናል፡፡

እግዚአብሔር እንደቃሉ ተጉዘን በረከት እንድናገኝ ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

 

 

ቅዱስ ቂርቆስ ወቅድስት ኢየሉጣ

                                                             በቀሲስ ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ     

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ሐምሌ ፲፱ ቀን የሚከበረው ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ኢየሉጣን እና ልጁዋን ቅዱስ ቂርቆስን ከፈላ ውኃ የታደገበት(ያዳነበት) የሚታሰብበት በዓል ነው፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- ”ይትአየን መልአከ እግዚአብሔር አውዶሙ ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ ጣዕሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል፤ እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱ ዕወቁም‘(መዝ.፴፫፥፯) በማለት እንደመሰከረው፡፡

በዘመነ ሰማዕታት በሮማውያን ቄሳሮች አማካይነት በክርስቲያኖች ላይ የግፍ ዓዋጅ በመታወጁ ስለ ክርስትናቸው ደማቸው በየሜዳው እንደ ጎርፍ እየፈሰሰ፣ አጥንታቸው እየተከሰከሰ ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ እንደ በግ እየታረዱ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር በመሆን ጸኑ፡፡ ስለ ስሙ የተሰውት በየቀኑ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ ሲሆኑ የቀሩት ደግሞ ተሰደዱ፡፡ ከተሰደዱት ክርስቲያኖች መካከል ደግሞ ቅድስት ኢየሉጣ አንዱዋ ናት፡፡

ቅዱስ ቂርቆስ ዕድሜው የሦስት ዓመት ሳለ እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ከሮሜ ወደ ሌላ ሃገር(ኢቆንዮን) ሸሽታ ይዛው ሄደች፤ በዚያም የሸሸችውን መኮንን(እለእስክንድሮስ) አገኘችው። የሚያውቋትም ሰዎች ሸሽታ እንደመጣች ስለተረዱ ለመኮንኑ ነገር ሰሩባት። መኮንኑም ቅድስት አየሉጣን አስጠራትና ስለምታመልከው አምላክ ጠየቃት። ቅድስት ኢየሉጣም፡- ”መኮንን ሆይ፡ ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነው ሕፃን አለ፤ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ” አለችው።

ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም ወደ አለበት ጭፍራውን ልኮ ወደ እርሱ አስመጣው ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና “አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ?” አለው። ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም መለሰለት፣ እንዲህም አለው፡- “አዎ እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ ደስታዬም ተጠብቆልኛል ላንተ ግን ሐዘንና ለቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏልና” አለው።

እግዚአብሔር አምላክ ኃይልንና ንግግርን ሰጥቶታልና በዚያ ለተሰበሰቡት ሰዎች እስኪደነግጡ ድረስ ስለሚያመልክው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ  ብዙ ተናገረ። ቅዱስ ቂርቆስም ንጉሡን መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው ከብርታቱም የተነሣ አደነቁ፡፡

መኮንኑም በአፈረ ጊዜ እጅግ ዘግናኝና ከባድ በሆነ ስቃይ ታላላቆች እንኳ የማይችሉትን  አስጨናቂ በሆነ ልዩ ልዩ መከራ አሰቃየው። እናቱ ቅድስት ኢየሉጣንም ከእርሱ ጋር እንደ እርሱ በጣሙን አሰቃያት። እግዚአሔብሔር ግን ያለ ምንም ጉዳት ያነሳቸው ነበር። ብዙዎች አሕዛብም ይህን አይተው አደነቁ፡፡ ክብር ይግባውና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።። የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ።

በሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ አደረበት። ታላላቅ ድንቅ ተአምራቶችንም ያደርግ ነበር። ብዙዎች በሽተኞችንም ያድናቸው ይፈውሳቸው ነበር። ይህንን ያየው መኮንኑም በታላቅ የናስ ጋን ውስጥ ውኃ ጨምረው በእሳት ያፈሉት ዘንድ አዘዘ። የፍላቱም ድምጽ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ሆነ ድምጹም በጣም ያስተጋባ ነበር። ይህን ያየችና የሰማች እናቱ ቅድስት ኢየሉጣም ፍርሃትና የሃይማኖት ጉድለት ታየባት። ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን ሁኔታዋን አይቶ ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ጸለየ።

ያን ጊዜ ልዑል እግዚአብሔር ልቧን ወደ ሰማይ አሳርጎ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳያት። ቅድስት ኢየሉጣም እንደገና በሃይማኖቷ ጸናች። እግዚአብሔር አምላኳንም አመሰገነችው። ልጇን ሕፃኑን ቅዱስ ቂርቆስንም “ልጄ ሆይ አንተ ከእንግዲህ አባቴ ነህ እኔም ልጅህ ነኝ በሥጋ ብወልድህና እናትህ ብሆንም በሃይማኖት እንድጸና በምክርህ እና በጸሎትህ ስለ እኔም ባቀረብከው ልመና በሃይማኖት ወልደኸኛልና” አለችው።

መልሳም ቅድስት ኢየሉጣ ለልጇ “ያች የተወለድክባት ዕለት ቀኗ የተባረከችና የተቀደሰች ናት” አለችውና ተጋድሎአቸውን እንዲፈጽሙ ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረገች ነገረችው። እሱም ስለ እናቱ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ የመኳንንቱ ጭፍሮችም እሳት ወደ አለበት ጋኖች ውስጥ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን በጨመሯቸው ጊዜ የውኃው ፍላት እንደ ክረምት ነጎድጓድ ድምጹ ይሰማ የነበረና ወደ ላይ ፲፬ ክንድ ያህል ይፍለቀለቅ የነበረ ቢሆንም  የክርስቶስ ባለሟሎች የሆኑት ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ ሲጣሉበት ወዲያውኑ ቀዘቀዘ። ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የእሳቱን ኃይል አቀዝቅዞታልና።

ከራስ ጸጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው የለበሱት ሰናፊል ሳይቀር የውኃው ፍላት እና የናሱ ብረት ግለት ሳይነካቸው በሰላም በሚፍለቀለቀው የውኃ ፍላት ውስጥ በደስታ ሲመላለሱበት የሚሆነውን ለማየት የተሰበሰቡ ሁሉ በመገረም ያዩ ነበር፡፡ ብዙ አሕዛብም ባዩት ተአምር በቅዱስ  ቂርቆስና በቅድስት ኢየሉጣ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ  አመኑ፡፡ ከንጉሡ ጭፍሮችም ብዙዎች ያመኑ ቢሆኑም ያላመኑት ያመኑትን በቁጣ ተነሣስተው በሰይፍ ገደሉአቸው፡፡ ብዙዎችም ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡

