በዓለ ቅዱስ ሩፋኤል

“ሩፋኤል” የሚለው ቃል “ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ” ማለት ነው፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ጳጉሜን ፫ ቀን በዓሉ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ “ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል (ጦቢ. ፲፪፥፲፭)፡፡  

በሌላ በኩል ደግሞ ሩፋኤል ማለት ከዕብራይስጥ ሁለት ቃላት ተጣምሮ የተገኘ ቃል ነው፡፡ “ሩፋ” ማለት ጤና፣ ፈውስ፣ መድኃኒት” ማለት ሲሆን “ኤል” የሚለው ቃል ደግሞ በሌሎቹም መላእክት ስም ላይ የሚቀጸል ስመ አምላክ ነው:: ይህ መልአክ እንደ ሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ ያለ ማቋረጥ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው፡፡ የሰው ልጆችንም ይጠብቃቸዋል፣ ያማልዳቸዋል፤ ከፈጣሪም ያስታርቃቸዋል፡፡ (ዘካ.፩÷፲፪፤ ዳን.፬÷፲፫፤ ዘፀ.፳፫÷፳፤ መዝ.፺÷፲፩-፲፫፤ ሉቃ..፲፫፥፮-፱፣)፡፡

የቅዱስ ሩፋኤል በዓሉ የሚከበርባቸው ምክንያቶችም አንደኛው በዓለ ሢመቱን ምክንያት በማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤቱ ነው፡፡

ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቍስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ “በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል (ሄኖ. ፲፥፲፫)፡፡ የሰው ልጆችንም በሥጋ ከታመሙበት ደዌም ሆነ ቍስል ይፈውስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቍስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” (ሄኖ. ፮፥፫)፡፡

እግዚአብሔር የመካኒቱን ማኅፀን ፈትቶ የተባረከ ልጅን የመስጠትን ጸጋ ለመላእኩ ቅዱስ ሩፋኤል  ሰጥቶታል፡፡ ሴቶች በሚፀንሱበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያቸውም፡፡ የወላድን ማኅፀን እንዲፈታ ስለተሾመ ከጌታ አዋላጅ ብትኖር ባትኖርም ሐኪም ቅዱስ ሩፋኤል አይታጣም፤ በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ ሴቶች ሁሉ የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም ብለው ማየ ጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ፡፡ ቅድስት ሣራን እና እንትኩይን (የሳሙኤል እናት) ወልዶ ለመሳም ያደረጋቸው ፈታሔ ማኅፀን የሆነው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሕፃኑ (ኗ በማኅፀን እያለ (ች) ተሥዕሎተ መልክዕ (በሥላሴ አርአያ መልኩ /ኳ/ መሳል) ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለያቸውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀልላቸዋል፡፡

አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በወለተ ራጉኤል ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል (ጦቢ. ፫፥፰-፲፯)፡፡ ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው (ሄኖ. ፪፥፲፰)፡፡ “ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሄኖ. ፫፥፭-፯)፡፡ የጦቢትን ልጁ ጦቢያን በሰው አምሳል ተገልጦ ከተራዳው በኋላ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ ራሱን ሲገልጥ “የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው” (ጦቢ. ፲፪፥፲፭)፡፡

በቅዱስ ሩፋኤል ተራዳዒነት ከተደረጉ ተአምራት መካከል በእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ ደሴት በታነጸች ቤተ ክርስቲያኑ ያደረገው ተአምር አንደኛው ነው፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር እና በድርሳነ ሩፋኤል እንደ ተጻፈው ብዙ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጠች፤ ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና፡፡ የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ዓሣ አንበሪው ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ምእመናኑም ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔር በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ፡፡ ያን ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ “እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጥ ጸጥ ብለህ ቁም!” ባለው ጊዜ አንበሪው ጸጥ ብሎ ቆሟል፡፡ በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገልጠዋል፡፡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆኗል፡፡ የቅዱስ ሩፋኤል ተረዳኢነት ከሁላችን ጋር ይሁንልን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ስንክሳር፣ ተአምረ ሩፋኤል

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *