ጾመ ነነዌ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ታሪኮች አንዱ ትንቢተ ዮናስ ሲሆን ሰብዓ ነነዌ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን መበደላቸውና ማሳዘናቸውን፤ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር መቅሰፍቱን በሕዝቡና በሀገሪቱ ላይ ከማውረዱ በፊት ንስሓ ይገቡ ዘንድ ነቢዩ ዮናስን እንደላከው እንመለከታለን፡፡ዮናስ ማለት ርግብ ማለት ነው፡፡ ርግብ የዋህ፣ ኃዳጌ በቀል እንደሆነች ሁሉ ዮናስ በሌሎች ላይ ተንኮል የማይሠራ ነውና፡፡ ትንቢተ ዮናስ የተጻፈው ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት መካከል አንዱ በሆነው ነቢየ እግዚአብሔር ዮናስ ሲሆን ዘመኑም ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይታመናል፡፡ ተንቢተ ዮናስ አራት ምዕራፎችንና አርባ ስምንት ቁጥሮችን ያቀፈ ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ከተጠቀሱት ቦታዎች መካከልም ኢዮጴ፣ ተርሴስና ነነዌ ይገኙበታል፡፡

የነነዌ ሰዎች በደል እጅግ የከፋ ነበርና እግዚአብሔር ዮናስን አሥነስቶ “ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፡ ክፋታቸውም ጩኸት ወደ ፊቴ ወጥቶአልና ለእነርሱ ስበክ፡፡” በማለት ሕዝቡ ወደ ንስሓ ይመለስ ዘንድ እንዲሰብክ አዘዘው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ግን የሕዝቡ ልብ ደንድኗልና እኔ ይህን እንዴት ማድረግ ይቻለኛል በሚል የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጥሶ ከነነዌ ወደ ተርሴስ ለመኮብለል ወደ ኢዮጴ አመራ፤ በዚያም ወደ ተርሴስ የምትሄድ መርከብ አገኝቶ ወደ ተርሴስ ተሳፈረ፡፡ ነገር ግን እንዳሰበው ወደ ተርሴስ መሄድ አልቻለም፡፡

እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አነፈሰ፤ ታላቅም ማዕበል በመነሣቱ መርከቧ ልትሰበር ደረሰች፡፡ በውስጡ የተሳፈሩት መንገደኛም ታላቅ ፍርሃትን ፈሩ፡፡ በመርከቢቱ ውስጥ የነበሩትን እቃዎች ሁሉ ወደ ባሕሩ ቢጥሉም መርከቢቱ ከመናወጥ አልዳነችም፡፡ ዮናስ ግን በታችኛው የመርከቢቱ ክፍል እንቅልፉን ተኝቶ አገኙት፡፡ የመርከቢቱም አለቃ ወደ ዮናስ መጥቶ “ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ” አለው፡፡ እርስ በርሳቸውም “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት መጣብን?” በማለት ዕጣ ተጣጣሉ፡፡ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ዮናስም ይህ በእርሱ ምክንያት እንደደረሰባቸው በመረዳቱ “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንደ አገኛችሁ ዐውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል” አላቸው፡፡ ዮናስንም ወስደው ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ማዕበሉም ጸጥ አለ፡፡ እግዚአብሔር በባሕሩ ውስጥ ዮናስን ይውጠው ዘንድ ዓሣ አንበሪውን አዘዘ፡፡ ዮናስም በዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ሳለ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ የልቡን ቅንነትና ንጽሕና እግዚአብሔር ያውቃልና ለነቢዩ ዮናስ አዘነለት በዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና ሌሊት አድሮ በእግዚአብሔር ቸርነት ዓሣ አንበሪው ዮናስን በየብስ ላይ ተፋው፡፡

የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ዮናስ መጣ፡- “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የነገርሁህን የመጀመሪያውን ስብከት ስበክላት” አለው፡፡ ዮናስም ወደ ነነነዌ ሄዶ እየጮኸ “በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች” አለ፡፡ የነነዌ ሰዎችም እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾምም ዐዋጅ ነገሩ፡፡ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡ ንጉሡም ከዙፋኑ ተነሥቶ ማቅ ለብሶ በራሱ ላይ አመድ ነስንሶ ዐዋጅ አስነገረ፡፡ እንዲህም አለ “ሰዎችና እንስሶች፣ ላሞችና በጎች አንዳች አይቅመሱ፤ አይሰማሩም ውኃም አይጠጡ፣ ከከፉ መንገዳቸውም ይመለሱ” በማለት አዘዘ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ ከተናገረው ክፉ ነገር ተመለሰ፤ አላደረገውምም፡፡

ነቢዩ ዮናስ ግን እግዚአብሔር ከቁጣው በመመለሱና ሕዝቡንም ይቅር በማለቱ እጅግ ተበሳጨ፡፡ “አቤቱ በሀገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፣ ታጋሽም፣ ምሕረትህም የበዛ ከክፉው ነገርም የምትመለስ አምላክ እንደሆን ዐውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኮብለል ፈጥኜ ነበር፡፡ አሁንም አቤቱ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህን ነፍሴን ከእኔ ውሰድ” በማለት ከእግዚአብሔር ጋር ተሟገተ፡፡ ዮናስም ከከተማይቱ ወጥቶ አንዲት ዛፍ (ድንኳን) ከጥላው በታች ተቀመጠ፡፡

እግዚአብሔር ዮናስን ከፀሐዩ ግለት ይከላከልለት ዘንድ ቅልን አዘዘ፤ ከራሱ በላይም ጥላ እንድትሆነው ከፍ ከፍ አደረጋት፡፡ ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ተደሰተ፡፡ በነጋም ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዝዞ ቅሊቱን መታቻት፤ ቅሊቱም ደረቀች፡፡ እግዚአብሔርም የምሥራቅን ነፋስ በማዘዝ ዮናስን ፀሐዩ ራሱን መታው፡፡ “በሞትኩ ይሻለኝ ነበር” ብሎም ተበሳጨ፡፡ እግዚአብሔር ግን ዮናስን ዝም አላላውም “አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት፣ ላላሳደግሃትም በአንድ ሌለት ለበቀለች፣ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል፡፡ እኔስ ቀኛቸውንናግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንም?” አለው፡፡

ነቢዩ ዮናስ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ወጥቶ በራሱ መንገድ በመሰለው የተጓዘበት መንገድ አላዋጣውም፡፡ ከእግዚአብሔርም ትእዛዝና ፈቃድ መውጣት ቅጣቱ የከፋ መሆኑን ከነቢዩ ዮናስ ታሪክ መረዳት እንችላለን፡፡ የነነዌ ሰዎች ግን በአንድ ዮናስ ስብከት ከበደላቸው ተመልሰው፣ ማቅ ለብሰው፣ አመድ ነስንሰው ከመሬት ወድቀው እግዚአብሔር ምሕረቱን ይልክላቸው ዘንድ በመለመናቸው እግዚአብሔር አዘነላቸው፣ የምሕረት ፊቱንም መልሶ ይቅር አላቸው፡፡ ንስሓ ምን ያህል ዋጋ እንዳለውም በዚህ እንረዳለን፡፡ እኛም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ በንስሓ ተመልሰን የስሙ ቀዳሾች የመንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ ምግባር ከሃይማኖት አስማምተን ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶ ልናፈራ ይገባል፡፡ ሰብዓ ነነዌን ከጥፋት የታደገ አምላካችን ሀገራችንና ሕዝቦችዋን  ከጥፋት ይጠበቅልን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *