ጉባኤ-ቃና መጽሔት-ነሐሴ-2016-ዓ.ም

ጉባኤ-ቃና መጽሔት-ነሐሴ-2016-ዓ.ም

ማኅበራዊ ሚዲያና ወጣቶች

ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ መግለጫ

የቤተ ክርስቲያናችን ስደት የሚቆመው ሁላችንም ድርሻችንን ስንወጣ ነው!!!

“ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፡፡” (ይሁዳ ፩፥፫)

ማኅበረ ቅዱሳን ከሦስት ዓመት በፊት ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሁለንተናዊ የአስተሳሰብ ውጊያ ሲደረግባት ቆይቷል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ውጊያ በጊዜ ሂደት መዋቅራዊና ስልታዊ ሆኖ ቀጥሎ ይኸው ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ከስደት አልተመለሰችም፡፡ ይልቁንም የቤተ ክርስቲያን መከራና ስደት በዓይነቱ ተለይቶ፣ ድግግሞሹ በዝቶ፣ በመጠኑም ጨምሮ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ባሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ በቤተ ክርስቲያንና በልጆቿ ላይ ተጠናክረው የተፈጸሙ ድርጊቶች በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች በተከታታይ ካህናት፣ መነኮሳትና ምእመናን በሃይማኖታቸው ተለይተው ተገድለዋል፣ ተሰደዋል፣ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ተቃጥለዋል፡፡ በተጨማሪም ንብረታቸውንም እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መዋቅርም እንዲናጋ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ በውስጥና በውጭ ባሉ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ቅንጅት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚፈታተኑ ተግባራት በድፍረትና በማን አለብኝነት ተፈጽመዋል፡፡ በቅርቡም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳገቡ መደረጋቸው፣ በተመሳሳይ በዝቋላ ገዳም መናኝ አባቶች ላይ የተፈጸመው የግፍ ግድያ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመ መዋቅራዊ ጥቃት ማሳያ ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በነነዌ ጾም መልእክታቸው ላይ እንዳስተላለፉት፡፡

“ይህንን የነነዌ ጾም ልንቀበል ዋዜማ ላይ ባለንበት በዚህ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ ከሆኑት ገዳማት አንዱ በሆነው በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የሚገኙ፣ ዓለሙን ትተው በፈቃዳቸው ረኃብተኛ እና ጥማተኛ ሆነው ሀገርን በጸሎት የሚጠብቁ መነኮሳት ጫካው መኖሪያችሁ፣ ዳዋው ልብሳችሁ፣ ቅጠሉ ምግባችሁ መሆን አይችልም ተብለው የሰማዕትነት ጽዋ ተጎንጭተዋል፡፡ እነርሱ በሥጋ እየሞቱ እኛም በየቀኑ ሟቾችን እየቆጠርን በኀዘን ለመኖር የተፈረደብን ሆኗል” ብለዋል፡፡

በሀገራችን ውስጥ የሕግ የበላይነት እስካልሰፈነና ጠያቂና ተጠያቂ እስካልኖረ ድረስ ወደፊትም በባሰ ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ስደት ይቆም ዘንድ የቤተ ክርስቲያን ልዕልና ይከበር ዘንድ ሁላችንም የድርሻችንን ለመወጣት በያለንበትም ሆነ በጋራ በመናበብ ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሥጋ ጥቅምን፣ ምድራዊ ሥልጣንና የግል ፍላጎትን አስወግደን በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሁላችንም ቁርጥ መንፈሳዊ አቋም በመያዝ ለሃማኖታችን ዘብ ልንቆምና የድርሻችንን በትጋት ልንወጣ እንደሚገባ ማኅበረ ቅዱሳን እያሳሰበ ለቤተ ክርስቲያን አካላት ሁሉ ጥሪውን ያስተላልፋል፤

  1. የተከበራችሁ አበው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሆይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድሮ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” እንዳለ በዚህ ታላቅ የፈተና ወቅት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማስጠበቅ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጣችሁን ኃላፊነት ለመወጣት ምእመናንን አቅጣጫ በመስጠት የቀደሙ አባቶቻችሁን ፈለግ በመከተል ዛሬም በጽናት እንድትተጉ፤ ያከበረቻችሁን ቤተ ክርስቲያን በአንድነት ሆናችሁ እንድትጠብቁ በልጅነት መንፈስ በትሕትና እንጠይቃለን፡፡ በተጨማሪም የአባትነት የዋህ ልቡናችሁን በመጠቀም ያዘኑ፣ የጠቀሙ፣ የተቆረቆሩ መስለው ቀርበው የግል ፍላጎታቸውን ለመፈጸም የሚጥሩ ስለሚኖሩ ሁሉንም በጥንቃቄ እንድትመረምሩ፣፤ ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን በመዋጀት አንድነታችሁን እንድታጠነክሩና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ለሚፈጠሩ ችግሮች በጥልቀት እንድትወያዩና እንድትመካከሩ እናሳስባለን፡፡
  2. ከዚህ ውጭ ቤተ ክርስቲያንን በማይጠቅማት ጉዳይ የግል ፍላጎትንና ምድራዊ ዓላማን መሠረት አድርጋችሁ ከቤተ ክርስቲያን ሕግ ቀኖና ውጭ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊን ለመተካት፣ ፓትርያርክ ለመሾምና የመሳሰሉትን ለመፈጸም የምትንቀሳቀሱ አንዳንድ አባቶች ከድርጊታችሁ እንድትታቀቡ ለማሰብ እንወዳለን፡፡ ማኅበራችን ይህንን ጉዳይ እየተከታተለ መረጃውን ለምእመናን የሚያደርስ መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ እንገልጻለን፡፡
  3. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መምህራነ ወንጌል፣ ካህናት ሆይ በጸሎትና በትምህርት ምእመናንን በማጽናናት፤ ከእውነት ጋር በመቆም እውነታውን በማሳየት ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ዘብ እንዲቆሙ በማድረግ ድርሻችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን፡፡
  4. ውድ ምእመናንና የማኅበራችን አባላት የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ከአሳዳጆቿ የመጠበቁ ዋነኛ ኃላፊነት በዘመኑ ባለን ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናትና ምእመናን ሁላችን እጅ ላይ ወድቆአል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ለአባቶችና ለካህናት ትተን “እኔ አያገባኝም፣ አይመለከተኝም” ልንል አይገባም፡፡ ሁሉም በየድርሻው ቤተ ክርስቲያኑን ለመጠበቅ መትጋት አለበት፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ጥፋትና ሊመጣ ያለውን ፈተና አስቀድሞ በመረዳት ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በወሰነው መሠረት በየአጥቢያችን፤ በተለያየ መልኩ በመደራጀት፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥፋት ለማድረስ የሚመጡትን በመከላከል የቤተ ክርስቲያንን ስደት ለማስቆም መንፈሳዊ ግዴታችን እንድንወጣ እንጠይቃለን፡፡
  5. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በልዩ ልዩ አገልግሎት እየተሳተፋችሁ ያላችሁ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ማኅበራትና ሌሎችም ሁላችንም አንድነታችንን በመጠበቅ በጋራ አገልግሎቶችን በመፈጸም ድርሻችንን እንድንወጣ ለተግባራዊነቱ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
  6. ገዳም ድረስ ገብቶ መሳሪያ ያልያዙና ራሳቸውን እንደ ሞቱ ቆጥረው እየኖሩ ያሉ መነኮሳት ላይ ግድያ የፈጸመ ማንኛውም የታጠቀ ኃይል (መደበኛም ይሁን ኢመደበኛ፣ በግልም ይሁን በቡድን፣ አማኝም ይሁን ኢአማኝ) ድርጊቱ ከሰውነት ተፈጥሮ የወጣ ነው፡፡ ምናኔንና የክህነት ክብርን በተቃረነ መልኩ ሰብእና የጎደለው ጥቃት ማድረስ ኢትዮጵያዊ ባህልም አይደለም፡፡ ጥቅም የሌለው ከንቱ ተግባር ነው፡፡ በዚህ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ ጤነኛ በሆነ አእምሮ ታስቦ የተፈጸመ ነው ማለትም አይቻልም፡፡ ማስተዋል ተወስዶባቸው እውቀት ተሰውሮባቸው እንጂ ይህንን ማድረግ ቀርቶ ማሰቡም የሙት ሐሳብ ነው፡፡ ቀድሞ የሞተው ሟቹ ሳይሆን ገዳዩ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የቤተ ክርስቲያን አማኞች ሲበዙ እንጂ ሲያንሱ በታሪክ አልታየም፡፡ ይህ ድርጊት ክርስቲያኖችን ሲያጠነክር እንጂ ሲያዳክም ታይቶ አይታወቅም፡፡ መጽሐፍ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንን ቤት ገፋው፤ በዐለት ላይ ስለተመሠረተ አልወደቀም” ባለው መሠረት ቤተ ክርስቲያን በጽኑ ዐለት ላይ የተመሠረተች ስለሆነ አታሸንፏትም፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም አላጠፋትም፤ ዲያብሎስም ዝናሩን እንዲሁ ጨረሰ፡፡ ስለዚህ አትድከሙ፤ አትሳቱም፡ እናንተ ሳትወለዱም የነበረች ቤተ ክርስቲያን እናንተም አልፋችሁም እንደ እናንተ ላሉት በስሑት መንገድ ለሚጓዙት ሁሉ እየጸለየች ትቀጥላለች፡፡ ሐሳቧም፣ ሥራዋም፣ ዓላማዋም፣ ግቧም ሰማያዊ ነውና፡፡

በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያን ሕልውና በላይ የሚያስቀድመው የሌለ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ፈተና ለማለፍ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት ጋር በመናበብ የሚጠበቅበትን መንፈሳዊ ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እያሳወቅን የሁላችንም መሰባሰብና የአገልግሎት ማእከል ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ ከሁሉም ነገር በፊት ቅድሚያ ሰጥተን ሊመጣ ካለው አደጋ ቤተ ክርስቲያናችንን የመጠበቅ ኀላፊነት በትጋት እንወጣ ሲል ማኅበረ ቅዱሳን በአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!!!

“የግቢ ጉባኤያት ተመራቂዎች ዲጂታል የምረቃ መጽሔት ዘመኑን ለዋጀ አገልግሎት አንዱ ማሳያ ነው”

በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ የተዘጋጀው የግቢ ጉባኤያት ተመራቂዎች ዲጂታል የምረቃ መጽሔት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት አንዱ ማሳያ መሆኑን የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ መ/ር ዋሲሁን በላይ  ገለጹ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ከዐሥር ወራት በላይ መረጃ በማሰባብ የዲጂታል መጽሔቱን ለማዘጋጀት ጊዜ እንደወሰደበትና በጥሩ አፈጻጸም መጠናቀቁን ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በነበረው የመጽሔት ምረቃ መርሐ ግብር ላይ ገልጸዋል፡፡ የዲጂታል የምረቃ መጽሔት ማዘጋጀት የተጀመረው ከ፳፻፲፩/፲፪ ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ለዐራተኛ ጊዜ መዘጋጀቱንና ወደፊትም እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኀላፊ አቶ አበበ በዳዳ በበኩላቸው ይህን የዲጂታል መጽሔት ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶችን ሲያብራሩም “በወረቀት መጽሔት ታትሞ ለተመራቂዎች ለማድረስ ከፍተኛ የሰው ኀይልና የገንዘብ ወጪ መጠየቁ፣ የግቢ ጉባኤያት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣትና የወረቀት ዋጋ መናር፣ ወደ ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት ለማዳረስ ከፍተኛ ወጪ መጠየቁ፣ …” ወደ ዲጂታል መጽሔት ዝግጅት ለመሸጋገር በምክንያትነት ካነሧቸው ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

የዲጂታል መጽሔቱን ለማዘጋጀት ሲጀመር በተማሪዎች ዘንድ በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ግን ተማሪዎች እየተረዱት በመምጣታቸው ቁጥራቸው ሊጨምር እንደቻለ አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡ እንደ ችግር ካነሧቸው ውስጥም፡- ከሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ጋር ተያይዞ ያልተካተቱ ግቢ ጉባኤያት መኖራቸው፣ አስፈላጊ መረጃዎችን በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት አሰባስበው ያለመላካቸው፣ የጽሑፎች መዘግየት፣ በወረቀት እናሳትማለን እያሉ ተማሪዎቹን ልብ የሚከፍሉ አካላት መኖራቸው፣ ከቅባት አስተምህሮ ጋር ተያይዞ በተማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረው ጫና፣ … የመሳሰሉት ጉዳዮች ይገኙባቸዋል፡፡

የዲጂታል መጽሔቱ ዝግጅት ጠንካራ ጎን በተመለከተም አቶ አበበ ሲገልጹ፡- “መጽሔቱ በየግቢ ጉባኤያቱ ተለይቶ መዘጋጀቱንና በወረቀትም ኮፒ ማድረግ እንደሚቻል፣ ሦስት ቋንቋዎችን ያካተተ መሆኑ (አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና እንግሊዝኛ)፣ የተመራቂ ተማሪዎች የምስጋና ቃል (Last words) መካተቱ፣ ክትትል ላይ ያሉ ግቢ ጉባኤያት መካተታቸው፣ በውጪ ሀገራት ያሉ ግቢ ጉባኤያት መካተት፣ ድጋፍ ሰጪዎች (Sponsers) አካላት ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፋቸውና ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ ማጠናቀቅ መቻላችን ውጤታማ አድርጎናል” ብለዋል፡፡ የዲጂታል መጽሔቱን ለማዘጋጀት ሙሉ ሥራውን በኀላፊነት ወስዶ ውጤታማ አገልግሎት መፈጸም እንዲቻል የበኩሉን ድርሻ የተወጣውን የ“ተክሌ ኮንሰልቲንግ” ድርጅት ኀላፊን ኪዳኔ መብራቱንና በዚህ አገልግሎት ውስጥ የተሳተፉትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡

የዲጂታል መጽሔቱ መታተም ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ አገልግሎቱን በመፈለግ የሚካተቱ ተመራቂ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ የጨመረ ሲሆን በ፳፻፲፩/፲፪ ዓ.ም አሥራ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሠለሳ፤ በ፳፻፲፫ ዓ.ም አምስት ሺህ ስምንት መቶ ሃምሳ አንድ፤ በ፳፻፲፬ ዓ.ም አሥር ሺህ ሃያ ስድስት፤ በ፳፻፲፭ ዓ.ም አሥራ ሁለት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ አምስት ተመራቂዎች ተካ’ተዋል፡፡ የእያንዳንዱ ዓመት ተመራቂዎች ዳታም እንደ ተካተትና አንድ ተመራቂ ተማሪ አገልግሎቱን በስድሣ ብር ማግኘት እንደቻለ በምረቃው ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች

በመ/ር ተመስገን ዘገዬ

ክፍል ፪

የተከበራችሁ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎቻችን በክፍል አንድ ዝግጅታችን ከምረቃ በኋላ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በተመለከተ ሦስት ነጥቦችን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ እነዚህም፡- እንደተመረቁ ሥራ አለመያዝ፣ አለመረጋጋት እና መወሰን የሚሉ ነጥቦችን አይተናል፡፡ ቀጣዩቹን ነጥቦች ደግሞ በክፍል ሁለት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ክርስትናም በእምነት እያደጉ እየጠነከሩ የሚጓዙበት ሕይወት እንጂ ባለህበት እርገጥ ዓይነት አይደለም፡፡ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመራቂ ከትናንት  ዛሬ፣  ከአምና ዘንድሮ አድጎና ጠንክሮ  መገኘት አለበት፡፡ ክርስትና ቱቻ ገመድ አይደለም፡፡ ተቹ  ገመድ ከሣር  የሚዘጋጅ ቆርቆሮ ባልነበረበት ዘመን ለቤት መሥሪያ አገልግሎት ያገለግል  ነበር፡፡ቱቻ ገመድ ውኃ ሲያገኝ በጣም ይጠብቃል፡ውኃ ሲያጣ ለመበጠስ ቀላል ነው፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በግል ሕይወታቸው ሥጋዊውን ኑሯቸውን ከመንፈሳዊ  ኑሯቸው ጋር አጣጥመው መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ብዙዎቻችን መንፈሳዊ ሥራን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጨረስን ይመስል ትተን እንደመጣን በሄድንበት ቦታ በዓለም ፍቅር እንደነዝዛለን፡፡ እንደ ዴማስ በሄድንበት በዓለም ተውጠን እንቀራለን፡፡ “ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና  ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል  ቄርቂስም  ወደ ገላትያ ቲቶም  ወደ ድልማጥያ  ሄደዋል “እንዳለ ( ፪ኛ ጢሞ.፬፥፲)

