አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ ለሚያስፈጽሙ አገልጋዮች ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል

ማኅበረ ቅዱሳን ለሁለተኛ ጊዜ የተከለሰውንና ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀውን ሥርዓተ ትምህርት ለመተግበር ከተመረጡ ማእከላት ለተውጣጡ መምህራንና አስተባባሪዎች የአሠልጣኞች ሥልጠና ከጥር ፴ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ማኀበረ ቅዱሳን የመጀመሪያውን የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ በ፳፻፮ ዓ.ም አድርጎ የነበረ ሲሆን ለአሥር ዓመታት አገልግሎት ላይ በማዋል ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትህምርት በተከታታይ ትምህርት (course) ሲያስተምር ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ቀድሞ የነበረውን ሥርዓተ ትምህርት መከለስ ያስፈለገበት ምክንያት የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኀላፊ የሆኑት አቶ አበበ በዳዳ ሲገልጹ፡- “ላለፉት አሥር ዓመታት ሲተገበር የነበረው ሥርዓተ ትምህርት በተደረገው የግምገማ ውጤት መሠረት አንዳንድ ጉድለቶች በመታየታቸው ነው፡፡” ብለዋል፡፡ እንደ ምሳሌም ሲጠቅሱ “በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የታዩ ጉድለቶች፣ በማኅበረ ቅዱሳን ተቋማዊ ለውጥ ትግበራ ላይ ስለ ግቢ ጉባኤያት የተካተቱት ሐሳቦች፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመርቀው ሲወጡም ዘመኑን የዋጁ፣ ምሉእ የሆኑና ቤተ ክርስቲያንና ሀገርን በተለያዩ ዘርፎች በሙያቸው እንዲያገለግሉ ለማስቻል፣ የሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት በ፳፻፲፩ ዓ. ም ለአገልግሎት መዋልና ከአንዳንዶቹ ጋር ተመሳሳይ መሆናቸው፣ በድጋሚ ከማስተማር ከዚያ የቀጠለው ላይ ትኩረት ማድረግ ስላስፈለገ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ፍኖተ ካርታ/ፖሊሲ/ መቀየር (ከሦሰት ዓመት ወደ አራት ዓመት ከፍ መደረጉ) ክለሳ ለመደረጉ እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡

የአሠልጣኞች ሥልጠናውን የሚወስዱት መምህራንና አስተባባሪዎች የተመረጡት በወጣላቸው መስፈርት መሠረት ደረጃ አንድና በከፊል ደግሞ ደረጃ ሁለት ካሟሉ ግቢ ጉባኤያት ውስጥ ነው፡፡ ሥልጠናውን እየሰጡ የሚገኙት በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ከፍተኛ ልምድ ባላቸውና በነባሩ ሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የግምገማ ሥራ በመሥራት ክለሳውን በማዘጋጀት ሰፊ ድርሻ ባላቸው ምሁራን አገልጋዮች ነው፡፡

በዛሬው ውሎም የሥልጠናው ዓላማና ሠልጣኞች ይዘው ሊሄዱ የሚገባቸውን ተልእኮ፣ የሙከራ ትግበራ ምን? ለምን? እንዴት? ክፍል አንድ የሥርዓተ ትምህርቱ መሠረታዊ ጉዳዮች፣ የነባሩ ሥርዓተ ትምህርት ግምገማ መሠረታዊ ግኝቶች፣ የሥርዓተ ትምህርቱ አደረጃጀትና አተገባበር ዕሳቤዎች በተለመከተ በባለሙያዎቹ ሰፊ ትንተና ተሠጥቷል፡፡  

በሥልጠናው ከ፲፪ ማእከላት የተውጣጡ መምህራንና አስተባባሪዎች ሲሆኑ ሙሉ ለሙሉ የተከለሰውን ሥርዓተ ትምህርት ከመተግበሩ በፊት በእነዚህ በተመረጡ ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት የሙከራ ትግበራ የሚከናወን ይሆናል፡፡ ሥልጠናው በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይውላል፡፡    

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *