ኒቆዲሞስ

ኒቆዲሞስ የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን፤ ድል ማድረግ ወይም አሸናፊነት ማለት ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ከፈሪሳዊውያን ወገን ነው፡፡ ፈሪሳውያን ሕግን የሚያጠብቁ፣ ሕዝብን የሚያስመርሩ፣ እነርሱ የማይፈጽሙትን ሕግ በሕዝብ ላይ የሚጭኑ፣ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ፣ አባታችን አብርሃም እያሉ የሚመጻደቁ ነገር ግን የአባታቸው የአብርሃምን ሥራ ከማይሠሩት ወገን እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ፈሪሳውን ከመመጻደቃቸውም የተነሣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከወግና ከልማድ ወጥተው ከጨለማ ወደ ብርሃን ይመለሱ ዘንድ የነፍስ ምግብ የሆነውን ወንጌልን ሲያስተምር፣ በተአምራቱ ድውያን ሲፈውስ፣ የተራቡትን አበርክቶ ሲያበላ፣ ውኃውን ወደ ወይንነት ሲለውጥና የተጠሙትን ሲያጠጣ በተመለከቱት ጊዜ ሕጋችንን ሻረ በማለት ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡

ይህንንም ሲገልጥባቸው “ልትገድሉኝ ትሻላችሁ፤ እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም በአባታችሁ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ” በማለት ከአባታቻው ከሰይጣን እንደሆኑ አላቸው፡፡ እነርሱም መልሰው “የእኛስ አባታችን አብርሃም ነው” አሉት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ አላቸው፡- “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑስ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ ነበር፡፡” (ዮሐ. ፰፥፴፱) በማለት ከሰይጣን እንደሆኑ ነግሯቸዋል፡፡  

ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ብቻ ሳይሆን የአይሁድም አለቃቸው ነው፡፡ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርትና ተአምራት ሰምቶና ተመልክቶ ቀን ቀን በአይሁድ ወንበር በሸንጎ እየዋለ በመምህርነቱ ሳይታበይ፣ አለቅነቱን መመኪያ ሳያደርግ፣ እውነትን ማግኘት ፈለጎ እንደ ባልንጀሮቹ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይቃወም በሌሊት ወደ እርሱ ዘንድ እየሔደ ወንጌልን ይማር ነበር፡፡ (ዮሐ. ፫፥፩) ሌሊትን ለምን መረጠ ቢሉ፡- መምህር ስለነበር ስማር ብዙ ሰዎች ሲያዩኝ በውዳሴ ከንቱ መምህር መባል ይቀርብኛል ብሎ፤ እንዳያዩትም ፈርቶ፣ ከቀን ይልቅ የሌሊት ልብ የተካተተ ስለሆነ በሙሉ ልቡ በማስተዋል ለመማር ስለፈለገ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የማታውን ክፍለ ጊዜ መረጠ፡፡ ሌሊት ጨለማ ነው፤ ብርሃን የለም ጨለማ የኃጢአት ምሳሌ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ በሌሊት መምጣቱ ኃጢአተኛ መሆኑንና በጌታችን ትምህርት አምኖ ንስሓ እንደሚፈልግ የሚያስረዳን ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ኒቆዲሞስ ከአይሁድ ተደብቆ በጨለማ ትምህርቱን ለመማር ከልቡናው ተነሣስቶ ወደ እርሱ ሲገሰግስ መምጣቱን ተመልክቶ ዳግመኛ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” በማለት አስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ምሥጢሩ አልተገለጠለትም ነበርና ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኀፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን? በማለት ለጌታችን ጥያቄ አቅርቧል፡፡ (ዮሐ. ፫፥፮፤ ፩ኛጴጥ. ፩፥፳፫)

እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውና፤  (ኤፌ. ፭፥፳፮) ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ቢያስረዳውም ምሥጢሩ ሊገለጥለት ግን አልቻለም ነበር፡፡ ይህ እንደምን ይቻላል? በማለትም ጌታችንን ጠይቋል፡፡

ኒቆዲሞስ ቀድሞ በአደባባይ ሔዶ መማርን ቢፈራም በሌሊት ከአምላኩ ተምሮ ምሥጢሩ ሲገለጥለት ምስክርነቱን መስጠት ጀመረ፡- መምህር ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል የለምና፡፡በማለት መሠከረ፡፡(ዮሐ. ፱፥፳፬፤ ሐዋ. ፲፥፴፰)

በመጨረሻም ኒቆዲሞስ አይሁድ ጌታችንን በቀራንዮ አደባባይ ያለ ኃጢአቱና በደሉ በምቀኝት በመስቀል ላይ በሰቀሉት ዕለት ፍርኃት ርቆለት ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ቅዱስ ሥጋውን ገንዞ ለመቅበርም በቅቷል፡ “ፍጹም ፍቅር ፍርኃትን አውጥቶ ይጥላልእንዲል፡፡ (ማቴ. ፳፯፥፶፰፤ ፩ኛ ዮሐ. ፬፥፲፰)፡፡

የፈሪሳውያን አለቃና ምሁረ ኦሪት ከነበረው ኒቆዲሞስም ራስን ዝቅ ማድረግን፣ ጎደለንን ማወቅ፣ ለመልካም ነገር ልቡናን ከፍ ማድረግን፣ ሳፈሩና ሳሰቀቁ የእውነት ምስክር መሆንን፣ በሌሊት በጸሎትና በትምህርት መትጋትን፣ እስከ መጨረሻ በመጽናት አብነት መሆንን እንማራለን፡፡ በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን  ታላቅ ሰው ለመዘከር የዐቢይን ጾም ሰባተኛው እሑድ በስሙ ሰይማ ታከብረዋለች፤ ተከታዮቿ ምእመናንም የእርሱን አሠረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለች፤ ታስተምራለችም፡፡

በዚህ በሰባተኛው ኒቆዲሞስ በተባለችው ሳምንት እሑድ የሚነበቡት ምንባባት (የቅዳሴ ምንባባት) የሚከተሉት ናቸው፡-

መልእክታት፡-

  • ሮሜ. ፯ ÷፩-፲፱
  • ፩ኛ ዮሐ. ፬ ÷ ፲፰-፳፩

ግብረ ሐዋርያት

  • የሐዋ.ሥራ ፭ ÷ ፴፬-፵፪

ምስባክ

  • መዝ. ፲፮ ÷ ፫-፬

ወንጌል፡-

  • ዮሐ. ፫÷፩-ፍጻሜው

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *