በዓለ ደብረ ታቦር!
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐሥሩን ደቀ መዛሙርት በእግረ ደብር ትቶ ሦስቱን የምስጢር ደቀ መዛሙርት የተባሉትን ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ቅዱስ ዮሐንስንና ቅዱስ ማርቅዱስን ይዞ ወደ ደብረ ታቦር ተራራ የወጣበትና በዚያም ከመቃብር ሊቀ ነቢያት ሙሴን፣ ከብሔረ ሕያዋን ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስን አምጥቶ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ዕለት በማሰብ ነሐሴ ፲፫ ቀን በየዓመቱ በድምቀት ታከብረዋለች፡፡
ደብረ ታቦር ከዘጠኙ ዐበይት የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓላት አንዱ ሲሆን በዓሉም በምእመናን ዘንድ ‘ቡሄ’ በመባል ይታወቃል፡፡ በዓለ ደብረ ታቦር ለምን ቡሄ ተባለ? ቡሄ ማለት ‘መላጣ፣ ገላጣ’ ማለት ነው፡፡ ታቦር ተራራ ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ ደቡብ በኵል ዐሥር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከናዝሬት ከተማ በስተ ምሥራቅ፣ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእስራኤል በርካታ ታላላቅ ተራሮች እያሉ ለምን ደብረ ታቦርን መረጠ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡

ምሥጢረ መንግሥቱን ለምን በታቦር ተራራ ላይ ገለጸ?
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሌሎች ተራሮች እያሉ ደብረ ታቦር ላይ ክብሩን የገለጠው ስለ ሁለት ምክንያት ነው፡፡ እነርሱም፡- ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ ትንቢቱን ለመፈጸም ማለታችን ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፣ ስምህንም ያመሰግናሉ” እያለ እንደዘመረው (መዝ. ፹፰፥፲፪) ይህን ትንቢትንም ለመፈጸም በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ክብረ መንግሥቱን ገለጠ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ምሳሌውን ለመፈጸም ጌታችን በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ተገለጠ፡፡ ቀድሞ ባርቅና ሠራዊቱ ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ወጥተው ሲሳራን ድል አድርገውበታልና (መሳ. ፬፥፮) ጌታም በልበ ሐዋርያት ጥርጥርን እና ፍቅረ ሢመትን (የሥልጣን ፍቅር) ያሳደረ ሰይጣንን ድል ነስቶላቸዋል፡፡ ከዚህም በመነሣት የደብረ ታቦር በዓል “የደቀ መዛሙርት (የተማሪዎች በዓል)” ተብሎም ይጠራል፡፡
እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ በመሥራታቸው በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቡስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ ሲሣራ ነበር፡፡ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና የእስራኤልንም ልጆች ሃያ ዓመት አስጨነቃቸው፡፡ (መሳ. ፬፥፩-፫) በዚያም ወራት የለፊዶት ሚስት ነቢይቱ ዲቦራም እስራኤልን ትገዛቸው ነበር፡፡ ባርቅን ጠርታ “ሄደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፣ ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች ዐሥር ሽህ ሰዎች ውሰድ፤ እኔም የኢያቢንን ሠራዊት አለቃ ሲሣራን፣ ሰረገሎቹንም፣ ሕዝቡንም ሁሉ ወደ አንተ ወደ ቂሶን ወንዝ እሰበስባለሁ፤ በእጄም አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለችው፡፡ ዲቦራም ከደባርቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች፡፡ ሲሣራም ባርቅ ከሠራዊቱ ጋር ወደ ደብረ ተራራ እንደ ወጣ ሰማ፡፡ ባርቅ ሠራዊቱን ይዞ ከደብረ ታቦር ተራራ በወረደ ጊዜ ሲሣራና ሠራዊቱን አስደነገጣቸው፡፡ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ፡፡ ባርቅም ሲሣራንና ሠራዊትን ድል ነስቶበታል፡፡ (መሳ. ፬፥፩-፲፯)
ሦስቱን ሐዋርያት ብቻ ይዞ ለምን ወደ ደበረ ታቦር ተራራ ወጣ?
፩. ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሳርያ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ!” ብሎ መሰከረ፡፡ (ማቴ. ፲፮፥፲፮) ቅዱስ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የመሰከረውን ምስክርነት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ይሰሙ ዘንድ፣ ከነቢያት (ሙሴና ኤልያስ) አንደበት ይረዱ፣ በተዓምራት የደነደነ ልባቸውን ይከፍት ዘንድ የጌታችንን ነገረ ተዋሕዶ ከመሰከረ ከስድስት ቀን በኋላ አዕማድ ሐዋርያት ተብለው የተጠሩትን ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ያዕቆብና ቅዱስ ዮሐንስን ይዞ ወደ ተራራ አወጣቸው (ማቴ. ፲፯፥፩-፲)፡፡
፪. ሙሴን ከመቃብር፣ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን ለምን አመጣቸው?
ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከሕግ (ከኦሪት)፣ ነቢዩ ኤልያስ ደግሞ ከታላላቅ ነቢያት የተመረጡበት ሌላው ምክንያት እግዚአብሔር በዘመነ ኦሪት ከሙሴ ጋር ቃል በቃል በደመና በሚነጋገርበት ጊዜ ሙሴ “ፊትህን (ክብርህን) አሳየኝ” ብሎ እግዚአብሔርን በጠየቀው ጊዜ “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም“ ብሎታል፡፡ በዚህም ብቻ ሳያበቃ “እስከ አልፍም ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ በዚያ ጊዜ ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴን ግን ለአንተ አታይም” ብሎታል፡፡ (ዘፀ.፴፫፥፲፫-፳፫)
በፊልጶስ ቂሳርያ ጌታ ሐዋርያትን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?” ብሎ ለጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ሙሴ ነው ይሉሃል ፤ እንዲሁም የኃይል ሥራህን ተመልክተው ኤልያስ ነው ይሉሃል” ብለው ነበር፤ ሙሴን ከመቃብር፤ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ “አንተ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህ” ብሎት ነበርና ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ “የኤልያስን ጌታ ኤልያስ ነው ይልሃል? እግዚአ ኤልያስ፤ አምላከ ኤልያስ ይበሉህ እንጂ” ሲል በደብረ ታቦር ተገኘ፡፡ ታያለህ የተባለው ሙሴም አየ፣ ትመሰክራለህ የተባለው ኤልያስም መሰከረ፡፡
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” ሲል ተደምጧል፡፡ ቃል በቃል ስናየው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው ማለቱ “አንተ እያበላኸን እየፈወስከን፣ ሙሴ እነዚህ መከራ ያደርሱቡኛል ይገድሉኛል ያልካቸውን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን እንዳይመጡ በደመና እየጋረደ፣ ቢመጡም አልያስ እሳት እያዘነመ እያባረራቸው በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው” ማለቱ ሲሆን ምሥጢራዊው መልእክቱ ግን “የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት በሚታመንበት፣ ወልድ ዋሕድ በምትለው ሃይማኖት መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ ሰይጣን ድል በተደረገባት በታቦር ተራራ ምሳሌም በምትሆን በወንጌል ሕይወት፣ በቤተ ክርስቲያን መኖር ለእኛ መልካም ነው” ማለቱ ነው፡፡
ወቅቱ በሀገራችን የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ብርሃን የሚገለጥበት፣ ወገግታ የሚታይበት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚሸጋገርበት ወቅት በመሆኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ፡፡ እንዲሁም በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበት ዕለት ስለሆነ ‘የብርሃን’ ወይም ‘የቡሄ’ በዓል ይባላል፡፡
በዚህ ሰሞን ልጆች የተገመደ ገመድ አዘጋጅተው ማጮሃቸው ሁለት ዓይነት ምስጢር የያዘ ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ግርፋቱንና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፤ ጅራፍ ሲጮህ እንደሚያስደነግጥ ሁሉ ከጌታ ጋር የነበሩት ሦስቱ ደቀ መዛሙርትም አብ በደመና ሆኖ ሲናገር መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን የሚያስታውስ ነው፡፡ ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል፤ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡
እናቶችም ለዚህ በዓል የሚሆን ዳቦ ለመጋገር ስንዴያቸውን ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉ ይሰነብታሉ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ (ነሐሴ ፲፪ ቀን) ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ “ቡሄ በሉ፤ ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ …” እያሉ ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ እያነሡ ይሰጧቸዋል፡፡ ለምን ሙልሙ ዳቦ ተዘጋጅቶ ለልጆች ይሰጣቸዋል ስንል፡- ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ ‘ቡሄ’ ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና በበዓሉ ችቦ የሚበራውም ከዚህ ታሪክ በመነሣት ነው፡፡
ጌታችን በፊታቸው ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ
ሦስቱ ሐዋርያትና ሁለቱ ነቢያቱ በተራራው ሳሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሲጸልይ ሳለ መልኩ በፊታቸው ተለወጠ፡፡ ፊቱም እንደ ፀሐይ ብሩህ ሆነ፡፡ ልብሱም እንደ በረድ ጸዓዳ ሆነ፡፡ ጌታችን “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” እንዳለ የሕይወት ብርሃን፣ የሰው ልጆች ተስፋ የሆነውን ብርሃኑን ገለጠ፡፡ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብትንም ብርሃን ያለበሰ እርሱ ነው፡፡ ለመላእክት፣ ለጻድቃን ለቅዱሳን ሁሉ የጽድቅ ብርሃንን ያደለ የማይጠፋ ብርሃን እርሱ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ተራራ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠ፡፡ ይህ ሁሉ ነገረ ተዋሕዶን እንዲረዱ የተደረገ መገለጥ ነው፡፡ ሰውነቱን አልካዱም፣ አምላክነቱን ግን ተጠራጥረው ነበርና አምላክነቱን ገለጠላቸው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስም የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፊቱ ብሩህ መሆን፣ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ መሆን እንደዚሁም የቅዱሳን የነቢያት መምጣት እና ከጌታችን ጋር መነጋገራቸውን ከሰማ በኋላ “እግዚኦ እግዚእ ሠናይ ለነ ኃልዎ ዝየ፤ ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው“ አለ፡፡ ቅዱሳን ነቢያቱ የወትሮ ሥራቸውን እየሠሩ ማለትም ሙሴ ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላት እያስገደለ፤ ኤልያስም ሰማይ እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናመ እያቆመ፤ አንተም አምላካዊ የማዳን ሥራን እየሠራህ ገቢረ ተአምራትህን እያሳየህ፤ በዚህ በተቀደሰ ቦታ በደብረ ታቦር መኖር ለእኛ እጅግ መልካም ነው” አለ፡፡ አምላካዊ ፈቃድህስ ከሆነ በዚህ ተራራ ላይ አንድ ለአንተ፤ አንድ ለሙሴ፤ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳስ እንሥራ ብሎም ጠየቀ፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው” ሲል ጌታችን በተአምራቱ ሲራቡ እያበላቸው፣ ሲጠሙ እያጠጣቸው፣ ሲታመሙ እየፈወሳቸው፣ ቢሞቱ እያነሣቸው፤ ሙሴም እንደ ቀድሞው ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላትን እየገደለ፤ ኤልያስ ደግሞ ሰማይን እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናም እያቆመ በደብረ ታቦር ለመኖር መሻቱን ያመለክታል፡፡ ዳግመኛም “ሦስት ጎጆ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፤ አንዱን ለሙሴ፤ አንዱን ለኤልያስ” በማለት የእርሱንና የሁለቱን ሐዋርያት ጎጆ ሳይጠቅስ አርቆ መናገሩ በአንድ በኩል ነቢያቱን አስቀድሞ ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን አለመጥቀሱ ትሕትናው ትሕትናውን፤ እንደዚሁም ከጌታችን ጋር ለመኖር ያለውን ተስፋ ያመለክታል፡፡
“የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት”
ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፡፡ በደመናም “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ፤ ልመለክበት የወደድኩት ለምስጢረ ተዋሕዶ የመረጥኩት የምወደው፣ የምወልደው ልጄ ይህ ነው እርሱንም ስሙት” የሚል ቃል መጣ፡፡ በዚህም የሥላሴ ምስጢር ለዓለም ተገለጸ፡፡ እግዚአብሔር አብ በደመና ሆኖ “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” እያለ፣ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋን ተዋሕዶ ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም ሰውም ሆኖ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በነጭ ደመና ተመስሎ ተገልጸዋል፡፡ ስለዚህም ደብረ ታቦር ጌታችን ብርሃነ መለኮቱ፣ ክብረ መንግሥቱ የገለጠበት እንዲሁም የሥላሴ አንድነትን ሦስትነት የተገለጠበት ነው ብላ ቤተ ክርስቲያናችን ታስተምራለች፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡– መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መምህር አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ ገጽ ፫፻፲፭–፫፻፲፯፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ ፳፻፯ ዓ.ም፣ ገጽ ፻፲፩፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!