“በእንተ ልደታ ለማርያም ፍስሐ ኮነ” (ቅዱስ ያሬድ)
“ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግንቦት ፩ ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአባቷ ኢያቄምና ከእናቷ ቅድስት ሐና መወለዷን ትመሰክራለች፡፡ (ስንክሳር ግንቦት ፩፣ ተአምረ ማርያም)፡፡ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ነቢያት በልዩ ልዩ አገላለጽ በትንቢትና በምሳሌ መስለው ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” (መዝ. ፵፬፥፱) በማለት የተናገረላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደችባት ዕለት ናት፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም “ድንግል ትጸንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች” (ኢሳ. ፯፥፲፬) ብሎ ትንቢት የተናገረላት ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህች ዕለት ተወለደች፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በማርያም ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ሆነ!” (ቅዱስ ያሬድ) ብሏል፡፡ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬምም በውዳሴ ማርያም “የመመኪያችን ዘውድ፣ የንጽሕናችንም መሠረት” እያለ ያወደሳት ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደችባት ዕለት ናት፡፡
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት በራዕይና በምሳሌም አስቀድሞ የተገለጸ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል ከእርሷ ሰባት ትውልድ አስቀድሞ እንዲሁም ለእናትና ለአባቷ የተገለጹት ምሳሌዎች በቅዱሳት መጻሕፍት በሰፊው ሰፍረው ይገኛሉ፡፡

ታሪኩንም ስንመለከት በቅድስና የሚኖሩ ነገር ግን መካን የነበሩት ቴክታና ጴጥርቃ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስትወጣ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስትደርስ፤ ስድስተኛዪቱ ጨረቃን ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ አይተው በሀገራቸው መፈክረ ሕልም (ሕልም ፈች ሊቅ) አለና ሂደው ነገሩት፡፡ ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም፤ እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል አላቸው፡፡ እነርሱም ጊዜ ይተርጉመው ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ልጅ ወለዱ፡፡ ስሟንም “ረከብኩ ስእለትዬ፤ ረከብኩ ተምኔትዬ›› /የተሳልኩትን አገኘሁ፤ የተመኘሁትን አገኘሁ/ ሲሉ ‹‹ሄኤሜን” አሏት፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ለአካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡
ኢያቄምና ሐናም መካን ስለነበሩ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ጸልየው፤ ሲሰጣቸውም መልሰው ለእርሱ እንደሚሰጡ ስዕለትን ተስለው ነበር፡፡ ጸሎታቸው ሲደርስ ለሐና በሕልም ተገልጾላት ለባለቤቷ ለኢያቄም “ብእሴሃ አነኑ ርኢኩ በሕልምየ ርግብ ጸዐዳ መጽአት ኀቤየ ወነበረት ዲበ ርእስየ ወቦአት ውስተ እዝንየ ወኀደረት ውስተ ከርሥየ፤ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብቶ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ” አለችው፡፡ የዚህ ራእይ ምሥጢርም ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን፤ ፀዓዳ (ነጭ) መሆኗ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፡፡ “ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ” ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መሆኗን ሲያጠይቅ ነው፡፡
በተመሳሳይ ኢያቄምም በሕልሙ ያየውን ለባለቤቱ ለሐና “እንዘ ይትረኀዉ ሰብዐቱ ሰማያት ዖፍ ጸዐዳ መጽአ ኀቤየ ወነበረ ዲበ ርእስየ፤ ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ዖፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ” ብሎ በሕልሙ የተገለጸለትን ነግሯታል፡፡ የዚህም ራእይ ምሥጢር ዖፍ የተባለው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባሕርዩ ነው፡፡ ኢያቄም “ከላይ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ” ማለቱ የኢያቄምን ባሕርይ ባሕርይ እንደሚያደርግ የሚያጠይቅ ሲሆን ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ባህርይው፣ ምልአቱ፣ ስፍሃቱ፣ ርቀቱ፣ ልእልናው፣ መንግሥቱ ናቸው፡፡
በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ፤ ለተመሰገነች ሚስቱ ለሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት። ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች። ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ስዕለትን ተሳለች፡፡
ከዚህም በኋላ ይህችን የከበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ፀንሳ ወለደች። ስሟንም “ማርያም” ብላ ሰየመቻት። ትርጓሜውም ‘እመቤት’ ነው። ደግሞም ‘ሀብትና ስጦታ’ ማለት ነው፡፡ በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት ናትና።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!