ጸሎተሐሙስ

በሰሙነ ሕማማት ባሉት ከሰኞ እስከ ረቡዕ ያሉትን ቀናት በተመለከተ በተከታታይ ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ ዕለተ ሐሙስ የተለያዩ ስያሜዎች ያሉት ሲሆን ጥቂቶቹን ቀጥለን እናቀርባለን፡፡

. ጸሎተ ሐሙስ፡- በዚህች ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ መጥተው እስከሚይዙት ድረስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ የአትክልት ቦታ በሆነው በጌቴሴማኒ ጸልዮአል፡፡ “ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆችን (ዮሐንስንና ያዕቆብን) ልጆች ወሰደ፡፡ ያዝንና ይተክዝ ጀመር፡፡ ከዚህም በኋላ ‘ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ተቀመጡ፤ ከእኔም ጋር ትጉ” አላቸው፡፡ ከዚህም ጥቂት ፈቀቅ አለና በግንባሩ ሰግዶ ጸለየ” (ማቴ. ፳፮፥፴፮-፵፮) በዚህም ምክንያት የጸሎተ ሐሙስ ቀን ተብሏል፡፡

ከዚህም በኋላ እርሱ ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ጋር ስላለው አንድነትና ክብር ለሐዋርያት ካስተማራቸው በኋላ የአስቆሮቱ ይሁዳ ይህችን ሥፍራ ቀድሞ ጌታ ይወዳት እንደነበር ያውቃልና የካህናት አለቆችንና ጸሐፍት ፈሪሳውያንን እንደዚሁም ጋሻና ጦርም የያዙትን ጭፍሮች አስከትሎ ወደ እርሱ መጣ፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ተነሡ እንሒድ! እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል አላቸው፡፡ ወደ ካህናት አለቆችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን ቀርቦም ማንን ትሻላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስን አሉት፡፡ (ዮሐ. ፲፰፥፩-፯) ያንጊዜም ይሁዳ ወደ እርሱ ቀርቦ፤ መምህር ሆይ ቸር አለህን፤ ሰላም ላንተ ይሁን›› ብሎ ሳመው፤ መሳሙም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል የትኛው እንደሆነ ለአይሁድ ለይቶ ለማሳየት የተጠቀመው የጥቆማ ምልክት ነበር፡፡ ምክንያቱም የጌታ መልክና የወንጌላዊው የዮሐንስ መልክ ይመሳሰልባቸው ነበርና ለይቶ ሲያሳያቸው ነው፤ ያንጊዜም ጌታችን የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጠዋለህን? ብሎታል፡፡ (ሉቃ. ፳፪፥፵፰)

ከዚህም በኋላ አይሁድና ጭፍሮቻቸው ጌታ ኢየሱስን በስድስተኛው ሰዓተ ሌሊት ያዙት፡፡ ወደ ሽማግሌዎችና ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት፡፡

. የምሥጢር ቀን፡ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መካከል አንዱ የሆነው ምሥጢረ ቊርባን የተመሠረተው በዚች ዕለት ነውና ይህቺ ዕለት የምሥጢር ቀን ተብላ ትጠራለች፡፡

መድኃኒታችን ክርስቶስ በዚህች ዕለት ሐሙስ ለዓርብ ምሽት በሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት

ኅብስቱን ባርኮ ለዐሥራ ሦስት ከፈተተ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጥቶአቸዋል፡፡ “ጌታችን ኢየሱሰስ ኅብስቱን አንሥቶ ባረከ፣ ቈረሰ፣ ለደቀ መዛሙርቱም “ይህ ሥጋዬ ነው፤ እንኩ ብሉ፤ ብሎ ሰጠ፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፡- ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ፡፡ ኃጢአትን ለማስተስረይ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” አላቸው

ዐሥራ ሦስተኛውን ደግሞ ምንም የሚጠቅመው ባይሆንም ለእርሱ የሚቀበለው አድርጎታል፡፡ ቀምሶ አቀመሳቸው እንዲል፡፡ አንድም አብነት ለመሆን እንደዚሁም ነገ በመልዕልተ መስቀል ዐሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል እቀበላለሁ ሲል ነው፡፡ ጌታ ይህን አርአያነት ባያደርግልን ኖሮ ዛሬ ካህኑ የጌታን ሥጋና ደም ሳይቀበል አቀብሎ ብቻ በሄደ ነበርና ይህን ሥርዓት ለማስተማር ነው፡፡ (አንድምታ ቅዳሴ ማርያም)

