በዓለ ሢመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል

በዲ/ን አብርሃም

ኅዳር ፲፪ ቀን ንዑድ ክቡር የሆነ ለፍጥረቱ ሁሉ የሚማልድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የተሾመበት ዕለት ነው። የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት “ኅዳር ፲፪ በዚህች ቀን ለሰው ወገን የሚያዝንና የሚራራ በእግዚአብሔር ጌትነት ፊት ሁል ጊዜ በመቆም ለፍጥረቱ ሁሉ የሚማልድ የመላእክት አለቃቸው ለሆነ ለቅዱስ ሚካኤል የበዓለ ሢመቱ መታሰቢያ ነው።” (መጽሐፈ ስንክሳር ኅዳር ፲፪፤ ድርሳነ ሚካኤል ዘኅዳር) በማለት ይገልጻሉ፡፡

ሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‘ሚ’- ‘መኑ’፣ ‘ካ’- ‘ከመ’፣ ‘ኤል’- ‘አምላክ’ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ “መኑ ከመ አምላክ፤ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?” ማለት ነው። እግዚአብሔር መልእክትን በፈጠረ ጊዜ ሳጥናኤልን የመላእክት ሁሉ አለቃቸው አድርጎ ሹሞት ነበር። ነገር ግን ሳጥናኤል ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ክብር ትቶ አምላክነትን በመሻቱ በትዕቢቱ ምክንያት ሥልጣኑን ገፍፎ ወደ ጥልቁ ጥሎታል፤ በቦታውም ቅዱስ ሚካኤልን ሹሞታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህን ምክንያት በማድረግ ኅዳር ፲፪ ቀን በየዓመቱ በዓለ ሢመቱን ታክብራለች።

ደጉ እና ሩኅሩኁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በስሙ ለተማጸንን ሁሉ ከእግዚአብሔር የሚያማልደን ምሕረትን የሚያሰጠን መልአክ ነው ”ተውህቦ ምሕረት ለሚካኤል” እንዲል (ሥርዓተ ቅዳሴ)። ቅዱስ ሚካኤል ለፍጥረታት ሁሉ የሚራዳና የሚያዝን በእግዚአብሔር ፊት የሚቆምልን የምሕረትና የሰላም መልአክ ነው። “በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል” (ዳን. ፲፪፥፩) ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤል ‎የቅዱስ ሚካኤልን ክብር ሲገልጥ ይህንን ብሎ ብቻ አልቀረም “ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ” በማለት እኛ የአዳም ልጆች ዲያብሎስ ባዘጋጀልን መሰናክል እንዳንወድቅ የሚረዳን መልአክ እንደሆነ ይናገራል፡፡ (ዳን. ፲፥፲፫)

“ቅዱስ ሚካኤል ሆይ የያሬድ ልጅ ሄኖክ እንደጻፈው። ከልዑል ስም አጠራር ጋር ለተባበረ ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁ። የእግዚአብሔር የምክሩ አበጋዝ ሆይ የተቸገሩትን የተጨነቁትን ዘወትር እንደምትረዳቸው ሁሉ እኔንም ለመርዳት ክንፍህን ዘርግተህ ፈጥነህ ድረስልኝ።” በማለት የቅዱስ ሚካኤልን ተራዳኢነት ይገልጻል፡፡ (መልክአ ሚካኤል)

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት የቅዱስ ሚካኤልንና የሌሎች መላእክትን ክብርና አገልግሎት ሲገልጥ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።”‎ (መዝ. ፴፫፥፯) እንዲል ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰዎች ዙሪያ ሁል ጊዜ ይከባሉ፤ ከሰይጣን ፈተና፣ ከረኃብ፣ ከችግር፣ ከመከራ ሁሉ ያድኑናል። ማዳናቸውም የክርስቶስን የማዳን ሥራ የሚተካከል አይደለም፤ እርሱ በሰጣቸው ጸጋ ከእርሱ ዘንድ ይቅርታንና ምሕረትን በማሰጠት የሚያድኑን ናቸው እንጂ።

ቅዱስ ሚካኤል አርምሞንና ትዕግሥትን የሚያስተምረን መልአክ ነው። “የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንኳን ስለ ሙሴ ሥጋ ከሰይጣን ጋር በተከራከረ ጊዜ የስድብ ቃልን ሊናገር አልደፈረም፤ ‘እግዚአብሔር ይገስጽህ’ አለው እንጂ” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (ይሁዳ ፩፥፱)

የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል ጥበቃው አይለየን! ከበዓሉ በረከት ይክፈለን!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *