ከተራ
እንኳን አደረሳችሁ፣ አደረሰን!
ከተራ፦ ከተረ ከበበ ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል፡፡ የምንጮች ውኃም ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይፈስ እንዲጠራቀም ይከተራል፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን “ከተራ” በመባል የሚታወቀው የጥምቀት ዋዜማው ነው። ሠርግው ሀብለ ሥላሴ (፲፲፻፹፩፤ ገጽ ፰) ብለው ሲፈቱት፣ ደስታ ተክለ ወልድ ደግሞ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው (፲፱፻፷፩፤ ፮፺፬) የጥምቀት ዋዜማ፣ ጥር ፲ የሚከበር የጠራ፣ ንጹሕ ወራጅ ውኃ የሚከተርበት፣ ታቦታትና ምእመናን ወደ ወንዝ የሚወርዱበት ጊዜ” ነው በማለት ይፈቱታል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም (፲፱፻፵፰፤ ገጽ ፭፻፶፭) ከተረ የሚለውን ቃል በቁሙ፣ “ዘጋ፣ አቆመ፣ አገደ፣ ከለከለ፡፡” ማለት ነው ብለው ይፈቱታል፡፡
በየዓመቱ ጥር ፲ ቀን የምእመናኑ አብዛኛው ሥራ ውኃውን መከተርና መገደብ በመሆኑ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውኃው የሚከተረው በማግስቱ ጥር ፲፩ ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው፡፡ በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ “ባሕረ ጥምቀት፣ የታቦት ማደርያ” እየተባለ ይጠራል።
በዓሉ የሚከበርበትን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ዳራ
የበዓለ ጥምቀት አከባበር በኢትዮጵያ የተጀመረው የክርስትና እምነት እንደገባ መሆኑ ቢታመንም እስከ ስድስተኛው መ/ክ/ዘመን ድረስ አሁን በምናከብርበት ሁኔታ የሚታሰብበት ሥርዓት አልነበረም። ጥምቀትን በሜዳ እና በውኃ አካላት ማክበር የተጀመረው በዘመነ ዐፄ ገብረ መስቀል (፭፻፴-፭፻፵፬ ዓ.ም ) ሲሆን የቅዱስ ያሬድ (፭፻፭-፭፻፸፪ ዓ.ም) ዜማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ታቦታቱ በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ጠዋት ወደ ወንዝ ወርደው ማታ ይመለሱ ነበር። (ሐመር መጽሄት ጥር/የካቲት ፲፱፻፺፷ ዓ.ም ገጽ ፮)
ከዚህም በተጨማሪ በቅዱስ ላልይበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውና እና በስብከተ ወንጌል ያገለግሉ የነበሩት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በመቐለና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል፡፡ በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት (፩፪፻፷-፲፪፻፸፭ ዓ.ም) በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (፲፪፻፫ ዓ.ም) አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዐተ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዐዋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና ክብካቤ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ ወስነዋል፡፡ የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና አድማሱ ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ፡፡
ከዐፄ ገብረ መስቀል ጀምሮ የአደባባይ በዓል የሆነው የጥምቀት በዓል በ፲፭ኛው ክ/ዘመን በደገኛው ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ(፲፬፻፳፮-፲፬፻፷ ዓ.ም) አማካኝነት ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር ፲ ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ፣ ሀገሩንም በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ ወሰኑ፡፡ ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ (፲፬፻፹፮-፲፭፻) ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበት እና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር፡፡ ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ከአወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ተጀመረ። ( ሐመር መጽሔት ጥር/የካቲት 1998 ዓ.ም)
ታቦታት ከአንድ በላይ ሆነው ወደ ከተራው ስለሚሄዱ እግዚአብሔር አምላክ ለነብዩ ሙሴ “የታቦት መኖር ከእናንተ ጋር የመኖሬ ምልክት ነው” (ዘፀ. ፳፭÷፩) እንዳለው ታቦተ ሕጉን ተሸክመው ዮርዳኖስን እንደ ተሻገሩት ካህናተ ኦሪት፤ ካህናቱ ታቦተ ሕጉን በራሳቸው ተሸክመው የብሉዩን ሥርዓት ከሐዲስ ኪዳን ጋር አንድ አድርገው የሐዲስ ኪዳን መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰቡ ወደ ከተራ (ዮርዳኖስ) ይጓዛሉ፡፡
የከተራ በዓል ምሳሌያት
በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድና የባሕረ ጥምቀቱ መዘጋጀት ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ አለው፡፡ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብሮ መጓዝና ወደ ወንዝ መወረድ የተጀመረው በአሮን ልጅ በአልዓዛር ጊዜ ነው፡፡ ኢያሱ በሙሴ እግር ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርስ ባሕሩ ከሁለት ይከፈልና ወራጁም ይቆም (ይከተር) ነበር፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ወደ ምድረ ርስት ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ሲሻገሩ፡- ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳኑን ታቦት በድንኳን ውስጥ አድርገው ሌዋውያኑ በዙሪያው፣ ካህናቱ ደግሞ በውስጥ ኾነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አድረው በማለዳ ተሻግረዋል (ኢያ. ፫÷፰-፱)፡፡ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብረው የወንዙን ዳርቻ በረገጡት ጊዜ እንደ ክረምት ማዕበል ይወርድ የነበረው ውኃ ግራና ቀኝ ተከፍሎ እንደ ግድግዳ ወደ ላይ ቆሟል፡፡ ሕዝቡ ተሻግሮ እስከሚያበቃ ታቦተ ጽዮንን ያከበሩት ካህናት ከወንዙ መሐል ይቆሙ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት “ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት፤ የካህናት እግሮቻቸው የዮርዳኖስን ውኃ በመርገጣቸው እንደ ጥምቀት ሆናቸው” እንዲል በሐዲስ ኪዳነ ጌታችን ለመሠረተው ሥርዐተ ጥምቀት ምሳሌ ነበር፡
ቤተ ክርስቲያናችን የጥምቀትን ዋዜማ ከተራ ብላ የጠራችው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል፡፡ የታቹም ወደ ታች ሸሽቷል፡፡ የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደ ክምር ተቆልሎ ቀርቷል። ቅዱስ ዳዊት የተመለከተውም ይህንኑ ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ፤ የታቹም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም የመጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡
እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ መሔዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከኃጢአት ቍራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት ወደ ዕረፍት መንግሥተ ሰማያት አቅንተው ለመሔዳቸው ምሳሌ ነው፡፡ ኢያሱ የጌታ፣ እስራኤል የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ምድረ ርስት የገነት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቱን አክብሮ የሚሔደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ ታቦቱ የጌታችን፣ ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ታቦታቱን አጅበው የሚሔዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሓ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸውና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያጠይቃል፡፡ “ጥምቀት የሞቱና የትንሣኤው ምሳሌ ነው፡፡ ከኃጥአን ጋር ተቆጥሮ እንዲጠመቅና እንዲሰቀል የተጻፈውን ቃል ንስሓና ጥምቀት የማያስፈልገው ሲሆን ነገር ግን ፍጹም ኃጥእ መስሎ በዮሐንስ እጅ ጥምቀትን ለመፈጸም በማየ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡” (ኪ.ወ.ክ፤ ፭፲፯)፡፡
ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያን ዘንድ የዝናብ፣ የበረዶ ወራት ነው፡፡ ከወንዝ ዳር ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም፡፡ በመሆኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር፡፡ በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ ድንኳኖች ዳሶች ይጣላሉ፡፡ እኛ በዚህ ወቅት ታቦት ይዘን፣ ከወንዝ ወርደን፣ ድንኳን ተክለን በማክበራችን ይፈጸማል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!