‹‹በመስቀሉ አርኀወ ገነተ፤በመስቀሉ ገነትን ከፈተ››ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ

በመ/ር ለይኩን አዳሙ ባሕር ዳርማእከል
  ክፍል -፩
ሊቅነትን ከትሕትና ምናኔን ከቅድስና ከአምላኩ እግዚአብሔር የተቸረው ማኀሌታዊው የሊቃውንቱ አባት የመንፈስ ቅዱስ ዕንዚራ የሆነው ሙራደ ስብሐት ቅዱስ ያሬድ ረቂቃን የሆኑ ሰማያውያን መላእክትን በምስጋና መስሎ እንደ ሰማያውያን መላእክት እግዚአብሔርን በአመሰገነበት የዜማ ድርሰቱ ክርስቶስ ጽኑዕ በሆነ ክንዱ መንጥቆ ሲኦልን በርብሮ ነፍሳትን ነጻ ካወጣ በኋላ ለ5500 ዘመን የሰው ልጆችን ስትውጥ የነበረችን ሲኦልን ዘግቶ በአዳም አለመታዝ የተዘጋችን ገነት በመስቀሉ ቁልፍነት በሥልጣኑ ከፈተ በማለት መስቀሉ ዲያብሎስ ድል የተነሣበት ገነት የተከፈተበት መሆኑን በሚገባ ተናገረ ፡፡
ይህ የተዘጋች ገነት የተከፈተባት መስቀል ለሰማያውያን መላእክት የድላቸው ምልክት የቅዱሳን አባቶቻችን የተጋድሏቸው አርማ ነው፡፡ይህ መስቀል ጎልጎታ ላይ የተተከለ መፍቀሬ ሃይማኖት ለሆነው ለቆስጠንጢኖስ በሰማይ የታየ ለሚፈሩትና ለሚያመልኩት ለኢትዮጵያ ምልክት ሆኖ የተሰጠ የሃይማኖት አርማ ነው፡፡በአዳም በደል ምክንያት ገነት ተዘግታ በኪሩቤል ሰይፍ ትጠበቅ እንደነበረና የዓለም መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ጥንተ ርስታችን ገነትን ከፈተልን ‹‹ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ የሚለውን የምሥራችም አሰማን›› (ሉቃ ፳፫÷፵፫) ቅዱስ ያሬድም ይህን መነሻ አድርጎ ከላይ በርእስነት የጠቀስነውን ቃል በበዓለ መስቀል በሚዘመረው ድጓ ላይ ዘምሮት እናገኘዋለን፡፡
፩. የመስቀል ትርጒም
መስቀል ማለት‹‹ሰቀለ፣ ሰቀለ›› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ምሥጢራዊ ትርጒሙ ወይም ፍችው መስቀያ፣መሰቀያ መከራ ማለት ነው፡፡ኢትዮጵያዊው ሊቅ እንዲህ ሲል ይተረጉማል ‹‹መስቀል ብሂል ዕፀ ሕይወት ብሂል፤መስቀል ማለት የሕይወት ዛፍ ማለት ነው››፡፡በማለት ሊቁ ክርስቶስ ዙፋኑ ያደረገውን ዓለም የዳነበትን ቅዱስ መስቀል የሕይወት ዛፍ በማለት ተርጒሞታል፡፡ አዳምና ሔዋን የበሉት ዕፀ በለስ ሞትና ውርደትን ፍርሃትና መቅበዝበዝን ወደ ዓለም ቢያመጣም ዳግማይ አዳም ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል ግን ሕይወትን ሰላምንና አንድነትን ክብርን ለአዳምና ለልጆቹ ያጎናጸፈ ስለሆነ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የሕይወት ዛፍ በማለት ድንቅ በሆነ አገላለጽ ተርጒሞታል፡፡
                                                                                                   መስቀል በብሉይ ኪዳን
መስቀል ከልደተ ክርስቶስ በፊት ወይም በብሉይ ኪዳን የዐመፀኞች፣የወንጀለኞች፣መቅጫ እንደ ነበረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ሰውን ለመጀመሪያ ጊዜ በመስቀል ላይ መቅጣት የተጀመረው ፋርስ ወይም ኢራን ተብላ በምትጠራ ሀገር ውስጥ ነው፡፡ በፋርስ ወይም በኢራን ሀገር የነበሩ ሰዎች የመሬት አምላክ ወይም ኦርዝሙድ የተባለውን ጣዖት ያመልኩ ስለነበረ በሀገራቸው ሰው ወንጀል ሲፈጽም ቅጣቱን በመሬት ላይ የተቀበለ እንደሆነ ደሙ ፈሶ ኦርዝሙድ ጣዖታቸውን የሚያረክሰው ስለሚመስላቸው ቅጣቱን በመስቀል ላይ ይፈጽሙበት ነበር፡፡
በእስራኤል ሀገር ሰው በደል ሠርቶ ሕግ ተላልፎ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ ሬሳው ለማስጠንቀቂያ ከዛፍ ላይ ይሰቀል እንደነበረ እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነው ቅዱስ መጽሐፍ ሕያው ምስክር ነው፤ ዘዳ ፳፩÷፳፫፡፡ በብሉይ ኪዳን ሙሴ የፈርዖንን መሰግላን (ጠንቋዮች) ድል ያደረገባት በትር የመስቀል ምሳሌ ነው፡፡

፪.መስቀል በሐዲስ ኪዳን
የሐዲስ ኪዳኑ መስቀል መድኃኒት አልባ ለሆነው ዓለም መድኃኒት ሊሆን ወደዚህ ዓለም የመጣ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ ክፋት በአንደበቱም ሽንገላ ሳይኖርበት እንደበደለኛ ተቆጥሮ ከበደለኞች ጋር በደልን በተመሉ በአይሁድ እጅ ተይዞ በግፍ በተሰቀለ ጊዜ አካሉ ያረፈበት የሰላም እግሮቹ የተቸነከሩበት የፍቅር እጆቹ የተዘረጉበት ጎኑ በጦር ተወግቶ ክቡር ደሙ የፈሰሰበት የፍቅር ዙፋን ነው፡፡
በመሆኑም የሐዲስ ኪዳኑ መስቀል አምላክ በክብሩ ያከበረው በቅድስናው የቀደሰው ስለሆነ ለደከሙት ኃይልን ለታመሙት ፈውስን ላዘኑት መጽናናትን ለዕውሮች ብርሃንን ማሰጠቱ ይታወቃል፡፡ የአምላክ ኃይሉና ጥበቡ ማዳኑ የተገለጠበት የፍቅር ዐደባባይ ነው፡፡

በልብ መታሰቡ በቃልም መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በገዛ ሥልጣኑ ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላም ድውይ በመፈወስ ሙት በማስነሣት ብርሃን ለሌላቸው ብርሃንን በመስጠት ድንቅ የሆነ ማዳኑንና ተአምራቱን የገለጸው በአከበረውና በቀደሰው መስቀል ነው፡፡ በዕለተ ዓርብ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከጲላጦስ ተካሰው ክርስቶስን በሐዲስ መቃብር ከቀበሩት በኋላ ከዚያው ከመቃብሩ አጠገብ አስቀምጠውት ነበር፡፡ ይህ መስቀልም ሙት የሚያነሣ ዕውር የሚያበራ ለምጻም የሚያነጻ በመሆኑ አይሁድ ለደካሞች ኃይልና ጉልበት ለነፍስ ቤዛ መድኃኒት በሆነው መስቀል ላይ በጠላትነት ተነሥተው የሕሙማን መዳን ያላስደሰታቸው ምቀኞች ስለሆኑ ጉድጓድ ቆፍረው ቀበሩት፡፡

፫. አይሁድ መስቀሉን የመቅበራቸው ምክንያት ምን ነበር?
ሙታንን እያስነሣ ዕውራንን እያበራ ጎባጣን እያቀና የአምላክን ጥበብና ድንቅ ድንቅ ተአምራቱን በመግለጡ ግፍን የተመሉ ሕዝበ አይሁድ በኃጢአት በፈረጠመ ክንዳቸው የሰው ልጆች እንዳይድኑ ጉድጓድ ምሰው መስቀሉን ቀበሩት፡፡ ሕዝበ አይሁድ መስቀሉን የቀበሩት በሦስት ምክንያት ነው፡፡
፩ኛ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ በሞተ ጊዜ ከተቀበረበት መቃብር ተነሥቶ እንዳይሄድ በሚል ሰቅለው የገደሉት አይሁድ ታላቅ ድንጋይ ከመቃብሩ አፍ ላይ አድርገውና መቃብሩን የሚጠብቁ ዘበኞችን ቀጥረው ማንም ሰው ወደ መቃብሩ እንዳይደርስ ወደ መቃብሩ የቀረበውን የቀረበ በድጋይ ወግረው እንዲገሉት ትእዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡እመቤታችን ድንግል ማርያም ግን ክርስቶስ ከተቀበረበት ቀን ጀምሮ ዘወትር ወደ ልጇ መቃብር እየሄደች ስትጸልይ አይሁድ ይመለከቱ ነበርና በእርሷ አመላካችነት ከነገሥታት አንዱ መጥቶ በክርስቶስ ላይ ስለደረሰው መከራ ሁሉ ይጠይቀናል የተሰቀለበትንም መስቀል ስጡኝ ብሎ ይጣላናል በሚል ፍራቻ የክርስቶስን መስቀል እንዲሁም በግራና በቀኝ የተሰቀሉትን የሁለቱን ሽፍቶች መስቀል፣ ጎኑን የተወጋበትን ጦር፣ ከራሱ ላይ፣ የደፉትን የሾህ አክሊልና የተቸነከረባቸውን ችንካሮች በአንድ ላይ ምድርን ቆፍረው የቀበሩበት አንዱ ምክንያት ነው፡፡
፪ኛ ንጹሓን ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል ርኵሳን አጋንንት ሲያወጡ ሙታንን ሲያስነሡ ለምጻሞችን ሲያነጹ መስማት የተሳናቸው መስማት እንዲችሉ ሲያደርጉ ጎባጣዎችን ሲያቀኑ ዓይነ ሥውራንን ሲያበሩና ወንጌልን ሰብከው በማስተማር ብዙ አሕዛብን በስመ ሥላሴ አሳምነው ሲያጠምቁ ልጅነት ሲያሰጡ በማየታቸው ተሰብስበው ክፉ ምክርን መክረው የሰው ልጆች መዳን ያላስደሰታቸው አይሁድ መስቀሉን ቆፍረው ቀበሩት ሁለተኛው ምክንያት ይህ ነው፡፡
፫ኛ. ድንቅ የሆነው አምላካችን በመስቀሉ ላይ አድሮ የሚደነቅ ተአምራቱን ሲገልጽ ያዩ ሰዎች ቅናተ ሰይጣን ስላደረባቸውና የኦሪትን ሕግ ምክንያት በማድረግ ምድር ቆፍረው ቀበሩት ፡፡ ይሁንም እንጂ እንደ ክፉዎቹ አይሁድ ሳይሆን በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ የሞተው ክርስቶስ ቅዱስ ነው፡፡ የተሰቀለበት መስቀልም ቅዱስ ነው፡፡ ክፉዎች አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን ከቀበሩት በኋላ በተቀበረው መስቀል ላይ ከታናሽ እስከታላቅ በአንድነት ጥርጊያ ለመድፋት ተማማሉ፡፡ ለከተማው ሰው አዋጅ ነገሩ፡፡ የመስቀሉ ስም አጠራር ከሰው አዕምሮ እንዲጠፋ እንዲረሳ ለማድረግ ጌታ የተሰቀለበትን ሕሙማን የዳኑበትን መስቀል ከሥር ጥጦስና ዳክርስ የተሰቀሉበትን ከላይ አድርገው ቀብረው የከተማውን ጥራጊ እያመጡ ይደፉበት ጀመር፡፡የደፉት ቆሻሻም ተራራ እንዳከለ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ዲያብሎስ ተዋርዶ አዳምና ልጆቹ የከበሩበት ሕሙማን የተፈወሱበት ገነት የተከፈተበት ቅዱስ መስቀል ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ ለሁለት መቶ ዓመታት ያህል በመቆየቱ ክርስቲያኖችም በጥጦስ ወረራ ከተማቸውን ለቀው በመሰደዳቸው የከተማዋ መልክአ ምድርም ተለውጦ ስለነበረ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ የት እንደሆነ የሚያውቀው አልነበረም፡፡
ይሁን እንጂ ጌታ በወንጌል “እስመ አልቦ ክዱን ዘኢይትከሠት ወአልቦ ኅቡዕ ዘኢይትዐወቅ፤ የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅ የተሠወረ ምንም የለም” በማለት አስቀድሞ እንደ ተናገረው ሁሉ(ማቴ፲÷፳፮፣ሉቃ.፲፪÷፪) ከሰዎች ኃይል የእግዚአብሔር ኃይል ከሰዎች ጥበብ የእግዚአብሔር ጥበብ ይበልጣልና እነርሱ ተሸፍኖ ወይም ተዳፍኖ ይቀራል ያሉት እግዚአብሔር የተሠወረው ተገልጦ እንዲወጣ ፈቃዱ ነበርና በሃይማኖት የጸናች በምግባር ያጌጠች የመስቀሉ ፍቅር ያላት አይሁድ በምቀኝነት እንደቀበሩት ትሰማ የነበረች ቅድስት ዕሌኒንና ልጅዋን ቆስጠንጢኖስን አስነሣ፡፡
…………….. ይቆየን !

በዓለ መስቀል

በመምህር ፈቃዱ ሣህሌ
ክፍል -፪

ከክፍል አንድ የቀጠለ……………..   

፩. በትምህርት፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በገለጠላት መሠረት ነገረ መስቀሉን አጉልታና አምልታ በማስተማር ክብረ መስቀልን ስትመሰክር ኖራለችም፤ ትኖራለች። ይህን የምታስተምረውም በጉባኤ፣ በመጽሐፍና በተግባር ነው። አስቀድሞ ነቢያት ለምሳሌም (መዝ. ፳፩፥፲፮-፲፱ ፤፷፰፥፳፩፣ ኢሳ. ፶፫፥፬-፲) በኋላም ሐዋርያትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ በአንደበታቸውም ኾነ በመጽሐፋቸው ስለ መስቀሉ ክብር በሰፊው በመግለጽ ተገቢውን ትምህርት ሰጥተዋል። አሁንም እንደቀድሞው ሊቃውንቱ በአብነት ጉባኤያት፣ በማኅሌት፣ በዝማሬ፣ በሰዓታት፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆች፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በዐውደ ምሕረት፣ በቅዱሳት መጻሕፍትና በአገልግሎቶች ሁሉ የመስቀሉን ክብር በመመስከር ላይ ትገኛለች።
፪. በመሳለም፦ ቅዱሱ አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም በላዩ ላይ ስለ ተሰቀለበት ዕፀ መስቀልም የተቀደሰ መሆኑን ከላይ ከተገለጹት ማብራሪያዎች መረዳት አያዳግትም። ይህንን ቅዱስ መስቀል መሳም ወይም መሳለም መቀደስ (ቅድስናን ማግኘት)፥ መባረክ መሆኑም ግርታን የሚፈጥር አይደለም። ይህንን ምሥጢር የበለጠ ለመረዳት እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይ ኪዳን ዘመን ካዘዛቸው ትእዛዛት አንዱን መመልከት መልካም ነው።
በኦሪት ዘፀአት እግዚአብሔር አምላካችን ለርእሰ ነቢያት ሙሴ ቅብዐ ቅዱስ የሚዘጋጅበትን መመሪያ ከሰጠ በኋላ በቅብዐ ቅዱሱ የሚከብሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሲገልጽልን “የመገናኛውንም ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥ ገበታውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም፥ ዕቃውንም፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ። ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፤ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ፤ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።” በማለት ያትታል (ዘፀ.፴፥፳፮-፴።)
ይህንን አስገራሚ የእግዚአብሔር ጸጋ በማስተዋል ያነበቡ ሁሉ በአድናቆትና በደስታ ሆነው ቢያንስ ራሳቸውን እንዲህ ብለን ለመጠየቅ መገደዳቸው አይቀርም።

“የሐዲስ ኪዳን ጥላ በሆነ በዘመነ ኦሪት በነበረ ሥርዓት በቅብዐ ቅዱስ የከበሩት በመቀደሳቸው ምክንያት የሚነኳቸውን ሁሉ የመቀደስ ኃይል ካገኙ፥ ቅዱሱ ጌታ አማናዊ በኾነው ዘመነ ሐዲስ በቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የቀደሰው መስቀልማ ምን ያህል ክብርና ቅድስና ይኖረው ይሆን? የሳሙትንና የተሳለሙትንስ እንዴት ያከብራቸውና ይቀድሳቸው ይሆን?” በዚህም መሠረት ክርስቲያኖች ቅዱስ መስቀሉን በመሳም ወይም በመሳለም ክብረ መስቀሉን እንመሰክራለን ።
፫. በመባረክ፦ ከላይ እንደገለጽነው በላዩ ላይ ከተሰቀለበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የተነሣ መስቀሉ ቅድስናንና ኃይልን ተጎናጽፏል። ለዚህም ምስክሩ ከላይ እንዳየነው በመስቀሉ ዲያብሎስ ድል ተደርጎበታል፤ የገነትም ደጅ ተከፍቶበታል፤ ፈያታዊ ዘየማንም ወደ ገነት አስገብቷል። በዚህም ምክንያት ከላይ እንደገለጽነው የነካቸውንና በእምነት የነኩትን ሁሉ የመባረክ (የመቀደስ) ኃይል አለው። የጌታችን ቀሚስ ለ፲፪ ዓመታት ደም ሲፈሳት የነበረችው ሴት በእምነት በዳሰሰችው ጊዜ ደሟን በቅጽበት እንዳደረቀላት ማስታወስ ለዚህ ንዑስ ርእሳችን ጥሩ ማነጻጸሪያ ነው። (ማቴ.፱፥፳-፳፫።)
መስቀሉ ኃይለ እግዚአብሔር ያደረበት ከመኾኑም በተጨማሪ ለካህናት አባቶቻችን በተሰጣቸውም ሥልጣን እኛ ክርስቲያኖችና የእኛ የሆነው ሁሉ እየተባረክንበት ክፉ የኾነውን ሁሉ እናርቅበታለን፤ ጸጋ መንፈስ ቅዱስንም እንቀበልበታለን። በዚህ አጋጣሚ እስራኤል የተባለ አባታችን ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን (የዮሴፍን ልጆች) በአባታቸው ዮሴፍ ጥያቄ የባረካቸው እጆቹን አመሳቅሎ (በመስቀል ምልክት) መሆኑን ልብ ይሏል። (ዘፍ.፵፰፥፲፪-፲፭።) ባራኪው እየባረከ፥ ተባራኪውም እየተባረከ ክብረ መስቀሉን ሲመሰክሩ ኖረዋል፤ እየመሰከሩም ይገኛሉ።
፬. በማማተብ፦ ክርስቲያኖች የሆንን እኛ በእንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ ማለትም ከቤት ስንወጣ፣ ወደ ቤት ስንገባ፣ ሥራችንን ስንጀምር፣ ማዕዳችንን ስንጀምርና ስንፈጽም፣ መንገዳችንን ስንጀምር፥ በየመኻሉና ስናጠናቅቅ፣ ጸሎታችንን ስንጀምርና ስንፈጽም፣ አስደንጋጭ ነገር ሲገጥመን፣ በጸሎታችን የመስቀልን ስም ከሚያነሣ አንቀጽ ስንደርስ፣. . . ወዘተ ጣቶቻችንን አመሳቅለን (መስቀል ሠርተን) እንድናማትብ ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዘወትር ታስተምረናለች። “እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።” (ሉቃ. ፲፩፥፳) የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ከዚሁ ጋር አያይዞ ማየት፥ ምሥጢሩንም በማገናዘብ መረዳት ይቻላል። ይህም የመስቀሉን ፍቅርና ክብር የምንገልጽበት ሌላው መንገዳችን ነው።
፭. በአንገት በማሠር፦  ክብረ መስቀልን ከምንገልጽባቸው ክርስቲያናዊ የሕይወት ጉዞዎች አንዱ መስቀሉን በአንገት ማሰር ነው። ይህንን የምናደርገው ላመንበት ሃይማኖት፥ ለተቀበልነውም መንፈሳዊ አደራ ያለንን ታማኝነት ለመግለጽ ነው። “በሃይማኖቴ አላፍርም፥ አልደራደርም፤ አንገቴንም እንኳን ሳይቀር ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፤” ለማለት ነው። በኦሪቱም እግዚአብሔር አምላካችን በሙሴ አማካኝነት የሰጠውን አምላካዊ ትእዛዝ መመልከት ቃሉን ይበልጥ ለመረዳት ይረዳናል።

ዳግመኛም “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፤ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሠረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደ ክታብ ይሁንልህ። በቤትህም መቃኖች፥ በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” በማለት የተናገረው ይህንኑ የሚያስገነዝብ ነው ። ጠቢቡ ሰሎሞንም በተመሳሳይ የተናገረው ከዚሁ ጋር ሊመሳከር የሚችል ነው። እንዲህ ያለው፦ “ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ ሁልጊዜ በልብህ አኑረው፤ በአንገትህም እሰረው። ስትሄድ ይመራሃል፤ ስትተኛም ይጠብቅሃል፤ ስትነሣ ያነጋግርሃል” (ምሳ ፮፥፳-፳፫)
፮. በሕዝቡ ባህልና የዕለት ተዕለት አኗኗር ውስጥ በመጠቀም፦ ቅዱስ መስቀል ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው የክርስቲያኖች የድኅነት ዓርማ ወይም ምልክት ነው። በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች ሁሉ ስለሚመኩበት በአንገታቸው በማሠር ብቻ ሳይወሰኑ በግንባራቸውና በእጆቻቸው በመነቀስ፣ በመኖሪያ ቤታቸው ጣሪያ ላይ በማድረግ፣ በልብሶቻቸው በመጥለፍና በመሳሰሉት ገላጭ ክንውኖች በመጠቀም ለአምላካቸው ለክርስቶስና ለተሰቀለበት መስቀል ክብር ያላቸውን ፍቅርና ታማኝነት በፊትም አባቶቻችን፥ ዛሬም ልጆቻቸው ሲመሰክሩ ኖረዋል፤ ይኖራሉ።
፯. በአባቶች እጅ ዘወትር በመያዝ፦ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጀምሮ እስከ ቀሳውስቱ ድረስ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በእንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ መስቀሉን ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት። የክርስቶስ ቤተሰቦች የሆኑትን ኦርትዶክሳውያን ምእመናንም በቤተ ክርስቲያንና በየቤቶቻቸው እንዲሁም በየመንገዱ ሁሉ ይባርኩበታል።

በተጨማሪም እንደሚታወቀው አባቶቻችን በአገልግሎት ሂደት ወቅት በተለየ ሁኔታ መስቀሉን ይጠቀማሉ። በቅዳሴና በምሥጢራት አጠቃቀም ጊዜ ዲያቆናትም የመጾር መስቀል በመባል የሚታወቀውን የሚጠቀሙ ሲሆን በጥቅሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያለ መስቀሉ የምትፈጽመው ምንም ዓይነት ምሥጢርና አገልግሎት የላትም። ይህም ለመስቀሉ ያለንን አክብሮትና ፍቅር የምንገልጽበት ሌላው ማሳያችን ነው።
. በጥንታውያን ቅርሶቻችን ላይ በማድረግ፦ሀገራችን ኢትዮጵያ ክርስትናን ከኢሩሳሌም ቀጥሎ ከሌሎች ሀገሮች ቀድማ የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ትእምርተ መስቀሉን ተቀብላ ያላትን ፍቅርና ክብር ለመግለጽ በልዩ ልዩ መገልገያዎቿ ላይ በመቅረጽ ስትጠቀምበት ኖራለች። ለማሳያ ያህልም፦ በመገበያያ ገንዘቦች (ሳንቲሞች)፣ በነገሥታት ዘውዶችና አልባሳት ላይ በመቅረጽ፣ በቤተ መንግሥት ቤቶች፣ አጥሮችና የመሳሰሉት ላይ የመስቀሉን ምልክት በማኖር ለመስቀል ያላትን ክብር ስትገልጽ ኖራለች፤ ዛሬም ስለ ክብሩ ትገልጻለች፡ትመሰክራለችም።
፱. በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉልላት፣ በበሮቿ፣ በግንቦቿ፣ በአጥሮቿና በንዋየ ቅድሳቷ ሁሉ ላይ ትእምርተ መስቀሉን በመጠቀም፦ ከላይ የጠቀስነው እንደ ሀገር ሲታይ ሲሆን አሁን ደግሞ እንደ ቤተ ክርስቲያን የሆነውን እንመልከት በገሃድ እንደሚታየው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጉልላቷ ጀምሮ በሕንጻ ቤተ ክርስቲያኗ ሁለንተና ላይ የመስቀሉን ምልክት ተሸክማ ትታያለች። ክብረ መስቀሉን ከምትመሰክርባቸው መንገዶች አንዱ በውስጥና በውጭ አገልግሎት ሁሉ በንዋየ ቅድሳትና ላይ መስቀሉ ተቀርጾበት ለአገልግሎት ማዋል የተለመደና የታወቀ ነው።
፲. በስሙ በመሰየም፦ በመስቀሉ ስም ታቦት (ጽላት) ቀርፆና ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ አክብሮ መገልገል የመጀመሪያው ማሳያ ነው። በተጨማሪም ካህናት ተጠማቂዎች ፡ ምእመናንን በመስቀሉ ስም ገብረ መስቀል፣ ወለተ መስቀል፣ ብርሃነ መስቀል፣ መስቀል ክብራ፣. . . እያሉ በመሰየም ነው።) ለመሰቀሉ ያላቸውን ክብርና ፍቅር ሲመሰክሩ ኖረዋል፤ይኖራሉም።
፲፩. በዓሉን በማክበር፦ እንደሚታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓለ መስቀልን ከዘጠኙ ንዑሳት የጌታ በዓላት መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጋለች። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት በተለይ ዓመታዊ በዓላቱን ክርስቲያኖች እንደ አቅማቸውና ዕውቀታቸው መታሰቢያውን እያደረጉ በማክበር ይማጸኑበታል። በይበልጥ ደግሞ በመስቀል ስም በተሰየሙ አብያተ ክርስቲያናት በልዩ ሥርዓት እያከበሩ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እያገኙና እያደሉ ይኖራሉ። በተለይም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በመላው ዓለም ዘንድ በታወቀው የመስከረም ፲፮ የደመራ በዓልና የመስከረም ፲፯ በዓለ መስቀል በምትሰጠው አገልግሎትና በምትፈጽመው ምስክርነት ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ታላቅ በረከትን ስታድል ኖራለች፤ ትኖራለችም። ለክብረ መስቀሉ ማክበሪያ ይሆን ዘንድም ቅድስት ቤተ ክርስቲናችን በመላው የሀገራችን ክፍሎች የመስቀል በዓል ማክብሪያ ዐደባባዮችን ተቀብላ ዓመታዊ በዓለ መስቀሉን በማክበር ላይ ትገኛለች።
፲፪. በልዩ ኹኔታ የተፈጸመ ምስክርነት፦ እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይ ኪዳን ክብሩን የገለጸባትን ታቦተ (ጽላተ) ጽዮንን ከዓለም ሀገራት መርጦ በኢትዮጵያ ማኖሩ ይታወቃል። በተመሳሳይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትንና ክብሩን የገለጸበትን ቅዱስ መስቀል (ግማደ መስቀል) በአደራ ያኖረው በኢትዮጵያ መሆኑም ግልጽ ነው።

በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን ግማደ መስቀል አባቶቻችንና እናቶቻችን በታላቅ ክብር ተቀብለው መስቀለኛ በሆነው ግሸን ደብረ ከርቤ ቅዱስ ተራራ አውጥተውና ለምድር አደራ ሰጥተው ዛሬም ድረስ በክብር ተቀምጦ ይገኛል። በዚህም መሠረት “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ስፍራ አኑር፤” በማለት በቅዱስ ዑራኤል አማካኝነት ልዑል እግዚአብሔር የሰጠውን ትእዛዝ በመፈጸም በፈሪሀ እግዚአብሔር የሚመሩ እውነተኛ የወንጌል አማኞች መሆናቸውን ለዓለም አሳይተዋል። ከመስቀሉ ጋር በተያያዘም በዚሁ ቅዱስ ስፍራ በያመቱ መስከረም ፲፮ እና ፲፯ እንዲሁም ፳፩ ቀናትን በልዩ ክርስቲያናዊ ሥርዓት በማክብር ለመስቀሉ ያለንን ክብር በመመስከር ላይ እንገኛለን።
እንደሚታወቀው ሁሉ ከቅድስት ዕሌኒ ጋር በተያያዘ ተረክቦተ መስቀሉን (የመስቀሉን መገኘት) ያለውን ታሪክ የዓለም ማኅበረሰብ የሚያውቀው፣ የሚጽፈውና የሚናገረው ነው። በዓለም ላይ የሚገኙ አኃትና ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት በየባህላቸው በዓለ መስቀልን የሚያከብሩበት የየራሳቸው መንገድ እንዳላቸውም ይታወቃል። ሌላው በክርስትና ስም የሚጠራው የምዕራቡ ዓለም ደግሞ እንኳን ሊያከብረው ይቅርና መስቀሉን በማጥላላትና በመንቀፍ የስህተት ትምህርት በማሠራጨት ተጠምዷል ፡፡በዚህ ሁሉ የተደበላለቀ ሁኔታ ውስጥ ከዓለም ሀገራት ተለይታ ለታወቀውና ለተገለጸው መስቀለ ክርስቶስ ተገቢውን ክብር በአፀደ ቤተ ክርስቲያን ሳትወሰን በዐደባባይ በዓልነት ወስና በደመቀ ሁኔታ ስትሰጥ የኖረችና በመስጠት ላይ ያለች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቲያን ያሉባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች።

መ. ማጠቃለያ
ቅዱስ መስቀል እንደ ተቋም ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፥ እንደ ኅብረትም ለአንዲቷ የምእመናነ ክርስቶስ ጉባኤ ሁለንተናዋ ነው። በተለይም ተጋዳዪቱ የክርስቶስ አካል ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኃይል፥ ጽንዕ፥ መመኪያ ትእምርት (ምልክት) ይሆናት ዘንድ ከጌታዋ በተሰጣት መመሪያ መሠረት ተሸክማውና ተመርኩዛው ነገረ ክርስቶስን ስትመሰክር ትኖራለች። “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ወዳጆችህ እንዲድኑ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኻቸው።” (መዝ. ፶፱፥፬።) ተብሎ በቅዱስ ዳዊት እንደተገለጸው፥ ከአምላኳ የተሰጣትን ቅዱስ መስቀል ተቀብላና አክብራ እንደ አስፈላጊነቱ ስትጠቀምበት ኖራለች፤ ትኖራለችም። በዓለ መስቀሉን አባቶቻችንና እናቶቻችን በአማረና በደመቀ ሁኔታ ሲያከብሩ ኖረዋል፥ እኛም እናከብራለን፤ ስንል ምን ማለታችን ነው? ጽኑዓን የሆኑት አባቶቻችንና እናቶቻችን የቻሉትን ማድረጋቸውና እኛም የቻልነውን ሁሉ ማድረጋችን ለመስቀሉ እነርሱ የጨመሩለት፥ እኛም ደግሞ የምንጨምረው ክብር ኖሮ አይደለም።
ይልቁንስ ለቅዱስ መስቀሉ ክብር የነበራቸውንና ያለንን ፍቅር ለመግለጽ ያህል እንጂ ዋናው ምሥጢር በመስቀሉ ከብረውበታል፤ እኛም እንከብርበታለን፤ ማለታችን ነው። በዓለ መስቀሉን ከላይ በገለጽናቸው ልዩ ልዩ መንገዶች ስናከብርም በቅዱስ መስቀሉ ያገኘነውን እና የተረጋገጠውን የመዳናችንን ምሥጢር እያወደስንና እያከበርን እየመሰከርንም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።በክፉዎች አይሁድ ተቀብሮና ጠፍቶ የነበረው ቅዱስ መስቀል በፈቃደ እግዚአብሔር በቅድስት ዕሌኒ አማካኝነት ወጥቶ ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ በዓለ መስቀል በልዩ ሁኔታ መከበር መጀመሩ ይታወቃል። በዚህ ዘመን የምንገኝ ክርስቲያኖችም በዓለ መስቀሉን ስናከብር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ በቆረሰው ቅዱስ ሥጋውና ባፈሰሰው ክቡር ደሙ የሰጠንን ሀብታት በማስታወስ መሆን እንደሚገባው መርሳት የለብንም። በመስቀሉ ሰላምን፣ ዕርቅን፣ አንድነትን፣ ሕይወትን፣ ፍቅርን፣ ደስታን፣ ክብርን፣ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ማግኘታችን ይታወቃል። ዛሬ ግን የመስቀሉን ስጦታዎች ወደ ጎን ገሸሽ አድርገናቸው በተቃራኒው የጥፋት መንገድ ውስጥ በመግባታችን ጦርነትን፣ ጸብን፣ መለያየትን፣ኅዘንን፣ ሞትን፣ ውርደትን፣ . . እያነገሥናቸው መሆኑም ግልጽ ነው።
ስለዚህ በዓለ መስቀሉን ስናከብር እግዚአብሔር አምላካችን አሁን ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚለውን ቆም ብሎ ማስተዋል ይኖርብናል። ይህ በዓል የቅዱስ መስቀሉን ትሩፋቶች በማሰብ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን፣ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ከኅዘን ይልቅ ደስታን፣ ከሞት ይልቅ ሕይወትን፣ ከውርደት ይልቅ ክብርን፣ ከቂምና ከበቀል ይልቅ ዕርቅን፣ . . . ለማረጋገጥ አቅም የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉ ምእመናንንና ምእመናትን ይፈልጋል። ከዚሀ ውጪ ሆነን ቀን ቆጥርን፣ ነጭ ለብሰን፣ ቤታችንን ጎዝጉዘን፣ ጠጅ ጥልን፣ ጠላ ጠምቀን፣ ፍሪዳ አርደንና አወራርደን፣ ታላቅ ድግስ በመደገስ መስቀሉን አጅበን፣ ሆ! ብለንና ዘምረን በማሳለፍ ብቻ በዓለ መስቀልን ያከበርን የሚመስለን ካለን የተሳሳትን መሆናችንን መገንዘብ ይኖርብናል።

በዓሉ ታሪኩን በመተረክ ላይ ብቻ ሳንወሰን እንደቀድሞው ሁሉ ዛሬም የጠፋውንና ያጣነውን ለኢትዮጵያ፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለሁላችንም በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ መፈለግንና ከተቀበረበት ቆፍሮ ማውጣትን ይፈልጋልና።
እንደ ደመራው እሳትም የፍቅርን፣ የሰላምን፣ የደስታንና የአንድነትን እሳት በሃይማኖት በማቀጣጠል (በማንደድ) ጥላቻን፣ መለያየትን፣ ዘረኝነትን፣ ኅዘንንና የመሳሰሉትን ጎጂ የሆኑ የሰው ልጅ ጠላቶች በተቀጣጠለው እሳት ማጥፋት ይጠበቅብናል። እያንዳንዳችን የመስቀሉ ወዳጆች የሆንን ሁሉ ራሳችንንም እንደ ዕጣኑ መዓዛ የተወደደ መሥዋዕት አድርገን እስከ ማቅረብም ደርሰን አስፈላጊውን ሁሉ መሥዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ተገቢ ነው። ከምንም በላይ እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር ጋር ሕጉንና ትእዛዙን በመጣስ መጣላት አለመጣላታችንን ማረጋገጥ አለብን። እኛው በድለን ከእርሱ ተጣልተንና ተለይተን ስንኖር ዕርቅ፣ ሰላምና አንድነትን የሰጠን ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ይታወቃል።
አሁን ራሳችንን መመርመር ያለብን በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የጥል ግድግዳ አቁመናል ወይስ አላቆምንም? የሚለውን ነው። የጥል ግድግዳ አቁመን ከሆነ በዓለ መስቀልን ልናከብር የሚገባው በመጀመሪያ የጥሉን ግድግዳ አፍርሰንና በንስሓ ወደ ቤቱ ከተመለስን ከኃጢአት ከበደላችን ከነጻን በኋላ በመስቀሉ ላይ የተቆረሰውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ነው። እንዲህ ባለ መንገድ ማክበር ከቻልን “መስቀል መልዕልተ ኵሉ ነገር ያድኅነነ እምፀር።ከጠላት የሚያድነን መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነው።” በማለት ከቅዱስ ያሬድ ጋር ለመዘመርና በዓለ መስቀሉን በእውነት ለማክበር እንችላለን።
     ልዑል እግዚአብሔር በኃይለ መስቀሉ ይጠብቀን ለዘለዓለሙ አሜን።

በዓለ መስቀል

በመምህር ፈቃዱ ሣህሌ
        ክፍል -፩
ሀ. ትርጒም
ከዚህ በታች የሁለቱን ቃላት መዝገበ ቃላታዊ ፍቺ በማሳየት ወደ ዋናው ትንታኔ ለመግባት እንሞክራለን። በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት አተረጓጎም መሠረት “በዓል” የሚለው ቃል ለዕለት (ለቀን) ሲነገር የደስታ፣ የዕረፍት ቀን፣ በዓመት፥ በወር፥ በሳምንት የሚከበር፣ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት፣ . . . ወዘተ በማለት ተተርጒሟል። (ኪ.ወ.ክ ፪፻፸፱።) “መስቀል” የሚለውን ደግሞ መስቀያ፣ መመዘኛ፣ መንጠልጠያ፣ ለሞት የሚያበቃ መከራ፣ . . .ወዘተ ብለው በማለት ተርጉመውታል (ኪ.ወ.ክ ፰፻፹፫።)እነዚህ ቃላት ዘርዘር ተደርገው በምሥጢር ሲብራሩም እንደሚከተለው ሊገለጹ ይችላሉ።
             ፩. በዓል፦ ዕለታት ለእግዚአብሔር ክብር ገላጭና መታሰቢያ ሆነው ከሌሎቹ ዕለታት ሲለዩ የበዓል ቀናት ተብለው ይጠራሉ። በባሕርዩ ቅዱስ የሆነው አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የጸጋ ቅድስና ከሰጣቸው ፍጥረታት መካከል አንደኞቹ ዕለታት ናቸው። እነዚህም ቅዱሳት ዕለታት ሳምንታዊ፣ ወርኃዊና ዓመታዊ በዓላት ተብለው ሊገለጹ ይችላሉ።
               ፪. መስቀል
ሀ. የጌታችንን መከራ በመሳተፍ እርሱን በትንሣኤ (በክብር) የምንመስልበት አንዱ የመንግሥተ ሰማያት በር ነው። ይህንንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል በተደጋጋሚ ገልጾልናል። መስቀሉን አስመልክቶ ጌታችን ካስተማራቸው ትምህርቶችም መካከል ለማሳያ ያህል ብናነሣ፦
 “መስቀሉን የማይዝ፥ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” (ማቴ. ፲፥፴፯)
 “እኔን መከተል የሚወድ ራሱን ይካድ፥ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝም” (ማቴ. ፲፮፥፳፬)
ለ. ሞትና ዲያብሎስ ድል የተደረጉበት መንፈሳዊ የጦር መሣሪያ ነው።
ሐ. ዓለም ከዘለዓለም ሞት የዳነበት፣ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀበት፣ ከሰይጣን ባርነት ነጻ የወጣበት፣ የተዘጋው የገነት ደጅ የተከፈተበትና አባታችን አዳም ከልጆቹ ጋር ወደ ቀደመ ርስቱ ተመልሶ የገባበት የምሥጢር ቁልፍ ነው።
መ. በዳግም ምጽአት ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ ለሁሉ የሚታይ የሰው ልጅ ምልክት ነው። (ማቴ. ፳፬፥፴።)
ሠ. የክርስቲያኖች ትምክሕታቸው (መመኪያቸው) ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት፥ እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ።” (ገላ. ፮፥፲፬።) በማለት እንደገለጸው።
ረ. የሚማፀኑበትና የሚተማመኑበት ክርስቲያኖች ከጠላት ፍላፃ የሚያመልጡበት ትእምርት (ምልክት) ነው። (መዝ. ፶፱፥፬።)
ሰ. ክርስቲያኖችን አሸናፊ የሚያደርግ ኀይለ እግዚአብሔር ነው። “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው።” (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲፰።) እንዲል።
ሸ. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ዙፋን፥ የአዲስ ኪዳንም መሠዊያ ነው።
ቀ. ቅዱሳን መላእክት ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ ጋር በተዋጉ ጊዜ ኃይል ይሆናቸው ዘንድ እግዚአብሔር በክንፋቸው ላይ የቀረፀላቸው የማሸነፋቸው ምሥጢር ነው። (መጽሐፈ አክሲማሮስ)
በዓለ መስቀል ክርስቲያኖች በላዩ ላይ ተሰቅሎ ያከበረውን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስንና ቅዱስ የኾነ መስቀሉን የሚያከብሩበትና አምልኮተ እግዚአብሔርን የሚገልጡበት የከበረ ዕለት ነው። ምእመናንና ምእምናት ጸንተው ምድራዊ የተጋድሎ ሕይወታቸውን በድል አድራጊነት የሚፈጽሙበት መኾኑን የሚመሰክሩበት እና በማያምኑበት ዘንድም እንኳን በናፍቆት የሚጠበቅ በዓል ነው። በዓለ መስቀልን በማክበር ክርስቲያኖች የክርስቶስን መከራ የሚሳተፉበትና በትንሣኤው የተገኘውን ሕይወትና ክብር የሚካፈሉበት ማለትም ክርስቶስን የሚመስሉበት፥ ለትውልድ ቀረፃም አዎንታዊ ሚና ያለው ተግባራዊ የሕይወት ትምህርት ቤት ነው። ከዘጠኙ ንዑሳት የጌታ በዓላት መካከል አንደኛው በዓለ መስቀል መኾኑ ይታወቃል። ይኸውም መስከረም ፲፯ እና መጋቢት ፲ ቀናት በአንድነት እንደ አንድ ቀን (በዓል) ተቆጥረው ነው።

                                                                       ለ. ክብረ መስቀል
መስቀሉ እንደሚታወቀው ሁሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ይገልጽ ዘንድ፣ሞትን በሞቱ ይገድለው ዘንድ፣ ትንቢቱንና ምሳሌውን ይፈጽም ዘንድ፣ መስተፃርራንን (ጠላቶች የነበሩትን) ያስታርቅ ዘንድ፣ የዲያብሎስን ጥበብ ያፈርስና ወጥመዱን ይሰብር ዘንድ፣ ጥበበኛ ነን ብለው የሚመኩ የክፉዎችን ጥበብና ምክር ከንቱ ያደርግ ዘንድ በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ ዐደባባይ የተሰቀለበት የክብር ዙፋኑ ነው።
በዓለ መስቀሉን በምናከብርበት ወቅት ሁሉ እነዚህን ምሥጢራት ማሰብ ይኖርብናል። ከበዓላተ መስቀልም በልዩ ሁኔታ ወርኃ መስከረም ከደመራው በዓልና ከመስቀሉ ጋር በተያያዘ ለማስታወስ እንገደዳለን። ይህ ወር ምድር በሥነ ጽጌያት፥ ሰማይም በሥነ ከዋክብት የሚያጌጡበት ከመሆኑም በላይ ምድሩ፣ ሰማዩና ዘመኑ በመስቀሉ በረከት መሞላቱና ፍጥረታት ሁሉ በመስቀሉ እንደሚባረኩ በልዩ ድምቀት የሚታሰብበት ልዩ ወር ነው።
በብሔራዊ ደረጃ (በዐዋጅ) የምናከብርበትም ምክንያት የነገረ ድኅነት ትምህርታችን አካል በመሆኑና በክርስቲያኖች ልቡና ታትሞ ያለ የሕይወታችን ዓርማ ስለሆነ ነው። በመላው ዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅና ዛሬም ተፈልጎ ሊገኝ በማይችል ልዩ፣ ድምቀትና ውበት የምናከብረው በመኾናችንም በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎን ቀልብ (ስሜት) ከመላው የዓለም መዓዝናት ለመሳብ በቅተናል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መዝገብ በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ሊመዘገብም መቻሉ የክብረ መስቀሉ መዓዛ ዓለሙን ምን ያህል እያወደና እየማረከው መሆኑን ያመለክታል።
                                       ሐ. መስቀሉን የምናከብረው እንዴት ነው?
መስቀሉን በላዩ ላይ ተሰቅሎ ያከበረውና የቀደሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ይታወቃል። እኛ መስቀሉን እናከብራለን ስንል ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ባደረገው ቤዛነት የፈጸመልንን የማዳን ሥራ እንመሰክራለን ማለታችን ነው። በዓል የምንለውም ይህንኑ ምስክርነት በልዩ ልዩ መንገድ የምንገልጽበትን ዕለት ማለታችን ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህንን ምስክርነት ለመስቀሉ እንዴት እንደሚሰጡ እንደሚከተለው እናያለን።

  ይቀጥላል……………………………..

በዓለ መስቀል

 

    በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው (ከአሜሪካ )

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን በዓል የምታከብረው መስከረም ፲፯ እና መጋቢት ፲ ቀን ነው። እነዚህም አይሁድ በክፋት ቀብረው ሠውረውት የነበረውን መስቀል ለማግኘት ቁፋሮ የተጀመረበት እና መስቀሉ የተገኘበት ዕለታት ናቸው። ክቡር መስቀሉ ከክርስቲያኖች ተሰውሮ የኖረው ለሦስት መቶ ዓመታት ነው።
  ክቡር መስቀሉ እንዴት ሊጠፋ ቻለ?
መስከረም ፲፮ እና ፲፯ የሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር፦ በክፋት የተመሉ አይሁድ፥ በጌታ መስቀል እና መቃብር ምክንያት ይፈጸሙ የነበሩትን አያሌ ተአምራት አይተው በምቀኝነት መነሣሣታቸውን ይተርካል። አይሁድ በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ እስከ ፷፬ ዓ.ም ድረስ ምንም ኃይል አልነበራቸውም። ከ፷፬ ዓ.ም በኋላ ግን ራሳቸውን ከሮማውያን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በጀመሩት ዓመጽ ኢየሩሳሌምን ሙሉ በሙሉ ተቈጣጠሩ።
በዚህን ጊዜ ክርስቲያኖቹን ወደ ጌታ መስቀል እና መቃብር እንዳይቀርቡ ከልክለው ቦታውን የቆሻሻ መድፊያ አደረጉት። ከብዙ ጊዜ በኋላ ሥፍራው ትልቅ ጉብታ ሆኖ ከቦታው ጋር ተመሳሳለ። ከዚህም ጋር እስራኤል በየጊዜው ይማርኩ ስለነበር፥ ከምርኮ ሲመለሱም የከተማዪቱ መልክ ስለሚለዋወጥባቸው መስቀሉ የተቀበረበትን ትክክለኛ ጉብታ መለየት አልተቻለም። በተለይም ከ፻፴፪ – ፻፴፭ ዓ.ም በተደረገው ጦርነት ኢየሩሳሌም ፈጽማ ጠፍታ ነበር። ዳግመኛም ንጉሥ ሐድርያን በ፻፴፭ ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን በአዲስ ፕላን በመሥራቱና በጎልጎታ የቬነስን መቅደስ በመገንባቱ ክርስቲያኖቹ ምንም ማድረግ አልተቻላቸውም ነበር። ያን ጊዜ ጎልጎታ ከከተማዋ ውጪ ነበር፥ ዛሬ ግን በአሮጌዋ የኢየሩሳሌም ከተማ ክልል ይገኛል።
  መስቀሉ እንዴት ሊገኝ ቻለ?
ክቡር መስቀሉን ፈልጋ ያገኘችው የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ናት። ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች ሙሉ ነፃነት የሰጠ ደገኛው የሮም ንጉሥ ነበር። ከዚያ በፊት ምንም ነፃነት አልነበራቸውም።ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች የሰጣቸው መብት፦
፩ኛ ቤተ ክርስቲያንን ከግብር ነፃ አደረጋት።
፪ኛ፦ ከመንግሥት ገቢ ለቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ድርሻ ሰጣት።
፫ኛ፦ ዕለተ እሑድ የክርስቲያኖች የበዓል ቀን በመሆኗ በግዛቱ ሥራ እንዳይሠራ በ፫፻፳፩ ዓ.ም አወጀ።
፬ኛ፦ ለቤተ ክርስቲያን ኑዛዜ የመቀበልና ውርስ የመውረስ መብት ሰጣት።
፭ኛ በክርስቲያኖች መካከል ለሚፈጠሩ አንዳንድ አለመግባባት፥ ወንጀል ነክ ላልሆነ ጉዳይ ለኤጲስ ቆጳሳት የዳኝነት ሥልጣን ሰጣቸው።
፮ኛ፦ ክርስትና የአገሩ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አደረገ።
በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን የወንጌልን የመዳን መልእክት እያወጀች ሐዋርያዊ ጉዞዋን እንድትቀጥል ያደረገ ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ ነው። ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ይህን ያደረገበት ምክንያትም በመስቀል ምልክት የተደረገለት ተአምር ነበር። ይኸውም የሮምን የምዕራቡን ክፍል ይገዛ የነበረው ማክሴንዲዮስ የጦር ኃይሉን ባዘመተበተት ጊዜ፥ እርሱም በበኩሉ «ምታ ነጋሪት፥ ክተት ሠራዊት»ብሎ ለጦርነት ተዘጋጀ። ገና በዝግጅት ላይ እንዳለም፦ «በዚህ ድል ታደርጋለህ፤» የሚል በመስቀል ቅርጽ የተጻፈ ጽሑፍ በጠፈረ ሰማይ አየ። በዚህን ጊዜ፦ ሠራዊቱ በፈረሱ አንገት፥ በጋሻው እምብርት መስቀላዊ ቅርጽ እንዲያደርግ አወጀ።
ሮምን ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ መግዛት የጀመረው ከዚህ በኋላ ነበር ።ከዚያ በፊት ለአርባ ዓመታት ለአራት ተከፍላ በኋላም ለሁለት ተከፍላ ትተዳደር ነበር። ጦርነቱም በመስቀሉ ኃይል ጠላቶቹን ድል አድርጎ ተመለሰ እናቱ ንግሥት ዕሌኒ በልጇ ዘመን የተገ   ኘውን የክርስትና ነፃነት ተጠቅማ በ፫፻፳፯ ዓ.ም. ክቡር መስቀሉን ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች። በዚያም ጉብታ የሆነውን ሥፍራ ሁሉ በማስቆፈር ብዙ ብትደክምም መስቀሉን ለማግ ኘት አልቻለችም። በዚህን ጊዜ ኪራኮስ የተባለው አረጋዊ፦ «ደመራ አስደምረሽ፥ ዕጣን አፍስሰሽ፥ ብታቀጣጥዪው ጢሱ ይመራሻል፤» ባላት መሠረት ሳትጠራጠር አደረገችው። የዕጣኑ ጢስ መስቀሉ ከተቀበረበት ጉብታ ላይ እንደ ቀስተ ደመና ተተክሎ በጣት ጠቅሶ የማሳየት ያህል አመለከታት።
ቁፋሮ ውም መስከረም ፲፯ ተጀምሮ መጋቢት ፲ ተፈጸመ። የተገኙት ሦስት መስቀሎች ስለነበሩ የክርስቶስን መስቀል በተአምራቱ ለዩት። ዕውር አበራ፥ አንካሳ አረታ፥ ለምጽ አነጻ፥ ሙት አስነሣ። ንግሥቲቱም ያን ተአምራትን የሚያደርግ ቅዱስ መስቀል የከበረ ቤተ ክርስቲያን አሠርታ በክብር እንዲቀመጥ አደረገች።
መስቀል፤ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ተላልፎ በመሰጠት ቅዱስ ሥጋውን የቆረሰበት፥ ክቡር ደሙንም ያፈሰሰበት ነውና ሃይማኖታዊ ትርጉም አለው። መሰቀል ድኅነታችን የተፈጸመበት (መዳናችን የተረጋገጠበት) ነው «ኢየሱስም ሆምጣጣውን ከተቀበለ በኋላ ተፈጸመ፥ አለ»ይላል (ዮሐ፲፱፥፴) በመስቀል ላይ የተፈጸመው ድኅነታችን (መዳናችን) ነው። ይኸውም የዕለት ፅንስ ሆኖ በማኅፀነ ድንግል ማርያም የጀመረውን የማዳን ሥራ ነው(ሉቃ. ፩፥፴፩)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «በእርሱም እንደ ቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፥ ኃጢአታችንም ተሠረየልን።» ብሏል። መድኃኒት ከድንግል ማርያም መወለዱን ለእረኞች አስቀድመው የሰበኩት ቅዱሳን መላእክት ናቸው(ሉቃ. ፪፥፲፩)መርገመ ሥጋ መርገም ነፍስን የተወገደበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የተወገደበት ነው አዳምና ሔዋን ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፋቸው የወደቀባቸው የሥጋና የነፍስ መርገም ለሰው ልጅ በጠቅላላ ተርፎት ነበር። «ነገር ግን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከአዳም እስከ ሙሴ (እስከ ክርስቶስ) የበደሉትንም ያልበደ ሉትንም ሞት ገዛቸው።» ይላል( ሮሜ ፭፥፲፬) ሙሴ ለክርስቶስ ምሳሌ ነው። በኦሪቱ እንደተጻፈው በእንጨት ተሰቅለው የሚሞቱ ርጉማን ነበሩ( ዘዳ.፳፩፥ ፳፫)
ይህንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው፥ ተብሎ ተጽፎአልና፤ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ (መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን ያመጣብንን ኃጢአት ለመደምሰስ ተላልፎ በመሠዋት) ከሕግ እርግማን ዋጀን።» በማለት ገልጦታል (ገላ. ፫፥፲፫) ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።»ብሏል (፩ኛ ጴጥ. ፪፥፳፬)

ዲያብሎስ የተሸነፈበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል፤ ዲያብሎስ የተሸነፈበት ነው ጥንተ ጠላታችንን (ገነትን ያህል ርስት፥ እግዚአብሔርን ያህል አባት ያሳጣንን ዲያብሎስን) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድል ያደረገልን በመስቀሉ ነው።«ጥልን በመስቀሉ ገደል፤» ይላልና። (ኤፌ.፪፥፲፮) ጥል የተባለው ለሰውና ለእግዚአ ብሔር መጣላት ምክንያት የሆነ ዲያብሎስ ነው። እኛም በኃይለ መስቀሉ ድል እያደረግነው የምንኖር ሆነናል።
   የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ቅዱስ መስቀል
መሰቀል የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ነው፤የጥል ግድግዳ የተባለው ኃጢአት ነው። እርሱም ሰውና እግዚአብሔ ርን ለያይቷቸው ኖሯል። «በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሠውሮታል።» ይላል (ኢሳ.፶፱፥፪) ይህ ከእግዚአብሔር ለያይቶን እግዚአብሔርን ሰውሮብን የኖረ የጥል ግድግዳ (በዲያብሎስ ምክር የተሠራ ኃጢአት) የፈረሰው በመስቀል ላይ በተፈጸመ የክርስቶስ ቤዛነት ነው። «በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው አፈረሰ፤» እንዲል (ኤፌ ፪፥፲፭)
ዕርቅ የተፈጸመበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል ዕርቅ የተፈጸመበት ፣ሰውና እግዚአብሔር የታረቁት በመስቀል ላይ በተፈጸመ ካሳ ነው። ሰውና እግዚአብሔር በመታረቃቸው ነፍስና ሥጋ፣ሰውና መላእ ክት፣ሕዝብና አሕዛብም ታርቀዋል። እኛ በበደልን እርሱ ክሶ (የደም ካሣ ከፍሎ ) ታርቆናል።«ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ታረቅን።»ይላልና (ሮሜ ፭፥፲፣፪ኛ ቆሮ. ፭፥፲፰፣ኤፌ.፪፥፲፮)በሌላ በኩል ደግሞ «ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማይ ላሉ ሰላምን አደረገ።» የሚልም አለ (ቈላ. ፩፥፳)
አምላካዊ ይቅርታ የተገኘበት ነው፤«አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።» በማለት ገር ፈው የሰቀሉትን በቃሉ ይቅር ብሎአቸዋልና (ሉቃ.፳፫፥፴፬) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦በሞቱ የሰውን ዘር በጠቅላላው ይቅር እንዳለው ሲናገር፦«አሁን ግን በፊቱ ለመቆም የተመረጣችሁና ንጹሓን፥ ቅዱሳንም ያደርጋችሁ ዘንድ በሥጋው ሰውነት በሞቱ ይቅር አላችሁ።»ብሏል (ቈላ.፩፥፳፪)
አምላካዊ ሰላም የተሰጠበት የተገኘበት ቅዱስ መስቀል
ነቢዩ ኢሳይያስ፦«ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም (ወልድ) ተሰጥቶናልና፥ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።»በማለት ትንቢት የተናገረለት አምላክ ፍጹም ሰላምን የሰጠን በመስቀሉ ላይ በፈጸመው ቤዛነት ነው።(ኢሳ.፱፥፯) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦«መጥቶም ቀርበን ለነበርነው ሰላምን፥ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን ሰጠን።» ብሏል( ኤፌ ፩፥፲፯)
      የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት ነው። ጌታችን የማታ ተማሪ የነበረውን ኒቆዲሞስን ሲያስተምረው፦ «እግዚአብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፤»ብሎታል።( ዮሐ.፫፥፲፮) ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ የጻፈውን የጌታችን ትምህርት መሠረት አድርጎ፦ «በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ላይ ታወቀ፥ በእርሱ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። የእግዚአብሔርም ፍቅሩ ይህ ነው፥ እርሱ ወደደን እንጂ እኛ የወደድነው አይደለንም፥ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ልጁን ላከው።»ብሏል (፩ኛ ዮሐ ፬፥፱-፲፩)

                                                                               የገነት በር የተከፈተበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል የገነት በር የተከፈተበት ነው፡፡ ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው፥ ድኅነተ ምእመናንንም በመስቀል ላይ የፈጸመው ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተዘግታ የነበረችውን ገነትን ለመክፈት ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ፥ በቀኙ ተሰቅሎ፥ «አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ»እያለ ሲማጸነው የነበረውን ወንበዴ፦«እውነት እልሃልሁ፥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ» ብሎታል(ሉቃ. ፳፫፥፵፪-፵፫)

  የምንመካበት ቅዱስ መስቀል
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦«ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት (ዓለም በእኔ ዘንድ ሙት የሆነበት)፥ እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት (እኔም በዓለም ዘንድ ሙት የሆንኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ፤»ብሏል፡፡(ገላ. ፮፥፲፬)
በመሆኑም ዓለምና ቅዱስ ጳውሎስ በጌታ ደም ላይ በተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን እና በደሙ በጸናች ወንጌል ምክንያት ተለያይተዋል። አንዳቸው ለአንዳቸው ሙት ናቸው። ዓለም ሕያው የሆነችልን፥ እኛም ሕያው የሆንላት የሚመስለን የዓለም ፈቃድ ፈጻሚዎች ከቅዱስ ጳውሎስ ልንማር ይገባል። ዓለም ታልፋለች፥ እኛም ከእሷ እንለያለንና።
                                                                                  ከአጋንንት የምንድንበት ቅዱስ መስቀል
በክርስቶስ ቅዱስ መስቀል ከአጋንንት ጦር እንድናለን ቅዱስ ዳዊት በትንቢት፦ «ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፥ ከቀስት ፊት (ከአጋንንት ጦር) ያመልጡ ዘንድ ወዳጆችህም እንዲድኑ።» ያለው ስለ መስቀል ነው። (መዝ.፶፱፥፬) በመሆኑም በመስቀል ምልክት አማትበን፥ ከአጋንንት ፈተና እንድናለን። መስቀል ኃይላችን ነው መስቀልን በእጅ መጨበጥ፥ በአንገት ማንጠልጠል፥ መሳለም በዓለም ዘንድ ሞኝነት ነው ለእኛ ለክርስቲያኖች ግን ድኅነት የተረጋገጠበት ነው። ለዚህም ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና» በማለት ያስተማረን ፡፡(፩ኛቆሮ.፩፥፲፰)
በመሆኑም በቀራንዮ በመስቀል ላይ አንድ ጊዜ የተገለጠ ኃይለ እግዚአብሔር እስከ ዘለዓለሙ አይለየንም። በመሆኑም ለቅዱስ መስቀሉ እንሰግዳለን። ቅዱስ ዳዊት፦ «እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን።» በአለው መሠረት የጌታችን እግሮች በመስቀል ላይ፥ ያውም በቀኖት ላይ ስለቆሙ ለመስቀሉ እንሰግዳለን። መስቀሉን በደሙ ቀድሶታልና፥ ለመስቀሉ የሚገባውን ክብር እንሰጣለን። እግዚአብሔር በረድኤት በደብረ ሲና ራስ በቆመ ጊዜ፥ «ወደዚህ አትቅረብ፥ የቆምክባት ሥፍራ የተቀደሰች ናትና፥ ጫማህን ከእግርህ አውጣ፤» በማለት ሙሴን አስተምሮታል፡፡(ዘዳ.፫፥፭)
እንኳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ይቅርና የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የቆመበትን መሬት፥ የተቀደሰ በመሆኑ፦«አንተ የቆምክበት ሥፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግር አውልቅ።» በማለት ኢያሱን ሲያዘው እርሱም የታዘዘውን እንዲደረግ ተረድተናል (ኢያ.፭፥፲፭) እንግዲህ መሬቱን፥ አፈሩን የቀደሰ አምላክ ፦ ሥጋውን የቆረሰበትን፥ ደሙን ያፈሰሰበትን፥ ነፍሱንም አሳልፎ የሰጠበትን መስቀል አልቀደሰውም ለማለት እንዴት ይቻላል? ፈጽሞ አይቻለም።ንግሥት ዕሌኒ በብዙ ድካም ከወርቅ ዙፏኗ ወርዳ ከአፈር ላይ ተቀምጣ፥ቆፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታለች።ዛሬ በእኛ ዘመን የተቀበረው ዳግም በመስቀሉ ያ የተገኘው ፍቅርና ሰላም ነው።
ፍቅር በጥላቻ፥ሰላም በጦርነት፥አንድነት በመለያየት፥እምነት በክሕደት፥ መንፈሳዊነት በሥጋዊነት የሕዝቦች ውሕደት በዘረኝነት ቆሻሻ ተቀብሮአል።ይህንን ቆፍረን ካወጣን ያን ጊዜ የዘመኑ ዕሌኒዎች እንሆናለን። መስቀሉን ተሸክመን በጥላቻና በዘረኝነት ቆሻሻ የተቀበርንም በቅድሚያ ራሳችንን ቆፍረን እናውጣ፥ ለብዙዎችም እንቅፋት አንሁን።ዘመኑን ከተቀበርንበት የምንወጣበት ያድርግልን።
የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፥ የመስቀሉ በረከት አይለየን፥ አሜን።