በዚህም መሠረት እኛ ከእርሱ ከመድኃኒታችን ክርስቶስ ጋር፣ አንድ የምንሆንበትን ምሥጢር ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠባት ዕለት በመሆንዋ ይህቺ ዕለት የምሥጢር ቀን ተብላ ትጠራለች፡፡በዚች ዕለት የቅዳሴ አገልግሎት የሚፈጸም ሲሆን የቅዳሴው ሥርዓትም ዝቅ ባለ ድምጽ በለሆሳስ ነው፡፡ የቃጭሉን አገልግሎት የሚተካው ጸናጽል ሲሆን ይህም አይሁድ ጌታችንን ሊይዙት በመጡ ጊዜ ድምጻቸውን ዝግ አድርገው በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው፤ በቅዳሴውም ጸሎተ ተአምኆ፣ ሥርዓተ ኑዛዜ የማይደረግ ሲሆን ሥርዓተ ቊርባን ግን ይፈጸምበታል፡፡ ይህም የሚደረገው ጌታችን ለእኛ ለምእመናን የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ለማሰብ ነው፡፡ በዚችም ዕለት ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ቀድመው ራሳቸውን በንስሓ በማዘጋጀት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ይቀበሉባታል፡፡

. የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ፡ ይህቺ ዕለት መድኃኒት ክርስቶስ ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ የገለጠባት በእንስሳት ደም ይቀርብ የነበረው መሥዋዕተ ኦሪትም አብቅቶ አማናዊው የሐዲስ ኪዳን መሥዋዕት ለድኅነተ ዓለም የተበሠረባትና የተጀመረባት ዕለት በመሆንዋ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ እየተባለች ትጠራለች፡፡ መድኃኒት ክርስቶስ ይህ ጽዋዕ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ በማለት እንደተናገረው፡፡ (ሉቃ. ፳፪፥፳)

. የሕፅበተ እግር ቀን፡ በዚህች ዕለት በመጀመሪያው ሰዓተ ሌሊት በመጽሐፍ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበት ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ እርሱም፦ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውላለህ አለው። ጴጥሮስም የእኔን እግር ለዘለዓለም አታጥበኝም አለው። ኢየሱስም ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ ሆይ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም አለው። ኢየሱስም፦ የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሓን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም አይደላችሁም አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፡፡ ስለዚህ ሁላችሁ ንጹሓን አይደላችሁም አለ። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው፦ያደረግሁላችሁን አስተውላችኋልን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ መምህርና ጌታ ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና ተብሎ በወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ተጻፈ፡፡ (ዮሐ. ፲፫፥፬-፲፭)

እንግዲህ ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው ከወንጌላዊው ቃል እንደምንረዳው ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ዘንድ በጴጥሮስ ጀምሮአል፡፡ ጴጥሮስ ግን እኔ የአንተ ደቀ መዝሙር ስሆን ባንተ በመምህሬ ልታጠብ አይገባኝም አለ፤ ጌታችንም መልሶ እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም፡፡ ከዚህም በኋላ ሌሎቹንም ሐዋርያት አጥቦአቸዋል፡፡ አሳልፎ የሚሰጠውን ይሁዳን እንኳን ሳይቀር እግሩን አጥቦታል፡፡ ጌታም ይህንን ያደረገው አሳልፎ እንደሚሰጠው ሳያውቅ ቀርቶ አልነበረም፤ ፍቅርን ሲያስተምረው ለንስሓም ጊዜን ሲሰጠው እንጂ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እኛንም ለሚወዱን ብቻ ሳይሆን ለሚጠሉን እንኳን በጎ ማድረግ እንደሚገባን ሲያስተምረን ነው፡፡ (ዮሐ. ፲፫፥፰)

በዚህም መሠረት ይህንን ሥርዓቱን አብነት በማድረግ በዚች ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን የሕፅበተ እግር ሥርዓቱ በሚከናወንበት ጊዜ ዲያቆኑ ውኃን ያቀርባል፤ በቀረበውም ውኃ ላይ ጸሎተ አኰቴት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነብቦ ውኃው በካህኑ ወይም በሊቀ ጳጳሱ እጅ ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓቱ ከካህናት እስከ አናጕንስጢስ እንደዚሁም ከወንዶች እስከ ሴቶች ላሉት ምእመናን ሁሉ በካህናቱ እጅ ይከናወናል፡፡

በዚህም ጊዜ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፤ ምሥጢሩም ወይራ ጽኑዕ ነው፡፡ ይህም ክርስቶስ ጽኑ መከራ መቀበሉን የሚያስረዳ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እኛም የእርሱን መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ የወይኑ ቅጠል ደግሞ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ ይሆናቸው ዘንድ መስጠቱን ለማዘከር ሲሆን በዚች ዕለት ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ የፈጸመው የኅጽበተ እግር ሥርዓትም ለካህናትና ለምእመናን የትሕትና ሥራን ለማስረዳት መሆኑን እናንተም ለባልንጀሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉ በማለት ነግሮናል፡፡

 የሕጽበተ እግር ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ምእመናን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፳፮ ፥ ዮሐ. ፲፫፥፲)

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *