‹‹በመስቀሉ አርኀወ ገነተ፤ በመስቀሉ ገነትን ከፈተ›› ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ

በመ/ር ለይኩን አዳሙ ባሕር ዳርማእከል
የመጨረሻው …ክፍል -፬
፰.መስቀል በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ሀገራችን ከቤተ እስራኤል ቀጥላ እግዚአብሔርን በማምለክ ከሌሎቹ ሀገራት ቀዳሚ እንደሆነች ታሪክ ያስረዳል፡፡ ሌሎቹ ሀገራት ለጣዖት ሲሰግዱ ሲንበረከኩ መሥዋዕት ሲሠው ኢትዮጵያ ሀገራች ግን በሦስቱም ሕግጋት (በሕገ ልቡና፣በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል) እግዚአብሔርን በማምለክ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እያቀረበች ብሉይን ከሐዲስ አንድ አድርጋ ይዛ ኑራለች፡፡ ወደ ፊትም በዚህ መልካም ሥራዋ ጸንታ ትኖራለች፡፡ ኢትዮጵያ አምልኮተ ጣዖትን ተጸይፋ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ የምትማጸን በመሆኗ እስትንፋሰ እግዚአብሔር የኾነው ቅዱስ መጽሐፍ ክብሯን ከፍ በማድረግ ከ፵ ጊዜ በላይ የከበረ ስሟን ለዓለም ሕዝብ ያስተዋውቃል፡፡
ኢትዮጵያ ባላት የሃይማኖት ጽናት የክርስቲያን ደሴት፣ ሀገረ እግዚአብሔር፣ ምዕራፈ ቅዱሳን ተብላ ትጠራለች፡፡ የክርስቲያን ደሴት ሀገረ እግዚአብሔር ከመባሏም በላይ የእግዚአብሔር ቸርነት ያልተለያት የበረከትና የረድኤት ሀገር ናት፡፡ የበረከት ሀገር የክርስቲያን ደሴት እንድትባል ያደረጋት የቃል ኪዳኑን ታቦትና የዓለም ቤዛ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ ዓለሙን ያዳነበትን ሥጋውን የቆረሰበትን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበትን ግማደ መስቀሉን ይዛ በመገኘቷና ባላት የሃይማኖት ጽናት ነው፡፡

፱ .ግማደ መስቀሉ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ መጣ?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የመጣው በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ታሪክ ይናገራል የመጣበትም ምክንያት በሀገራችን በተደጋጋሚ ረኀብ በሽታ ተክሥቶ ስለ ነበር በዘመኑ የነበሩት ንጉሥ ዳዊት ረኀብና በሽታው እንዲቆም ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ችግሩ ሊወገድ የሚችለው የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ሲመጣ እንደሆነ በራእይ ነገራቸው፡፡ ንጉሡም ወደ ኢየሩሳሌም ቅድስት ዕሌኒ አስቆፍራ ካስወጣችው ከጌታ ግማደ መስቀል ከፍለው እንዲልኩላቸው ለገጸ በረከት የሚሆን ብዙ ወርቅ እና አልማዝ አስጭነው ወደ ኢየሩሳሌሙ ፓትርያሪክ ላኩ፡፡
ፓትርያሪኩ መልእክቱን ተቀብሎ የመስቀሉን ክፋይ አክሊለ ሦክ ቅዱስ ሉቃስ የሣላትን የእመቤታችን ምስለ ፍቁር ወልዳን ሥዕለ አድኅኖ ጨምረው ላኩላቸው፡፡ መልክእተኞችም ይህን ተቀብለው የሲና በረሃ አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከመግባታቸው በፊት የክብር አቀባበል ሊያደርጉላቸው ሲሄድ የተቀመጡበት ባዝራ ጥሏቸው በክብር ዐረፉ እርሳቸው ቢሞቱም በኢትዮጵያውያን ጀግኖችና በልጃቸው በዘርዐ ያዕቆብ ጥረት በጌታ ፈቃድ ግማደ መስቀሉ ወደ ሀገራች ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል፡፡ መጥቶም የኢትዮጵያን ምድር ተዟዙሮ ከባረከ በኋላ መቀመጫውን እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራእይ ገለጸላቸው ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አስቀምጥ›› ካላቸው በኋላ አፈላልገው ቦታውን አግኝው አሁን ካለበት ቦታ ላይ በወሎ ክፍለ ሀገር በግሸን አንባ ወይም ደብረ ከርቤ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በክብር አስቀምጡት፡፡ ከዚያ ዕለት ጀምረው ብዙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቦታው ድረስ ሄደው መስቀሉን ተሳልመው ቦታውን ረግጠው በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ሲያገኙ ኖረዋል ወደ ፊትም ይኖራሉ፡፡

                                                         ፲. የደመራው ምሥጢር
ደመረ ሰበሰበ አከማቸ አንድ ላይ አደረገ በአንድነት አቆመ ማለት ሲሆን ደመራ ማለት ደግሞ መደመር አንድ ማድረግ ማቆም ማለት ነው፡፡ ይህም ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ያሳየናል፡፡
አንደኛ በዓለ መስቀልን ለማክበር ከአራቱም አቅጣጫ በአንድነት ከታናሽ እስከ ታላቅ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የተሰበሰቡትን የቆሙትን ኦርቶዶክሳውያን ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለመስቀል በዓል ከመድረሱ ፊት ከጫካ ተቆርጦ ተለቅሞ ተሰብስቦ መጥቶ እርጥቡ ከደረቁ፣ ደረቁ ከእርጥቡ በአንድነት ተሰብስቦ የሚቆመውን የደመራ እንጨት ያመለክታል፡፡
በእኛ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ደመራ የሚከመርበት ምክንያት ቅድስት ዕሌኒ የተቀበረውን መስቀል ከማውጣቷ በፊት እንጨት ከምራ ወይም ጨምራ ስለነበረ ያን አብነት በማድረግ በዓለ መስቀልን ለማክበር እንጨት እንጨምራለን እንከምራለን፡፡ በደመራው ፊት ለፊት ካህናቱ ጸሎተ አኮቴት ጸሎተ ምሕላውን ከጨረሱ በኋላ በዲያቆኑ ምስባኩ ከተሰበከ የዕለቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላና ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቶ የተደመረውን ደመራ ሊቃውንቱ ‹‹መስቀል አብርሃ በከዋክብት አሠርገወ ሰማየ እምኵሉሰ ፀሐየ አርአየ እያሉ ደመራውን ይዞራሉ፡፡ ምእመናኑም ‹‹እዮሃ አበባየ መስከረም ጠባየ›› እያሉ ምእመናን በዕልልታና በዝማሬ ደመራውን እየዞሩ በተመረጡ አባቶች ይለኮሳል፡፡ የደመራው እንጨት ነዶ ከአበቃ በኋላ የተጸለየበትና በአባቶች የተባረከ ስለሆነ ምእመናኑ ወደ ቤታችው ይወስዱታል ሰውነታቸውን ይቀቡታል ልጆቻቸውን ከክፉ መንፈስ እንዲ ጠብቅላቸው ከአንገታቸው ላይ ያሥሩታል፡፡
    ፲፩. መስቀሉ ለኦርቶዶክሳውያን
ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔርን መስቀል ያላመኑበት ሰዎች አይጠቀሙበትም፡፡ የምናምንበት እኛ የተዋሕዶ ልጆች ግን ከሕይወታችን ጋር የተሳሰረ ከደማችን ጋር የተዋሐደ በልቡናችን ውስጥ ሥር የሰደደ ነው፡፡ ይህንን ስንልም ከአእምሮአችን አንቅተን ከልቡናችን አመንጭተን አይደለም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገን ነው እንጂ፡፡ ስለሆነም፡-
     ፩ኛ. ቅዱስ መስቀል ለኦርቶዶክሳውያን አጥር ነው፡-አጥር ከዘራፊ ከቀጣፊ ከወራሪ እንደ ሚከለክል ሁሉ ቅዱስ መስቀልም ከሰይጣን ደባ ከአጋንንት ድብደባ የሚከላከል አጥር ነው፡፡ ይህንም ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ሲል ይገልጻል ‹‹መስቀል ምጽንዓተ ቅጽርነ መስቀል ፀሐይ ሠርጐ ነገሥት ሠናይ፤ መስቀል የአንባችን ማጽኛ አጥር ነው መስቀል የተወደደ የነገሥታት ሽልማት ነው፡፡ መስቀል ፀሐይ ነው፡፡›› በማለት ለሰው ልጆች ሁሉ አጥር መሆኑን ገልጧል፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የመስቀሉን አጥርነትና ኃይል አምነን እንዲህ በማላት ዘወትር ይማጸናሉ ‹‹መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንዕነ መስቀል ቤዛነ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ›› በማለት መስቀሉ አጥር ቅጥር መሆኑን እንመሰክራለን፡፡
    ፪ኛ. ቅዱስ መስቀል ለኦርቶዶክሳውያን መመከቻና ጠላትን ማጥቂያ ነው፡- አባቶቻችን ጠላት ሲነሣባቸው ፈተና ሲገጥማቸው በመስቀሉ ኃይል ተመክተው ድል ያደርጉ ነበር፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ዕንዚራ የሆነው ቅዱስ ያሬድ የቅዱስ ዳዊትን ቃል መነሻ አድርጎ በዜማ ድርሰቱ ላይ እንዲህ ሲል ይዘምራል ‹‹ብከ ንወግኦሙ ለኵሎሙ ፀርነ ይቤ ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት በእንተ ዝንቱ ዕፀ መስቀል ዘተሰቅለ ዲቤሁ ቃለ አብ ወበስምከ ነኀሥሮሙ ለእለ ቆሙ ላዕሌነ ወካይበ ይቤ ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመ ያምስጡ እምገጸ ቅስት ወይድኃኑ ፍቁራኒከ ወንሕነኒ ንትፈሣሕ ዮም ወንግበር በዓለ በዛቲ ዕለት፤ዳዊት በትንቢት መንፈስ ጠላቶቻችን ሁሉ በአንተ እንወጋቸዋለን በዚህ ዕፀ መስቀል ላይ የተሰቀለ የአብ አካላዊ ቃል ነው፡፡በላያችን ላይ የቆሙትን በስምህ እናጎሳቁላቸዋለን ዳግመኛም ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኻቸው ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ እኛም በዚች ዕለት ደስ ይበለን በዓልንም እናድርግ አለ›› በማለት እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ለሚያመልኩ የጠላት መመከቻና ማጥቂያ እንደሆነ አስረግጦ ተናግሯል፡፡
በገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ከመክስምያኖስ ጋር ጦርነት በገጠመ ጊዜ ሊሸነፍ ሳለ በሰማይ በፀሐይ ብርሃን ላይ ተቀርጾ በራእይ ‹‹በዚህ መስቀል ጠላትህን ድል ታደርጋለህ›› የሚል ጽሑፍ አነበበ ቆስጠንጢኖስም ሳይጠራጠር በመስቀሉ ኃይል አምኖ በፈረሱና በበቅሎዎቹ ልጓም በጦር መሣሪያው በሠራዊቶቹ ልብስ ላይ እንዲሁም በሰንደቅ ዓላማው ላይ አስቀርጾ ቢገጥም መክስምያኖስና ሠራዊቶቹን ድል አድርጓቸዋል፡፡ ለብዙ ዘመናት ተከፋፍላ ትኖር የነበረችውን ሮምንም አንድ አደርጎ በመልካም አስተዳደር መርቷታል፡፡ እኛም የዚህ ዓለም ገዥ የሆነውን ጠላታችን ዲያብሎስ እና ሠራዊቱን በመስቀሉ ኃይል ድል እንድናደግ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
   ፫ኛ. ምልክታችን ወይንም መለያችን ነው፡-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታታይ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናን የሆነው ሁሉ ከሌላው እምነት የሚለየው በመስቀሉ ምልክትነት ነው፡፡መስቀል ለኛ ለተዋሕዶ ልጆች የማንነታችን መለያ የሕይወታችን አሻራ ነው፡፡ መስቀል መለያ ወይም ምልክት ይሆነን ዘንድ የሰጠን እግዚአብሔር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ‹‹ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው›› (መዝ ፶፱÷፬) በመስቀሉ ምልክትነት ከዓለም ሕዝብ የለየን ለአንድ ዓላማ የጠራን እግዚአብሔር ነው፡፡ የእርስዎ መለያ ምልክት ምንድን ነው? መስቀሉ ወይስ ሌላ?
    ፬ኛ. መስቀል ሰላማችን ነው፡– ሰላም ስምምነት አንድነት ኅብረት ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ ሰላም የሰው ልጅ ወጥቶ ሊገባ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ሲፈጥረው በሰላም በስምምነት በአንድነት መኖር እንዲችል አድርጎ ነው፡፡ ይሁንም እንጂ የሰው ልጅ ትእዛዘ እግዚአብሔርን በማፍረሱና ከእግዚአብሔር በመለየቱ ለ፭ ሺህ ፭፻ ዘመን ሰላሙን አጥቶ በመቅበዝበዝ ኑሯል፡፡ የሰው ልጆች መቅበዝበዝ ያለ ሰላም መኖር ያሳዘነው ጌታ ወደ ዚህ ዓለም መጥቶ የሰላምን ወንጌል አስተምሮ የተበተነውን ሕዝብ ሰብስቦ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የተነጠቁትን ሰላም ለአዳምና ለልጆቹ መለሰላቸው፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ‹‹በመስቀሉ ሰላምን አደረገ›› ሲል የዘመረው በመስቀሉ ሰላምን ኅብረትን አንድነትን ሕይወትን አግኝተናል በመሆኑም ቅዱስ መስቀል ለኛ ለተዋሕዶ ልጆች ሰላማችን ነው(ቆላ. ፬÷፲፱ ኤፌ.፪÷፲፫-፲፰)
፲፪.መስቀል ለምን እንሳለማለን ?
ሐዋርያዊት ጥንታዊት፣ ዓለም ዓቀፋዊት ኵላዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ደመ ወልደ እግዚአብሔር የፈሰሰበትን ሥጋ ወደሙ የተፈተተበትን ከዲያብሎስ ወጥመድ አምልጠን ነጻ የወጣንበት ከባዱን የዲያብሎስን ሸክም ያቀለልንበት ቅዱስ መስቀልን አክብረን እንድንሳለመው ዘወትር ታስተምራለች፡፡ የተወዳዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የተቀደሰውን ነገር አክብረን ብንሳለመው ብንዳስሰው በረከት እንደምናገኝና እንደምንቀደስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡ ‹‹ሁሉንም ትቀድሳችዋለህ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱሳን ይሁናሉ›› (ዘፀ.፴÷፳፱) በማለት ያስረዳል፡፡ እኛም በቅዱስ መስቀሉ ላይ አድሮ እግዚአብሔር እንደሚቀደሰንና እንደሚባርከን አምነን እንሳለመዋለን፡፡ በአጠቃላይ መስቀል የምንሳለመው ስለ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች ነው፡-
፩. ሥርየተ ኃጢአትን ለመቀበል፣
፪. መንፈሳዊ ክብርንና ፀጋን ለመቀበል፣
፫. ለመስቀሉ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ ስንል መስቀል እንሳለማለን፡፡

፲፫.በመስቀል መባረክ ወይም መሳለም የተጀመረው መቼ ነው?
በመስቀል አምሳል መባረክ ወይንም መሳለም የተጀመረው በዘመነ ኦሪት ወይም በብሉይ ኪዳን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሙሴናእና ካህኑ አሮን ይባርኩ እንደነበረና እግዚአብሔርም ቡራኬያቸውን ተቀብሎ ሕዝቡን በማያልቅበት በረከት ይባርክ እንደ ነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ ‹‹ስትባርካቸውም እንዲህ በላቸው እግዚአብሔር ይባርክህ ይጠብቅህም—–እኔምእባርካቸኋለሁ›› ‹‹አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ ባረካቸውም››(ዘሌ.፱÷፳፪) ይላል፡፡ኦሪትን ሊሽር ሳይሆን ሊያጸናት የመጣ ፈጻሜ ሕግ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን ደቀ መዛሙርቱን ሲባርካቸውም በኋላ ወደ ዓለም ለወንጌል አገልግሎት እንደላካቸው ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ ‹‹እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጁንም አንሥቶ ባረካቸው››(ሉቃ.፳፬÷፶) አባቶቻችን ካህናትም እግዚአብሔር ለሙሴ እና ለአሮን የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩ እንዲህ በሏቸው በተባሉት የቡራኬ ቃል መሠረት ይባርኩናል በረከትንም እንቀበላለን፡፡
     ፲፬. በዓለ ቅዱስ መስቀል
ክርስቶስ በወርቀ ደሙ የዋጃት ቤተክርስቲያን ምእመናን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እንዲያገኙ ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ጋር እንዲኖሩ ለቅዱሳን ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት እንዲገልጹ በዓላትን ሰፍራ ቆጥራ ይዛ በየወሩና በየዓመቱ መታሰቢያቸውን በላቀና በደመቀ ሁኔታ ታከብራለች፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱና ዋነኛው ክርስቶስ ተሰቅሎ ፍቅሩን ለዓለም ሕዝብ የገለጠበት የከበረ ሥጋውንና ደሙን ለልጆቹ ያደለበት መስከረም ፲፯ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የመስቀል በዓል ተጠቃሽ ነው፡፡
ሀገሯ ሀገረ እግዚአብሔር ሕዝቧ ሕዝበ እግዚአብሔር ምድሯ ምዕራፈ ቅዱሳን በሆነችው በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በሊቃውንቱ ያሬዳዊ ዝማሬ በእናቶች ዕልልታ በወጣቶች ሆታ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ዝማሬ ተውበውና ደምቀው ከሚከበሩ መንፈሳዊና ዓመታዊ በዓላት መካከል አንዱ በዓለ ቅዱስ መስቀል ነው፡፡
ይህን መንፈሳዊ በዓል ለማክበር ኦርቶዶክሳውያን እንደ ሰማያውን መላእክት ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው በልብሳቸውም መስቀሉን አስጠልፈው ለቅዱስ መስቀል ያላቸውን ፍጹም የሆነ ፍቅር ይገልጻሉ፡፡ ይህን በዓል ለማክበር ነገሥታት ከዙፋናቸው ጳጳሳት ከመንበራቸው መነኮሳት ከገዳማቸው መምህራን ደቀመዛሙርት ከጉባኤ ቤቶቻቸው ካህናት ዲያቆናት ምእመናን በአንድነት በአራቱም መዓዝናት ወጥተው እንደ ቅድስት ዕሌኒ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነውና ታምነው በመስቀሉ ፍቅር ተማርከው በፍጹም ደስታ በየዓመቱ በአደባበይ ያከብሩታል፡፡
ምእመናን ይህን በዓል ሲያከብሩ በዓይነ ሕሊና የመስቀሉን ቅርጽ ብቻ ሳይሆን በመስቀል ላይ ለሰው ልጆች ሲል በችንካር የተቸነከረ ደሙን ያፈሰሰ የክርስቶስን ውለታ በዓይነ ሕሊና ስለው በአዕምሯቸው ቀርጸው በልቡናቸው አንግሠው አንደበታቸውን በዝማሬ ያከብሩታል፡፡ ቅዱስ መስቀል በኢትዮጵያ ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ይታሰባል፡፡ ምንም እንኳ መስቀል የሌለበት ቤተ ክርስቲያን ባይኖርም በተለይ በቅዱስ መስቀል ስም በታነፁት አብያተ ክርስቲያናት ዘወትር ክብረ መስቀል ይነገራል፡፡
ከዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላትም አንዱ ቅዱስ መስቀል ነው፡፡ይሄውም በየዓመቱ መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት ከ፪፻ ዓመት በላይ ተቀበሮ ከኖረ በኋላ ተቆፍሮ የወጣበትን ምክንያት በማድረግ በከተማም ይኹን በገጠር በላቀና በደመቀ ሁኔታ ይከበራል፡፡ግማደ መስቀሉ በተቀመጠበትም በግሸን ደብረ ከርቤ መስከረም ፳፩ ቀን ብዙ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ዜጎች በተገኙበት ይከበራል፡፡ እኛም መስቀሉን አክብረን በመስቀሉ ኃይል አምነን ዲያብሎስን ድል ነሥተን ስለእኛ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተውን ክርስቶስን አምልከን በተዋሕዶ ሃይማኖት ጸንተን የመንግሥተ ስማያት ዜጎች እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡ወለወላዲቱ ድንግል፡ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡

‹‹በመስቀሉ አርኀወ ገነተ፤ በመስቀሉ ገነትን ከፈተ›› ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ

በመ/ር ለይኩን አዳሙ ባሕር ዳር ማእከል
ክፍል -፫
                                                               ፭.ቅዱስ መስቀሉን ፍለጋ
ዕሌኒም ታሪኳን ለውጦ ሕይወቷን አስተካክሎ ለዚህ ክብር እንድትበቃ ኅዘኗን እንድትረሳ ያደረጋትን እግዚአብሔርን እያስታወሰች አይሁድ በምቀኝነት የቀበሩትን ክርስቶስ የተሰቀለበት ገነት የተከፈተበትን ዓለም የዳነበትን ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት ጉድጓድ ለማውጣት አሰበች ልጇ ቆስጠንጢኖስንም ወደ ኢየሩሳሌም ሂጄ የጌታዬን መስቀል ማውጣት እፈልጋለሁና ሠራተኛ ስጠኝ አለችው፡፡ እርሱም ብዙ ሠራዊት ሰጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ላካት፡፡ከእርሷም ጋር የተላኩት ሠራዊት ብዛት ሠላሳ ሺህ ታንከኞች፣ሠላሳ ሺህ ፈረሰኞች ሠላሳ ሺህ ብረት ለበሶች፣ሠላሳ ሺህ፣ሰይፍና ጦር የያዙ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ይህን ድርሳነ መስቀል እንዲህ ሲል ይገልጠዋል ‹‹ወለ ባዕዳንሰ ሠራዊት አልቦሙ ኁልቊ ከመ ከዋከዋክብተ ሰማይ ወከመ ኆፃ ዘንድጋገ ባሕር ብዝኆሙ፤ሌሎች ሠራዊት ብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደ ባሕር አሽዋ ነው››ይላል (ድርሳነ መስቀል ፲፮÷፱)
ብቻዋን ባሕር ውስጥ ተጥላ የነበረች ሴት በሠራዊት ታጅባ ኢየሩሳሌም ገባች፡፡ እርሷም ኢየሩሳሌም እንደ ገባች ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን በፈጸመባቸው ቅዱሳት መካናት እየዞረች ጾም ጸሎት ምሕላ ያዘች፡፡
፮.ቅድስት ዕሌኒ ሱባኤ የገባችባቸው ቦታዎች
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አርአያና ምሳሌ ሊሆነን ከቦታዎች ሁሉ መርጦ አምላካዊ ሥራ የሠራባቸው ድንቅ የሆኑ ቦታዎች አሉ፡፡ አምላካችን ቅዱስ ስለሆነ እርሱ የተናገረው እርሱ የረገጣቸው ቦታዎች ሁሉ ቅድስናን የተመሉ በመሆናቸው በእነዚህ ቦታዎች ሱባኤ መያዝ ደግሞ የተሠወረው እንደሚገለጽለት ቅድስት ዕሌኒ ስለምታውቅ ሱባኤ ይዛለች፡፡ እነዚህም ቦታወችም የሚከተሉት ናቸው፡፡
፩. ክርስቶስ በተወለደበት ቅድስት ቤተ ልሔም ሰባት ቀን፤
፪. ክርስቶስ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ቀን፤
፫. ክርስቶስ ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት በጾመበት በገዳመ ቆሮንቶ ሰባት ቀን፤
፬. ጌታ ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት በደብረ ታቦር ተራራ ሰባት ቀን፤
፭. ጌታ ዓለሙን ለማዳን በተሰቀለበትና መከራ በተቀበለበት ቀራንዮ ሰባት ቀን፤
፮. የአምላክ እናት ድንግል ማርያም በተቀበረችባት በጌቴሴማኒ ሰባት ቀን እና
፯. አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበረባት በጎልጎታ ዐሥራ አራት ቀን ነው፡
በእነዚህ ቦታዎች ላይ ከጾመችና ከጸለየች በኋላ ጎልጎታ ላይ ሕዝበ አይሁድን ሰብስባ ድንኳን አስተክላ ጉባኤ አደረገች የጌታዬ መስቀል የተቀበረበትን አሳዩኝ አለቻቸው፡፡ እነርሱ ግን ተማምለው ስለነበረ ለማሳየት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲሰቅሉት ሲያዳፉት ጲላጦስ “ንጹሕ አነ እምደሙ ለዝ ብእሲ” ባለጊዜ አይሁድ “ደሙ ይኩን ላዕሌነ ወላዕለ ውሉድነ” ብለው ወስነው ነበርና አሁንም መስቀሉን ሲቀብሩት ይህንኑ ውሳኔ አጽድቀው ስለነበር ለማሳየት ፈቃደኛ አልነበሩም፡
ንግሥት ዕሌኒም ማስተማሪያ ይሆኑ ዘንድ መርጣ የተወሰኑትን ቀጣቻቸው፡፡ ሌሎችምንም ተመልሳ አባቶቻችሁ የጌታዬን መስቀል የት ላይ ነው የቀበሩት ንገሩኝ ብላ አጥብቃ ጠየቀቻቸው አይሁድ ግን‹‹ አባቶቻችን መስቀሉን አልቀበሩም እኛም የተቀበረ መስቀል አናውቅም›› በማለት መለሱላት፡፡ እርሷም ክፋታቸውን አይታ በርኀብና በውኃ ጥም ቀጣቻቸው አሁንም እንቢ ሲሏት ከእህል ከውሃ ተከልክላ ሱባኤ ገባች የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾ የከበረ ሰላምታ አቀረበላት፡፡
እርሱንም የመስቀሉን ምሥጢር እያደነቀች አይሁድ ከምን ቦታ እንደቀበሩት ንገረኝ አለችው መልአኩም ‹‹የመስቀሉ ነገር በእኛ በመላእክት ዘንድ ጭንቅ ነው አልተገለጸልንም ሥልጣን የተሰጠው ለአንች ብቻ ነው ነገር ግን ኪራኮስና አሚኖስ የሚባሉ ሽማግሌዎች ታገኛለሽ እነርሱን ጠይቂ እነርሱ ይነግሩሻል›› ብሏት ተሠወረ፡፡  እርሷም ወደ ኪራኮስና አሚኖስ ሂዳ ‹‹መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አሳዩኝ›› በማለት ጠየቀቻችው፡፡ ይህንም ሊቁ በዜማ ድርሰቱ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል ‹‹ትቤሎሙ ዕሌኒ ለኪራኮስ ወለአሚኖስ ንግሩኒ ኀበ ሀሎ መስቀሉ ለወልድ ዋሕድ ኀሠሠት ወተረክበ ዕፀ መስቀል ኅበ ደፈኑ አይሁድ መስቀሎ በቀራንዮ ዘስሙ መካን፤ ዕሌኒ ኪራኮስና አሚኖስ የወልድ ዋሕድ መስቀሉ ያለበትን ንገሩኝ አለቻቸው ስሙ ቀራንዮ በሚባል ቦታ የተሰቀለበትን መስቀል አይሁድ የቀበሩበትን ፈለገች›› በማለት ይገልጻል፤(ድጓ ዘመስቀል)