መጾም መጸለይ ከትናንሽ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በማኀበር ፡ በሰንበት ትምህርት ቤት መቀመጥ ይከብደናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ወንድሞች በኀብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም   ነው፡፡እነሆም  ያማረ ነው” ይላል  (መዝ.133፥1)  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች  ከእግዚእበሔር ክብር ይልቅ የራሳችንን ክብር ይታየናል፡፡ ለሥጋችን ምቾት እንጂ  ለክርስትና መስፋፋት  ግዴለሾችና  በእንቅልፍ ማሳለፍ እናበዛለን፡፡

ስለሆነም ከምረቃ በኋላ የምናገኘው የአካባቢና የኑሮ ለውጥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያመጣ ይችላል፡፡

ስለዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በአካባቢ፣ በጓደኛ፣ በኑሮ ለውጥ ተውጠን   የግል ሕይወታችን ተበላሽቶ እንዳይቀር ራሳችን መግለጽ፤ ዘወትር መጸለይ፤ ከእግዚአብሔር አለመራቅ፤ በማይመች አካሄድ አለመጠመድ፤ ከምክንያተኝነት መራቅ፤ ተስፋ  አለመቁረጥ፤ ኑሮን በመርሐ ግብር መምራት፤ የምሥጢራት ተካፋይ መሆን ይገባል፡፡

ራስን መግለጽ፦ይህ ሲባል ግን  እኔ የማኀበሩ አባል ነኝ፣ እኔ ሰባኪ ነኝ ማለት ሳይሆን  በኑሯችን እንግለጸው ለማለት  ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው  በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት  ይብራ” ብሏል፡፡ (ማቴ .፭፥፲፮)

ክርስትና ማስመሰል ሳይሆን ሁኖ መገኘት ይፈልጋል፡፡ መንፈሳዊ ሕይወታችን ጊዜና ቦታ የሚወስነው ሳይሆን የሁል ጊዜ ኑሯችንና መታወቂያችን ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስትና የምንተርከው ታሪክ ሳይሆን የምንኖረው ሕይወት ስለሆነ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት “ተግባር ከቃል የበለጠ ይሰብካል“ ይላሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን አንደበተ ርቱዕ የሆኑ ሰዎች አላጣችም፤ የተቸገረችው በሕይወቱ አርአያና ምሳሌ የሚሆን ሰው ግን ማግኘት በ፳፩ኛ ክፍለ ዘመን እየተቸገርን ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂ ወጥ የሆነ ክርስቲያናዊ ሕይወት ሊኖረው ይገባል፡፡ ከግቢ ጉባኤው ተመረቆ ሲወጣ መንፈሳዊ አገልግሎትን የሚዘነጋ (የሚተው) ከሆነ  መንፈሳዊ አገልግሎት ማለት ምን  ማለት እንደሆነ ገና አልገባውም ማለት ይቻላል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስ ልጁን ጢሞቴዎስን “ቃሉን ስበክ፣ በጊዜውም አለ ጊዜውም ጽና   ፈጽመህ እየታገሥክና እያስተማርክ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” ብሎታል፡፡ (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፪)      በነገራችን ላይ  ማስተማር በዐውደ ምሕረት አትሮንስ ላይ በመሆን ማስተማር ብቻ አይደለም፡፡ በሕይወት በሥራና  በተግባር  ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች  በምንሄድበት ቦታ ሁሉ፣ በቤታችን ውስጥ፣ በሠፈራችን፣ በሥራ  ቦታችን ክርስትናችን በኑሯችን ሊገለጥ ይገባል፡፡ ክርስትናችን የሚነበብ መጽሐፍ መሆን አለበት ፡፡

“…በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም፣ በንጽሕናም ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን” (፩ኛ ጢሞ. ፬፥፲፩-፲፪) የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ከላይ በተጠቀሱት መሠረታዊ ነጥቦች ስንመዘን ምሳሌ የሚሆን ሕይወት ይኖረን ይሆን? አንዳንዶች ራስን መግለጽ ሲባል “ግብዝነት” ይመስላቸዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው በዓለም ቀልጠው የቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ማንነታችን በሰዎች ዘንድ ከታወቀ ሰዎች ለእኛ ታላቅ ክብር አላቸው፡፡ ይህ ክብር   የእግዚአብሔር መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ እንደ ክርስትና የሚስከብር ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በጸሎት ሕይወት  መበርታት ይኖርባቸዋል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች” ይላል (ያዕ. ፭÷፲፯) ማር ይስሐቅ “ዕንባሕ ከመፍሰስ እንዳያቆም ከወደድህ በጸሎት ጽሙድ ሁን” ይላል። “ጸሎት ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ናት” (ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው አንቀጽ ፲ ወ፬ቱ)

ጌታችንም በመከራው ሌሊት ፫ ጊዜ ጸለየ ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ “አለ፡፡ (ማቴ. ፳፮÷፵፩) የዕውቀት ደጋፊዎችን ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ለጸሎት መትጋት ይኖርብናል። የዲያብሎስ አጽመ ርስት ኃጢአት እንዳይነግስብን በጸሎት ሕይወት ፍኖተ አበውን በመከተል መትጋት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች አንዱ የቤት ሥራ ነው፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ሕዋሳትን ሰብስበን በሰቂለ ኀሊና:በነቂሐ ልቡና ሁነን ወደ እግዚአብሔር መጮኽ አለብን። ከሌሊቱ ዕንቅልፍ በመቀነስ መጸለይ ብልህነት ነው ። የጸሎት መጽሐፍ፣ ምስለ ፍቁር ወልዳ በሁሉም እንቅስቃሴያችን መለየት የለባቸውም፡፡ ጥሩ የጸሎት ሕይወት ያለው ክርስቲያን አይወድቅም፣ ቢወድቅም ይነሳል፡፡

ነቢዩ “ጠላቴ ሆይ ብወድቅ እነሣለሁና በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና “እንዳለ (ሚክ. ፯፥፰) እኛም በሥራችን፣ በአገልግሎታችን መውደቅ፣ መነሣት መኖሩን መረዳት ይኖርብናል፡፡ ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡

የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሕገ ወጡን ተሿሚ አገደ

@የምስራቅ ሐረርጌ ሐገረ ስብከት ጽ/ቤት Eastern Hararge Diocese secretary office

ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ በተፈጸመው “የጳጳስ ሹመት” ከታች የተዘረዘሩት አህጉረ ስብከት ላይ የስም ዝርዝራቸው የሚገኙትን የአህጉረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስ እና ከቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድና እውቅና ውጭ ወረራ እንዲፈጸምበት ስምሪት የተሰጠ በመሆኑ በየአካባቢው የምትገኙ ካህናትና ምእመናን መንበረ ጵጵስና አህጉረ ስብከቱን እንድትጠብቁ ጥሪ ቀርቧል፡፡

1.”አባ” ገ/ማርያም ነጋሳ – ምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት
2.”አባ” ተ/ሃይማኖት ወልዱ – ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት
3.”አባ” ገብርኤል ወ/ዮሐንስ – ጉራጌ ሶዶ ሀገረ ስብከት
4.”አባ” ገ/እግዚአብሔር ታደለ – ምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት
5.”አባ” ሚካኤል ገ/ማርያም – ከምባታ ሀገረ ስብከት
6.”አባ” ኃይሉ እንዳለ – ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት
7.”አባ” ተ/ማርያም ስሜ – ጉጂ ሊበን ሀገረ ስብከት
8.”አባ” ኃ/ኢየሱስ መንግሥቱ – ከፋ ሀገረ ስብከት
9.”አባ” ወ/ኢየሱስ ኢፋ – ቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት
10.”አባ” ጳውሎስ ከበደ – ሀዲያ ሀገረ ስብከት
11.”አባ” ኃ/ኢየሱስ ተስፋዬ – ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት
12.”አባ” ገ/ኢየሱስ ገለታ – ሆሮ ጉዱሩ ሀገረ ስብከት
13.”አባ” ጸጋዘአብ አዱኛ – ምሁር ኢየሱስ ገዳም “የበላይ ጠባቂ”
14.”አባ” ኃ/ማርያም ጌታቸው – ምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት
15.”አባ” ወ/ጊዮርጊስ ኃ/ሚካኤል – ከሚሴ ሀገረ ስብከት
16.”አባ” እስጢፋኖስ ገብሬ – ባሌ ሀገረ ስብከት ረዳት
17.”አባ” ገ/መድኅን ገ/ማርያም – ጎፋ ባስኬቶ ሀገረ ስብከት
18.”አባ” ኃ/ሚካኤል ንጉሤ – ጊኒር ሀገረ ስብከት
19.”አባ” አብርሃም መስቀሌ – ዳውሮ፣ኮንታ ሀገረ ስብከት
20.”አባ” ንዋየ ሥላሴ አክሊሉ – ምዕራብ ጉጂ ሀገረ ስብከት
21.አባ ኪ/ማርያም ቶሎሳ – ጅማና የም ሀገረ ስብከት
22.”አባ” ወ/ማርያም ጸጋ – ቦረና ሀገረ ስብከት
23.”አባ” አምደሚካኤል ኃይሌ – አርሲ (አሰላ) ሀገረ ስብከት
24.”አባ” መርሐጽድቅ ኃ/ማርያም – ጌዴኦ ፣ቡርጁ፣ አማሮ ሀገረ ስብከት
25.”አባ” ሞገስ ኃ/ማርያም – መናገሻ አምባ ቅድስት ማርያም ፣ ጋራ መድኃኔዓለምና ደ/ፀሐይ ቅ/ጊዮርጊስ “የበላይ ጠባቂ”
26.”አባ” ገ/ኢየሱስ ንጉሤ – ቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት
@ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት

ከጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ በዛሬው ዕለት መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

በመግለጫውም የሣውላ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የነበሩት በቀን 14 /5 / 2015 ዓ.ም በአቡነ ሳዊሮስ ከተሰጠው “የጳጳሳት ሹመት” ውስጥ ቆሞስ አባ ገ/መድኅን ገብረማርያም የጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተብለው የተሾሙትን ኮሚቴውና ሕዝቡ የማያውቀው ምንም አይነት ከጥያቄያችን ጋር ግንኙነት የሌለው ስለሆነ ኮሚቴውና ሕዝቡ በአሁኑ ሰዓት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በትዕግሥት መጠበቅ እንደሚገባ እና ቤተ ክርስቲያናችንን በቅርበት ማየትና መከታተል ያስፈልጋል ሲል ኮሚቴው ገልጿል፡፡

ከጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ በዛሬው ዕለት መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

ከጉራጌ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

በአሁኑ ወቅት ኤጲስ ቆጶሳትን ሾምን፤ በሚያገለግሉበትም ቦታ መደብን የሚሉ ሕገ ወጥ አካላት የሕግና የሥርዓት ምንጭ የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክብር የሚያቃልል፤ አንድነቷን የሚከፋፍል፤ ቀኖናዋንና ትውፊቷን የሚሸረሽር ተግባር ፈጽመዋል፡፡ የጉራጌ ሶዶ ሀ/ስብከት ጳጳስና የምሁር ኢየሱስ ገዳም የበላይ ጠባቂ ጳጳስ ተደርገው ሁለት ሰዎች ለጉራጌ ሀ/ስብከት መመደባቸውንም በአግራሞት ተመልክተናል፡፡
በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን የማታውቃቸው ሕገ ወጥ ሿሚና ተሿሚዎች እኛን የሰበሰበችንን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመበተን የሚያደርጉትን የቀኖና ጥሰት ለማውገዝ የጉራጌ ሀ/ስብከት አስተዳደር ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገናል፡፡
በመሆኑም፡-
፩) የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆናችሁ አባቶቻችን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጽናት በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት የምትወስኑትን የአንድነት ውሳኔ በአንቃዕድዎ ሆነን እየጠበቅን መሆናችንን በታላቅ አክብሮት እንገልጻለን፤
፪) የጉራጌ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት፣ የሀ/ስብከቱ ወረዳ አብያተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀ/ስብከቱ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኗ ካህናትና ምእመናን በሙሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ከወትሮው በተለየ ንቃትና ታማኝነት በመጠበቅ፤ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግና መረጃዎችን በመለዋወጥ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ አጥብቀን እናሳስባችኋለን፤
፫) በጉራጌ ዞን በየደረጃው ያላችሁ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅና በማስጠበቅ ሀገራዊ አደራችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የጉራጌ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት
ወልቂጤ-ኢትዮጵያ
ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም.