የተተኪ አመራርና መምህራን ሥልጠና በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ
ማኅበረ ቅዱሳን በስድስት ማስተባበሪያዎችና በዐሥራ አንድ ሥልጠና ማእከላት የደረጃ ሁለት ተተኪ አመራርና መምህራን ሥልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ የተቋማዊ ልማት አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪ ሓጋዚ አብርሃ ገለጹ፡፡
የደረጃ ሁለት ተተኪ አመራርነት ሥልጠናው በመሐል ማእከላት፡- በአዲስ አበባ፣ በአዳማ (በአፋን ኦሮሞ) ፤ በደቡብ ማስተባበሪያ፡- በወላታና ሐዋሳ፤ በምሥራቅ ማስተባበሪያ፡- ድሬዳዋ፤ በሰሜን ምሥራቅ ማስተባበሪያ፡- ደሴ፤ በሰሜን ምዕራብ ማስተባበሪያ ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ ለሰባት ቀናት ሲሰጥ ቆይቶ ተጠናቋል፡፡ በምዕራብ ማስተባበሪያ ጅማ እና በመሐል ማእከላት ማስተባበሪያ ደብረ ብርሃን የሚሰጠው ሥልጠና ደግሞ በሐምሌና ነሐሴ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን ሠልጣኞቹ በየማስተባበሪዎቻቸው በሚገኙ ግቢ ጉባኤያት በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፎች ሲያገለግሉ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በዚህ ሥልጠናም “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመሪነት ሚና፣ የምዕራባዊነትና የአረባዊነት መዳረሻ ከኦርቶዶክሳዊ ሉላዊነት አንጻር፣ የኦርቶዶክሳዊነት ሕይወትና ክሂሎት፣ የአኀትና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ” በሚሉና በሌሎችም ዋና ዋና ርእሰ ጉዳዮች ሥልጠናው የተሰጠ ሲሆን ምሽት ላይ በሚኖረው መርሐ ግብርም የግቢ ጉባኤያት የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥና ተሞክሮ በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ መቻሉን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
የደረጃ ሁለት የአዳዲስ ተተኪ መምህራን ሥልጠናም በምሥራቅ ማስተባበሪያ ድሬዳዋ እና በሰሜን ምዕራብ ማስተባበሪያ ባሕር ዳር ሲሰጥ ቆይቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በጎንደርና በደብረ ማርቆስ የሚሰጠው ሥልጠና በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በሌሎች ሰባት ማእከላት ደግሞ በሐምሌና በነሐሴ ወራት እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡

የደረጃ ሁለት መምህራን ሥልጠናው ከ፳፭-፴ ቀናት የሚወስድ ሲሆን ዐሥር ርእሰ ጉዳዮችን እንዳካተተ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ሕይወተ ቅዱሳን፣ ክርስትና በሀገራዊ ጉዳዮች፣ የስብከት ዘዴ፣ ሃይማኖትና ሳይንስ፣” እንዲሁም ሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በደረጃ ሁለት ተተኪ አመራርነት ፫፻፷፮፣ በተተኪ መምህርነት ፻፵ ከተለያዩ ማእከላት የተውጣጡ ሠልጣኞች እንደተካተቱ ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ የተቋማዊ ልማት አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪ ሓጋዚ አብርሃ ገልጸዋል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!