ይህን ያየ መኮንኑም ይባስ እልህ ውስጥ ስለገባ ሥጋቸው ተቆራርጦ እስከሚወድቅ ድረስ በመቃጥን ውስጥ አድርገው አንዲጎትቷቸው አዘዘ። ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል አዳናቸው። ጨካኙ ንጉሥ በታላቅ ስቃይ ያሰቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ መኮንኑ በወህኒ ቤት ዘጋባቸው። በዚህን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስን አረጋጋው፤ አጽናናው ስሙንም ጠርተው መታሰቢያ ለሚያደርጉለትም በረከትን እንደሚያገኝና ሌላ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው። ለቅድስት ኢየሉጣም እንዲሁ ቃል ኪዳን ሰጥቶ አጽናናት፡፡ በወህኒም እንዲቆዩ ተደረገ፡፡

በሌላ ጊዜ መኮንኑ ከመካነ ምኩናኑ ተቀምጦ ቅዱስ ቂርቆስን ካለበት አስጠርቶ “የተመለስከው መመለስ አለን?” አለው:: ቅዱስ ቂርቆስም አይሆንም አልመለስም” አለው:: ጋሻ ጃግሬውን ጠርቶ ”ንሳ በሰይፍ ቅጣው” አለው:: በሰይፍ መታው፡፡ ጌታም ነፍሱን ከመካነ ዕረፍት ሥጋውንም ነጥቆ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮለታል:: እናቱ ቅድስት ኢየሉጣንም እንዲሁ በሰይፍ እንዲቆርጡዋት አዘዘ፡፡ እርሱዋም እንደ ልጅዋ በጽናት ስለ ክርስቶስ መስክራ ሁለቱም እናትና ልጅ በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ ዕረፍት መታሰቢያ በዓላቸውም ጥር ፲፭ ቀን ይከበራል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና የእናቱ የቅድስት ኢየሉጣ በረከታቸውና ረድኤታቸውን ያድለን አሜን።

ምንጭ፡- ስንክሳር ሐምሌ ፲፱፣ ገድለ ቅዱስ ቂርቆስ ወኢየሉጣ)

ቅድስት ሥላሴ

የሁሉ ፈጣሪ የዓለም ገዢ አምላካችን እግዚአብሔር ለስሙ ክብር ይግባውና በሐምሌ ፯ ቀን ወደ ጻድቁ አብርሃም ቤት በመግባት በአንድነትና በሦስትነት ክብሩ ተገለጠለት፡፡ በዚህች በከበረችም ቀን አብርሃም በደጃፉ ሆኖ ዓይኖቹን አንሥቶ ሲመለከት ሦስት አረጋውያንን አየ፤ ሮጦ ሄዶም ተቀበላቸው፡፡ ‹‹ውኃ እናምጣላችሁ፤ እግራችሁን እንጠባችሁ፡፡ ከዛፉም ሥር ዕረፉ፤ እንጀራም እናምጣላችሁና ብሉ፤ ከዚያም በባሪያችሁ ዘንድ ከአረፋችሁ በኋላ፥ ወደ አሰባችሁት ትሄዳላችሁ›› አላቸው፡፡

‹‹እንደምታየን ሽማግሌዎች ነን፤ የመጣነው ደግሞ ከሩቅ ነው፡፡ ስለዚህ አዝለህ ወደ ድንኳንህ አስገባን›› አሉት፡፡ አንደኛውን አዝሎ ወደ ድንኳን ሲያስገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ ገብተው ተገኙ፡፡ አብርሃምም ነገሩ እየረቀቀበት ሲሄድ በጓዳ ለነበረችው ለሚስቱ ሣራ ‹‹ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ ለውሺ፤ እንጎቻም አድርጊ›› አላት፡፡

ሚስቱ ሣራም እንዳዘዛት አድርጋ ጋግራ አቀረበች፤ እርሱም ቤት ለነበረ አንድ ብላቴና ወይፈኑን አርዶ አወራርዶ እንዲያመጣለት ካዘዘው በኋላ ከወተትና ማር ጋር አብሮ አቀረበላቸው፡፡ እነርሱም አብርሃምን ደስ ለማሰኘት በሉ፤ መብላታቸውም እሳት ቅቤ በላ እንደ ማለት ነው፤ በግብር አምላካዊ ነውና አይመረመረም፡፡ ከዚያም የታረደውና የተወራረደው ወይፈንም ተነሥቶ በድንኳኑ ደጃፍ ‹‹ስብሐት ለአብ፣ ስብሐት ለወልድ፣ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ›› ብሎ ሥላሴን አመሰገነ፡፡

አብርሃም ደነገጠ፡፡ ‹‹እንግዳ ከመጣልህ በትሑት ሰብእና በቅን ልቡና ሆነህ ተቀበል፤ እንግዳ ካልመጣ ጾምህን አትደር፤›› አሉት፤ ከዚያም ስለ ይስሐቅ  አበሠሩት፡፡ (ዘፍ. ፲፰፥፩-፰፣አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፲፰)

ጻድቁ አባታችን አብርሃም አምላኩን ለማወቅ ሽቶ በእምነትና በሃይማኖት ጽናት ሥላሴን በአንድነትና በሦስትነት ለማየት በቅቷል፡፡ በእርሱም የጽድቅ ሥራ ለብዙዎች ድኅነት ከመሆን አልፎ ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹የአብርሃሙ ሥላሴ›› በማለት አብርሃምን ታመሰግነዋለች፡፡ ቅድስት ሥላሴ የሁሉ ፈጣሪ በመሆናቸው ክርስቲያን የሆነ ሁሉም የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት ሊያውቅ ይገባል፡፡

በ ‹‹ምሥጢረ ሥላሴ›› ትምህርት እንደምንረዳው ቅድስት ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸው፡፡  ‹‹ሥላሴ›› የሚለው ቃል ‹‹ሠለሰ፤ ሦስት አደረገ›› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ሦስትነት ማለት ነው፡፡  (መጽሐፍ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፮፻፷፱)

ቅድስት ሥላሴ ስንልም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ማለታችን ነው፡፡  ‹‹ቅድስት›› ተብሎ ደግሞ በሴት አንቀጽ /ቅድስት ሥላሴ/  ይጠራል፤ ‹‹ቅድስት›› እና ‹‹ልዩ ሦስት›› የሚባልበትም ሃይማኖታዊ ምሥጢር፡-

.    ቅድስት

ሥላሴ ‹‹ቅድስት›› ተብለው በሴት አንቀጽ መጠራታቸው ሴት /እናት/ ልጅዋን መውለዷን እንደማትጠረጥረው ሁሉ ሥላሴም ይህን ዓለም መፍጠራቸውን ስለማይጠረጥሩ ነው፡፡ ሁሉም ከእነርሱ፣ ለእነርሱ፣ በእነርሱ ሆኗልና፡፡ ሴት ወይም እናት ልጅዋ ቢታመምባት እንዲሞትባት አትሻም፤ ሥላሴም ከፍጥረታቸው አንዱ እንኳን በጠላት ዲያብሎስ እንዲገዛባቸው አይፈቅዱም፡፡ ሴት ፈጭታ ጋግራ ቤተሰቦቿን እንደምትመግበው ሥላሴም በዝናም አብቅለው በፀሐይ አብስለው ፍጥረቱን ሁሉ ስለሚመግቡ ‹‹ቅድስት ሥላሴ›› እያልን እንጠራቸዋለን፡፡

ልዩ ሦስትነት

በትምህርተ ሃይማኖት ሥላሴ በቅድምና፣ በፈጣሪነት፣ በሥልጣን፣ በመመስገን፣ በክብር፣ በፈቃድ አንድ /እግዚአብሔር/ ሲሆኑ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት መሆናቸውን ይገልጻል፡፡

.    በስም

የቅድስት ሥላሴ የስም ሦስነትነት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ተብለው መጠራታቸው ነው፡፡  አብ በራሱ ስም አብ ይባላል እንጂ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ ወልድም ወልድ ይባላል እንጂ አብ ወይንም መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ቢባል እንጂ አብ ወይም ወልድ አይባልም፤ ስማቸው ፈጽሞ የማይፋለስ ነውና፡፡

ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ በሦስተኛነት በአንጾኪያ ተሹሞ የነበረው ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹አብሂ ውእቱ አብ ወኢኮነ ወልደ ወኢ መንፈሰ ቅዱሰ፣ ወልድሂ  ውእቱ ወልድ ወኢኮነ አበ ወኢ መንፈሰ ቅዱሰ፣ ወመንፈስ ቅዱስሂ መንፈስ ቅዱስ ውእቱ ኢኮነ አበ ወኢ ወልደ፣ ኢይፈልስ  አብ ለከዊነ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወኢ ወልድ ለከዊነ አብ ወወልድ፤ ወኢ መንፈስ ቅዱስ ለከዊነ አብ ወወልድ፤ አብም አብ ነው እንጂ ወልድን መንፈስ ቅዱስን አይደለም፤ ወልድም ወልድ ነው እንጂ አብን መንፈስ ቅዱስንም አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ አብን ወልድን አይደለም፤ አብ ወልድን መንፈስ ቅዱስን ወደመሆን አይለወጥም፤ ወልድም አብን መንፈስ ቅዱስን ወደመሆን አይለወጥም፤ መንፈስ ቅዱስም አብን ወልድን ወደመሆን አይለወጥም››  ብሏል፡፡ (ሃይ. አበው ዘቅዱስ አግናጥዮስ ምዕ. ፲፩. ገጽ. ፴፯)

የቅድስት ሥላሴ ስማቸው ከአካላቸው፣ አካላቸው ከስማቸው ሳይቀድም ቅድመ ዓለም የነበረ ስም ነው እንጂ ድኅረ ዘመን የተገኘ አይደለም፡፡ ቅድምናቸው ዘመኑን ቢወስነው እንጂ ዘመኑ ቅድምናቸውን አይወስነውምና፡፡ (መንገደ ሰማይ-በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ገጽ. ፴፪)

ስለዚህም ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት ‹‹ወናሁ ንቤ ካዕበ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወአኮ እሉ አስማት ዘቦኡ ላዕሌሆሙ ድኅረ አላ እሙንቱ እስመ አካላት፡፡ ወብሂለ ሰብእሂ አኮ ውእቱ ስም ዳዕሙ ፍጥረት ውእቱ… ወአካሎሙኒ ለሥሉስ ቅዱስ ወአስማቲሆሙ አልቦ ውስቴቶሙ ዘይዴኀር አላ እሉ እሙንቱ ብሉያነ መዋዕል እምቀዲሙ ዘእንበለ ጥንት ወዘመን፤ አሁን ደግሞ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንላለን ግን አካላት ተቀድመው ተገኝተው እሊህ ስሞች ኋላ የተጠሩባቸው አይደለም፤ ሰው ማለት ኋላ የወጣ ስም አይደለም፡፡ ባሕርዩ ነው እንጂ የሥላሴ አካላቸውም ቀድሞ ስማቸው ከአካላቸው በኋላ የተገኘ አይደለም፡፡ ጥንት ሳይኖራቸው ዘመን ሳይቀድማቸው የነበሩ ናቸው እንጂ›› ብሎ ተናግሯል፡፡ (ሃይ-አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት ፲፫፥፬-፰ ገጽ ፵)

.    በአካል

የቅድስት ሥላሴ የአካል ሦስትነታቸው ደግሞ አብ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ወልድም ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ሊቁ አቡሊዲስ ስለ ሥላሴ የአካል ሦስትነት ሲገልጽ ‹‹ነአምን በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ሠለስቱ ገጻት ፍጹማነ መልክእ ወአካል እሙንቱ እንዘ አሐዱ መለኮቶሙ ዘበአማን፤ ባሕርያቸው በእውነት አንድ ሲሆን በመልክ፣ በአካል ፍጹማን እንደሆኑ ሦስት ገጻት እንደሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን›› ብሏል፡፡ (ሃይ. አበ. ዘአቡሊዲስ ምዕ. ፴፱፥፫ ገጽ ፻፴፯)

.    በግብር

የቅድስት ሥላሴ የግብር ሦስትነታቸው ሲተረጎም የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረፅ ነው፤ ወልድን ወልዷል፣ መንፈስ ቅዱስንም አሥርፇልና፡፡ የወልድ ግብሩ መወለድ ነው፤ ከአብ ተወልዷልና፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረፅ ነው፤ ከአብ ሠርፇልና፡፡

አብ ወልድን ቢወልድ፣ መንፈስ ቅዱስንም ቢያሠርፅ እንጂ አይወለድም፣ አይሠርፅም፡፡ ወልድ ቢወለድ እንጂ አይወልድም፤ አይሠርፅም፤ አያሠርፅም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ቢሠርፅ እንጂ አይወለድም፤ አያሠርፅም፤ በመሆኑም ቅድስት ሥላሴ በዚህ ግብራቸው አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ ተብለው ይጠራሉ፡፡

በእርግጥ ምሥጢረ ሥላሴን በሚገባ መርምሮ መረዳት ለማንም ቢሆን አይቻለውም፡፡ እርሱ ባወቀ ግን ምሥጢረ ሥላሴ በምሥጢረ ጥምቀት ተገልጧል፡፡  እንግዲህ እምነታችንን በቅድስት ሥላሴ ላይ በማድረግ በቀናች ሃይማኖት ልንጸና ይገባል፡፡

ምንጭ፡ኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ፣ መጽሐፍ ስዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት በአለቃ ኪዳነ ወልድ፣ ሃይማኖተ አበው (ዘቅዱስ አግናጥዮስ፣ ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ

መንክራት፣ዘአቡሊደስ) እና መንገደ ሰማይበብፁዕ አቡነ መቃርዮስ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

“የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል”(መዝ.፻፳፮፥፮)

ሐምሌ አምስት ቀን በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ የክቡራን የዐበይት አባቶቻችን የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስ የሰማዕትነታቸው መታሰቢያ ዕለት ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ አሣ አጥማጅ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን አኢየሱስ ክርስቶስ ከመረጣቸው ፲፪ቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱስ ጴጥሮስ በፊት ወንድሙ እንዲርያስን የጠራው ሲሆን ለሐዋርያነት ከተመረጠበት ጊዜ አንስቶ ከጌታችን እግር ሥር እየተከተለ በዋለበት እየዋለ፣ ባደረበት እያደረ የቃሉን ትምህርት፣ የእጁን ተአምራት እየሰማና እያየ የኖረ፤ አስከ ሕይወቱ ፍፃሜም የተጠራበትን የሐዋርያነት አገልግሎት በተጋድሎ የፈጸመ፣ ጌታችንም በሐዋርያት ሁሉ ላይ አለቃ አድርጎ የሾመው፣ በኋላም በመስቀል ላይ ቁልቁል ተሰቅሎ በሰማዕትነት ያረፈበት ዕለት ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ “የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?” ብሎ በጠየቀ ጊዜ ቅዱስ ጳጥሮስ ከሐዋርያት መካከል “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ሲል መስክሯል፡፡ በዚህም ምክንያት “አንተ ዐለት ነህ በዚህችም ዐለት ላይም በቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፤ የሲዖል በሮችም አይበረቱባትም፤ የመንግሥተ ሰማያትንምመክፈቻዎች እሰጥሃለሁ” ብሎ ጌታችን የመሠከረለትና የሐዋርያት ሁሉ አለቃ አድርጎ የሾመው ሐዋርያ ነው፡፡(ማቴ.፲፮፥፲፫-፲፱)፡፡

፲፪ቱ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ዕለትም ሦስት ሺህ ሰዎችን በስብከቱ ያሳመነ ታላቅ ሐዋርያ ነው፡፡ በጥላውና በለበሰው ልብሱ ታላላቅ ተአምራትንም በማድረግ፣ ወንጌልንም በልዩ ልዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ያለ ፍርሃት አስተምሯል፡፡ ነገር ግን በቅዱስ ጴጥሮስ የወንጌል ትምህርት ብዙዎችን ወደ ክርስትና እየመለሰ፣ ጣዖታትን እያጠፋ ስላስቸገራቸው የሮሜ መኳንንት ሊገድሉት ተስማሙ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም እንዲገድሉት መስማማታቸውን በሰማ ጊዜም ልብሱን ቀይሮ ከሮሜ ከተማ ሲወጣ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተሸክሞ ወደ ከተማ ሲገባ አገኘው፡፡ “አቤቱ ጌታዬ ወዴት ትሄዳለህ?” አለው፡፡ ጌታችንም “ልሰቀል ወደ ሮሜ ከተማ እሄዳለሁ” ብሎ መለሰለት፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “አቤቱ ዳግመኛ ትሰቀላለህን?”አለው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ “ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ እጅህ ታጥቀህ ወደ ወደድከው ትሄዳለህ፤ በሸመገልክ ጊዜ ግን እጅህን ታነሣና ሌላ ያስታጥቅሃል” ያለውን የጌታችንን ቃል አሰበ፤ አስተዋለውም፡፡ ተጸጽቶም ወደ ሮሜ ተመለሰ፡፡ ንጉሡ ኔሮንም እንዲሰቅሉት አዘዘ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን “እንደ ጌታዬ ልሰቀል አይገባኝምና ቁልቁል ስቀሉኝ” በማለቱ ቁልቁሊት ተሠቅሎ ሰማዕትነት ተቀብሏል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሐምሌ ፭ ቀኑን ታስበዋለች፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ሁለት መልእክታትንም ጽፏል፡፡

በዚህም ቀን የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መታሰቢያው ነው፡፡ ሳውል ቀድሞ ሕገ ኦሪትን ጠንቅቆ የሚያውቅና ክርስቲያኖችን የሚያሳድድ ሰው ነበር፡፡ ክርስቲያኖችንም ለማሰቃየትና ለመግደል ደብዳቤ ለምኖ ወደ ደማስቆ አቅራቢያ ሄደ፡፡ ደማስቅ በደረሰ ጊዜም ከሰማይ መብረቅ ብልጭ ብሎበት በምድር ላይ ወደቀ፡፡ ወዲያውም “ሳውል፣ ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምጽ ሰማ፡፡(ሐዋ.፱፥፬)፡፡

ሳውልም “አቤቱ አንተ ማነህ?” አለ፡፡ ጌታችንም “አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ በሾለ ብረት ላይ ብትረግጥ ለአንተ ይብስብሃል” ሲል ተናገረው፡፡ “አቤቱ ምን እንዳደርግ ትሻለህ?” ሲል ጠየቀ፡(ሐዋ.ሐዋ.፱፥፭-፮)፡፡ ጌታችንም ከደቀ መዛሙርት አንዱ ወደሆነው ሐናንያ እንዲሄድ ነገረው፡፡ ዐይኖቹም ታውረው ነበር፡፡ ሳይበላና ሳይጠጣም በደማስቆ ለሦስት ቀናት ቆየ፡፡ ሐናንያም ባገኘው ጊዜ “ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ታይ ዘንድ፣ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ይሞላብህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮኛል” አለው፡፡ ከሳውል ዐይኖች ላይም ቅርፊት መሰል ነገር እየተቀረፈ ወደቀ፡፡ ለማየትም ቻለ፤ ወዲያውም ተጠመቀ፤ ምግብም በልቶ በረታ፡፡ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅነትንም መሰከረ፡፡ ስሙም ጳውሎስ ተባለ፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የተጠራበትን ተልእኮ ለመፈጸም እየተዘዋወረ የክርስቶስን ወንጌል እየሰበከ ታላላቅ ተአምራትንም ማድረጉን ቀጠለ፤ ወደ ሮሜ ከተማም ገብቶ በስብከቱ ብዙዎች ሰዎች አምነው አጠመቃቸው፡፡ ነገር ግን ንጉሡ ኔሮን ቅዱስ ጳውሎስን ይዞ ከፍተኛ ሥቃይ አደረሰበት፡፡ በመጨረሻም አንገቱ ተሰይፎ እንዲሞት ተፈርዶበት ሐምሌ ፭ ቀን ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ አሥራ አራት መልእክታትን ጽፏል፡፡

ምንጭ፡- ስንክሳር

ገድለ ሐዋርያት

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረት

ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረት ስናነሣ ዘመኑ የኮምዩኒዝም ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ የሰፈነበት፤ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት አስቸጋሪ የሆነበትና ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሔድ እንደ ኋላ ቀርነት የሚቆጠርበት ዘመን ነበር ፲፱፻፸፯ ዓ.ም፡፡ በተለይም በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በሚገኙ ተማሪዎች ዘንድ ቃለ እግዚአብሔርን በግልጽ መነጋገርም ሆነ መስማት የማይታሰብበት ወቅት ነበር፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይም በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች እንዲያስተምሩ ከምዕራባውያኑ ሀገሮች መጥተው የነበሩ ሚሲዮናውያን የኑፋቄ ትምህርታቸውን ያሠራጩ የነበረውም በእነዚሁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ያ ዘመን ትውልዱ በየአቅጣጫው በሚሲዮናውያኑ የኑፋቄ ትምህርት እንዲሁም በኮምዩኒዝም ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ እየተነጠቀ ከኦርቶዶከሳዊት ተዋሕዶ እምነት የኮበለለበት ዘመን ነበር፡፡ (ለዝርዝሩ ሊንኩን ይጫኑ)፡፡ brocher pdf final 

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቁጥር ፻፷፬ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማህበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
፩. የ፳፻፲፫ ዓ.ም. ግንቦት ርክበ ካህናት የጉባኤ መክፈቻ በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ማለትም፡-
ስለ አገር ደኅንነትና ስለ ሕዝቦች አንድነት፣
ከቄያቸው ስለተፈናቀሉና ለስደት ስለተዳረጉ ወገኖች፣
በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ስለአሉ አለመግባባቶች የሚያመላክት እና ይህንንም በመግባባት በውይይት በይቅርታ መፍታት እንደሚገባ ከሁሉም በላይ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ምሕረት መጠየቅ እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ በመሆኑ ጉባኤው ተቀብሎ በተግባር ላይ እንዲውል ተስማምቷል፡፡
፪. አገራዊ ሰላምን አስመልክቶ ጉባኤው በስፋት ከተነጋገረ በኋላ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የጠፋው የሰው ሕይወት የታረዱና ከቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በችግሩ ምክንያት የወደመ ንብረት በዓይነትና በቁጥር ተለይቶ በየአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
፫. የቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥፍራ ስምና እስከዛሬ ተጠብቆ የቆየ ክብሯ እንዲሁም በካህናትና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለ ሞት፣ ስደት የመሳሰለው ከየአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ ሪፖሪት እንዲቀርብ መንግሥትም አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
፬. ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን የነበረውንና የቆየውን ታሪካዊ ሂደት ለመቀየር በዚህም አጋጣሚ የኖረውንና ዓለም የሚያውቀውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ የተመዘገበ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል አደባባይና የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች እንዲሁም የአምልኮ ሥፍራዎችን ምክንያት በመፍጠር አንዳንድ ወገኖች የግጭትና የትንኮሳ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑ ጉባኤውን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡
በመሆኑም ይህ በቤተ ክርስቲያናችን ስም የቆየው የዘመናት ታሪክ አገራዊ ታሪክ ተደርጐ ልዩ ጥበቃና ክብካቤ ሊደረግለት ስለሚገባ አሁንም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የኖረው የቤተ ክርስቲያኒቱና የአገሪቱ ታሪክ ክብሩ ከነማንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር የበኩሉን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት አሳስቧል፡፡
፭. አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ እንደሚታወቀው ዳር ድንበሯን ጠብቃና አስጠብቃ ያለ ቅኝ ግዛት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በአገር ወዳድ መሪዎቿ አንድነቷን ጠብቃ የቆየች መሆኗ አለም የሚያውቀው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የውጭ አገራት ከሩቅና ከቅርብ ግንባር በመፍጠር በአገራችን ሕልውና ላይ እያደረጉት ያለው ጣልቃ ገብነት፣
– አገራዊ የመልማት ፍላጐታችንን ለመግታት
– ዳር ድንበራችንን ለመድፈር እያደረጉ ያለውን ሙከራ ጐረቤት አገራት ጭምር በጠላትነት እንዲነሳሱብን እያደረጉ ያለው ቅስቀሳ ተዘዋዋሪ ቅኝ ግዛት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ተቃውሞአል፡፡ ሕዝባችንም ከምንጊዜውም በተለየ መልኩ አገራዊ አንድነቱን በመጠበቅ አገሪቱን ከውጭ ወራሪ በመከላከል አገራዊ ልማትን በማፋጠን የበኩሉን እንዲወጣ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
፮. አገራችን ኢትዮጵያ በልማት እንድታድግ ሌሎች አገራት ከደረሱበት ደረጃ ለማድረስ በዚህም ዜጐችን ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማውጣት ታስቦ እየተገነባ ያለው ህዳሴ ግድባችን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተቃረበ እና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የአንድነታችን ማሳያ እየሆነ በመምጣቱ አሁንም ለግንባታው ፍጻሜ መላው ኢትዮጵያ እንዲረባረብ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
፯. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ታሪኳ የአብያተ ክርስቲያናትን አፀድ በመትከል አረንጓዴ ልምላሜን በማስፋፋት ጠብቃ የቆየች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ መንግሥታችን በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠር ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ማዘጋጀቱ ለአየር ጥበቃና በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው አገራዊ ጥረት የሚደገፍ በመሆኑ በዘንድሮውም የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር መላው ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
፰. ከአንድ ዓመት በፊት በመላው ዓለም ተከስቶ ብዙዎችን ለሕልፈተ ሕይወት የዳረገው ኮቪድ 19 ተላላፊ በሽታ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በመስፋፋቱ ብዙዎች ወገኖቻችን ለሞት እየዳረገ የሚገኝ በመሆኑ መላው ሕዝባችን ከምንግዜውም በበለጠ በአሁኑ ጊዜ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክረ ሐሳብ በመቀበል ራሱን ከወረርሽኑ እንዲጠብቅ ጉባኤው አሳስቧል፣
፱. በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ያለመጠለያ የሚገኙ እና በዚሁ ተላላፊ በሽታ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ወገኖቻችንን በተለመደውና በኖረው የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባሕላችን ከምንግዜው በላይ አሁን ለችግራቸው እንድንደርስላቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
፲. አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በሽግግር ላይ የምትገኝ በቀጣይም ሕዝባዊ ምርጫ ለማካሄድ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎች ለአገራችንና ለሕዝባችን የሚጠቅመውን ሰላማዊ መንገድ እንዲከተሉ መላው ሕዝባችንም ለአገርና ለወገን ይጠቅማሉ የሚባሉትን በመምረጥ ሁሉም አካል ውጤቱን በፀጋ በመቀበል ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የምናስመሰክርበት ምርጫ እንዲሆን ጉባኤው የሰላም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
፲፩. በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በጐንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ በምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነምሕረት በሕገ-ወጥ መንገድ ዶግማና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በጣሰ መልኩ ራሳቸውን በራሳቸው ጳጳስና ፓትርያርክ አድርገው የሾሙ፡-
፩. መምህር ሄኖክ ፈንታ
፪. መምህር አባ ኪዳነማርያም
፫. መሪጌታ ሙሉ
ከግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወግዘዋል፡፡ የገዳሙንም ሀብትና ንብረት አስረክበው ከገዳሙ እንዲወጡ ተወስኗል፡፡ የዚህ ተባባሪ የነበሩ መነኮሳት ካህናትና ዲያቆናትም የተወገዙ ሲሆን በዚህ የዶግማና የቀኖና ጥሰት ምክንያት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተሳስተው ድጋፍ ሲሰጡና ሲከተሏቸው የነበሩ ምእመናን ንስሐ እየገቡ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ጉባኤው ወስኗል፡፡
፲፪. በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው፡-
– የርስ በርስ አለመግባባት እንዲቆም፣
– ሞትና ስደት እንዲያበቃ ፣
– ተላላፊ በሽታ ከምድራችን ጠፍቶ ሰዎች በጤንነት እንዲኖሩ፣
– መጪው አገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ጨዋነት በአንድነትና በሰላም እንዲጠናቀቅ፣
ለዚሁ ሁሉን ቻይና ሁሉን አድራጊ የሰላም አምላክ እግዚአብሔር አገራችንና ሕዝባችንን በሰላምና በምሕረቱ እንዲጐበኝ ሁላችንንም ይቅር እንዲለን ከአሁን ጀምሮ በግልም ሆነ በማኅበር ጸሎት በማድረግና ችግረኞችን በመርዳት እንድንተባበር ሆኖ ከምርጫው ሰኔ ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምሌ ፬ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ድረስ በመላው አገራችንና በውጭም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት ፲፯ እስከ ግንቦት ፳፫ ለስድስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ አጠናቆ በጸሎት ዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይጠብቅ፡፡
ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም.
አዲስ አበባ

የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ

መ/ር ሕሊና በለጠ
ክፍል ሁለት
የሞቱና የትንሣኤው ፍሬ ነገሮች
ጌታችን በመስቀል ላይ ሲሞት ድኅነታችን ተከናወነ፣ ሞትን ድል አድርጎ ሲነሣ ደግሞ ትንሣኤያችን እውን ሆኖ ተገለጠ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የማይቋረጥ አገልግሎት መሠረት የሆነ ድል፣ የምድርም የደስታዋ ምንጭ ሆነ፡፡ “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ፤ በክርስቶስ ደም ታጥባ ምድርም ደስታን ታደርጋለች” በማለት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እንደገለጸልን እኛም ደስታችንን ለመግለጽ እናመሰግናለን፡፡
ከነገረ ድኅነት አንጻር የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ያመጣውን ውጤት በሦስት ከፍለን እንመልከት፡
ሀ. በሲኦልና በሞት ላይ የተገኘ ድል
የሰው ልጅ ገነትን ካጣ በኋላ ኑሮው በሁለት የተከፈለ ነበር፡፡ የምድር ሕይወቱ እና ከሞት በኋላ የሚኖረው ሕይወቱ፡፡
የምድር ሕይወቱ ነፍሱ ከሥጋው ስትለይና የሥጋ ሞትን ሲሞት ያበቃል፡፡ ከዚያም ገነት የተዘጋች ናትና ነፍሱ ወደ ሲኦል ትሔዳለች፡፡ ሲኦል ደግሞ በጽልመትና በስቃይ የተሞላ፣ እንዲሁም የጨለማው ገዢ ዲያቢሎስ የሠለጠነበት ሥፍራ ነው፡፡ መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት “በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው?” (መዝ.፮፥፭) ሁሉም የጌታችንን መምጣት፣ መሞትና መነሣትን በታላቅ ተስፋ የሚጠብቅ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን ሲገልጽ “እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ በይኗልና” ብሏል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፴፱-፵)፡፡
ጌታችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለእኛ ሲል ከሞተ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ሲወርድ፣ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወርዶ ነበር፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ይህንን ምሥጢር እንዲህ ይዘክረዋል፡- “ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ፡ ያን ጊዜ በሲኦል ፈጥኖ ብርሃን ታየ፡፡ ጌታችን በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ፡፡ ሲኦል ተነዋወጠች፤ መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ፤ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ አጸናት፤ ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፡፡ ከኅልፈት ጠበቃት፤ በርሷ ያለውንም ሁሉ ጠበቀ፡፡ ስለ ፍጥረት ሁሉ ሥጋውን በመስቀል እንደተሰቀለ ተወው፡፡ ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወረደች፤ ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች፤ ሲኦልንም በዘበዘች፤ ፍጥረትንም ሁሉ ገንዘብ አደረገች፡፡ ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፡፡” እያለ በዕለተ ዐርብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ልጆቹን ለማዳን በመስቀል ላይ የከፈለውን ዋጋ ያሳየናል፡፡
ለዘመናት በሞት ጥላ ውስጥ ሆነው በተስፋ ሲጠብቁት ለነበሩት ነፍሳት ሁሉ በሲኦል ውስጥ ድኅነትንና ሰላምን ሰበከላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ሲነግረን “ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ፣ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው” (፩ጴጥ.፫፥፲፰-፲፱) አለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገር “ምርኮን ማርከህ ወደ ሰማይ ወጣህ፤ ጸጋህንም ለሰው ልጅ ሰጠህ” ይላልና ከምድር በታች (ሲኦል) ካልወረደ መውጣቱ ምንድን ነው? የወረደው እርሱ ነው፤ ሁሉንም ይመላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ እርሱ ነው” ሲል ገልጾታል፡፡ (ኤፌ.፬፥፰-፲)፡፡
ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ የዘመነ ብሉይ ሰዎችን ጩኸት እግዚአብሔርም እንደሰማቸውና፣ መለኮት ከሥጋ ጋር በመቃብር ከነፍስም ጋር በሲኦል በተዋሕዶ እንደ ነበር ሲያስረዳ “ነቢይ ዳዊትም ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ የባሕርይ ልጅህንም ሙስና መቃብርን ያይ ዘንድ አሳልፈህ አትሰጠውም አለ፡፡ ይህም ጌታ በተዋሐደው አካል ያለውን የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ያስረዳል፤ የቀና ልቡና ዕውቀት በእርሱ ጸንቶ ይኖር ዘንድ፡፡ ዳዊት እንደተናገረው እውነት ሆነ፤ ነፍስ መለኮትን ተዋሕዳ ወደ ሲዖል ወርዳለችና፤ ሥጋም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ሳለ መለኮት ከሥጋ አልተለየም” ብሏል፡፡
ይህ ሁሉ የሚያስረዳው በማኅፀነ ማርያም መለኮት ከትስብእት፣ ትስብእት ከመለኮት ጋር ከተዋሐደ በኋላ ምንም ዓይነት መለያየት ሳይኖር መለኮት በሥጋ እየተሰደደ፣ እየደከመ፣ እየተራበ፣ እየተጠማ፣ እየታመመ፣ እንዲሁም በመስቀል ተሰቅሎ በሞቱ ዓለምን ያዳነ መሆኑን ነው፡፡ ከላይ የሆኑት ሁሉ መለኮት በሥጋ ብለን የምንገልጸው ሲሆን እንዲሁ ሥጋም በመለኮት ሕሙማንን እየፈወሰ፣ ዕውራንን እያበራ፣ የተራበ እያበላ፣ ሙት እያነሣ፣ የተፈጸመ የነገረ ድኅነት ጉዳይ እንደሆነ ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በትንሣኤ በዓል ድርሳኑ “ሲኦል ወደዚያ በወረደው በክርስቶስ ምርኮ ሥር ሆነ፤ ተበረበረ” ሲል ገልጾታል፡፡
ሲኦልን መበዝበዙን ቅዱስ ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት “ታመመ፤ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፤ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደ መሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዓት ፈጸመ፡፡ ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ሁሉን ያጠግባል፤ አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤ አያንቀላፋም፤ አይታመምም፤ አይሞትም፤ ሕይወትን ለሁሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዚያ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ፤ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ” ብሎ አስተምሯል፡፡
አስቀድመን በሰፊው እንዳየነው ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ሞት አስፈሪነቱ ጠፋ፡፡ ሞት ከምድራዊው ሕይወት የሚያርፉበት ዕረፍት፣ ወደ ሰማያዊው ሕይወት መሸጋገሪያ ሆነ፡፡ በክርስቶስ ትንሣኤ ባገኘነው ክብር በትንሣኤ ዘጉባኤ እስክንነሣ ድረስ ብቻ ነፍስ ከሥጋ የሚለያዩበት ሆነ፡፡ “አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች አስቀድሞ ተነስቷል።” እንዲል ሐዋርያው (፩ቆሮ.፲፭፥፳)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይበልጥ ሲያብራራውም “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው ብሏል፡፡ (፩ቆሮ.፲፭፥፳፪-፳፫)፡፡ በመቀጠልም የሞትን በክርስቶስ ሞት ፍጹም መሻርና መደምሰስ ሲገልጽልን “የኋለኛው ጠላት ይሻራል፣ ይኸውም ሞት ነው” ሲል አስተምሯል፡፡ (፩ቆሮ. ፲፭፥፳፮)፡፡ በዚህም ሃይማኖቱን አጽንቶ፣ ምግባሩን አቅንቶ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምኖ የሚኖር ሰው ሁሉ ይህን ሞት የሚናፍቀው እንጂ የሚፈራውና የሚጠላው አይደለም፡፡
ለ. የቅዱሳን በገነት መክበር፣ የድል አድራጊዋ ቤተ ክርስቲያን ወይም የክርስቶስ መንግሥት መገለጥ
ጌታችን ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት “በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ ቦታ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ እላችሁ ነበር፤ ከሄድሁና ቦታ ከአዘጋጀሁላችሁም ዳግመኛ እመጣለሁ፤ እናንተም እኔ ባለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔ እወስዳችኋለሁ” (ዮሐ.፲፬፥፪-፫) ብሏቸው ነበር፡፡ በጸለየ ጊዜም “አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ” ማለቱም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ (ዮሐ.፲፯፥፳፬)፡፡ በእርግጥ ሐዋርያቱም “ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና” (ፊል.፩፥፳፫) ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ እንደመሰከረው ከምድር ሕይወት ተለይተው ከእርሱ ጋር ለመሆን ይናፍቁ ነበር:: “በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ” እንዳላቸው ያውቃሉና፡፡ (፪ቆሮ. ፭፥፩)፡፡ እንዳለው ውጣ ውረድ፣ ድካም፣ ረኀብ፣ ጥም፣ ኃጢአት፣ ወዘተ ከአለበት ዓለም ይህ ሁሉ ችግር በሌለባት ዓለመ ነፍስ በሆነችው በገነት መኖር የተቻለው በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው፡፡
በገነት ያለውን የቅዱሳን ሕይወት እንዴት እንደ ሆነ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ገልጾታል፡፡ “በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር” (ራእ.፬፥፬)፡፡ “… ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች” አየ፡፡ (ራእ.፮፥፱)፡፡ ከዚህ በኋላ በራእዩ ምን እንዳየ ሲነግረንም “…አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ” ሲል ጽፎልናል፡፡ ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በፊት ይህ ሁሉ አልነበረም፡፡ በእንዲህ ያለ ሕይወት መኖር የተቻለው ደግሞ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሞት ሥልጣን ከተሻረ በኋላ ነውና ይህን ክብር ለማግኘት ሁሉም ቅዱሳን ከዚህ ዓለም መሄድን ይመርጣሉ፡፡
በሰማይ ለቅዱሳን የተዘጋጁት ብርሃናማ መኖሪያዎች በቅዱሳት መጻሕፍት “የእግዚአብሔር ከተማ” (ዕብ.፲፪፥፳፪)፤ “የንጉሥ ከተማ”፤ “የጽዮን ተራራ” (መዝ.፵፯፥፪)፤ ፵፯፥፲፩)፤ “ሰማያዊት ኢየሩሳሌም”፣ (ቅድስት ማርያም)፣ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” (ገላ.፬፥፳፮)፤ “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” (ራእ.፳፩፥፪) ተብለዋል፡፡ ስለዚህ ከትንሣኤው በኋላ በሰማይ ያለች የክርስቶስ መንግሥት ለቅዱሳን ተገለጠች፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩት ሁሉ ወደ ውስጧ ገቡ፡፡
እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ፣ የቅዱሳን ሰዎች በገነት መክበር ስንል ፩ኛ. ከድካማቸው ማረፋቸውን፣ ፪ኛ. ከኀዘንና ከስቃይ እንግልት መለየታቸውን (ራእ.፲፬፥፲፫፤ ፥፲፮)፣ ፫ኛ. ከአበውና ከሌሎች ቅዱሳን ጋር ፍጹም የሆነ አንድነትን ማግኘታቸውን፣ ፬ኛ. እርስ በራሳቸውም ሆነ ከአዕላፍ መላእክት ጋር አንድ መሆናቸውን፣ ፭ኛ. ከበጉ ዙፋን ፊት ቆመው ማመስገናቸውንና እርሱን ማገልገላቸውን ነው፡፡
ሐ. ርደተ መንፈስ ቅዱስ
ጌታችን ከሕማማቱና ከስቅለቱ በፊት ለሐዋርያት ከእነርሱ ጋር እስከ ዘለዓለም ድረስ አብሮ የሚቆየውንና የሚያስተምራቸውን እንዲሁም እርሱ ያስተማራቸውን በማጽናት የሚመራቸውን ሌላኛውን አጽናኝ ከአብ የሚወጣ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር፡፡ (ዮሐ.፲፭፥፳፮)፡፡ ከትንሣኤው በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦላቸው የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሲያድላቸው ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። “ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው”፡፡ (ዮሐ.፳፥፳፪-፳፫)፡፡ ከዕርገቱ በዐሥረኛው ቀንም በበዓለ አምሳ መንፈስ ቅዱስን “እንደ እሳት በተከፋፈሉ ልሳኖች” ላከላቸው፡፡ (ሐዋ. ፪፥፫)፡፡
የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በመጀመሪያ ለሐዋርያት በተሰጡት የመፈወስ፣ በልሣን የመናገርና በመሳሰሉት አስደናቂ ስጦታዎች የተገለጸ ሲሆን፣ በመቀጠልም በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ ወደ ፍጹምነትና ወደ ድኅነት በመውሰዱ የታወቀ፣ የተረዳ ሆኗል፡፡
“የመለኮቱ ኃይል፥ … ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ሰጥቶናል፡፡ (፩ጴጥ. ፩፥፫)፡፡ እነዚህ የጸጋ ስጦታዎች ሁሉ ጌታችን በመሠረታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የቅድስናችንንና የድኅነታችንን ምሥጢር ሁሉ የያዙ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ዋናው የክርስቶስ ሰው መሆን፣ መሰደድ፣ መራብ፣ መጠማት፣ መሰቀል፣ መነሣት በሰው ልጅ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሞት ድል አድርጎ ሰውን ለማዳን ነው፡፡ እንደ ሰው ድንቅ ውለታ የተዋለለት ፍጥረት የለም፡፡ በአባቱ ሞት የዳነ፣ ጠላቱን ያሸነፈ፣ ሠልጥኖበት ከነበረው ጠላት ነጻ የወጣ የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡ በሰው ሰውኛው አንድ ሰው እናት አባት ሲሞትበት አሳዳጊ ያጣል፤ የሚያለብሰው፣ የሚያጎርሰው፣ የሚያስተምረው፣ ርስት ጉልቱን የሚያወርሰው እና ከድኅነት የሚያወጣው ያጣል፡፡ በአባታችን በክርስቶስ ሞት ግን ያጣነውን ሁሉ አግኝተናል፡፡ ባለጸጎች ሆነናል፤ ወደ ርስታችን ተመልሰናል፡፡ አሁንም በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነን፣ የተከፈለልንን ውለታ እያሰብን በሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር፣ እንዲሁ ከበዓለ ስቅለቱና ከበዓለ ትንሣኤው በረከት ያድለን ዘንድ አምላከ ቅዱሳን ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!