በእኔ ውስጥ ያሉ ተኩላዎች

ብፁዕ አቡነ ሙሳ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን

የወጣቶች ጉዳይ ሊቀ ጳጳስ

   ዲ/ን በረከት አዝመራው እንደተረጎመው

ክፍል ሁለት

በኃጢአት የጎሰቆለ አእምሮ እንደ ተኩላ

አእምሮ /Mind/ በኃጢአት ጨልሟል፡፡ በዚህ ጨለማነት ምክንያት ብሩህ ካልሆነውና ከጨለመው አእምሮ የወጡ ብዙ ፍልስፍናዎችና የእምነት መጣመሞች /deviation/ አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል እግዚአብሔርን መካድ መርሑ የሆነው አቴይዝም /atheison/፤ እግዚአብሔር መኖሩን የሚያምነው ነገር ግን ከእርሱ ጋር መገናኘትን የማይፈልገው በዚህ መርሑም “በሰማይ ያለህ አባታችን ሆይ፣ አንፈልግህምና በዚያው ቆይ” የሚለው ኤግዚሰተንሻሊዝም /Existentialism/፤ ሁሉም ነገር /ወንበሩም ድንጋዩም/ የእግዚአብሔር የአካል  ክፍል እንደሆነ የሚናገረው ፓንትይዝም /pantheism/ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አእምሮ የጨለመው በኃጢአት ነው፡፡ አእምሮ ብሩህ ሲሆን ግን እግዚአብሔርን እናውቀዋለን፤ በመኖሩም በሁሉም እየሠራ እንደሆነ እንረዳለን፤ ወደ ዘለዓለማዊው መንግሥት የሚመራን እውነተኛው አምላክ እርሱ እንደሆነ እናውቃለን፡፡

በቅርቡ አንድ ታሪክ በኢንተርኔት አንብቤአለሁ፡፡ የተወሰኑ ልጃገረዶችን በክፍሏ የምታስተምር መምህርት ወደ አትክልት ቦታ ወሰደቻቸው፡፡ ከእነዚህ ወጣት ልጃገረዶች አንዷን ”ከጓደኞችሽ ፊት ሆነሽ መልሽልኝ፤ ይህ ዛፍ ይታይሻል?” አለቻት፡፡

“አዎ” አለች

“ያ ሕንፃስ ይታይሻል?” አለቻት፡፡

“አዎ” አለች፡፡

“እግዚአብሔርንስ ታይዋለሽ?”

“አላየውም” ልጅቷ መለሰች፡፡

መምህሯም “ስለዚህ እግዚአብሔር የሚባል ነገር የለም” አለች፡፡

ሌሎች ልጆች በመደናገጥ ላይ ሳሉ አንዷ ልጅ ተነሥታ “መምህር ዛፉ ይታይሻል?” አለቻት፡፡

“አዎ” አለች፡፡

“ወፎችስ ይታዩሻል?”

መምህሯም “አዎ” አለች፡፡

“ሰማዩስ ይታይሻል?” አለች ተማሪዋ ወደ ሰማይ እያየች፡፡

“አዎ” አለች መምህሯ፡፡

ተማሪዋ ጥያቄዋን ቀጠለች፡፡ “አእምሮሽን ታይዋለሽ?” ስትል ጠየቀች

“አላየውም” ብላ መለሰች መምህሯ፡፡

ተማሪዋም መምህሯን እየተመለከተች “ስለዚህ መምህር አእምሮ የለሽም” አለቻት፡፡

በብሩህና በጨለምተኛ አእምሮ መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ማየትና መንካት ምን ልዩነት ይፈጥር ይሆን? የቴሌቪዥን ሞገድን ማየት እንችላለን? ኤሌክትሪክንስን መንካት እንችላለን? ስለዚህ የሉም ማለት ነውን?

ብሩሃን ልንሆን ይገባል፣ ብሩህነትም ሊገኝ የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዎች በመታነጽ ነው፡፡

ዲያብሎስ በተለያየ መንገድ ዕውቀትና ጥበብ ያለን በማስመሰል ያታልለናል፤ እውነተኛው አብርሆት /Enlightmet/ ያለው ግን በቅዱሳት መጻሕፍት ነው፡፡ በዳዊት መዝሙር “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው” ብሏል፡፡ አንተ ብሩህ ነህ /Enlightened/ ከሆንክ ሌሎችን ብሩሃን ማድረግ ለመንገዳቸው ብርሃን መስጠት ይቻልሃል፡፡ ይህም በሥራህ፣ በዘመዶችህ እና በጓደኞችህ ሁሉ ይሆናል፡፡

የሥጋ ምኞት እንደ ተኩላ

ሥጋ ተኩላ ሊሆን ይችላል፡፡ ሥጋ ነፍስን፣ ነፍስም ሥጋን እንደሚዋጉ እና እርስ በእርሳቸው እንደሚቀዋወሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል፡፡ ይህ ከክርስቶስ መምጣት በፊት ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ክርስቶስ ግን ይህን የሥጋ ኃጢአት ዝንባሌ በእኛ ውስጥ ያሸንፈዋል፤ እንቆጣጠረውም ዘንድ ኃይል ይሰጠናል፡፡ በእርግጥ ኃጢአት እንደተመረዘ ማር ይጣፍጣል፡፡ ከክርስቶስ ጋር ያለች ነፍስ ግን ኃጢአትን መከላከልና መተው ይቻላታል፡፡ በመጽሐፈ ምሳሌ እንደተጻፈ በክርስቶስ “የጠገበች ነፍስ የማር ወለላ /ኃጢአትን/ ትረግጣለች” እንደተባለ፡፡

በኢንተርኔት የሙሰራጭ የዝሙት /pornographic/ ፊልሞችን ጨምሮ ወደ ኃጢአት የሚገፋፉ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉባችሁ አውቃለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እንደ ተርታ ነገር እየተለመደ ሲሄድ ዝሙት በሁሉም ቦታ የሚገኝ ተገቢ /normal/ እና ቅቡል /accepted/ እየሆነ ነው፡፡

ነገር ግን ይህ ወደ በለጠ ጥማት ነው የሚመራው፡፡ ስለዚህ በሥጋ ፍላጎት እየተመሩ በዝሙት ከመውደቅ መታቀብ ሕገ እግዚአብሔርን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ ሥጋህን ጨዋማ ውሃ ከሰጠኸው ሁሌም ሳይረካ ሲጠማ ይኖራል፡፡ በክርስትና ግን እስከ ጋብቻ ድረስ በንጽሕና መቆየት ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ያለበትን ቅዱስ ጋብቻ በእግዚአብሔር ቅድስና ሆነን ራሳችን በንጹሕ የጋብቻና የግንኙነት ቅዱስ ሕይወት እንመራ ዘንድ ይገባናል፡፡

በሥጋ የምትኖሩ ከሆነ በሥጋችሁም ትሞታላችሁ፡፡ ድል አድራጊ ሊያደርግህ የሚችል ብቸኛው አማራጭ ግን መንፈሳዊነት ነው፡፡ በመንፈስ ስትኖር በእርካታና በደስታ ትኖራለህ፡፡ በጭንቀትና በጾታዊ ፍላጎት /sexual desire/ መካከል ጥብቅ ግንኙነት አለ፡፡ በእግዚአብሔር ታምነህና ደስ ተሰኝተህ የምትኖር ከሆ ግን ከዚህ ጭንቀትና በዚህም ከሚመጣው ተገቢ ያልሆነ የሥጋ ፈቃድና ምኞት ነጻ ትሆናለህ፡፡ በጭንቀትና በስህተት፣ በአስቸጋሪ ነገሮች በተከበበ ሕይወት የምትኖር ከሆነ ምንም ይሁን ምን ደስታን የምታገኝበት መንገድ መፈልገህ አይቀርም፡፡ ከኃጢአት የሚመጣው ደስታ ጊዜአዊና ወዲያው ደግሞ የበደለኝነት እና ጸጸት ስሜት የሚያስከትል በመሆኑ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ደስታ ግን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ በእኛ ያደረገው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነውና፡፡ ይህ ደስታ በሕይወታችን የምንረካበት፣ የኃጢአትና የምኞት መንገዶችን እንዳንፈልግ በማድረግ ሁል ጊዜ በርካታ ያኖረናል፡፡ ለዘለዓለማዊ ሕይወትም እንድንበቃ ያደርገናል፡፡

ለማጠቃለል እነዚህን ተኩላዎች ለመከላከል በዚህ መንገድ እንዝመት

  • እኔነት /Ego/፡- በሕይወታችን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ እናድርግ እኛነታችን ግን ዝቅ ይበል፡፡
  • አእምሮ /Mind/፡- በእግዚአብሔር ቃል አእምሯችንን ብሩህ እናድርግ
  • ሥጋ /Flesh/፡- የክፉ ምኞት ደስታዎችን ከመፈለግ ተቆጥበን “የወይን ወለላን እስክንረግጥ” ድረስ የደስታ እርካታን የምናገኝበትን መንፈሳዊነትን ለማግኘት እንታገል፡፡

ምንጭ፡- ጉባኤ ቃና ጥቅምት ፳፻፬ ዓ.ም

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

“በእኔ ውስጥ ያሉ ተኩላዎች”

ብፁዕ አቡነ ሙሳ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን

የወጣቶች ጉዳይ ሊቀ ጳጳስ

   ዲ/ን በረከት አዝመራው እንደተረጎመው

ክፍል አንድ

እየተነጋገርንበት ያለው ርእስ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በውጭና በውስጥ ያሉብንን ተግዳሮቶች እንዴት መዋጋት እንዳለብን የሚያመልክት ነው፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች በእኛ ውስጥ እና ከእኛ ውጭ ያሉ “ተኩላዎች” ናቸው፡፡ እኛ እንደ በጎች ነን፤ ውስጣዊውንና ውጫዊውን ሕይወታችንን እየተፈታተኑ ሊናጠቁ የሚሞክሩት ደግሞ ተኩላዎች ናቸው።

የዛሬው ትምህርት ስለ ውስጣዊ ተኩላዎች ነው፡፡ እነዚህም በሕይወታችን የሚታዩ ውስጣዊ ተቃርኖዎችና ጠላቶች ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ፣ በማኅበራዊና ዘለዓለማዊ የሕይወት ጉዟችን በትክክለኛው አቅጣጫ እንጓዝ ዘንድ ይህንን ርእስ ልንነጋገርበት ይገባል፡፡ ሁሉን ብናገኝ ዘለዓለማዊነታችንን ግን ብናጣ ምን ይጠቅመናል? ስለዚህ ዘለዓለማዊነትን እንድናገኝ አጥብቀን መሥራትና በሕይወታችን ትልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባ ውሳኔን ይጠይቃል፡፡ እንደምታዩት ዓለም ትለዋወጣለች፤ ስለዚህ እውነታ ሊሆን የሚችለው የማይለወጠው ዘለዓለማዊነት ነው፡፡ ዓለምና ክብሯም ያልፋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ዓለም ሕይወት አሻግረን ፊታችን ያለውን ልንመለከት ግድ ይለናል፡፡፡ ቁሳዊውን ዓለም ብቻ የሚያስቡ ሰዎች ግን ታላቅ ስህተት ፈጽመዋል፡፡ ወሰንና መጨረሻ ከሌለው ከዘለዓለማዊው ዓለም ከእግዚአብሔር መንግሥት ይልቅ በውስኑ ዓለም ባክነው ይቀራሉና፡፡