አረጋዊው ኪራኮስ የቅድስት ዕሌኒን መቸገር አይቶ ‹‹አንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውንም በከንቱ አታድክሚ እንጨት ሰብስበሽ ከምረሽ ዕጣን አፍሽበት በእሳትም አያይዥው የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሸ በዚህም ምልክት አስቆፍሪው ታገኝዋለሽ›› አላት እርሷም ጸሎቷን ወደ እግዚአብሔር ካቀረበች በኋላ አረጋዊ ኪራኮስ እንዳላት ደመራ አስደምራ ዕጣኑን ጨምራ ደመራውን ብታቀጣጥለው የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ላይ ጢሱ ሰገደ፡፡ይህም በእጅ ጠቅሶ እንደ ማሳየት ያለ ነው፡፡ ሊቁ በዜማ ድርሰቱ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል ‹‹አረጋዊ አንገሃ ገይሰ ብእሲ ዘስሙ ኪራኮስ ዘዕጣን አንጸረ ሰገደ ጢስ በጎልጎታ ዘደፈኑ አይሁድ ዮም ተረክበ ዕፀ መስቀል፤ ስሙ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊ ማልዶ ገሠገሠ የዕጣኑ ጢስ ሰግዶ አይሁድ በጎልጎታ የደፈኑበትን አመለከተ ዛሬ ዕፀ መስቀል ተገኘ›› በማለት ሊቁ እንደ ሻማ ጠቅልሎ እንደወርቅ አንከብሎ ገልጾታል፡፡
፯.ዕፀ መስቀሉ ተገኘ
ቅድስት ዕሌኒም ጢሱ ሰግዶ ካረፈበት ቦታ ላይ መስቀሉ እንዳለ በማመን መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ማስቆፈር ጀመረች፡፡ ብዙ ጥራጊዎችንና ድንጋዮችን ሲያነሡ ጥጦስና ዳክርስ ተሰቅለውባቸው የነበሩ መስቀሎች በቀደም ተከተል ተገኙ፡፡ ቅድስት ዕሌኒም ይህ የጌታዬ መስቀል አይደለም ቁፋሮው ይቀጥል አለች፡፡ ቁፋሮውንም ቀጠሉ ብዙ ከቆፈሩ በኋላ ድንጋይ አገኙ ድንጋዩን ሲያነሡት ተቀብሮበት የነበረው ጉድጓድ ብርሃን ተመላ ሲቆፍሩ የነበሩ ሰዎች ሊነኩት አልቻሉም እየተውት ሄዱ ካህናት አብረው ስለነበሩ እነርሱ እንዲያወጡት አዘዘች ካህናቱ ሲያወጡት፡፡ ቅድስት ዕሌኒም ‹‹የጌታዬ መስቀል እሄዋ›› አለች እኛም እርሷን አብነት አድርገን ‹‹እዮሐ›› እንላልን፡፡ በኢየሩሳሌም በሙሉ አበራ ጨለማ ጠፋ ቀንና ሌሊት የማይለያይ ሆነ፡፡ ቅድስት ዕሌኒም ምኞቷን የፈጸመላትን እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ ለቅዱስ መስቀሉም የጸጋ ስግደት ሰግዳ ተሳለመችው፡፡
በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ከታናሽ እስከ ታላቅ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እየመጡ ተሳለሙት አክብረውም ሰገዱለት፡፡ ሕሙማንም ተፈወሱ ዕውራን ዐይናቸው በራ ቅድስት ዕሌኒም እግዚአብሔር ያደረገላትን ቸርነት እያደ ነቀች ለልጇ ለቆስጠንጢኖስ መልእክተኞችን ላከ የመስቀሉን መገኘት እንዲነግሩት አደረገች፡፡ እርሱም ደስ አለው ወደ መስቀሉ ሄደ ሕዝቡም በዝማሬ በዕልልታ ተቀበሉት እርሱም መስቀሉን አክብሮ የጸጋ ስግደት ሰገደለት ተሳለመው፡፡ በመስቀሉ የተደረጉ ገቢረ ተአምራቶችን ተረኩለት ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጦ ወደሀገሩ ተመለሰ፡፡ በቅድስት ዕሌኒ አማካኝነት ተሠርቶ መስከረም ፲፮ ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ ወደጎልጎታ እንደገባ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
እኛም እንላለን እናታችን ዕሌኒ ሆይ በፈተና በማዕበልና በሞገድ ውስጥ ሁነሽ፣ በቤተ መንግሥትም የንጉሥ ሚስት፣ የንጉሥ እናትና ንግሥት ሁነሽ የዚህ ዓለም ድሎትና ምቾት ከመስቀሉ ፍቅር ያልየሽ እንዴት የመስቀሉ ኃይል የክርስቶስ ፍቅር ቢገባሽ ነው? ያስተማረሽ መምህር እንዴት አድርጎ በመልካሙ የልቡናሽ እርሻ ላይ የወንጌሉን ዘር ቢዘራው ነው? የማያልፈውን በጎ ዕድል እንድትመርጭ አድርጎሻልና፡፡
በሰንበት ትምህርት ቤቶች በጽዋ ማኅበራት በግቢ ጉባኤያት ብዙ እኅቶቻችን ይማራሉ ይዘምራሉ ከእዚህ ውስጥ እንደ አንቺ ያሉ እኅቶችን አስነሽልን ምዕራባውያን በፍቅር ላይ ጥላቻን በቅድስና ላይ ርኵሰትን በአንድነት ላይ መለያየትን በትሕትና ላይ ትዕቢትን በጸና እምነት ላይ የጥርጣሬ ቆሻሻን ከምረውብናልና ከተቀበረበት ቆፍረው እንዲያወጡልን ፍቅር፣ ትሕትና፣ አንድነት፣በጎነት ቅድስና፣ ፍጹም መንፈሳዊነት ከተቀበሩበት ይውጡና እንደ ቅዱስ መስቀሉ ብርሃናቸውን ለዓለሙ ሁሉ እንዲለግሡ ወደ  በቅድስት ሀገር እናቶቻችን እኅቶቻችን እንድታስነሽልን ነይ በረድኤት እንልሻለን፡፡

                                                     …………….. ይቆየን !

‹‹በመስቀሉ አርኀወ ገነተ፤ በመስቀሉ ገነትን ከፈተ›› ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ

በመ/ር ለይኩን አዳሙ ባሕር ዳርማእከል
ክፍል -፪
  ፬.ቅድስት ዕሌኒ ማን ናት ?
ከመልካም ዛፍ የተገኘች መልካም ፍሬ የሆነችው ቅድስት ዕሌኒ መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ጥበብን የሚያሳውቁ ቅዱሳት መጻሕፍትን እያነበበችና እየተማረች በጥበብና በሞገስ ካደገች በኋላ ተርቢኖስ ከተባለ ሰው ጋር በሕገ ቤተ ክርስቲያን ትዳር መሥርታ መኖር ጀመረች፡፡ የሚተዳደሩትም በንግድ ነበር፡፡ በድሮ ዘመን ነጋዴዎች ለንግድ ወደ ሌላው ሀገር ሲሄዱ ከአምስትና ከስድስት ዓመታት በላይ ቆይተው ለብዙ ዓመታት የሚሆናቸውን ገንዘብ አፍርተው ይመለሱ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ የዕሌኒ ባል ተርቢኖስም የሚተዳደረው ትዳሩንም የሚመራው በንግድ ስለነበረ ወደ ንግድ ሲሄድ ለቅድስት ዕሌኒ የምትረዳት የምታገለግላት ሠራተኛ ቀጥሮላት ከባልንጀሮቹ ጋር ወደ ንግድ ሄደ፡፡
ተርቢኖስ ጓደኞቹ ከአምስት ዓመታት በኋላ አቀበት ወጥተው ቁልቁለት ወርደው ባሕር አቋርጠው የሚሸጠውን ሽጠው የሚገዛውን ገዝተው ማዕበሉ ሞገዱ ሳያሰጥማቸው ወረታቸውን ይዘው ከተሻገሩ በኋላ በእግዚአብሔር ቸርነት ያሰብነው ተሳክቶልን ከማዕበል ከሞገድ ተርፈን ከዚህ መድረሳችን መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ሚስቶቻችን ሌላ ወንድ ወደውና ለምደው እንዳይቆዩን እንጂ ተባባሉ፡፡ተርቢኖስም እንዲህ አለ «እኔስ ማዕበሉን ሞገዱን አምላኬ ጠብቆ ከዚህ አደረሰኝ እንጂ ሚስቴን እንዲህ ባለ ግብር አልጠራጠራትም» አለ ባልንጀሮቹም ‹‹የአንተ ሚስት ከሔዋን ልጆች የተለየች ናትን በማለት ተዘባበቱበት ፡፡ እርሱም መልሰ የእናንተ ሚስቶች ሃይማኖትና ምግባር ስለሚጎድላቸው ነው የኔ ሚስት ግን ሃይማኖትና ምግባር ፈሪሃ እግዚአብሔር በውስጧ ስላለ በዚህ አልጠራጠራትም በማለት መለሰላቸው፡፡
ከባልንጀሮቹ መካከል አንዱ እንዲህ አለ‹‹ሂጀ ወድጃት ለምጃት ብመጣ ምን ይቅጣህ አለው፡፡ እርሱም «በግብር ማወቅ ቀርቶ መልኳን አይተህ ብትመጣ እስከ አሁን ወጥቼ ወርጄ ያተረፍሁትን ወረቴን እሰጥሃለሁ አንተስ ወደሃት ለምደሃት ባትመጣ ምን ይቅጣህ» አለው ያም ነጋዴ የለፋሁበትን ወረቴን አስይዛለሁ»አለ ይህን ንግግራቸውን በመሐላ አጸኑት ተነሥቶም ወደ ተርቢኖስ ቤት ሂዶ ከደረሰ በኋላ የተርቢኖስን ጎረቤቶች ዕሌንኒን ጥሩልኝ አላቸው፡፡እነርሱም እርሷንስ ባሏ ከሄደ ጀምሮ እንኳንስ ሰው ፀሐይም አይቷት አያውቅ አሉት፡፡እርሱም ሠራተኛዋን ጥሩልኝ አለ የቤት ሠራተኛዋን አስጠርቶ እመቤትሽን ዕሌኒን እፈልጋታለሁ ጥሪልኝ አላት ሠራተኛዋም እርሷስ ይህ ሥራዋም አይደለም ለኔም አይቻለኝም አለችው፡፡
ብዙ ገንዘብ እሰጥሻለሁ ለእርሷም እሰጣታለሁ አላት ገንዘብ አያታልለው የለምና ሠራተኛዋም እሽ ብላ ወደ ዕሌኒ ሂዳ ሰው ይጠራሻል አለቻት ትሰፋ ነበር ቢሉ በወስፌዋ ትፈትል ነብር ቢሉ በእንዝርቷ እንዲህ ያለግብር ከወዴት ታውቂብኝ አለሽ ብላ መታቻት፡፡ ተመልሳ ተው ብልህ አስመታኽኝ አለችው፡፡ እርሱም ባልና ሚስቱ የሚተዋወቁበት አንድ ነገር ስጭኝ ብሎ ብዙ ገንዘብ ሰጣት እርሷም እንዲህ አለችው ‹‹በከተማው ነጋዴዎች መጡ ከባሕር ወጡ የብስ ረገጡ ብለህ አስነግር›› አለችው እርሱም ይህን ቃል በከተማው እንዲነገር አደረገ፡፡
ሠራተኛዋም ዕሌኒን ‹‹ነጋዴዎች መጡ ከባሕር ወጡ የብስ ረገጡ እየተባለ በከተማው ይነገራል ተነሽና ገላሽን ታጠቢ ልብስሽን ቀይሪ›› አለቻት፡፡ ቅድስት ዕሌኒም እውነት መስሏት ‹‹ይህን እኮ የምታደርጊው አንች ነበርሽ›› አለቻት፡፡ ‹‹በይ ተነሽ መታጠቢያ ቤት ግቢ ገላሽን ልጠብሽ›› አለቻት ዕሌኒም ወደ መታጠቢያ ቤት ገብታ ልብሷን አወለቀች ከደረቷ ላይ የበቀለ የአንበሳ ፀጉር የሚመስል ነበራት፡፡ ባልና ሚስቱ ሲጨዋወቱ የሚመለከቱት ከዕንቊ የተሠራ ቀለበት ከዚያ ላይ አስሮላት ነበር ስትታጠብ አውልቃ አስቀምጣው ስለነበረ ታጥባ ተመልሳ ስትቀመጥ ሠራተኛዋ አውጥታ ለዚያ ነጋዴ ሰጠቸው፡፡ እርሱም ደስ እያለው ወደጓደኞቹ ሄደ እንዴት ሁነህ መጣህ? አሉት ‹‹ወድጃት ለምጃት ወዳኝ ለምዳኝ መጣሁ›› አላቸው፡፡
ተርቢኖስም ‹‹አላምንም የኔ ሚስት ይህን አታደርገውም››አለው፡፡ ያነጋዴም ሁለቱ የሚተዋወቁበትን ያን የዕንቊ ቀለበት አሳየው እርሱም እውነት መስሎት ለብዙ ዓመታት የደከመበትን ወረቱን ለነጋዴው አስረከበና ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ጓደኞቹ ከቤታቸው ገብተው ከሚስቶቻቸው ጋር ተድላ ደስታ ሲያደርጉ እርሱ ግን አዝኖ ተክዞ ተቀመጠ፡፡ ዕሌኒም እንዲህ አለችው ‹‹ምነው በጓደኞችህ ቤት ተድላ ደስታ እየተደረገ አንተ አዘንህ ተከዝህ አንገትህን ደፋህ? አለችው ›› ተርቢኖስም እንዲህ አላት፡፡ ‹‹እነርሱ እኮ ወረታቸውን ማዕበል ሞገድ ሳያሰጥምባቸው በሰላም ይዘው ገብተው ነው እኔ ያላዘንሁትን ማን ይዘን? የወጣሁበትን የወረድሁበትን ንብረቴን ባሕር ሲያሰጥምብኝ›› አላት፡፡
እርሷም ‹‹ይህማ ምን ቁም ነገር አለው ያንተ ስልሳ ዘመድ የኔ ስልሳ ዘመድ አለን ተበድረህ ትሠራለህ አይዞህ›› አለችው፡፡ እርሱም በነገር እንዲህ ሲል ወጋት ‹‹አንችን እኮ ሁሉ ያምንሻል ይወድሻል እኔን ማን ይወደኛል? ማንስ ያምነኛል? እኔስ በተከበርኩበት ሀገሬ ተዋርጀ ባበደረሁበት ሀገሬ ተበድሬ አልኖርም ሀገሬን ጥየ እኼዳለሁ አላት›› እርሷም ‹‹አንተና እኔ አንድ አካል ነን ከምትሄድበት አብሬ እሄዳለሁ›› ብላ ተነሣች ‹‹እርሱም በይ ነይ›› ብሎ አስከተላት ወደ መርከብ ይዟት ገባ መርከብ ላይ ከተሳፈሩ በኋላ ‹‹እኅቴ ምነው ሳምንሽ ከዳሽኝ? ስወድሽ ጠላሽኝ?›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹አንተን ጠልቼ ማነን ወድጄ? አንተን ከድቼ ማንን ለምጄ?›› አለችው፡፡
ተርቢኖስም የወደድሽው የለመድሽውማ ይኸው አለና ያን የሚተዋወቁበትን ዕንቊ አሳያት ‹‹እርሷም እንኳንስ ልወደው ልለምደው መልኩንም አላየሁት መልኬንም አላየኝ አለችው፡፡ ታግዘኝ ብለህ የሰጠኸኝ ሠራተኛ ነገሩን ነገረችኝ እንቢ ብየ መጥቼ መለስኋት ነጋዴዎች መጡ ይባላል ገላሽን ታጠቢ ልጠብሽ ብላ ከደረቴ ፈታችው ከዚያም ወስዳ ሰጥታው ይሆናል እንጂ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው የማውቀው ነገር የለም አለችው”፡፡
ተርቢኖስም እንዲህ አላት ‹‹እግዚአብሔር ምስክርሽ ከሆነ ምንም ነገር ካለወቅሸማ ብሎ በሳጥን ቆልፎ ‹‹ግብርኪ ይትሉኪ፤ሥራሽ ይከተልሽ›› ብሎ ወደ ባሕሩ ወረወራት፡፡ እርሷም ዮናስን በባሕር ውስጥ የጠበቀ የምታመልከው አምላኳ በረድኤት ከልሏት ሳጥኑ ሳያፍናት ባሕሩም ሳያሰጥማት ብዙ መንገድ ከሔደች በኋላ ምንም ሳትሆን ሮም የምትባል ሀገር ላይ ስትደርስ ባሕሩ ሳጥኑን የብስ ላይ ተፋው፡፡
በዚያም የንጉሡ ባለሟሎች ነበሩና የነጋዴ ወርቅ መስሏቸው ደስ አላቸው ከፍተው ቢያዩት እንደ ፀሐይ የምታበራ ሴት አገኙ፡፡ ይቺስ ለእኔ ትገባለች ለእኔ ትገባለች በማለት እርስ በርሳቸው ተጣሉ መስማማት ሲያቅታቸው እንግዲያው ‹‹ለንጉሥ እንጂ ለእኛ አትገባም›› ብለው ወስደው ለንጉሡ ሰጡት፡፡

          ንጉሡ ቁንስጣም አይቶ በጣም ደስ አለው የአሕዛብ ነገሥታት ለግብረ ሥጋ ግንኙት አይቸኩሉምና የውስጥ ሰውነቷን የሚያጠራ ምግብና መጠጥ የውጭ ሰውነቷን የሚያጠራ ቅባትና ልብስ እየሰጣት ከቆየች በኋላ ለጋብቻ ጠየቃት፡፡ እርሷም አንተ አሕዛብ እኔ ክርስቲያን እንዴት ይሆናል? አለችው፡፡ በመልኳ ማማር ባነጋገሯ ለዛ ወዷታልና የአንቺን ሃይማኖት እከተላለሁ አምላክሽን አመልካለሁ አላት፡፡
እንግዲያወስ ዐርባ ቀን ስጠኝ ወደ አምላኬ ልጸልይ አለችው እሽ አላት፡፡ ሱባኤ ያዘች ወደ እግዚአብሔርም ጮኸች የዳዊት አባት የዳዊት ልጅ ሆይ ምነው ለአሕዛብ አሳልፈህ ሰጠኸኝ ብላ ከምግብ ተከልክላ በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን ጠየቀች፡፡ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ ያንቺ ደም እርሱን ይቀድሰዋል በደምሽ አጥምቂው ከእርሱም ደግ ልጅ ትወልጃለሽ የአባቱንም መንግሥት ይወርሳል ንጉሥም ይሆናል አላት፡፡ እርሷም እንዲህ ስትል አምላኳን አመሰገነች ‹‹ከአቅሜ በላይ እንድፈተን ያልተውኸኝ አምላኬ አመሰግንሃለሁ በማለት አምላኳን አመሰገነችና እሽ በጄ አለችው፡፡ በዚያውን ቀን በግብር ተዋወቁ ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች ስሙንም ቆስጠንጢኖስ አለችው፡፡ ቆስጠንጢኖስ ማለት ሐመልማል ወይም ልምላሜ ማለት ነው፡፡
እናቱ ወደ ባሕር በተጣለች ጊዜ በእግዚአብሔር ጥበቃ ወጥታ ከወንዝ ዳር በሚገኝ ለምለም ቦታ ተገኝታ ነበርና፡፡ ቆስጠንጢኖስ ማለት ሐመልሚል ወይም ኅብረ ብዙ ማለት ሲሆን ኅብረ ነገዱን፣ኅብረ ትውልዱን፣ኅብረ ጥበቡን አስመልክቶ የወጣለት ምሥጢራዊ ስም ነው፡፡ በኅብረ ነገድ ከሁለት ወገን ከሕዝብና ከአሕዛብ ተወልዷልና በኅብረ ትውልድ በአባቱ አረማዊ ሲሆን በእናቱ አይሁዳዊ ነውና በኅብረ ጥበብም ጥበብ ሥጋዊ ጥበብ መንፈሳዊ ተሰጥቶታልና፡፡ ቅድስት ዕሌኒም ልጇን ክርስትናን ማለትም የክርቶስን ግርፋቱን ስቅላቱን ሞቱን ትንሣኤውን ዕርገቱን እየነገረች ስለክርስትና ሃይማኖትና በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን ግፍና መከራ ስደት የአብያተ ክርስቲያቱን መቃጠልና መዘጋት የመጻሕፍቶቹን መቆንጸል እየነገረች አሳደገቸው፡፡ የንጉሥ ልጅ ንጉሥ እንደሚሆን አስቀድማ ተረድተታ ነበርና፡፡

        ቁንስጣም ለመንግሥት የሚበቃ ልጅ ስላልነበረው ወንድ ልጅ ስለወለደችለት ከደስታው ብዛት የተነሣ የከበረ ስጦታ በመስጠት በዕንቊና በወርቅ አስጊጦ መኳንንቱና መሳፍንቱ ታላላቅ ሰዎች በተገኙበት በዓል አድርጎ አነገሣትና ንግሥት ዕሌኒ ተባለች (ድርሳነ መስቀል ዘጥር)
ቆስጠንጢኖስን የሀገሩን ባህልና ቋንቋ ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበረ በበታቹ መስፍን አድርጎ ሾመው፡፡እርሱን በሾመው በሁለት ዓመቱ ቁንስጣ በተወለደ በዘጠና ዓመቱ ዐረፈ፡፡ ቆስጠንጢኖስም የአባቱን መንግሥት ተረክቦ የሮም ንጉሥ ኾነ ዕሌኒም የንጉሥ ሚስት የንጉሥ እናት ለመሆን በቃች፡፡
…………….. ይቆየን !

‹‹በመስቀሉ አርኀወ ገነተ፤በመስቀሉ ገነትን ከፈተ››ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ

በመ/ር ለይኩን አዳሙ ባሕር ዳርማእከል
  ክፍል -፩
ሊቅነትን ከትሕትና ምናኔን ከቅድስና ከአምላኩ እግዚአብሔር የተቸረው ማኀሌታዊው የሊቃውንቱ አባት የመንፈስ ቅዱስ ዕንዚራ የሆነው ሙራደ ስብሐት ቅዱስ ያሬድ ረቂቃን የሆኑ ሰማያውያን መላእክትን በምስጋና መስሎ እንደ ሰማያውያን መላእክት እግዚአብሔርን በአመሰገነበት የዜማ ድርሰቱ ክርስቶስ ጽኑዕ በሆነ ክንዱ መንጥቆ ሲኦልን በርብሮ ነፍሳትን ነጻ ካወጣ በኋላ ለ5500 ዘመን የሰው ልጆችን ስትውጥ የነበረችን ሲኦልን ዘግቶ በአዳም አለመታዝ የተዘጋችን ገነት በመስቀሉ ቁልፍነት በሥልጣኑ ከፈተ በማለት መስቀሉ ዲያብሎስ ድል የተነሣበት ገነት የተከፈተበት መሆኑን በሚገባ ተናገረ ፡፡
ይህ የተዘጋች ገነት የተከፈተባት መስቀል ለሰማያውያን መላእክት የድላቸው ምልክት የቅዱሳን አባቶቻችን የተጋድሏቸው አርማ ነው፡፡ይህ መስቀል ጎልጎታ ላይ የተተከለ መፍቀሬ ሃይማኖት ለሆነው ለቆስጠንጢኖስ በሰማይ የታየ ለሚፈሩትና ለሚያመልኩት ለኢትዮጵያ ምልክት ሆኖ የተሰጠ የሃይማኖት አርማ ነው፡፡በአዳም በደል ምክንያት ገነት ተዘግታ በኪሩቤል ሰይፍ ትጠበቅ እንደነበረና የዓለም መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ጥንተ ርስታችን ገነትን ከፈተልን ‹‹ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ የሚለውን የምሥራችም አሰማን›› (ሉቃ ፳፫÷፵፫) ቅዱስ ያሬድም ይህን መነሻ አድርጎ ከላይ በርእስነት የጠቀስነውን ቃል በበዓለ መስቀል በሚዘመረው ድጓ ላይ ዘምሮት እናገኘዋለን፡፡
፩. የመስቀል ትርጒም
መስቀል ማለት‹‹ሰቀለ፣ ሰቀለ›› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ምሥጢራዊ ትርጒሙ ወይም ፍችው መስቀያ፣መሰቀያ መከራ ማለት ነው፡፡ኢትዮጵያዊው ሊቅ እንዲህ ሲል ይተረጉማል ‹‹መስቀል ብሂል ዕፀ ሕይወት ብሂል፤መስቀል ማለት የሕይወት ዛፍ ማለት ነው››፡፡በማለት ሊቁ ክርስቶስ ዙፋኑ ያደረገውን ዓለም የዳነበትን ቅዱስ መስቀል የሕይወት ዛፍ በማለት ተርጒሞታል፡፡ አዳምና ሔዋን የበሉት ዕፀ በለስ ሞትና ውርደትን ፍርሃትና መቅበዝበዝን ወደ ዓለም ቢያመጣም ዳግማይ አዳም ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል ግን ሕይወትን ሰላምንና አንድነትን ክብርን ለአዳምና ለልጆቹ ያጎናጸፈ ስለሆነ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የሕይወት ዛፍ በማለት ድንቅ በሆነ አገላለጽ ተርጒሞታል፡፡
                                                                                                   መስቀል በብሉይ ኪዳን
መስቀል ከልደተ ክርስቶስ በፊት ወይም በብሉይ ኪዳን የዐመፀኞች፣የወንጀለኞች፣መቅጫ እንደ ነበረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ሰውን ለመጀመሪያ ጊዜ በመስቀል ላይ መቅጣት የተጀመረው ፋርስ ወይም ኢራን ተብላ በምትጠራ ሀገር ውስጥ ነው፡፡ በፋርስ ወይም በኢራን ሀገር የነበሩ ሰዎች የመሬት አምላክ ወይም ኦርዝሙድ የተባለውን ጣዖት ያመልኩ ስለነበረ በሀገራቸው ሰው ወንጀል ሲፈጽም ቅጣቱን በመሬት ላይ የተቀበለ እንደሆነ ደሙ ፈሶ ኦርዝሙድ ጣዖታቸውን የሚያረክሰው ስለሚመስላቸው ቅጣቱን በመስቀል ላይ ይፈጽሙበት ነበር፡፡
በእስራኤል ሀገር ሰው በደል ሠርቶ ሕግ ተላልፎ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ ሬሳው ለማስጠንቀቂያ ከዛፍ ላይ ይሰቀል እንደነበረ እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነው ቅዱስ መጽሐፍ ሕያው ምስክር ነው፤ ዘዳ ፳፩÷፳፫፡፡ በብሉይ ኪዳን ሙሴ የፈርዖንን መሰግላን (ጠንቋዮች) ድል ያደረገባት በትር የመስቀል ምሳሌ ነው፡፡

፪.መስቀል በሐዲስ ኪዳን
የሐዲስ ኪዳኑ መስቀል መድኃኒት አልባ ለሆነው ዓለም መድኃኒት ሊሆን ወደዚህ ዓለም የመጣ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ ክፋት በአንደበቱም ሽንገላ ሳይኖርበት እንደበደለኛ ተቆጥሮ ከበደለኞች ጋር በደልን በተመሉ በአይሁድ እጅ ተይዞ በግፍ በተሰቀለ ጊዜ አካሉ ያረፈበት የሰላም እግሮቹ የተቸነከሩበት የፍቅር እጆቹ የተዘረጉበት ጎኑ በጦር ተወግቶ ክቡር ደሙ የፈሰሰበት የፍቅር ዙፋን ነው፡፡
በመሆኑም የሐዲስ ኪዳኑ መስቀል አምላክ በክብሩ ያከበረው በቅድስናው የቀደሰው ስለሆነ ለደከሙት ኃይልን ለታመሙት ፈውስን ላዘኑት መጽናናትን ለዕውሮች ብርሃንን ማሰጠቱ ይታወቃል፡፡ የአምላክ ኃይሉና ጥበቡ ማዳኑ የተገለጠበት የፍቅር ዐደባባይ ነው፡፡

በልብ መታሰቡ በቃልም መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በገዛ ሥልጣኑ ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላም ድውይ በመፈወስ ሙት በማስነሣት ብርሃን ለሌላቸው ብርሃንን በመስጠት ድንቅ የሆነ ማዳኑንና ተአምራቱን የገለጸው በአከበረውና በቀደሰው መስቀል ነው፡፡ በዕለተ ዓርብ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከጲላጦስ ተካሰው ክርስቶስን በሐዲስ መቃብር ከቀበሩት በኋላ ከዚያው ከመቃብሩ አጠገብ አስቀምጠውት ነበር፡፡ ይህ መስቀልም ሙት የሚያነሣ ዕውር የሚያበራ ለምጻም የሚያነጻ በመሆኑ አይሁድ ለደካሞች ኃይልና ጉልበት ለነፍስ ቤዛ መድኃኒት በሆነው መስቀል ላይ በጠላትነት ተነሥተው የሕሙማን መዳን ያላስደሰታቸው ምቀኞች ስለሆኑ ጉድጓድ ቆፍረው ቀበሩት፡፡

፫. አይሁድ መስቀሉን የመቅበራቸው ምክንያት ምን ነበር?
ሙታንን እያስነሣ ዕውራንን እያበራ ጎባጣን እያቀና የአምላክን ጥበብና ድንቅ ድንቅ ተአምራቱን በመግለጡ ግፍን የተመሉ ሕዝበ አይሁድ በኃጢአት በፈረጠመ ክንዳቸው የሰው ልጆች እንዳይድኑ ጉድጓድ ምሰው መስቀሉን ቀበሩት፡፡ ሕዝበ አይሁድ መስቀሉን የቀበሩት በሦስት ምክንያት ነው፡፡
፩ኛ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ በሞተ ጊዜ ከተቀበረበት መቃብር ተነሥቶ እንዳይሄድ በሚል ሰቅለው የገደሉት አይሁድ ታላቅ ድንጋይ ከመቃብሩ አፍ ላይ አድርገውና መቃብሩን የሚጠብቁ ዘበኞችን ቀጥረው ማንም ሰው ወደ መቃብሩ እንዳይደርስ ወደ መቃብሩ የቀረበውን የቀረበ በድጋይ ወግረው እንዲገሉት ትእዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡እመቤታችን ድንግል ማርያም ግን ክርስቶስ ከተቀበረበት ቀን ጀምሮ ዘወትር ወደ ልጇ መቃብር እየሄደች ስትጸልይ አይሁድ ይመለከቱ ነበርና በእርሷ አመላካችነት ከነገሥታት አንዱ መጥቶ በክርስቶስ ላይ ስለደረሰው መከራ ሁሉ ይጠይቀናል የተሰቀለበትንም መስቀል ስጡኝ ብሎ ይጣላናል በሚል ፍራቻ የክርስቶስን መስቀል እንዲሁም በግራና በቀኝ የተሰቀሉትን የሁለቱን ሽፍቶች መስቀል፣ ጎኑን የተወጋበትን ጦር፣ ከራሱ ላይ፣ የደፉትን የሾህ አክሊልና የተቸነከረባቸውን ችንካሮች በአንድ ላይ ምድርን ቆፍረው የቀበሩበት አንዱ ምክንያት ነው፡፡
፪ኛ ንጹሓን ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል ርኵሳን አጋንንት ሲያወጡ ሙታንን ሲያስነሡ ለምጻሞችን ሲያነጹ መስማት የተሳናቸው መስማት እንዲችሉ ሲያደርጉ ጎባጣዎችን ሲያቀኑ ዓይነ ሥውራንን ሲያበሩና ወንጌልን ሰብከው በማስተማር ብዙ አሕዛብን በስመ ሥላሴ አሳምነው ሲያጠምቁ ልጅነት ሲያሰጡ በማየታቸው ተሰብስበው ክፉ ምክርን መክረው የሰው ልጆች መዳን ያላስደሰታቸው አይሁድ መስቀሉን ቆፍረው ቀበሩት ሁለተኛው ምክንያት ይህ ነው፡፡
፫ኛ. ድንቅ የሆነው አምላካችን በመስቀሉ ላይ አድሮ የሚደነቅ ተአምራቱን ሲገልጽ ያዩ ሰዎች ቅናተ ሰይጣን ስላደረባቸውና የኦሪትን ሕግ ምክንያት በማድረግ ምድር ቆፍረው ቀበሩት ፡፡ ይሁንም እንጂ እንደ ክፉዎቹ አይሁድ ሳይሆን በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ የሞተው ክርስቶስ ቅዱስ ነው፡፡ የተሰቀለበት መስቀልም ቅዱስ ነው፡፡ ክፉዎች አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን ከቀበሩት በኋላ በተቀበረው መስቀል ላይ ከታናሽ እስከታላቅ በአንድነት ጥርጊያ ለመድፋት ተማማሉ፡፡ ለከተማው ሰው አዋጅ ነገሩ፡፡ የመስቀሉ ስም አጠራር ከሰው አዕምሮ እንዲጠፋ እንዲረሳ ለማድረግ ጌታ የተሰቀለበትን ሕሙማን የዳኑበትን መስቀል ከሥር ጥጦስና ዳክርስ የተሰቀሉበትን ከላይ አድርገው ቀብረው የከተማውን ጥራጊ እያመጡ ይደፉበት ጀመር፡፡የደፉት ቆሻሻም ተራራ እንዳከለ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ዲያብሎስ ተዋርዶ አዳምና ልጆቹ የከበሩበት ሕሙማን የተፈወሱበት ገነት የተከፈተበት ቅዱስ መስቀል ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ ለሁለት መቶ ዓመታት ያህል በመቆየቱ ክርስቲያኖችም በጥጦስ ወረራ ከተማቸውን ለቀው በመሰደዳቸው የከተማዋ መልክአ ምድርም ተለውጦ ስለነበረ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ የት እንደሆነ የሚያውቀው አልነበረም፡፡
ይሁን እንጂ ጌታ በወንጌል “እስመ አልቦ ክዱን ዘኢይትከሠት ወአልቦ ኅቡዕ ዘኢይትዐወቅ፤ የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅ የተሠወረ ምንም የለም” በማለት አስቀድሞ እንደ ተናገረው ሁሉ(ማቴ፲÷፳፮፣ሉቃ.፲፪÷፪) ከሰዎች ኃይል የእግዚአብሔር ኃይል ከሰዎች ጥበብ የእግዚአብሔር ጥበብ ይበልጣልና እነርሱ ተሸፍኖ ወይም ተዳፍኖ ይቀራል ያሉት እግዚአብሔር የተሠወረው ተገልጦ እንዲወጣ ፈቃዱ ነበርና በሃይማኖት የጸናች በምግባር ያጌጠች የመስቀሉ ፍቅር ያላት አይሁድ በምቀኝነት እንደቀበሩት ትሰማ የነበረች ቅድስት ዕሌኒንና ልጅዋን ቆስጠንጢኖስን አስነሣ፡፡
…………….. ይቆየን !

በዓለ መስቀል

በመምህር ፈቃዱ ሣህሌ
ክፍል -፪

ከክፍል አንድ የቀጠለ……………..   

፩. በትምህርት፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በገለጠላት መሠረት ነገረ መስቀሉን አጉልታና አምልታ በማስተማር ክብረ መስቀልን ስትመሰክር ኖራለችም፤ ትኖራለች። ይህን የምታስተምረውም በጉባኤ፣ በመጽሐፍና በተግባር ነው። አስቀድሞ ነቢያት ለምሳሌም (መዝ. ፳፩፥፲፮-፲፱ ፤፷፰፥፳፩፣ ኢሳ. ፶፫፥፬-፲) በኋላም ሐዋርያትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ በአንደበታቸውም ኾነ በመጽሐፋቸው ስለ መስቀሉ ክብር በሰፊው በመግለጽ ተገቢውን ትምህርት ሰጥተዋል። አሁንም እንደቀድሞው ሊቃውንቱ በአብነት ጉባኤያት፣ በማኅሌት፣ በዝማሬ፣ በሰዓታት፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆች፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በዐውደ ምሕረት፣ በቅዱሳት መጻሕፍትና በአገልግሎቶች ሁሉ የመስቀሉን ክብር በመመስከር ላይ ትገኛለች።
፪. በመሳለም፦ ቅዱሱ አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም በላዩ ላይ ስለ ተሰቀለበት ዕፀ መስቀልም የተቀደሰ መሆኑን ከላይ ከተገለጹት ማብራሪያዎች መረዳት አያዳግትም። ይህንን ቅዱስ መስቀል መሳም ወይም መሳለም መቀደስ (ቅድስናን ማግኘት)፥ መባረክ መሆኑም ግርታን የሚፈጥር አይደለም። ይህንን ምሥጢር የበለጠ ለመረዳት እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይ ኪዳን ዘመን ካዘዛቸው ትእዛዛት አንዱን መመልከት መልካም ነው።
በኦሪት ዘፀአት እግዚአብሔር አምላካችን ለርእሰ ነቢያት ሙሴ ቅብዐ ቅዱስ የሚዘጋጅበትን መመሪያ ከሰጠ በኋላ በቅብዐ ቅዱሱ የሚከብሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሲገልጽልን “የመገናኛውንም ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥ ገበታውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም፥ ዕቃውንም፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ። ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፤ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ፤ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።” በማለት ያትታል (ዘፀ.፴፥፳፮-፴።)
ይህንን አስገራሚ የእግዚአብሔር ጸጋ በማስተዋል ያነበቡ ሁሉ በአድናቆትና በደስታ ሆነው ቢያንስ ራሳቸውን እንዲህ ብለን ለመጠየቅ መገደዳቸው አይቀርም።

“የሐዲስ ኪዳን ጥላ በሆነ በዘመነ ኦሪት በነበረ ሥርዓት በቅብዐ ቅዱስ የከበሩት በመቀደሳቸው ምክንያት የሚነኳቸውን ሁሉ የመቀደስ ኃይል ካገኙ፥ ቅዱሱ ጌታ አማናዊ በኾነው ዘመነ ሐዲስ በቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የቀደሰው መስቀልማ ምን ያህል ክብርና ቅድስና ይኖረው ይሆን? የሳሙትንና የተሳለሙትንስ እንዴት ያከብራቸውና ይቀድሳቸው ይሆን?” በዚህም መሠረት ክርስቲያኖች ቅዱስ መስቀሉን በመሳም ወይም በመሳለም ክብረ መስቀሉን እንመሰክራለን ።
፫. በመባረክ፦ ከላይ እንደገለጽነው በላዩ ላይ ከተሰቀለበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የተነሣ መስቀሉ ቅድስናንና ኃይልን ተጎናጽፏል። ለዚህም ምስክሩ ከላይ እንዳየነው በመስቀሉ ዲያብሎስ ድል ተደርጎበታል፤ የገነትም ደጅ ተከፍቶበታል፤ ፈያታዊ ዘየማንም ወደ ገነት አስገብቷል። በዚህም ምክንያት ከላይ እንደገለጽነው የነካቸውንና በእምነት የነኩትን ሁሉ የመባረክ (የመቀደስ) ኃይል አለው። የጌታችን ቀሚስ ለ፲፪ ዓመታት ደም ሲፈሳት የነበረችው ሴት በእምነት በዳሰሰችው ጊዜ ደሟን በቅጽበት እንዳደረቀላት ማስታወስ ለዚህ ንዑስ ርእሳችን ጥሩ ማነጻጸሪያ ነው። (ማቴ.፱፥፳-፳፫።)
መስቀሉ ኃይለ እግዚአብሔር ያደረበት ከመኾኑም በተጨማሪ ለካህናት አባቶቻችን በተሰጣቸውም ሥልጣን እኛ ክርስቲያኖችና የእኛ የሆነው ሁሉ እየተባረክንበት ክፉ የኾነውን ሁሉ እናርቅበታለን፤ ጸጋ መንፈስ ቅዱስንም እንቀበልበታለን። በዚህ አጋጣሚ እስራኤል የተባለ አባታችን ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን (የዮሴፍን ልጆች) በአባታቸው ዮሴፍ ጥያቄ የባረካቸው እጆቹን አመሳቅሎ (በመስቀል ምልክት) መሆኑን ልብ ይሏል። (ዘፍ.፵፰፥፲፪-፲፭።) ባራኪው እየባረከ፥ ተባራኪውም እየተባረከ ክብረ መስቀሉን ሲመሰክሩ ኖረዋል፤ እየመሰከሩም ይገኛሉ።
፬. በማማተብ፦ ክርስቲያኖች የሆንን እኛ በእንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ ማለትም ከቤት ስንወጣ፣ ወደ ቤት ስንገባ፣ ሥራችንን ስንጀምር፣ ማዕዳችንን ስንጀምርና ስንፈጽም፣ መንገዳችንን ስንጀምር፥ በየመኻሉና ስናጠናቅቅ፣ ጸሎታችንን ስንጀምርና ስንፈጽም፣ አስደንጋጭ ነገር ሲገጥመን፣ በጸሎታችን የመስቀልን ስም ከሚያነሣ አንቀጽ ስንደርስ፣. . . ወዘተ ጣቶቻችንን አመሳቅለን (መስቀል ሠርተን) እንድናማትብ ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዘወትር ታስተምረናለች። “እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።” (ሉቃ. ፲፩፥፳) የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ከዚሁ ጋር አያይዞ ማየት፥ ምሥጢሩንም በማገናዘብ መረዳት ይቻላል። ይህም የመስቀሉን ፍቅርና ክብር የምንገልጽበት ሌላው መንገዳችን ነው።
፭. በአንገት በማሠር፦  ክብረ መስቀልን ከምንገልጽባቸው ክርስቲያናዊ የሕይወት ጉዞዎች አንዱ መስቀሉን በአንገት ማሰር ነው። ይህንን የምናደርገው ላመንበት ሃይማኖት፥ ለተቀበልነውም መንፈሳዊ አደራ ያለንን ታማኝነት ለመግለጽ ነው። “በሃይማኖቴ አላፍርም፥ አልደራደርም፤ አንገቴንም እንኳን ሳይቀር ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፤” ለማለት ነው። በኦሪቱም እግዚአብሔር አምላካችን በሙሴ አማካኝነት የሰጠውን አምላካዊ ትእዛዝ መመልከት ቃሉን ይበልጥ ለመረዳት ይረዳናል።

