ጾም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ
ክፍል አንድ
በዲ/ን መብራቱ ስንታየሁ (ከአዳማ ማእከል)
ጾም ለሰውነት የሚያምረውን እና የሚያስጎመዠውን ነገር ሁሉ ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ብሎ መተው፣ ራስን በመግዛት ጣዕመ ዓለምን በመናቅ እግዚአብሔርን መከተል ማለት ነው፡፡ ጾም ራስን ከክፉ ሥራዎች ሁሉ በማሸሽ የመንፈሳዊ ተጋድሎ መፈጸሚያ መሣሪያ እና የሥጋ ልጓም ነው፡፡ መንፈሳዊ በረከትን ለማግኘት ለትእዛዘ እግዚአብሔር ራስን ማስገዛት ነው፡፡ ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔርን ርዳታ ማግኛ የፍቅር መንገድ ነው፡፡ ጾም ሃይማኖትን መግለጫ በተግባር ማሳያ መታመኛ መሣሪያ ነው፡፡ ጾም፤ ወዶ ፈቅዶ ምግብን በጊዜ ገደብ ጥሉላትን በቀናት/በወራት ገደብ እንዲሁም ነፍስን ከሚያሳድፉ ክፉ ሥራዎች መከልከል ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ያለን ፍጹም ፍቅር የሚገለጠው በጾም በጸሎት እና ምጽዋት ነው፡፡ የቀና እና የተስተካከለ መንፈሳዊ ሕይወትን ከሚያደናቅፉ ማናቸውም እኩይ ተግባራት መራቅ እና መከልከል ጾም ተብሎ ይተረጎማል፡፡
ነፍስን ሊያቆስላት የሚችለው ምንድን ነው? ስንል መልሱ የሥጋ ፈቃድን መፈጸም፣ በደል፣ ኃጢአት …ነው የሚል ይሆናል፡፡ ሰው ተማሪ ቢሆን ሠራተኛም ቢሆን በምንም ዓይነት ሥራ እና ሁኔታ ላይ ቢሆን ክርስቲያናዊ ሕይወቱን ለማረም ዕለት ዕለት መንፈሳዊ ተግባራትን መተግበር ያስፈልጋል፡፡ በይበልጥ ሐዋርያት የሥራ መጀመሪያ ያደረጓትን ጾምን እኛም አጥብቀን ልንይዝ ይገባል፡፡ “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።” (ሮሜ. ፰፥፮)፡፡ ሥራችንን ክርስቲያናዊ ጉዞአችንን ፍጹም የሚያደርግልን ጾም ነው፡፡ ለዚህም ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስን እንደ ምሳሌ መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ስለዚህ ተማሪዎች ቀዳሚት ትእዛዝ የሆነች ሕግን ገንዘብ በማድረግ ሕይወታችንን ሰማያዊ ዋጋ በሚያሰጥ መልክ እንምራ፡፡
ጾምን ለምን እንጾማለን?
ጾም በመጀመሪያ ለሰው የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ የሰው ልጅ ቢመራበት የዘላለምን ሕይወት የሚወርስበት ልዩ የእግዚአብሔር የፍቅር ሕግ ነው፡፡ ሰው ፍትወቱን በዚህች ባማረች ሕግ ገዝቶ ዓይኑን ክፉ ከማየት፣ ጆሮውን ክፉ ከመስማት፣ ምላሱን ክፉ ከመናገር ከማማት፣ እግሩን እጁን ከመስረቅ ደም ለማፍሰስ ወደ ክፉ ከመገስገስ ቢከለክል ዋጋው ምንኛ ያማር ይሆን ነበር፡፡ እኛ በዚህ ዘመን ያለን ወጣቶች በዓለሙ ካለ ክፋት የትኛውን ተጸይፈን እንተዋለን? ዘመነኛው ቴክኖሎጂ ያመጣልንን ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ክፉኛ ወደሚያቆስለን ለገሃነም ወደሚሰጠን የሥጋ ሥራ አዘንብለናል፡፡ ነገር ግን የተሰጠንን በጎ አእምሮ በመጠቀም ወደ ኃጢአት ከመሄድ ራሳችንን ልንጠብቅ እና ልናነጻ ይገባል፡፡ እስኪ አሁን ደግሞ የጾምን ጥቅም በቅደም ተከተል እንመልከት፡-
፩. ኃይለ እግዚአብሔርን ለማግኘት
አብዝቶ መመገብ ፈቃደ ሥጋ በፈቃደ ነፍሳችን ላይ እንዲሰለጥን ሰፊ በር ይከፍታል፡፡ ፍትወታተ ሥጋ እንዲሰለጥኑብንም ዋነኛ ሞተራቸው በመሆን ይጠቀሳል፡፡ ጥጋብን፣ ትዕቢትን፣ ንዝህላልነትን፣ ዝሙትን በማምጣት መንፈሳዊ ፍሬን እንዳናፈራ ያግደናል፡፡ ሰዶምን በእሳት እንድትቃጠል ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ እንጀራን መጥገብ እንደሆነ (ሕዝ. ፲፮፥፵፱) ተገልጧል፡፡ ፈቃደ ሥጋችን በፈቃደ ነፍሳችን ላይ ኃይል እንዳይኖረው ጾም መጾም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ነቢዩ ዳንኤል ከሦስቱ ሕፃናት ጋር ከኢየሩሳሌም ተማርከው ወደ ናቡከደነፆር ግዛት ከተወሰዱ ዕብራውያን ወጣቶች መካከል ተመርጦ ሦስት ዓመት በከለዳውያን ትምህርት ቤት የከለዳውያንን ጥንቆላ (ኮከበ ቆጣሪ)፣ ሕልም መፍታት፣ ቋንቋ እና ባህላቸውን ከሦስቱ ወጣቶች ጋር በመሆን እንዲያጠኑ በተቃራኒው ደግሞ የራሳቸው የሆነውን የእስራኤልን እምነት እና ባሕል እንዲረሱ በተደረጉበት ጊዜ ዳንኤል እንዲመገቡ የተፈቀዱላቸውን የንጉሡን ምግብ እና መጠጥ ከመብላት እንቢ አለ፤ የአሕዛብ ምግብ እንደሚያረክሰው አስቧልና፡፡ ይልቁንም ቆሎ እየበሉ ይማሩ እንደነበር ትንቢተ ዳንኤል ያስገነዝበናል፡፡
ሰውነታቸው ቅቤን በማጣት ቢነጣም ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ኅብረት በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ በጾም መጠንከራቸው በትምህርታቸው ጎበዝ እና በንጉሥ ፊት ሞገስ ያላቸው የሚመረጡ ከመሆን አላገዳቸውም፤ እንዲያውም ከሌሎቹ በላይ ሞገስ እንዲኖራቸው በሀገሪቱ ውስጥ ሥልጣን እንዲያገኙ፣ የተደበቀን ምሥጢር በመግለጥ የበረቱ እንዲሆኑ አደረጋቸው እንጂ፡፡ እግዚአብሔርም በነገር ሁሉ ይረዳቸውና ከጎናቸው ይሆንላቸው እንደነበረ መጽሐፍ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በጾም በመጽናታቸው እና ከኃጢአት ራሳቸውን በመጠበቃቸው ባገኙት ኃይለ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቶች (የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች) ስንጾም በትምህርታችን ልንደክም እንደምንችል እያሰብን እግዚአብሔር ከሚሰጠን ኃይል እና ጥበብ እንዳንርቅ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
ክርስቲያን መንፈሳዊ ተግባራትን በተመቸው ቀን ብቻ የሚተገብር አይደለም በጊዜውም ያለጊዜውም ጸንቶ የሚገኝ ነው እንጂ፡፡ ጾም ሌሎችን ምግባራት (ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት…) ለመፈጸም ፍጹም ኃይልን የምትሠጥ በጎ ተግባር ናት፡፡ የመንፈሳውያን ኃይል የሆኑትን ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ ራስን መግዛትን … ወዘተ ገንዘብ ለማድረግ ጾም ዋና መሣሪያችን ነው እና ገንዘብ እናድርገው፡፡
፪. ተጋድሎን መፈጸሚያ ነው
በመንፈሳዊ ሕይወታችን የምንጋደለው ከመንፈሳውያን የክፋት ሠራዊት ጋር እንደሆነ እንዲህ በማለት ተነግሮናል “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።” (ኤፌ. ፮፥፲፪)፡፡ ለመጋደል የተዘጋጀ ሰው ደግሞ መሣሪያ እንደሚያስፈልገው ይታወቃል ስለዚህ ጾም ከሁሉ ቀድሞ የሚገኝ ተጋድሎ የመፈጸሚያ መሣሪያ ነው፡፡ በቀንና በሌሊት ከቤተ መቅደስ ሳይለዩ እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት ያገለገሉ ቅዱሳን የክፋት ሠራዊትን ድል የማድረግ ኃይልን ተጎናጽፈዋል፡፡ ልባችን በጸጋ እንጂ በምግብ እንዳይጸና ሐዋርያው አስጠንቅቆናል፤ ምግብን አብዝቶ በመብላት እና ለምግብ በማድላት የተጎዳ እንጂ የተጠቀመ እንደሌለ አስተምሮናልና (ዕብ. ፲፫፥፱)፡፡
የተወደዳችሁ ተማሪዎች ተድላና ደስታን በመፈለግ መንግሥተ እግዚአብሔር አትወረስም፡፡ እስኪ ሊቀ ነቢያት ሙሴን እንመልከት ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከክርስቶስ ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መራብን መረጠ፡፡ በዚህ ምክንያት ከሞቀ መኖሪያ ከቤተ መንግሥት ለስደት ተዳረገ፤ ተራበም፤ ተጠማም የሚያገኘውን ዋጋ በዚያ ዘመን ሆኖ ተመልክቷልና (ዕብ. ፲፩፥፳፬-፳፭)፡፡ ይህን በማድረጉ ተጎዳ ወይስ ተጠቀመ? በጣም ተጠቀመ እንጂ የተጎዳው አንዳች አልነበረም፡፡ ሙሴ ለዐርባ ቀናት ከምግብ በመከልከል ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር ሕግጋትን ታቦትን ከአምላከ ቅዱሳን መቀበል የቻለው በጾም በመጋደሉ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ሰማይን እስከ መለጎም የደረሰ ሥልጣንን ማግኘት የቻለው ዐርባ ቀን እና ሌሊት ለመጾም ይከብድብኛል ሰውነቴ ይከሳል ሳይል ሳይፈራ በጾም በጸሎት በመቆሙ ከክፉዎች ጋር ባለመተባበሩ ነው፡፡ ስለዚህ በረጅሙ የክርስትና ጉዙአችን ውስጥ ጾም በጣም ወሳኝ ነገር መሆኑን ማሰብ እንደሚገባ ልንጋደል ይገባል፡፡ የሥጋችን ፈቃድ ለመግዛት በምናደርገው ተጋድሎ ውስጥ ጾም ጉልህ ሚና አለው፡፡ ጾም የነፍስን ቁስል ትፈውሳለች፤ የሥጋንም ፈቃድ ወይም ፍላጎት ዝም ጸጥ ታሰኛለች እና ለተጋድሎ ጠቃሚ መሣሪያ ናት፡፡
፫. እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመኖር
የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰው ሕያው ሆኖ እንዲኖር ነው፡፡ ማንም በሞት እንዲጠፋ ከገነት ከመንግሥተ ሰማይ እንዲጎድል አይፈልግም፡፡ የሰው ትልቁ ተስፋ መንግሥተ እግዚአብሔርን ወርሶ ዘለዓለማዊ መሆን ነው፡፡ የሕይወት መውጫው ልባችን እንደሆነ መጽሐፍ ይነግረናል “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።” (ምሳ. ፬፥፳፫) አዳም አባታችን አትብላ የምትለውን ሕግ በመሻሩ የሥጋ ፈቃዱን በመፈጸም ከፈቃደ እግዚአብሔር ርቆ በእግረ ሞት ተረግጧል፤ እኛም ከዚህ ሕግ ፈቀቅ ብንል የአዳም ዕጣ ሊገጥመን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ታዲያ ፈቃደ እግዚአብሔር እየፈጸምን ለመኖር ምን ያስፈልገናል? ካልን ራስን መግዛት የምታስችለውን ጾምን ገንዘብ ማድረግ ነው፡፡ (ኢዩ. ፪፥፲፪) በፍጹም ልብ በመጾም ወደ እርሱ እንድንመለስ መማጸኑ እግዚአብሔር የሚወዳት ጾም ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመፈጸም የሚያስችል ትልቅ ኃይል እንዳላት ያመለክታል፡፡ ጾም በሰው ጥበብ የተጀመረች ሕግ አይደለችም ምን እንደምትጠቅም የሚያውቅ አምላክ ፈቃዱን እንድንፈጽምባት የሠራት ሕግ ናት እንጂ፡፡
በመጀመሪያ ከመጾማችን በፊት ጾም አድካሚ እና ጎጂ ሕግ ነው ብለን ከመሳት ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል፡፡ ይህ ሕግ የፍቅር ሕግ ነው፤ ከአምላካችን ጋር ኅብረት የምናደርግበት የምሕረት ዓይኑ እንድትመለከተን የምታደርግ ሕግ ስለሆነች በጾም ወደ ፈጣሪ መመለስን እንደ መጎዳት ማሰብ ፈጽሞ ስህተትን ያስከትላልና እንጠንቀቅ፡፡ ፈተና እየተፈተንም ቢሆን እያጠናን ልወድቅ እችላለሁ በሚል ፍርሃት አምላክን ከማሳዘን ከመንግሥቱ ከመጉደል መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡
በአጠቃላይ የክርስትና ዋና ዓላማ በእንግድነት በዚህ ዓለም ባለንበት ዘመን ከፈቃደ ሥጋ መራቅ፤ ነፍስና ሥጋን ማንጻትና የእግዚአብሔር ማደሪያ ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ በብዙ ድካምና ተጋድሎ የሚሳካ ነው። በመጽሐፍ “. . . ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል።” (ሐዋ. ፲፬፥፳፪) እንደተባለ መንገዱ የተደላደለ ሳይሆን ብዙ ተጋድሎ የሚያስፈልገው መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። ገዢዋ የሥጋ ፈቃድ የሆነባት ሰውነት ሞት ያገኛታል “በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘለዓለምን ሕይወት ያጭዳል።” (ገላ. ፮፥፰) እንዲል ሥጋን በጾም ለነፍስ ማስገዛት ሕይወትን ያስገኛል።
“እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። ” (ሮሜ. ፰፥ ፲፫-፲፬) ጾም ፈጽሞ የሥጋ ሥራን ማስወገጃ፣ ተጋድሎን መፈጸሚያ መንገድ ነው። “መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው” (፩ኛቆሮ. ፮፥፲፫)። ሥጋዊ መብልን በመብላት የሚሠራ ጽድቅ የለም፤ ይልቁንም ብዙ ምግብ ለዝሙት፣ ለትዕቢት የሚያጋልጥ በመሆኑ በጾም ሰውነታችንን ከትዕቢት እንዲሁም ከዝሙት እንጠብቅ። ይህንን ካደረግን ከሆድ ጋር ከመጥፋት ራሳችንን እንታደጋለን። መንፈሳዊ ፍሬን ለማፍራት የምትቀድም ምግባር ጾም ናት ስለዚህ አጥብቀን እንፈልጋት እንያዛትም። “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።” (ሮሜ. ፲፬፥፲፯) በጾም የምናገኛት ተስፋችን ምን እንደምትመስል በታወቀ ጊዜ ከምግብና ከክፋት በመራቅ የምንገባባት መሆኗንስ ተረዳን? ሰው ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚያስፈልገው ጾም እንጂ ምግብ አይደለም “መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም።” (፩ኛቆሮ. ፰፥፰) እንደተባለ። የምግብ ኃይል ለሥጋ ነው የጾም ኃይሏ ግን ለነፍስ ነው “የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።” (ገላ. ፭፥፳) የተባለውን እናስተውል።
ይቆየን
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!