ነገረ ቅዱሳን
መ/ር መስፍን ምትኬ
ክፍል አንድ
ቅድስና ምንድን ነው?
ቅዱስ የሚለው ቃል ቀደሰ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አመሰገነ፣ ለየ፣ መረጠ፣ አከበረ ማለት ነው፤ ስለዚህ ቅዱስ ማለት ልዩ፣ ክቡር፣ ንጹሕ፣ ምስጉን ማለት ነው።
ቅድስና በሁለት ይከፈላል፡፡ እነርሱም፦ የባሕርይና የጸጋ ቅድስና ናቸው፡፡
፩. የባሕርይ ቅድስና
የባሕርይ ቅድስና ለእግዚአብሔር ብቻ ገንዘቡ የሆነ ነው፡፡ ይህም ማለት ቅድስናው ከእርሱ የማይለይ፣ ከማንም ያልተቀበለው፣ ማንም ሊወስድበት የማይችል የራሱ ገንዘብ የሆነ ማለት ነው፡፡
በእርሱ ዘንድ ከቅድስና ሌላ ሊታሰብ የማይችል ርኩሰት የሌለበት ነው፡፡ ስለዚህ “ቅዱስ እግዚአብሔር” ይባላል፡፡ ይህን ቅድስናውንም ሱራፌል ኩሩቤል ያለ ዕረፍት “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት ፍጹም ምሉዕ ቅድሳተ ስብሐቲከ፤ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች” በማለት የባሕርይ የሆነ ቅድስናውን ያመሰግኑታል፡፡ (ኢሳ. ፮፥፫፤ ራእ. ፬፥፰)
- ቅድስና ለእግዚአብሔር የባሕርይው ገንዘቡ ስለሆነ ቅድስናን በጊዜ ሂደት ወይም በትሩፋት ያገኘው አይደለም፡፡
- እግዚአብሔር ሁል ጊዜም ቅዱስ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ቅድስና ተመሳሳይ ወይም ተወዳዳሪ የለውም፡፡ “እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ” ይላል ቅዱስ እግዚአብሔር (ኢሳ. ፵፥፳፭)
- “ለዘለዓለም በአርያም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፤ በቅዱሳን ላይ አድሮ የሚኖር፣ …” (ኢሳ. ፶፯፥፩፭)
- “ስሙም ቅዱስ ነው” (ሉቃ. ፩፥፵፭)
- “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው፤ ጌታ ሆይ አንተን የማይፈራና ስምህን የማያከብር ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና” (ራእ. ፭፥፫-፬)
ስለዚህ ለእግዚአብሔር ቅድስና ታላቅ ክብርና ምስጋና ልንሰጥ ይገባናል፡፡ አቻ ተወዳዳሪ የለውም፤ ለሌላውም ልንሰጥ አንችልም፤ የባሕርይ ክብሩ ነውና፡፡
፪. የጸጋ ቅድስና
ጸጋ ማለት ቸርነት፣ ምሕረት፣ በጎነት፣ ያለ ብድራትና ያለ ዋጋ የሚሰጥ ስጦታ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ከእግዚአብሔር የሚገኝ ማንኛውም ስጦታ ሁሉ ጸጋ ይባላል፡፡ በዚህም መሠረት በባሕርይው ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በረድኤት ያደረባቸው በጸጋ የተዋሐዳቸው የሃይማኖት ሰዎች ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ይኸውም ሃይማኖት ለመያዝ፣ ምግባር ለመሥራት ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው በማስገዛት ከክሕደት፣ ከጥርጥር፣ ከክፋትና ከርኵሰት በመጠበቃቸው ነው፡፡
እግዚአብሔር ራሱ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌ. ፲፱፥፪) በማለት ሰዎች ቅድስናን ገንዘብ እንዲያደርጉ በቃሉ ያስተማረን፡፡ ይህንንም መሠረት አድርጎ ቅድስ ጴጥሮስ “ነገር ግን የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም እንዲሁ በአካሄዳችሁ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” የሚል ተጽፏልና፡፡ (፩ኛጴጥ. ፩፥፲፫-፲፮)
ቅዱሳን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመሆናቸው ቅዱሳን ናቸው፡፡ “እናንተ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔር መንፈስም በእናንተ ላይ አድሮ እንደሚኖር አታውቁምን?” (፩ኛቆሮ. ፫፥፲፮-፲፯) ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ “እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ጻድቅ ነው” ብሏል (፩ዮሐ. ፫፥፯)
ከላይ እንደተመለከትነው እግዚአብሔር ቅዱስ ነው ስንል ቅድስና የባሕይው ገንዘቡ መሆኑን ዐውቀን ነው፡፡ ቅዱሳንን ቅዱስ ስንል ደግሞ ቅድስናቸው የጸጋ (የስጦታ) መሆኑን ዐውቀን ነው፡፡ “የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው፣ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው” ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ፩ኛቆሮ. ፲፪፥፬)
በቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ተብለው የሚጠሩት እነማን ናቸው?
፩. ቅዱሳን ሰዎች ፭. ቅዱሳት ዕለታት
፪. ቅዱሳን መላእክት ፮. ቅዱሳት መጻሕፍት
፫. ቅዱሳት ንዋያት ፯.ቅዱሳትመካናት
፬. ቅዱሳት ሥዕላት
ነገረ ቅዱሳንን መማር (ማወቅ) ለምን አስፈለገ?
