ማኅበረ ቅዱሳን ፲፫ኛውን የግቢ ጉባኤያት ዓለም አቀፍ ሴሚናር በማካሄድ ላይ ይገኛል
በመላው ዓለም የሚገኙና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ የግቢ ጉባኤያት ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የስድስቱ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች፣ የማእከላትና የወረዳ ማእከላት የግቢ ጉባኤያት ዋና ክፍል ተወካዮች የሚሳተፉበት ፲፫ኛው የግቢ ጉባኤያት ሴሚናር ከየካቲት ፳፩-፳፫ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም ድረስ በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን (በብሔራዊ ሙዚየም) በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ዓርብ የካቲት ፳፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም በተደረገ አቀባበልም ከእጽበተ እግር ጀምሮ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ሥራ አስፈጻሚ መ/ር ዋሲሁን በላይ እና የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ሥራ አስፈጻሚ አጾ አበበ በዳዳ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ቅዳሜ በነበረው መርሐ ግብርም በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ልዑካን በጸሎት ወንጌል የተጀመረ ሲሆን
የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ አባል የሆኑት ዲ/ን ብንያም አያሌው በ፲፫ኛው የግቢ ጉባኤያት ሴሚናር ላይ ለተገኙ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል። በዚህ ጉባኤ ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካካልም፡- የማኅበሩን ተቋማዊ ለውጥ አስመልክቶ በተለይም በግቢ ጉባኤያት የተደረጉ ማሻሻያዎችን ማስተዋወቅ፣ የአዲሱን ሥርዓተ ትምህርት አተገባበር እና የግቢ ጉባኤያት ድርሻ፣ በግቢ ጉባኤያት የመምህራን እጥረት ለመቅረፍ የተዘጋጀ ፕሮጀክት ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ ማስቀመጥ እና ከተመረጡ ግቢ ጉባኤያት እና አባላት ልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ቀጥሎም በመ/ር ብርሃኑ አድማስ “አንተ ጎበዝ ተነሥ እልሃለሁ” (ሉቃ. ፯፥፲፬) በሚል ርእስ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ሥራ አስፈጻሚ መምህር ዋስይሁን በላይ የሁለት ዓመት የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት ሪፖርትም፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ከቅዱስ ሲኖዶስ በብቸኝነትና በቀዳሚነት ከተሰጡት አገልግሎቶች አንዱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች) የሚማሩ ኦርቶዶክሳዊያን ትምህርተ ሃይማኖት እያስተማረ ለአገልግሎት ማሰማራት ነው ብለዋል፡፡ ይህንንም ላለፉት ፴፫ ዓመታት በእግዚአብሔር ቸርነት ፣ ከቤተ ክርስቲያን አካላት ጋር በጋር ሲያከናውን መቆየቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ማኅበሩ የግቢ ጉባኤ አገልግሎትን የሚመራበት ዓላማ ኦርቶዶክሳውያንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ሙሉ ሰብእናን የሚገነባ ሥርዓተ ትምህርት በማስተማር ዘመኑን የዋጁ ምሉዕ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ፣ በቤተ ክርስቲያን አስተዳዳራዊ መዋቅር የሚያገለግሉ፣ እንዲሁም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ በፖለቲካዊ እና በሀገረ አስተዳደር ጉዳዮች መሪ/ንቁ ተሳታፊ አገልጋዮችን ለማፍራት እና ለማሠማራት ነው ብለዋል፡፡
በአሁን ሰዓት በሀገር ውስጥ በሚገኙ ፫፲፭ ግቢ ጉባኤያት በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች እና ፩፻፶፪ ግቢ ጉባኤያት በግል ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ከ፩፻፷ ሺህ በላይ ተማሪዎች በተዘጋጀላቸው ሥርዓተ ትምህርት እየተማሩ ሲሆን በውጭ ሀገር በስድስት ማእከላት አንድ ግንኙነት ማእከል፣ ፲፰ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ላይ በቨርቹዋል ፲፬፻ በላይ ተማሪዎች እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህም በአንድ ሳምንት ፳፻፶ የትምህርት መርሐ ግብር ተዘርግቶ ፳፻፶ መምህርን ተመድበው በማስተማር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
መምህር ዋሲሁን ሪፖርታቸውን በመቀጠል፡-
- የመማሪያ መጽሐፍትን ለተማሪዎች በጥራት አዘጋጅቶ በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን፣
- የግቢ ጉባኤ መጽሐፍት ከ፲፱፻፺፰ ዓ.ም ጀምሮ በተዘዋዋሪ ጥብቅ ፈንድ የሚመራ ሲሆን የተዘጋጁትን የኮርስ መጽሕፍት ፸፪ ሺህ ሰባት መቶ አሥራ ሰባት ኮፒ በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋ ታትሞ ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ተሠራጭዋል።
- ለግቢ ጉባኤያት ለሚገኙ ግቢ ጉባኤያት የንስሓ አባቶች እና አማካሪዎች ተከታታይ ዓቅም ማሳደጊያ ሥራ ተሠርቷል።
- አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላለፉት ሁለት ዓመታት በከፍተኛ ባለሙያዎች ነባሩን ሥርዓተ ትምህርት በመገምገም፣ በመንግሥት እየተተገበረውን ያለውን የሀገሪቱን አዲሱ ሥርዓተ ትምህርትና መልክ ከ፪፻፲፩ ጀምሮ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ያለውን የሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት በማገናዘብ ተዘጋጅቷል።
- ዘመኑን የዋጀ፣ አካታች፣ ሙሉ ሰብእና የሚገነባ፤ የግቢ ጉባኤ ምሩቃንን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ በማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን ንቁ ተሳታፊ እና መሪ የሚያደርግ ሥርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶ በዚሁ ዓመት በ፳ ግቢ ጉባኤያት ትግበራ ተጀምራል፡፡
- በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤ ለተመረጡ ፳፻፲፮ ተመራቂ ተማሪዎች እንደየዝንባሌያቸው ሀገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያገለግሉ የሚያግዛቸውና በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እና በሀገር አስተዳደር ተሳታፉ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው አቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች በባለሙያዎች ተሰጥቷቸዋል።
- የማኅበሩ አባላት፣ የሰት/ቤት መምህራንና በየአጥበያው የሚገኙ መምህራን በተጨማሪ በግቢ ጉባኤያት የሚያስተምሩና የሚያሠለጥኑ እንዲሁም አገልግሎቱን የሚያስተባብሩ ፶፩ መደበኛ መምህራን እና የግቢ ጉባኤ አስተባባሪዎች በሙሉ ጊዚአቸው ተመድበው አገልግሎቱን እያፋጠኑ ይገኛሉ ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሪፖርታቸው ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንደተቻለ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በ፲፫ኛው ዓለም አቀፍ የግቢ ጉባኤያት ሴሚናር መርሐ ግብር በመገኘት በሰጡት ቃለ ምእዳን “ማኅበረ ቅዱሳን ባይኖር ወጣቱን ማን ይይዝልን ነበር፡፡ በዚህ በ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን ወጣቱ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያውቅ ሀገሩን እንዲያገለግል እያደረገ ነው” ብለዋል፡፡

ከስዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብርም የማኅበረ ቅዱሳን ተቋማዊ ለውጥ በግቢ ጉባኤያት በተመለከተ በመ/ር ዋሲሁን በላይ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ሥራ አስፈጻሚና በአቶ ግዛቸው ሲሳይ የማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አመራር አባል ቀርቦ ለቀረቡ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በመቀጠልም ከአሜሪካ ማእከል የግቢ ጉባኤያት ተሞክርን አስመልክቶ የጆርጅ ማሰን ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ሰብሳቢ በሆኑት ማርያማዊት በርታ እና በመቅደላዊት መርሻ የቨርቱዋል ግቢ ጉባኤ ሰብሳቢ በቨርቹዋል ቀርቧል፡፡ የግቢ ጉባኤያት ሁለንተናዊ አገልግሎት ተሞክሮ በተመለከተም በዲ/ን ብርሃኑ ታደሰ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር አባል እና በአቶ አበባ በዳዳ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ሥራ አስፈጻሚ ቀርቦ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በምሽት በነበረ መርህ ግብር ላይ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ትግበራም በተመረጡ ግቢ ጉባኤያት ቀርቦ በአቶ በቃሉ ለይኩን በሥራ ዘርፍ ከመሠማራት ቅድመ ዝግጅት ወይም የሲቪ አዘገጃጀት ቀርቦ የዕለቱ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!