ዳግመኛም “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፤ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሠረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደ ክታብ ይሁንልህ። በቤትህም መቃኖች፥ በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” በማለት የተናገረው ይህንኑ የሚያስገነዝብ ነው ። ጠቢቡ ሰሎሞንም በተመሳሳይ የተናገረው ከዚሁ ጋር ሊመሳከር የሚችል ነው። እንዲህ ያለው፦ “ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ ሁልጊዜ በልብህ አኑረው፤ በአንገትህም እሰረው። ስትሄድ ይመራሃል፤ ስትተኛም ይጠብቅሃል፤ ስትነሣ ያነጋግርሃል” (ምሳ ፮፥፳-፳፫)
፮. በሕዝቡ ባህልና የዕለት ተዕለት አኗኗር ውስጥ በመጠቀም፦ ቅዱስ መስቀል ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው የክርስቲያኖች የድኅነት ዓርማ ወይም ምልክት ነው። በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች ሁሉ ስለሚመኩበት በአንገታቸው በማሠር ብቻ ሳይወሰኑ በግንባራቸውና በእጆቻቸው በመነቀስ፣ በመኖሪያ ቤታቸው ጣሪያ ላይ በማድረግ፣ በልብሶቻቸው በመጥለፍና በመሳሰሉት ገላጭ ክንውኖች በመጠቀም ለአምላካቸው ለክርስቶስና ለተሰቀለበት መስቀል ክብር ያላቸውን ፍቅርና ታማኝነት በፊትም አባቶቻችን፥ ዛሬም ልጆቻቸው ሲመሰክሩ ኖረዋል፤ ይኖራሉ።
፯. በአባቶች እጅ ዘወትር በመያዝ፦ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጀምሮ እስከ ቀሳውስቱ ድረስ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በእንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ መስቀሉን ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት። የክርስቶስ ቤተሰቦች የሆኑትን ኦርትዶክሳውያን ምእመናንም በቤተ ክርስቲያንና በየቤቶቻቸው እንዲሁም በየመንገዱ ሁሉ ይባርኩበታል።

በተጨማሪም እንደሚታወቀው አባቶቻችን በአገልግሎት ሂደት ወቅት በተለየ ሁኔታ መስቀሉን ይጠቀማሉ። በቅዳሴና በምሥጢራት አጠቃቀም ጊዜ ዲያቆናትም የመጾር መስቀል በመባል የሚታወቀውን የሚጠቀሙ ሲሆን በጥቅሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያለ መስቀሉ የምትፈጽመው ምንም ዓይነት ምሥጢርና አገልግሎት የላትም። ይህም ለመስቀሉ ያለንን አክብሮትና ፍቅር የምንገልጽበት ሌላው ማሳያችን ነው።
. በጥንታውያን ቅርሶቻችን ላይ በማድረግ፦ሀገራችን ኢትዮጵያ ክርስትናን ከኢሩሳሌም ቀጥሎ ከሌሎች ሀገሮች ቀድማ የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ትእምርተ መስቀሉን ተቀብላ ያላትን ፍቅርና ክብር ለመግለጽ በልዩ ልዩ መገልገያዎቿ ላይ በመቅረጽ ስትጠቀምበት ኖራለች። ለማሳያ ያህልም፦ በመገበያያ ገንዘቦች (ሳንቲሞች)፣ በነገሥታት ዘውዶችና አልባሳት ላይ በመቅረጽ፣ በቤተ መንግሥት ቤቶች፣ አጥሮችና የመሳሰሉት ላይ የመስቀሉን ምልክት በማኖር ለመስቀል ያላትን ክብር ስትገልጽ ኖራለች፤ ዛሬም ስለ ክብሩ ትገልጻለች፡ትመሰክራለችም።
፱. በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉልላት፣ በበሮቿ፣ በግንቦቿ፣ በአጥሮቿና በንዋየ ቅድሳቷ ሁሉ ላይ ትእምርተ መስቀሉን በመጠቀም፦ ከላይ የጠቀስነው እንደ ሀገር ሲታይ ሲሆን አሁን ደግሞ እንደ ቤተ ክርስቲያን የሆነውን እንመልከት በገሃድ እንደሚታየው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጉልላቷ ጀምሮ በሕንጻ ቤተ ክርስቲያኗ ሁለንተና ላይ የመስቀሉን ምልክት ተሸክማ ትታያለች። ክብረ መስቀሉን ከምትመሰክርባቸው መንገዶች አንዱ በውስጥና በውጭ አገልግሎት ሁሉ በንዋየ ቅድሳትና ላይ መስቀሉ ተቀርጾበት ለአገልግሎት ማዋል የተለመደና የታወቀ ነው።
፲. በስሙ በመሰየም፦ በመስቀሉ ስም ታቦት (ጽላት) ቀርፆና ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ አክብሮ መገልገል የመጀመሪያው ማሳያ ነው። በተጨማሪም ካህናት ተጠማቂዎች ፡ ምእመናንን በመስቀሉ ስም ገብረ መስቀል፣ ወለተ መስቀል፣ ብርሃነ መስቀል፣ መስቀል ክብራ፣. . . እያሉ በመሰየም ነው።) ለመሰቀሉ ያላቸውን ክብርና ፍቅር ሲመሰክሩ ኖረዋል፤ይኖራሉም።
፲፩. በዓሉን በማክበር፦ እንደሚታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓለ መስቀልን ከዘጠኙ ንዑሳት የጌታ በዓላት መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጋለች። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት በተለይ ዓመታዊ በዓላቱን ክርስቲያኖች እንደ አቅማቸውና ዕውቀታቸው መታሰቢያውን እያደረጉ በማክበር ይማጸኑበታል። በይበልጥ ደግሞ በመስቀል ስም በተሰየሙ አብያተ ክርስቲያናት በልዩ ሥርዓት እያከበሩ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እያገኙና እያደሉ ይኖራሉ። በተለይም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በመላው ዓለም ዘንድ በታወቀው የመስከረም ፲፮ የደመራ በዓልና የመስከረም ፲፯ በዓለ መስቀል በምትሰጠው አገልግሎትና በምትፈጽመው ምስክርነት ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ታላቅ በረከትን ስታድል ኖራለች፤ ትኖራለችም። ለክብረ መስቀሉ ማክበሪያ ይሆን ዘንድም ቅድስት ቤተ ክርስቲናችን በመላው የሀገራችን ክፍሎች የመስቀል በዓል ማክብሪያ ዐደባባዮችን ተቀብላ ዓመታዊ በዓለ መስቀሉን በማክበር ላይ ትገኛለች።
፲፪. በልዩ ኹኔታ የተፈጸመ ምስክርነት፦ እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይ ኪዳን ክብሩን የገለጸባትን ታቦተ (ጽላተ) ጽዮንን ከዓለም ሀገራት መርጦ በኢትዮጵያ ማኖሩ ይታወቃል። በተመሳሳይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትንና ክብሩን የገለጸበትን ቅዱስ መስቀል (ግማደ መስቀል) በአደራ ያኖረው በኢትዮጵያ መሆኑም ግልጽ ነው።

በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን ግማደ መስቀል አባቶቻችንና እናቶቻችን በታላቅ ክብር ተቀብለው መስቀለኛ በሆነው ግሸን ደብረ ከርቤ ቅዱስ ተራራ አውጥተውና ለምድር አደራ ሰጥተው ዛሬም ድረስ በክብር ተቀምጦ ይገኛል። በዚህም መሠረት “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ስፍራ አኑር፤” በማለት በቅዱስ ዑራኤል አማካኝነት ልዑል እግዚአብሔር የሰጠውን ትእዛዝ በመፈጸም በፈሪሀ እግዚአብሔር የሚመሩ እውነተኛ የወንጌል አማኞች መሆናቸውን ለዓለም አሳይተዋል። ከመስቀሉ ጋር በተያያዘም በዚሁ ቅዱስ ስፍራ በያመቱ መስከረም ፲፮ እና ፲፯ እንዲሁም ፳፩ ቀናትን በልዩ ክርስቲያናዊ ሥርዓት በማክብር ለመስቀሉ ያለንን ክብር በመመስከር ላይ እንገኛለን።
እንደሚታወቀው ሁሉ ከቅድስት ዕሌኒ ጋር በተያያዘ ተረክቦተ መስቀሉን (የመስቀሉን መገኘት) ያለውን ታሪክ የዓለም ማኅበረሰብ የሚያውቀው፣ የሚጽፈውና የሚናገረው ነው። በዓለም ላይ የሚገኙ አኃትና ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት በየባህላቸው በዓለ መስቀልን የሚያከብሩበት የየራሳቸው መንገድ እንዳላቸውም ይታወቃል። ሌላው በክርስትና ስም የሚጠራው የምዕራቡ ዓለም ደግሞ እንኳን ሊያከብረው ይቅርና መስቀሉን በማጥላላትና በመንቀፍ የስህተት ትምህርት በማሠራጨት ተጠምዷል ፡፡በዚህ ሁሉ የተደበላለቀ ሁኔታ ውስጥ ከዓለም ሀገራት ተለይታ ለታወቀውና ለተገለጸው መስቀለ ክርስቶስ ተገቢውን ክብር በአፀደ ቤተ ክርስቲያን ሳትወሰን በዐደባባይ በዓልነት ወስና በደመቀ ሁኔታ ስትሰጥ የኖረችና በመስጠት ላይ ያለች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቲያን ያሉባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች።

መ. ማጠቃለያ
ቅዱስ መስቀል እንደ ተቋም ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፥ እንደ ኅብረትም ለአንዲቷ የምእመናነ ክርስቶስ ጉባኤ ሁለንተናዋ ነው። በተለይም ተጋዳዪቱ የክርስቶስ አካል ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኃይል፥ ጽንዕ፥ መመኪያ ትእምርት (ምልክት) ይሆናት ዘንድ ከጌታዋ በተሰጣት መመሪያ መሠረት ተሸክማውና ተመርኩዛው ነገረ ክርስቶስን ስትመሰክር ትኖራለች። “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ወዳጆችህ እንዲድኑ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኻቸው።” (መዝ. ፶፱፥፬።) ተብሎ በቅዱስ ዳዊት እንደተገለጸው፥ ከአምላኳ የተሰጣትን ቅዱስ መስቀል ተቀብላና አክብራ እንደ አስፈላጊነቱ ስትጠቀምበት ኖራለች፤ ትኖራለችም። በዓለ መስቀሉን አባቶቻችንና እናቶቻችን በአማረና በደመቀ ሁኔታ ሲያከብሩ ኖረዋል፥ እኛም እናከብራለን፤ ስንል ምን ማለታችን ነው? ጽኑዓን የሆኑት አባቶቻችንና እናቶቻችን የቻሉትን ማድረጋቸውና እኛም የቻልነውን ሁሉ ማድረጋችን ለመስቀሉ እነርሱ የጨመሩለት፥ እኛም ደግሞ የምንጨምረው ክብር ኖሮ አይደለም።
ይልቁንስ ለቅዱስ መስቀሉ ክብር የነበራቸውንና ያለንን ፍቅር ለመግለጽ ያህል እንጂ ዋናው ምሥጢር በመስቀሉ ከብረውበታል፤ እኛም እንከብርበታለን፤ ማለታችን ነው። በዓለ መስቀሉን ከላይ በገለጽናቸው ልዩ ልዩ መንገዶች ስናከብርም በቅዱስ መስቀሉ ያገኘነውን እና የተረጋገጠውን የመዳናችንን ምሥጢር እያወደስንና እያከበርን እየመሰከርንም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።በክፉዎች አይሁድ ተቀብሮና ጠፍቶ የነበረው ቅዱስ መስቀል በፈቃደ እግዚአብሔር በቅድስት ዕሌኒ አማካኝነት ወጥቶ ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ በዓለ መስቀል በልዩ ሁኔታ መከበር መጀመሩ ይታወቃል። በዚህ ዘመን የምንገኝ ክርስቲያኖችም በዓለ መስቀሉን ስናከብር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ በቆረሰው ቅዱስ ሥጋውና ባፈሰሰው ክቡር ደሙ የሰጠንን ሀብታት በማስታወስ መሆን እንደሚገባው መርሳት የለብንም። በመስቀሉ ሰላምን፣ ዕርቅን፣ አንድነትን፣ ሕይወትን፣ ፍቅርን፣ ደስታን፣ ክብርን፣ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ማግኘታችን ይታወቃል። ዛሬ ግን የመስቀሉን ስጦታዎች ወደ ጎን ገሸሽ አድርገናቸው በተቃራኒው የጥፋት መንገድ ውስጥ በመግባታችን ጦርነትን፣ ጸብን፣ መለያየትን፣ኅዘንን፣ ሞትን፣ ውርደትን፣ . . እያነገሥናቸው መሆኑም ግልጽ ነው።
ስለዚህ በዓለ መስቀሉን ስናከብር እግዚአብሔር አምላካችን አሁን ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚለውን ቆም ብሎ ማስተዋል ይኖርብናል። ይህ በዓል የቅዱስ መስቀሉን ትሩፋቶች በማሰብ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን፣ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ከኅዘን ይልቅ ደስታን፣ ከሞት ይልቅ ሕይወትን፣ ከውርደት ይልቅ ክብርን፣ ከቂምና ከበቀል ይልቅ ዕርቅን፣ . . . ለማረጋገጥ አቅም የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉ ምእመናንንና ምእመናትን ይፈልጋል። ከዚሀ ውጪ ሆነን ቀን ቆጥርን፣ ነጭ ለብሰን፣ ቤታችንን ጎዝጉዘን፣ ጠጅ ጥልን፣ ጠላ ጠምቀን፣ ፍሪዳ አርደንና አወራርደን፣ ታላቅ ድግስ በመደገስ መስቀሉን አጅበን፣ ሆ! ብለንና ዘምረን በማሳለፍ ብቻ በዓለ መስቀልን ያከበርን የሚመስለን ካለን የተሳሳትን መሆናችንን መገንዘብ ይኖርብናል።

በዓሉ ታሪኩን በመተረክ ላይ ብቻ ሳንወሰን እንደቀድሞው ሁሉ ዛሬም የጠፋውንና ያጣነውን ለኢትዮጵያ፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለሁላችንም በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ መፈለግንና ከተቀበረበት ቆፍሮ ማውጣትን ይፈልጋልና።
እንደ ደመራው እሳትም የፍቅርን፣ የሰላምን፣ የደስታንና የአንድነትን እሳት በሃይማኖት በማቀጣጠል (በማንደድ) ጥላቻን፣ መለያየትን፣ ዘረኝነትን፣ ኅዘንንና የመሳሰሉትን ጎጂ የሆኑ የሰው ልጅ ጠላቶች በተቀጣጠለው እሳት ማጥፋት ይጠበቅብናል። እያንዳንዳችን የመስቀሉ ወዳጆች የሆንን ሁሉ ራሳችንንም እንደ ዕጣኑ መዓዛ የተወደደ መሥዋዕት አድርገን እስከ ማቅረብም ደርሰን አስፈላጊውን ሁሉ መሥዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ተገቢ ነው። ከምንም በላይ እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር ጋር ሕጉንና ትእዛዙን በመጣስ መጣላት አለመጣላታችንን ማረጋገጥ አለብን። እኛው በድለን ከእርሱ ተጣልተንና ተለይተን ስንኖር ዕርቅ፣ ሰላምና አንድነትን የሰጠን ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ይታወቃል።
አሁን ራሳችንን መመርመር ያለብን በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የጥል ግድግዳ አቁመናል ወይስ አላቆምንም? የሚለውን ነው። የጥል ግድግዳ አቁመን ከሆነ በዓለ መስቀልን ልናከብር የሚገባው በመጀመሪያ የጥሉን ግድግዳ አፍርሰንና በንስሓ ወደ ቤቱ ከተመለስን ከኃጢአት ከበደላችን ከነጻን በኋላ በመስቀሉ ላይ የተቆረሰውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ነው። እንዲህ ባለ መንገድ ማክበር ከቻልን “መስቀል መልዕልተ ኵሉ ነገር ያድኅነነ እምፀር።ከጠላት የሚያድነን መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነው።” በማለት ከቅዱስ ያሬድ ጋር ለመዘመርና በዓለ መስቀሉን በእውነት ለማክበር እንችላለን።
     ልዑል እግዚአብሔር በኃይለ መስቀሉ ይጠብቀን ለዘለዓለሙ አሜን።

በዓለ መስቀል

በመምህር ፈቃዱ ሣህሌ
        ክፍል -፩
ሀ. ትርጒም
ከዚህ በታች የሁለቱን ቃላት መዝገበ ቃላታዊ ፍቺ በማሳየት ወደ ዋናው ትንታኔ ለመግባት እንሞክራለን። በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት አተረጓጎም መሠረት “በዓል” የሚለው ቃል ለዕለት (ለቀን) ሲነገር የደስታ፣ የዕረፍት ቀን፣ በዓመት፥ በወር፥ በሳምንት የሚከበር፣ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት፣ . . . ወዘተ በማለት ተተርጒሟል። (ኪ.ወ.ክ ፪፻፸፱።) “መስቀል” የሚለውን ደግሞ መስቀያ፣ መመዘኛ፣ መንጠልጠያ፣ ለሞት የሚያበቃ መከራ፣ . . .ወዘተ ብለው በማለት ተርጉመውታል (ኪ.ወ.ክ ፰፻፹፫።)እነዚህ ቃላት ዘርዘር ተደርገው በምሥጢር ሲብራሩም እንደሚከተለው ሊገለጹ ይችላሉ።
             ፩. በዓል፦ ዕለታት ለእግዚአብሔር ክብር ገላጭና መታሰቢያ ሆነው ከሌሎቹ ዕለታት ሲለዩ የበዓል ቀናት ተብለው ይጠራሉ። በባሕርዩ ቅዱስ የሆነው አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የጸጋ ቅድስና ከሰጣቸው ፍጥረታት መካከል አንደኞቹ ዕለታት ናቸው። እነዚህም ቅዱሳት ዕለታት ሳምንታዊ፣ ወርኃዊና ዓመታዊ በዓላት ተብለው ሊገለጹ ይችላሉ።
               ፪. መስቀል
ሀ. የጌታችንን መከራ በመሳተፍ እርሱን በትንሣኤ (በክብር) የምንመስልበት አንዱ የመንግሥተ ሰማያት በር ነው። ይህንንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል በተደጋጋሚ ገልጾልናል። መስቀሉን አስመልክቶ ጌታችን ካስተማራቸው ትምህርቶችም መካከል ለማሳያ ያህል ብናነሣ፦
 “መስቀሉን የማይዝ፥ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” (ማቴ. ፲፥፴፯)
 “እኔን መከተል የሚወድ ራሱን ይካድ፥ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝም” (ማቴ. ፲፮፥፳፬)
ለ. ሞትና ዲያብሎስ ድል የተደረጉበት መንፈሳዊ የጦር መሣሪያ ነው።
ሐ. ዓለም ከዘለዓለም ሞት የዳነበት፣ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀበት፣ ከሰይጣን ባርነት ነጻ የወጣበት፣ የተዘጋው የገነት ደጅ የተከፈተበትና አባታችን አዳም ከልጆቹ ጋር ወደ ቀደመ ርስቱ ተመልሶ የገባበት የምሥጢር ቁልፍ ነው።
መ. በዳግም ምጽአት ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ ለሁሉ የሚታይ የሰው ልጅ ምልክት ነው። (ማቴ. ፳፬፥፴።)
ሠ. የክርስቲያኖች ትምክሕታቸው (መመኪያቸው) ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት፥ እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ።” (ገላ. ፮፥፲፬።) በማለት እንደገለጸው።
ረ. የሚማፀኑበትና የሚተማመኑበት ክርስቲያኖች ከጠላት ፍላፃ የሚያመልጡበት ትእምርት (ምልክት) ነው። (መዝ. ፶፱፥፬።)
ሰ. ክርስቲያኖችን አሸናፊ የሚያደርግ ኀይለ እግዚአብሔር ነው። “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው።” (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲፰።) እንዲል።
ሸ. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ዙፋን፥ የአዲስ ኪዳንም መሠዊያ ነው።
ቀ. ቅዱሳን መላእክት ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ ጋር በተዋጉ ጊዜ ኃይል ይሆናቸው ዘንድ እግዚአብሔር በክንፋቸው ላይ የቀረፀላቸው የማሸነፋቸው ምሥጢር ነው። (መጽሐፈ አክሲማሮስ)
በዓለ መስቀል ክርስቲያኖች በላዩ ላይ ተሰቅሎ ያከበረውን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስንና ቅዱስ የኾነ መስቀሉን የሚያከብሩበትና አምልኮተ እግዚአብሔርን የሚገልጡበት የከበረ ዕለት ነው። ምእመናንና ምእምናት ጸንተው ምድራዊ የተጋድሎ ሕይወታቸውን በድል አድራጊነት የሚፈጽሙበት መኾኑን የሚመሰክሩበት እና በማያምኑበት ዘንድም እንኳን በናፍቆት የሚጠበቅ በዓል ነው። በዓለ መስቀልን በማክበር ክርስቲያኖች የክርስቶስን መከራ የሚሳተፉበትና በትንሣኤው የተገኘውን ሕይወትና ክብር የሚካፈሉበት ማለትም ክርስቶስን የሚመስሉበት፥ ለትውልድ ቀረፃም አዎንታዊ ሚና ያለው ተግባራዊ የሕይወት ትምህርት ቤት ነው። ከዘጠኙ ንዑሳት የጌታ በዓላት መካከል አንደኛው በዓለ መስቀል መኾኑ ይታወቃል። ይኸውም መስከረም ፲፯ እና መጋቢት ፲ ቀናት በአንድነት እንደ አንድ ቀን (በዓል) ተቆጥረው ነው።

                                                                       ለ. ክብረ መስቀል
መስቀሉ እንደሚታወቀው ሁሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ይገልጽ ዘንድ፣ሞትን በሞቱ ይገድለው ዘንድ፣ ትንቢቱንና ምሳሌውን ይፈጽም ዘንድ፣ መስተፃርራንን (ጠላቶች የነበሩትን) ያስታርቅ ዘንድ፣ የዲያብሎስን ጥበብ ያፈርስና ወጥመዱን ይሰብር ዘንድ፣ ጥበበኛ ነን ብለው የሚመኩ የክፉዎችን ጥበብና ምክር ከንቱ ያደርግ ዘንድ በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ ዐደባባይ የተሰቀለበት የክብር ዙፋኑ ነው።
በዓለ መስቀሉን በምናከብርበት ወቅት ሁሉ እነዚህን ምሥጢራት ማሰብ ይኖርብናል። ከበዓላተ መስቀልም በልዩ ሁኔታ ወርኃ መስከረም ከደመራው በዓልና ከመስቀሉ ጋር በተያያዘ ለማስታወስ እንገደዳለን። ይህ ወር ምድር በሥነ ጽጌያት፥ ሰማይም በሥነ ከዋክብት የሚያጌጡበት ከመሆኑም በላይ ምድሩ፣ ሰማዩና ዘመኑ በመስቀሉ በረከት መሞላቱና ፍጥረታት ሁሉ በመስቀሉ እንደሚባረኩ በልዩ ድምቀት የሚታሰብበት ልዩ ወር ነው።
በብሔራዊ ደረጃ (በዐዋጅ) የምናከብርበትም ምክንያት የነገረ ድኅነት ትምህርታችን አካል በመሆኑና በክርስቲያኖች ልቡና ታትሞ ያለ የሕይወታችን ዓርማ ስለሆነ ነው። በመላው ዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅና ዛሬም ተፈልጎ ሊገኝ በማይችል ልዩ፣ ድምቀትና ውበት የምናከብረው በመኾናችንም በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎን ቀልብ (ስሜት) ከመላው የዓለም መዓዝናት ለመሳብ በቅተናል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መዝገብ በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ሊመዘገብም መቻሉ የክብረ መስቀሉ መዓዛ ዓለሙን ምን ያህል እያወደና እየማረከው መሆኑን ያመለክታል።
                                       ሐ. መስቀሉን የምናከብረው እንዴት ነው?
መስቀሉን በላዩ ላይ ተሰቅሎ ያከበረውና የቀደሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ይታወቃል። እኛ መስቀሉን እናከብራለን ስንል ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ባደረገው ቤዛነት የፈጸመልንን የማዳን ሥራ እንመሰክራለን ማለታችን ነው። በዓል የምንለውም ይህንኑ ምስክርነት በልዩ ልዩ መንገድ የምንገልጽበትን ዕለት ማለታችን ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህንን ምስክርነት ለመስቀሉ እንዴት እንደሚሰጡ እንደሚከተለው እናያለን።

  ይቀጥላል……………………………..

በዓለ መስቀል

 

    በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው (ከአሜሪካ )

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን በዓል የምታከብረው መስከረም ፲፯ እና መጋቢት ፲ ቀን ነው። እነዚህም አይሁድ በክፋት ቀብረው ሠውረውት የነበረውን መስቀል ለማግኘት ቁፋሮ የተጀመረበት እና መስቀሉ የተገኘበት ዕለታት ናቸው። ክቡር መስቀሉ ከክርስቲያኖች ተሰውሮ የኖረው ለሦስት መቶ ዓመታት ነው።
  ክቡር መስቀሉ እንዴት ሊጠፋ ቻለ?
መስከረም ፲፮ እና ፲፯ የሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር፦ በክፋት የተመሉ አይሁድ፥ በጌታ መስቀል እና መቃብር ምክንያት ይፈጸሙ የነበሩትን አያሌ ተአምራት አይተው በምቀኝነት መነሣሣታቸውን ይተርካል። አይሁድ በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ እስከ ፷፬ ዓ.ም ድረስ ምንም ኃይል አልነበራቸውም። ከ፷፬ ዓ.ም በኋላ ግን ራሳቸውን ከሮማውያን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በጀመሩት ዓመጽ ኢየሩሳሌምን ሙሉ በሙሉ ተቈጣጠሩ።
በዚህን ጊዜ ክርስቲያኖቹን ወደ ጌታ መስቀል እና መቃብር እንዳይቀርቡ ከልክለው ቦታውን የቆሻሻ መድፊያ አደረጉት። ከብዙ ጊዜ በኋላ ሥፍራው ትልቅ ጉብታ ሆኖ ከቦታው ጋር ተመሳሳለ። ከዚህም ጋር እስራኤል በየጊዜው ይማርኩ ስለነበር፥ ከምርኮ ሲመለሱም የከተማዪቱ መልክ ስለሚለዋወጥባቸው መስቀሉ የተቀበረበትን ትክክለኛ ጉብታ መለየት አልተቻለም። በተለይም ከ፻፴፪ – ፻፴፭ ዓ.ም በተደረገው ጦርነት ኢየሩሳሌም ፈጽማ ጠፍታ ነበር። ዳግመኛም ንጉሥ ሐድርያን በ፻፴፭ ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን በአዲስ ፕላን በመሥራቱና በጎልጎታ የቬነስን መቅደስ በመገንባቱ ክርስቲያኖቹ ምንም ማድረግ አልተቻላቸውም ነበር። ያን ጊዜ ጎልጎታ ከከተማዋ ውጪ ነበር፥ ዛሬ ግን በአሮጌዋ የኢየሩሳሌም ከተማ ክልል ይገኛል።
  መስቀሉ እንዴት ሊገኝ ቻለ?
ክቡር መስቀሉን ፈልጋ ያገኘችው የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ናት። ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች ሙሉ ነፃነት የሰጠ ደገኛው የሮም ንጉሥ ነበር። ከዚያ በፊት ምንም ነፃነት አልነበራቸውም።ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች የሰጣቸው መብት፦
፩ኛ ቤተ ክርስቲያንን ከግብር ነፃ አደረጋት።
፪ኛ፦ ከመንግሥት ገቢ ለቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ድርሻ ሰጣት።
፫ኛ፦ ዕለተ እሑድ የክርስቲያኖች የበዓል ቀን በመሆኗ በግዛቱ ሥራ እንዳይሠራ በ፫፻፳፩ ዓ.ም አወጀ።
፬ኛ፦ ለቤተ ክርስቲያን ኑዛዜ የመቀበልና ውርስ የመውረስ መብት ሰጣት።
፭ኛ በክርስቲያኖች መካከል ለሚፈጠሩ አንዳንድ አለመግባባት፥ ወንጀል ነክ ላልሆነ ጉዳይ ለኤጲስ ቆጳሳት የዳኝነት ሥልጣን ሰጣቸው።
፮ኛ፦ ክርስትና የአገሩ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አደረገ።
በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን የወንጌልን የመዳን መልእክት እያወጀች ሐዋርያዊ ጉዞዋን እንድትቀጥል ያደረገ ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ ነው። ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ይህን ያደረገበት ምክንያትም በመስቀል ምልክት የተደረገለት ተአምር ነበር። ይኸውም የሮምን የምዕራቡን ክፍል ይገዛ የነበረው ማክሴንዲዮስ የጦር ኃይሉን ባዘመተበተት ጊዜ፥ እርሱም በበኩሉ «ምታ ነጋሪት፥ ክተት ሠራዊት»ብሎ ለጦርነት ተዘጋጀ። ገና በዝግጅት ላይ እንዳለም፦ «በዚህ ድል ታደርጋለህ፤» የሚል በመስቀል ቅርጽ የተጻፈ ጽሑፍ በጠፈረ ሰማይ አየ። በዚህን ጊዜ፦ ሠራዊቱ በፈረሱ አንገት፥ በጋሻው እምብርት መስቀላዊ ቅርጽ እንዲያደርግ አወጀ።
ሮምን ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ መግዛት የጀመረው ከዚህ በኋላ ነበር ።ከዚያ በፊት ለአርባ ዓመታት ለአራት ተከፍላ በኋላም ለሁለት ተከፍላ ትተዳደር ነበር። ጦርነቱም በመስቀሉ ኃይል ጠላቶቹን ድል አድርጎ ተመለሰ እናቱ ንግሥት ዕሌኒ በልጇ ዘመን የተገ   ኘውን የክርስትና ነፃነት ተጠቅማ በ፫፻፳፯ ዓ.ም. ክቡር መስቀሉን ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች። በዚያም ጉብታ የሆነውን ሥፍራ ሁሉ በማስቆፈር ብዙ ብትደክምም መስቀሉን ለማግ ኘት አልቻለችም። በዚህን ጊዜ ኪራኮስ የተባለው አረጋዊ፦ «ደመራ አስደምረሽ፥ ዕጣን አፍስሰሽ፥ ብታቀጣጥዪው ጢሱ ይመራሻል፤» ባላት መሠረት ሳትጠራጠር አደረገችው። የዕጣኑ ጢስ መስቀሉ ከተቀበረበት ጉብታ ላይ እንደ ቀስተ ደመና ተተክሎ በጣት ጠቅሶ የማሳየት ያህል አመለከታት።
ቁፋሮ ውም መስከረም ፲፯ ተጀምሮ መጋቢት ፲ ተፈጸመ። የተገኙት ሦስት መስቀሎች ስለነበሩ የክርስቶስን መስቀል በተአምራቱ ለዩት። ዕውር አበራ፥ አንካሳ አረታ፥ ለምጽ አነጻ፥ ሙት አስነሣ። ንግሥቲቱም ያን ተአምራትን የሚያደርግ ቅዱስ መስቀል የከበረ ቤተ ክርስቲያን አሠርታ በክብር እንዲቀመጥ አደረገች።
መስቀል፤ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ተላልፎ በመሰጠት ቅዱስ ሥጋውን የቆረሰበት፥ ክቡር ደሙንም ያፈሰሰበት ነውና ሃይማኖታዊ ትርጉም አለው። መሰቀል ድኅነታችን የተፈጸመበት (መዳናችን የተረጋገጠበት) ነው «ኢየሱስም ሆምጣጣውን ከተቀበለ በኋላ ተፈጸመ፥ አለ»ይላል (ዮሐ፲፱፥፴) በመስቀል ላይ የተፈጸመው ድኅነታችን (መዳናችን) ነው። ይኸውም የዕለት ፅንስ ሆኖ በማኅፀነ ድንግል ማርያም የጀመረውን የማዳን ሥራ ነው(ሉቃ. ፩፥፴፩)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «በእርሱም እንደ ቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፥ ኃጢአታችንም ተሠረየልን።» ብሏል። መድኃኒት ከድንግል ማርያም መወለዱን ለእረኞች አስቀድመው የሰበኩት ቅዱሳን መላእክት ናቸው(ሉቃ. ፪፥፲፩)መርገመ ሥጋ መርገም ነፍስን የተወገደበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የተወገደበት ነው አዳምና ሔዋን ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፋቸው የወደቀባቸው የሥጋና የነፍስ መርገም ለሰው ልጅ በጠቅላላ ተርፎት ነበር። «ነገር ግን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከአዳም እስከ ሙሴ (እስከ ክርስቶስ) የበደሉትንም ያልበደ ሉትንም ሞት ገዛቸው።» ይላል( ሮሜ ፭፥፲፬) ሙሴ ለክርስቶስ ምሳሌ ነው። በኦሪቱ እንደተጻፈው በእንጨት ተሰቅለው የሚሞቱ ርጉማን ነበሩ( ዘዳ.፳፩፥ ፳፫)
ይህንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው፥ ተብሎ ተጽፎአልና፤ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ (መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን ያመጣብንን ኃጢአት ለመደምሰስ ተላልፎ በመሠዋት) ከሕግ እርግማን ዋጀን።» በማለት ገልጦታል (ገላ. ፫፥፲፫) ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።»ብሏል (፩ኛ ጴጥ. ፪፥፳፬)

ዲያብሎስ የተሸነፈበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል፤ ዲያብሎስ የተሸነፈበት ነው ጥንተ ጠላታችንን (ገነትን ያህል ርስት፥ እግዚአብሔርን ያህል አባት ያሳጣንን ዲያብሎስን) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድል ያደረገልን በመስቀሉ ነው።«ጥልን በመስቀሉ ገደል፤» ይላልና። (ኤፌ.፪፥፲፮) ጥል የተባለው ለሰውና ለእግዚአ ብሔር መጣላት ምክንያት የሆነ ዲያብሎስ ነው። እኛም በኃይለ መስቀሉ ድል እያደረግነው የምንኖር ሆነናል።
   የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ቅዱስ መስቀል
መሰቀል የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ነው፤የጥል ግድግዳ የተባለው ኃጢአት ነው። እርሱም ሰውና እግዚአብሔ ርን ለያይቷቸው ኖሯል። «በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሠውሮታል።» ይላል (ኢሳ.፶፱፥፪) ይህ ከእግዚአብሔር ለያይቶን እግዚአብሔርን ሰውሮብን የኖረ የጥል ግድግዳ (በዲያብሎስ ምክር የተሠራ ኃጢአት) የፈረሰው በመስቀል ላይ በተፈጸመ የክርስቶስ ቤዛነት ነው። «በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው አፈረሰ፤» እንዲል (ኤፌ ፪፥፲፭)
ዕርቅ የተፈጸመበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል ዕርቅ የተፈጸመበት ፣ሰውና እግዚአብሔር የታረቁት በመስቀል ላይ በተፈጸመ ካሳ ነው። ሰውና እግዚአብሔር በመታረቃቸው ነፍስና ሥጋ፣ሰውና መላእ ክት፣ሕዝብና አሕዛብም ታርቀዋል። እኛ በበደልን እርሱ ክሶ (የደም ካሣ ከፍሎ ) ታርቆናል።«ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ታረቅን።»ይላልና (ሮሜ ፭፥፲፣፪ኛ ቆሮ. ፭፥፲፰፣ኤፌ.፪፥፲፮)በሌላ በኩል ደግሞ «ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማይ ላሉ ሰላምን አደረገ።» የሚልም አለ (ቈላ. ፩፥፳)
አምላካዊ ይቅርታ የተገኘበት ነው፤«አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።» በማለት ገር ፈው የሰቀሉትን በቃሉ ይቅር ብሎአቸዋልና (ሉቃ.፳፫፥፴፬) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦በሞቱ የሰውን ዘር በጠቅላላው ይቅር እንዳለው ሲናገር፦«አሁን ግን በፊቱ ለመቆም የተመረጣችሁና ንጹሓን፥ ቅዱሳንም ያደርጋችሁ ዘንድ በሥጋው ሰውነት በሞቱ ይቅር አላችሁ።»ብሏል (ቈላ.፩፥፳፪)
አምላካዊ ሰላም የተሰጠበት የተገኘበት ቅዱስ መስቀል
ነቢዩ ኢሳይያስ፦«ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም (ወልድ) ተሰጥቶናልና፥ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።»በማለት ትንቢት የተናገረለት አምላክ ፍጹም ሰላምን የሰጠን በመስቀሉ ላይ በፈጸመው ቤዛነት ነው።(ኢሳ.፱፥፯) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦«መጥቶም ቀርበን ለነበርነው ሰላምን፥ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን ሰጠን።» ብሏል( ኤፌ ፩፥፲፯)
      የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት ነው። ጌታችን የማታ ተማሪ የነበረውን ኒቆዲሞስን ሲያስተምረው፦ «እግዚአብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፤»ብሎታል።( ዮሐ.፫፥፲፮) ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ የጻፈውን የጌታችን ትምህርት መሠረት አድርጎ፦ «በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ላይ ታወቀ፥ በእርሱ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። የእግዚአብሔርም ፍቅሩ ይህ ነው፥ እርሱ ወደደን እንጂ እኛ የወደድነው አይደለንም፥ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ልጁን ላከው።»ብሏል (፩ኛ ዮሐ ፬፥፱-፲፩)

                                                                               የገነት በር የተከፈተበት ቅዱስ መስቀል
መስቀል የገነት በር የተከፈተበት ነው፡፡ ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው፥ ድኅነተ ምእመናንንም በመስቀል ላይ የፈጸመው ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተዘግታ የነበረችውን ገነትን ለመክፈት ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ፥ በቀኙ ተሰቅሎ፥ «አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ»እያለ ሲማጸነው የነበረውን ወንበዴ፦«እውነት እልሃልሁ፥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ» ብሎታል(ሉቃ. ፳፫፥፵፪-፵፫)

  የምንመካበት ቅዱስ መስቀል
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦«ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት (ዓለም በእኔ ዘንድ ሙት የሆነበት)፥ እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት (እኔም በዓለም ዘንድ ሙት የሆንኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ፤»ብሏል፡፡(ገላ. ፮፥፲፬)
በመሆኑም ዓለምና ቅዱስ ጳውሎስ በጌታ ደም ላይ በተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን እና በደሙ በጸናች ወንጌል ምክንያት ተለያይተዋል። አንዳቸው ለአንዳቸው ሙት ናቸው። ዓለም ሕያው የሆነችልን፥ እኛም ሕያው የሆንላት የሚመስለን የዓለም ፈቃድ ፈጻሚዎች ከቅዱስ ጳውሎስ ልንማር ይገባል። ዓለም ታልፋለች፥ እኛም ከእሷ እንለያለንና።
                                                                                  ከአጋንንት የምንድንበት ቅዱስ መስቀል
በክርስቶስ ቅዱስ መስቀል ከአጋንንት ጦር እንድናለን ቅዱስ ዳዊት በትንቢት፦ «ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፥ ከቀስት ፊት (ከአጋንንት ጦር) ያመልጡ ዘንድ ወዳጆችህም እንዲድኑ።» ያለው ስለ መስቀል ነው። (መዝ.፶፱፥፬) በመሆኑም በመስቀል ምልክት አማትበን፥ ከአጋንንት ፈተና እንድናለን። መስቀል ኃይላችን ነው መስቀልን በእጅ መጨበጥ፥ በአንገት ማንጠልጠል፥ መሳለም በዓለም ዘንድ ሞኝነት ነው ለእኛ ለክርስቲያኖች ግን ድኅነት የተረጋገጠበት ነው። ለዚህም ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና» በማለት ያስተማረን ፡፡(፩ኛቆሮ.፩፥፲፰)
በመሆኑም በቀራንዮ በመስቀል ላይ አንድ ጊዜ የተገለጠ ኃይለ እግዚአብሔር እስከ ዘለዓለሙ አይለየንም። በመሆኑም ለቅዱስ መስቀሉ እንሰግዳለን። ቅዱስ ዳዊት፦ «እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን።» በአለው መሠረት የጌታችን እግሮች በመስቀል ላይ፥ ያውም በቀኖት ላይ ስለቆሙ ለመስቀሉ እንሰግዳለን። መስቀሉን በደሙ ቀድሶታልና፥ ለመስቀሉ የሚገባውን ክብር እንሰጣለን። እግዚአብሔር በረድኤት በደብረ ሲና ራስ በቆመ ጊዜ፥ «ወደዚህ አትቅረብ፥ የቆምክባት ሥፍራ የተቀደሰች ናትና፥ ጫማህን ከእግርህ አውጣ፤» በማለት ሙሴን አስተምሮታል፡፡(ዘዳ.፫፥፭)
እንኳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ይቅርና የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የቆመበትን መሬት፥ የተቀደሰ በመሆኑ፦«አንተ የቆምክበት ሥፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግር አውልቅ።» በማለት ኢያሱን ሲያዘው እርሱም የታዘዘውን እንዲደረግ ተረድተናል (ኢያ.፭፥፲፭) እንግዲህ መሬቱን፥ አፈሩን የቀደሰ አምላክ ፦ ሥጋውን የቆረሰበትን፥ ደሙን ያፈሰሰበትን፥ ነፍሱንም አሳልፎ የሰጠበትን መስቀል አልቀደሰውም ለማለት እንዴት ይቻላል? ፈጽሞ አይቻለም።ንግሥት ዕሌኒ በብዙ ድካም ከወርቅ ዙፏኗ ወርዳ ከአፈር ላይ ተቀምጣ፥ቆፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታለች።ዛሬ በእኛ ዘመን የተቀበረው ዳግም በመስቀሉ ያ የተገኘው ፍቅርና ሰላም ነው።
ፍቅር በጥላቻ፥ሰላም በጦርነት፥አንድነት በመለያየት፥እምነት በክሕደት፥ መንፈሳዊነት በሥጋዊነት የሕዝቦች ውሕደት በዘረኝነት ቆሻሻ ተቀብሮአል።ይህንን ቆፍረን ካወጣን ያን ጊዜ የዘመኑ ዕሌኒዎች እንሆናለን። መስቀሉን ተሸክመን በጥላቻና በዘረኝነት ቆሻሻ የተቀበርንም በቅድሚያ ራሳችንን ቆፍረን እናውጣ፥ ለብዙዎችም እንቅፋት አንሁን።ዘመኑን ከተቀበርንበት የምንወጣበት ያድርግልን።
የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፥ የመስቀሉ በረከት አይለየን፥ አሜን።