፩. ሕይወታቸው የወንጌልን እውነት ይበልጥ ስለሚያስረግጥልን፡-
“ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።” (ማር. ፰፥፴፬) ይህንንም መሠረት አድርገው ቅዱሳን ሐዋርያት ሁሉን ትተው እንደ አጠራራቸው ሳይጠራጠሩ ተከትለውታል፡፡ “ተከተለኝ” አለው፤ ተነሥቶም ተከተለው።” (ማቴ. ፱፥፱) እንደ ቀራጩ ማቴዎስ ሁሉ ሌሎቹንም ለሐዋርያነት መርጦ የሚሠሩትን ሁሉ ትተው ከተከተሉት በኋላ ያልተመለሰላቸው ጥያቄ ነበራቸው፡፡ ጥያቄውንም ቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያትን ወክሎ አቅርቧል፡፡ “እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንግዲህ ምን እናገኛለን?” ሲል። ጌታችንም መልሶ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በዐሥራ ሁለቱ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል ትፈርዳለችሁ” አላቸው፡፡ (ማቴ. ፲፱፥፳፯)
ሐዋርያት ሁሉን ትተው ከተከተሉት በኋላ በአደረበት እያደሩ፣ በዋለበት እየዋሉ የቃሉን ትምህርት፣ የእጁን ተአምራት እያዩ ኖረዋልና በዕለተ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ሞልቶባቸው ፍሩሃን የነበሩት ጥቡዓን ሆነዋል፡፡ በሐዋርያት እግር የተተኩት ሐዋርያነ አበውም የሚደርስባቸውን መከራ ሁሉ ታግሠው ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተከትለውታል፡፡ የእውነት ምስክርም ሆነዋል፡፡ እንደ ምሳሌም፡-
➢ ዓይኑን ያወጣ ስምዖን ጫማ ሰፊው፣
➢ እጁን የቆረጠ አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት ዘአንጾኪያ፣
➢ እግሩን የቆረጠ አባ መርትያኖስ፣ … ሌሎችም፡፡
፪. ነገረ ቅዱሳንን ስንማር ከቅዱሳኑ ታሪክ ባሻገር የቅዱሳንን ሁሉ አስገኚ፣ የቅዱሳን ሁሉ ክብርና አክሊል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ላላወቁ ለማሳወቅ፣ ላወቁትም ለማጽናት፡፡
“እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፣ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና” (ዮሐ. ፲፭፥፭)
“ያዘጋጃቸውን እነርሱን ጠራ፤ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፤ የአጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ” እንዲል፡፡ (ሮሜ ፰፥፴)
“ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳን፣ ንጹሓንና ያለ ነውር የሌለን በፍቅር ያደርገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን፤ በኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ውድ ፈቃዱ ለእርሱ ልጆች ልንሆነን አስቀድሞ ወሰነን” (ኤፌ. ፩፥፬)
፫. ቅዱሳን የተቀበሉትን መከራ፣ ያሳዩትን ትዕግሥትና ጽናት፣ የከፈሉትን ሰማዕትነት ለምእመናን ያለውን አርአያነት በቃልና በጽሑፍ ለማስተማርና ማንነታቸውን ለማሳወቅ
በእምነትና በሕይወት ቅዱሳንን እንድንመስላቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲያስተምር “እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ” (፩ኛቆሮ. ፲፩፥፩) ብሏል፡፡
“የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” (ዕብ. ፲፫፥፯) ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም፡- “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ” በማለት ስለ እምነታቸው የከፈሉትን መሥዋዕትነት ያመለክተናል፡፡
፬. ከእግዚአብሔር ያገኙትን የቃል ኪዳን በረከት በተለያየ መንገድ እኛ ምእመናን ተምረን እንድንጠቀምበት፡፡
“ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ በደቀ መዝሙሬ ስም ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋውን አያጣም።” (ማቴ. ፲፥፵፪)
፭. ታሪካቸው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አካል በመሆኑ የነበሩበት ዘመን፣ ያበረከቱት አስተዋጽኦና አጠቃላይ ሁኔታዎች በወቅቱ የነበረውን የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ለማወቅና ለመረዳት።
“በዚያ ወራትም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፤ ከሐዋርያትም በቀር ሁሉም በይሁዳና በሰማርያ ባሉ አውራጃዎች ሁሉ ተበተኑ። (ሐዋ. ፰፥፩)
፮. መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማጥናት ስለሚቆጠር
➢ የሐዋርያት ታሪክ መማር የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ማንበብ ነው።
➢ የአስቴር ታሪክ መማር መጽሐፈ አስቴርን ማንበብ ነው።
➢ የሩትን ታሪክ መማር የሩትን መጽሐፍ እንደ ማንበብ ነው።
➢ የአብርሃምን፣ የይስሐቅን፣ የያዕቆብን ታሪክ መማር የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍን እንደ ማንበብ ነው።
➢ የሳሙኤልን፣ የዳዊትን፣ የሰሎሞንን፣ የኤልያስን፣ የኤልሳዕን፣ የሕዝቅያስን ታሪክ መማር አራቱን መጽሐፍተ ነገሥት እንደ ማንበብ ነው።
፯. ቅዱሳንን ማውቅ ዐውቆም መቀበል፤ እነርሱንም መምሰል ክርስቶስን መመሰል ስለሆነ።
“እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ ካመኑ ከእነዚህ ከታናናሾች ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁትን ሁሉ ለእኔ አደረጋችሁት” (ማቴ. ፳፭፥፵)
“እውነት እላችኋለሁ ካልተመለሳችሁ እንደዚህም ሕፃን ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም፡፡ እንደዚህም ሕፃን ራሱን ዝቅ ያደረገ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ ይህ ነው፡፡ እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፡፡ በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን የሚያሰናክል አህያ የሚፈጭበት ወፍጮ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም ይሻለዋል፡፡” (ሉቃ. ፲፰፥፫-፮)
“እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” (ማቴ. ፲፥፵)
ይቆየን
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!