በደረጃ ሁለት ተተኪ አመራርነት ሥልጠና የወሰዱ ሠልጣኞች ተመረቁ
በማኅበረ ቅዱሳን የደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በሥሩ ለሚገኙና ከተለያዩ ግቢ ጉባኤያት ለተወጣጡ ፸፮ አገልጋዮች የደረጃ ሁለት ተተኪ አመራርነት ሥልጠና በመስጠት አስመረቀ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩትን አባላት አቅም ለመገንባትና የማኅበሩን እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በሚገባ የተረዱ፤ መንፈሳዊ ሕይወታቸውም የተስተካከለና አርአያ ሆነው ግቢ ጉባኤን ሊመሩ የሚችሉ የአመራር አባላትን ለማፍራት ታስቦ በክረምት ወቅት በተለያዩ ማስተባበሪያዎች ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በሐዋሳ እና በወላይታ ሶዶ የሥልጠና ማእከላት የደረጃ ሁለት ተተኪ አመራርነት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በሐዋሳ የሥልጠና ማእከል ከሐዋሳ፣ ከባሌ ሮቤ፣ ከሻሸመኔ፣ ከዲላ ማእከላትና ከቡሌ ሆራ ልዩ ወረዳ ማእከል ከሚገኙ ግቢ ጉባኤያት ውስጥ ለተመለመሉ ፳፮ አገልጋዮች የደረጃ ሁለት የተተኪ አመራርነት ሥልጠና ከሰኔ ፩ እስከ ሰኔ ፯ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም. ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ሥልጠናዎቹም፡-
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመሪነት ሚና ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ
- ኦርቶዶክሳዊነት ሕይወቱና ክህሎቱ
- የአኀት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ
- ዓለማዊነት (Secularism) ከኦርቶዶክስ እሳቤና ኑሮ አንጻር
- ማኅበረ ቅዱሳን ማነው?
በሚሉና ሌሎችም ርእሰ ጉዳዮች ላይ ልምድ ባላቸው መምህራን የተሰጠ ሲሆን ከሥልጠናውና ከአሠልጣኖቹ የሕይወት ተሞክሮና ልምድ ዕውቀት እንዳገኙም ሠልጣኞቹ አስረድተዋል፡፡ በሥልጠናውም ሦስት እኅቶችና ፳፫ ወንዶች ተሳትፈው ሰኔ ፯ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም ተጠናቋል፡፡
በተመሳሳይ በወላይታ ሶዶ ማእከል በርእሰ አድባራት ወገዳማት ደብረ መንክራት አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ከአርባ ምንጭ፣ ከወላይታ ሶዶ፣ ከጂንካ፣ ከሆሳዕና እና ከዱራሜ ማእከላት ስር ከሚገኙ ግቢ ጉባኤያት የተመለመሉ ፴፰ ወንዶችና ፲፪ እኅቶች በድምሩ ፶ ሠልጣኞች ከሰኔ ፰ እስከ ፲፬ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም የደረጃ ሁለት አመራርነት ሥልጠና ወስደው ተመርቀዋል፡፡
የደረጃ ሁለት የአመራርነት ሥልጠናው በሐዋሳ ማእከል ከተሰጠው ሥልጠና ጋር ተመሳሳይ ርእሰ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የወላይታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ተገኝተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክትም የተካሄደው ሥልጠና እጅግ ጠቃሚ የሆነና ሊበረታታ የሚገባ መሆኑን ጠቅሰው “ሠልጣኞች በተሰጠው ሥልጠና እግዚአብሔርን በመፍራት ሕይወታችሁን እንድትመሩ፣ የተቀበላችሁትንም መክሊት በማትረፍ፣ በሄዳችሁበት ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ሀገራችሁን ማገልገል ይጠበቅባችኋል” በማለት የአደራ መልእክትና አባታዊ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡

በሁለቱም ማስተባበሪያዎች በሁለት ዙር በተሰጡት ሥልጠናዎች ፷፩ ወንዶችና ፲፭ ሴቶች በድምሩ ፸፮ የደረጃ ሁለት ተተኪ አመራር ሠልጣኞች ተሳትፈውበታል፡፡ በሥልጠና ቆይታቸውም ሠልጠኞቹ ስለ አገልግሎትና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚገጥሟትን ፈተናዎች ትሻገር ዘንድ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲያበረክቱ ኀላፊነት እንዲሰማቸው ያደረገና ጥሩ ተሞክሮም ማግኘት እንዲችሉ የረዳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!