የተፈጠርነው በእኛ ውስጥና ውጪ ካሉ ተኩላዎች ጋር አይደለም፡፡ እነዚህ በኃጢአት የሚመጡ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በመጀመሪያ አዳምንና ሐዋንን ሲፈጥር ያለ እነዚህ ተኩላዎች ነው፡፡ እነርሱ በኤደን ገነት የእግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር መኖር እየተሰማቸው ከእርሱ ጋር ይኖሩ ነበር፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ከዕፀ በለስ በስተቀር በገነት ውስጥ ካለው ዛፍ ሁሉ ይበሉም ነበር፡፡ የተፈቀደውም ጉዞ ሲደርሱ ከዕፀ ሕይወትም መብላቸው አይቀርም ነበር፡፡ እነርሱ ግን የተለየ ምርጫ መረጡ፡፡ በእርግጥ በዚህ ውሳኔአቸው ብዙም አንጸጸትበትም፡፡ ለድኅነት ታሪክ እኛ በእርሱ እርሱም በእኛ የሚኖርበትን ነገር ፈጥሯልና እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው በመሆኑ የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን ጠርቶናል፡፡ እነሆ አሁን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እስክንደርስ ድረስም ሁሉ ከፍ ከፍ የምንል ሆነናል፡፡

ስንፈጠር የተፈጠርነው በእግዚአብሔር አምሳል ነው፡፡ በጥበብና በአእምሮ ቅድስና በምንላቸው በፍቅር፤ በመንፈስና በምግባራት፣ በነፃነትና ነፃ ፈቃድ እንዲሁም በዘለዓለም ሕይወታችን እግዚአብሔርን የምንመስል ሆነናል፡፡ ሆኖም አዳምና ሔዋን ነፃነታቸውን ያለ አግባብ በተጠቀሙበት ጊዜ ከዕውቀት ዛፍ በሉ፤ ኃጢአትን በሠሩ ጊዜ ብሩህ አእምሯቸውን ማጣት ጀመሩ፡፡ ነፃነት ወደ አዳምና ሔዋን ውድቀት አመራ፤ ፈተና ከዲያብሎስ መጣ፤ ከኤደን ገነትም መውጣትም በእግዚአብሔር ተደረገ፡፡

በወደቀው ሰብእናቸው ለዘለዓለም እንዳይኖሩ በማሰብ ከሕይወት ዛፍ እንዳይበሉ በፍርዱ ከኤደን አስወጣቸው፡፡ ለዘለዓለም እንዲኖሩ ቢፈልግም ከድኅነት በኋላ መሆን ነበረበት፡፡ ስለዚህም ከመንግሥቱ ተለይተን እንዳንቀር ገነት ከእርሱ ጋር እንኖር ዘንድ ድኅነትን ማዘጋጀት ጀመረ፡፡

ስለዚህ የተኩላዎቹ ፈጣሪዎች እኛ እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ሁሉን ከፈጠረ በኋላ ሁሉም መልካም ነበርና ሰውንም ከፈጠረ በኋላ “በጣም መልካም” ብሏልና፡፡ ተኩላዎቹ ማደግ የጀመሩት በእኛ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ የውስጥ ተኩላዎች ምንድን ናቸው?

የመጀመሪያው ክፉ እኔነት ነው፡፡ ሁለተኛው የኃጢአት ሕግ የተጠናወተው አእምሮ ነው፡፡ ይህ አእምሮ እንደዚህ እንዲሆን ባይፈጠርም በኃጢአት ከጨለመ በኋላ እንደዚህ ሆነ፡፡ ሦስተኛው ሥጋችን ነው፡፡ ነገር ግን ሥጋ በራሱ ችግር እንዳልሆነ ማወቅ ይገባናል፡፡ ተኩላ የሚያደርገው በውስጣችን የሚኖረው ኃጢአት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ዐይን መልካምም ክፉም ነገር ሊያይ ይችላል፡፡ መንፈሳዊ እድገታችንና አኗኗራችንን የሚያሰናክሉት ሦስት የውስጥ ተኩላዎች እንዚህ ናቸው፡፡

የክፉ እኔነት ተኩላ /Ego/

እኔነት እንዴት ተኩላ ሊሆን ይችላል? እኔነት/Ego/ ከእግዚአብሔር እና ከሌሎች ተለይተን በራሳችን ውስጥ ታጥረን በትዕቢት፤ በከንቱ ውዳሴና በራስ ወዳድነት እንድንያዝ ምክንያት ይሆናል፡፡ ከቅዱስ ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ከሚለው መልእክት በተቃራኒ በራሳችን ብቁ እንደሆንን እና አግዚአብሔር ሳያስፈልገን ሁሉን ማድረግ እንደምንችል እንድናምን ያደርገናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን “ሁሉን እችላለሁ” ብሎ አላቆመም፤ እነዚህን ማድረግ የሚችል በእግዚአብሔር መሆኑን ዐውቋል፡፡ እኔነት የተጠናወተው ሰው በሕይወቱ ያሉትን መልካም ነገሮች ከእግዚአብሔር ጋር ማዛመድ አይፈልግም፡፡ ክፉ እኔነት/Ego/ በኤደን ገነት የኃጢአቶች ምንጭ ነበር፡፡ ዲያብሎስ የወደቀው እንደ እግዚአብሔር  ሊሆን በመፈለጉ ነውና፡፡ አዳምና ሔዋንም በእባቡ የተታለሉት እንደ እግዚአብሔር መሆን ፈልገው ነው፡፡

እግዚአብሔር በሕይወትህ ሲኖር መንፈስህ ከፍ ከፍ ይላል፤ እኔነትህ ግን ዝቅ ዝቅ ይላል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ “እርሱ ሊበዛ እኔ ግን ላንስ ይገባል” እንዳለ በሕይወትህ የእግዚአብሔር ቦታ ከጨመረ እኔነትህ /Ego/ እየቀነሰ ነው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርን በሕይወታችን የምንፈልገውም ለዚህ ነው፡፡ በንስሓ፣ በቍርባን፣ በጸሎት፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት፣ በጾም፣ በስግደት እና በምሥጋና እግዚአብሔር በውስጣችን ያድራል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በምናደርገው በማንኛውም ግንኙነት ወደ ላይ የተዘረጋ መስመር እንመሠርታለን፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ወደ ውስጥ እንዘረጋለን እርሱም እኔነት /Ego/ ነው፡፡

ምድራዊው ገጽታ ደግሞ ሥጋዊነት ነው፡፡ ወደ ላይ እንመለከት ዘንድ ካህኑ በቅዳሴ ጊዜ “ልባችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” የሚለን እኛም “ከመንፈስህ ጋር ነው” ብለን የምንመልሰው ይህንን ነው፡፡ መፍትሔአችን እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱን በውስጣችን ልንይዝ ይገባል፡፡ ይህንን ምሳሌ ተመልከቱ፡፡ ልብን በጎነ ሦስት/Triangle/ ብንመስለው /በእርግጥም ልብ ሦስት ጎን ቅርጽ አለው፤ ዓለምን በጎነ ሦስቱ /Triangle/ ዙሪያ በተሳለ ክብ ቅርጽ ብንወክላት፣ ውስጥ ያሉት ማዕዘናት በምንም ተአምር በክቡ ሊሞሉ አይችሉም፡፡ ጎነ ሦስት የሆነውን ልብ ለመሙላት በሦስትነት የሚኖረው እግዚአብሔር ያስፈልጋል፡፡ የቅድስት ሥላሴ ፍቅር ግን ልቡናህን በደስታ፣ በቅድስና፣ በጥበብ እና በዘለዓለማዊነት ይመላዋል፡፡ እንድትኖር ወደተፈጠርክለት የእግዚአብሔር አምሳልነት ይመልስሃል፡፡

የክፉ እኔነትን /Ego/ ውጥንቅጥ ለመፍታት እግዚአብሔር ፍቅር፣ አምልኮቱ በልቡናህ ውስጥ ማደግ አለበት፣ በዚህ ጊዜ ክፉ እኔነትህ ይቀንሳልና፡፡

ምንጭ፡- ጉባኤ ቃና ጥቅምት ፳፻፬ ዓ.ም

ይቆየን፡፡

ዘረኝነት፤ የዘመናችን ወጣቶች ተግዳሮት

በአዱኛ ጌታቸው

ክፍልሦስት

ከዘረኝነት ጠባይ ለመራቅ ወጣቶች ምን ማድረግ አለባቸው?

ሥጋዊ ማንነትንና ክርስትናን መለየት

በማነንት ጉዳይ ብዙ ክርክሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ምድራዊው ማንነት በሰዎች መንፈስ የተገነባ ሲሆን ሰማያዊው ማንነት ደግሞ በመስቀል ላይ የተገነባ ነው ይላሉ፡፡ ምድራዊ ማንነት ሙሉ በመሉ ሰው ሠራሽ ነው ብሎ መቀበል ቢከብድም ኃላፊ ጠፊ መሆኑ ግን አያጠራጥርም፡፡ በምድራዊው ማንነት ውስጥ በተፈጥሯዊ ሂደት የምንወርሳቸው ማንነቶች ይኖራሉ፤ በጊዜ ሂደት በመማር ወይም በመላመድ የምንወርሳቸው ማንነቶች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ ጾታን፣ የቆዳ ቀለምን፤ አካላዊ ቁመና የመሳሰሉትን በተፈጥሮ የምንወርሳቸው ማንነቶች ናቸው፡፡ ቋንቋ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ በአጠቃላይ የሰዎች የአኗኗር ዘዬ ከማኅበረሰብ የሚወረሱ ማንነቶች ናቸው፡፡ ግለሰቦችን ወይም ማኅበረሰቦችን አንድ የሚያደርጋቸው ማንነት ይኖራል፤ የሚለያቸው ማንነትም ይኖራል፡፡

አንድ የሚያደርጉንም ሆነ ልዩ የሚያደርጉን ሥጋዊ ማንነቶች ከሃይማኖታችን ዓላማ ወይም እሳቤ ጋር እስካልተጋጩ ድረስ አክብሮና ተቀብሎ መኖር ሰላማዊና ጤናማ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲኖረን ይረዳናል፡፡ ግጭት ወይም አለመግባባት የሚፈጠረው የራስን አድንቆ የሌላውን ማንቋሸሽ ሲጀመር እንዲሁም የእኔን ማንነት ካልተቀበልክ ብሎ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ጫና ለማሳደር መሞከር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ከእግዚአብሔር መንግሥት ሊለየን ይችላል፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ በማለት ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯቸዋል፡፡ (ማቴ. ፯፥፲፪)

በመሆኑም የሌሎች ወንድሞቻችንን ማንነት አክብረን በሰላም መኖር ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ምድራዊ ማንነት ቢኖረውም ከክርስትናው ሊበልጥበት አይገባም፡፡ ምክንያቱም ምድራዊ ማንነት በምድር የሚቀርና ጊዜያዊ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ማንነት ግን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ በፍርድ ቀን የምንጠየቀው የምንናገረውን ቋንቋ ወይም የምንከተለውን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወይም ደግሞ የኖርንበትን ማኅበረሰባዊ ባህል አይደለም፡፡ ስለ ሠራነው መልካም ሥራ እንጂ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓለም ስንኖር የማንነታችን ሚዛን ሊሆን የሚገባው ክርስትናችን ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ተራ ነገር ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ “በዚህ በሚሞት ሰውነታችሁ ኃጢአትን አታንግሧት፣ ለምኞቱም እሺ አትበሉት፡፡ ለእግዚአብሔር ራሳችሁን መሥዋዕት አድርጉ እንጂ ሰውነታችሁን ለኃጢአት የዐመፅ የጦር መሣሪያ አታድርጉት” ይላል፡፡ (ሮሜ ፮፥፲፪)፡፡  ስለሆነም ክርስቲያን ወጣቶች ፖለቲከኞችና የጎሳ አቀንቃኝ ቡድኖች ለራሳቸው ጥቅም በሚቀይሱት የጥፋት መነገድ ተጠልፎ ላለመግባት ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡

በወጣትነት ዘመን እንደ ዜጋ ለሀገርና ለማኅበረሰብ የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንደ ሃይማኖት ሰው ደግሞ በመንፈሳዊ ሕይወት ለማሳደግ መትጋት እንጂ ለሥጋም ለነፍስም በማይበጅ ሐሳብ መጠመድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

ለሕሊና መኖር

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ “ብፁዓን ነጹሐነ ልብ” በሚለው መጽሐፋቸው “የሃይማኖት ሰው መሆን የሚቻለው መጀመሪያ በሕሊናችን ማዘዝ ስንችል ነው” ይላሉ፡፡ ሕሊና የመፈተሸ፣ የመመርመር፣ የመምረጥ፣ የአመክንዮ ችሎታ አለው፡፡ ሕሊና የእውነት ሚዛን ነው፡፡ ሊባንዮስ የሚባል በዐራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረ የታወቀ ፈላስፋ ነበር፡፡ በዘመኑ የምርምር መስክ እጅግ የተራቀቁ ተማሪዎችን ስላፈራ ከነዚህ ለየትኛው የመምህርነት መንበሩን እንደሚያወርስ ቢጠይቁት “ለዮሐንስ ነበር ወደ ክርስትና ተሻገረ እንጂ” ብሎ መለሰ ይባላል፡፡

ዮሐንስ የተባለው ትልቁ የቤተ ክርስቲያችን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡ ታላቁ አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕሊናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ ይላል፡፡ ሕሊናን ከፍ ከፍ ማድረግ ማለት ከተራው፣ ከሚለያየው፣ ከሚከፋፍለው አስተሳሰብ፣ ከደሴቱ ከሥርቻው ወደ ኮረብታው ወደ ተራራው ውጡ፤ ወደ ሰማይም ቀና በሉ፤ ተገቢ ቦታችሁን ዐውቃችሁ በዚያ ቁሙ፣ የእውነት ቃል የደግነት ዜና ስሙ፤ አዳምጡም፤ ማለት ነው፡፡ እኛ ሕያውያን ፍጥረታት መሆናችንን ስናስብ የሚለያየንና የሚከፋፍለን አጀንዳ ሁሉ ተራና የማይጠቅም ሐሳብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኃላፊና ቁሳዊ በሆነ አጀንዳ ልቡናችን ከባዘነ ግን ከሕሊና በታች እንሆናለን፡፡

በፖለቲካው ዘርፍ በንቃት መሳተፍ

በአገራችን በማንነት ላይ የተመሠረተ ግጭት በስፋት የሚስተዋለው ክርስቲያኖች ከፖለቲካና ከውሳኔ ሰጪነት በመራቃቸው ነው፡፡ ክርስቲያን ሲባል የስም ክርስቲያን ሳይሆን ለእውነት የቆመውንና ለእውነት የሚተጋውን ማለታችን ነው፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ለፍትሕና ለሰው ልጅ እኩልነት ይተጉና ፍርድ ጎደለ ደኃ ተበደለ ብለው የሚሠሩ እንደነበር በልዩ ልዩ የታሪክ መዛግብት ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ኢትዮጵያውያን እንኳንስ ለራሳቸው ዜጋ ይቅርና ለወራሪ ጠላት እንኳ የሚራሩ እንደነበር በታሪክ መዛግብት ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡

ኢትዮጵያውያን በግብረ ገብነት እንዲታወቁ ያደረጋቸው በዋናነት እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሕዝቦች በመሆናቸው ነው፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠረው የሰው ልጅ ይራራ ዘንድ ግድ ይለዋልና፡፡ ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያን ይመሩና ያስተዳድሩ የነበሩ ነገሥታት ሁሉ እንከን አልነበራቸውም ማለት እንዳልሆነ ልገነዘብ ይገባል፡፡ ክርስቲያኖች በፖለቲካው ቢሳተፉ ዛሬ ላይ የምናስተውላቸው መለያየቶች ባልተፈጠሩ ነበር፡፡

ምክንያቱም ዳዊት ደስታ ኦርቶዶክሳውያን እና ፖለቲካ በሚለው መጽሐፉ ከገጽ ፩፻፫ ጀምሮ እንደገለጠው ክርስቲያኖች በፖለቲካው በንቃት ቢሳተፉ ዴሚክራሲ ይሠፍናል፤ የፖለቲካ መረጋጋት ይመጣል፤ አገርን ከመፍረስና ከመበታተን መታደግ ይቻላል፤ ክርስቲያኖች በሀገራቸው በክፉ መሪዎች አንዳይሞቱና ለስደትና ለእንግልት እንዳይዳረጉ መታደግ ይቻላል፤ ክርስቲያንም ሆነ ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ተከብሮ በነጻነት እንዲኖር ማድረግ ይቻላል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚተጉ የውጭና የውስጥ ኃይሎችን መከላከል ይቻላል፤ ብልሹ አሠራር እንዳይኖርና ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላል፤ ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን የምንመኘውን መልካም ተግባር መፈጸም ይቻላል፤ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በሰውነቱ ተከብሮ እንዲኖር ማድረግ ይቻላል፤ የሥጋም ሆነ የነፍስ ድህነትን ለማስወገድ ዕድል መፍጠር ይቻላል፤ ዛሬ ላይ የምናስተውለው የጎሳ ግጭት እንዳይፈጠር ማድረግ ይቻላል፤ ወዘተ፡፡ ነገር ግን አቅምና ችሎታ ያላቸው ክርስቲያኖች በራሳቸውና በውጫዊ ምክንያቶች ከፖለቲካው በመራቃቸው ከላይ የተዘረዘሩትን በጎ ተግባራት ማከናወን አልተቻለም፡፡ ዛሬም ቢሆን አልረፈድምና ወጣቶች በፖለቲካው በንቃት በመሳተፍ አገርንና ቤተ ክርስቲያንን ከአጥፊዎች ለመታደግ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን አለባቸው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዘረኝነት፡ የዘመናችን ወጣቶች ተግዳሮት

በአዱኛ ጌታቸው 

ክፍል ሁለት

የዘረኝነት አስተሳሰብ በኢትዮጵያ መቼ ተጀመረ?

አንዳንድ የዓለማችን ሀገራት እየተባባሰ የመጣውን የዘር ጥላቻ ለማስወገድ በሕግ አስደግፈው ቢሠሩም ዘርን ወይም ማንነትን መሠረት ያደረ ጥላቻንና መድሎን ማስቀረት አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡ ሠለጠኑ በሚባሉት አገራት ሳይቀር የዘረኝነትን ጠባይ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አልቻሉም፡፡ የዘረኝነት እሳቤ በአገራችን መቼ እንደገባ በትክክል ባይታወቅም በሰነድ የተደገፈ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከ፲፱፻፷ዎቹ ጀምሮ እንደሆነ የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ማንነቶች ያሏቸው ሕዝቦች ባለቤት በመሆኗ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ማንነትን የፖለቲካ ማእከላቸው በማድረግ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ማንነትን መሠረት ያደረገ አለመግባባት ወይም ግጭት ሊፈጠር ይችላል፡፡

በሀገራችን በሕዝቦች መካከል ማንነትን መሠረት ያደረገ ግጭት አሁን ባለበት ደረጃ ባይሆንም በታሪክ አጋጣሚ በተለያየ ምክንያት በሕዝቦች መካከል አለመግባባትና ግጭት ተፈጥሮ ያውቃል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት መዋቅር የተደገፈና በማንነት ላይ የተመሠረተ መገፋፋት እየተባባሰ የመጣው ከዐለፉት ሠላሳና ዐርባ ዐመታት ወዲህ ነው፡፡

ስለ ዘረኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ “እርሱም በምድር ሁሉ ላይ ይኖሩ ዘንድ ሰዎችን ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ ይኖሩባትም ዘንድ ዘመንንና ቦታን ወስኖ ሠራላቸው” በማለት ይገልጻል፡፡  እንዲሁም ከሊቀ ነቢያት ሙሴ መጻሕፍት መካከል “አዳምም የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን ብሎ ጠራት” የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ዘሩ አንድ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም” አላቸው፡፡ (ሐዋ. ፲፯፥፳፮፣ ዘፍ. ፫፥፳፣ ፩፥፳፰)

በመሆኑም አዳምና ሔዋን ለመላው የሰው ዘር አባትና እናት እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የኖኅ ዘመን ሰዎች በኃጢአታቸው ምክንያት የጥፋት ውሃ መጥቶ በምድር ላይ ያለውን ሁሉ ባጠፋ ጊዜ ኖኅና ቤተሰቡ ከመጣው የጥፋት ውሃ ድነዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የኖኅ ልጆች እንደሆንን መረዳት እንችላለን፡፡ (ዘፍ.፱፥፲፰)

ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ በማለት ክርስቲያኖች ገንዘብ ሊያደርጉት የሚገባውን ማንነት አስተምሯቸዋል፡፡፣ ማቴ. ፳፫፥፰)

ከምንም በላይ ክርስቲያኖች ለአንድነት ይተጉ ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርአያ ሆኖ አስተምሮናል (ዮሐ. ፲፯፥፳)፡፡ አንድነትንና አብሮነትን አጥብቆ የሰበከው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልእክት “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እማልዳችኋለሁ፤ እንዳትለያዩም አንድ ልብና አንድ ሐሳብ ሆናችሁ ኑሩ” በማለት ክርስቲያኖች ከመከፋፈልና ከመለያየት ሐሳብ እንዲርቁ አስተምሯል፡፡(፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲)

ይኸው ሐዋርያ በመልእክቱ “እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳሁም ብልቶች ናችሁ” በማለት ክርስቲያኖች በክርስቶስ አንድ እንደሆንን ይመሰክራል፡፡ (፩ኛቆሮ. ፲፪፤፳፯)፡፡ በአጠቃላይ ከቅዱሳት መጻሕፍት የምንማረው መለያየትን ሳይሆን አንድነትን፣ ጠላትነትን ሳይሆን ወንድማማችነትን፣ ጥልን ሳይሆን ሰላምን፣ ራስ ወዳድነትን ሳይሆን መተሳሰብን፣ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን ነው፡፡

ዘረኝነትና የክርስትና ሕይወት አብረው መሄድ ይችላሉን?

ለዚህ ጥያቄ መልሱ አብረው አይሄዱም ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደተናገረው ስንፍና አምላክን እስከመካድ ያደርሳል(መዝ. ፲፫፥፩)፡፡ ዘረኝነት ስንፍና ነው፡፡ ዘረኝነት ሃይማኖትን እስከ መካድ ያደርሳል፡፡ ዘረኝነት ከግብረ ገብነት ያፈነገጠ ጠባይ ነው፡፡ ከግብረገብነት የወጣ ሰው ደግሞ ለምኞቱ ድንበር የለውም፡፡ በዘረኝት የተለከፈ ሰውም ለጥፋቱ ዳርቻ የለውም፡፡ ክርስትና ክርስቶስን መምሰል ሲሆን ዘረኝነት ደግሞ ሰይጣንን ወይም ዲያብሎስን መምሰል ነው፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፲፩፥፩)

ክርስትና አንድነትንና ፍቅርን ይሰብካል፤ ዘረኝነት ደግሞ መለያየትንና ጥላቻን ይደሰኩራል፤ ክርስትና ባልእንጀራን እንደ ራስ መውደድን ያስተምራል፤ ዘረኝነት ደግሞ ባልንጀራን መግደልን ማሳደድን ይሰብካል፡፡ ክርስትና “የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ፤ ደስ ከሚለው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሰው ጋርም አልቅሱ፡፡ እርስ በእርሳችሁም በአንድ ሐሳብ ተስማሙ በማለት ያስተምራል፡፡(ሮሜ. ፲፪፡፲፮) ዘረኝነት ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ በቀልን ጠላትነትን ይሰብካል፡፡ ስለሆነም ዘረኝነትን ልንርቀው የሚገባ ክፉ ጠባይ ነው፡፡

ይቆየን፡፡

ዘረኝነት፡ የዘመናችን ወጣቶች ተግዳሮት

በአዱኛ ጌታቸው

ክፍል አንድ

መግቢያ

እንደ ማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች የወጣትነት ዘመን የሽግግር ዘመን ነው፡፡ ይህ ሽግግር በሁለት ይመደባል፡፡ አንደኛው ከልጅነት ወደ ጎልማሳነት የሚሸገጋሩበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከቤተሰብ ጥገኝነት ራስን ወደ መቻል የሚሸጋገሩበት ዘመን ነው፡፡ ይህ የሽግግር ዘመን ወጣቶች ጊዜያቸውን በማስተዋል ከመሩት ለፍሬ የሚበቁበት በማስተዋል ካልመሩት ደግሞ ለጥፋትና ለውድቀት የሚደራጉበት ጊዜ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ስለ ወጣትነት ዘመን ሲናገሩ “በአበባ ውስጥ የፍሬ እንቡጥ ለመያዝ መጀመሪያ የአትክልቱ አያያዝ ደንበኛ ሆኖ ሲገኝ ይጠቅማል፡፡ ወጣትም ከፍሬ ለመድረስ የሚችለው በወጣትነቱ በሠራው ሥነ ምግባር ነው፡፡ ወጣት ሰውነቱን በቆሻሻ ምግባር ያቆራመደው እንደሆነ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ያቀደውም ነገር ከመንገድ ይመለሳል፡፡ መንፈሳዊ ዕድል እንዲያውም አይታሰብም” ይላሉ፡፡ (ሥነ ምግባር ገጽ ፶፫)

በአጠቃላይ የወጣትነት ጊዜ ለቀጣይ የዕድሜ ዘመናት መሠረት የሚጣልበት በመሆኑ በማስተዋል መጓዝን የሚጠይቅ ነው፡፡ ወጣቶች በዘመናቸው ልዩ ልዩ አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ተግዳሮቶች ሊገጥሟቸው ይችላል፡፡ ከእነዚህ ተግዳሮቶችም አንዱ ዘረኝት ነው፡፡

ዘረኝነት ምንድነው?

በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ወጥነት ያለው ትርጕም ለመስጠት አስቸጋሪ ከሆኑ ቃላት አንዱ ዘር ወይም በእንግሊዝኛው (Race) የሚባለው ነው፡፡ በተለይም ዘር፣ ጎሳ፣ ነገድ፣ ብሔር ወዘተ የሚሉ ቃላት በተለያዩ አገራት የተለያየ ትርጕምና ይዘት ሊኖራቸው ስለሚችል ተመሳሳይ ግንዛቤ ለመያዝ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

ለአብነት አንዳንድ ሰዎች ከቅርብ ዐሥርት ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የሚታየው የሕዝብ አለመረጋጋትና ቀውስ ምንጩ ተግባራዊ እየሆነ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አወቃቀር ዘርን ወይም ጎሳን ወይም ቋንቋን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡ ፖለቲከኞችም ይሁን የፖለቲካ ተንታኞች ይህን ይበሉ እንጂ አሁን ላይ ያለው የሃገሪቱ ሕገ መንግሥት መንግሥታዊ መዋቅሩ በዘር፣ ወይም በጎሳ፣ ወይም ደግሞ በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ነው አይልም፡፡

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፵፮ “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ የማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው” ይላል፡፡ ስለዚህ ከሕገ መንግሥት አንጻር ከተመለከትነው የሀገራችን ሕገ መንግሥት ለብቻው ነጥሎ በዘር፣ ወይም በቋንቋ፣ ወይም በጎሳ ላይ የተመሠረተ ነው እንደማይል አንብቦ መረዳት ይቻላል፡፡ ታዲያ መንግሥታዊ አወቃቀሩ በዘር ላይ ወይም በጎሳ ወይም በቋንቋ ላይ ነው የተመሠረተው የሚለው አባባል ምንጩ ምን ይሆን? ለሚለው መላምት ከመስጠት የዘለለ ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡

እርግጥ አንዳንድ ፖለቲከኞችና የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ ግለሰቦች ሕገ መንግሥቱን በራሳቸው አረዳድና ፍላጎት በመተረጎም ለራሳቸው ዓላማ ማስፈጸሚያ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያውያን በቋንቋቸው፣ በባህላቸው፤ በሃይማኖታቸው በአጠቃላይ በማንነታቸው ምክንያት በደል ሊደርስባቸው ይችላል እንጂ የሀገራችን ሕገ መንግሥት ዘረኝነትን አያበረታታም፡፡ እንዲያውም “ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑንና ማንኛውም ሰው በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው” ተብሎ በአንቀጽ ፳፭ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ የሰው ልጅ እኩልነትን ያረጋግጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ የሕግ ባለሙያዮች የበለጠ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይችላሉ፡፡ በግርድፉ መረዳት የምንችለው ጉዳይ ቢኖር ግለሰቦችና ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ከሕግ በአፈነገጠ መንገድ በመጓዝ ሕዝብን ከሕዝብ የሚለያዩ አጀንዳዎችን በማቀበል አፍራሽ ተግባር ላይ መሠማራታቸውን ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ የተጠቀሰውና ምናልባትም የዘረኝነት ምንጭ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚገመተው “ማንነት” የሚለው ቃል ነው፡፡ ማንነት የሚለው ቃል ደግሞ የብዙ ጥቃቅን ማንነቶች ድምር ውጤት እንጂ በቀጥታ ዘርን ብቻ አያመለክትም፡፡ ለምሳሌ ጾታ ራሱን የቻለ ማንነት ነው፣ የቆዳ ቀለም አንድ ማንነት ነው፤ሃይማኖት አንድ ማንነት ነው፣ ኢትዮጵያዊነት አንድ ማንነት ነው፣ ቋንቋ አንድ ማንነት ነው፣ ወጣትነት ወይም ጎልማሳነት ወይም እርግና ሌላኛው ማንነት ነው፣ ወዘተ፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉት ማንነቶች በአንድ ሰው ጥቅል ማንነት ላይ ሊኖሩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኚዎች ዘር የሚለውን ቃል በዋናነት ሁለት መገለጫዎች እንዳሉት ይናገራሉ፡፡ አንደኛው በግልጽ የሚታይና ከሌላው ማኅበረሰብ ሊለይ የሚችል የአካል ወይም የቆዳ ቀለም ልዩነት ሊኖር ይገባል ይላሉ፡፡ ለምሳሌ በምዕራቡ ዓለም የሰው ልጅ ጥቁርና ነጭ ተብሎ እንደሚከፋፈለው ዓይነት በግልጽ ሊታይ የሚችል አካላዊ መለያ ሊኖር ይገባል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የእገሌ ዘር አባል ነን ብለው ራሳቸውን ከሌላው ማኅበረሰብ አግልለው የራሳቸውን ማኅበረሰብ የፈጠሩና ከብዙኃኑ ማኅበረሰብ ራሳቸውን ያገለሉ ከሆነ ዘር የሚለውን መስፈርት ሊያሟሉ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ዘር የማንነት አካል ሊሆን ይችላል እንጂ ማንነትን ሙሉ ለሙሉ ሊተካ አይችልም ማለት ነው፡፡

በአንጻሩ ጎሳ ማለት ሦስት መመዘኛዎችን የሚያሟላ ነው፡፡ የመጀመሪያው በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩና የጋራ ማንነት ያላቸው ናቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንደኛውን ጎሳ ከሌላው ጎሳ የሚለዩበት ማንነት በዋናነት አካላዊ ገጽታ (Phisical appearance) ሳይሆን የጋራ የሚሉት ባህላቸው፣ ታሪካቸው፣ ቋንቋቸው ነው፡፡ ሦስተኛው መመዘኛ ደግሞ ከሌላው ማኅበረሰብ በተለየ ሁኔታ በቁጥራቸው ጥቂት(Minority) ስሜት ያላቸው ናቸው፡፡ በእኛ አገር ፖለቲከኞች ጎሳ የሚለውን ትርጓሜ ብሔር ወይም ብሔረሰቦች የሚለው ቃል ጥቅም ላይ ሲውል እንመለከታለን፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ ትርጕም እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ስለ ማንነት፣ ስለ ዘር፣ እንዲሁም ስለ ጎሳ ይህን ካልን እገሌ ዘረኛ ነው፤ እገሊት ዘረኛ ናት፤ እነ እገሌ ዘረኞች ናቸው፣ በመካከላችን ዘረኝነት ተስፋፍቷል ወዘተ ስንል ምን ማለታችን ይሆን የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ እውነት በሀገራችን የምናስተውለው የእርስ በርስ መገፋፋት ጎሰኝነት የወለደው ነው ወይስ ዘረኝነት የወለደው የሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኝዎች ዘረኝነትን ከአካላዊ ገጽታ ባሻገር ሰፋ አድርገው ይመለከቱታል፡፡

አንድን ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ወይም ተቋም የሌላ ዘር ወይም ጎሳ አባል በመሆኑ ብቻ በማንነት ላይ የተመሠረተ ጭፍን፣ ጥላቻ፣ አድልዎ ወይም ጠላትነት ማለት ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በሀገራችን የምንመለከተው ጭፍን ጥላቻ፣ አድልዎ ወይም ጠላትነት የአካል ገጽታን ወይም የዘር ሐረግን መሠረት ያደረገ ሳይሆን በዋናነት ባህልን፣ ቋንቋንና ሃማኖትን መሠረት ያደረገ ነው ብንል አሳማኝ ይሆናል፡፡

እዚህ ላይ አንድ እውነታን መረዳት የግድ ይለናል፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የሀገራችን ሕገ መንግሥት ለማንነት ትልቅ ቦታ ይሰጣል፡፡ ለሰው ልጅ እኩልነትም ትልቅ ቦታ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በማንነት ላይ የተመሠረተ መንግሥታዊ አስተዳደር በባሕርዩ አግላይ በመሆኑ በሕዝቦች መካከል አለመግባባትና ግጭት እንዲፈጠር ዕድል ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳ በሕግ ደረጃ የተቀመጠ አግላይነት ባይኖርም በመንግሥት መዋቅር ላይ የተቀመጡ አንዳንድ ፖለቲከኞች የእኔ ለሚሉት ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ሊያደሉ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተዳደር በሕዝቦች መካከል ማንነትን መሠረት ያደረገ ጭፍን ጥላቻና አግላይነት ሊፈጥር ይችላል፡፡ አሁን ላይ በአገራችን እየተስተዋለ ያለው የዜጎች መፈናቀል፣ ስደትና ሞት በዋናነት በማንነት ላይ የተመሠረተ ጭፍን ጥላቻና አግላይነት የወለደው እንደሆነ እሙን ነው፡፡

ይቆየን፡፡

የቴክኖሎጂ ጥቅም በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና እይታ

በዲ/ን በረከት አዝመራው

የሰው ልጆች በምድራውያኑ ፍጥረታት ውስጥ ካሉት ድርሻዎች ውስጥ መሪነት እና ገዢነት ይጠቀሳሉ፡፡ “ምድርን ሙሏት … ግዟትም” የሚለው ቃል ለሰው ልጅ የተሰጠውን ኃይል፣ ዕውቀትና ሥልጣን የሚገልጥ ነው፡፡ (ዘፍ. ፩፥፳፰)፡፡ ይህ ገዢነትና በእነዚህ ፍጥረታት ላይ የተሰጠው ሥልጣን በምን ገለጣል? ሰው ይህን ለማድረግ የሚያበቃ ምን ነገር አለው? እንዲገዛቸውና እንዲጠቀምባቸው ከተፈጠሩት ፍጥረታት መካከል ከእርሱ የሚበረቱ፣ የሚፈጥኑ እና የሚገዝፉ ፍጥረታት እንዴት ከበታቹ ሊሆኑ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን፡፡

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የምናገኘው የሰውን ጥንት ተፈጥሮ በማስተዋል ነው፡፡ ሰውን ይህን ክብር ያቀዳጀው የሰው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል መፈጠሩ ነው፡፡ (ዘፍ. ፩፥፳፮-፳፯)፡፡ ሰው በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ተፈጠረ ስንል የእግዚአብሔር የባሕርይው መገለጫዎች ወሰን የሌላቸው እና ከማንም ያልተቀበላቸው ናቸው፤ ባሕርይውን ደግሞ ለሰው ልጅ በፀጋ ሰጥቶታል ለማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው አዋቂ እንደሆነ ሁሉ ሰውም የፀጋ አዋቂነት ተሰጥቶታል፤ እግዚአብሔር በባሕርይው ገዥ(ንጉሥ) እንደሆነ ሁሉ ለሰውም በፀጋ በምድራዊው ሁሉ ገዥነት ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር የባሕርይ አምላክ በመሆኑ ሁሉም ፍጥረታት በፍርሃት እና በአክብሮት ሆነው በፊቱ እንደሚቆሙ ሁሉ ሰውም እግዚአብሔር ከሰጠው የፀጋ አምላክነት እና ግርማ የተነሣ በኃጢአት ከመጎስቆሉ በፊት ምድራውያን ፍጥረታት በአክብሮትና በፍርሃት ይታዘዙት ነበር፡፡ ይህም የሚታወቀው አስፈሪ የሆኑ አራዊት እንኳን ሳይቀሩ ለቅዱሳን በሚያሳዩት አክብሮትና መታዘዝ ነው(ዘፍ. ፪፥፳)፡፡

ለሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተሰጠው ዕወቀት፣ ጥበብ እና ማስተዋል አለው፡፡ ሰው ቢበድለውም እንኳን የሰጠውን ዕውቀት፣ ጥበብ እና ማስተዋል አለመግፈፉ ከቸርነቱ የተነሣ ነውና ይህ የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ ለሰው ያለውን ርኅራኄ እና መግቦት ያሳያል፡፡ በዓለማችን በዘመናት የምናያቸው ዕውቀቶች፣ ጥበቦች እና በማስተዋል የተገኙ ግኝቶች ሁሉ ከዚህ ከእግዚአብሔር ሥጦታ ምንጭ እንደ ወንዝ የሚፈሱ የፀጋ ሥጦታዎች ናቸው፡፡

በዘመናችን ተስፋፍትው የምናያቸው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግኝቶችም የዚሁ አካል ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ይህ በተፈጥሮ የተሰጠውን አዋቂነት እና ጥበብ ተጠቅሞ በየዘመኑ ሕይወቱን ያሳልጥበታል፤ የየዘመኑን ፈተናዎች ይቋቋምበታል፤ በአጠቃላይ ሕይወቱን በአግባቡ ለመምራት ይጠቀምበታል፡፡

ጠለቅ ብለን ስናየው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት እግዚአብሔር በሰው ውስጥ ያስቀመጠው መግቦት ነው፡፡ ይህን በጥንት ተፈጥሮ የሰጠውን ፀጋ በበደለው ጊዜ እንኳን አልነሳውም፤ ይህም ከላይ እንዳልነው የቸርነቱ ውጤት ነው፡፡

ልዑል እግዚአብሔር ለሰው የመግቦት አካል ይሆን ዘንድ፣ በኑሮው የሕይወቱን ውጣ ውረድ እንዲያቀልለት ዕውቀትንና ጥበብን በመስጠቱ ሰው በአእምሮው የዕውቀት ምጥቀትና በጥበቡ እየታገዘ እግዚአብሔር የፈጠራቸውን ፍጥረታት በመጠቀም ብዙ ድንቅ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አስገኝቷል፡፡ ይህ መልካም ነገር ነው፤ እግዚአብሔርንም የምናመሰግንበት አንድ ትልቅ ምክንያትም ነው፡፡ በመልካም ልቡና ስናስተውለው የእግዚአብሔርን ቸርነት እና ኃያልነት የምናስብበት ሥጦታ ነው! የፈጠረው ሰው ይህን ያህል ጥበብና ኃይል እንዲኖረው ያደረገ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

ነገር ግን ቴክኖሎጂ መልካም የሚሆነው ለመልካም ነገር ስንጠቀምበት ነው፡፡ ዕውቀቱንና ማስተዋሉ ሲሰጠን ለመልካም እንድንጠቀምበት ቢሆንም ለክፉም ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ ይህም ከነፃ ፈቃድ የተነሣ ነው፤ እግዚአብሔር ለሰው የሰጠው ዕውቀትን ብቻ ሳይሆን ወደ ፈለገው የሚሄድበትን ነጻ ፈቃድም ጭምር ነውና፤ ለመልካም ብንጠቀምበት እግዚአብሔርንም ሰውንም እናስደስታለን፤ ለበለጠ ሰማያዊ እና ዘለዓለማዊ ዕወቅትም የተገባን ሆነን እንገኛለን፡፡ ለኃጢአት ብንጠቀምበት ግን እንኳን የሠራነው ቴክኖሎጂ ቀርቶ የገዛ ሰውነቶቻችንም ይረክሳሉ፤ ከሰማያዊው ርስት ዕድል ፈንታ አይኖረንም፡፡ ስለዚህ ቴክኖሎጂ በመልካም ኅሊና ሊመራ ይገባዋል ማለት ነው፡፡

አሁን የምናየው የቴክኖሎጂ ዕድገት የሚመራው በምን ኅሊና ነው? ይህ በተለይ በክርስቲያኖች ዘንድ ሊስተዋል የሚገባው ጠቃሚ ጥያቄ ነው፡፡ ቴክኖሎጂን የሚመራው የሰው ኅሊና ለመልካምነቱ ወሳኝ ነው፤ ኅሊና ጤናማ ከሆነ ቴክኖሎጂም ጤናማ አገልግሎት ይሰጣል፤ ካልሆነ ግን ወደ ሞት ይዞን ሊወርድ ይችላል፡፡

ይህን የተክኖሎጂ ጤነኛነት ቢያንስ በሁለት መንገድ ልንመዝነው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ለስንፍና፣ ለኃጢአት፣ ለትዕቢት እና ለአምባገነንነት መሣሪያ ከሆነ ጤናማ አይደለም፡፡ ሰው ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ኃጢአት የሚሠራ እና ሌሎችን የሚበድል ከሆነ ለራሱ መጥፊያ እየተጠቀመበት ነው ማለት ነው፡፡ በቴክኖሎጂ ብዛት የማይዳንባት የእግዚአብሔር ፍርዱም የኋለ ኋላ ታጠፋዋለች፡፡

ሁለተኛው ችግር ደግሞ ቴክኖሎጂን ከመጠን በላይ ቦታ ሰጥቶ እንደ አምላክ ማየት ነው፡፡ የሕይወት መጨረሻ መንግሥተ ሰማዯትን ወርሶ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንጂ ቴክኖሎጂን እንደ ምኞት መዳረሻ ቆጥሮ በዚህ ምኞት ውስጥ ራስን አስክሮ መኖር አይደለም፡፡ “በሰለጠነው ዓለም” ሰዎች ለራሳቸው ለፈጠሯቸው ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ሥራዎች ለፈጣሪ የሚሰጠውን ዓይነት አክብሮትና ምስጋና ሲቸሯቸው እናስተውላለን፡፡ ቴክኖሎጂ ጣዖታችን ከሆነ መሞቻችን ሆኗል ማለት ነው፡፡

እኛ ክርስቲያኖች ግን ቴክኖሎጂን መጠቀም ያለብን የምኞታችን ሁሉ መዳረሻ አድርገን ሳይሆን በዚህ ምድር ለምንኖረው ኑሮ ለመልካም ሥራ መሣሪያ እንዲሆነን እንጂ በራሱ ግብ ስለሆነ አይደለም፡፡

ይህች ዓለም በቴክኖሎጂ ሳይሆን በእግዚአብሔር ኃይል እና መግቦት እንደምትኖር ያለ ግብዝነት ልናምን ይገባል፡፡ ቴክኖሎጂ ራሱ እግዚአብሔር ለሰው ከሰጠው ዕውቀት የተነሣ እንደሆነና በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለመልካም ነገር መሣሪያ የሚሆን የሰው ልጅ ሀብት እንደሆነ ሁል ጊዜ ማሰብ ማሰላሰል ይኖርብናል፡፡ ካልሆነ ግን መልካም ሥጦታነቱ ቀርቶ ለሰው ልጅ የከንቱነት ምክንያት እንዲሁም ለጥፋቱ መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል እናውቃለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም

መ/ር በትረ ማርያም

ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እውነተኛና ሐሰተኛ መረጃዎችን በጽሑፍ፣ በድምጽ፣ በምስል ወድምጽና በመሳሰሉት መንገዶች ለሕዝብ የሚሰራጭበት የመገናኛ ዘዴ ነው። ሆኖም አንድ ሰው ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሲጠቀም በሐሰቱ እንዳይጎዳ፣ በእውነቱ እንዲጠቀም እውነቱን ከሐሰት የሚለይበት ማንጸሪያ ወይም መመዘኛ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ የተጻፈ ወይም የተነገረና የታየ ሁሉ እውነት አይደለምና።

የሰው ልጅ ለተለያየ ዓላማ አንድን ሐሳብ በፈለገው መንገድ ሊገልጽ ይችላል፡፡ ነገር ግን የገለጸበት መንገድና ሁኔታ ምን ዓይነት መረጃ፣ ለማን፣ እንዴት፣ ወዘተ ለሚሉት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ምላሽ የሚሰጥ መሆን ይገባዋል፡፡ መረጃውም ሊጠቅምና ሊጎዳ እንደሚችል በቅድሚያ መረዳት ይገባል፡፡ እውነትን ቢናገር እንኳ የተናገረው ምን አስቦ ወይም ለምን ዓላማ እንደሆነ ስለማናውቅ የመታለል ዕድላችን ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚለቀቁ መረጃዎች ትክክለኛ ከሆኑ አዎንታዊ ተጽእኖ በሐሰት የተሞሉ ከሆኑ ደግሞ አሉታዊ ተጽእኖ በማኅበረሰቡ ላይ የማሳደር አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የተጻፉ ጽሑፎችን፣ የተለጠፉ የምስል ወድምጽ መልእክቶችን ስናይ ስለ ማንነታቸውና ስለ ውጤታቸው አዎንታዊነትና አሉታዊነት ለመረዳት መጠየቅ ያለብን ጥያቄዎች አሉ። ጥቂቶቹን ብንመለከት፡-

 . መልእክቱ ምንድን ነው?፡- በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን የተላለፈው ጉዳይ መልእክት ምንነት እና ፍሬ ነገር ምንድን ነው? የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል። ዝም ብለን የጉዳዩን ምንነት ሳንረዳ ሌሎች ስላራገቡት የምንቀበለው መሆን የለበትም። በተአምረ ኢየሱስ የተጻፈ አንድ ታሪክ አለ።

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አብነት ለመሆን ትምህርት ይማር ዘንድ ወደ መምህር ሄደ። (አስተውል ለመምህሩ ዕውቀትን የሰጠ ጌታ ለእኛ አብነት ለመሆን ሲል ሄደ እንጂ አዲስ ዕውቀት ለመገብየት አይደለም)። ከዚያ መምህሩ ፊደል ሊያስተምረው “አሌፍ” በል አለው። ጌታም “አሌፍ” አለ። ከአሌፍ ቀጥሎ ያለው ፊደል “ቤት” ነውና “ቤት” በል አለው።

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መጀመሪያ የአሌፍ ትርጉሙ ምንድን ነው? የዚህን ምሥጢር ንገረኝና ቀጣዩን እለዋለሁ ብሎታል። ስለዚህ እኛም ጉዳዩን በቅርበት በስሜት ሕዋሳቶቻችን ዳስሰን፣ ዐይተንና ቀምሰን ያላረጋገጥነውን ጉዳይ ወይም በሃይማኖት ትምህርት ያልተማርነውን ጉዳይ የሆነ አካል ጽፎት ብናገኝ ስለተጻፈው ጽሑፍ ምንነት የጻፈውን አካል ጠይቀን ወይም በሌላ መንገድ መረዳት ይጠበቅብናል፡፡ ይህም የመልእክቱን ምንነት መለየትና መገንዘብ ያስችለናል፡፡

. ማን ጻፈው?፡- ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ “ይደልዎ ለዘያነብብ ቅድመ ይዝክር ስሞ ለበዓለ መጽሐፍ ወእምዝ ያንብብ ወይምሀር፤ የተጻፈን ነገር ለሚያነብ ሰው የተጻፈውን ጉዳይ ከማንበቡ በፊት የጸሓፊውን ማንነት ይወቅ፣ ካወቀ በኋላ አንብቦ ያነበበውን ያስተምር” ይላል። የጸሓፊውን ማንነት ማወቅ የጽሑፉን ስሜት እንድንረዳው ይረዳናል። ከዚያም ጽሑፉን አንብቦ የተጻፈበትን ዐውድ ተረድቶ ምን ለማለት እንደፈለገ በቀላሉ መረዳት ያስችላል፡፡ ክርስቶስን ሐዋርያት ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ነበር። ነገር ግን የሚከተለው ሕዝብ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የነበረው አመለካከት የተለያየ ነበር። “መጥምቁ ዮሐንስ ነው የሚሉ አሉ፤ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ፡፡”(ማቴ.፲፮፥፲፬)፡፡ አስተውል የሚከተሉትን ሰው ማንነት አለማወቅ ከትልቅ ክሕደት ውስጥ ይከታል። ፈጣሪያቸውን እንደ ፍጡር አቅርበውት ነበር። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ ቢላቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ብሎ ቢመልስ “አንተ ብፁዕ ነህ” ተብሎ ክብር ተሰጥቶታል።

በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ባለቤታቸው የማይታወቁ ብዙ ጽሑፎች እና የድምጽ እንዲሁም የምስል ወድምጽ መረጃዎች ይለቀቃሉ። በዚህን ጊዜ በአእምሯችን የሚጭኗቸው መልእክቶች ይኖሯቸዋል። ስለዚህ መልእክቱ ከእውነተኛነቱ አልፎ ክርስቲያናዊ ወይም ኦርቶዶክሳዊ ነው ወይ? የሚለውን መመዘን ያስፈልጋል። ስለዚህ ማኅበራዊ መገኛ ብዙኃን ስንጠቀም መምረጥ አለብን ማለት ነው።

. የት ተጻፈ?፡- ድርጊቱ የተፈጸመው የት ነው? የሚለው መታወቅ አለበት። በውጭ ሀገር የተደረገውን ድርጊት በሀገራችን እንደተደረገ እያደረጉ እያቀረቡ ሰውን ስሜታዊ የሚያደርጉ፣ ዋሽተው የሚያስዋሹ ብዙ ሰዎች አሉ። ስለዚህ የሆነን ድርጊት ወይም ጉዳይ አምነን ከመቀበላችን በፊት በተለያየ መንገድ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ይገባል። ለማረጋገጥ በቂ ማስረጃ ካላገኘን ጉዳዩን ለሌሎች ከማካፈል መቆጠብ፣ እኛም ከመደናገጥና ከስሜታዊነት ርቀን በሰከነ መንገድ ልንጓዝ ያስፈልጋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ የሶስናን ታሪክ ሙሉውን ስናነብ የምናስተውለው አንድ ነገር አለ። ረበናት ከሶስና ጋር መተኛት ይፈልጋሉ። እርሷ ግን እምቢ ትላቸዋለች። በዚህ ምክንያት በሐሰት ይከሷታል። የሚመለከታቸው አካላትም ጉዳዩን ሳይመረምሩ ሶስናን ለመግደል ይዘጋጃሉ። ዳንኤል ግን ጉዳዩን እንመርምረው ብሎ የት አገኛችኋት ብሎ ሲጠይቃቸው ከተለያየ ቦታ ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ውሸታቸው ታውቋል። ስለዚህ እኛም በውሸት እንዳንታለል “የት?” ብለን መጠየቅ አለብን።

. መቼ ተጻፈ? የሰማነው ወይም ያየነው ነገር መቼ የተፈጸመ ነው? የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከዓመታት በፊት የተደረገውን ጉዳይ ዛሬ እንደተደረገ አድርገው ከዚህ ቀደም ያላየውን ሰው ያታልሉበታል። ከውጭ ሀገርም ይሁን በሀገር ውስጥ ከዓመታት በፊት የተቃጠለውን ቤት፣ የሞተውን ሰው ዛሬ የተደረገ አስመስለው ሰውን ከሰው ያጣሉበታል። ስለዚህ የምንሰማውን ነገር መቼ እንደተደረገ ማወቅ ያስፈልጋል። ጌታችን ሐዋርያትን በደብረ ዘይት ሰብስቦ ስለ ዳግም ምጽአት እና ምልክቶቹ ሲነግራቸው ይህ መቼ ይሆናል? ብለው ጠይቀውታል። (ማቴ. ፳፬፥፫) እኛም መረጃን ለማጣራት መቼ ብለን መጠየቅ አለብን። አለበለዚያ ግን ተሳስተን ልናሳስት የተሳሳተ መረጃ አጋርተን እኛንም ሌላውንም ልንጎዳበት እንችላለንና መጠንቀቅ አለብን።

. ስንት?፡- ብዙ ጊዜ አንዱ የሠራውን በደል ብዙ ሰው እንደሠራው አድርጎ ማቅረብ እና ብዙ ሰው የሠራውን አንድ ሰው ወይም ጥቂት ግለሰቦች እንደሠሩት አድርጎ መረጃ ሊለቀቅ ይችላል።

ለምሳሌ በአንዱ ሰው ወንጀል ያ ሰው የተወለደበትን ሰፈር ወይም ብሔር መስደብ ትልቅ ችግር ሊያስከትል የሚችል ነው። ተጠያቂም መሆን ካለበት ራሱ ተናጋሪው አካል ወይም ቡድን እንጂ በጅምላ የተወለዱበትን ቦታ መስደብ ትልቅ በደል ነው። ምናልባት ወንጀል ፈጻሚው ሰው በሥነ ምግባሩ ምክንያት ሕዝቡ የናቀው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንድን ጉዳይ ዝም ብለን ከመቀበላችን በፊት ስንት ሰው አደረገው? የሚለውን መረጃ ጠይቀን ማወቅ ይጠበቅብናል ማለት ነው። ስንት የቦታን ስፋት፣ የጊዜን መጠን፣ የሰውን ብዛት ሊያሳውቀን ይችላልና። ብዙዎች የሠሩትን ወንጀል አንድ ሰው እንደሠራው አድርጎ ማቅረብም ሊኖር ይችላል።

፮. እንዴት?፡- በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚለቀቁ  አንዳንድ መልእክቶች ደግሞ ከነባራዊው እና ከተፈጥሯዊው ጉዳይ ያፈነገጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ዝም ብለን የምንቀበላቸው አይደሉም። እኛ ከለመድነው እንዲሁም ከተማርነው እና ካየነው የተለየ ነገር ሲነገር እና ሲተላለፍ እንዴት? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።

፯. ለምን?፡- በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ብዙ መረጃዎች በተለያየ መንገድ ይለቀቃሉ። መልእክቶቹን የሚለቀው ሰው ግን ምክንያት አለው። እውነቱንም ይሁን ሐሰቱን መረጃው ለሚደርሳቸው አካላት ማሥረፅ የፈለገው ጉዳይ አለው። ስለዚህ አንድን መልእክት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጽፎ ስናገኘው ቀጥታ በእኛ አረዳድ ብቻ ሳይሆን በጸሓፊው አረዳድ ልንረዳው ይገባል። መልእክቱን ዐይተን ቀጥታ ማመን የለብንም። ለምን ብለን መጠየቅ አለብን። አንድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በተማሪዎች የሚነገር ቀልድ (ተረት) አለ። በአንድ ወቅት ምሽት ላይ አንድ የተማሪዎች ማደሪያ ክፍል መቃጠል ይጀምራል። ከዚያ ተኝተው የነበሩ ተማሪዎች ይነቁና ማደሪያ ክፍላቸው እየተቃጠለ መሆኑን ሲያውቁ ራሳቸውን ለማትረፍ ተደናግጠው ራቁታቸውን እየሮጡ ይወጣሉ፡፡ ከዚያ ቤተ መጻሕፍት ቆይቶ የመጣ ተማሪ ወደ ቤቱ ሲመለስ ብዙ ሰው ራቁቱን እየሮጠ ያያል። ይህን ጊዜ እርሱም ልብሱን አውልቆ ተከተላቸው ይባላል። አሁን ይህ ሰው ያለ ምክንያት የሚንቀሳቀስ ሰው ነው። እነርሱስ ከምንቃጠል ብለው ለማምለጥ በደመ ነፍስ ያደረጉት ነው። እርሱ ግን ዝም ብሎ እነርሱን ብቻ ዐይቶ ምክንያቱን ሳይረዳ አውልቆ ተከትሏቸዋል። እኛም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነ ታወቂ ሰው ወይም የማኅበራዊ አንቂ(Activist) ግለሰብ ስለጻፈው እሱን ተከትለን የምናስተጋባና ለሌሎች የምናጋራ መሆን የለብንም።

ግለሰቡ ለሆነ ዓላማ ውሸቱንም ይሁን እውነቱን መረጃውን ሲያዘጋጀው የሚያስከትለውን ችግር ተረድቶም ሆን ሳይረዳ ወይም ሆነ ብሎም ሲያደርገው ተከፍሎት ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ከየት ወደ የት፣ ከምን፣ በምን፣ እስከምን…. ወዘተ” እያልን ነገርን አጥርተን ለነፍሳችንም ለሥጋችንም የሚጠቅመንን መረጃ ልንይዝ ይገባናል።

ከላይ እንደተገለጸው መረጃ ስላገኘን ብቻ የሚያስከትለውን ችግር ሳንረዳ በማኅበራዊ ሚዲያ መልቀቅ በርካታ ችግሮችን በግለሰቦች፣ በቤተሰብ፣ በአካባቢና ብሎም በሀገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ከግንዛቤ በማስገባት መዝነን መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የምንጠቀምበት ሰዓትም ገደብ ሊኖረው ይገባል። ቀኑን ሙሉ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ ተጠምዶ መዋልና መከታተል ሱስ እንዳይሆንብንም መጠንቀቅ አለብን።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።

አስተርእዮ​ ​ማርያም

አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ ማለት ነው። ቃሉ አስተርአየ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት(የታየበት)፣ አንድነት ሦስትነቱም የተገለጠበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል። የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር “አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል።

ልቡናዋ በይኩነኒ የጸና ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡና አስተባብራ የያዘች ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ተንሥኢ ወንዒ፤  የነፍሴ ደስታ የኾንሽ ውድ እናቴ ሆይ ተነሥተሽ ወደ እኔ ነዪ” (መኃ ፪፥፲) ብሏታል።

ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ

ቅዱስ ዳዊት ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ማኅፀንሽን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የኖረብሽ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው የተደረገው ነገር ዕጹብ ድንቅ ነው እንዳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ሆና ማረፏ ይደንቃል። ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ገልጾታል።

ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ በነገረ ማርያም አበው እንደሚያስረዱት ዕረፍቷ በጥር ፳፩ እሑድ ነው። አባቶቻችን በጾመ ፍልሰታ ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያም ሲተረጉሙ የእረፍቷን ነገር እንዲህ ብለው ይተርካሉ።

የእረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉ ስድሣ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር ፳፩ በእሑድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት። ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን? አለችው። በሲዖል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል አላት። እሊህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው። ቅድስት ሥጋዋን ከቅዱስ ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጋት። ደቀ መዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ሥጋዋን በክብር አሳርፉ አላቸው። ሐዋርያት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴሰማኒ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ ቀድሞ ልጇን ተነሣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሣች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን በእሳት እናቃጥላታለን ብለው ተነሡ። ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው። መልአክ መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ። በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት እጁ ተመልሶለታል። ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ጨምሮ በደመና ነጥቆ ከገነት አግብቶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት።

ቅዱስ ዮሐንስን እንደምን ሆነች አሉት ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች አላቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ ሁለት ሱባዔ ሲፈጸምም እሑድ አምጥቶ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ በሶስተኛው ቀን ማክሰኞ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ተነሥታለች።” ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት፡፡ ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ዛሬም ደግሞ ያንችን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን ብሎ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ፤ ከሐዘኑ የተነሣ ሊወድቅ ወደደ” እመቤታችንም አይዞህ አትዘን እሊያ ትንሣኤዬን ዕርገቴን አላዩም አንተ አይተሃል ተነሣች ዐረገች ብለህ ንገራቸው ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው። ከዚህ በኋላ ሂዶ የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ አላቸው አግኝተን ቀበርናት አሉት ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተው ይህ ነገር አይመስለኝም አላቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ ልማድህ ነው አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራልህ ብሎ ተቆጥቶ ወደ መቃብሩ ሂዶ ቢከፍተው አጣት፤ ደንግጦ ቆመ ሐዋርያው ቶማስም አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችንስ ተነሣች ዐረገች አላቸው፤ የያዘውንም ሰበን ሰጣቸው፤ ለበረከትም ተካፍለውታል። በዓመቱ ሐዋርያት ቅዱስ ቶማስ ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ ብለው ጾም ጀመሩ በ፲፮ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር አድርጎ ቅዱስ ጴጥሮስን ካህን ዘይትራድኦ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ በዚያው ላይ ቀድሶ አቁርቧቸዋል። ቤተ ክርስቲያንም ይህንን መታሰቢያ አድርጋ በየዓመቱ ታከብረዋለች።

ሰአሊ ለነ ቅድስት

የኃጥአንን ለቅሶና ሐዘን አይተሽ ስለ እነርሱ ድኅነት(መዳን) ዕረፍትሽን በሀሴት የተቀበልሽ እመቤታችን ሆይ ሐዋርያት በሱባዔ ትንሣዔሽን ለማየት በቅተዋልና እኛም በዓለ ዕረፍትሽን አክብረን ልጅሽ በሰጠሽ ቃል ኪዳን በቀኙ እንቆም ዘንድ ለምኝልን። አሜን።

ምንጭ፡- በኢት/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጅ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ

በዓለ ጥምቀት

ጥምቀት አጥመቀ፤ አጠመቀ (ነከረ)፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውና የሌሎች ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መግቢ በር ነው፡፡ በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡ መቶ ሃምሳው አባቶች “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት፤ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት እንደመሰከሩት፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት በዓልን ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት  ቀጥላ ከቅጽረ  ቤተ ክርስቲያን ወጥታ  በዱር፣ በሜዳ፣  በወንዝ፣ በባሕር  ዳርቻ  ጥር ፲፩  ቀን  በየዓመቱ  በታላቅ ድምቀት የምታከብረው በዓል ነው፡፡

ጥምቀት ሰው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቆ የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆንበት ታላቅ ምሥጢር ነው (ማቴ፣ ፳፰፥፲፰)፡፡ ይህ ምሥጢር ከምሥጢራት ሁሉ የመጀመሪያ ነው። ምሥጢር መባሉም በዓይን በሚታይና በጆሮ በሚሰማ አገልግሎት በዓይነ ሥጋ የማይታይና በዕዝነ ሥጋ የማይሰማ ጸጋ ስለሚገኝበት ነው። አገልግሎቱ ሲፈጸም ይታያል፣ ይሰማል፤ ተጠማቂው ከውኃና ከመንፈስ ተወልዶ የልጅነት ጸጋ ሲያገኝ ግን አይታይም፣ አይሰማም። ይህ ምሥጢር የሌሎች ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር ነው። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን በወንጌል “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ብሏል (ዮሐ. ፫፥፯)፡፡ ይህንን ነው ጌታችን ዳግም ልደት ያለው (ዮሐ. ፫፥፫)፡፡ የመጀመሪያው ልደት ከአባት አብራክና፣ ከእናት ማኅፀን በሥጋ መወለድ ሲሆን ሁለተኛው ልደት ግን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ረቂቅ በሆነ ልደት በመንፈስ መወለድ ነው። ይህንንም ጌታችን “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው” ብሎታል (ዮሐ. ፫፥፮)፡፡

ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ነው። በጥምቀት በዓል የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ ነው። በዮርዳኖስ የተጠመቀውም ስለ ሁለት ነገር ነው፦

፩ኛ• ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ባሕር አየች ሸሸችም፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ” ብሎ የተናገረውን ትንቢት በእርሱ ጥምቀት ለመፈጸም( መዝ፣፻፲፫፥፫)፡፡

፪ኛ• በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤያችንን እንደ ሰውነቱ ረግጦ፤ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ ሊደመስስልን።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በሠላሳ ዓመቱ ለድኅነተ ዓለም፣ አንድም ለአብነት በፈለገ ዮርዳኖስ በዮሐንስ ወልደ ዘካርያስ ተጠምቋል። በተጠመቀ ጊዜም የባሕርይ አባቱ አብ በደመና ሆኖ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ መስክሯል፤ መንፈስ ቅዱስም በፀአዳ ርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀምጧል። (ማቴ. ፫፥ ፲፫–፲፯)፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ መጠመቁን ምክንያት በማድረግ ለዚህ ቅዱስ ዕለት በዓል ሠርታ ታከብረዋለች፡፡ በየዓመቱም ታቦታቱ በዋዜማው ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወጥተው በአደባባይ በሊቃውንቱ እና በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም በምእመናን በዝማሬ ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባሕር በመውረድ በወንዝ ዳር ወይም  በሰው ሠራሽ የውሃ ግድብ አጠገብ በዳስ ወይም በድንኳን ያድራሉ። ሌሊቱንም በማኅሌትና በቅዳሴ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ሥርዓተ ቅዳሴው ይፈጸማል። ሲነጋም በወንዙ ዳር ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ አራቱም ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል።

ጥምቀት ረቡዕ ቢውል ገሀድ ማክሰኞ፤ አርብ ቢውል ገሀድ ሐሙስ ለውጥ ሁኖ ይጦማል። ጥምቀት የሚውልባቸው አርብና ረቡዕ ስለ በዓሉ ታላቅነት ፍስክ ይሆናሉ። ጥምቀት በፍስክ ቀናት ቢውልም በዋዜማው ይጾማል።

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን ራሱ ከፈጸመ በኋላ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ በማለት ጥምቀተ ክርስትናን እንደመሠረተ፣ ሰው ዳግመኛ ከውኃና፣ ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ እንደማይችል ያመልክተናል።

በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት መሠረት ሁለተኛ መወለድ ማለት እንደገና ወደ እናት ማሕፀን ተመልሶ በሥጋዊና በደማዊ ፈቃድ መወለድ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ረቂቅ ልደት /የነፍስን ልደት/ መወለድ ማለት ነው፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር የመወለድ ጸጋ የሚገኘው በጥምቀትመሆኑን ያሳየናል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን መሠረት አድርጋ ከማይጠፋ ዘር የምንወለደውን ልደት ወንድ ልጅ በተወለደ በ፵ ቀኑ ሴት ልጅ በተወለደች በ፹ ቀኗ ታጠምቃለች፡፡እንዲሁም ዘግይው የመጡትን ግን እንደ አመጣጣቸው አንድነቱን ሦስትነቱን፣ አምላክ ሰው፤ ሰው አምላክ መሆኑ ተምረው ካመኑ በኋላ ታጠምቃቸዋለች። (ማር. ፲፮፥፲፮)፡፡

ይህ ከእግዚአብሔርየመወለድ ጸጋ የተገኘውም በሃይማኖት ነው። ክርስቶስን አምላክ ወልደ አምላክ ነው ብሎ በሃይማኖት ያልተቀበለ ከእግዚአብሔር መወለድ አይችልም። ለአመነና በሃይማኖት ለተቀበለ ብቻ የሚሰጥ ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስ ይህንን ታላቅ የመዳን ምሥጢር እና ከእግዚአብሔር ልጅነትን የማግኘት ሥልጣን ሲያስረዳ “በስሙ ያመኑ የእግዚአብሔር ልጆች ይባሉ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” (ዮሐ. ፩፥፲፩–፲፫) በማለት አምልቶና አስፍቶ ጽፎልናል።

ስለዚህ ጥምቀት ምሥጢር የተባለበት ምክንያት፡– 

  • ላመኑ እንጂ ላላመኑ አይሰጥምና በዐይን የሚታየው በእጅ የሚዳሰሰው ግዙፍ ነገር በመንፈስ ቅዱስ ሲለወጥ አይታይምና፣
  • ምእመናንም በጥምቀት በሚታየው የማይታየውን ጸጋ ሲቀበሉ አይታይም፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግ ጠባዕያዊያን በመፈጽም፣ ለእናቱ እየታዘዘ አድጎ ፴ ዓመት ሲሆነው  በዘመነ ሉቃስ ጥር ፲፩ ቀን  ማክሰኞ ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት በባሕረ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል፡፡ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል”  በማለት ሰው ሁሉ ይድን ዘንድ ተጠምቆ ተጠመቁ ሲለን አርአያ ይሆነን ዘንድ ተጠመቀ፡፡ (ማር ፲፮፥፲፮)፡፡

ጌታችን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሲሱስ ክርስቶስ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ወርዶ እንደሚጠመቅ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በትንቢት መነጽርነት ዐይቶ በመዝሙሩ እንዲህ ሲል ተናግሯል “ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ ወአድባር  አንፈርዐጹ ከመ ሐረጊት ወአውግርኒ  ከመ መሓስአ አባግዕ ምንተ ኮንኪ ባሕር ዘጎየይኪ ወአንተኒ ዮርዳኖስ ዘገባእከ፤ ባሕር አየች ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ ተራሮች እንደ ኮርማዎች ኮረብታዎችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ፡፡ አንቺ ባሕር የሸሸሽ አንቺ፣ ዮርዳኖስ ወደ ኋላ የተመለስሽ ምን ሆናችኋል? እናንተ ኮረብቶችስ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ”  (መዝ. ፻፲፫፥፫-፮)፡፡

ጌታችን ወደ ዮሐንስ ሄዶ የተጠመቀበት ምክንያት፡-

፩. ትሕትናን ሲያስተምር ነው፡- ምነው ጌታ ፈጣሪ፤ እግዚእ ሲሆን ወደ ዮሐንስ ሄደ ቢሉ ሥጋ መልበሱ ለትሕትና ነውና፡፡ ይህ ባይሆን ዛሬ ነገሥታት ቀሳውስትን ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን አቁርቡን ይሉ ነበርና፡፡

፪. ትንቢቱና ምሳሌውን ለመፈጸም (ሕዝ. ፴፮፥፳፤ መዝ.፻፲፫፥፫-፮)

ጌታችን መድኃኒታችን መጠመቅ ለምን  አስፈለገው?

፩. ጥምቀት ለሚያስፈልገን ለእኛ አርአያ ለመሆን ነው፡- እርሱ ተጠምቆ ተጠመቁ ባይለን ኑሮ ጥምቀት አያስፈልግም፡፡ አስፈላጊ ቢሆንማ ጌታ ራሱ ተጠምቆ አብነት በሆነን ነበር እንዳይሉ መናፍቃን ምክንያት አሳጣቸው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዩሐንስም ”ወአርኃወ ለነ አንቀጸ ጥምቀት ከመ ንጠመቅ፤ እንጠመቅ ዘንድ የጥምቀትን በር ከፈተልን” ሲል የጥምቀትን ምስጢር ያስረዳናል፡፡

፪. ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ፡- “አቤቱ ውኃዎች አዩህ ውኃዎች አይተውህ ፈሩ ጥልቆችም ተነዋወጡ  ወኃዎችም ጮሁ  ደመኖችም ድምጽን ሰጡ  ፍላጾችም ወጡ” (መዝ.፸፯፥፲፮-፲፯) የሚል ትንቢት ነበርና ይህ እንዲፈጸም፡፡

፫. በዮርዳኖስ ውስጥ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ( ሰኞ ውዳሴ ማርያም)

፬. አንድነትና ሦስትነቱን ለማስረዳት፡- ከዚህ በፊት የሥላሴ ሦስትነት በግልጽ አይታወቅም ነበር፡፡ ጌታ በዮርዳኖስ በሚጠመቅበት ጊዜ ግን ምሥጢረ ሥላሴ ግልጽ ሁኖ አብ በደመና ሁኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀምጦ ሲታይ ወልድ በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ ተገለጠ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

በዓለ ግዝረት

ግዝረት ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ንዑሳን በዓላት የሚባሉትም ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ፣ ግዝረት፣ ቃና ዘገሊላ፣ ልደተ ስምዖን፣ ደብረ ዘይት፣ የመጋቢት ፲ መስቀልና የመስከረም ፲፯ መስቀል ናቸው፡፡

ፍቅር ወልድን ከዙፋኑ ስቦት ወርዶ ሥጋ ማርያምን ተዋሕዶ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ማሕፀኗን ዓለም አድርጎ ከቆየ በኋላ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ በዘመነ ማቴዎስ ተወለደ፡፡ በተወለደ በስምንተኛ ቀኑ ሥርዓተ ኦሪትን ሊፈጽም ተገረዘ፡፡ ግዝረትን በስምንተኛው ቀን መፈጸሙ፣ በተወለደ በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ መሔዱ ሕገ ኦሪትን ሊያጸና፣ ሊፈጽም፣ ምሳሌውን በአማናዊው ሊተካ እንጂ ኦሪትን ሊሽር ላለመምጣቱ እማኝ ምስክር ነው፡፡

ክርስቶስ ዘር ምክንያት ሳይሆነው እንደተፀነሰ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለውጥ እንደተወለደ እንደ ነቢዩ ሕዝቅኤል “ሳይከፈት ገብቶ ሳይከፍት እንደወጣ” ስለት ምክንያት ሳይሆነው፣ በግዝረት ምክንያት ደም ሳይፈስ በተአምራት ተገረዘ፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ በስምንተኛው ቀን እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ግዝረት ይፈጸምለት ዘንድ ሕፃኑ ጌታችንን ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ሲገረዝ የሊቀ ካህን ልጅ ነው ብለው ሊገርዙት ወደ እርሱ መጡ፡፡ ጌታችን ግን ወደ ምድር የመጣው ለትሕትና ነው እንጂ ለልዕልና አይደለምና ወሰዱት አለ /ትርጓሜ ወንጌለ ሉቃስ/፡፡ ስሙም ገና በሥጋ ሳይፀነስ የእግዚአብሔር መልአክ ባወጣለት ስም “ኢየሱስ” ተብሎ ተጠራ /ሉቃ. ፪፥፳፩-፳፬/፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ጌታ ክርስቶስ በሥጋው ግዝረትን ተቀበለ፡፡ ለአባቶች የተሰጠውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ” በማለት እንደ ተናገረው /ሮሜ. ፲፭፥፰/፣ የክብር ባለቤት መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ ግዝረት በመግባት የኦሪትን ሕግ ፈጽሟል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም አረጋዊው ዮሴፍን “እንደ ሕጉ ልጄን እንዲገርዘውና ስሙንም እንድንሰይመው ብልህ የኾነ ገራዥ ሰው አምጣልኝ” አለችው፡፡ ጻድቁ ዮሴፍም እንዳዘዘችው የሚገርዝ ባለሙያ ይዞ መጣ፡፡ ባለሙያውም በእናቱ በንጽሕት ድንግል ማርያም ክንድ ላይ ሕፃኑ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ባየው ጊዜ እንድገርዘው በጥንቃቄ ያዙት” አላቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስም “ባለሙያ ገራዥ ሆይ! ደሜ ሳይፈስ ልትገርዘኝ ትችላለህን? በዕለተ ዓርብ በመስቀል ስሰቀል ካልኾነ በስተቀር ደሜ አይፈስምና፡፡ ጐኔን በጦር ሲወጉኝ ያን ጊዜ ውኀና ደም ይፈሳል፡፡ ይኸውም ለአዳምና ለሚያምኑ ልጆቹ መድኀኒት ይኾናል” አለው፡፡

የክብር ባለቤት ጌታችን የተናገረውን ይህን ቃል ባለሙያው በሰማ ጊዜም አደነቀ፡፡ ዕቃውንም ሰብስቦ ተነሣና ከጌታችን እግር በታች ወድቆ ሰገደ፡፡ ያንጊዜም ምላጮቹ በእጁ ላይ እንዳሉ እንደ ውኀ ቀለጡ፡፡ ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንም “ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፡፡ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ ይህ ልጅሽ ስለ እርሱ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት የሕያው አምላክ ልጅ ነው” አላት፡፡

ጌታችንም ባለሙያውን “እኔ ነኝ! ትገዝረኛለህን ወይስ ተውክ? ወይስ የአባቶቼ አባቶች እንዳደረጉ ላድርግ?” አለው፡፡ ባለሙያውም መልሶ”የአባቶችህ አባቶች እነማን ናቸው?”ሲል ጠየቀው፡፡ ጌታችንም አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ የሕዝቡ ሁሉ አባት እንደ ሆኑ ካስገነዘበው በኋላ “ለእነርሱም ይህ ግዝረት አስቀድሞ ከአባቴ ዘንድ ተሰጣቸው” በማለት የግዝረትን ሕግ አስረዳው፡፡ ባለሙያውም ይህን ምሥጢር ሲሰማ እኔ ከአንተ ጋር እነጋገር ዘንድ አልችልም፡፡ በአንተ ህልውና መንፈስ ቅዱስ አለና” ብሎ የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት መሰከረ፡፡

በዚህ ጊዜ ጌታችን ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ “አባት ሆይ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ አስቀድሞ ግዝረትን የሰጠሃቸው፤ ያቺን ግዝረት ዛሬ ለእኔ ስጠኝ” አለ፡፡ ያንጊዜም ያለ ሰው እጅ በጌታችን ላይ ግዝረት ተገለጠ (የግዝረት ምልክት ታየ)፡፡ ከዚህ ላይ ጌታችን ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር አብ ልመና ማድረሱ የለበሰው ሥጋ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ መሆኑንና ጸሎት ማቅረብ የሚስማማው ሥጋን መልበሱን ለማጠየቅ ነው እንጂ በእርሱና በአብ መካከል ልዩነት ኖሮ አይደለም፡፡

ጌታችን ድንግልናዋን ሳያጠፋ ከድንግል ማኅፀን እንደ መውጣቱ ግዝረቱም አይመረመርም፡፡ በተዘጋ ቤት ወደ ሐዋርያት እንደ ገባና እንደ ወጣ ሁሉ እርሱ በሚያውቀው ረቂቅ ጥበብ ከሥጋው ምንም ምን ሳይቈረጥ፣ ምንም ደም ሳይፈሰው መገረዙ ተገለጠ፡፡

ገራዡም የጌታችንን ቃል ከመስማቱ ባሻገር በሥጋው ላይ የተደረገውን ተአምር ባየ ጊዜ እጅግ አደነቀ፡፡ ከክብር ባለቤት ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር በታች ወድቆም ሦስት ጊዜ ሰገደና “በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የእስራኤልም ንጉሥ ነህ!” በማለት በክርስቶስ አምላክነት አመነ፡፡ ከዚህ በኋላ ያየውንና የሰማውን ሁሉ እየመሰከረ ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- ቅዱስ ወንጌል

        ስንክሳር ጥር ፮