ደብረ ዘይት (የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት)

ደብረ ዘይት የቃሉን ፍቺ ስንመለከት ደብር ተራራ ማለት ሲሆን ዘይት” የሚለው ቃል ደግሞ ወይራ ማለት ነው። ስለዚህ ደብረ ዘይት በወይራ ዛፍ የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው። 

ይህ የደብረ ዘይት ተራራ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በደብረ ቄድሮን ሸለቆ ብቻ አለ። ከታች ጌቴ ሴማኒ የተባለው የአትክልት ስፍራ ሲገኝ የጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተያዘበትና በኋላም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋዋ ረፈበት በዚህ ተራራ ግርጌ ነው። ቤተ ፋጌ እና ቢታንያ በኮረብታው ጫፍ እና በምሥራቅ ዳገታማ ቦታ ላይ ይገኛሉ። ይህ ተራራ በመጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ቦታ ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ ዓለም ፍጻሜና ስለ ዳግም ምጽአቱ የተናገረው በዚህ ተራራ ላይ ነው። ቀን ቀን በከተማና በገጠር ሲያስተምር ውሎ ሌሊት የሚያድርበት የኤሌዎን ዋሻም የሚገኝበት ነው፣ በዚሁ ተራራ ላይ ወደ ሰማይ ዐርጓል፣ ምጽአቱም በዚሁ ተራራ ላይ እንደሚገለጥ ትንቢት ተነግሯል። (ዘካ. ፲፬፥፫-፭)

አንድ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ ደቀ መዛሙርቱም የቤተ መቅደሱን ሕንፃ አድንቀው አሠራሩን አያሳዩት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ አላቸው፡፡ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፡፡” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም “ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመመጣትህና የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?” አሉት፡፡

“የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡ ጦርነትን፣ የጦርነት ወሬም ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፤ አትደንግጡ ነገር ግንፍጻሜው ገና ነው፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ፤ በየሀገሩም ረኃብና ቸነፈርም፣ የምድር መናወጥም ይሆናል፡፡ …” (ማቴ. ፳፬፥፩-ፍጻሜው) በማለት መለሰላቸው፡፡   

የዳግም ምጽአት ምልክቶች፦

. የሐሰተኞች ክርስቶሶች መምጣት (ራእ. ፲፫፥ ፭፣፳፫)

. ጦርነት (ማቴ. ፳፬፥፮)

. ረኃብ (ማቴ. ፳፬፥፯)

. የመሬት መንቀጥቀጥ (ማቴ. ፳፬፥፯)

. የክርስቲያኖች መከራ (ማቴ. ፳፬፥፱)

. የሐሰተኞች ነቢያት መምጣት (ማቴ. ፳፬፥፲፩፣፳፮)

. የፍቅር መጥፋት (ማቴ. ፳፬፥፲፪)

. የወንጌል ለዓለም መዳረስ (ማቴ. ፳፬፥፲፬)

የምጽአቱ ምሳሌዎች

ፍጥነቱ፦ ፈጥነቱ እንደ መብረቅ ነው። “መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናል» (ማቴ. ፳፬፥፳፯) ተብሏልና።

ቀኑ አለመታዎቁ፦ እንደ ሌባ ነው። ያን ግን ዕወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር … የሰው ልጅም በማታስቡበት ሰዓት ይመጣል (ማቴ. ፳፬፥፵፫-፵፬)።

ወቅታዊ መልእክቱ

ተጠንቀቁ፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ((ማቴ. ፳፬፥፬)።

ንቁ፦ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ ((ማቴ. ፳፬፥፵፪)

ተማሩ፣ ዕወቁ፦ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ [ከላይ የተናገራቸውን ምልክቶች ሁሉ] ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ (ማቴ. ፳፬፥፴፫))።

አትደንግጡ፦ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ (ማቴ. ፳፬፥፮))

ትጉና ጸልዩ፦ ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ (ማቴ. ፳፬፥፳)

ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፦ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።((ማቴ. ፳፬፥፵፬)

ጽኑ፦ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል (ማቴ. ፳፬፥፲፫)

በዚህች ደብረ ዘይት በተባለች ሳምንት እሑድ ጌታችን በዚህች ምድር ሲመላለስ የፈጸመውን ሥራ የሚያስረዱ የሚነበቡት ምንባባት የሚከተሉት ናቸው፡፡

መልዕክታት፡- (፩ኛ ተሰ. ፬፥፲፫-፲፰)

(፪ኛ ጴጥ. ፫፥፯-፲፭)

ግብረ ሐዋርያት፡- (ሐዋ. ፳፬፥፩-፳፪)

ምስባክ፡- (መዝ. ፵፱፥፪-፫)

“እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ፤

ወአምላክነሂ ኢያረምም፤

እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፡፡”

ትርጉም፡-

“እግዚአብሐር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፤አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤

እሳቱ በፊቱ ይቃጠላል፡፡”

ወንጌል፡- (ማቴ. ፳፬፥፩-፳፮)

ቅዳሴ፡- ቅዳሴ አትናቴዎስ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *