“የሕይወት ቀን” በግቢ ጉባኤያት

ወርቃማው የወጣትነት ዘመናችን በተስፋ፣ በመልካም ምኞትና በትጋት የተሞላ፣ ዕውቀትንና አቅምን ያማከለ ማንነታችን የሚታነጽበት፣ መንፈሳዊነታችን የሚገለጽበት የዕድሜ ክልል እንደመሆኑ የሕይወታችን መሠረት ነው፡፡ መንፈሳዊ ፍሬን አፍርተን ርስተ መንግሥተ ሰማያት ለምንወርስብትም የሕይወት ስንቅ የምንሰንቅበት የተጋድሎ ዘመን ስለመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከልጅነታችን ጀምሮ አበክራ ታስተምረናለች፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤቶቿም ኮትኩታ አሳድጋ መንፈሳዊ ፍሬ ለማፍራት ታበቃናለች፡፡ ለዚህ የመሸጋገሪያ ዕድሜ በደረስንበት ጊዜም የሕይወታችን መርሕ የሆነው ትምህርተ ወንጌል እንዳይጓደልብን በዐውደ ምሕረቷ ላይ ጉባኤ ዘርግታ ሰማያዊ ኅብስትን አዘጋጅታ ትመግበናለች፡፡

በጉባኤያት የሚሰበኩ ትምህርቶች ለክርስቲያናዊ ሕይወት እንድንበቃ የሚረዱንና ለዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያበቁን ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የምትመግበን ምግበ ሕይወት ግን በዚህ ብቻ አይወሰንም፡፡ ዘወትር መንፈሳዊ ዝለት አጋጥሞን ከቤቷ እንዳንርቅና በዓለም እንዳንጠፋ ዓለም ባፈራቻቸው የመገናኛ ብዙኀን በየቤታችን፣ በትምህርት ቤታችንና በየአካባቢያችን የሕይወትን ምግብ እየመገበች ታኖረናለች፡፡ ቅዱስ ቃሉን ሰምትንም ለሥጋ ወደሙ እንድንበቃ ምሥጢራቷን ታካፍለናለች፡፡

ለዚህም ተልእኮ ተደራሽነት በሀገራችን የመንፈሳዊ አገልግሎት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤ አገልግሎቱ ውስጥ ለኦርቶዶክሳዊያን ወጣት ተማሪዎች ከሚሰጠው ሥርዓተ ትምህርት በተጨማሪ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ይካፈሉ ዘንድ ዘወትር እሑድ የሚቀርበው “የሕይወት ቀን” ተጠቃሽ ነው፡፡ በዓመት በሁለቱ የአጽዋማት ወቅት በነቢያትና በዐቢይ ጾም የሚካሄደው ይህ አገልግሎት በአብዛኛው የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች የሚሳተፉበት ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከማስተማር ባሻገር በንጽሕና ሕይወት ኖረው ለቅዱስ ቁርባን እንዲበቁ ለማድረግ ባለው ቁርጠኛ ሐሳብ  በጀመረው በዚህ መርሐ ግብር በተለይም በአዳማ፣ በሐሮማያ፣ በጎንደር እና በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን የንስሓ አባት ከማስያዝ ጀምሮ ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ይረዳቸዋል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” በማለት እንደተናገረው እኛ ክርስቲያኖች በንስሓ ሕይወት ተመላልሰን ለሥጋ ወደሙ እንድንበቃ የአምላካችን ቅዱስ ቃል ይገልጻልና የተማርነው ትምህርትም ይሁን የምንኖረው ክርስቲያናዊ ሕይወት ፍጻሜው ቅዱስ ቁርባን በመሆኑ ተማሪዎቹ ይህንን ተረድተው እንዲተገብሩት ማኅበራቸው ማኅበረ ቅዱሳን እገዛ ያደርግላቸዋል፡፡ (ዮሐ. ፮፥፶፫)

ይህን ተልእኮ ለመፈጸም በግቢ ጉባኤያት ለአገልግሎት የተመደቡ መምህራንና ሰባኬ ወንጌላውያን ተማሪዎቹን ለቅዱስ ቁርባን ዝግጁ እንዲሆኑ የእግዚአብሔርን ቃል ከማስተማር ባሻገር አስቀድመው በንስሓ አባቶቻቸው አማካይነት ንስሓን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ከዚህም ቀጥሎ ለአንድ ሳምንት ያህል ሥርዓተ ንስሓን የሚፈጽሙበት “የንስሓ ሳምንት መርሐ ግብር” ይከናወናል፡፡ ተማሪዎች አስፈላጊውን ሥርዓት ተከትለውና በምክረ ካህን ታግዘውም ቅድመ ዝግጅታቸውን ሲያጠናቀቁ ሥራ አስፋጻሚ ቢሮው ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ ጋር በመነጋገር በተለይም በዐበይት የአጽዋማት ወቅቶች ማለትም በዐቢይ ጾመና በጾመ ነቢያት ሥጋ ወደሙ ከሚቀበሉበት ዕለተ እሑድ ዋዜማ የአዳር መርሐ ግብር በማዘጋጀት ትምህርተ ወንጌልና ውይይት ያደርጋል፡፡

በመቀጠልም በቤተ ክርስቲያናቱ ተገኝተው ሥርዓተ ቁርባን እንዲካፈሉ ካደረገ በኋላ ከመምህራኑ ጋር በመተባበር ማኅበሩ የአጋፔ መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ያቀርብላቸዋል፡፡ የአጋፔ መርሐ ግብሩንም ተከትሎ የተለያዩ መርሐ ግብራትን በማዘጋጀት የሕይወት ምግብን እንዲመገቡ ያደርጋል፡፡ ቀሪው ዘመናቸውን በሃይማኖት ጸንተው አንዲኖሩና እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ለቅዱስ ቁርባን የበቁ እንዲሆኑ ለመርዳት የድኅረ ጉባኤያት መርሐ ግብር አዘጋጅቶም የማያቋርጥ እገዛ ያደርግላቸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት ያስመረቃቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የቀና መንፈሳዊ ሕይወትም ጉዳዬ ብሎ የያዘው ተልእኮው በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን በየጊዜው ይህን ሥራውን ለማከናወን የሚረዱ መርሐ ግብራትን ያዘጋጃል፡፡ በተለይም ተልእኮውን ተደራሽ ለማድረግ የሚረዱ የዐቅም ማጎልበቻ ሥራዎችና ለአገልግሎቱ ስኬት እክል የሚሆኑ ችግሮችን የመፍታት ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ማኀበሩ ለዚህ እንደ መነሻ ያደረገው በ፳፻፲፫ የተጠናው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች እጥረት፣ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የመማርያ ግብአቶች አለመሟላት እንዲሁም ሌሎች ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች በመሆናቸው ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያግዙትን ተግባራት በመለየት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ስለሆነም ይህን ተግዳሮት ለማከናወን ማኅበሩ የበጎ አድራጊ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች እገዛ እንደሚያስፈልጉት በማመን በዚህ በያዝነው የግንቦት ወር ባወጣው ዕቅድ መሠረት የ፳፻፲፭ ዓ.ም የግንቦት ልደታ ለማርያምንበዓል “ግንቦት ልደታን ለግቢ ጉባኤ” በሚል ርእስ መርሐ ግብር አዘጋጅቷል፡፡ በዋናው ማእከል ደረጃ ከሚያዝያ ፳፰/ ፳፻፲፭ ዓ.ም እስከ ግንቦት ፮ /፳፻፲፭ ዓ.ም ድረስ ይህ መርሐ ግብር ይከናወናል፡፡ በዋነኛነትም የማኅበሩን የ፴፩ ዓመት አገልግሎት የግቢ ጉባኤ ፍሬዎችን አስተዋጽዖ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለምእመናን፣ ለተማሪ ወላጆች፣ ለሀገር እና ለዓለም በማስተዋወቅ ነው፡፡

የማኅበረ ቅዱሳንን የግቢ ጉባኤያት መርሐ ግብርን መደገፍ የተማሪዎችን መንፈሳዊ ሕይወት መርዳት ብቻ ሳይሆን ጠቀሜታው ለሀገር፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለሁላችንም ጭምር በመሆኑ ተገቢውን እገዛ የማድረግ ኃላፊነት አለብን፡፡ ለዚህም የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ እንዲሆንልን በጸሎት ማሳሰብም ተገቢ ነው፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

“በማርያም ልደት ዛሬ ደስታ ሆነ” (ቅዱስ ያሬድ)

በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግንቦት አንድ ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት የሚከበርበት ዕለት ነው፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት እግዚአብሔር አስቀድሞ በትንቢት፣ በምሳሌና በራዕይ የሰውን ልጅ ድኅነት በጉጉት ሲጠባበቁ ለነበሩ ነቢያት ገልጿል፡፡ በልዩ ልዩ ምሳሌዎችም መስለው ከፊታቸው ያለውን ዘመን አሻግረው በመመልከት ተናግረዋል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ይወጣል፡፡” ብሎ ትንቢት የተናገረላት፤ ልበ አምላክ ዳዊት “የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ፤ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ “ፀሐይን የተጎናጸፈች፣ ጨረቃን የተጫማች፣ አሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል በራሷ ላይ ያላት” በማለት ተባብረው የመሰከሩላት ቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደችባት ቀን ናት፡፡ (ኢሳ. ፲፩፥፩ ፤ መዝ. ፵፬፥፱፤ ራዕ. ፲፪፥፩)

ነቢየ እግዚአብሔር ሰሎሞን በመኃልየ መኃልየ ድርሰቱም “ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ፤ ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ” እያለ ተናግሮላታል፡፡ ይህም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት በሊባኖስ ሀገር ስለመሆኑ ያመለክታል፡፡ (መኃ. ፬፥፰) በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት መሠረት የእመቤታችን የትውልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለው ተራራማ ሀገር ነው፡፡

የእመቤታችንን የዘር ሐረግ ወደ ኋላ ሰባት ትውልድ ስንቆጥር ቴክታና ጴጥርቃ የተባሉ ባልና ሚስት ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስትወጣ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስትደርስ፤ ስድስተኛዪቱ ጨረቃን ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ በሕልም በማየታቸው በሀገራቸው ለሚገኝ መፈክረ ሕልም (ሕልም ፈች ሊቅ) ሄደው ነገሩት፡፡ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም” አላቸው፡፡ እነርሱም ጊዜ ይተርጉመው ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ልጅ ወለዱ፡፡ ስሟንም “የተሳልኩትን አገኘሁ፤ የተመኘሁትን አገኘሁ” ሲሉ “ሄኤሜን” አሏት፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ለአካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡

ኢያቄምና ሐና መካን ስለነበሩ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ጸልየው፤ ሲሰጣቸውም መልሰው ለእርሱ እንደሚሰጡ ስዕለትን ተስለው ነበር፡፡ ጸሎታቸው ሲደርስ ለሐና በሕልም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጸላት፡፡ ፀዓዳ ርግብ ሰባቱ ሰማያትን ሰንጥቃ መጥታ በራሷ ላይ ተቀምጣ በጆሮዋም ገብታ በማሕፀኗ ስትተኛ አየች፡፡ ኢያቄምም በተመሳሳይ ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ዖፍ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ ሁለቱም በሕልም ያዩትን በመግለጥ ተነጋገሩ፡፡

ሐናም ፀነሰች፤ ሐና መጽነሷ በታወቀ ጊዜም የአርሳባንን ልጅ ዓይን በማብራቷና ሳሚናስ የሚባለውን የጦሊቅን ልጅ ከሞት በማስነሣቷ አይሁድ በቅናት ተነሳስተውባቸው ሊገድሏቸው እንደሚሹ ለሐናና ኢያቄም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ ስለነገራቸው ወደ ሊባኖስ ተራራ እንደሄዱ እና በጨረቃ የተመሰለች ድንግል ማርያም በሊባኖስ ተራራ እንደ ተወለደች የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን፤ ፀዓዳ (ነጭ) መሆኗ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፡፡ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መሆኗን ሲያጠይቅ ነው፡፡

በሐዲስ ኪዳን ሊቃውንትም ትንቢተ ነቢያትንና ወንጌልን በማጣጣም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት አመስጥረው አስተምረዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ጥቂቶቹን ብንመለከት፡-  ቅዱስ ያሬድ “ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች” ሲል ተናግሯል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደፈረሰው ዓለም በንጽሕና፣ በቅድስናና በድንግልና ስታበራ መኖሯንና ኋላም የዓለም ብርሃን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መውለዷን አመስጥሮ ተናግሯል፡፡

አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ” በማለት የድንግል ማርያምን በንጽሕና፣ በቅድስና መወለድ ተናግሯል፡፡

ሐና እና ኢያቄም ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደው በአድባረ ሊባኖስ ሥር እመቤታችንን ወለዱ፡፡ በወቅቱ ከቤት የወጡት ለሽሽት ነበርና ስንቅ ስላልያዙ ምግባቸው ንፍሮና ጥራጥሬ ነበር፡፡ ይህንን ትውፊት በመያዝ ምእመናን ንፍሮ አዘጋጅተው በዝማሬና በእልልታ እንደሚያከብሩት ሁሉ አንዳንዶች ባልተገባና ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ባፈነገጠ ሁኔታ ሲያከብሩትም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ አካሄድ ፍጹም ተገቢ ባለመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡

በእውነት የእርሷ ልደት የልዑል እግዚአብሔር ማደሪያው መቅደስ የተሠራባት፣ የነቢያት ትንቢት የተፈፀመባት፣ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰው ልጆች ሁሉ (ለሕያዋን ሁሉ) ታላቅ የደስታ ቀን በመሆኑ ሁላችንም “ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ እነሆ ዛሬ በእመቤታችን ልደት ደስታ ሆነ” እያልን በዝማሬ እናመስግናት።

የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን እና ግቢ ጉባኤያት

ክፍል ሁለት

ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ በይፋ ዕውቅና ተሰጥቶት በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆኖ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ መሠረት አድርጎ የአገልግሎቱን ትኩረት  በዋናነት ግቢ ጉባኤያት ላይ አደረገ፡፡ በዚህም መሠረት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን ከመደበኛው ትምህርታቸው ውጪ በየአጥቢያቸው የሚገኙ  የስብከተ ወንጌል አዳራሾችን በመጠቀም፣ አዳራሽ የሌላቸም በዛፍ ሥር እየተሰባሰቡ መምህራንን በመመደብ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከሰ/ት/ቤቶች ጋር በመቀናጀት ማስተማሩን ቀጠለ፡፡

ከ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ጀምሮም ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ፳፪ የትምህርት ዓይነቶችን በመለየት ለእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነትም መጻሕፍትን በማዘጋጀት ተማሪዎች ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸውን፣ አስተምህሮዋን እና አገልግሎቷን እንዲረዱ፣ ከተለያዩ ያልተገቡ ጠባያት ምግባራት ርቀው እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲሆኑና በመደበኛ ትምህርታቸውም ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ ከፍተኛ ጥረት ተደረገ፡፡

በየጊዜውም የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችን፣ የተማሪዎችን አቀባበል እና አፈጻጸማቸውን በመገምገም በድጋሚ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት እንዲዘጋጅ በማስፈለጉ በ፳፻፬ ዓ.ም የትምህርት ዓይነቶቹን በመከለስ ወደ ፲፩ ዝቅ እንዲሉ ተደርገዋል፡፡ መምህራንን በየማእከላቱ በመደበኛነት እና በበጎ ፈቃደኝነት እንዲያስተምሩ፤ ከዚያም አልፎ ከተማሪዎች ውስጥ የተተኪ መምህራን እና የአመራር ሥልጠና ወስደው በየግቢያቸው በመመደብ፣ አፈጻጸሙንም በመከታተል ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በዚህም ተማሪዎች ተመርቀው ሲወጡ በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ በመፍጠር የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አደራ ተቀብለው እንዲወጡ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የአንገት ማተብና መስቀል ይደረግላቸዋል፡፡

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ውጤት የሚመረቁ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችም “ለውጤታማነታችን ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ማኅበረ ቅዱሳን ነው” በማለት የተሸለሙትን  ሜዳልያ እና ዋንጫቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም የተሸለሙትን ሜዳልያ ለማኅበረ ቅዱሳን በመስጠት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሒኪም የሆኑት ፕሮፌሰር እንግዳ አበበ ይጠቀሳሉ፡፡ ወደ ሥራ ሲሠማሩም ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ መልሰው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፣ በሚሠማሩበት የሥራ መስክም በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግሉ አስችሏቸዋል፡፡ በቅድስት ቤተ ክርሰቲያን መዋቅር ውስጥ በመግባትም በሰ/ት/ቤቶች እና በሰበካ ጉባኤያት እንዲሁም በአብነት ትምህርት ገፍተው ዲቁና ተቀብለው የሚወጡትም በቤተ ክርስቲያን በውስጥ አገልግሎት እንዲሳተፉ ማድረግ ተችሏል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከተከታታይ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በተጨማሪ በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ አማካይነት “ጉባኤ ቃና” የተሰኘ ተማሪ ተኮር መረጃዎችን የያዘ መጽሔት ከ፳፻ ዓ.ም ጀምሮ በማሳተምና መልሶ ለተማሪዎች በማሠራጨት፣ በምረቃ መጽሔት፣ በድረ ገጽ፣ በፌስቡክ፣ በቴሌግራም ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው እንዲረዱ እገዛ ሲደረግላቸው ቆይቷል፡፡

በበጎ አድራጎት ተግባራትም የመንፈሳዊ ጉዞ መርሐ ግብር፣ ነዳያንን መመገብ፣ አረጋውያንን መንከባከብ፣ ለሕፃናት የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ አብያተ ክርስቲያናት እና የስብከተ ወንጌል አዳራሾችን በማነጽ፣ … ወዘተ ተግባራትን በማከናወን ረገድ ግቢ ጉባኤያት አርአያ የሚሆኑ ሥራዎችን ሠርተዋል ወደፊትም በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላሉ፡፡

ግቢ ጉባኤያትን ለማስተማርና ብቁ ዜጋ አድርጎ ለመቅረጽ የማኅበረ ቅዱሳን ድርሻ ከፍተኛውን ቦታ የሚይዝ ሲሆን እንዚህን ሥራዎች ለመሥራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በርካታ ችግሮችም በእግዚአብሔር ቸርነት ታልፈው ዛሬ ላይ መድረስ ተችሏል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህልም፡-

ውጫዊ ችግሮች ከምንላቸው ውስጥ፡- ዓለማዊነትና ሉላዊነት/Globalization/ አስተሳሰብ መስፋፋት፣ የመገናኛ ብዙኀንና ማኅበራዊ ሚዲያዎች መስፋፋት፣ የምዕራባዊ የባሕል ወረራ፣ የተማሪዎች ከኢትዮጵያዊነት እሴት ማፈንገጥ/ ውርጃ፣ ሱሰኝነት፣ ግብረ ሰዶም፣ ዝሙት፣ ሌሎችም መስፋፋት/፣ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ እና የጎሣ ፖለቲካ አስተሳሰብ መስፋፋት ይጠቀሳሉ፡፡ ውስጣዊ ችግሮችን ስንመለከት ደግሞ፡- የግብረ ገብነት መቀነስ፣ የሙስና መስፋፋት፣ ለሱስ ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች መበራከት፣ ዓለም አቀፋዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ተሳትፎ አናሳ መሆን፣ ለግቢ ጉባኤያት አገልግሎት በብዛትና በጥራት በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያገለግሉ አገልጋዮች እና መምህራን ያለመኖር እንደ ችግር የሚታዩ ናቸው፡፡

ግቢ ጉባኤያት ማኅበረ ቅዱሳን ወደፊት አገልግሎቱን በማጠናከር ተቋማዊ ለውጥን በመተግበር የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ልዩ ትኩረት ሠጥቷቸው ከሚሠራባቸው ዘርፎች አንዱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የጉባኤ ቤት ደቀ መዛሙርትን ለግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማሠልጠን፣ ኢ-መደበኛ መምህራንን በማእከላት ማፍራት፣ መደበኛ መምህራንን እና የአብነት መምህራንን መቅጠር፣ ከአንድ በላይ ተጨማሪ ቋንቋ ለሚያስተምሩ እና ለሚያሠለጥኑ መምህራን የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና መስጠትና ማሠማራት፣ ተተኪ መምህራንን በደረጃ ፫ በልዩ ሁኔታ ማሠልጠን፣ ግቢ ጉባኤያት ተኮር የአንድ ሰዓት የብሮድ ካስት መርሐ ግብር ሥርጭት መጀመር እና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡ ፡ በዚህም የወደፊት ተስፋችን በቅንነትና በታማኝነት ሀገርንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚረከቡ እንዲሁም ሊያገለግሉ የሚችሉ በሁለት ወገን ማለትም በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ዘርፍ የተሣለ ሰይፍ ሆነው የሚወጡ ወጣቶችን ማፍራት ነው፡፡

በዚህም መሠረት የግቢ ጉባኤያትን አገልግሎት ለማጠናከር “ግንቦት ልደታን ለግቢ ጉባኤያት” በሚል መሪ ቃል ከሚያዚያ ፳፰ እስከ ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ልዩ ልዩ መርሐ ግብራትን በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በተለይም በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ውስጥ የሚያጋጥመው የፋናንስ እጥረት ለመቅረፍ ከበጎ አድራጊ ምእመናን፣ ከግቢ ጉባኤያት ተመርቀው በልዩ ልዩ ሥራ ላይ የሚገኙ ወንድሞችና እኅቶች፣ ሌሎችም ተባባሪ አካላት ድጋፍ ለማሰባበሰብ እየሠራ ይገኛል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

ግቢ ጉባኤያት በቤተ ክርስቲያን

ቅዱስ ያሬድ “ሀገረ ክርስቶስ አዳም ወሠናይት ከመ ፀሐይ ብርህት ወከመ መርዓት ሥርጉት፤ የክርስቶስ ሀገር በጣም ያማረች፣ እንደ ፀሐይ የበራች እንደ ሙሽራም የተሸለመች ናት” በማለት የሚገልጻት ቤተ ክርስቲያን እናት ልጇ ምግብ አልበላላት ሲል ከምትጨነቀው ጭንቀት የበለጠ እናት ቤተ ክርስቲያን ከደገሰችው ድግሥ ልጆቿ አልመገብ ሲሉ ዘወትር ታዝናለች ትተክዛለች።(ጾመ ድጓ ዘምኵራብ)

የደገሠችልን ድግሥም ዛሬ በልተነው ነገም የሚያሻን አብዝተን ብንበላው ሕመም የሚያመጣብን ሳይሆን ከማርና ከስኳር ይልቅ ለሕይወታችን አስፈላጊ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል፣ ሕይወት የሚሆነን ሥጋ ወ-ደሙን ነው።

ነገር ግን የመጀመሪያው ሰው አዳም “በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትምታለህና፡፡” ተብሎ የተነገረውን ትእዛዘ እግዚአብሔር በመተላለፍ በልቶ የሞት ሞትን እንደሞተ ሁሉ ዛሬ ደግሞ ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ በሕይወትም ትኖራላችሁ ቢለንም ባለመብላት ወደ ሞት መንገድ ጉዞ የጀመርን ብዙዎች ነን። ((ዘፍ. ፪፥፲፮-፲፯)

መድኃኒት የሚያሻው ለታመመ እንደሆነ ሁሉ በኃጢአት የታመመ ብዙ ነው፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛል። ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ከተለያዩ አካባቢዎች እንደመሰባሰባቸው የተለያየ የሕይወት ተሞክሮ ያላቸው በመሆኑ ልጓም የሚሆናቸው መንፈሳዊ ዕውቀት ካላገኙ በተለያዩ የኃጢአት ደዌያት እንደሚያዙ የሚያጠራጥር አይደለም።

ከቤተሰብ፣ ከዘመድ ርቀው በመኖራቸው ነፃነት ስለሚያገኙ ከመንፈሳዊው ሕይወት ይልቅ መጥፎ በሆነ ሱስ ራሳቸውን የሚደብቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ በሥጋዊ ሥራዎች (በዝሙት፣ በምንፍቅና፣ በዘረኝነት) በሽታ ተይዘው ክርስቲያናዊ ሕይወታቸውን፣ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ያጣሉ። ይህን ፈተና እንዲቋቋሙ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን በተደራጀ መንገድ እንድትቀጥል ግቢ ጉባኤ ሰፊውን ድርሻ ይይዛል።

ግቢ ጉባኤያት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷና ትውፊቷን ይዛ ከማስቀጠል አንጻር ምን ሠራ?

ቤተ ክርስቲያን ማለት እያንዳንዱ ምእመን፣ ሕንጻው፣ ኅብረታችንን ማለታችን እንደሆነ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ “ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸውታል። የመጀመሪያው እያንዳንዱ ክርስቲያን ትውልድ እንዲቀጥል የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ ነው። እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲቀጥል ማድረግ  ማለት  አባት  እናት  ሲሞት ልጅ  ይተካል። ተተኪው ትውልድ ከሚባለው ውስጥ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያልፉት  ይገኙበታል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም አስተምህሮዋን ዶግማዋን ቀኖናዋን እና ትውፊቷን ይዛ የምትቀጥለው ርትዕት የሆነችውን  የአባት  የእናቱን  ሃይማኖት  ጠንቅቆ  ባወቀ  ትውልድ  ነው።  ለዚህ ደግሞ  ግቢ  ጉባኤያት  አስፈላጊ  ናቸው።

ሁለተኛው የክርስቲያኖች ኅብረት ነው። እያንዳንዱ ክርስቲያን ትውልዱን ማስቀጠል ከቻለ የክርስቲያኖች ኅብረትም ይቀጥላል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰባሰቡ ተማሪዎች ከሀገራችን ከሁሉም  አቅጣጫ የሚመጡ  ስለሆነ  ግቢ ጉባኤያት  ላይ  በሚገናኙበት  ወቅት የአኗኗር ባህላቸው ሳያግዳቸው እርስ  በእርሳቸው  ተግባብተው አንዱ ከሌላው እየተማረ በሃይማኖት፣ በምግባር በጎ  ነገር  የሚማሩበት ነው። ስለዚህ ሰው ከጎረቤቱ ጋር መኖር በከበደው በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ አንድነት ብለን የምናቀነቅነውን ሐሳብ እየታደጉ ያሉት እነዚህ  የግቢጉባኤያት ተማሪዎች ናቸው።

በክርስቲያናዊ መዋደድ የሚዋደዱ፣ የሚረዳዱ፣ የሚተሳሰቡ ተማሪዎችን ብንፈልግ ከፍ ያለውን ቦታ የሚይዙት የግቢ ጉባኤያት ፍሬዎች ናቸው። ለማኅበራዊ አንድነትም ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንዳለው በዚህ መረዳት ይቻላል። የክርስቲያኖች ኅብረት እንዲታነጽ፣ እንዲቀጥል ያደርጋልና።

