አዲስ አበባ ማእከል የግቢ ጉባኤት ተማሪዎችን አስመረቀ
በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል በልዩ ልዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መደበኛ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩና በበርካታ ሰንበት ትምህርት ቤቶች መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ ሠላሳ በላይ የግቢ ጉባኤት ተማሪዎችን በማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም አስመረቀ።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ የወንጌል ትምህርት፣ በተመራቂዎች ያሬዳዊ ወረብና የበገና ዝማሬ የቀረበ ሲሆን በከፍተኛ ማዕረግ ለተመረቁ ተማሪዎች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ተመራቂዎች በበኩላቸው በግቢ ጉባኤ ሕይወት ውስጥ ማለፋቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዓለማዊ ፈተናዎች ጠብቃ እንዳቆየቻቸውና ለውጤታማነታቸው ትልቁን ድርሻ እንደነበራት በመመስከር በቀጣይም በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
በማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንና በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በተከናወኑ መርሐ ግብሮች ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን ተመራቂዎች የአደራ መስቀል ተበርክቶላቸዋል።
በማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ስድስት መቶ ሃምሳ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ደግሞ አምስት መቶ ሰማንያ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ማስመረቁን የአዲስ አበባ ማእከል ሚዲያ ክፍል ዘግቧል፡፡
ምንጭ፡- የአዲስ አበባ ማእከል ሚዲያ ክፍል




Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!