አዲሱን የግቢ ጉባኤያት ሥርዓተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ ለሚያስፈጽሙ ሠልጣኞች የተሰጠው ሥልጠና ተጠናቀቀ
ማኅበረ ቅዱሳን ለሦስተኛ ጊዜ የተገመገመውንና ለሁለተኛ ጊዜ የተከለሰውን አዲሱን የግቢ ጉባኤያት ሥርዓተ ትምህርት ለሚያስፈጽሙ መምህራንና አስተባባሪዎች ከጥር ፴ እስከ የካቲት ፪ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው የአሠልጣኞች ሥልጠና ተጠናቀቀ፡፡
ሥልጠናው ከአቀባበል ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከቀድሞው ሥርዓተ ትምህርት ግምገማ አንስቶ የሥርዓተ ትምህርቱን የክለሳ ኀላፊነት ወስደው ሲያዘጋጁ በነበሩ ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የተሰጠ ሥልጠና ነው፡፡

ሥልጠናው በዲ/ን አንዱአምላክ ይበልጣል “የሥልጠናው ዓላማ እና ሠልጣኞች ተሸክመው ሊሄዱ የሚገባቸውን ተልእኮ በተመለከተ፣ የሙከራ ትግበራ ምን? ለምን/ እንዴት/፣ ክፍል አንድ የሥርዓተ ትምህርቱ መሠረታዊ ጉዳዮች፣ የነባሩ ሥርዓተ ትምህርት ግምገማ መሠረታዊ ግኝቶች፣ የሥርዓተ ትምህርቱ ተለማጭነት አተገባበር፣ ዝቅተኛ የመማር ብቃት፣ የተመረጡ የትምህርት ዓይነቶችን እንደማሣያ” በተሰኙ ርእሰ ጉዳዮች ለአንድ ቀን ሙሉ ሥልጠናውን ሰጥተዋል፡፡
የካቲት ፪ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም በቀጠለው የአሠልጣኞች ሥልጠናም በዶ/ር ወርቁ ደጀኔ “አሳታፊ የመማር ማስተማር ዘዴ፣ ጠማሪዎች አያያዝድጋፍ” እንዲሁም በዶ/ር ቴዎድሮስ ሀብቴ “በሥርዓተ ትምህርቱ ትግበራ ከመምህራን የሚጠበቁ ክሂሎቶች፣ የምዘናና ግምገማ ሥርዓት” በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ሰፊ ትንታኔ የቀረበ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለሚቀርቡ ጥያቄዎችም በምሁራኑ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ሥልጠናውን ከወሰዱት መምህራንና አስተባባሪዎች መካከል ከአዳማ ማእከል ተወክለው የመጡት ዲ/ን መብራቱ ስንታየሁ ስለ ሥልጠናው ሲገልጹ፡- “በሥልጠናው ስለ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖረኝ፣ ነባሩ ሥርዓተ ትምህርት በምን ምክንያት መከለስ እንዳስፈለገውና በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርትም የተካተቱት መሠረታዊ ጉዳዮች እንድረዳ አስችሎኛል፡፡ ወደ ማእከል ተመልሼም ባገኘሁት ሥልጠና መሠረት ሥርዓተ ትምህርቱ በግቢ ጉባኤያት ላይ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባን ለሚመለከታቸው አካላት በማስረዳት ተግባራዊ እናደርግ ዘንድ በቁርጠኝነት እናገለግላለን” በማለት ገልጸዋል፡፡
ከወልቂጤ ማእከል የመጡት ዲ/ን አበበ ስሜ ስለ ሥልጠናውና ከሥልጠናው የተረዱትን ሲገልጹ “ባለፉት ሦስት ተከታታይ ቀናት የወሰድነው ሥልጠና አዲሱ ሥርዓተ ትምህርትን በተመለከተ በበቂ ሁኔታ ግንዛቤው እንዲኖረኝ፣ የተካተቱት አዳዲስ ነጥቦችንም እንድረዳ አስችልኛል፡፡ የትምህርት አሰጣጡንም ሕይወት ተኮር እንዲሆን፣ ተማሪዎች መንፈሳዊ ሕይወትን እንዲለማመዱና በዚያም ጸንተው እንዲኖሩ የሚያግዝ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከማእከል ወንድሞችና እኅቶች ጋር በመሆን ሥርዓተ ትምህርቱ ወደ መሬት በማውረድ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ጥረት እናደርጋለን” በማለት ሥልጠናው ኃላፊነትን በአገባቡ መወጣት እንዲችሉ ግንዛቤ እንደፈጠራላቸው አስረድተዋል፡፡
ከሥልጠናው በኋላም በተከናወነ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኀላፊ አቶ አበበ በዳዳ “ከሥርዓተ ትምህርቱ ግምገማ ጀምሮ የክለሳውን ኀላፊነት በመውሰድ ሲያዘጋጁ የነበሩት ምሁራን አብረውን አሉ፡፡ ከአሁን በኋላም በርካታ ሥራዎች ይጠብቀናል፡፡ የመጻሕፍት ዝግጅት፣ የድኅረ ምረቃ እና የውጪ ማእከላት ግቢ ጉባኤያት ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት፣ መጻሕፍቱ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚተረጎሙ በመሆኑ እነዚህ ምሁራን አብረውን ይቆያሉ፡፡ በዚህም መሠረት አገልግሎት ወስዶ ለፍጻሜ በማብቃትና ውጤታማ ሥራ የሚሠራውን ደግሞ እናመሰግናለን ማለትን መልመድ አለብን” በማለት በሥርዓተ ትምህርቱ ግምገማና ክለሳ ላይ ለተሳተፉት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት መ/ር ዋሲሁን በላይ ባስተላለፉት መልእክትም “ዓላማችንን ለማሳካት የተማረ የሰው ኃይል ስናፈራ ብቻ ነው፡፡ ይህን የሰው ኃይል ማፍራት የሚቻለው ደግሞ በተዘጋጀ ሥርዓተ ትምህርት ነው፡፡ ሰው ላለመው ዓላማ የሚበቃው በዚህ መንገድ ሲያልፍ ብቻ ነው፡፡ በሥርዓተ ትምህርት ያላለፈ ሰው ተጎጂ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሠልጣኞች ወደየማእከሎቻችሁ ስትሄዱ ለማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ፣ ለመምህራን፣ ለማኅበራችን አባላት፣ ተባበሪ አካላት (ሰበካ ጉባኤ፣ ሰ/ት/ቤቶች) ማኅበረ ቅዱሳን ሥርዓተ ትምህርቱን እንደለወጠ (እንደከለሰ) በሚገባ የማስረዳትና የማሳወቅ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡ ከእናንተ ውጪ ለዚህ ሥርዓተ ትምህርት መተግበር ጥብቅና የሚቆም ስለሌለ አብዝታችሁ መትጋት ይጠበቅባችኋል” ብለዋል፡፡
በሥርዓተ ትምህርት ግምገማና ክለሳ ለተሳተፉት ከፍተኛ ባለሙያዎችና መምህራንም “ላለፉት ዓመታት የከፈላችሁት ኃላፊነት የተሞላበት አገልግሎት በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን” በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሄኖክ “ሁሉም ነገር በሥርዓት ይሁን” እንዲል ትምህርትም በሥርዓት ካልሆነ ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ተበጅቶለት ተለክቶና ተቀምሞ ሲቀርብ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ይህን ያህል ጊዜ ሲሊለፋበት የቆየው ውጤታማ እንዲሆን ነው፡፡ ለውጤታማነቱ ደግሞ የሙከራ ትግበራ ለማድረግ እናንተ ሠልጣኞች ተመርጣችኋል፡፡ ይህንንም ሥርዓተ ትምህርት ይዛችሁ ከሥር ላሉት መምህራን፣ አባላትና ምእመናን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለባችሁ መሆኑን ተረድታችሁ በትጋት ማስፈጸም ይጠበቅባችኋል” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ሥርዓተ ትምህርቱን በመገምገምና በመከለስ ለተሳተፉ ከፍተኛ ባለሙያዎችና መምህራን የማስታወሻ ስጦታ የተበረከተላቸው ሲሆን ለሠልጣኞቹም የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!