ሦስተኛው፡- ክርስቲያኖች እስካሉ ድረስ ሥርዓተ አምልኮን ለመፈጸም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መኖር አለበት። ቤተ ክርስቲያን የምትታነጸውም በሃይማኖቱ በጸና፤ አስተምህሮዋን ተረድቶ ለአገልግሎት ራሱን ባዘጋጀና ለሌሎች ፍቅር በሚሰጥ፣ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ወደፊትን አሻግሮ ማየት በሚችል ትውልድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ግቢ ጉባኤያት ከፍ ያለ አበርክቶት አላቸው።

ዛሬ ላይ በግቢ ጉባኤያት ያለፉ ልጆች አንዳንዶቹ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ ተስማምተውላቸው ዓለምን ንቀው መንነው ለሀገር ሰላም እና አንድነት ይለምናሉ፤ አንዳንዶቹ በሥርዓተ  ቤተ ክርስቲያን ጸንተው  በዲቁና፣ በሕግ እየኖሩ ማለትም (በቅስና) እያገለገሉ ይገኛሉ። አንዳንዶች የዘመናዊ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ጉባኤ ቤት ገብተው የሚማሩም አሉ። የተማሩት ደግሞ እንደ አባቶቻቸው ወንበር ተክለው የሚያስተምህሩም አሉ።

በሃይማኖት ዐይን ለተመለከተው ይህ ቀላል የሚባል አይደለም። “ግንቦት ልደታን ለግቢ ጉባኤ” በማለት ሳምንቱ የግቢ ጉባኤ ሳምንት እንዲሆን የተደረገውም እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ወደፊት ግቢ ጉባኤ ከዚህ የተሻለ አሠራር እንዲኖረው ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገር የሚጠቅም ትውልድ ለመፍጠር በማሰብ ነው።

የአንድ ሳምንት የገንዘብ ማሰባሰብ ዓላማውም ቅዱስ ጳውሎስ “ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና።”  (፪ኛጴጥ. ፩፥፲) እንዲል በአእምሮ የጎለመሱ፣ በጥበብ ያደጉ፣ ዘመኑን የዋጁ የቤተ ክርስቲያንን ልጆች የበለጠ ማትጋት ስለሚያስፈልግ ግቢ ጉባኤያትን ማጠናከር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በመሆኑ የግቢ ጉባኤ ባለአደራዎች የተጣለባችሁን ኃላፊነት እና አደራችሁን ተወጡ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ማኅበረ ቅዱሳን እና ግቢ ጉባኤያት

ክፍል አንድ

ኢትዮጵያ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ጠበቃ የሆኑ ዘመን ተሻጋሪ አሻራዎችንና ታሪኮችን በማኖር ዛሬ ድረስ ወደፊትም ስማቸው ሲወሳ የሚኖር ነገሥታትና ሊቃውንት ያፈራች ሀገር ናት፡፡ ሀገርን በመገንባት ረገድም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ድርሻዋ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያበረከተችውን ሁሉ በመዘንጋት እንደ ኋላ ቀር በመቁጠር ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ጀምሮ ወታደራዊው መንግሥት “እግዚአብሔር የለም” አስተሳሰብን በማራመድ በተለይም ኦርቶዶክስ ጠል ርእዮተ ዓለም የሆነውን ማርክሳዊ እና ሌኒናዊ አስተሳሰብን አሰፈነ፡፡ ኦርቶዶክሳውያንም እምነታቸውን በግልጽ እንዳያራምዱ ክልከላን እስከ ማድረግ አደረሰው፡፡ በወጣቱ ትውልድ ላይም የሶሻሊዝም ርእዮተ ዓለም ጽንሰ ሐሳብን በማሥረጽ ከቤተ ክርስቲያን እንዲርቅና የሶሻሊዝም አቀንቃኝ እንዲሆን ከፍተኛ ቅስቀሳ አደረገ፡፡

ቢሆንም ኦርቶዶክሳውያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ኦርቶዶክሳዊነት እንደ ኋላ ቀርነት መቆጠሩ ሳይበግራቸው ያለውን ተጽእኖ በመቋቋም በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ሕንፃ ቁጥር ፭፻፭ ዶርም ፳፰ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፲፱፻፸፯ ዓ.ም በቅዱስ ገብርኤል ስም በ፭ ወንድሞች የጽዋ ማኅበር ጀመሩ፡፡ የጽዋ ማኅበሩ መጀመር ቀስ በቀስ አዲስ አበባ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች እና ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በፍጥነት ለመስፋፋት ቻለ፡፡

ወቅቱ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት መንግሥት የሰፈራ ጣቢያዎችን በማቋቋም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ወደ አካባቢዎቹ ሲያሰማራ ጋምቤላ እና መተከል የደረሳቸው ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በአንድነት በመሰባበሰብ የጸሎት እና የትምህርት መርሐ ግብራትን ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከ፲፱፻፹ ዓ.ም ጀምሮም በዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ጥቂት የቤተ ክርስቲያን ልጆች በክረምት ወቅት በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው በአቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ አማካይነት ሥልጠና የመውሰድ ዕድል ገጠማቸው፡፡

ወቅቱ ጦርነት እየተጠናከረ የመጣበት ጊዜ ስለነበር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ ወደ ተለያዩ ማሠልጠኛዎች እንዲገቡ ተደረገ፡፡ በተለይም በብላቴ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ቦታም ሳሉ ማታ ማታ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ተገናኝተው ጸሎት ማድረግ፣ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት መማራቸውን ቀጠሉ፡፡

ከመንግሥት ለውጥ በኋላም እነዚህ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በመሰባበሰብ ቤተ ክርስቲያንን በዕውቀታቸው፣ በሙያቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ባላቸው ነገር ሁሉ የሚያገለግሉ ወጣቶችን ለማፍራትና ለማሠማራት፣ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጥናትና ምርምሮቻቸውን የሚያደርጉ ወጣቶችን ለማፍራት፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው፣ ሀገሩን እና ቤተ ክርስቲያንን የሚወድ፣ ለእውነት እና ለፍትሕ የሚቆም፣ በሚሠራው ሥራ ኃላፊነቱን የሚወጣ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ እና ከሙስና የጸዳ መልካም ዜጋ ለማፍራት በዋናነት ግቢ ጉባኤያት ላይ እንዲሠራ በማሰብ ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት ፩ ቀን ፲፱፹፬ ዓ.ም በይፋ የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ በማጽደቅ ተመሠረተ፡፡

ይቆየን

“ግንቦት ልደታን ለግቢ ጉባኤያችን”

ማኅበረ ቅዱሳን የተመሠረተበትን ፴፩ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ “ግንቦት ልደታን ለግቢ ጉባኤያችን” በሚል መሪ ቃል ከሚያዚያ ፳፰ እስከ ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች እንደሚከበር ዐቢይ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ባለፉት ፴፩ ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት መሠረት ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ በማስተማር በዕውቀት እና በሥነ ምግባር የታነጹ፤ ለሀገር እና ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ትውልድ በማፍራት የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱንና ወደፊትም ያመጣቸውን ለውጦች መነሻ በማድረግ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዐቢይ ኮሚቴው ምክትል ኃላፊ  አቶ አበበ በዳዳ ገልጸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶችና መልካም አጋጣሚዎችን መነሻ በማድረግ የተሻለ አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ለማበርከት ባለው ጽኑ ዓላማ መሠረት ግቢ ጉባኤያትን በማጠናከር ያጋጠሙትን ችግሮች በመፍታት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት እንዲፈጽም ታስቦ “ግንቦት ልደታን ለግቢ ጉባኤያችን” በሚል መሪ ቃል ለማክበር መወሰኑን አቶ አበበ አብራርተዋል፡፡

አቶ አበበ በማብራሪያቸው “በእነዚህ የአገልግሎት ዘመናት የታዩ ውጤታማ ለውጦች የበለጠ ለማገልገል የሚያነሳሱ በመሆናቸው ማለትም፡- ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ ማስተማሩ፣ የአብነት ትምህርት ተምረው በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሱታፌ እንዲኖራቸው ማድረጉ፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው በመደበኛ ትምህርታቸው ውጤታማ በመሆን የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚዎችን ማፍራቱ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅም ትውልድ መፍጠሩ፣ ተተኪ መምህራንን ማፍራቱ… ወዘተ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት በተጠናከረ ሁኔታ ለመስጠት እንዲነሳሳ አድርጓል” ብለዋል፡፡

ከሚያዚያ ፳፰ እስከ ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በሚኖረው መርሐ ግብርም በዋናነት በግቢ ጉባኤት ላይ የሚታዩ መልካም ለውጦችን ለማስቀጠል፣ ችግሮችን ለመፍታት እና አገልግሎቱን ለማጠናከር የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እንደሚኖር አመልክተዋል፡፡

በዚህም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ከግቢ ጉባኤ ተማሪዎች፣ ከግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ወላጆች፣ እንዲሁም ከግቢ ጉባኤ ተመርቀው በልዩ ልዩ ሥራ እና አገልግሎት ከተሠማሩ አካላት እና ምእመናን ገቢ ለማሰባበሰብ መታቀዱን አቶ አበበ አስታውቀዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥ ፵፰፣ በውጪ ሀገር ፬ ማእከላት ሲኖሩት በአጠቃላይ ፬፻፶፪ ግቢ ጉባኤያት (፬፻፴፭ በሀገር ውስጥ፣ ፳፫ በውጭ ሀገራት) እንዳሉት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ዕለታት ስያሜዎች

ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ባለው አንድ ሳምንት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሰባቱን ዕለታት የተለያዩ ምሥጢራዊ ስያሜዎችን ሰጥታ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ታከናውንባቸዋለች፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ቤዛ አድርጎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ተቀብሮ፣ ሙስና መቃብር ሳይወስነው መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሞቱ ሞትን ሽሮ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አውጇልና ኦርቶዶክሳውያን በልዩ ድምቀት የሳምንቱን ዕለታት እናከብራለን፡፡ በዚህም መሠረት የሰባቱ ዕለታት ስያሜዎችን እንደሚከተለው እናቀርባቸዋለን፡፡

ሰኞ

ሰኞ – ማዕዶት ትባላለች፡፡ ማዕዶት ማለት መሻገር፣ ማለፍ ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ፋሲካችን ክርስቶስ  ነፍሳትን ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሐሳር ወደ ክብር፣ ከሲኦል ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ናት፡፡ (ዮሐ. ፲፱፥፲፰፤ ሮሜ. ፭፥፲-፲፯)፡፡

ማክሰኞ 

ይህች ዕለት ለሐዋርያው ለቅዱስ ቶማስ መታሰቢያ ትሆን ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን “ቶማስ” ተብላ ሰይማዋለች፡፡ ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን፤ በቀኖት የተቸነከረው እጁንና እግሩን ካላየሁ አላምንም በማለቱ ክርስቶስም “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን” ብሎታል። ቶማስም ጣቶቹን አስገብቶ በዳሰሰው ጊዜ ስለተቃጠለ “ጌታዬ አምላኬ” ብሎ አመነ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም “ስለ አየኸኝ አመንህን? ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አለው (ዮሐ ፳፥፳፯-፳፱)፤ ቶማስም የጌታን ፍቅር ተገንዝቦ ትንሣኤውን ስላመነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቶማስ ብላ ትታሰባለታች።

ረቡዕ 

አልአዛር ተብላ ትታሰባለች፡፡ የማርታ እና የማርያም ወንድም የሆነው አልአዛር ከሞተና ከተቀበረ ከአራት ቀናት በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቃብር ጠርቶ አስነሥቶታል፡፡ ጌታችን በሥልጣኑ አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱንና በአምላክነቱ ያደረገውን ተአምራት የተመለከቱ ሁሉ በጌታችን አመኑ፡፡ በዚህም መሠረት ረቡዕ “አልዓዛር” ተብላ ትታሰባለች (ዮሐ. ፲፩፥፴፰-፵፮)፡፡ 

ኀሙስ 

ይህቺ ዕለት የአዳም ሐሙስ ተብላ ትጠራለች፡፡ ቃል የተገባለት የአዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ሆና ተሰይማለች፡፡ (ሉቃ. ፳፬፥፳፭-፵፱)፡፡ይህም አዳም እና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፈው በመገኘታቸውና የሞት ሞት ተፈርዶባቸው ከገነት ተባረው ነበር፡፡ ነገር ግን የአምላካቸውን ትእዛዝ ተላልፈዋልና በፍጹም ፀፀት እያነቡ ንስሓ በመግባታቸው ይቅርታን የሚቀበል አምላክ “ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፤ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ተወለደ፤ ለሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከኃጢአት በስተቀር በምድር ላይ ተመላልሶ በስቀል ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ሞትን በሞቱ ሽሮ ተነሥቶ በትንሣኤው ትንሣኤን አውጆ አዳምና ልጆቹን ወደ ቀደመ ክብራቸው መልሷቸዋልና ዕለቲቱ “የአዳም ሐሙስ” ተብላለች፡፡

 ዐርብ

ስድስተኛዋ ቀን ዐርብ “ቤተ ክርስቲያን” ተብላ ተሰይማለች፡፡ በክርስቶስ ደም ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ናት፡፡ ይህም ሁሉም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመባት ዕለት በመሆኗ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ያደረገውን ተአምራት በመስቀሉ ድኅነትን እንዳሳየ፤ በቀራንዮ የሕንፃዋ መሠረት እንደተተከለላትና ሥጋ መለኮት እንደተቆረሰላት፤ ልጆቿን ከማሕፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ ገቦ እንደፈሰሰላት ተገልጾባታል፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት

ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ስያሜ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጕልበታቸው ላገለገሉት፤ በስቅለቱ ጊዜ እስከ ቀራንዮ ድረስ በልቅሶና በዋይታ ለተከተሉት፤ (ሉቃ. ፳፫፥፳፯) በዕለተ ትንሣኤው ደግሞ ሽቱና አበባ ይዘው ወደ መቃብር የገሰገሱትን፤ ከሁሉም ቀድሞ ጌታችን በዕለተ ሰንበት ተነሥቶ ለተገለጸላቸው ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት፣ ሰሎሜንም መታሰቢያ ለማድረግ ነው፡፡”ከሳምንቱ በመጀመሪያይቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ” እንዲል፡፡ ((ማቴ. ፳፭፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፬ ፥ ፩)፡፡

እሑድ

ዳግም ትንሣኤ፡፡ ከዋናው ትንሣኤ ሳምንት በኋላ የምትመጣዋ ዕለተ እሑድ “ዳግም ትንሣኤ” ተብላ ትዘከራለች፡፡ ጌታችን በትንሣኤው ዕለት ማታ በዝግ በር ገብቶ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ተገኝቶ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን! በማለት ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ነገሩት፡፡ እርሱ ግን ከማመን ይልቅ በኋላ እናንተ ‘አየን’ ብላችሁ ልትመሰክሩ፤ ልታስተምሩ፤ እኔ ግን ‘ሰምቼአለሁብዬ ልመሰክር፤ ላስተምር? አይሆንም፡፡ እኔም ካላየሁ አላምንም አለ፡፡

ስለዚህም የሰውን ሁሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው የወዳጆቹን የልብ ዐሳብ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት ሐዋርያት በተዘጋ ቤት በአንድነት ተሰባስበው እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ “ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!” በማለት በመካከላቸው ቆመ፡፡ ቶማስንም “ያመንህ እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን፤ እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ፤” ብሎ አሳየው፡፡ እርሱም ጣቶቹን ወደ ተወጋው ጎኑ አስገባ፤ ጣቶቹም ኩምትር ብለው ተቃጠሉ፡፡ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደ ፍላጎቱ በመረዳቱ “ጌታዬ፣ አምላኬ” ብሎ መስክሮ የክርስቶስን ትንሣኤ አመነ፡፡ በዚህም ምክንያት   የሳምንቱ ዕለተ ሰንበት የትንሣኤው ምሥጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመሆኑ “ዳግም ትንሣኤ” ተብሎ ይጠራል፤ ይከበራል፡፡ (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡

ብርሃነ ትንሣኤውን የገለጸልን አምላካችን ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

 

“ዳግመኛ ልትወለዱ ይገባችኋል” (ዮሐ. ፫፥፯)

ይህንን ቃል የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ መምህር ለሆነው ኒቆዲሞስ በጥምቀት ዳግመኛ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርስ እንደማይችል ባስረዳበት ትምህርቱ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ምንም እንኳን የአይሁድ መምህር ቢሆንም ምሥጢሩን እያመሠጠረ የኦሪትን ትምህርት ቢያስተምርም ስለ ዳግም መወለድ ምሥጢር ተሠውሮበት ጌታችንን ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲጠይቅ እንመለከታለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ሲመላለስ ኢአማንያንን በትምህርቱ ፣ የታመሙትን በተአምራት እየፈወሰ፣ አምስት እንጀራና ሁለት አሣን አበርክቶ የተራቡትን አጥግቦ፣ የተጠሙትን አጠጥቶ እንደመሻታቸው ፈጽሞላቸዋል፡፡ ነገር ግን አምላክ ሲሆን የአዳምን ሥጋ ለብሷልና ራሱን “የእግዚአብሔር ልጅ” እያለ ይጠራል በማለት አይሁድ በምቀኝነት ተነሥተው በየጊዜው ይፈትኑት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ነጻ የሚያወጣቸው መሲሕ ይፈልጋሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለብዙ ዘመናት በሮማውያን በባርነት ቀንበር ስለ ተሰቃዩ ተስፋ ቆርጠው ነበር፡፡ መሲሕ ቢመጣ እንኳ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ጦር ይዞ፣ ሠራዊት አስከትሎ እንደሆነ ነበር የሚያምኑት፡፡ ለዚህም ነው የክርስቶስን መሲሕነት ያልተቀበሉት፡፡

ለዚህም ትልቅ ማሳያ የሚሆነን ከፈሪሳውያን ወገን የሆነው የኦሪት መምህሩ ኒቆዲሞስ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ሰው ለማሰብ የዐቢይን ጾም ሰባተኛ ሳምንት እሑድ በስሙ ሰይማ ታከብረዋለች፡፡ ተከታዮቿ ምእመናንም የእርሱን አሠረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለች፤ ታስተምራለችም፡፡

ኒቆዲሞስ ማነው?

ከአይሁድ መካከል ፈሪሳውያን ሕግን የሚያጠብቁ ቀሚሳቸውንም የሚያስረዝሙ፣   የማይፈጽሙትን ሕግ በሕዝብ ላይ የሚጭኑና ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ከፍ የሚያደርጉ፣ የአብርሃምን ሥራ ሳይሠሩ አባታችን አብርሃም ነው እያሉ የሚመጻደቁ ናቸው፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ምንም እንኳ ፈሪሳዊ ቢሆንም አለቃ እንዲሆን በሮማውያን የተሾመ ባለ ሥልጣን ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ለአይሁድ መምህራቸው ሲሆን የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቱን ሰምቶ፣ ተአምራቱን አይቶ በፍጹም ልቡ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብሎ የተሠወረውን ይገልጥለት ዘንድ ለመማር ራሱን ከዚህ ሕዝብ ለይቶ በፍጹም ልቡ ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ፈሪሳዊ ነው፡፡ በቀን በብርሃን ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ ለመማር የአይሁድን ክፋትና ተንኮልን ያውቃልና ይህንን ፍራቻ በጨለማ አምላኩን ፍለጋ መጥቷል፡፡ “መምህር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” በማለትም መስክሯል፡፡ (ዮሐ. ፫፥፪)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኒቆዲሞስን ምስክርነት ሲሰማም “እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” በማለት መልሶለታል፡፡ ኒቆዲሞስ ምሥጢሩ ቢረቅበትና መረዳት ቢሣነው “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” ሲል ጠይቋል፡፡ ጌታችንም የኒቆዲሞስን ጥያቄ “እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፡፡ ስለዚህ ዳግመኛ ልትወለዱ ይገባችኋል ስላልሁህ አታድንቅ” በማለት ለእግዚአብሔር ምንም የሚሣነው ነገር እንደሌለና የኒቆዲሞስ አመጣጥ ከልብ መሆኑን አውቆ ምሥጢረ ጥምቀትን (ዳግም ልደትን) ገለጸለት፡፡ (ዮሐ.፫፥፭-፯)

ኒቆዲሞስ ከጌታችን ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር ጭ ብሎ ተምሯልና በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ “እስከ ሞት ከአንተ አንለይህም” ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ከዮሐንስ በቀር ሲበታተኑ፣ ቀራንዮ ላይ የተገኘው ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ጌታችን “ሁሉ ተፈጸመ” ብሎ ነፍሱን ከሥጋው ሲለይ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ሆነው የክርስቶስን  ሥጋ ከአለቆች ለምነው በመገነዝ በአዲስ መቃብር ለመቅበር በቃ፡፡ በዚህ ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዐቢይ ጾም ሰባተኛው ሳምንት “ኒቆዲሞስ” በማለት ታከብራለች፡፡(ማቴ.፳፮፥፴፩-፴፭፤ ዮሐ. ፲፱፥፴)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

“ለሦስት ቀናት በጾምና በጸሎት በአንድ ልብ ሆነን ወደ ፈጣሪያችንን እንድንጮህ አደራ እንላለን”-ቋሚ ሲኖዶስ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የጾምና የምሕላ አዋጅ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ ለጾም አዋጅ ነገሩ!
ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ” (ትንቢተ ዮናስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 5)
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በተከሰተው ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ መዋቅሮቿን በመጣስ መፈንቅለ ሲኖዶስ በማድረግ በሕገወጥ መንገድ ኤጲስ ቆጶስነት ሢመት በሰጡትና በተሾመ ግለሰቦች ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥር 18 ቀን 2015ዓ.ም. ቃለ ውግዘት ማስተላለፉ ይታወቃል።
     ይሁን እንጂ እነዚህ ሕገወጥ ቡድኖች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ካለመቻላቸውም በላይ በመንግሥት ኃይሎች በመታገዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታስተዳድራቸውን መንበረ ጵጵስናዎችንና ቢሮዎችን በኃይል በመውረርና በመስበር ከፍተኛ ጥፋት እያደረጉ ከመሆኑም በላይ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችን ሠራተኞች ካህናትና ምእመናን በማሰርና በማንገላታት ላይ ይገኛል፡፡
መንግሥትም ሕግ ከማስከበር ይልቅ ለሕገ ወጥ ቡድኖች ድጋፍ በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና መብት ሊያስከብር ስላልቻለ ሁሉን ማድረግ ወደሚቻለው አምላካችን በመማፀን ጸሎትና ምሕላ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተረድቷል።በመሆነም ጾመ ነነዌን ምክንያት በማድረግ በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን ጥቁር ልብስ ብቻ በመልበስ በጾምና በጸሎት ምሕላ በመያዝ በቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት በመገኘት ወደ እግዚአብሔር ጾም፤ ጸሎትና ምሕላ እንድታቀርቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ጥቁር ልብስ የምንለብሰው በመከራ መጽናት ለመግለጽ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ጥቁር የእውቀት ምልክት ነው ተማሪዎች አውቀናል ሲሉ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፡፡ እኛ ከእውቀት በላይ የሆነውን አምላካችንን በመማፀን ከዚህም ማንም ሊያናውጽን እንደማይችል የምናረጋግጥበት፤ ጥቁር የእውነት ምልከት ነው ዳኞች እውነት እንፈርዳለን ሲሉ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፡፡ እኛም መከራው የሚያሰቅቀን ሳይሆን ይበልጥ ልንጸናና ልንበረታ የሚገባ መሆኑን ለዓለም ሕዝብ የምናሳይበት በመሆኑ ከጥር 29 እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ለሦስት ቀናት በጾምና በጸሎት በአንድ ልብ ሆነን ወደ ፈጣሪያችንን እንድንጮህ አደራ እንላለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

“ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደረሰባት የውስጥ ፈተና ሀዘኗ ከባድ ነው።” ብፁዕ አቡነ አብርሃም

ብፁዕ አቡነ አብርሃም

ብፁዕ አቡነ አብርሃም

        ብፁዕ አቡነ አብርሃም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ይህን የገለጹት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ የተፈጸመውን “የጳጳስ ሹመት” አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ነው።
         ብፁዕነታቸው እንደገለጹት በፈተና የሚያጸናው ሁል ጊዜ ፈተናዎችን እያሳለፈ ለዘመናት ሲጠብቃት የነበረ እግዚአብሔር ዛሬም ጥበቃውና መግቦቱ እንደማይለያት ሙሉ እምነት አለን። በደረሰው ክስተትም እጅግ አዝነናል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ታዝናለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ3ሺ ዘመን በላይ የራሷን አንድነት ከማስጠበቅ አልፋ የሀገርን አንድነት ስታስጠብቅ ለሰው ልጆች አንድነት ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ስትሠራ የኖረች አሁንም ያለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነች በማለት ገልጸዋል።
              ይህንን አንድነቷን የሚንድ ሕጋዊ ሰውነቷን የሚጥስ አላስፈላጊ ክስተት ተፈፅሟል። በዚህም ቅዱስ ፓትርያርኩ በአስተላለፉት ጥሪ መሠረት ከሀገር ውስጥ ከሀገር ውጭ የምትገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከነገው ዕለት ጀምሮ የቅዱስነታቸውን ጥሪ በመቀበል እንድትገኙ በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም የተፈጠረውን ችግር በዝርዝርና በጥናት ቅዱስ ሲኖዶስ አይቶ የመጨረሻውን ውሳኔ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ምእመናንና አገልጋዮች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሁላችሁም በየአላችሁበት ቤተ ክርስቲያንን እንድትጠብቁ ሲሉ አሳስበዋል። ተመሳስለውና የሌለ ሀሳብ እያቀረቡ ሕዝብን ከሚለያዩ ሠዎች እንድትጠበቁና እንድትጠብቁ በጽናት፣ በትእግስትና በፍቅር ሕጋዊ በሆነ ነገር ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን እንድትጠብቋት በአንድነቷ የተረከብናትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአንድነቷ ለነገው ትውልድ ለማስረከብ የእያንዳንዳችንን ድርሻ እንድንወጣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ብለዋል።
            በመጨረሻም ሕጋዊ ሰውነቷ የተረጋገጠ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሕጋዊ ሰውነቷ የመጠበቅ የማስጠበቅ ኃላፊነቱ የመንግሥት ስለሆነ ይህን የተፈጸመውን ግፍ መንግሥት ተመልክቶ የቤተ ክርስቲያኗን ሉዓላዊነት በመጠበቅና በማስጠበቅ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ጥሪ አቅርበዋል ።