ፅንሰታ ለማርያም

ቅደስት ቤተ ክርስቲያናችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተፀነሰችበትን ዕለት ነሐሴ ፯ ቀን በየዓመቱ በድምቀት ታከብረዋለች፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች በእናቷ ሐና በኩል ቅድመ አያቶቿ ጴጥሪቃና ቴክታ ደጋጐችና እግዚአብሔርን የሚፈሩና በፍጹም ልቡናቸው እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ነበሩ፡፡

እግዚአብሔርን ማምለክ ብቻ ሳይሆን በባለጠግነታቸውም የታወቁ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልጅ ስላልነበራቸው በጣም ያዝኑና ይተክዙ ስለነበር አንድ ቀን ጰጥሪቃ የሀብቱን ብዛት ተመልክቶ ሚስቱን (ቴክታ)ን “ያለን ገንዘብና ንብረት እንኳን ለእኛ ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ነው፡፡ ነገር ግን ወራሽ ልጆች የሉንም” እያለ በትካዜ ተናገራት፡፡ ቴክታም ከእርሷ ልጅ ባለመውለዱ ሌላ ወላድ ሴት የፈለገ መስሏት ‘እግዚአብሔር ከእኔ ልጅ ባይሰጥህ ነውና ሌላ አግብተህ ወለድ” አለቸው በትካዜ ውስጥ ሆና፡፡  

ጴጥሪቃም “ይህንንስ በልቤ እንዳላሰብኩና እንዳልተመኘሁ እግዚአብሔር ያውቃል” በማለት ተናገራት፡፡ ቴክታም በሐዘን ወስጥ ሆና ሳለች ራእይ ታያለች፤ ነጭ እንቦሳ ከማሕኅፀኗ ስትወጣ፤ እንቦሳዪቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ሰባት ስትደርስ፣ ሰባተኛዋ ጨረቃን ስትወልድ፤ ጨረቃም ፀሐይን ስትወልድ አየች። እርሷም ባየችው ራእይ ተገርማ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ አደነቀች፡፡ “በሕልሜ ነጭ ጥጃ ከማኅፀኔ ስትወጣ፣ ያችም ነጭ ጥጃ ደግሞ ነጭ ጥጃ ስትወልድ፣ እንደዚህ እየሆነ እስከ ሰባት ትውልድ ሲደርሱ ሰባተኛዪቷም ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋ ደግሞ ፀሐይን ስትወልድ አየሁ” በማለት አስረዳችው።

ጰጥሪቃም ባለቤቱ ባየችው ራእይ ተደንቆ ሕልም ለሚፈታ ሰው የሚስቱን ራእይ ተናገረ፡፡ ሕልም ተርጓሚውም ምስጢር ተገልጾለት “ሰባት አንስት ጥጆች መውለዳችሁ ሰባት ሴቶች ልጆች ይወለዳሉ፤ ነጭ መሆናቸው ደጋጎች ልጆች መሆናቸውን ሲያመለክት፤ ሰባተኛዪቱ ጨረቃን መውለዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ናት፤ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም” በማለት ተረጐመለት፡፡ ጰጥሪቃም በተተረጎመለት ራእይ ተገርሞ ለሚስቱ ነገራት፤ እርሷም “የእስራኤል አምላክ የሚያደርገውን እርሱ ያውቃል” በማለት ፈጣሪዋን አመሰገነች፡፡

ቴክታ ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ሔሜን አሏት፤ ሔሜን – ዴርዴን ወለደች፤ ዴርዴም – ቶናን፤ ቶናም – ሲካርን ወለደች፤ ሲካርም – ሴትናን፤ ሴትናም – ሔርሜላን ወለደች፤ ሔርሜላም የተከበረችና የተመረጠች ዓለሙን ሁሉ ለፈጠረ ጌታ አያት ለመሆን የበቃችውን ሐናን ወልዳለች። ሐና በመልካም አስተዳደግ አድጋ አካለ መጠን ስታደርስ ከነገደ ይሁዳ ከመንግሥት ወገን የተወለደ የቅስራ ልጅ የአልዓዛር የልጅ ልጅ ከሚሆን ከኢያቄም ጋራ አጋቧት፡፡ ሁለቱም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት በመሄድ ለዐይናቸው ማረፊያ ለልባቸው ተስፋ የሚሆን ልጅ እንዲሰጣቸው ይለምኑ ነበር፡፡

ከዕለታት በአንደኛው ቀን ሁለቱም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሄደው ሲጸልዩ ውለው ሲመለሱ ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሏቸው ሲጫወቱ አይተው ሐና “አቤቱ ጌታዬ ግዕዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሣኸኝ?” ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፡፡ ወዲያው ሳይውሉ ሳያድሩ ሱባኤ ይገባሉ፤ ኢያቄም ወደ በረሃ ሄዶ ሲጸልይ ሐና ደግሞ በቤቷ ዙሪያ ባለው የአትክልት ቦታ ሱባኤ ያዘች፤ በሱባኤያቸው ፍጻሜም ሁለቱም ራእይ አይተው ተነጋግረዋል፡፡

ኢያቄም “ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ ብሎ የተገለጸለትን ለሐና ነግሯታል፤ ይኸውም የራእዩ ምስጢር፡- ወፍ የተባለው አካላዊ ቃል ክርስቶስ ሲሆን፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባሕርዩ ነው፤ ከላይ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ ማለቱ የኢያቄምን ባሕርይ ባሕርይ እንደሚያደርግ ሲያጠይቅ ሲሆን፤ ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ምልአቱ፣ ስፍሐቱ፣ ርቀቱ፣ ልዕልናው፣ ዕበዩ ናቸው፡፡

ሐናም ተገልጾላት ለባሏ “ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማኅፀኔ ስትተኛ አየሁ” አለችው። ምስጢሩም፡- ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን፤ ነጭነቷ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፤ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ ወደ ዦሮዬ ገብታ በማኅፀኔ ስትተኛ አየሁ ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በዦሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መሆኗን ሲያጠይቅ ነው፡፡

ኢያቄምና ሐናም ይህንን ራእይ ሐምሌ ፴ ቀን ካዩ በኋላ “ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ ይርዳን አንልም ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ይሆናል፤ ሴትም ብንወልድ ለቤተ እግዚአብሔር መጋረጃ ፈትላ ትኑር” ብለው ስእለት ከተሳሉ በኋላ ራእይ አየን ብለው ዕለቱን አልተገናኙም፤ አዳምንና ሔዋንን “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት” ብሎ የተናገረው አምላክ ለእኛም ይግለጽልን ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ሰባት ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ።

ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን “ከሰው የበለጠች ከመላእክት ሁሉ የከበረች ልጅ ትወልዳላችሁ” ብሎ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለሐና ነግሯት በፈቃደ እግዚአብሔር በብሥራተ መልአክ እመቤታችን ነሐሴ ሰባት ቀን እሑድ ተፀንሳለች፡፡ ለዓለም ሁሉ የድኅነት መገኛ የሆነች ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተፀነሰችበት ዕለት ነሐሴ ሰባት የተባረከች እንደመሆኗ መላው ክርስቲያን በዓሏን ሊያከብር ይገባል፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በከበሩ ኢያቄምና ሐና ጸሎት ይማረን፤ በረከታቸው ከእኛ ጋር ይኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ

       መጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ፣ ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *