ወርኀ ጽጌ
ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ያለው ወቅት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዘመነ ጽጌ ወይም ወርኀ ጽጌ ተብሎ ይጠራል፡፡ ክረምቱ አልፎ ሰማዩ የሚጠራበት፣ የምድር አበቦች የሚፈኩበትና የሚደምቁበት፣ ሜዳውና ሸንተረሩ ልምላሜ የሚላበሱበት፣ ወንዞች የሚጠሩበትና ለፍጥረታት ሁሉ ተስማሚ አየር የሚነፍስበት ጊዜ ነው፡፡
ይህ ወቅት ሄሮድስ ከእኔ ሌላ ንጉሥ እስራኤልን ማን ሊገዛ ይችላል? በሚል በይሁዳ ክፍል በቤተ ልሔም በከብቶች ግርግም የተወለደውን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል መነሣቱን የምናስብብት ጊዜ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም በሕልም ለአረጋዊው ዮሴፍ ተገልጦ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ኑር” በማለት ሲነግረው ሕፃኑና እናቱን ይዞ ሰሎሜን ትረዳቸው ዘንድ አስከትሎ ወደ ግብጽ ሸሸ፡፡

በነቢያት የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ “የይሁዳ ምድር አንቺ ቤተልሔም ከይሁዳ አለቆች ከቶ አታንሺም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና” ተብሎ እንደተጻፈ ሄሮድስ በቅናት ተነሣስቶ በቤተ ልሔምና በአውራጃዎችዋ የተወለዱትን ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች ዕድሜ ያላቸውን ፻፵፬ ሺህ ሕፃናትን አስገደለ፤ ዋይታና ጩኸትም ሆነ፡፡ በነቢዩ ኤርምያስ የተነገረው ትንቢትም ተፈጸመ፡፡ “ራሔል ስለ ልጆችዋ ስታለቅስ ብዙ ልቅሶና ዋይታ በራማ ተሰማ፤ መጽናናትንም እንቢ አለች፤ ልጆችዋ የሉምና” (ማቴ. ፪፥፲፰) ተብሎ እንደተጻፈው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ፀንሳ በነበረች ጊዜ ለአረጋዊው ዮሴፍ አንዳንድ ጊዜ ቀይ የነበረው መልኳ ተለውጦ እንደ ሮማን አበባ ቀይ፣ ቀይ የነበረው ጸዓዳ ነጭ አበባ፣ ነጭ የነበረው እንደ ጽጌረዳ ቀይ ሲሆንና የሚያውቀው መልኳ ሲለዋወጥበት ዮሴፍ እየደነገጠ እርሷ መሆኗን “ማርያም” እያለ ያረጋግጥ ነበር፡፡ (ነገረ ማርያም) ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ “የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም” ያለውን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲተረጉመው “መልኳ እንደ ጽጌረዳና እንደ ሮማን አበባ ይለዋወጥበት ስለነበር በአንድ ዓይነት መልክ አላወቃትም” ብሏል፡፡ (ማቴ. ፩፥፳፭) ያንን ለማውሳት ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ያለው ወቅት ወርኀ ጽጌ ተባለ፡፡
የእመቤታችን ወደ ግብፅ ሀገራችን ኢትዮጵያ መሰደድ
ጌታችን ሁለት ዓመት ሲሞላው ሄሮድስ ሊገለው እንደፈለገ የእግዚአብሔር መልአክ ለአረጋዊው ዮሴፍ ከተናገረው በኋላ ወደ ግብፅ ሲሰደዱ በርካታ መከራዎችን አስተናግደዋል፡፡ የቀን ሐሩር፣ የሌሊት ቊር እየተፈራረቁባቸው፣ እሾሁ እየወጋቸው፣ እንቅፋቱ እየመታቸው፣ መውጫና መግቢያው በማይታወቅ በረሃ ውስጥ ብዙ ተሰቃይተዋል፡፡
በግብጽ በረሃ ሲጓዙም እመቤታችን ወደ ትዕማን ቤት በሄደች ጊዜ የቤቱ እመቤት ስታያት “ከየት መጣሽ?” ብላ ጠየቀቻት፤ እመቤታችንም “ከይሁዳ ምድር የተሰደድኩ ስደተኛ ነኝ” አለች፡፡ “አንቺ ሴት ደረቅ ነሽ መሰለኝ፤ በድርቅናሽ ቤትሽን ትተሽ ትዞርያለሽ፤ እንዳንቺ ያለች ቆንጆ ሴት ከአዳራሽ ወደ ዕልፍኝ ይላል እንጂ ሀገሩን ትቶ ሀገር ለሀገር አይንከራተትም” ብላ ተተናኮለቻት፡፡ (ነገረ ማርያም) ዮሴፍም “ለለማኝ ቢኖር ይሰጡታል፤ ባይኖር ደግሞ ካለበት ያድርስህ ይባላል እንጂ እንዲህ እንደ ፍላጻ ልብ የሚወጋ ነገር ምን ያናግርሻል” ብሎ በመለሰላት ጊዜ ኮቲባ የተባለችው የእመቤቲቱ አገልጋይ “ይህ ሽማግሌ ደፍሮ እመቤቴን እንዲህ ይመልስላታል?” ብላ ዮሴፍን በጥፊ ቃጥታ ሕፃኑን ደግሞ ነጥቃ ወደ መሬት ጣለችው፡፡ ሕፃኑም ምርር ብሎ ሲያለቅስ እመቤታችን እርሱን ተከትላ ምርር ብላ አለቀሰች፤ ልታነሣውም በምትሞክርበት ጊዜ ዮሴፍ “ተይው፤ አምላክነቱን ይገለጽ” አላት፡፡ ትዕማንን ከእነ ገረድዋ መሬት ተከፍቶ ዋጣቸው፡፡
ከበረሃውም አልፈው በየዱሩ ከአንዱ መከራ ወደ ሌላው መከራ እየተሸጋገሩ ከቆዩ በኋላ ዕረፍትን ያገኙት ወደ ኢትዮጵያ ከደረሱ በኋላ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በተዘዋወሩበት ሁሉ ሕዝቡ በእንግድነት እየተቀበለ አስተናግዷቸዋል፤ በዚህም ምክንያት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን የአሥራት ሀገር አድርጎ ሰጥቷታል፡፡
ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ከተፈጸመ በኋላ ጊዜው ሲደርስ ሲያሳድዳቸው የነበረው ሄሮድስ በመሞቱ ለዮሴፍ መልአኩ በሕልም ተገልጦ “የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ” (ማቴ.፪፥፳) አለው፡፡ ዮሴፍም የእግዚአብሔር መልአክ እንደነገረው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሰሎሜ ጋር ይዞ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፡፡
አባቶቻችን ይህንን መሠረት አድርገው የእመቤታችንን ስደት በማሰብ በወርኀ ጽጌ በየሳምንቱ ቅዳሜ ለእሑድ ዋዜማ ሌሊት በማሕሌት “አዘክሪ ድንግል ረኀበ ወጽምዐ፣ ድንግል ሆይ ረኀቡንና ጥሙን አሳስቢ” እያልን ከአባቶቻችን ጋር እንዘምራለን፣ ጊዜውንም እናስባለን፡፡ በርካታ ምእመናንም በዚህ ወቅት የእመቤታችንን ስደት በማሰብ ይጾማሉ፣ ይጸልያሉ፡፡
አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ “አዘክሪ ድንግል ንግደቶ ዘምስሌኪ እንዘ ትጐይዪ ምስሌሁ እምሀገር ለሀገር በመዋዕለ ሄሮድስ ርጉም አዘክሪ ድንግል አንብዐ መሪረ ዘውኅዘ እምአዕይንትኪ ወወረደ ዲበ ገጸ ፍቁር ወልድኪ አዘክሪ ድንግል ረኀበ ወጽምዐ ምንዳቤ ወኀዘነ ወኵሎ ዐፀባ ዘበጽሐኪ ምስሌሁ፤ ርጉም ሔሮድስ በነገሠበት ወራት ከአንቺ ጋር ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር የተሰደደውን መሰደድ አሳስቢልን፤ በፊትሽና በልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር ዕንባ አሳስቢልን፤ ረኀቡን ጥሙን ችግሩንና ኀዘኑን ያገኘሽንም ልዩ ልዩ መከራ አሳስቢልን” (ቅዳሴ ማርያም) ሲል ያዘክራል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!