ጀምሬአለሁ

በአዶና እንዳለ

የግድግዳው ሰዓት እየቆጠረ ነው። ግን ደግሞ ጊዜው እየሄደ አይደለም። ሌሊቶች እንዲህ ረዝመውብኝ አያውቁም። ከቤታችን ሳሎን መስኮት ጭላንጭል ብርሃንን እየጠበቅሁ ዓይኖቼን ከመጋረጃው ላይ መንቀል አቃተኝ። ለካ በእያንዳንዷ ማለዳ የምናያት ብርሃን ምን ያህል ትርጉም እንዳላት የምናውቀው ብርሃንን ስንናፍቅ ነው።

“ቤቴል፣ ቤቴል! ተነሽ እንጂ ነጋ እኮ!” ከነበርኩበት የሰመመን እንቅልፍ ያስወጣኝ የእናቴ ድምጽ ነበር።

እናቴ መጋረጃውን ስትከፍተው ያቺ ከመጋረጃው ሾልካ የገባችው የፀሐይ ብርሃን ግን እንደናፈቅኋት ሰላሜን ልትሰጠኝ አልቻለችም፤ ይልቁንም አስጨነቀችኝ። ከአልጋዬ ላይ ተስፈንጥሬ ተነሥቼ ስልኬን መጎርጎር ጀመርኩ፤ በይነ መረቡ ተጨናንቋል፣ ልቤ በፍጥነት ሲመታ ይታወቀኛል። እናቴ ሁኔታዬ ግራ አጋብቷት “ለምን አትረጋጊም? መሆን ያለበት ነገር ከመሆን ወደ ኋላ አይልም።” አለች በፍቅር ዓይኖቿ እየተመለከተቸኝ፡፡

እኔ ግን እናቴን ተረጋግቼ የማዳምጥበት ሁኔታ ላይ አልነበርኩም። ስልኬ ላይ እንዳፈጠጥኩ ሰዓታት ነጎዱ። “አይሠራም፤ አሁንም እየሠራ አይደለም” አልኩ ሳላስበው ቃላቶች አምልጠውኝ” ልቤ በአፌ ልትወጣ ደርሳለች።

“የኔ ልጅ አትጨነቂ! እግዚአብሔር ለአንቺ ያለውን አያስቀርብሽም ተረጋጊ” ብላ ጎንበስ ብላ ግንባሬን ስማ ፊቴን በቀኝ እጇ መዳፍ ዳበሰችኝ፡፡ እሷም የእኔ መጨነቅ እንደተጋባበት ታስታውቃለች፣ ነገር ግን እንት ናትና ልታረጋጋኝ ሞከረች፡፡

ከደቂቃዎች በኋላ ስልኬ ጮኸ። አባቴ ነበር። የምሞትበትን ቀን ሊያረዳኝ ይመስል እጄ በፍርሃት መንቀጥቀጥ ጀመረ። ራሴን እንደ ምንም አረጋግቼ ስልኩን አነሣሁት።

“ሄ…ሎ፣ ሄሎ ቤቴል!”  አጠራሩ የሐዘን ቅላጼ ነበረው።

“አ…ቤት”

“ውጤትሽን አይቼዋለሁ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ የሚሆን አላመጣሽም። ለሪሚዲያል ግን የሚሆን ነጥብ አምጥተሻል፡፡ ለመረጋጋት ሞክሪ እሺ?! … እባክሽ እየሰማሽኝ ነው አይደል? … ሄሎ ቤቴል ቤቴል …” አባቴን ለመስማት ዐቅም አልነበረኝም፡፡

ዓይኔን ስገልጥ ቀድሜ ያየሁት የእናቴን ፊት ነበር። ድንገት ከየት መጣ ያላልኩት ዕንባ ፊቴን ሲያርሰው ተሰማኝ። የእናቴን ፊት ማየት አልቻልኩም። ፊቴን አዙሬ ማልቀስ ጀመርኩ።

ታናሽ ወንድሜ ደንግጦ በፍርሃት ያስተውለኛል፡፡ ለማጥናት የማደርገው ጥረትና ድካሜን ያውቀዋል፡፡ የራሱን የወደፊት ውጤት ምን እንደሚሆን እያሰበ ስጋት የገባውም ይመስላል፡፡

“ቤቴል ልጄ ተይ እባክሽ እንደዚህ አትሁኚ፡፡ በቃ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም። ለምን ከእግዚአብሔር ጋር ትግል ትገጥሚያለሽ? ሁሉን ለበጎ የሚያደርግ አምላክ እኮ ነው።” ያዞርኩባትን ፊቴን መልሳ ወደ ራሷ አዙራ እቅፏ ውስጥ ሸጎጠችኝ። ማልቀስ ማቆም አቃተኝ።

እናቴ እቅፍ ውስጥ ሆኜ እንቅልፍ ወሰደኝ።

ለሳምንታት ከራሴ ጋር ስጣላ ቆየሁ። ነገን ሳስብ ድቅድቅ ጨለማ ይታየኝ ጀመር። በእኔ ሐዘንና ጭንቅት ሐሳብ ውስጥ የገቡት እናትና አባቴ መላ ፍለጋ መዳከር ጀመሩ። በርካታ ሐሳቦችን አውጥተው አውርደው ተነጋግረዋል፡፡ ነገር ግን ለሪሚዲያል መዘጋጅት እንዳለብኝና በርትቼ አጥንቼ በዩኒቨርሲቲው ለመቆየት እገዛ ሊያደርጉልኝ እኔን ለማግባበት ሞከሩ፡፡ እኔ ግን እጅግ ተጎድቻለሁ፣ ያልጠበቅሁት ውጤት ነበርና፡፡

ጊዜያት እየነጎዱ በሄዱ ቁጥር ከነበርኩበት ተስፋ ማጣትና ድብርት የሚያወጣኝን ትንሽዬ ተስፋዬን ለማስቀጠል ወሰንኩ። የተማርኳቸውን ኮርሶች ድጋሚ ተምሬ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባኝን ነጥብ ማምጣት።

አማራጬ ይህ ነበር። ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት አለፉ። ቀኑ ደርሶ ወደ ተመደብኩበት ጅማ ዩኒቨርሲቲ አቀናሁ። ከቤተሰቦቼ መለየት እንደ ሞት የምቆጥር ልጅ በዩኒቨርሲቲ ለብቻዬ ኑሮን መግፋት ግድ ሆነብኝ። ሳይደግስ አይጣላም አይደል የሚባለው በዚህ አጭር ቆይታዬ በፍጹም ልረሳቸው የማልችላቸውን ጓደኞች አፈራሁ። ሕይወት በአንድም በሌላም በኩል ታስተምራለችና።

የእኔ ራስን የመሆን የሕይወት ጉዞ የጀመረው እዚሁ ነው። በዩኒቨርሲቲ ለመቆየት የሚያሰችለኝን ውጤት ለማምጣት በተመደብኩበት ዩኒቨርሲቲ በነበረኝ የአራት ወራት የማካካሻ ትምህርቴን ቀጠልኩ፡፡

በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ እንደማለፌ ራሴን ለማረጋገትና ግቢውን ለመልመድ የግቢ ጉባኤው ወንድሞችና እኅቶች ድጋፍ፣ ምክር የሚያስገርም ነበር፡፡ ዓርብ እስኪደርስ ይጨንቀኝ ነበር፡፡ የጸሎት ሥርዓቱ፣ ምክር አዘል ትምህርቱ፣ … ባይተዋር ከመሆን ታደገኝ፡፡ እግዚአብሔርም ረድቶኝ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ቻልኩ። በውጤቴ እኔም ቤተሰቦቼም ደስተኞች ነበርን። “ሕይወት ብዙ አቅጣጫዎች አሏት!” ያለው ምን ነበር?

እኔም የሕይወት ጉዞዬን “ሀ” ብዬ ጀምሬአለሁ። በአሁኑ ወቅት የጅማ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት የቅድመ ምሕንድስና ትምህርት ክፍል ተማሪ ነኝ። እርግጥ ነው ብዙ ያላየኋቸው ገና የማያቸው ብዙ ምዕራፎች እንደሚጠብቁኝ አውቃለሁ። ይህ ጅማሬ ነው። የሰው ልጅ የስኬቱ መነሻ አንድ እርምጃው ነው፤ እኔም ጉዞውን ጀምሬአለሁ፣ እደርሳለሁም፡፡ እያንዳንዳችን መድረስ እና መሆን የምንፈልገው ቦታ ላይ እስክደርስ ሁል ጊዜም ጀማሪዎች ነን። እኔም እነሆ ጀምሬአለሁ! ከእግዚአብሔር ጋር አሳካዋለሁም!!!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *